ክቡር ሚኒስትር

[ክቡር ሚኒስትሩ የግምገማ አዳራሹ ውስጥ ከመግባታቸው በፊት ከሌላ ሚኒስትር ጋር እያወሩ ነው]

 

 • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ምነው?
 • ፊትዎ ጠቋቁሯል፡፡
 • ሰሞኑን ግምገማም አይደል እንዴ?
 • ቢሆንስ ታዲያ?
 • እንቅልፍ ተኝቼ አላውቅም፡፡
 • ግምገማና እንቅልፍ ምን አገናኘው?
 • እንዴት አያገናኘው?
 • ንፁህ ሕሊና መልካም ትራስ ነው ሲባል አልሰሙም?
 • አልጋማ እንቅልፍ እንደማያመጣ አሁን ነው የተረዳሁት፡፡
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • አልጋ እንቅልፍ ቢያመጣማ ኖሮ ዋናው ሥራዬ እንቅልፍ ነበረ፡፡
 • አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር?
 • አልጋዬ ዋተር ቤድ ነው፡፡
 • ዋተር ቤድ?
 • አዎና፡፡
 • ከየት አምጥተው?
 • እ…
 • ማለቴ ውድ ነው ብዬ ነው?
 • አዎ ስጦታ ተሰጥቶኝ ነው፡፡
 • ይቻላል እንዴ?
 • ምኑ?
 • ስጦታ መቀበል፡፡
 • መቼም እምቢ አይባል?
 • ለነገሩ እርስዎ ገር ነዎት እኮ፡፡
 • እንዴት?
 • እሺ ባይ ነዎት ማለቴ ነው፡፡
 • እምቢ የሚለው ቃል ይከብደኛል፡፡
 • ሁሌ እሺ ማለት ግን ጉዳት አለው፡፡
 • የምን ጉዳት?
 • እምቢ ማለት ያለብዎት ነገሮች አሉ፡፡
 • ለምሳሌ?
 • ሙስና፡፡
 • እ…
 • ለማንኛውም ንፁህ መሆን ነው የሚያዋጣው፡፡
 • አሁን አንተ ንፁህ ነህ?
 • ንፁህ ራሱ በእኔ ዓይን ሲታይ ቆሻሻ ነው፡፡
 • እና ንፁህ ነኝ እያልክ ነው?
 • እንዴታ?
 • እኔ አላምንህም፡፡
 • ለምን?
 • በአሁን ዘመን እንደዚህ ዓይነት ሰው አለ?
 • እኔ የምመራው በዘመን አይደለም፡፡
 • ማነው መሪህ?
 • ንፁህ ሕሊናዬ፡፡
 • ወይ ሕሊና?
 • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
 • በአሁን ዘመን ሰው ሕሊና የለውም፡፡
 • እንዴት?
 • ቢኖረውም ደግሞ ደንዝዟል፡፡
 • በምን?
 • በገንዘብ፡፡
 • በገንዘብ እኮ አይኖርም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ታዲያ በደመወዝ ነው የሚኖረው?
 • ገንዘብማ ሕይወት እንደማያመጣ ቅድም እኮ ሲነግሩኝ ነበር፡፡
 • ምን ብዬ?
 • ውድ ዋጋ የሚያወጣ አልጋ ቢኖርዎትም፣ እንቅልፍ ግን ሊያመጣልዎት አልቻለም፡፡
 • እ…
 • ለማንኛውም ንፁህ መሆን ያዋጣል፡፡

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ ግምገማ አዳራሹ ገቡ፡፡ ግምገማውም ተጀመረ፡፡ ክቡር ሚኒስትሩ መገምገም ጀመሩ]

 • ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • አቤት፡፡
 • ግምገማችንን በእርስዎ ነው የምንጀምረው፡፡
 • እሺ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር አድሮ ቃሪያ ሆነዋል፡፡
 • ደግሞ ማንን አቃጠልክ ልትሉኝ ነው?
 • ባለፈው ጉባዔያችን ክፉኛ ተገምግመው ነበር፡፡
 • እ…
 • አሁንም ከስህተትዎ ሊታረሙ አልቻሉም፡፡
 • ምን አጠፋሁ?
 • ይህን ዶክመንት ይመለከቱታል?
 • ምንድነው እሱ?
 • እርስዎ ላይ የቀረበ ክስ ነው፡፡
 • የምን ክስ?
 • አይቸኩሉ፤ አንድ በአንድ ይሰሙታል፡፡
 • እሺ ቀጥል፡፡
 • ከአልጋዎት እንጀምር፡፡
 • አልጋዬ ደግሞ ምን ሆነ?
 • አልጋዎት ዋተር ቤድ ነው፡፡
 • ታዲያ መደብ ላይ ልተኛ?
 • ሰርቀው ውኃ ላይ ከሚተኙ፣ ሰርቀው መደብ ላይ ቢተኙ ይሻላል፡፡
 • ማን መደብ ላይ ተኝቶ አሳየን?
 • ለመሆኑ ከየት አመጡት?
 • ወዳጆቼ ስጦታ ሰጥተውኝ፡፡
 • እርስዎስ ምን ስጦታ ሰጧቸው?
 • የምን ስጦታ?
 • የ50 ሺሕ ብር ስጦታ ተቀብለው የ50 ሺሕ ዶላር ስጦታ እኮ ነው የሰጡት?
 • ኧረ እኔ ምንም አልሰጠኋቸውም፡፡
 • ማስረጃ እኮ እዚህ አለ፡፡
 • ወይ ጣጣ፡፡
 • ሒስዎትን ይውጣሉ?
 • ሌላ ምን ምርጫ አለኝ?
 • ልቀጥል?
 • እሺ ቀጥል፡፡
 • የባለቤትዎ መኪና ከየት ነው የመጣው?
 • ከጀርመን፡፡
 • የጀርመን መኪና መሆኑንማ አውቃለሁ፤ ጥያቄዬ ማን ነው የሰጣቸው?
 • ዘመዶቿ ነው የላኩላት፡፡
 • ውሸት!
 • የምን ውሸት ነው?
 • ማስረጃው እኮ እጄ ላይ ነው፡፡
 • ምን ይላል?
 • መኪናውን እዚህ አገር ያስገባው ድርጅት እዚህ ማስረጃ ላይ አለ፡፡
 • እ…
 • እርስዎም በምትኩ ትልቅ መሬት ድርጅቱ እንዲያገኝ አድርገዋል፡፡
 • እ…
 • ሒስዎትን ይውጣሉ አይውጡም?
 • ቆይ መጀመሪያ መድኃኒቴን ልዋጥ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ ነው እኮ የመጡት?
 • ኧረ እኔ ክብደት ብቻ ነው የጨመርኩት፡፡
 • ከክብደት ውጪ ሀብትና ሌብነትም ጨምረዋል፡፡
 • እ…
 • ሒስዎትን ይውጣሉ አይውጡም?
 • እውጣለሁ፡፡
 • እንቀጥል፡፡
 • እሺ፡፡
 • ፋብሪካ ያለው ሚኒስትር ሳውቅ እርስዎ የመጀመሪያዬ ነዎት፡፡
 • የምን ፋብሪካ? በስሜ ምንም ፋብሪካ የለም፡፡
 • በስምዎትማ አይደለም፡፡
 • ታዲያ በማን ስም ነው?
 • በአክስትዎት ልጅ፡፡
 • እ…
 • ገጠር ያለ ገበሬ እንዴት ነው ፋብሪካ ሊኖረው የሚችለው?
 • እኔ ምን ላድርግ? ራሳችሁ ናችኋ፡፡
 • ምን ማለት ነው?
 • መንግሥት ኢኮኖሚያችን ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መቀየር አለበት ይላል፡፡
 • ታዲያ ቢልስ?
 • ስለዚህ ዘመዶቼ ከግብርና ወጥተው ወደ ኢንዱስትሪ ዘርፉ እንዲቀላቀሉ አድርጌያለሁ፡፡
 • ውሸት ነው!
 • እ…
 • ሁሉም ማስረጃ በእጄ አለ፡፡
 • ምን ተሻለኝ?
 • ሒስዎትን ይውጣሉ ወይስ አይውጡም?
 • እንዳያንቀኝ እኮ ፈርቼ ነው፡፡
 • ማወራረጃ ይፈልጋሉ?
 • እህሳ?
 • ከፈለጉ በውኃ አሊያም በሌላ ነገር ያወራርዱት፡፡

[ግምገማው ለሻይ ዕረፍት ተቋረጠ፡፡ ክቡር ሚኒስትሩም ሚስታቸው ጋ ደወሉ]

 • ዛሬ አዋረድሽኝ፡፡
 • ምን አድርጌ?
 • በሰው ፊት ነው መሳቂያ ያስደረግሽኝ፡፡
 • እኮ ምን አድርጌ?
 • በመኪናሽ አስገመገምሽኝ፡፡
 • አንተ ግን ትንሽ አታፍርም?
 • በምኑ?
 • ለነገሩ ስትሰርቅ ካላፈርክ አሁን እንዴት ታፍራለህ?
 • ምን እያልሽ ነው?
 • ድሮስ ስትሰርቅ አልገመግምም ብለህ አስበህ ነበር?
 • የዛሬ ግን ባሰብኝ፡፡
 • በሌላ በምን ተገመገምክ?
 • በአልጋዬ በይ፣ በፋብሪካው በይ፡፡
 • በቃ?
 • አሁን ለሻይ ዕረፍት ወጥተን ነው፡፡
 • በል በዚሁ እንዲያልፍልህ ፀልይ፡፡
 • ምን ብዬ ልፀልይ?
 • በምታምንበት ነገር ፀልይ፡፡
 • ያመንኩት ነገር አይደል እንዴ እየጨፈጨፈኝ ያለው፡፡
 • ይህ ጥሩ ጊዜ ነው፡፡
 • ምን ለማድረግ?
 • ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ፡፡

[የሻይ ዕረፍቱ አልቆ ግምገማው ቀጠለ]

 • ክቡር ሚኒስትር ግምገማችንን እንቀጥላለን፡፡
 • አሁንም እኔው ነኝ?
 • እርስዎ ከተገመገሙ፣ ሌሎችም በእርስዎ ውስጥ ይገመገማሉ ማለት ነው፡፡
 • ወይ ጣጣ፡፡
 • ፓርቲያችን ውስጥ ዲሲፕሊን ከፍተኛ ቦታ ይሰጠዋል፡፡
 • አውቃለሁ፡፡
 • የፓርቲያችንን የዲሲፕሊን መመርያ ካረቀቁት ሰዎች መካከልም አንዱ እርስዎ ነዎት፡፡
 • ልክ ነው፡፡
 • እርስዎ ደግሞ ባለትዳርና የልጆች አባት ነዎት፡፡
 • እውነት ነው፡፡
 • በየሄዱበት ከተማ ግን ይማግጣሉ፡፡
 • ቢራም አትጠጣ እያላችሁኝ ነው?
 • ቢራ መጠጣት ይችላሉ፤ አርዓያ የሌለው ተግባር ግን መፈጸም አይችሉም፡፡
 • ይህ እኮ ግላዊ ሕይወቴ ነው፡፡
 • የተቀመጡት ግን ግላዊ ቦታ ላይ አይደለም፡፡
 • ወይ ጣጣ፡፡
 • ልቀጥል?
 • እሺ ቀጥል፡፡
 • ልጅዎት የት ነው የምትማረው?
 • ውጭ አገር፡፡
 • እንዴት ውጭ አገር ልትማር ቻለች?
 • ስኮርላርሽፕ አግኝታ፡፡
 • ውሸት!
 • እ…
 • ማስረጃ አለኝ፡፡
 • ምን ይላል?
 • እዚህ አገር በቀላሉ የገባ የውጭ ኩባንያ የልጅዎን የትምህርት ቤት ክፍያ እንደሚከፍል እናውቃለን፡፡
 • የውጭ አገር ኩባንያም አገር ውስጥ አይግባ እያላችሁኝ ነው?
 • መግባት ይችላል፤ አላግባብ ግን እንዲገባ አይፈቀድለትም፡፡
 • አሁንስ አልበዛም?
 • ግምገማው ገና ይቀጥላል፡፡

[ክቡር ሚኒስትሩ ሒሱ ስለበዛባቸው መበሳጨትና መሳደብ ጀመሩ]

 • አሁን እናንተ ጤነኛ ሆናችሁ ነው?
 • የታመመ ካለ ዛሬ ይመረመራል ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እዚህ ውስጥ አንድም ንፁህ ሰው የለም፡፡
 • እሱን እርስዎ አሉ፡፡
 • ሁሉም ሌባ ነው፡፡
 • እርስዎ ግን ከዚያም በላይ ነዎት፡፡
 • ምንድን ነኝ?
 • የሌባ ፈልፋይ!