ክቡር ሚኒስትር

[ክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊያቸውን ጠሯት]

 

 • ማስታወቂያው ወጣ?
 • የምን ማስታወቂያ ክቡር ሚኒስትር?
 • የሥራው ማስታወቂያ ነዋ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ሰው ሊቀጠር?
 • በሚገባ ነዋ፡፡
 • ተጨማሪ ሰው እኮ አያስፈልገንም፡፡
 • ሚኒስትርም ሆነሽልኛላ?
 • እንደሱ ማለቴ አይደለም፡፡
 • ያልገባሽ ነገር ስላለ ነው፡፡
 • ምንድነው?
 • በሁለተኛው ጂቲፒ ከፍተኛ ሥራ እንደሚጠብቀን ታውቂያለሽ?
 • እሱንማ ሁሌም ትላላችሁ፡፡
 • ስለዚህ ይህ ሥራ ለጂቲፒው መሳካት እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡
 • እኔ’ኮ በርካታ ሥራ የፈቱ ሰዎች እዚህ አሉ ብዬ ነው፡፡
 • አንደኛው የጂቲፒው ዓላማ እኮ ሕዝቡ የሥራ ዕድል እንዲያገኝ ማድረግ ነው፡፡
 • ዓላማውን ቀየራችሁት እንዴ?
 • ምን ማለት ፈልገሽ ነው?
 • በጂቲፒው እኮ ሥራ ፈጣሪ እንጂ ተቀጣሪ ብዙም አይበረታታም፡፡
 • እንዳትሳሳቺ ቀጣሪና ተቀጣሪ ባላንስ ማድረግ አለባቸው፡፡
 • እንዴት ማለት?
 • ሁሉም ሥራ ፈጣሪ ከሆነ ተቀጣሪ ይጠፋላ፡፡
 • ለዚህ ነው ጥቂት መሪና ብዙ ተመሪ ያለው?
 • ታዲያ ሁሉም መሪ ይሁንልሽ?
 • ግን አንድ ዓይነት መሪ ብቻ ከሚኖር ለአማራጭ ሌሎች መሪዎችም ቢኖሩ ጥሩ ነው፡፡
 • ምን ማለት ፈልገሽ ነው?
 • ማለቴ የተለያዩ የሥራ ፈጣሪዎች ካሉ ለተቀጣሪዎችም የተለያዩ የሥራ ዕድሎች ይከፈታሉ፡፡
 • እሱ ላይ እኮ ነው እየሠራን ያለነው፡፡
 • ፖለቲካው ላይማ ከኢሕአዴግ ውጪ ምን አለ?
 • አጋር ፓርቲዎቹስ?
 • አያስቁኝ እስቲ ክቡር ሚኒስትር?
 • ምንድነው የሚያስቅሽ?
 • እኔ ተቃዋሚ የለም ለማለት ፈልጌ ነው፡፡
 • ታዲያ ሁሉም ከደገፈን ምን እናድርግ?
 • ኧረ ሰው እንዳይታዘብዎት?
 • ታዛቢ መጥራት ካቆምን እኮ ቆየን፡፡
 • አሁን ለሁለተኛው ጂቲፒ ያስፈልጋል ያሉት ሥራ ምንድነው?
 • በመጀመሪያ የምነግርሽን ጻፊ፡፡
 • እሺ፡፡
 • ይህ የሥራ ቦታ ሁለተኛውን ጂቲፒ በመሥሪያ ቤታችን ለማስፈጸም ወሳኝ ነው፡፡
 • እሺ፡፡
 • ለሥራ ቦታው የሚመጥነው የትምህርት ደረጃ አራተኛ ክፍል ነው፡፡
 • እ…
 • ያው እንደነገርኩሽ አንዱ የሁለተኛው ጂቲፒ ዓላማ ለሕዝቡ የሥራ ዕድል መፍጠር ነው፡፡
 • እሺ ስንት ሰው ነው የሚያስፈልገው?
 • አንድ፡፡
 • እንዴ ለሕዝቡ የሥራ ዕድል እንፈጥራለን አላሉኝም እንዴ?
 • አንድ ሰው ራሱ የሕዝቡ አካል መሆኑን አትርሺ፡፡
 • መቼ ነው መቀጠር ያለበት?
 • በአስቸኳይና በአፋጣኝ አልኩሽ፡፡ ሌላው…
 • ሌላው ምን?
 • የዚህን የቅጥር ሒደት እኔ ነኝ የምመራው፡፡
 • ለምን ክቡር ሚኒስትር? እርስዎ እኮ ትልቅ ኃላፊነት ያለበዎት ሚኒስትር ነዎት፡፡
 • ከዚህ በላይ ትልቅ ኃላፊነት የለም፡፡
 • አልገባኝም? ስንት የመልካም አስተዳደርና የሙስና ችግሮች እርስዎን እየጠበቅዎት፣ እዚህ የቅጥር ሒደት ውስጥ መግባት ያስፈልግዎታል?
 • በሥራ ቅጥር ሒደታችን ውስጥ በርካታ የመልካም አስተዳደርና የሙስና ችግሮች እንዳሉብን ስንተች ቆይተናል፡፡
 • ለነገሩ እርስዎ የማያውቁት ቅጥር እኮ ተፈጽሞ አያውቅም፡፡
 • ለዚህ ነው፤ አሁን ደግሞ በደንብ መሳተፍ እፈልጋለሁ፡፡
 • ለመሆኑ የሥራው ዓይነት ምንድነው?
 • ካርኒ ቆጣሪ፡፡

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ የሥራ ቅጥሩን ማስታወቂያ በጋዜጣ ማስወጣቷን ነገረቻቸው፡፡ እሳቸውም አንድ ዘመዳቸው ጋ ደወሉ]

 • ሰላም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንዴት ነህ አቶ ዋጣቸው?
 • አለሁ፤ ዛሬ ከየት ተገኙ?
 • ባለፈው ከገጠር የመጣችው ዘመዳችን አንተው ጋ ናት?
 • አዎን እኔው ጋ ነው ያለችው፡፡
 • ምን ያህል ጊዜ ሆናት ከመጣች?
 • አንድ ወር ሊሞላት ነው፡፡
 • ሥራ ጀመረች እንዴ?
 • ምን ትጀምራለች? በዚያ ላይ ትምህርት ራሱ የላትም፡፡
 • እንዴ በዚህ ኑሮ ውድነት ሰውን ለወር ያለሥራ መቀለብ እኮ ከባድ ነው፡፡
 • በጣም እንጂ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • በል እኔ ጋ ላካት፤ አንድ ሥራ አለ፡፡
 • ኧረ ክቡር ሚኒስትር እርስዎ ጋ ለመሥራት እኮ ቢያንስ ትንሽ ትምህርት ያስፈልጋታል፡፡
 • እሱን ለእኔ ተወው፡፡
 • ለነገሩ እርሶ ምን ይሳንዎታል?
 • ፈላጭም ቆራጭም እኔው ነኝ፡፡
 • ተፈላጭና ተቆራጭ ብቻ ነው የሚያስፈልግዎት፡፡

[የክቡር ሚኒስትሩ ዘመድ የላኩዋት ልጅ ቢሯቸው መጣች]

 • ሰላም ጋሼ እንዴት ነዎት?
 • እዚህ ስሜ ጋሼ አይደለም ክቡር ሚኒስትር ነው፡፡
 • እሺ ክቡር ሚኒስትር ጋሼ፡፡
 • በይ ተይው፡፡
 • ምን አሉኝ ክቡር ሚኒስትር ጋሼ?
 • ሥራ ላስቀጥርሽ ነው፡፡
 • የት ጋሽዬ?
 • እዚህ እኔ ጋ፡፡
 • አይ ጋሽዬ ከእሜቴ ጋር እስማማለሁ ብለው ነው?
 • የለም የለም፤ እዚህ እኛ መሥሪያ ቤት ነው፡፡
 • ኧረገኝ እኔ የቢሮ ሥራ ልሠራ ጋሼ?
 • ቁጥር ትችያለሽ አይደል?
 • ያው እስከ ሁለት ተምሬያለሁ፤ አያቅተኝም፡፡
 • በቃ እዚህ ካርኒ ቆጣሪ ሆነሽ ትቀጠሪያለሽ፡፡
 • አመሰግናለሁ ክቡር ሚኒስትር ጋሼ፡፡
 • ለመጀመሪያው በሁለት ሺሕ የወር ደመወዝ ትጀምሪያለሽ፡፡
 • መቼ ይሆን ውለታውን የምከፍለው ክቡር ሚኒስትር ጋሼ?
 • እናትሽ አደራ ብላኝ ነው የሞተችው፡፡
 • እሷም ከሰማይ ውለታውን ትመልስልዎታለች፡፡
 • አይ እሷ ያለችበት ቦታ እኔ እሄዳለሁ ብለሽ ነው?
 • ከዚያማ ማን ይቀራል ብለው ነው?
 • አይ እሷ መልካም ሰው ስለሆነች፣ እሷ ያለችበት ቦታ እኔ አልሄድም ብዬ ነው፡፡
 • ከዚህ በላይ መልካምነት የት አለ ብለው ነው ክቡር ሚኒስትር ጋሼ?
 • እንደ አፍሽ ያድርግልኝ፤ ለማንኛውም ሲቪሽን አዘጋጂ፡፡
 • እሱ ደግሞ ምንድነው?
 • የሥራ ማኅደርሽ ውስጥ የሚቀመጥ ዶክመንት ነው፡፡ ስለ አንቺ የሚገልጽ ማለት ነው፡፡
 • አይ ጋሽዬ ከዚህ በላይ ለእርስዎ ምን ብዬ እገልጽልዎታለሁ?
 • በይ እሺ ተይው ለአቶ ዋጣቸው እነግረዋለሁ፤ እሱ ያዘጋጅልሻል፡፡

[ክቡር ሚኒስትሩ የሰው ኃይል አስተዳደር ኃላፊውን ጠሩት] 

 • አንድ አዲስ ሰው ልንቀጥር መሆኑን ሰምተሃል?
 • አዎን ክቡር ሚኒስትር፣ የሥራ ማስታወቂያ እኮ ወጥቷል፡፡
 • የሚቀጠረውን ሰው እኔ አመጣልሃለሁ፡፡
 • እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
 • የምን እንዴ ነው?
 • የሥራ ማስታወቂያ አውጥተን እኮ በርካቶች ሲቪያቸውን እያስገቡ ነው፡፡
 • የእነሱን ሲቪ ለሌላ ጊዜ እንጠቀመዋለን፡፡
 • ታዲያ ለምን ማስታወቂያውን አወጣን?
 • ይህ አዲስ ነገር ሆኖ ነው? ለፎርማሊቲ ነዋ፡፡
 • የኢሕአዴግ ችግር ይኼ ነው እየተባለ ነው፡፡
 • እንዴት?
 • ሰሞኑን የፕሮቪደንት ፈንድን አስመልክቶ አንድ ረቂቅ አዋጅ ወጥቶ ነበር፡፡
 • አውቃለሁ፡፡
 • ያው ረቂቁ በሕዝብ ዘንድ ጫጫታ ስላስነሳ የሕዝብ ውይይት ተደርጐ ነበር፡፡
 • እሱንም ሰምቻለሁ፡፡
 • በውይይቱ ወቅት በርካታ ቅሬታዎች የተነሱ ሲሆን፣ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ያልተደረገበት ረቂቅ መሆኑ ተገልጾ ነበር፡፡
 • ለዚያ እኮ ነው ውይይቱ የተደረገው?
 • ውይይቱ መደረጉ መልካም ቢሆንም፣ በወቅቱ ባለድርሻ አካላቶች ረቂቁ ባለበት እንዳይፀድቅ የተለያዩ ግብዓቶችን እንዲካተቱ ሐሳብ ተሰጥቶ ነበር፡፡
 • እና አልተካተቱም?
 • ይኸው እነዚያ ግብዓቶች ሳይካተቱ ረቂቁ ፀደቀ፡፡
 • ማነው ለመሆኑ ይህን የነገረህ?
 • ባለቤቴ ናት፡፡
 • የት ነው የምትሠራው?
 • አንድ የግል ድርጅት ነው፡፡
 • ኦ ኪራይ ሰብሳቢዎቹ ጋ፡፡
 • ኧረ እነሱ ኪራይ ሰብሳቢዎች አይደሉም፡፡
 • ኪራይ ሰብሳቢዎች ስለሆኑማ ነው እንዲህ የሚንጫጩት፡፡
 • ይህ ኪራይ መሰብሰብ ከሆነ አሁን እኛም እኮ ኪራይ ሰብሳቢዎች ነን ማለት ነው?
 • ማን አንተ? እኛ?
 • እህሳ?
 • እኛ ኪራይ ሰብሳቢዎች ሳንሆን ጡረታ ሰብሳቢዎች ነን፡፡
 • እነሱም እኮ ፕሮቪደንት ሰብሳቢዎች ነበሩ?
 • አንተ ራስህ ኪራይ ሰብሳቢ ነህ ልበል?
 • እርስዎ ደግሞ ዘመድ ሰብሳቢ ነዎት ልበል?

[ክቡር ሚኒስትሩ አማካሪያቸውን ጠሩት]

 • የጂቲፒ ስብሰባው እንዴት እየሄደ ነው?
 • ኧረ ሕዝቡ አልመጣም እያለ ነው፡፡
 • ለምን?
 • ተሰብስበን ለውጥ ላናመጣ ለምን ወንበር እናሞቃለን? እያሉ ነው፡፡
 • የምትመጡት ወንበር ለማሞቅ ሳይሆን ለመሳተፍ ነው አትሏቸውም?
 • እንደዚያ ብንላቸውም አሻፈረኝ እያሉ ነው፡፡
 • እኮ ለምን?
 • ሐሳባችንን ሰምታችሁን አታውቁም፣ ስለዚህ አንመጣም ብለዋል፡፡
 • ታዲያ ሐሳባቸውን ለምን አንሰማቸውም?
 • መስማትማ እንሰማቸዋለን ግን ሁሌም አናካትተውም፡፡
 • ይካተታ ታዲያ?
 • የኪራይ ሰብሳቢ ሐሳብ ነው ስለሚባል ነዋ፡፡
 • ሕዝቡ ታዲያ ኪራይ ከሰበሰበ እኛ ምን እናድርገው?
 • ለዚህ ነው ሕዝቡ አንመጣም የሚለው፡፡
 • ለምን አበል አይሰጥም?
 • እሱንም ሞክረናል፡፡
 • እና ምን አሉ?
 • ከዚህ በኋላ ህሊናችንን በገንዘብ አንሸጥም አሉ፡፡
 • ታዲያ በነፃ ይሽጡልና?
 • በኋላ አካሄዳችን ግን ችግር እንዳያስከትልብን እንጠንቀቅ፡፡
 • የምን ችግር?
 • ሕዝቡ እኛን ማዳመጥ እንዳያቆም፡፡
 • ለምንድን ነው የሚያቆመው?
 • የማያዳምጥ መንግሥት አይደመጥም ሲባል አልሰሙም፡፡
 • ይህ የኪራይ ሰብሳቢዎች ወሬ ነው፡፡
 • ብቻ ያስቡበት፡፡

[ክቡር ሚኒስትሩ ምሳቸውን ለመብላት ቤት ሄዱ፡፡ ከሚስታቸው ጋር እየበሉ ነው]

 • እንዴት ነበር ቀንህ?
 • ዛሬ ብዙ ሥራ ነው የሠራሁት፡፡
 • ምን ሠርተህ ነው?
 • ያቺን ዘመዴን እኛ ጋ ላስቀጥራት ነው፡፡
 • ይቺን ሙስና አሁንም አልተውካትም፡፡
 • ይህ ሙስና ሳይሆን ሁለቱ ‹‹መ››ዎች ናቸው፡፡
 • ሁለቱ ‹‹መ››ዎች ምንድን ናቸው?
 • መረዳዳትና መደጋገፍ፡፡
 • ሦስተኛውን ‹‹መ›› የት ረስተኸው ነው?
 • ምንድን ነው ሦስተኛው ‹‹መ››?
 • መዝረፍ፡፡
 • ምነው አፍ ለቀቀብሽ?
 • ለመሆኑ ርቦሃል እንዴ?
 • ለምን ጠየቅሽኝ?
 • የቀረበልህን ጥርግ አርገህ በላሃው ብዬ ነው፡፡
 • ርቦኝ ሳይሆን ባህላችን ነው፡፡
 • ምንድን ነው ባህላችሁ?
 • ጠራርጐ መብላት!