ክቡር ሚኒስትር

[ክቡር ሚኒስትሩ የኦባማን መምጣት አስመልክቶ የተቋቋመውን ኮሚቴ እንዲመሩ ተሹመዋል፡፡ ክቡር ሚኒስትሩ አማካሪያቸውን አስጠሩት]

 

 • አቤት ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • የፋይናንሱ ስብሰባ እንዴት እየሄደ ነው?
 • አሁንማ ወደ ማብቂያው እየተቃረበ ነው፡፡
 • ስለዚህ በሰላም አልፏላ?
 • በሚገባ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • አሁን ቀጣዩ የቤት ሥራችን ላይ ነው ማተኮር ያለብን፡፡
 • የትኛው የቤት ሥራ?
 • ትልቁ የቤት ሥራ ነዋ፡፡
 • ጂቲፒ 2 ነው የሚሉኝ?
 • ከሱ የማይተናነሰው ሌላው የቤት ሥራ፡፡
 • ደግሞ ጂቲፒ 2ን የሚያክለው የቤት ሥራችን ምንድነው?
 • የኦባማ መምጣት፡፡
 • ምን አሉኝ?
 • ሰምተሃል፤ የኦባማ መምጣት፡፡
 • እሱ ምን አዲስ ነገር አለው?
 • ምን እያልከኝ ነው? እንዴት የለውም?
 • በርካታ መሪዎች መጥተው አስተናግደናል እኮ?
 • እሱ እኮ ለየት ያለ መሪ ነው፡፡
 • ቢሆንስ?
 • ለየት ያለ ዝግጅት ያስፈልገዋል፡፡
 • እኮ ምን ይደረግ?
 • አንተ የኮሚቴው ጸሐፊ አይደለህ እንዴ? ምን ይደረግ ትላለህ?
 • ክቡር ሚኒስትር ተሰብስበን እኮ አናውቅም፡፡ ስለዚህ አቅጣጫ ሳይሰጠኝ ምን ማድረግ እችላለሁ?
 • ለአንተ አቅጣጫ ሳይሆን መቀጫ ነበር መስጠት፡፡
 • ምን አደረግኩ?
 • ሁሌ ምሪት የምትፈልግ ዜጋ ነሃ፡፡
 • መሮኝ እኮ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • አገሪቷ በማደጓ ነው የመረረህ?
 • አይ ስብሰባ በዛብኝ፤ እንዲያው አንዳንዴ ያደገችው በስብሰባ ይመስለኛል፡፡
 • በሚዲያው ስለዕድገታችን እየተዘመረ አይደል እንዴ? ዜና አትከታተልም እንዴ?
 • ኧረ እከታተላለሁ፡፡
 • እኮ ዜናው ምን ያወራል?
 • ስለግሪክና ስለኢራን ነዋ፡፡
 • የትኞቹን ነው የምትከታተለው?
 • ዓለም አቀፍ የዜና ተቋማትን ነዋ፡፡
 • እ… ኒዮሊብራሎቹን፡፡
 • እርስዎ የቱን ተከታትለው ነው ስለዕድገታችን እየተዘመረ ነው ያሉት?
 • ኢቢሲን ነዋ፡፡
 • እሱማ ከመዘመር ውጪ አያለቅስ?
 • አንዳንዴ እንኳን ያለቅሳል፡፡
 • መሪ ሲሞት ነዋ፡፡
 • አሁን ለማንኛውም በኦባማ መምጣት ላይ የታችኛው የኅብረተሰብ ክፍል ድረስ መሥራት አለብን፡፡
 • ታዲያ ምን ይደረግ?
 • ሁሉንም ጥራልኝ፡፡
 • እነማንን ልጥራ?
 • የሴቶች ሊግ፣ የወጣቶች ሊግና የደጋፊ ነጋዴዎች ማኅበርን፡፡
 • መቼ ይጠሩ?
 • አሁኑኑ፡፡

[የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ የሴቶች ሊግ ተወካይን ጠርቷቸው ሚኒስትሩ ጋ ገቡ]

 • ጤና ይስጥልኝ እሜቴ፡፡
 • ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እየተዘጋጃችሁ ነው?
 • ያው ይህቺ የፍልሰታ ጾም ትለፍ ብለን ነው፡፡
 • ለምንድነው የምትዘጋጁት?
 • ለአዲሱ ዓመት ነዋ፡፡
 • አይደለም እሜቴ፣ እኔ የምልዎት ለኦባማ መምጣት ነው፡፡
 • ለእሱ መምጣት የተለየ ነገር ያስፈልጋል እንዴ?
 • አዎ ለየት ያለ ዝግጅት ያስፈልጋል፡፡
 • የእኛ ወዳጆች እኮ ቻይናዎች ናቸው ስለምትሉን ነው፡፡
 • እኛ ወዳጅ ለመሆን ለሚፈልግ በራችን ክፍት ነው፡፡
 • ዝግ የሆነው ለሚቃወም ነው ማለት ነው?
 • እኛን መቃወም ክልክል ነው!
 • እኛስ የምንደግፈው ወደን ነው?
 • ለማንኛውም አሁን ለእሱ ምን አዘጋጅታችኋል?
 • ፈንዲሻ፣ ቡና፣ ዳቦ ነዋ፡፡
 • ለኦባማ?
 • እህሳ? እሱ ከጠቅላይ ሚኒስትራችን ይለያል? ለእሳቸውም እሱን ነው ያቀረብነው፡፡
 • እሱ እንግዳ ነው ብዬ ነው፡፡
 • እንግዳም ቢሆን ቤት ያፈራውን ነዋ የሚቀርብለት፡፡
 • ለማንኛውም አሁን አንድ ነገር እንዲያደርጉ ነው የጠራሁዎት፡፡
 • ምን ላድርግ?
 • ሙሉ ከተማዋ መፅዳት አለባት፡፡
 • ለምን?
 • ለኦባማ፡፡
 • እሺ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ስለዚህ እርስዎ ሴቶቹን ሁላ አስተባብረው መንደሩን ሁሉ ያፀዱት፡፡
 • ብዙ ወጪ ግን ይኖረዋል፡፡
 • የሚያስፈልገው በጀት ሁሉ ይመደባል፡፡
 • በጀት ካለማ አይደለም ማፅዳት አቆሽሹ ብትሉንስ ማድረጋችን መቼ ይቀራል?
 • በቃ ወደ ፅዳት፡፡

[ክቡር ሚኒስትሩ አማካሪያቸውን አስጠሩት] 

 • አቤት ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • አሁን ደግሞ የወጣቶችን ሊግ በአስቸኳይ አስጠራልኝ፡፡
 • እሺ ክቡር ሚኒስትር፡፡

[የወጣቶች ሊግ ተወካይ ክቡር ሚኒስትሩ ቢሮ ገባ]  

 • አቤት ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • አምሮብሃል እባክህ?
 • ዕድሜ ለጂቲፒ 2 እንዴት አያምርብኝ?
 • እየተዘጋጃችሁ ነው?
 • ይኸው የአንድ ለአምስት አደረጃጀቱን ወደ አንድ ለሦስት ለመቀየር ተግተን እየሠራን ነው፡፡
 • ማን አዘዛችሁ?
 • ጂቲፒ 2 ነዋ፡፡
 • እኮ እንዴት?
 • ያው ለወጣቱ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ነዋ፡፡
 • ለማንኛውም እኔ ያልኩህ ለኦባማ መምጣት ነው፡፡
 • ምን ይደረግ? እዘዙኝ አስፈጽማለሁ፡፡
 • ችግኞች ይተከሉ፡፡
 • ለምን?
 • ኦባማን በቀይ ምንጣፍ ሳይሆን በአረንጓዴ ምንጣፍ ነው የምንቀበለው፡፡
 • እንዴ ችግኞቹ እኮ በአንዴ አያድጉም፡፡
 • አንተ ምን ቸገረህ? ትከል ብቻ ነው የተባልከው፡፡
 • በኋላ ይነቀላሉ?
 • ስለመንቀሉ በስብሰባ ይወሰናል፡፡
 • ለዚህ ግን ከፍተኛ በጀት እኮ ያስፈልጋል፡፡
 • የሚያስፈልጋችሁ በጀት ሁሉ ይመደብላችኋል፡፡
 • በጀት ካለውማ አይደለም ትከሉ ንቀሉ ብትሉንስ አናደርገውም እንዴ?
 • በቃ አሁን ወደ ችግኝ ተከላ፡፡

[ክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊያቸው የደጋፊ ነጋዴዎች ተወካይን እንድትጠራቸው ነገሯት] 

 • ፈለጉኝ ክቡር ሚኒስትር?
 • እየተዘጋጃችሁ ነው?
 • ለምኑ ክቡር ሚኒስትር?
 • ለኦባማ መምጣት ነዋ፡፡
 • አልተዘጋጀንም፣ ግን አሁን ከነገሩኝ መዘጋጀት እንችላለን፡፡
 • ያው እንደተለመደው ፈሰስ ማድረግ አለባችሁ፡፡
 • ኧረ ክቡር ሚኒስትር እሱንማ አሁን ማድረግ አንችልም፡፡
 • ለምን?
 • የታክስ መዓት ነው የተቆለለብኝ፡፡
 • ያለታክስም መሥራት አስበህ ነበር?
 • ለመሆኑ ለምንድነው ፈሰሱ የተፈለገው?
 • መንገድ ላይ ያሉት ለማኞች ሁሉ አዲስ ልብስ መልበስ አለባቸው፡፡
 • ለምን?
 • ለኦባማ ነዋ፡፡
 • ወይ ይኼ ኦባማ?
 • ለአንተም በሰማይ ቤትም፣ በእኛም ዘንድ ያፀድቅሃል፡፡
 • መፅደቅማ ማን ይጠላል ብለው ነው?
 • አንተ አሁን ልብስ ትነግዳለህ አይደል?
 • አዎን፡፡
 • በቃ አንድ አሥር ኮንቴይነር ልብስ ለለማኞቹ ለግስ፡፡
 • ከየት አምጥቼ?
 • ከቻይና ነዋ፡፡
 • ለኦባማ ግን ከቻይና ትቀበላላችሁ?
 • አሜሪካዊ ነው ብለህ ነው? እነሱም እዛው አይደል እንዴ የሚያሠሩት?
 • ክቡር ሚኒስትር ለእኛ እናንተ ስትኖሩ ነው ጥቅማችን፣ ስለዚህ ያሉኝን ሁሉ አደርጋለሁ፡፡
 • በል ይህን የከተማ ለማኝ ሁላ በአዲስ ልብስ አሳምርልኝ፡፡
 • በሉ እርስዎም የታክሱን ጉዳይ ያሳምሩልኝ፡፡

[ክቡር ሚኒስትሩ አማካሪያቸውን አስጠሩት] 

 • አቤት ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ሌላ ምን መሠራት አለበት ትላለህ?
 • ለመሆኑ እስካሁን ምን ተሠራ?
 • ችግኝ ተተክሏል፣ ከተማ ፀድቷል፣ ለማኝ ተለውጧል፣ ሌላ ምን ቀረ?
 • ለመሆኑ የሚጐበኛቸው ቦታዎች ይታወቃሉ እንዴ?
 • ለምን ጠየቅከኝ?
 • ያረጁና አሮጌ ቤቶች በሚበዙባቸው ሠፈሮች እንዳያልፉ ብዬ ነው፡፡
 • እስኪ መንገድ ዳር ያሉ አሮጌ ሠፈሮችን አጣርተህ አምጣልኝ፡፡
 • እሺ ክቡር ሚኒስትር፡፡

[አማካሪያቸው በክቡር ሚኒስትሩ ጥያቄ መሠረት ጥናት አድርጐ ውጤቱን ነገራቸው፡፡ አሮጌ ቤቶች የሚበዙበት ሠፈር የክፍለ ከተማ ኃላፊ ጋ ደውሉ] 

 • አቤት ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እነዚህ አሮጌ ቤቶች ለምን አይፈርሱም?
 • ደሃው የት ይሂድ ክቡር ሚኒስትር?
 • አገራችን እያደገች ስለየትኛው ደሃ ነው የምታወራው?
 • ዕድገቱ እኮ ለደሃው እየደረሰ አይደለም፡፡
 • ሀብት እኮ እንደ ውኃ ነው፡፡
 • እንዴት?
 • ከላይ ወደ ታች ነው የሚፈሰው፡፡
 • እኮ ታች አልደርስ አለ፡፡
 • አንድ ቀን ይደርሳል፡፡
 • እንዲህ እያልን ሕዝቡ እንዳይደርስብን፡፡
 • ለማንኛውም አሁን ቤቶቹ ፈርሰው በግንብ ይሠሩ፡፡
 • ያው በመልሶ መልማቱ ሁሉም በግንብ መሠራታቸው አይቀርም፡፡
 • እኔ እያልኩ ያለሁት መንገድ ዳር ያሉት ቤቶች ፈርሰው በግንብ ይሠሩ፡፡
 • ከኋላ ያሉት ለእኛም ሥሩልን ቢሉንስ?
 • እነሱ ወጥቶላቸው ነው በሏቸው፡፡
 • ምን?
 • ዕጣ፡፡
 • ለመሆኑ ለምንድነው በግንብ የሚሠሩት?
 • ለኦባማ፡፡
 • ሰውዬው እዚህ የሚመጣው ሊኖር ነው እንዴ?
 • ያልተጠየቅከውን አታውራ፡፡

[ክቡር ሚኒስትሩ አማካሪያቸውን አስጠሩት] 

 • ይኸው አንተ ቁጭ ብለህ እኔ የአንተን ሥራ እሠራለሁ፡፡
 • ምን ሠሩ ክቡር ሚኒስትር?
 • ከተማዋን ቀያየርኳት፡፡
 • እኮ ለምን?
 • ለኦባማ ነዋ፡፡
 • ምነው ለሕዝቡ እንዲህ ቢቀያይሩለት?
 • ለሕዝቡም በ2025 ይቀየርለታል፡፡
 • እንዴት ሆኖ?
 • ሒሳብ አትችልም እንዴ?
 • እኮ እንዴት?
 • ለኦባማ በሦስት ቀን እንደዚህ ከቀየርነው፣ ለ90 ሚሊዮን ሕዝብ በ2025 እናደርሳለን፡፡
 • እንዲህ ዓይነት ሒሳብ ሰምቼ ባላውቅም፣ ግን ይሁንልዎት፡፡
 • አሁን ሌላ ምን ይቀረናል?
 • የሰብዓዊ መብት ጉዳዩን ምን እናድርገው?
 • ደግሞ የምን የሰብዓዊ መብት ጉዳይ ነው?
 • ያሰርናቸው ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞችስ?
 • ይፈቱ፡፡
 • ምን?
 • አሁኑኑ ይፈቱ፡፡
 • ለምን?
 • ለኦባማ ነዋ፡፡
 • ወይ ኦባማ?
 • ለኦባማ አይደለም ጋዜጠኛና ፖለቲከኛ አንበሶቹም ይፈታሉ፡፡
 • ምኖቹ?
 • አንበሶቹ፡፡
 • የትኞቹ?
 • የስድስት ኪሎዎቹ፡፡
 • እኔ ደግሞ ሌሎቹ አንበሶች መስለውኝ ነበር፡፡
 • ስለዚህ በአፋጣኝ ይፈቱ፡፡
 • መልሰው ግን ይታሰሩ እንዳይሉኝ፡፡
 • ለምን?
 • ኦባማ ሲሄድ ነዋ፡፡
 • ድሮስ?
 • ለመሆኑ ለስንት ጊዜ ነው የሚመጣው?
 • ለአንድ ቀን ነዋ፡፡
 • እዚህ ትንሽ ቢቆይ ግን ጥሩ ነው፡፡
 • ለምን?
 • አገሪቱ በአጭር ጊዜ ትቀየር ነበር፡፡
 • እ…
 • ከጂቲፒ 2 እንዲያውም እሱ እዚህ ቢቆይ ፈጣን ለውጥ ሳይመጣ አይቀርም፡፡
 • ወሬኛ ቢጤ ነህ፡፡

[ክቡር ሚኒስትሩ ከቢሮ ሲወጡ ጸሐፊያቸው ጠረጴዛ ላይ ወረቀቶች ተበታትነው አዩ] 

 • ምንድነው አንቺ?
 • ወረቀት ነዋ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • በአፋጣኝ ይፅዳ፡፡
 • አፀዳዋለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ጊዜ የለም፣ መምጫው ደርሷል፡፡
 • የማን?
 • የኦባማ፡፡

[ክቡር ሚኒስትሩ መኪናቸው ጋ ሲደርሱ ከሾፌራቸው ጋር ማውራት ጀመሩ] 

 • መኪናው እኮ ቆሽሿል፡፡
 • ኧረ ጠዋት ነው ያጠብኩት ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ጐማው እኮ ጭቃ ነው?
 • ክረምት መሆኑን ረሱት እንዴ? መንገዱ ሁሉ ጭቃ ነው እኮ?
 • ከአሁን በኋላ ጐማው በየአምስት ደቂቃው ይታጠብ፡፡
 • እየሄድን ቢሆንም?
 • አቁመህ ማጠብ አለብህ፡፡
 • ለምን ክቡር ሚኒስትር?
 • ኦባማ ሊመጣ ነዋ፡፡
 • የውጭ አልጋ የውስጥ ቀጋ አሉ፡፡

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንገድ እየሄዱ አቧራ የለበሱ ልጆች አዩና ሾፌሩ እንዲያቆም ነገሩት] 

 • እናንተ ልጆች ምን ሆናችኋል?
 • ምን ሆንን?
 • እንዲህ ነጫጭባ የሆናችሁት፡፡
 • የደሃ ልጆች ነና፡፡
 • በሉ ቤተሰቦቻችሁ ሰሞኑን ይህን ክሬም እንዲቀቧችሁ አስጠንቅቋቸው፡፡

[ከኪሳቸው ክሬም አውጥተው ሰጧቸው]

 • ለምን?
 • ኦባማ ይመጣላ፡፡

[የክቡር ሚኒስትሩ ሾፌር ተናዶ ጥያቄ ይጠይቃቸው ጀመር] 

 • ሰሞኑን ምነው ፅዳት ላይ አተኮሩ?
 • እሱ ፅዳት ይወዳላ፡፡
 • ማን?
 • ኦባማ፡፡
 • ጉድ ፈላ በሉኝ፡፡
 • ለምን?
 • አንድ የጨቀየ ነገር አለና፡፡
 • ምኑ?
 • ፖለቲካው!