ክቡር ሚኒስትር

[የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ ሊያነጋግራቸው ቢሯቸው ገባ]

 

 • ሰላም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንዴት ነህ?
 • አንድ ዲፕሎማት ሊያገኝዎት ይፈልጋል፡፡
 • እኔ አንድ ዲፕሎማ ካለው ሰው ጋር ልገናኝ?
 • አይደለም ዲፕሎማት እኮ ነው ያልኩዎት፡፡
 • እእእ …
 • እና አንዳንድ ነገር ላይ ሊያነጋግርዎት ይፈልጋል፡፡
 • የምን አንዳንድ ነገር ነው?
 • ያው ስለምርጫ ጉዳይ ነዋ፡፡
 • ታዲያ ምን አንዳንድ ነገር ትላለህ? ስለምርጫ ነው አትልም?
 • አዎ ስለምርጫ ነው፡፡
 • እኮ ስለምርጫ ምን ሊያወራኝ ነው?
 • ምርጫው እኮ ብዙ ነገሮች አሉት፡፡
 • እኔ ስለምን እንደሚያወራኝ አውቀዋለሁ፡፡
 • ስለምን ሊያወራዎት ነው?
 • ያው እንታዘብ ሊሉ ነዋ፡፡
 • ምኑን ነው የሚታዘቡት?
 • ምርጫውን ነዋ፡፡
 • ታዲያ ይታዘቡዋ፡፡
 • ኢሕአዴግ ሐሜት አይወድም፡፡
 • እንዴት?
 • ታዛቢ ሁሌም ሐሜተኛ ነው፡፡
 • ምን አሉኝ?
 • በተለይ ምዕራባዊያን ታዛቢዎች ሁሌም ሐሜት ነው የሚያወሩት፡፡
 • ምን ተሻለ ታዲያ?
 • እኛ አፍሪካዊያኑና የራሳችን ታዛቢዎች ይበቁናል፡፡
 • ለሐሜት ግን እነዚህ አይብሱም ብለው ነው?
 • ያው አፍሪካዊያኑ የእኛ አገር ምርጫ እጅግ ዴሞክራሲያዊ ስለሆነ ሊያሙን አይችሉም፡፡
 • የአገር ውስጥ ታዛቢዎቹስ?
 • እነሱን ደግሞ እኛ ስለምንታዘባቸው ችግር የለውም፡፡
 • እ… ገባኝ፡፡
 • ምን ገባህ?
 • የገባኝ ገባኝ፡፡
 • ወሬኛ፡፡
 • ለማንኛውም ከዲፕሎማቱ ጋር ነገ የምሳ ቀጠሮ ይዤልዎታለሁ፡፡
 • አሁን ስለእኛ ምርጫ እነሱ ምን አገባቸው?
 • እንዲህማ ማለት አንችልም፡፡
 • ለምን አንችልም?
 • የእነሱ አገር በርካታ ዜጐች እዚች አገር ላይ ኢንቨስት አድርገዋል፡፡
 • ቢያደርጉስ ታዲያ?
 • ያው አገሪቷ ሰላም መሆኗን ማረጋገጥ ይፈልጋሉ፡፡
 • የእርጐ ዝንብ ናቸው፡፡
 • የእርጐ ንብ ነው ያሉኝ?
 • ንብ ሳይሆን ዝንብ ነው ያልኩት፡፡
 • ለምን አሉ?
 • በሰው ጉዳይ ጥልቅ ይላሉ፡፡
 • ለነገሩ ዝንብ እንጂ ንብ ጥልቅ አትልም፡፡
 • እሱን እኮ ነው የምልህ፡፡
 • ንብ ትናደፋለች እንጂ አትጠልቅም፡፡
 • ምን አልከኝ?
 • ንብ ማር ነው የምታመርተው፡፡
 • ልክ ብለሃል፡፡
 • ለማንኛውም የነገ ቀጠሮውን እንዳይረሱት፡፡
 • እሺ አልረሳውም፡፡

[ክቡር ሚኒስትሩ በጠዋቱ ዘንጠው ከቤት ሊወጡ ሲሉ ባለቤታቸው ወሬ ጀመሩዋቸው]

 • ምንድን ነው ዛሬ?
 • ረቡዕ ነዋ፡፡
 • ማለቴ እንዲህ የዘነጥከው ለምንድን ነው?
 • የአገሪቷ የ11 ፐርሰንት ዕድገት መገለጫ ነው፡፡
 • ዝነጣው ለዚያ ነው?
 • ቀጠሮም አለኝ፡፡
 • ከማን ጋር?
 • ከአንድ ዲፕሎማት ጋር፡፡
 • በምን ጉዳይ?
 • ያው በምርጫው ላይ ነዋ፡፡
 • ታዲያ ምን ልትለው ነው?
 • እሱ የሚፈልገውን ሳይሆን እኔ የምፈልገውን እነግረዋለሁ፡፡
 • ምነው አገርህ የምትፈልገውን ነገር ብትነግረው?
 • እኔ የምፈልገው እኮ አገሬ የምትፈልገው ነው፡፡
 • የኢትዮጵያ የሕዝብ ቁጥር ከ90 ሚሊዮን በላይ መስሎኝ?
 • እኔ ታዲያ ስንት ነው አልኩ?
 • አንድ፡፡
 • እንዴት?
 • ይኸው እኔ የምፈልገው ማለት አገሬ የምትፈልገው ነው አላልክም?
 • ያው የግለሰብ መብት ሲጠበቅ እኮ ነው የአገር መብት የሚጠበቀው?
 • ወሬውንማ ትችልበታለህ፡፡
 • ወሬውን ብቻ ሳይሆን ሥራውንም እችልበታለሁ፡፡
 • ሠርተህ አሳየና?
 • እመኚኝ፡፡
 • ማየት ማመን ነው፡፡
 • ማመን ነው ማየት እባክሽ?
 • ብቻ አሳየን?

[ክቡር ሚኒስትሩ የምሳ ሰዓት ሲደርስ ከሹፌራቸው ጋር ወደ ቀጠሮ ቦታ መሄድ ጀመሩ]

 • ወዴት ልሂድ ክቡር ሚኒስትር?
 • የባለፈው ቦታ፡፡
 • የባለፈው ቦታ የቱ ቦታ?
 • ባለፈው ምሳ የበላሁበት፡፡
 • እዚያ ውዱ ቦታ?
 • አዎ፡፡
 • ኧረ ክቡር ሚኒስትር ትንሽ እንኳን ለሞራሌ ያስቡልኝ?
 • እንዴት?
 • የሦስት ወር ደመወዜን ለአንድ ምሳ ሊከፍሉት ነው እኮ?
 • ምን ላድርግ ብለህ ነው?
 • ኧረ ክቡር ሚኒስትር ባይሆን መንገዱን ያሳዩኝ?
 • የምኑን መንገድ?
 • የሚታደግበትን መንገድ፡፡
 • ማደግህ አይቀርም፡፡
 • እንዴት እንደሚታደግ እኮ ግራ ነው የገባኝ?
 • ትምህርት እየተማርክ ነው?
 • ሕይወት ብዙ እያስተማረችኝ ነው፡፡
 • ያን ሥልጠና እየወሰድክ ነው?
 • የቱን ሥልጠና?
 • አብዮታዊ ዴሞክራሲ፡፡
 • እኔ እሱ ትምህርት አልገባህ አለኝ፡፡
 • ታዲያ ምንድን ነው የሚገባህ?
 • አረቄያዊ ዴሞክራሲ፡፡
 • ምን?
 • አርቆ አሳቢ ዴሞክራሲ፡፡
 • ደግሞ እሱን የት ነው የምትማረው?
 • ያው ማታ ማታ መሸታ ቤት ነዋ፡፡
 • በማታ ከመማር በቀን መማር አይሻልህም?
 • የቀኑ ቀርቶብኝ የማታው በገባኝ፡፡ 

[ክቡር ሚኒስትሩ ከዲፕሎማቱ ጋር ተገናኙ]

 • እንዴት ነዎት ክቡር ሚኒስትር?
 • እንዴት ነህ?
 • ምርጫው እንዴት እየሄደ ነው?
 • ያው ጊዜው እየደረሰ ነው፡፡
 • በጣም ቢዚ እንደሆኑ አውቃለሁ፡፡
 • የእናንተ ምርጫ ሲያልቅ የእኛ ደግሞ ሊጀምር ነው?
 • እኛም እኮ ዕረፍት የለንም፡፡
 • እንዴት?
 • ማሸነፋችንን ባወቅን በነገታው ነው ለቀጣዩ ምርጫ መሥራት የምንጀምረው፡፡
 • እኛም እኮ ለዚህ ምርጫ አምስት ዓመት ነው የሠራነው፡፡
 • ታዲያ ምርጫውን እንዴት ያዩታል?
 • ያው በዓይኔ ነዋ፡፡
 • ማለቴ ምን ይመስላል?
 • እንደምናሸንፍ ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ነኝ፡፡
 • የባለፈው ይደገማል እያሉኝ ነው?
 • አሁን ለመድፈን ነው የምንሄደው፡፡
 • ተቃዋሚዎቹስ?
 • ቋሚ እንጂ ምን ተቃዋሚ አለ?
 • እና ተፎካካሪ የለንም እያሉኝ ነው?
 • ፎካሪ እንጂ ተፎካካሪ የለም፡፡
 • ተፎካካሪ ከሌለ እኮ ምርጫው ተዓማኒነት ሊኖረው አይችልም፡፡
 • ታዲያ እኛ ተፎካካሪ አንፈጥር?
 • አቅማቸውን አጠናክሩላቸው፡፡
 • እነሱ እኮ አቅም አይደለም ያነሳቸው፡፡
 • ምንድን ነው ያነሳቸው?
 • አቅል ነው ያነሳቸው፡፡
 • ለምን ሁሉም ተሰባስበው አንድ ጠንካራ ተፎካካሪ ፓርቲ እንዲፈጥሩ አታደርጓቸውም?
 • ተልከህ ነው እንዴ የመጣኸው?
 • እኔ እንዲሁ ምክር መለገሴ ነው፡፡
 • ይኼ ምክር ነው መከራ?
 • እሱ እንዳመለካከትዎት ነው፡፡

[ክቡር ሚኒስትሩ ቢሯቸው ሲገቡ እየጠበቋቸው የነበሩትን ሚኒስትር አገኙ]

 • ሰላም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንዴት ነህ እባክህ?
 • ምርጫ እንዴት ነው?
 • ሁሉም ነገር ቦታ ቦታውን ይዟል፡፡
 • ተቃዋሚዎቹስ?
 • ኪራይ ሰብሳቢዎቹስ ማለትህ ነው?
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • ይኸው እኛ ለምርጫ ከመደብነው በላይ በጀት እየያዙ?
 • እ…
 • ኪራይ ካልሰበሰቡ ከየት ሊያመጡት ይችላሉ?
 • ዕቁብ ሰብስበው ቢሆንስ?
 • ቁብ የማይሰጣቸው ሰዎች ከየት ዕቁብ ይሰበስባሉ ብለህ ነው?
 • ለነገሩ እውነትዎትን ነው፡፡
 • ኪራይ ሰብሳቢዎች ናቸው፡፡
 • እኔ እኮ ኪራይ ሰብሳቢ ነጋዴ ብቻ ይመስለኝ ነበር፡፡
 • ኪራይ ሰብሳቢ ተቃዋሚም አለ፡፡
 • ምርጫው አያስፈራንማ?
 • ምርጫ እኮ የረጅም ርቀት የፖለቲካ ሩጫ ነው፡፡
 • እሱማ ግልጽ ነው፡፡
 • ተቃዋሚዎች ደግሞ የአጭር ርቀት የፖለቲካ ሯጮች ናቸው፡፡
 • እንዴት?
 • ዝግጅት የሚጀምሩት ምርጫው ወራት ሲቀሩት ነዋ፡፡
 • እኛም እኮ ከእነሱ እኩል ነው ዝግጅት የምንጀምረው፡፡
 • ቢሆንም ብዙ ልምድ አለን፡፡
 • ስለዚህ አያሰጋንማ?
 • ምን ነካህ? ቦልትን ከኃይሌ ጋር 10 ሺሕ ሜትር ሩጥ ብትለው ማን ያሸንፋል?
 • ኃይሌ ነዋ፡፡
 • በቃ እነሱ ቦልት እኛ ኃይሌ ነን፡፡
 • ያው ሩጫው ላይ ግን መንገድ መዝጋት የለብንም፡፡
 • መንገድ መዝጋት እኮ በሕግ ያስጠይቃል፡፡
 • ጠያቂውም ተጠያቂውም አንድ ከሆነ ግን ጥያቄ አለ ማለት አይቻልም፡፡
 • ለማንኛውም እኛ በሩጫ አንታማም፡፡
 • በምን ዓይነት ሩጫ?
 • በአጭሩም፣ በመካከለኛውም፣ በረጅሙም፡፡
 • በአጭሩ ግን እንታማለን፡፡
 • በየትኛው አጭር?
 • በቅብብሎሹ፡፡
 • የቅብብሎሽማ ችግር የለብንም፡፡
 • ማቀበል አቅቷችኋል እየተባልን ነው እኮ?
 • ያቃተን እኮ ጠፍቶ ነው፡፡
 • ምን?
 • ተቀባይ!