ክቡር ሚኒስትር

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚስታቸው ጋር ስለትንሹ ልጃቸው ጉዳይ እየተወያዩ ነው]

 

 • ሰማህ አይደል ጉድህን?
 • የምን ጉድ ነው?
 • የትንሹ ልጅህን ጉድ ነዋ፡፡
 • ደሞ የምን ጉድ ነው?
 • ጀምሮልሃል፡፡
 • ምን? ትምህርት?
 • ሱስ ይዞታል፡፡
 • የምን ሱስ?
 • የምን ሱስ እንድልህ ነው የምትጠብቀኝ?
 • የአብዮታዊ ዴሞክራሲ?
 • እሱ ይሻለው ነበር፡፡
 • ታዲያ የምን ሱስ ነው የያዘው?
 • የሲጋራ፡፡
 • ምን?
 • ይኸውልህ ክፍሉ ያገኘሁት የሮዝማን ፓኬት፡፡
 • ጭራሽ ሮዝማን ነው የሚያጨሰው?
 • ምን እንዲያጨስ ፈልገህ ነበር?
 • እኛ ሌት ተቀን ኢምፖርት ሰብስቲትዩሽን ላይ እየሠራን፡፡
 • ምንድን ነው የምትቀባጥረው?
 • የአገር ውስጥ ሲጋራ እያለ የውጭ ሲጋራ?
 • ትቀልዳለህ ልበል?
 • እሱ ነው እንጂ እየቀለደ ያለው፡፡
 • ኧረ ሰውዬ ሰው ጉድ እንዳይልህ?
 • እሱን ነው እንጂ ጉድ የሚለው እኔማ ምን አደረኩ?
 • ሌላ ልጨምርልህ?
 • ጨምሪልኝ፡፡
 • ጫትም ጀምሮልሃል፡፡
 • አይደረግም?
 • ተደርጓል ስልህ፡፡
 • ልጁ ምን ነክቶታል?
 • እስቲ አንተ ጠይቀው፡፡
 • አገሪቷን የውጭ ምንዛሪ እያሳጣልኝ ነዋ?
 • አልገባኝም፡፡
 • ኤክስፖርት የሚደረግ ምርትን እዚሁ አገር ውስጥ እየተጠቀመበት ነው እኮ?
 • ጤነኛ ነህ ግን?
 • ጤነኛ ያልሆነውማ እሱ እኮ ነው፡፡
 • ምንድን ነው የምትዘባርቀው?
 • ልጁ ለአገር ማሰብ አቁሟል ማለት ነው?
 • አንተ ደግሞ ለልጅህ ማሰብ አቁመሃል ማለት ነው፡፡
 • ለአገሬ ካሰብኩ እኮ ለልጄም አሰብኩ ማለት ነው፡፡
 • ለዛ ነዋ የምትቦጠቡጣት?
 • ታዲያ በአንዴ በልቼ ልጨርሳት?
 • ለማንኛውም ውጤቱን ተመልከተው፡፡
 • የምን ውጤት ነው?
 • የክረምት ትምህርቱ ፈተና ነው፡፡
 • ስንት ነው ያመጣው?
 • ዘጠኝ ከሃምሳ፡፡
 • አይደረግም?
 • ተደርጐማ እያየኸው ነው፡፡
 • አገሪቱ በሁለት ዲጂት እያደገች የእኔው ጉድ ነጠላ አኃዝ ውጤት ያመጣል፡፡
 • እውነትም ጤና የለህም፡፡
 • በቃ ዛሬ ማታ መቀመጥ አለብን፡፡
 • ምንድን ነው የምንቀመጠው?
 • ግምገማ፡፡

[ክቡር ሚኒስትሩ ከአማካሪያቸው ጋር እያወሩ ነው]

 • እንኳን ደስ አለዎት ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ለምኑ?
 • ለሹመቱ ነዋ፡፡
 • ተሾምኩ እንዴ?
 • ያው የሥራ አስፈጻሚው ውስጥ ገቡ አይደል እንዴ?
 • ታዲያ እሱ ሹመት ነው?
 • ለነገሩ ስጦታ ነው ብለው ነው?
 • ምን ማለት ፈልገህ ነው?
 • ያው በጣም ተገምግመው ስለነበሩ …
 • ይባረራሉ ብለህ አስበህ ነበር?
 • እህሳ፡፡
 • እና ለዛ ነው ስጦታ ነው ያልከኝ?
 • ትክክል ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እባክህ ይኼን ጨዋታ በሚገባ አውቀዋለሁ፡፡
 • የቱን ጨዋታ?
 • የግምገማ ጨዋታውን፡፡
 • ለነገሩ ከሃያ ዓመታት በላይ ተጫወቱት አይደል?
 • ስለዚህ ጨዋታውን ለእኛ ተወው፡፡
 • እኔ የምለው ተዋችሁት እንዴ?
 • ምኑን?
 • መተካካቱን፡፡
 • ለጥቂት እኮ ነው የተረፍኩት፡፡
 • እንዴት?
 • እኛን ቄስ እግዚአብሔር ዕድሜ ይስጣቸው፡፡
 • አልገባኝም?
 • ይህ መገፋፋት እንጂ መተካካት አይደለም ብለው እኮ ነው ስበው የመለሱኝ፡፡
 • እንጂ ተተክተው ነበር?
 • ለጥቂት ነው የተረፍኩት ስልህ፡፡
 • ለወጣቶቹ ግን ለምን አይለቁም?
 • ለቀን የት እንሂድ?
 • ኧረ ክቡር ሚኒስትር ይህ እንዴት ያስጨንቅዎታል?
 • እንዴት አያስጨንቀኝ?
 • ቢያንስ ጥሩ አባት መሆን ይችላሉ፡፡
 • ይኸው አሁንስ ቢሆን የዘጠና ሚሊዮን ሕዝብ አባት አይደለሁ እንዴ?
 • ለነገሩ ይኼ የሁላችሁም ፖለቲከኞች ችግር ነው፡፡
 • እንዴት?
 • ተቃዋሚዎቹም ቢሆኑስ ከጥቂቶቹ በስተቀር ሁሉም ሥልጣናቸውን መቼ መልቀቅ ይፈልጋሉ?
 • እኛ እስረኛ ከለቀቅን አይበቃንም እንዴ?
 • ብቻ ክቡር ሚኒስትር ይኼን መተካካት ያስቡበት፡፡
 • ይኸው አንተ ወጣት ሆነህ ከእኔ ጋር እየሠራህ አይደል እንዴ?
 • ወጣቱ ሥልጣን ላይ መውጣት አለበት፡፡
 • ሥልጣን ላይ ካልወጣ አገር ማገልገል አይችልም?
 • እናንተስ ከሥልጣን ወርዳችሁ አገር ማገልገል አትችሉም?
 • ይኼ መገፋፋት ነው፡፡
 • የለም መተካካት ነው፡፡

[የክቡር ሚኒስትሩ ወዳጅ ባለሀብት ደወለላቸው]

 • በሰላም ጨረሳችሁ ክቡር ሚኒስትር?
 • የማያልቅ ነገር የለም ያው አለቀ፡፡
 • ሳይጨርሳችሁ መጨረሳችሁ መልካም ነው፡፡
 • እንዴት ማለት?
 • ያው አደገኛ ግምገማ መሆኑን ሰምቻለሁ፡፡
 • አደገኛ ብቻ? ዋናው መትረፋችን ነው፡፡
 • ግምገማ ብቻ ምንም ጥቅም የለውም፡፡
 • እንዴት ማለት?
 • ከፍተኛ ችግር ነዋ ያለው፡፡
 • የምን ችግር?
 • የመልካም አስተዳደር፣ የፍትሕ፣ የሙስና ኧረ ስንቱ፡፡
 • እኛም የተገማገምነው እሱ ላይ ነው፡፡
 • እርስዎም ክፉኛ እንደተገመገሙ ሰምቻለሁ፡፡
 • አዎን ተገምግሜያለሁ፡፡
 • እና ምን ወሰኑ?
 • ያው ለመለወጥ ወስኛለሁ፡፡
 • አይ ጥሩ ነው፡፡
 • ስለዚህ ከአንተ ጋርም ያለኝ ግንኙነት መቀነስ አለበት፡፡
 • ይሻላል?
 • ያው ለውጡ ከዚህ ነው የሚጀምረው፡፡
 • ያፅናልዎት፡፡
 • አሜን!

[የክቡር ሚኒስትሩ ወዳጅ ሌላ ሚኒስትር ደወሉ]

 • ተረፉ ክቡር ሚኒስትር?
 • ከምኑ?
 • ከመዓቱ፡፡
 • ይኸው ቆሜ እሄዳለሁ፡፡
 • ቀጣዩስ ምንድን ነው?
 • ሹመት ነዋ፡፡
 • ሽረቱንም መጠበቅ ጥሩ ይመስለኛል፡፡
 • የሰማኸው ነገር አለ እንዴ?
 • የሚወራውማ ብዙ ነው፡፡
 • እኮ ምን ሰማህ?
 • ሊቀየሩ ይችላሉ?
 • ወዴት?
 • ወደ ሌላ መሥሪያ ቤት፡፡
 • ለምን?
 • ያው በግምገማው ምክንያት ነዋ፡፡
 • ይኼማ ሊደረግ አይችልም፡፡
 • ለምን?
 • የመሥሪያ ቤቱ ራዕይስ?
 • የሚመጣው ሰው ያስቀጥለዋላ፡፡
 • በሕይወት እያለሁ ሌላ ሰው ሊያስቀጥለው?
 • ምን ችግር አለው?
 • ራዕዩንማ እኔ ነኝ ማስቀጠል ያለብኝ፡፡
 • ተፈርቶ እኮ ነው፡፡
 • ምንድን ነው የተፈራው?
 • ራዕዩን እንዳያቋርጡት፡፡
 • ሂሴን ዋጥኩ አይደል እንዴ ከዚህ በላይ ምንድን ነው የምትፈልጉት?
 • ሂስዎትን እንዲያወራርዱት ነዋ፡፡
 • በምንድን ነው የማወራርደው?
 • ከሥልጣን በመውረድ ነዋ፡፡
 • ኧረ ይቀየርልኝ፡፡
 • በምን?
 • በውኃ እንዳወራርደው፡፡
 • ሳይዋረዱ መውረድ ነው የሚሻለው እባክዎት፡፡
 • ከየት?
 • ከሥልጣን!

[ክቡር ሚኒስትሩ ቤት ሲገቡ ልጃቸውን መገምገም ጀመሩ]

 • ምንድን ነው የምሰማው?
 • ምን ሰማህ አባዬ?  
 • ሱስ ይዞሃል አሉ፡፡
 • የምን ሱስ?
 • የአብዮታዊ ዴሞክራሲ አልልህ የሲጋራ ነዋ፡፡
 • እ…
 • ብለህ ብለህ የአገር ውስጥ እያለልህ የውጭ ሲጋራ?
 • ምን?
 • በዛ ላይ የኒዮሊብራሎቹን ሲጋራ ታጨስልኛለህ?
 • ምንድን ነው የምታወራው አባዬ?
 • ኢምፖርት ሰብስቲትዩሽን ላይ እየደከምን ጉድ ትሠራን?
 • ኧረ አልገባኝም?
 • ከዚያም አልፎ ኤክስፖርት የሚደረግ ምርት ለአገር ውስጥ ፍጆታ እያዋልክልኝ ነው?
 • የምን ኤክስፖርት የሚደረግ ምርት ነው?
 • ጫት ነዋ፡፡
 • እ…
 • ይህ አልበቃ ብሎህ የነጠላ አኃዝ ውጤት ማስመዝገብ ጨምረሃል፡፡
 • የምን ነጠላ አኃዝ ነው?
 • በፈተና ያመጣኸው ውጤት ነው፡፡
 • ከብዶኝ ነዋ፡፡
 • ቢከብድህስ እንዴት ነጠላ አኃዝ ውጤት ታመጣለህ?
 • ምን ላድርግ ታዲያ?
 • ምን እየተደረግክ እንደሆነ ታውቃለህ?
 • አላውቅም፡፡
 • እየተገመገምክ ነው፡፡
 • በምን?
 • በኪራይ ሰብሳቢነት!
 • ልክ እንደ አንተ?