ክቡር ሚኒስትር

 [የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ ቢሯቸውን በርግ ዶ ገባ]

 • ጉዱን ሰሙ ክቡር ሚኒስትር?
 • የምን ጉድ ነው?
 • መቼም እንደዚህ ዓይነት ጉድ ሰምቼ አላውቅም፡፡
 • እኛማ በጣም ብዙ ጉድ የሚያስብል ሥራ እንሠራለን፡፡
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • ይኸው የከተማ ባቡር ሥራ ከጀመረ ቆሞ ያውቃል?
 • ኧረ አያውቅም፡፡
 • ከዚህ ባለፈ ወደ ጂቡቲ የሚሄደው ባቡር በቅርቡ ሥራ ይጀምራል፡፡
 • እኔ የማወራው አልገባዎትም፡፡
 • እንዴ ግድቡስ ቢሆን 70 በመቶ ደርሷል አይደል?
 • ኧረ ክቡር ሚኒስትር እኔ የማወራው ሌላ ጉድ ነው፡፡
 • ታክሲዎቹ ዳግመኛ አድማ መቱ እንዴ?
 • ክቡር ሚኒስትር ችግርዎ ምን እንደሆነ ያውቃሉ?
 • እኔ ችግር አለብኝ?
 • ለዚያውም ከፍተኛ ችግር ነዋ፡፡
 • ምንድን ነው ችግሬ?
 • አለማዳመጥ፡፡
 • ማንን ነው የማላዳምጠው?
 • ማንንም፡፡
 • እሺ ልስማህ እስቲ ምንድን ነው ጉዱ?
 • ተሰረቀ እኮ፡፡
 • ምኑ ግድቡ ነው?
 • ግድቡማ እንዴት ይሰረቃል?
 • ያው ሰሞኑን ኮንዶሚኒየም ቤቶች ተሰረቁ ሲባል ስለሰማሁ ሌቦቹ በነካ እጃቸው ግድቡንም ከሞጨለፉት ብዬ ነው፡፡
 • ለነገሩ ሥጋትዎ ይገባኛል፡፡
 • እና ምንድን ነው የተሰረቀው?
 • ፈተናው ነዋ፡፡
 • የምን ፈተና?
 • የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና፡፡
 • ኤጭ፡፡
 • ያሳዝናል አይደል ክቡር ሚኒስትር?
 • ምን ዓይነት ቀሽም ሌባ ነው?
 • እንዴት ማለት?
 • ሰው ካልጠፋ ነገር ወረቀት ይሰርቃል?
 • አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር?
 • ተልካሻ ሌባ ነው፡፡
 • ምን እያሉ ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • እኔ እኮ የማይገባኝ ይኼን ፕሮፌሽን እንደዚህ ዓይነት ሌቦች ናቸው የሚያሰድቡት፡፡
 • እ…
 • እኛ ይኼ ፕሮፌሽን የላቀ ደረጃ እንዲደርስ ሌት ተቀን እየሠራን፣ በጐን ግን እንደዚህ ዓይነት ሌቦች ወደ ታች ይጐትቱናል፡፡
 • ምን እያሉ ነው ክቡር ራማኒስትር?
 • ስንት የሚሰረቅ ነገር እያለ ሰው እንዴት ፈተና ይሰርቃል?
 • ምን የሚሰረቅ ነገር አለ?
 • ለምሳሌ መሬት፡፡
 • ሌላስ?
 • ሕንፃ፡፡
 • ሌላስ?
 • ቪላ፡፡
 • ሌላስ?
 • ፋብሪካ፡፡
 • እ…
 • ቅርጫ፡፡
 • ምርጫ ነው ያሉኝ?

[ክቡር ሚኒስትሩ የፋይናንስ ኃላፊውን አስጠሩት]

 • ለምን እንደጠራሁህ ታውቃለህ?
 • አላወቅኩም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • የበጀት መዝጊያ እየተቃረበ ነው አይደል?
 • አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ከበጀታችን ምን ያህሉን ተጠቅመናል?
 • 30 በመቶውን፡፡
 • እንዴ 30 በመቶውን ብቻ?
 • አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንዴት ሆኖ?
 • መጀመሪያም እኮ ለጥጠን ነው ያቀድነው፡፡
 • እና መለጠጥ የለበትም ነው የምትለው?
 • እህሳ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ለመሆኑ ምንድን ነው ያጠናኸው?
 • 12ኛ ክፍል ነው የጨረስኩት፡፡
 • እንዴት ነው ታዲያ የፋይናንስ ኃላፊ የሆንከው?
 • በጣም አነባለሁ፡፡
 • ምንድን ነው የምታነበው?
 • አዲስ ራዕይ አንድም አምልጦኝ አያውቅም፡፡
 • በጣም ጥሩ፡፡
 • በዛ ላይ የጠራ የልማታዊ አስተሳሰብ ነው ያለኝ፡፡
 • ሌላስ?
 • ለፓርቲው ታማኝ ነኝ፡፡
 • ቀጥል፡፡
 • ቦታው ላይም የተመደብኩት በብሔር ተዋፅኦ ነው፡፡
 • እንዲህማ ከሆነ ለቦታው ከበቂ በላይ ነህ፡፡
 • ልክ ነዎት ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ስለዚህ በጀታችንን በሚገባ መጠቀም አለብን፡፡
 • ምን ይደረግ?
 • ፕሮጀክት ይቀረፅ፡፡
 • ምን ዓይነት ፕሮጀክት?
 • እሱን ለእኔ ተወው፡፡

[ክቡር ሚኒስትሩ ሚስታቸው ጋ ደወሉ]

 • መገናኘት አለብን፡፡
 • ምን ተገኘ?
 • ተገናኝተን መቅረፅ አለብን፡፡
 • ቪዲዮ ነው?
 • ሴትዮ ምን ሆነሻል?
 • ቅርፃ ቅርፅ ነው?
 • ጤነኛ ነሽ ግን?
 • ታዲያ ምንድን ነው የምንቀርፀው?
 • ፕሮጀክት፡፡
 • የምን ፕሮጀክት?
 • መሥሪያ ቤታችን 30 በመቶ በጀቱን ብቻ ነው የተጠቀመው፡፡
 • 70 በመቶውስ?
 • እሱን ወደ እኛ ማስገባት አለብን፡፡
 • እንዴት አድርገን?
 • መጀመሪያ የሕንፃችን ቀለም መቀየር አለብን፡፡
 • ምን ዓይነት ልታደርጉት?
 • ልማቱን የሚያመላክት ቀለም መሆን አለበት፡፡
 • እኮ ምን ዓይነት?
 • አረንጓዴ ነዋ፡፡
 • ውይ አረንጓዴ ቀለም ግን የለንም፡፡
 • ስቶክ ውስጥ ያለን ምን ዓይነት ቀለም ነው?
 • ጉበት ከለር፡፡
 • በቃ እሱ ይቀባላ፡፡
 • ልማታዊ ቀለም ግን አይደለም እኮ፡፡
 • እሱን ችግር በሌላ ነገር እንፈታዋለን፡፡
 • በምን እንፈታዋለን?
 • ልማታዊ ቀቢ እንዲቀባው እናደርጋለን፡፡
 • ልማታዊ ሐሳብ ነው፡፡
 • ሌላ ደግሞ የመሥሪያ ቤታችን ሙሉ ምንጣፍ መቀየር አለበት፡፡
 • እንዴ ከኢራን የመጡ ምንጣፎች አሉን አይደል?
 • ከግድግዳው ከለር ጋር የሚሄድ ምንጣፍ አዘጋጂ፡፡
 • ምንጣፍ ግን ያለን አረንጓዴ ከለር ብቻ ነው፡፡
 • ተፈላጊው ከለር እሱ አይደል እንዴ?
 • እንዴት?
 • ይኸው በዝናብ ምክንያት አረንጓዴ ነገር ስለጠፋ ቢያንስ ቢሯችን አረንጓዴ ምንጣፍ መኖሩ ግዴታ ነው፡፡
 • ለነገሩ ልማቱን በደንብ ያመላክታል፡፡
 • ሌላው መጋረጃዎች በአጠቃላይ ይቀየራሉ፡፡
 • መጋረጃ ግን ያለን ቀለም ውኃ ሰማያዊ ብቻ ነው፡፡
 • ይህቺን ሰማያዊ ከለር ግን አልወዳትም፡፡
 • ምን ይሻላል ታዲያ?
 • ይሁና ዓይኔ እያየ መቼም በጀቱ አይመለስም?
 • እኔማ ደስ ይለኛል፡፡
 • ሌላው በየቢሮው ሥዕል መሰቀል አለበት፡፡
 • እኛ እኮ ሥዕል አንሸጥም፡፡
 • ታዲያ ምን ችግር አለው? ገዝተን አትርፈን መሸጥ ነዋ?
 • ይኼ ልማታዊ ሐሳብ ነው፡፡
 • ሥዕሎቹ ግን እንትኑን ማንፀባረቅ አለባቸው፡፡
 • ምኑን?
 • ልማቱን!

[ክቡር ሚኒስትሩ የፋይናንስ ኃላፊውን አስጠሩት]

 • አቤት ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • በጀቱን ለመጠቀም የሚከተሉት ነገሮች ይለወጡ፡፡
 • ምኖቹ ክቡር ሚኒስትር?
 • የሕንፃችንና የቢሯችን ቀለም፡፡
 • እሺ፡፡
 • መጋረጃና ምንጣፍ፡፡
 • ሌላስ?
 • የግድግዳ ሥዕሎች፡፡
 • ምንም ችግር የለውም፡፡
 • ስለዚህ እነዚህ ሲገዙ ዕቃዎች የበጀታችንን ምን ያህል ተጠቀምን ማለት ነው?
 • 32 በመቶ ይደርሳል፡፡
 • እና ቀሪውን ልንመልስ?
 • ታዲያ ምን ይደረጋል?
 • የማደርገውንማ እኔ አውቃለሁ፡፡
 • ምን ሊያደርጉ?
 • አንመልስም እላለሁ፡፡
 • ለምን ቢባሉ ምን ይመልሳሉ?
 • አንዴ ሰጥታችሁናል ሰጥታችሁናል!

[ክቡር ሚኒስትሩ ቤት ምሳ በልተው ከሾፌራቸው ጋ እየተመለሱ ነው]

 • ዊኬንድ ኳስ አየህ እንዴ?
 • አላየሁም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ለምን አላየህም?
 • በኢቢሲ አይተላለፍም ነበር እኮ፡፡
 • ኢቢሲ ታያለህ እንዴ?
 • እኔ ታዲያ እንደ እርስዎ ዲኤስቲቪ የለኝ፡፡
 • ለምን አታስገባም?
 • ክቡር ሚኒስትር ደመወዜ ለአቅመ ዲኤስቲቪ አትደርስማ፡፡
 • እንደ አንተ ዓይነቱ እኮ ናቸው የሚያሰድቡን፡፡
 • እንዴት ማለት?
 • ኢኮኖሚያችን በ11 ፐርሰንት እየተምዘገዘገ ባለበት ወቅት ደመወዜ ለአቅመ ዲኤስቲቪ አትደርስም ስትል ያሳዝናል፡፡
 • የደላው ሙቅ ያኝካል አሉ፡፡
 • እና አንተ ምንድን ነው የምታኝከው?
 • ብሶት!

[ክቡር ሚኒስትሩ ቢሮ ገብተው ቲቪ እያዩ ነው፡፡ ጸሐፊያቸው ገባች]

 • ክቡር ሚኒስትር…
 • ፀጥ በይ!
 • ምነው?
 • ወሳኝ ሰዓት ላይ ነው የመጣሽው፡፡
 • ምን እያደረጉ ነው?
 • ቲቪ እያየሁ ነዋ፡፡
 • ውይ እኔም ትላንት ለቅሶ ሄጄ አምልጦኝ ነበር፡፡
 • ወንበር ስበሽ ቁጭ በይ በቃ፡፡
 • ውይ ባለጉዳዮቹ ግን…
 • እንዳታስመልጪኝ ዝም በይ አልኩሽ እኮ፡፡
 • ቢሮ ባለጉዳዮች አሉ ብዬ ነው፡፡
 • በዚህ ሰዓት እኛ ሁለት ባለጉዳዮች ብቻ ነው ያሉን፡፡
 • እነማን ናቸው?
 • ዛራና ቻንድራ!