ክቡር ሚኒስትር

[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ጋዜጠኛ ደወለላቸው]

 

 • ሰላም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ሰላም እንዴት ነህ?
 • እግዚአብሔር ይመስገን፡፡
 • መቼም ጥሩ አድርጋችሁ ነው የምትዘግቡት?
 • ምኑን?
 • የኦባማን ጉብኝት ነዋ፡፡
 • ለእሱማ እናንተን እየጠበቅናችሁ ነው፡፡
 • ደግሞ ከመቼ ጀምሮ ነው ዘገባ ለመዘገብ እኛን የምትጠብቁት?
 • ማለቴ ሥልጠናውን እየጠበቅን ነው፡፡
 • የምን ሥልጠና?
 • የውጭ ሚዲያዎች የሚሰጡንን ሥልጠና ነዋ፡፡
 • የምን ሥልጠና ነው የሚሰጧችሁ?
 • ዘገባውን እንዴት መዘገብ እንዳለብን ነዋ፡፡
 • እናንተ ደግሞ ለሌላው ታስተምራላችሁ እንጂ ትማራላችሁ እንዴ?
 • እኛማ እንደዚያ ነበር የሚመስለን እንደዚያ እንዳልሆነ ግን አሁን አወቅን፡፡
 • እንዴት?
 • ሰደባችሁን እኮ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እኛ?
 • እህሳ፡፡
 • ምን ብለን?
 • የኢትዮጵያ ሚዲያ ሥነ ምግባር የለውም ብላችሁ ሞለጫችሁን እኮ፡፡
 • ኧረ እኛ እንደሱ አላልንም፡፡
 • አላችሁ እንጂ፣ እንዲያውም የውጭ አገር ሚዲያዎች ለእኛ ሥልጠና እንዲሰጡን ተማጸናችሁ፡፡
 • እ…
 • እኔ የምለው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምንድነው አንተ የምትለው?
 • ማያ ነገር ናችሁ ልበል?
 • የምን ማያ ነው የምታወራው?
 • ስፔስ 99 የሚለውን ፊልም አያስታውሱትም?
 • ኧረ አላስታውሰውም፡፡
 • ለነገሩ ያኔ በኢቲቪ ሲተላለፍ እናንተ በረሃ ነበራችሁ፡፡
 • ምን ለማለት ፈልገህ ነው?
 • ማያ የምትባል አክተር ፊልሙ ላይ ነበረች፡፡
 • እሺ፡፡
 • እና ማያ ስትፈልግ ጭራቅ፣ ስትፈልግ ቆንጆ ሴት፣ ስትፈልግ ወንድ፣ ኧረ ስንቱን ነበር የምትሆነው፡፡
 • ታዲያ እዚህ ምን አመጣት?
 • እናንተም ማያ ሆናችሁብን እኮ፡፡
 • እንዴት?
 • ከዛሬ አራትና አምስት ዓመት በፊት የውጭ ሚዲያውን ኒዮሊብራሊስትና የግል ኩባንያዎች ተቀጣሪዎች ናቸው ትሉን ነበር፡፡
 • አዎን ልክ ነው፡፡
 • አሁን ደግሞ ተቀይራችሁ ለአገራችን ሚዲያዎች ሥልጠና ስጡልን አላችሁ፡፡
 • ታዲያ ምን ችግር አለው?
 • እኮ እንደ እስስት እየተቀያየራችሁ የራሳችሁን ጥቅም ለማስከበር ትቆማላችሁ፡፡
 • እኛ እኮ እንዲያግዟችሁ ብለን ነው፡፡
 • ከእነሱ ይቅል እናንተ ብታግዙን ይጠቅመናል፡፡
 • እንዴት እናግዛችሁ?
 • ሚዲያውን አበረታች የኢንቨስትመንት ዘርፍ አድርጉት፡፡
 • እ…
 • ጋዜጠኞች እንደ ልባቸው እንዲጽፉና እንዲናገሩ አድርጉ፡፡
 • እንደ ልባቸው ከጻፉና ከተናገሩማ ዕድገት አይኖርም፡፡
 • ታዲያ ምንድነው የሚኖረው?
 • ውድቀት፡፡
 • ይኼ ነው ችግራችሁ፡፡
 • እንዴት?
 • ሰዎች ሮቦት አይደሉም፡፡
 • እሱንማ አትነግረኝም፡፡
 • ስለዚህ ሁሉም ሰው የተለያየ አመለካከት አለው፡፡ ከእናንተ ስለተለየ ብቻ ማጥላላት ተገቢ አይደለም፡፡
 • ለማንኛውም ሥልጠናው ያስፈልጋችኋል፡፡
 • ለመሆኑ እኛን ማን ነው የሚያሠለጥነን፡፡
 • አንዳቸው ናቸዋ፡፡
 • የአሜሪካው ኒውዮርክ ታይምስ ማለት ነው? ወይስ የእንግሊዙ ዘ ሰን ነው? ወይስ የቻይናው ፒፕልስ ዴይሊ ነው?
 • ምን ልዩነት አላቸው?
 • ትልቅ ልዩነት አላቸው፡፡ ሁሉም የራሳቸው የሆነ ርዕዮተ ዓለም ያራምዳሉ፡፡
 • ለእኛ ርዕዮተ ዓለም የትኛው ይቀርባል፡፡
 • የቻይናው ይመስለኛል፡፡
 • እንዲያውም እነሱ ናቸው ሥልጠናውን የሚሰጧችሁ፡፡
 • የአሜሪካኖቹን እኮ ስጡልን ብላችሁ ተማጽናችሁ ነበር፡፡
 • ተሰርዟል እንላቸዋለን፡፡

[የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ ቢሯቸው ገባ] 

 • እንዴት አለፈ እባክህ?
 • ስኬት ብቻ ነበር ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • አንተስ እንዴት ገመገምከው?
 • አስፈነደቅነው አይደል እንዴ?
 • እንዴት?
 • ቅድመ አያቱን አገናኘነው፡፡
 • የኦባማ ቅድመ አያት ኢትዮጵያዊ ናት እንዴ?
 • አይ ማለቴ ሉሲን ልልዎት ፈልጌ ነው፡፡
 • እኔ ደግሞ ይኼንን እስከዛሬ እንዴት ሳላውቅ ብዬ ልቆጭ ነበር፡፡
 • ቡናም አስጠጣነው፡፡
 • ልክ ነው፡፡
 • ጭፈራም ቢሆን አስጨፈርነው፡፡
 • ተጠምቆ ነዋ፡፡
 • በምን?
 • በአብዮታዊ ዲሞክራሲ፡፡
 • ሰው እኮ ገርሞታል፡፡
 • ምኑ ነው የገረመው?
 • ያው ስለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ምናምን አደገኛ ትችት ይሰጣል ተብሎ ነበራ የሚጠበቀው፡፡
 • በመርፌ እኮ ነው የሰጠነው፡፡
 • ምኑን?
 • አብዮታዊ ዲሞክራሲን፡፡
 • አንድ ግን ቅር ያለችኝ ነገር ነበረች፡፡
 • ምኑ ነው ቅር ያለህ?
 • የእሱ ሴኪዩሪቲዎች ናቸዋ፡፡
 • ምን አደረጉ?
 • እኛ እኮ ቅኝ ግዛት ያልተገዛን አገር ነን፡፡
 • አውቃለሁ፡፡
 • የእኛን ጥበቃዎች እኮ አላስጠጋ ብለው እነሱ ነበሩ ሲራወጡብን የነበረው፡፡
 • ያው ለደኅንነት ብለው ነዋ፡፡
 • እኛ እኮ ክቡር ሚኒስትር፣ አይደለም ኦባማን ዳር ድንበራችንን ከጥንት ጀምሮ ሳናስነካ የቆየን ኩሩ አገር ነን፡፡
 • እሱማ ልክ ነው፡፡
 • ቅኝ ግዛት የማያውቁት ጠባቂዎቻችን እኮ ቅኝ ተገዙ፡፡  
 • በማን?
 • በኦባማ ሴኪዩሪቲዎች ነዋ፡፡
 • እ…
 • ከዚህ በኋላ ከመጣ ይኼ መደገም የለበትም፡፡
 • እውነትህን ነው፡፡

[የክቡር ሚኒስትሩ ወዳጅ የሆኑ ነጋዴ ደወሉላቸው] 

 • ከአሜሪካ ከመጡት ኩባንያዎች ጋር ተፈራረምክ እንዴ?
 • በየትኛው ዕድሌ ክቡር ሚኒስትር?
 • ለምን አልተፈራረምክም?
 • መንግሥት ሁሉን ነገር ጠራረገው እኮ፡፡
 • ምን?
 • እንዲያው ለእናንተ ሲዘንብ ለእኛም ቢያካፋ ጥሩ ነው፡፡
 • ምን ማለትህ ነው?
 • ለመሆኑ የኦባማ መምጣት ጥቅሙ ምንድነው?
 • በንግድና ኢንቨስትመንት ልንተሳሰር ነዋ፡፡
 • እንዴት ማለት?
 • በርካታ የአሜሪካ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ ሊጐርፉ ነዋ፡፡
 • ምን ሊያደርጉ?
 • ሊነግዱ ነዋ፡፡
 • እ…
 • እንደ ድሮው ለምነን ሳይሆን ሠርተን ማደር ልንጀምር ነው፡፡
 • ግን ይታሰብበት፡፡
 • ምኑ ነው የሚታሰብበት?
 • ዕድገታችን ተቀልብሶ ልመና ውስጥ እንዳይከቱን፡፡
 • እንዴት?
 • የአሜሪካ ኩባንያዎች እኮ እዚህ መጥተው ቢነግዱ፣ የሚያገኙትን ትርፍ ጠራርገው ነው የሚወስዱት፡፡
 • እ…
 • እኛ ግን ብናተርፍ እዚሁ ነው ኢንቨስት የምናደርገው፡፡
 • ስለዚህ?
 • ይህ ጉዳይ በሚገባ ሊታሰብበት ይገባል፡፡
 • አሁን ጥቅሜ ይነካል ብለህ ነው አይደል?
 • አይደለም ክቡር ሚኒስትር፣ በደንብ አስቡበት ብዬ ነው፡፡
 • እንዲያውም ሥልጠና የሚያስፈልጋቸው ጋዜጠኞች ሳይሆኑ እናንተ ናችሁ፡፡
 • የምን ሥልጠና?
 • የውጭ ኩባንያዎች ለእናንተ ሥልጠና መስጠት አለባቸው፡፡
 • በምን ጉዳይ?
 • በሁሉም ጉዳይ፡፡
 • ብቻ አስቡበት፡፡

[የክቡር ሚኒስትሩ ጓደኛ ሌላ ሚኒስትር ደወሉ] 

 • እንዴት አየኸው የኦባማን ጉብኝት?
 • አጨራረሱ ጥሩ አይደለም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንዴት?
 • የአፍሪካ ኅብረቱን ንግግር አልሰሙም እንዴ?
 • ሰምቼዋለሁ፡፡
 • በአሽሙር እኮ ነው የነገረን፡፡
 • ምን ብሎ?
 • ምርጫ ማድረግ ዴሞክራሲ አለ ማለት አይደለም ብሎ ነዋ፡፡
 • እ…
 • የአፍሪካ መሪዎች ሥልጣን ለምን አለቅም እንደሚሉ እኮ አይገባኝም ነው ያለው፡፡
 • አገርን ማገልገል ስለምንወድ ነዋ፡፡
 • ሥልጣን ለቃችሁ አገር ማገልገል ትችላላችሁ ብሎ እኮ ነው ወረፍ ያደረገን፡፡
 • እ…
 • በዚያ ላይ ደግሞ ያንን ሁላ ገንዘብ ይዘው ለምን ሥልጣን እንደማይለቁ ነው ግራ የሚገባኝ እኮ ነው ያለው፡፡
 • አፍሪካዊ መሪ ቢሆን ይገባው ነበር፡፡
 • ደግሞ የእኛም ባለሥልጣናት ሲያጨበጭቡለት ነበር፡፡
 • አሽሙሩ ስላልገባቸው ይሆናላ፡፡
 • ለማንኛውም አጨራረሱን አልወደድኩትም፡፡
 • ምን ታደርገዋለህ?
 • በአፍሪካ አስመስሎ እኛን በአሽሙር ወግቶን ነው የሄደው፡፡
 • የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳም አሉ፡፡

[ክቡር ሚኒስትሩ ቤት ሲገቡ ሚስታቸውን አገኟቸው] 

 • ነይ ተመልከቺ ይኼን ፎቶ፡፡
 • የምን ፎቶ ነው?
 • ከኦባማ ጋር የተነሳሁት፡፡
 • ምን ያደርግልሃል?
 • ይኼ እኮ ቅርሴ ነው፡፡
 • የምን ቅርስ?
 • ለልጆቼ አሳልፌ የምሰጣቸው ቅርስ፡፡
 • ፎቶ ከምትሰጣቸው መርህ ብትሰጣቸው የበለጠ ይጠቅማቸዋል፡፡
 • ለማንኛውም ይህ ታሪክ ነው፡፡
 • ለመሆኑ እንዴት አለፈ?
 • ስኬት በስኬት ነበር፡፡
 • ደግሞ ብላችሁ ብላችሁ የሰፈር ሴቶችንና ወጣቶችን ቲሸርት አስለብሳችሁ አዘመራችኋቸው አይደል?
 • እንግዳ ተቀባይ መሆናችንን አትርሺ፡፡
 • ያ ሁሉ የአንድ ወር በሥራ መጠመድ ለዚሁ ነው?
 • ምናለ ማመስገን ብትለምጂ?
 • ለማንኛውም ይኼ ደብል ዲጂት ዕድገታችሁ ሰለቸኝ፡፡
 • ለምንድነው የሚሰለችሽ?
 • በየሚዲያው እሱን እኮ ነው የምትለፍፉት፡፡
 • አሜሪካ ራሷ በደብል ዲጂት እያደገች አይደለም፡፡
 • ሌላው የረሳሁት ደግሞ፡፡
 • ደግሞ ምን ረሳሽ?
 • ጂምናስቲክ ጀምረሃል እንዴ?
 • ጠዋት ጠዋት ስፖርት እሠራለሁ እንጂ የምን ጂምናስቲክ አመጣሽ?
 • አይ ፕሬዚዳንቱ ከአውሮፕላን ሲወርድ እንደዚያ ወገባችሁ እስኪሰበር ድረስ ምን ሆናችሁ ነው ብዬ ነዋ፡፡
 • እሱ ለየት ያለ አቀባበል ነው፡፡
 • ምን የሚሉት አቀባበል?
 • ልማታዊ አቀባበል!