ክቡር ሚኒስትር

[የክቡር ሚኒስትሩ ወዳጅ የሆነ ነጋዴ ደወለላቸው]

 

 • ሄሎ!
 • እንዴት ነዎት ክቡር ሚኒስትርዬ?
 • አለሁልህ ወዳጄ፡፡
 • ክረምቱ እንዴት ይዞዎታል?
 • በጋው ማለትህ ነው?
 • ለምን እንደዚያ አሉ?
 • ያው ዝናብ የለም ብዬ ነዋ፡፡
 • እርስዎ ይፈልጉ እንጂ ማስመጣት እንችላለን፡፡
 • ምኑን?
 • ዝናቡን፡፡
 • ከየት?
 • ከቻይና ነዋ፡፡
 • ቀልደኛ ሆነሃል ልበል?
 • ለፈገግታ ብዬ ነው፡፡
 • ታዲያ ምን ልርዳህ?
 • ክቡር ሚኒስትር ዕቃዎቼ ወደብ ደርሰዋል፡፡
 • ምን ትቀልዳለህ?
 • አዎን ክቡር ሚኒስትር፣ ባይሆን ዝናቡ ለእኛ ሊዘንብ ነው፡፡
 • ምን ዝናብ ብቻ በረዶ ነው በለኝ እንጂ፡፡
 • ልንበሸበሽ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • አሁን ታዲያ ምን ያስፈልጋል?
 • ክቡር ሚኒስትር ቀረጡ እጅግ ከፍተኛ ነው የሚሆነው፡፡
 • ምን ችግር አለ ይቀነሳላ?
 • እሱን ነው የምልዎት፡፡
 • በዚያ ላይ አንተ ደንበኛ ነህ፡፡
 • አይደል?
 • ለዚያውም የ24 ዓመት ደንበኛ፡፡
 • እሱማ ልክ ነው፡፡
 • ቅናሽ ብቻ ሳይሆን ሌላም ነገር ሊኖር ይችላል፡፡
 • ሌላ ምን?
 • በነፃስ ቢገባ?
 • አድርገውት ነው፡፡
 • ብቻ የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን፡፡
 • እኔም ሐሳቤን እፈጽማለሁ፡፡
 • ምንድን ነው ሐሳብህ?
 • ክቡር ሚኒስትር የእርስዎ ነገር ሁሌም ያሳስበኛል፡፡
 • እንዴት?
 • ይህቺን አገር እኮ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ነው የሚያገለግሉት፡፡
 • ምን ላድርግ ብለህ ነው?
 • አንዳንዴ ደግሞ ዕረፍት ያስፈልግዎታል፡፡
 • እሱማ ያስፈልጋል፡፡
 • ስለዚህ እኔም ማረፊያ ነገር እሠራልዎታለሁ፡፡
 • ማለት?
 • ጥሩ ቤት እሠራልዎታለሁ፡፡
 • የት? እዚህ?
 • ምን በወጣዎት ክቡር ሚኒስትር?
 • ታዲያ የት ነው?
 • ከፈለጉ ዱባይ፣ ከፈለጉም አውሮፓ ወይም አሜሪካ፡፡
 • እ…
 • ብቻ ይህቺን ጉዳይ ያስጨርሱልኝ፡፡
 • ሌላ ምን ሥራ አለኝ አሁንማ?
 • በቃ እሱን ነው የምልዎት፡፡
 • አታስብ ስልህ?
 • እርስዎም አያስቡ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ሰው ሁሉ እንዲህ ቢተሳሰብ ይህቺ አገር የት በደረሰች?
 • ምቀኛ ብቻ በዛ፡፡
 • አያልፍላቸውም ተዋቸው፡፡
 • እኛም ሳያልፍብን መረዳዳት ነው፡፡
 • እንደ አንተ ዓይነት ቀና ልብ ያላቸውን ነው የምንፈልገው፡፡
 • ቆንቋና ከመሆን ቅን መሆን ይሻላል፡፡

[ክቡር ሚኒስትሩ ስልኩን ዘግተው ቢሯቸው ተክዘው ቁጭ ብለዋል፡፡ አማካሪያቸው በድንገት ቢሯቸው ገባ]

 • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ምን ሆንክ?
 • ተክዘዋል፡፡
 • ስንት የሚያስተክዘኝ ጉዳይ አለ እባክህ?
 • ምርጫውን አሸንፈን በምንደሰትበት ወቅት የምን ትካዜ ነው?
 • የዚህች አገር ጉዳይ ያሳስበኛል፡፡
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • ይህ ሕዝብ እኮ አደራ ነው የሰጠን፡፡
 • ታዲያ ሁሌም አደራችንን እንደተወጣን ነው፡፡
 • ለነገሩ አራዳ አደራ አይፈራም፡፡
 • ምን አሉኝ?
 • የድሮ አራዳ ነኝ እኮ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር አሁን አደራ መጠበቅ ነው እንጂ የሚያዋጣው አራዳ መሆን አያዋጣም፡፡
 • ለምን?
 • ግምገማ ደርሷላ፡፡
 • እ…
 • ምነው ደነገጡ?
 • እሷ ነገር ደስ አትለኝም፡፡
 • ምን ችግር አለው ክቡር ሚኒስትር?
 • ብዙ ችግር ነው ያለው፡፡
 • ዋናው እኮ ንፁህ መሆን ነው፡፡
 • እ…
 • እርስዎ ደግሞ በዚህ አይጠረጠሩም፡፡
 • አይደል?
 • የንፁሆች ንፁህ ነው እኮ የሚባሉት፡፡
 • ግን ግምገማ አልወድም፡፡
 • ለምን?
 • በኔትወርክ ነዋ የሚያጠቁህ፡፡
 • እርስዎ የሙስና ኔትወርክ ውስጥ አሉበት እንዴ?
 • አይደለም ግምገማም የሚካሄደው በኔትወርክ ነው፡፡
 • እኔ እኮ የድርጅቱ አባል ስላልሆንኩ አይገባኝም፤ ምን ማለት ነው?
 • ግምገማ ሲካሄድ በቡድን ተደራጅተው ነው የሚያጠቁህ፡፡
 • ልክ እንደ ሙስናው፡፡
 • ለዚያ እኮ ነው አራዳ መሆን አለብህ የምልህ፡፡
 • ለማንኛውም እንግዲህ ይቅናዎት፡፡

[ክቡር ሚኒስትሩ የመሥሪያ ቤታቸው የድርጅት ክንፍ መሪ ጋ ደወሉና ቢሯቸው እንዲመጣ ነገሩት]

 • ፈለጉኝ ክቡር ሚኒስትር?
 • ለሁለት ነገር ነው የፈለግኩህ፡፡
 • ምን ልታዘዝ?
 • የወዳጃችን ዕቃ ወደብ ደርሷል፡፡
 • አይሉኝም?
 • ደርሷል ስልህ?
 • ተተኮስና?
 • ሕይወታችን ሊቀየር ነው፡፡
 • ታዲያ ምን ላድርግ?
 • ታክስ አካባቢ ያሉ ሰዎቻችንን ንገራቸው፡፡
 • ሌላ ምን ሥራ አለኝ ክቡር ሚኒስትር?
 • ስለዚህ ዕቃው ቶሎ እንዲለቀቅ ይደረግ፡፡
 • ምንም አያስቡ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ታክሱ ላይ የሚደረገው ነገር ይደረግለት፡፡
 • እሱ እኮ ደንበኛ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ስለዚህ ለደንበኛ ደግሞ ቅናሽ መደረግ አለበት፡፡
 • በነፃስ ቢደረግለት ክቡር ሚኒስትር፣ ምን ችግር አለው?
 • ሁሉም ሰው እንደ አንተ ቢሆን የት በደረስን ነበር?
 • ክቡር ሚኒስትር አያስቡ፣ እንደ ጀመርን እንጨርሰዋለን፡፡
 • ምኑን?
 • ሁሉንም ነገር፡፡
 • ዋነኛው ነገር ሁለተኛው ነው፡፡
 • ምንድን ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ግምገማችን፡፡
 • እ…
 • አካሄዳችን ጥንቃቄ የተሞላበት መሆን አለበት፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር እውነቱን ልንገርዎት፡፡
 • ንገረኝ፡፡
 • እንቅልፍ ከወሰደኝ ቆየሁ፡፡
 • ለምን?
 • ግምገማውን ሳስበው ነፍሴ ትጨነቃለች፡፡
 • የሰማሃው ነገር አለ እንዴ!
 • ምን የማይሰማ ነገር አለ ብለው ነው?
 • ስለማን ነው የሰማሃው?
 • ስለራሴ ነዋ፡፡
 • ምን ይባላል?
 • ቤት አለው፡፡
 • እ…
 • መኪና አለው፡፡
 • ወይ ጉድ፡፡
 • ኧረ ስንቱ አለ፡፡
 • ስለእኔስ ምን ሰምተሃል?
 • ስለ እርስዎ እንኳን ብዙም አልሰማሁም ግን መጠንቀቁ አይከፋም፡፡
 • ወይ ጣጣ፡፡
 • ግምገማው ደግሞ ያው በኔትወርክ ነው የሚካሄደው፡፡
 • ስለዚህ እኛም የራሳችንን ኔትወርክ እናዘጋጅ፡፡
 • እሺ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ያው ሁሌም የምናቀማምሳቸው ሰዎች ስለእኔም ሆነ ስለአንተ መልካም ነገር እንዲያወሩ ይደረግ፡፡
 • እሺ፡፡
 • እሱ ብቻ ሳይሆን እኔንም ሆነ አንተን ሊገመግሙ የሚችሉ ሰዎችን አስቀድመው አንገታቸውን እንዲደፉ ማድረግ አለባቸው፡፡
 • እሺ፡፡
 • ለመሆኑ ሊገመግሙን የሚችሉ ሰዎች ይታወቃሉ እንዴ?
 • እሱ እንኳን አይታወቁም ግን የምጠረጥራቸው አሉ፡፡
 • ስለዚህ እነዚህ ሰዎች ላይ የምናቀርበውን ወቀሳ እዚያው ግምገማው ውስጥ በቴክስት እንላላካለን፡፡
 • እሺ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • አንተም ላይ ክስ ከቀረበብህ እዚያው በቴክስት የምልክልህን ነገር ታወራለህ፡፡
 • አደራዎትን ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ብቻ በቻልከው መጠን ኔትወርካችንን አጠናክር፡፡
 • የሚቻለኝን አደርጋለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ ግምገማ ከመግባታቸው በፊት ጸሐፊያቸው ቢሯቸው ገባች]

 • ምን ፈለግሽ?
 • ስልክዎትን ልቀበልዎት ነው፡፡
 • ለምን ሲባል?
 • አይ ያው ወደ ግምገማ ሊገቡ ነው ብዬ ነዋ፡፡
 • ከቻልሽ እንዲያውም ሌላ ስልክ ብትጨምሪልኝ ደስ ይለኛል፡፡
 • ግምገማ ውስጥ ደግሞ ስልክ ምን ያደርግልዎታል?
 • ግምገማችንም እንደ አገራችን ትራንስፎርም አድርጓል፡፡
 • እንዴት?
 • ስልካችን ለግምገማ ወሳኝ ነው፡፡
 • ግምገማ በስልክ?
 • ለማንኛውም ኔትወርኩ እንዳይጠፋ ፀልይልኝ፡፡

[ክቡር ሚኒስትር ግምገማው አስጀመሩት፣ የድርጅት ክንፍ መሪው ክፉኛ እየተገመገመ ነው]

 • እሺ አንተ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ሰውዬው አደገኛ ነው፡፡
 • እንዴት?
 • ደመወዙ መቼም ይታወቃል፡፡
 • በሚገባ ነው የሚታወቀው፡፡
 • የራሱ የግል ቤት አለው፡፡
 • እሺ፡፡
 • በዚያ ላይ ሚስቱ ዘመናዊ አውቶሞቢል ነው የምትነዳው፡፡
 • ሌላስ?
 • በእናቱ ስምም በባንክ የተቀመጠ ከፍተኛ ገንዘብ አለ፡፡
 • እሺ ሌላስ?
 • በሚስቱ ስም የተመዘገበም ሱቅ አለ፡፡

[ክቡር ሚኒስትሩ በግምገማው ወቅት ለድርጅቱ ክንፍ መሪ ምን ብሎ መናገር እንዳለበት ቴክስት አደረጉለት፡፡ የድርጅቱን ክንፍ መሪ የሚገመግመው ሰውዬ መናገር ካቆመ በኋላ ተገምጋሚውን መጠየቅ ጀመሩ]

 • የሚባለውን ክስ እየሰማህ ነው?
 • አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • የሚባለው እውነት ነው?
 • እ…
 • መልስልኝ እንጂ?

[ተገምጋሚው ግራ ተጋብቶ ያለቅሳል]

 • ለቅሶውን ትተህ ለምን አትመልስልኝም?

[ተገምጋሚው አሁንም ለቅሶውን ቀጠለ]

 • ምላሽ የለህም?
 • እእእ…

[ክቡር ሚኒስትሩ ግምገማው ሲያልቅ የድርጅቱ ክንፍ መሪውን አገኙት]

 • ጉድ አደረጉኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምን ሆነህ ነው ምላሽ ያልሰጠኸው?
 • ምን ምላሽ ልስጥ?
 • በቴክስት የላኩልህን ነዋ፡፡
 • አልደረሰኝም፡፡
 • ለምን?
 • ኔትወርኩ አይሠራም!