ክቡር ሚኒስትር

[ክቡር ሚኒስትሩ አማካሪያቸው በአስቸኳይ እንዲመጣ ነገሩት]

 

 • ፈለጉኝ ክቡር ሚኒስትር?
 • በሚገባ መዘጋጀት አለብን፡፡
 • የምን ዝግጅት ነው?
 • ለውይይቱ ነዋ፡፡
 • የትኛው ውይይት ክቡር ሚኒስትር?
 • የጂቲፒ 2 ውይይት ነዋ፡፡
 • እሱ ላይማ ከፍተኛ ዝግጅት ማድረግ አለብን፡፡
 • አዎና፣ የመጀመሪያው ምዕራፍ ተጠናቋል፤ ወደ ሁለተኛውም እየተሸጋገርን ነው፡፡
 • እንግዲህ የመጀመሪያው ምዕራፍ ለሁለተኛው ዋነኛ ግብዓት ይሆናል፡፡
 • ለመሆኑ ከእነማን ጋር ነው ውይይት የምናካሂደው?
 • ከወጣቶች ጋር፡፡
 • እነሱማ የእኛው ናቸው፡፡
 • ከሴቶች ጋር፡፡
 • እነሱም የእኛ ደጋፊዎች ናቸው፡፡
 • ከምሁራን ጋር፡፡
 • እነሱን ፍራ፡፡
 • ከግሉ ዘርፍ ጋር፡፡
 • እነሱም ሌላ የራስ ምታት ናቸው፡፡
 • ለምን ግን ክቡር ሚኒስትር?
 • ምሁራንና የግሉ ዘርፍ ቻሌንጅ ሊያደርጉን ይችላሉ፡፡
 • እኮ ለምን?
 • በመጀመሪያው ጂቲፒ ላይ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ እምብዛም ነበር፡፡
 • እሱማ ጥፋታችን ነው፡፡
 • ስለዚህ አሳማኝ ሐሳብ ይዘን መቅረብ አለብን፡፡
 • የምን አሳማኝ ሐሳብ?
 • ለምን በመጀመሪያው ጂቲፒ ትኩረት እንዳልሰጠናቸው ነዋ፡፡
 • ለእሱማ ይቅርታ መጠየቅ እንጂ አሳማኝ ሐሳብ ማቅረብ አይጠቅመንም፡፡
 • እሷ ነገር እኮ ናት ደስ የማትለኝ፡፡
 • የቷ ነገር?
 • ይቅርታ የሚሏት፡፡
 • እንዲያውም እኛ በዚህ እንጀምረው ብለን ነው እንጂ ያደለው ጋማ ቁንጥጫ አለ፡፡
 • የምን ቁንጥጫ?
 • ክቡር ሚኒስትር አንድ ጥያቄ ልጠይቅዎት፡፡
 • እሺ ቀጥል፡፡
 • አንድ ዜጋ የኤሌክትሪክ ሒሳቡን ካልከፈለ ምን ይደረጋል?
 • ኤሌክትሪክ ይቋረጥበታል በዚያ ላይ ቅጣት ይጣልበታል፡፡
 • መንግሥት ኤሌክትሪክ ሲያቋርጥስ ምን ይደረጋል?
 • ምንም፤ ደግሞ ምን እንዲደረግ ፈለግክ?
 • ይኼን ነው የምልዎት፡፡
 • እኮ ምንድነው የምትለኝ?
 • ሕዝቡ የኤሌክትሪክ ሒሳቡን ካልከፈለ፣ ይቋረጥበታል ደግሞም ይቀጣል፡፡
 • ያ መንግሥትን ኪሳራ ላይ ስለሚጥለው እኮ ነው፡፡
 • መንግሥት ግን ኤሌክትሪክ በማቋረጡ ሕዝቡ ላይ ለሚደርሰው ኪሳራ አይጠየቅም፡፡
 • እ…
 • ስለዚህ ቁንጥጫ ያልኩዎት ይኼንን ነው፡፡
 • እና መንግሥትም መቆንጠጥ አለበት፡፡
 • መንግሥት ሲያጠፋ መቆንጠጥ መጀመር አለበት፤ ባህልም ሊሆን ይገባል፡፡
 • ጥሩ ነጥብ ነው ያነሳኸው፡፡
 • ለምሳሌ ባለፈው የፈጠርነውን ትርምስ ያስታውሳሉ?
 • የምን ትርምስ?
 • ፕሮቪደንት ፈንድን አስመልክተን ባወጣነው ረቂቅ የተፈጠረው ትርምስ ነዋ፡፡
 • ረቂቁን ያወጣነው እኮ ለሕዝቡ አስበን ነው፡፡
 • ምን አሉኝ?
 • ረቂቁን ያወጣነው ለሕዝቡ አስበን ነው፡፡
 • እንዴት ሆኖ?
 • ሁሉም የግል ድርጅት ሠራተኞች በጡረታ ቢታቀፉ ያዋጣቸዋል፡፡
 • እንዴ ለምን?
 • ጡረታ ዘለቄታዊ ማኅበራዊ ዋስትና ይሰጣል፡፡
 • ፕሮቪደንትስ?
 • እሱ ክፍተቶች አሉበት፡፡
 • ክፍተቶቹን ማስተካከል ያለብን እኛው ነና፡፡
 • ለመሆኑ አንተ የትኛው ይሻላል ትላለህ?
 • እኔማ ከጡረታ ውጪ ምን አማራጭ አለኝ?
 • እኮ ምረጥ ብትባል የትኛውን ትመርጣለህ?
 • ፕሮቪደንትን ነዋ፡፡
 • ምን?
 • ፕሮቪደንትን ነው የምመርጠው፡፡
 • ኪራይ ሰብሳቢ ነህ ልበል፡፡
 • ኪራይ ሰብሳቢ ሆኜ አይደለም፡፡
 • ታዲያ ምን ሆነህ ነው?
 • በእርግጥ እንደሚሻል ስለማውቅ ነው፡፡
 • እኮ እንዴት?
 • ባለፈው ብቸኛ የሆነውን ወንድሜን ማሳከሚያ አጥቼ ሕይወቱ በማለፉ እስካሁን ከውስጤ አልወጣም፡፡
 • ይህ ከፕሮቪደንት ጋር ምን አገናኘው?
 • ፕሮቪደንት ፈንድ ቢኖረኝማ ወንድሜን አሳክሜ ሕይወቱን ባተረፍኩት ነበር፡፡
 • ታክሞም እኮ ላይተርፍ ይችል ነበር?
 • ቢያንስ ለእኔ የህሊና ቁስል አይሆንም፡፡
 • እሱስ ልክ ነህ፡፡
 • ከዚያ ውጪ የ40/60 ዕጣ ቢወጣልኝ ከየት እንደማመጣ እግዚአብሔር ነው የሚያውቀው፡፡
 • ቤት የለህም እንዴ?
 • ያው የመንግሥት ቤት ውስጥ ነው የምኖረው፡፡
 • እሱ አይበቃህም ታዲያ?
 • ቤቱ የሚኖረው መንግሥትን እስካገለገልኩ ድረስ ነው፡፡ ይህን ሥራዬን ከለቀኩ ቤተሰቤ ያለመጠለያ መቅረቱ ነው፡፡
 • ልክ ብለሃል፡፡
 • ለዚህ ነው ፕሮቪደንት ይሻላል የምለው፡፡
 • ታዲያ ረቂቁ ልክ አይደለም እያልከኝ ነው?
 • ረቂቁ መውጣት ካለበት ከጡረታ ሁሉም ወደ ፕሮቪደንት ይዙር ብለን ነው፡፡
 • እኛንም ጨምሮ?
 • ሠራተኛው ከመረጠው ምን ችግር አለው?
 • መንግሥት ገንዘብ አይኖረውማ፡፡
 • ቅድሚያ ሊታሰብ የሚገባው ለሕዝብ ነው፡፡
 • እሱስ ልክ ብለሃል፡፡

[የክቡር ሚኒስትሩ ጓደኛ ሚኒስትር ደወሉላቸው] 

 • ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንዴት ነህ ወዳጄ?
 • የጂቲፒ 2 ስብሰባ እንዴት ይዝዎታል?
 • ያው ሁሉን ዝግጅት ጨርሰናል፡፡
 • እኔም አስፈላጊውን ዝግጅት አድርጌያለሁ፡፡ ለማንኛውም ዛሬ የደወልኩት ለሌላ ጉዳይ ነው፡፡
 • የምን ጉዳይ?
 • በቀጣይ አገራችን ትልቅ ዓለም አቀፋዊ ስብሰባ ታስተናግዳለች፡፡ በዚያ ላይ ኦባማ ወደ ኢትዮጵያ ይመጣል፡፡
 • ታዲያ ስንት መሪዎች ተቀብለናል አይደል እንዴ? ምን አዲስ ነገር አለው?
 • አይደለም ክቡር ሚኒስትር፣ ይህ አገራችንን ለማስተዋወቅ ወሳኝ አጋጣሚ ነው፡፡
 • ያው እንግዲህ እኔ የፕሬዚዳንቱን የአቀባበል ጉዳይ በተመለከተ የተዋቀረው ኮሚቴ ውስጥ ስላለሁ በሚገባ እከታተለዋለሁ፡፡
 • እኔም ኮሚቴው በአግባቡ ሥራውን እየሠራ አለመሆኑን ሰምቼ ነው የደወልኩት፡፡  
 • አታስብ እኔ አላሳፍርህም፡፡
 • ለማንኛውም አዳዲስ ሱፎችን መግዛት እንዳይረሱ፡፡
 • ምን እኔ የፕሮቪደንት ፈንድ የለኝ፤ ከየት አመጣለሁ ብለህ ነው?
 • ፕሮቪደንት ፈንድ እኮ ለወሳኝ ነገር እንጂ ለእንደዚህ ዓይነት ነገር መውጣት አይችልም፡፡
 • ያው እኛም ቢኖረን ጥሩ ነው ለማለት ነው፡፡
 • ምን?
 • ፕሮቪደንት ፈንድ፡፡

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሾፌራቸው ጋር ወደ ቤታቸው እየሄዱ ነው] 

 • ቀልድ ነው የተያዘው ክቡር ሚኒስትር?
 • የምን ቀልድ አመጣህ?
 • ባለፈው ቅዳሜ ጂቲፒ 2 ላይ ለመወያየት ቀበሌ ጠርተውኝ ሄጄ ነበር፡፡
 • እሺ፡፡
 • የመጀመሪያው ጂቲፒ አፈጻጸም ሪፖርት ተደረገ፡፡
 • ከዚያስ?
 • ከዚያማ ስለጂቲፒ 2 ተነቦልን ስብሰባው አለቀ፡፡
 • በቃ?
 • አዎና እኔ እኮ ጂቲፒ 2 ገና እየታቀደ በመሆኑ ለእሱ ግብዓት የሚሆን ነገር ለመስጠት ነው እንጂ የሄድኩት አልሄድም ነበር፡፡
 • ምን የምትሄድበት ቦታ አለ ደግሞ?
 • ኧረ ስንት ቦታ አለ፡፡ ሌላ ደግሞ፡፡
 • ደግሞ ሌላ ምን አለህ?
 • ኦባማ ሊመጣ ነው አሉ፡፡
 • አሁን ገና መስማትህ ነው?
 • እሱማ ቆየሁ፤ ለመሆኑ ምን ሊያደርግ ነው የሚመጣው?
 • ያው ልማታችንን ሊያደንቅና ሊያበረታታ ነዋ፡፡
 • አሜሪካ የግብረ ሰዶማውያንን መብት በሁሉም ስቴቶቿ ማፅደቋን ሰምተዋል አይደል?
 • ያፅድቁዋ፤ እኛ ምን አገባን? ያ የውስጥ ጉዳያቸው ነው፡፡
 • አይ የኦባማ ጉብኝት ሌላም ዓላማ አለው እየተባለ ነው፡፡
 • የምን ሌላ ዓላማ?
 • በአገራችን ያሉ ግብረ ሰዶማውያን መብት እንዲጠበቅ አድቮኬት ለማድረግ ነው ይባላል፡፡
 • እኔ በቁሜ እያለሁ?
 • መቼም ኦባማ ሲመጣ ይሞታሉ ብዬ አልገምትም፡፡
 • ኢትዮጵያ እኮ የእምነት አገር ናት፡፡
 • አሁን ክቡር ሚኒስትር እውነት እናውራ ከተባለ የእርስዎ ሃይማኖት አብዮታዊ ዲሞክራሲ አይደለም?
 • አብዮት ይብላህ፡፡
 • ለማንኛውም የድብቅ ዓላማውን ጉዳይ ነገር አደራ፡፡
 • ይህ በፍጹም ሊሆን አይችልም፡፡

[ክቡር ሚኒስትሩ ቤት ሲገቡ ሚስታቸውን አገኟቸው]

 • ሰሞኑን ትልቅ ስብሰባ እንዳለብኝ ታውቂያለሽ?
 • የምን ትልቅ ስብሰባ?
 • በርካታ መሪዎች ወደ አገራችን ይመጣሉ፡፡
 • ምን ሊያደርጉ?
 • ኦባማን ጨምሮ ሌሎች ታላላቅ መሪዎች በቅርቡ አገራችንን ይጐበኛሉ፡፡
 • ኦባማ ለምንድነው የሚመጣው?
 • የአገራችንን ዕድገት ሊያደንቅ ነዋ፡፡
 • ለመሆኑ ተቃዋሚዎቹስ ምን ይላሉ?
 • አሁን ኢንተርኔት ላይ አላነበብኩም ለማለት ፈልገሽ ነው?
 • ምን ዌብሳይቱን ሁሉ ዘግታችሁት የት አነባለሁ ብለህ ነው?
 • ምንም ቢሉ ኦባማ መምጣቱ አይቀርም፡፡
 • ግን የምር ምን ይላሉ?
 • ሁለት አይደለም ገና ሦስት ዓይነት ፀጉር ያበቅላሉ፡፡
 • ምን ዓይነት ፀጉር?
 • ነጭና ጥቁር…
 • ሌላስ?
 • ሰማያዊ!