ክቡር ሚኒስትር

[ክቡር ሚኒስትሩ አማካሪያቸውን ቢሮ አስጠሩት]

 

 • ፈለጉኝ ክቡር ሚኒስትር?
 • ያዘዝኩህን ሪፖርት ከምን አደረስከው?
 • ትንሽ ነው የቀረኝ፡፡
 • ለነገሩ የፈለኩህ ለሌላ ነገር ነው፡፡
 • ለምን ፈለጉኝ?
 • ለመሆኑ የዓለም አቀፍ ሚዲያ እየተከታተልክ ነው?
 • አዎን እከታተላለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እሱ ጉዳይ እኛንም ይመለከተናል፡፡
 • የቱ ጉዳይ?
 • በሚዲያ እየተላለፈ ያለው ነዋ፡፡
 • የተለያዩ ዜናዎች ናቸው እኮ የሚተላለፉት፤ የትኛውን ነው የሚሉኝ?
 • የአሸባሪነቱን ነዋ፡፡
 • በጣም ነው እኮ የሚያሳዝነው፡፡
 • ማዘን ምን ያደርጋል? ዋናው መጠንቀቅ ነው፡፡
 • አሁን እኛ ከእነሱ በላይ ተጠንቅቀን ነው ብለው ነው ያው እግዚአብሔር ጠብቆን ነው እንጂ?
 • ልታጣላኝ ፈልገህ ነው?
 •  ከማን ጋር?
 • ከእግዚአብሔር ጋር ነዋ፡፡
 • መቼ ተስማምተው ያውቃሉ ብዬ ነው?
 • ምን ለማለት ፈልገህ ነው?
 • የእርስዎ አምላክ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ነው ብዬ ነው፡፡
 • እኔ የምለው ስለእምነቴም አማክረኝ ብዬሃለሁ እንዴ?
 • ኧረ እንዲሁ ጨዋታውን ነው፡፡
 • የጠራሁህ ለሥራ መስሎኝ የምን ጨዋታ ነው?
 • ይቅርታ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ለማንኛውም ለፈረንሣይና ለሩሲያ ካልተመለሱ ለእኛም አይመለሱም፡፡
 • ዋናው ጥያቄ እኮ ሌላ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምንድነው ጥያቄው?
 • መግባት ወይም አለመግባት?
 • ምን አልከኝ?
 • ምነው ደነገጡ ክቡር ሚኒስትር?
 • የት ፓርላማ ነው?
 • የለም የለም፤ ሶሪያ ነው እንጂ፡፡
 • እኔ እኮ መግባት ወይም አለመግባት ስትለኝ ፓርላማ መስሎኝ ልቤ ደነገጠ፡፡
 • ለምን ደነገጠ?
 • ምን ይታወቃል እኛ ሳናውቅ ምርጫ ተካሄደ ብዬ ነዋ፡፡
 • ይኼማ እንዴት ሊሆን ይችላል?
 • አይሆንምን ትተህ ይሆናልን አስብ፡፡
 • እንዳሉ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ለዚህ ነው እኮ መጠናከር አለበት የምልህ፡፡
 • ምኑ?
 • የፀረ ሽብር ሕጉ፡፡
 • ከዚህ በላይ እንዴት ይጠንክር?
 • የእያንዳንዱን ዜጋ እንቅስቃሴ መቆጣጠር አለብን፡፡
 • እንዴት አድርገን?
 • ስማ የሁሉም ሰው ስልክና ኢሜይል ይጠለፍ፡፡
 • እሱማ ያስጠይቀናል፡፡
 • ለምንድንው የምንጠየቀው?
 • ዜጐች በሕገ መንግሥቱ የተሰጣቸውን መብት የሚጋፋ ነው፡፡
 • ይህ መብትን መጋፋት አይደለም፡፡
 • ታዲያ ምንድን ነው?
 • ደኅንነታቸውን መጠበቅ፡፡
 • ሕግ እየጣስን?
 • ፈረንሣይን ያየ በሽብር አይቀልድም፡፡
 • ይህን ማድረግ እኮ ከአቅማችን በላይ ነው፡፡
 • ለበላይ አካልም ቢሆን ሐሳቡን ማቅረብ አለብን፡፡
 • ብቻ ቢታሰብበት ጥሩ ነው፡፡
 • ለመሆኑ ዲሽ አለህ?
 • አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ዲኤስቲቪ ነው ዲሽህ?
 • እሱማ የሀብታሞቹ ነው፤ እኔ ዓረብ ሳት ነው ያለኝ፡፡ ለምን ጠየቁኝ ግን?
 • አይ እኔ የምመለከተው ቢግ ብራዘርስ የሚባል ቻናል አለ፡፡
 • እኔማ ኢሳት ነው የማየው፡፡
 • ጭራሽ እሱን ነው የምታየው?
 • አይ ባላንስ ለማድረግ ብዬ ነው፡፡
 • ማንን ነው ባላንስ የምታደርገው?
 • ኢቲቪን ነዋ፡፡
 • ብቻ ለማንኛውም ቢግ ብራዘርስ የሚባለው ቻናል የሰዎቹን እያንዳንዱን እንቅስቃሴ ይቆጣጠራል፡፡
 • ስለዚህ ምን ይደረግ እያሉ ነው?
 • እኛም የእያንዳንዱን ሰው እንቅስቃሴ መቆጣጠር አለብን፡፡
 • ለምን?
 • የአገሪቱ ቢግ ብራዘርስ ስለሆንን፡፡
 • የእኛ አገር ሰላም ለመሆኑ እኮ ሰሞኑን የተካሄደው ሩጫ ይመሰክራል፡፡
 • የትኛው ሩጫ?
 • ታላቁ ሩጫ ነዋ፡፡
 • ሮጠህ ነበር?
 • አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንዴት ነበር ታዲያ?
 • ቢያንስ የራሴን ሰዓት ማሻሻል ችያለሁ፡፡
 • አንተም እንደ ኢሕአዴግ የሚፎካከረኝ ስለሌለ ከራሴ ጋር ነው የተወዳደርኩት እያልከኝ ነው?
 • አይ ባለፈው ዓመት ከገባሁበት ሰዓት በተሻለ ነው የገባሁት ለማለት ፈልጌ ነው፡፡
 • ለመሆኑ ሩጫው የኪራይ ሰብሳቢዎችና የአፍራሽ ኃይሎች መፈንጫ ነበር?
 • ኧረ በፍጹም በሰላማዊ መንገድ ነው የተካሄደው፡፡
 • ስለዚህ የአሸባሪዎች ጥቃት አያሠጋንም እያልከኝ ነው?
 • ይልቁኑ አንድ ያሳሰበኝ ነገር ነበር፡፡
 • ምንድነው ያሳሰበህ?
 • በዚህ ዓመት ውድድሩ የተጀመረውና የተፈጸመው በመስቀል አደባባይ ነበር፡፡
 • ምን ችግር አለው ታዲያ?
 • አይ ያው አደባባዩ መፈቀዱን ተመልክተው ሠልፍ እንዳይጠሩ ብዬ ነው፡፡
 • እነማን?
 • ተቃዋሚዎች፡፡
 • ምንድን ነው እሱ ነገር አስታውሰኝ እስቲ?
 • እየቀለዱ ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ምን እቀልዳለሁ እውነቴን ነው እንጂ፡፡
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • ይህን ቃል የምትሰማው ምርጫ ሲመጣ ብቻ ነው፡፡
 • ለነገሩ እውነትዎን ነው፡፡
 • በነገራችን ላይ አሁን አሁን ዓለም ላይ የምንታወቅበት ሌላው ነገር እየሆነ መጥቷል፡፡
 • ምኑ?
 • ምርጫ ሲደርስ ብቻ ተቃዋሚዎች መንቀሳቀሳቸው ነዋ፡፡
 • ስለዚህ አያሳስበንም እያሉኝ ነው?
 • ቢያንስ ለሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ሩጫው መስቀል አደባባይ መካሄዱ ችግር የለውም፡፡
 • ከዚያ በኋላስ?
 • ምርጫውማ ሲደርስ ሰበብ ፈልገን እንመልሰዋለን፡፡
 • ወዴት?
 • ወደ ጃንሜዳ!

[ክቡር ሚኒስትሩ የፋይናንስ ኃላፊውን አስጠሩት]  

 • አቤት ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • በአስቸኳይ ይውጣ፡፡
 • ምኑ ክቡር ሚኒስትር?
 • ጨረታው፡፡
 • የምን ጨረታ?
 • በሪስትራክቸሩ ምክንያት አዳዲስ የሥራ ኃላፊዎች ወደ መሥሪያ ቤታችን እንደሚመጡ ታውቃለህ አይደል?
 • አውቃለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ስለዚህ እስካሁን የተገዙላቸው መኪኖች ብቻ ስለሆኑ ሙሉ የቢሮ ዕቃ መገዛት አለበት፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር አሁን የሚሉኝ ነገር እኮ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ያስወጣናል፡፡
 • ለሥራው አስፈላጊ እስከሆነ ድረስ ማንኛውም ነገር መደረግ አለበት፡፡
 • ጊዜው ጥሩ አይደለም ብዬ ነው፡፡
 • ጊዜው ምንድን ነው?
 • ያው ወገኖቻችን በድርቅ የተጐዱበት ጊዜ ነዋ፡፡
 • እና አሁን ይኼ ከዚህ ጋር ምን ያገናኘዋል?
 • ያው በጀቱ ከመንግሥት ካዝና ውስጥ ነው የሚወጣው ብዬ ነው፡፡
 • ለመሆኑ አንተን ማን ነው አማካሪዬ ያደረገህ?
 • ኧረ ማንም አላደረገኝም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ስለዚህ አድርግ የተባልከውን ነገር ብቻ አስፈጽም፡፡
 • እሺ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ጨረታው ውስን ጨረታ ነው የሚሆነው፡፡
 • እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
 • የምን እንዴ ነው?
 • በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ስለሆነ ውስን ጨረታ ማድረግ አንችልም፡፡
 • ለምንድን ነው የማንችለው?
 • መመርያው ይከለክለናላ፡፡
 • ለመሆኑ መመርያውን ማን ነው ያወጣው?
 • መንግሥት ነዋ፡፡
 • እኛስ ምንድን ነን?
 • እ…
 • እኛም መንግሥት መሆናችንን አትርሳ፡፡
 • ተጠያቂነትን ያስከትላል ብዬ ነው እኮ፡፡
 • ስነግርህ አትሰማም እንዴ?
 • ምኑን?
 • የአንተ ሥራ የማዝህን ብቻ ማስፈጸም ነው፡፡
 • ይቅርታ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ስለዚህ ለተለመዱት ተጫራቾች ሰነዱ ይላክ፡፡
 • እሺ ክቡር ሚኒስትር፡፡

[ክቡር ሚኒስትሩ አንድ ባለሀብት ወዳጃቸው ጋ ደወሉ] 

 • እንዴት ነዎት ክቡር ሚኒስትር?
 • እንዴት ነህ ወዳጄ?
 • አለን ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ሥራ እንዴት ይዞሃል?
 • ሥራ ተቀዛቅዟል፡፡
 • ይኸው ዛሬ ደረስኩልሃ እኔ፡፡
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • መሥሪያ ቤታችን አንድ ጨረታ እያወጣ ነው፡፡
 • ፈጥኖ ደራሽ እኮ ነዎት ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እዛው የፈርኒቸር ቢዝነስ ውስጥ ነው ያለኸው አይደል?
 • አዎን ክቡር ሚኒስትር ዋናው ሥራዬ እሱ አይደል?
 • በቃ የብዙ ሚሊዮን ብር ጨረታ ነው፤ ተዘጋጅ፡፡
 • የፀሎቴ መልስ ነዎት ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • የምን ፀሎት?
 • በቃ ይኸው አሁን ሌት ተቀን የምፀልየው የመልካም አስተዳደር በአገሪቷ ላይ እንዲሰፍን ነው፡፡
 • እንግዲህ ፀሎትህ ተሰምቷል፡፡
 • አሁንማ ስለቴን አስገባለሁ፡፡
 • ለማን ነው የምታስገባው?
 • ለታቦቱም ለእርስዎም ነዋ፡፡
 • በል እንግዲህ ስለቱን አታዘግየው፡፡
 • ታዲያ ዛሬ ምሳ ልጋብዝዎታ?
 • የት ነው የምትጋብዘኝ?
 • ፆም ሊገባ ስለሆነ ሥጋ ልጋብዝዎታ?
 • በጣም ሰው የሚበዛበት ቦታማ መታየት እኮ የለብኝም፡፡
 • ምን ችግር አለው ክቡር ሚኒስትር?
 • ያው በአገሪቷ ድርቅ ስላለ እኔ ሥጋ ቤት ስታይ ጥሩ አይደለም ብዬ ነው፡፡
 • የኢሕአዴግን ሲስተም እንጠቀማለን፡፡
 • ምን ዓይነት ሲስተም?
 • ሥጋ ቤቱን አዘግተን እንቆጣጠረዋለን፡፡
 • ማለት?
 • 100 ፐርሰንት እንቆጣጠረዋለን፡፡