ክቡር ሚኒስትር

[ክቡር ሚኒስትሩ ከአማካሪያቸው ጋር እያወሩ ነው]

 

 • እንዴት አለፈ ክቡር ሚኒስትር?
 • ምኑ?
 • ግምገማው?
 • እንግዲህ የመጀመሪያው ዙር በድል ተጠናቋል፡፡
 • እርስዎ ለነገሩ በግምገማ ጥርስዎን ነቅለዋል፡፡
 • ምንም ያህል በግምገማ ጥርስህን ብትነቅልም፣ ጨዋታው ካልገባህ ልትነቀል ትችላለህ፡፡
 • ከምን?
 • ከሥልጣንህ ነዋ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር እርስዎ ይነቅላሉ እንጂ ይነቀላሉ እንዴ?
 • ከፍተህ ከተጫወትክ መነቀልህ አይቀርም፡፡
 • ግምገማው እንደ ቦክስ ጨዋታ ያደርገዋል ማለት ነው?
 • የማያደርገውን ነገር ጠይቀኝ፡፡
 • ለማንኛውም ዋናው በድል መወጣትዎ ነው፡፡
 • ወሳኙ እኮ ቀጣዩ ታላቁ ጉባዔ ነው፡፡
 • ያው እንደዚኛው ግምገማ ይወጡታላ?
 • የዚህኛው ጨዋታ ትንሽ ከበድ ይላል፡፡
 • ያው የለመዱትን ታክቲክ መተግበር ነዋ፡፡
 • እሱ ነው እኮ ያስጨነቀኝ፡፡
 • እንዴት?
 • ግምገማው ላይ ስልክ አይገባም እየተባለ ነው፡፡
 • ለምን?
 • እንዴ የባለፈውን ግምገማ እኮ ያሸነፍነው በስልካችን ነው፡፡
 • እንዴት?
 • አንዱ ሲገመገም ለአንዱ ቴክስት ታደርጋለህ፡፡
 • እሺ፡፡
 • በላከው ቴክስት ሲገመገም ሌላ ቴክስት ለሌላ ሰው ትልካለህ፡፡
 • እሺ፡፡
 • በቃ  እንዲህ እያደረግህ ተገምጋሚውን ትንፋሽ ታሳጥረዋለህ፡፡
 • ወይ ጉድ?
 • ከዛም አዳራሹ ሐዘን ቤት እስኪመስል ድረስ ታስለቅሰዋለህ፡፡
 • አይጣል ነው መቼም፡፡
 • ከዛም አንተን መገምገም ስለማይችል አንገቱን አስደፍተህ ታስወጣዋለህ፡፡
 • የሚገርም ታክቲክ ነው፡፡
 • በዚህ ታክቲክ ነው እንግዲህ ድል የነሳነው፡፡
 • ኔትወርኩ ግን እንዴት ነበር?
 • ኔትወርክህማ ወሳኝ መሆን አለበት፡፡
 • ማለቴ የቴሌው?
 • እሱ ነበር ችግር ሲፈጥርብን የነበረው፡፡
 • ታዲያ አሁን እንዴት ሊያደርጉ ነው?
 • ስለምኑ?
 • ማለቴ ስልክ የማይገባ ከሆነ?
 • እኔም ማጠፊያው አጥሮብኛል እባክህ?
 • ታዲያ በወረቀት ለምን አያደርጉትም?
 • ምኑን?
 • መልዕክት መላላኩን፡፡
 • ከጻፍኩት በኋላ በምን እልከዋለው?
 • ያው አጣጥፈው መወርወር ነዋ፡፡
 • በልጅነታችን ፈተና ላይ መልስ እንደተላላክነው?
 • እህሳ?
 • ኧረ አይታሰብም፡፡
 • ካልሆነ መቅረት ነው፡፡
 • ምን ብዬ አቀራለሁ?
 • አሞኛል ብለው ነዋ፡፡
 • ብችልማ ደስ ይለኛል፡፡
 • አይቻልም እንዴ?
 • ቢያመኝ ራሱ በቃሬዛ መጥቼ እገመግማለሁ እንጂ መቅረት አልችልም፡፡
 • ታዲያ ምን ተሻለ?
 • በፀሎትህ አስበኝ፡፡
 • በየትኛው ፀሎት?
 • በአብዮታዊ ዴሞክራሲ!

[የክቡር ሚኒስትሩ ወዳጅ የሆነ ዳያስፖራ ወዳጃቸው ደወለላቸው]

 • ወደዳችሁት አቀባበላችንን?
 • ደስ የሚያሰኝ ነበር፡፡
 • አገሪቷንስ እንዴት አገኛችኋት?
 • ዕድገት መኖሩን ልመሰክር እወዳለሁ፡፡
 • እንግዲህ እናንተም በዚህ ዕድገት መሳተፍ አለባችሁ፡፡
 • ለዛም ብለን ነው ወደዚህ ያቀናነው፡፡ ግን…
 • የምን ግን ነው?
 • አሁንም ሊሻሻሉ የሚገባቸው ነገሮች አሉ፡፡
 • ምን ይሻሻል?
 • ቢሮክራሲው፡፡
 • እ…
 • ሙስናው፡፡
 • እ…
 • መልካም አስተዳደሩም፡፡
 • ያው እንግዲህ ታዳጊ ደሞክራሲ ስላለን መታገስ አለባችሁ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር የ24 ዓመት ጎረምሳ ታዳጊ ማለት አይከብድም?
 • ጀመርክ ፖለቲካህን?
 • እንዳልኩዎት ይቀይሩት፡፡
 • ምኑን?
 • ታዳጊን በጎረምሳ፡፡

[ክቡር ሚኒስትሩ ትንሽ ስለጨነቃቸው ያለወትሯቸው በሥራ ቀን ግራውንድ ቴኒስ የሚጫወቱበት ቦታ ሄዱ፡፡ አንድ ወዳጃቸውን እዚያው አገኙ]

 • ምነው ያለወትሮው ክቡር ሚኒስትር?
 • ምን ላድርግ ትንሽ ጨንቆኝ ነው፡፡
 • ምን ያስጨንቆዎታል?
 • ይኸው ግምገማ ነዋ፡፡
 • ውይ ሳልጠይቅዎት እንዴት አለፈ?
 • የመጀመሪያዋን እንኳን በድል አጠናቅቄያታለሁ፡፡
 • እርስዎ እኮ በግምገማ አይታሙም፡፡
 • ቀጣዩ ጉባዔ እንኳን አስጨንቆኛል፡፡
 • እርስዎ ይገመግማሉ እንጂ አይገመገሙ?
 • ችግሩ የተገመገምኩ ቀን ነዋ፡፡
 • እሱን ነው መፍራት፡፡
 • አሁን እኮ ቢጨንቀኝ ነው የመጣሁት፡፡
 • ፊትዎት ያስታውቃል፡፡
 • ለመሆኑ እነዚህ እነማን ናቸው?
 • እነማን ክቡር ሚኒስትር?
 • በርካታ አዳዲስ ሰዎች እኮ ናቸው ያሉት?
 • ክቡር ሚኒስትር እርስዎ እኮ ጠፍተዋል፡፡
 • ምን ላድርግ ሥራ በዛ?
 • ለዛ ነው አዲስ ሰው የበዛብዎት፡፡
 • ለመሆኑ ይኼ ማን ነው?
 • አዲስ ነጋዴ ነው፡፡

[ግራውንድ ቴኒስ ከሚጫወቱት አንድ አዲስ ነጋዴ ወደ ክቡር ሚኒስትሩ ጠጋ ብሎ ወሬ ጀመሩ]

 • እንዴት ነዎት ክቡር ሚኒስትር?
 • አይቼህ አላውቅም አዲስ ነህ?
 • መምጣት ከጀመርኩ ወራት አለፉ፤ እርስዎ መጥተው ስለማያውቁ ነው፡፡
 • ታዲያ እዚህ እንዴት መምጣት ጀመርክ?
 • ያው እርስዎን ለማግኘት ነዋ፡፡
 • እኔን ለማግኘት እዚህ ድረስ?
 • ሲኦልስ ና ቢሉኝ አልመጣም እንዴ?
 • እኮ ለምን?
 • እርስዎን ለማግኘት ነዋ፡፡
 • ምን አደርግልሃለው?
 • እርስዎ በር መሆንዎትን ሰምቻለሁ፡፡
 • የምን በር?
 • የሁሉም በር፡፡
 • እሱስ ልክ ብለሃል፡፡
 • ለማንኛውም እንኩ ይህቺን፡፡
 • ምንድን ናት?
 • ከእንግሊዝ ያመጣሁልዎት ስኒከር ናት፡፡
 • እንግሊዝም ሄደሃል?
 • አዎን፡፡
 • ሲያዩህ እኮ አዲስ አበባ ለመጀመሪያ ጊዜ የመጣህ ነው የምትመስለው፡፡
 • ለማንኛውም ጫማውን ከወደዱት ኮንቴይነር ሙሉ ላስመጣልዎት እችላለሁ፡፡
 • ኧረ አንተ እንደዚህ አይባልም፡፡
 • ይቅርታ አጠፋሁ?
 • ብዙ መማር ያለብህ ነገር አለ፡፡
 • ጥሩ ተማሪ ለመሆን ዝግጁ ነኝ፡፡
 • እስቲ እናያለን፡፡
 • እርስዎም ጥሩ አስተማሪ መሆንዎትን ሰምቻለሁ፡፡
 • አልተሳሳትክም፡፡

[የክቡር ሚኒስትሩ ወዳጅ ሚኒስትር ደወሉላቸው]

 • አሁንስ ሰለቸን ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምኑ?
 • ማደራደሩ፡፡
 • ለምን?
 • አልስማማ አሉ፡፡
 • እስቲ ለወጥ ያለ ቦታ አደራድሯቸው፡፡
 • ጉልቻ ቢለወጥ ወጥ አያጣፍጥም አሉ፡፡
 • እንዴት?
 • ያልተሞከረ ነገር የለም እኮ?
 • አስረዳኝ እስቲ፡፡
 • እዚህ ሲመጡ የሚያርፉት እጅግ ዘመናዊ ሆቴሎች ውስጥ ነው፡፡
 • አውቃለሁ፡፡
 • እሱም ከሰለቻቸው ብለን ከከተማ ውጪም ሞከርናቸው፡፡
 • አይ ኖው፡፡
 • ብቻ ያልተሞከረ ነገር የለም፡፡
 • ቀብጠው ይሆን እንዴ?
 • መሰለኝ፡፡
 • ታዲያ ምን ተሻለ?
 • አሁን እኮ ካልተስማሙ ጉዳዩን UN ሊረከበው ይችላል፡፡
 • እሱማ አይሆንም፡፡
 • ለምን?
 • እኛ እኮ የአፍሪካ ጀርመን ነን፡፡
 • እንዴት?
 • ሚዲያ አትከታተልም እንዴ?
 • ኧረ እከታተላለሁ፡፡
 • ታዲያ ጀርመን የአውሮፓ ፈላጭ ቆራጭ አይደለች?
 • እሱማ ልክ ነው፡፡
 • እኛም የአፍሪካ ፈላጭ ቆራጭ ነን፡፡
 • ደስ ይላል ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ስለዚህ እኛው እንደጀመርን እኛው እንጨርሰዋለን፡፡
 • ግድቡን ነው?
 • ድርድሩን፡፡

[የክቡር ሚኒስትሩ የቅርብ ዘመድ ስለወለደች እሷን ለመጠየቅ ከሾፌራቸው ጋር እየሄዱ ነው]

 • ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • አቤት፡፡
 • ግርማ ሞገስዎት እኮ ደስ ይላል፡፡
 • እንዴት?
 • ስብሰባ ላይ ያለዎት ግርማ ሞገስ ደስ ይላል፡፡
 • አንተ ግን ብዙም አልተገመገምክም አይደል?
 • እኔ እኮ ድሃ ነኝ፤ በምን እገመገማለሁ ብለው ነው?
 • አገሪቱ በ11 ፐርሰንት እያደገች ድሃ ነኝ ትላለህ?
 • ማደግማ አድጌያለሁ፡፡
 • ጐሽ፡፡
 • ያደኩት ግን በ0.11 ፐርሰንት ነው፡፡
 • ነገረኛ፡፡

[ክቡር ሚኒስትሩ የወለደችው ዘመዳቸው ጋር ደረሱ፤ ከሌላ ዘመዳቸው ጋር ማውራት ጀመሩ]

 • እንዲያውም ክቡር ሚኒስትሩ ይገላግሉን፡፡
 • ምንድን ነው የምገላግላችሁ?
 • ለልጅቷ ስም እያወጣን ነበር፡፡
 • እሺ ማን አላችኋት?
 • እማሆይ ጽዮን አሏት፡፡
 • ጥሩ ስም ነው እኮ ታዲያ?
 • አይ የልጅቷ አጎት ከፌዴራል ሥርዓታችን ጋር የሚሄድ ስም መውጣት አለበት እያለ ነው፡፡
 • ታዲያ ማን አላት?
 • ብዙነሽ፡፡
 • እርሱ ግን የቀረ ስም ነው፡፡
 • አክስቷ ሌላ ሐሳብ አምጥታ ነበር፡፡
 • ምን አለቻት?
 • ህዳሴ፡፡
 • ይሄ እኮ ጥሩ ስም ነው፡፡
 • እናቷ ግን አልወደደችውም፡፡

[የክቡር ሚኒስትሩ ወዳጅ ዳያስፖራ ቢደውልላቸውም ስልኩን አላነሱትም]

 • እንደውም ሐሳብ መጣልኝ፡፡
 • ማን እንበላት ክቡር ሚኒስትር?
 • ዳያስፖራ!