ክቡር ሚኒስትር

[የክቡር ሚኒስትሩ ወዳጅ እንኳን ደስ አለዎት ለማለት ደወለ]

 

 • እንኳን ደስ አለዎት ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንኳን አብሮ ደስ አለን፡፡
 • አይ እኔ እኮ አልተሾምኩም፡፡
 • ባትሾምም ቢያንስ ስምህ ተሾመ ነው፡፡
 • እና በእሱ ልፅናና?
 • ሰው ባለው ነው ወዳጄ፡፡
 • እሱማ እውነት ነው፤ ለማንኛውም እንኳን ያለዎት ነገር አልተወሰደ፡፡
 • ማን ይወስደዋል ብለህ ነው?
 • ክቡር ሚኒስትር ረሱት እንዴ?
 • ምኑን?
 • የግምገማውን ጊዜ፡፡
 • እሱማ እንዴት ይረሳል?
 • ለነገሩ የወጋ ቢረሳ የተወጋ መቼ ይረሳል አይደል ነገሩ?
 • ተወግተሃል እያልከኝ ነው?
 • ዋናው ተወግተውም መቀጠልዎ ነው፡፡
 • ይነሳል ብለህ ፈርተህ ነበር እንዴ?
 • ማን እርስዎ?
 • እህሳ!
 • እርስዎማ እንኳን ከሥልጣን ሊነሱ ፎቶ ራሱ መቼ ተነስተው ያውቃሉ?
 • የሚያነሳኝ አጥቼ ነዋ፡፡
 • አገራችን እኮ ለዚህ አልታደለችም፡፡
 • እንዴት?
 • እኛ አገር ሥልጣን ላይ ለመውጣትም በትግል ነው፣ ከሥልጣን ለመውረድም በትግል ነው፡፡
 • የትጥቅ ትግል አቀንቃኝ ነህ ልበል?
 • ኧረ አልወጣኝም፡፡
 • ታዲያ ምን እያልክ ነው?
 • ማለቴ በሌሎች አገሮች ያሉት ባለሥልጣናት ጥፋት ሲያጠፉ በራሳቸው ፈቃድ ከሥልጣናቸው ይወርዳሉ ብዬ ነው፡፡
 • ማን ሲወርድ አይተናል? እስቲ አንድ ጥቀስ፡፡
 • ያው የምዕራባውያን አገር መሪዎች አሉ፡፡
 • የአሜሪካ ሴናተሮች በ1960ዎቹ ተሹመው እስካሁን ያገለግላሉ አይደል እንዴ?
 • ሕዝብ መርጧቸው ነዋ፡፡
 • እኛም እኮ ሕዝብ መርጦን ነው፡፡
 • እሱን እንኳን ውስጡን ለቄስ፡፡
 • ውስጡንማ እኛ ተቆጣጥረነዋል፣ ከፈለጉ ውጭ ይሁኑ፡፡
 • ማን?
 • ቄሱ፡፡
 • ለማንኛውም ለውጥ ይኖራል ብዬ ነበር፡፡
 • የምን ለውጥ?
 • ሹመቱ ላይ ነዋ፡፡
 • አሁን እኔን ማን ይተካኛል?
 • እርስዎን ማለቴ ሳይሆን ሌሎች የአቅም ችግር የነበረባቸውን ማለቴ ነው፡፡
 • በማን ይተኩ?
 • በወጣት መሪዎች ነዋ፡፡
 • መሪ ለመሆን እኮ ልምድ ወሳኝ ነው፡፡
 • አቅም ያላቸው ወጣት መሪዎች እኮ አሉ፡፡
 • ለመሆኑ የትኛው ድርጅት ነው ፍሬሽ ግራጁዌት የሚቀጥረው?
 • እ…
 • እኛስ ለማን ብለን ነው መንግሥትን መለማመጃ የምናደርገው?
 • እና ለዘመናት እየመራችሁ ልትኖሩ ነው?
 • ይኸውልህ ቴዲ አፍሮ ለዘፈን እንደተፈጠረ እኔም ለመምራት ነው የተፈጠርኩት፡፡
 • እና ዕድሜ ልክዎን ሲመሩ ሊኖሩ?
 • ዘፋኙ ዕድሜ ልኩን ሲዘፍን አይደል እንዴ የሚኖረው?
 • የባሰ አታምጣ አለ የአገሬ ሰው፤ እና የወጣቱ ተስፋ ምንድነው?
 • እኛው ነን፡፡

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ ቢሯቸው ገባች] 

 • እንኳን ደስ አለዎት ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • በአምላክሽ፡፡
 • እኔማ ጨንቆኝ ነበር፡፡
 • ምኑ ነው የጨነቀሽ?
 • አዲስ አለቃ ይመጣል ብዬ ነዋ፡፡
 • የምነሳ መስሎሽ ነበር?
 • የግምገማው ጊዜ እኮ አይጣል ነበር፡፡
 • ለነገሩ ፓርቲያችን ሂስሽን ዋጪ እንጂ አይጨክንብሽም፡፡
 • እሱንማ በእርስዎ አረጋገጥን፡፡
 • ከዚህ በኋላ ግን በቃኝ፡፡
 • ምኑ?
 • ሂስ መዋጥ ነዋ፡፡
 • እውነት?
 • አዎና ሂስ ውጬ መድኃኒት ውጬ እችለዋለሁ?
 • እሱማ ያስቸግራል፡፡
 • ስለዚህ ለውጥ ያስፈልጋል፡፡
 • የምን ለውጥ?
 • ለውጡ ከውስጥ ነው መጀመር ያለበት፡፡
 • እኮ ምን እንለውጥ?
 • መጀመሪያ ይኼን ምንጣፍ፣ ጠረጴዛና ወንበር ለውጭልኝ፡፡
 • እሺ፡፡
 • መኪናዬም ይለወጥ፡፡
 • ሌላስ?
 • የመሥሪያ ቤቱ ሁሉም ኮምፒዩተር ይለወጥ፡፡
 • እ…
 • የመሥሪያ ቤቱ ቀለምም ይለወጥ፡፡
 • ሌላስ?
 • ሁሉም አሮጌ ነገር ተለውጦ አዲስ መሆን አለበት፡፡
 • እነዚህን ነገሮች ግን አምና ነው የቀየርናቸው፡፡
 • አሁን በአዲስ መልክ ሥራ ልንጀምር ነዋ፡፡
 • ሌላ የሚቀየር የለም?
 • ሌላ ምን እንቀይራለን?
 • አዲስ አመራር ነዋ፡፡
 • ሰው ክቡር ስለሆነ መቀየር አይቻልም፡፡
 • ሰዎቹን መቀየር ባይቻል ቢያንስ አስተሳሰባቸው ለምን አይቀየርም?
 • በምንድነው የሚቀየረው?
 • ለዚህ ሁሉ ነገር ገንዘብ ከሚወጣ ሰዎቹ ለምን አቅማቸውን እንዲያጐለብቱ አይሠለጥኑም?
 • በቃ ለእሱ በጀት ይያዝለት፣ አበላቸውም ጠቀም ያለ ገንዘብ ይሁን፡፡
 • እኔ ግን አበል አይከፈል ባይ ነኝ፡፡
 • ለምን?
 • ሰዎች ከሥልጠናው የሚያገኙት ነገር እንዲለውጣቸው ነው እንጂ ማድረግ ያለብን አበል እንዲለውጣቸው ማድረግ የለብንም፡፡
 • ኪራይ ሰብሳቢ ነሽ ልበል?
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • ሰው እንዲጠቀም አትፈልጊማ፡፡
 • ኪራይ ሰብሳቢ ሆኜ እኮ አይደለም፡፡
 • ምን ሆነሽ ነው ታዲያ?
 • ኪራይ በታኝ፡፡

[የክቡር ሚኒስትሩ ወዳጅ ባለሀብት ቢሯቸው መጣ] 

 • እንኳን ደስ አለዎት ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንኳን አብሮ ደስ አለን፡፡
 • እኔማ ከእርስዎ በላይ ነው የፈነደቅኩት፡፡
 • በምኑ?
 • ሲሾሙ ነዋ፡፡
 • ለምን?
 • ክቡር ሚኒስትር ለእርስዎ ካልዘነበ ለእኔ መቼ ያካፋል?
 • አሁን ለሁሉም ዜጐች እኩል ነው የሚዘንበው፡፡
 • ያድርግልና፡፡
 • ምን ልርዳህ አሁን?
 • አንድ የውጭ ኢንቨስተር ከእኔ ጋር ለመሥራት ወደዚህ እየመጣ ነው፡፡
 • እሺ፡፡
 • ስለዚህ ለፕሮጀክታችን ሰፊ ቦታ እንፈልጋለን፡፡
 • ታዲያ የሚመለከታቸውን አካላት አናገራችሁ?
 • ክቡር ሚኒስትር እኔ እኮ ሁሉን ነገር በእርስዎ ነው የማስጨርሰው፡፡
 • አሁን ነገሮች ተቀይረዋል፡፡
 • ምን ተፈጠረ?
 • እንደ ወዳጅ ምን ማድረግ እንዳብህ ልመክርህ እችላለሁ፡፡ ከዚያ ውጪ ግን ሁሉን ነገር በራስህ መጨረስ አለብህ፡፡
 • ለማንኛውም ክቡር ሚኒስትር አንድ ስጦታ ይዤ መጥቻለሁ፡፡
 • የምን ስጦታ?
 • እንኩ ቼክ ነው፡፡
 • በል በል በል እዚያው ያዘው፡፡
 • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ሥራ በአዲስ መልክ ጀምረናል አልኩ እኮ፡፡
 • ይኼ እኮ ስለተሾሙ የደስታ ምኞት መግለጫዬ ነው፡፡
 • አሁን ሳትዋረድ ከዚህ ቢሮዬ ውጣልኝ፡፡
 • እውነት ነው ማለት ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ምኑ?
 • የመልካም አስተዳደር ችግር አለ የሚባለው፡፡
 • ለዚያ እኮ ነው ይኼን ቼክ የማልቀበልህ፡፡
 • እኔም ችግር አለ ያልኩት እኮ አልቀበልም ስላሉኝ ነው፡፡
 • ጭራሽ?
 • ያለመድኩት ሆኖብኝ ነዋ፡፡

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሾፌራቸው ጋር ወደ ቤት እየሄዱ ነው] 

 • በጣም ነው ደስ ያለኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • በምኑ?
 • ደግመው በመሾምዎት፡፡
 • ይኼን ያህል ሕዝቡ ይወደኛል ማለት ነው?
 • ከጭንቀት ነዋ የገላገሉኝ፡፡
 • ከምን ጭንቀት?
 • አዲስ አለቃ ከመልመድ፡፡
 • እ…
 • ምን እሱ ብቻ፡፡
 • ሌላስ ምን አለ?
 • አዲስ የአለቃ ሚስት፣ አዲስ የአለቃ ጥበቃ፣ አዲስ የአለቃ የቤት ሠራተኛ፣ ኧረ ስንቱ?
 • ይኼን ያህል ተጨንቀህ ነበር?
 • እህሳ፡፡
 • ለማንኛውም ሹመቱን እንዴት አየኸው?
 • ያስገረሙኝ ነገሮች ነበሩ፡፡
 • ምን አስገረመህ?
 • በአብዛኛው እኮ ደግመው ነው የተሾሙት፡፡
 • ታዲያ ምን ጠብቀህ ነበር?
 • አይ ያው ያ ሁሉ ችግር ተወርቶ፣ ሰዎቹ መልሰው ሲቀጥሉ ገርሞኛል፡፡
 • ለውጥ በሒደት ነው የሚመጣው፡፡
 • ሌላው ያስገረመኝ የአንዳንዶቹ አወቃቀር ነው፡፡
 • እንዴት?
 • አሁን ፆም ሊገባ ስለሆነ የፆም ሚኒስቴሩ ሥራ ሊበዛበት ነው፡፡
 • የምን የፆም ሚኒስቴር?
 • ማለቴ የዓሳ ሀብት ሚኒስቴሩ፡፡
 • የፆም ብቻ አይደለም የፍስክም ነው፡፡
 • እንዴት?
 • የእንስሳትና የዓሳ ሀብት ሚኒስቴር ነዋ፡፡
 • ሌላው የገረመኝ ደግሞ አርብቶ አደር ለብቻ፣ እንስሳት ሀብት ለብቻ ተዋቅረዋል፡፡ አርብቶ አደሩ የሚያረባው እንስሳት መስሎኝ?
 • እ…
 • ሌላው ያስገረመኝ ደግሞ የማዕድን፣ የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር ነው፡፡
 • ለምን?
 • የተፈጥሮ ጋዝ እኮ ነዳጅ ውስጥ መካተት ይችላል፡፡
 • የተፈጥሮ ጋዝ እኮ ስለተገኘ ነው፡፡
 • ቀጥሎ የፖታሽ ሚኒስቴርም ይመጣላ፡፡
 • ለአገር የሚጠቅም ከሆነ ምን ችግር አለው?
 • ስለዚህ ሌላ አገር የሚጠቅም ሚኒስቴርም እንጠብቃ፡፡
 • የምን ሚኒስቴር?
 • የዝንጅብል፣ የነጭ ሽንኩርትና የጥቁር አዝሙድ ሀብት ሚኒስቴር፡፡