ክቡር ሚኒስትር

[ክቡር ሚኒስትሩ አማካሪያቸው አርፍዶ ቢሮ ሲገባ አገኙት] -አንተ? -አቤት ክቡር ሚኒስትር፡፡ -ሰዓቱን አይተኸዋል፡፡ -አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡ -ታዲያ አሁን ነው ሥራ መግቢያ ሰዓት? -ምን ላድርግ ተቸግሬ ነው? -የምን ችግር ነው? -የትራንስፖርት ነዋ፡፡ -ሕፃን ልጅ አደረከኝ እንዴ? -ኧረ ክቡር ሚኒስትር እርስዎ ሕንፃ አለዎት እንጂ ሕፃን እ ንኳን አይደሉም፡፡ -ምን አልክ አንተ? -ኧረ እርስዎ በፍጹም ሕፃን አይደሉም፡፡ -ይኸው አንተ ግን እንደ ሕፃን ልጅ ልታታልለኝ ሞከርክ፡፡ -ምን አድርጌ? -የትራንስፖርት ችግር አለብኝ ብለህ ነዋ፡፡ -ታዲያ እውነቴን እኮ ነው፡፡ -ቀጣፊ ደግሞ እውነቴን ነው ስትል ትንሽ አታፍርም፡፡ -እንደ እናንተ የሆንኩ መስሎዎት ነው አይደል ክቡር ሚኒስትር? -እንዴት ማለት? -ያው እናንተ እየዋሻችሁም አታፍሩማ፡፡ -እኔ ጠፋሁ? -ተሳሳትኩ ክቡር ሚኒስትር? -ጭራሽ ውሸትህ አልበቃህ ብሎ ስድብ ጨመርክበት፡፡ -ክቡር ሚኒስትር እየተሳደብኩ ሳይሆን እውነቱን እያወራሁ ነው፡፡ -ለመሆኑ ከእውነታ ጋር ትተዋወቃላችሁ? -ሰው ሁሉ እንደ እርስዎ ይመስሎዎታል አይደል? -ያልተጠየከውን አታውራ፡፡ -ለጠየቁኝማ ምላሽ ሰጠሁ፡፡ -እኮ የምን የትራንስፖርት ችግር ነው የምታወራው? -ክቡር ሚኒስትር ከተማው ውስጥ አይደል እንዴ የሚኖሩት? -እሱንማ አንተ ታውቀዋለህ፡፡ -ለነገሩ ከተማው ውስጥ ቢኖሩም መቼ የከተማውን ችግር ያውቁታል? -የምን ችግር ነው የምታወራው? -ብዙ ችግር አለ፤ አንዱና ዋነኛው ደግሞ የትራንስፖርት ነው፡፡ -እኔም ውሸታም ያልኩህ እኮ የትራንስፖርት ችግር አለ ስትለኝ ነው፡፡ -እንዴት? -የትራንስፖርት ችግርማ ተቀረፈ፡፡ -በምን? -በባቡሩ ነዋ፡፡ -አያስቁኝ እስቲ፡፡ -እንዴት? -በምን ቤት አንድ ጣት ብርቅ ናት አሉ፡፡ -አሽሙርህን ተወው፤ የትራንስፖርት ችግሩ ግን ተቀርፏል፡፡ -አንድ ነገር ልንገርዎት ክቡር ሚኒስትር? -ምን? -በእርግጥ ይህ የባቡር ፕሮጀክት የሚደነቅ ነው፡፡ ግን… -የምን ግን ነው? -የትራንስፖርት ችግሩ ገና አልተቀረፈም፡፡ -እኮ እንዴት ሆኖ? -የተጠቃሚው ቁጥርና የባቡሩ ቁጥር የሚጣጣም አይደለም፡፡ -እንዴት ማለት? -ባቡሩ ቢኖርም ተጠቃሚው ከፍተኛ ስለሆነ ሠልፍ አለ፡፡ -የምን ሠልፍ? -ባቡሩ ውስጥ ለመግባት ነዋ፡፡ -እና አሁንም ሠልፍ አለ እያልከኝ ነው? -አዎና፡፡ -ይኼ ሕዝብ ግን ሠልፍ ይወዳል ልበል? -ወዶ አይደለም፡፡ -ምን ወዶ አይደለም ትለኛለህ? ሕዝቡማ ሠልፍ ይወዳል፡፡ -ለዚያ ነው የከለከላችሁት? -ምን? -ሰላማዊ ሠልፍ! [የክቡር ሚኒስትሩ ጓደኛ ሚኒስትር ስልክ ደወሉ] -ሄሎ ክቡር ሚኒስትር! -ሰላም ወዳጄ፡፡ -ምን እየተደረገ ነው ክቡር ሚኒስትር? -ምን ተደረገ? -መፈንጫ እኮ ሆነ፡፡ -ምኑ? -ይኼ የፋይናንስ ሴክተር፡፡ -እኔ እኮ ተናግሬ ነበር፡፡ -ምን ብለው? -ሴክተሩን ለኪራይ ሰብሳቢዎች መልቀቅ የለብንም ብዬ፡፡ -እርስዎ እኮ ክቡር ሚኒስትር፣ ሚኒስትር ብቻ አይደሉም፡፡ -ታዲያ ምንድን ነኝ? -ነብይም ነዎት፡፡ -ልክ ብለሃል፡፡ -ስለዚህ ምን ተሻለ? -በአፋጣኝ ዕርምጃ መውሰድ አለብን፡፡ -ምን ዓይነት ዕርምጃ? -ፖሊሲ መረቀቅ አለበት፡፡ -የምን ፖሊሲ? -የፋይናንስ ሴክተሩን በጥብቅ የሚቆጣጠር ነዋ፡፡ -ክቡር ሚኒስትር ከፖሊሲ በላይ ግን የሚያስፈልገን ነገር አለ፡፡ -ምን? -የማስፈጸም ብቃት፡፡ -እሱማ ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው፡፡ -ከፍተኛ አደራ ነው የተሸከምነው፡፡ -ስለዚህ በሸክማችን ላይ ሸክም የሆኑ ኪራይ ሰብሳቢዎችን ማራገፍ አለብን፡፡ -እኮ እንዴት? -መጀመር ያለብን ከራሳችን ነው፡፡ -ምኑን? -ማራገፉን፡፡ -ሁላችንም ተራገፍን በሉኝ፡፡ -መጀመሪያ ከፍተኛ ክብደት ያላቸውን ማራገፍ፡፡ -እኮ እሱ ነው ችግሩ? -ምኑ ነው ችግሩ? -እነሱ በቀላሉ አይራገፉም? -ለምን? -ኔትወርካቸው ውስብስብ ነው፡፡ -ውስብስቡን ኔትወርክ መበጣጠስ ነዋ፡፡ -ቢቻልማ ደስ ይለኛል፡፡ -አይቻልም የሚባል ነገር የለም፡፡ -እንዴት ክቡር ሚኒስትር? -የኢትዮጵያን ዕድገት እስቲ ተመልከት፡፡ -እንዴት ማለት? -ብዙዎች ይህ ዕድገት ዕውን ይሆናል ብለው አያምኑም ነበር፡፡ -እርሱስ ልክ ነዎት፡፡ -ከአንጀት ካለቀሱ እንባ አይገድም አይደል የሚባለው? -እና ሁላችንም ልናለቅስ? -የሚያለቅሰው ያለቅሳል፤ የሚስቀውም ይስቃል፡፡ [አንድ ኢንቨስተር ክቡር ሚኒስትሩ ቢሮ ገባ] -እንዴት ዋሉ ክቡር ሚኒስትር? -እንዴት ዋልክ? -ቢዚ እንደሆኑ አውቃለሁ ግን ተቸግሬ ነው፡፡ -ምን ልርዳህ? -ክቡር ሚኒስትር እርስዎ ጋ የመጣሁት ጨንቆኝ ነው፡፡ -እኮ ምንድን ነው የሚያስጨንቅህ? -ይኼ የውጭ ምንዛሪ ጉዳይ ነዋ፡፡ -ይኸው ዕርምጃ መውሰድ ጀምረናል፡፡ -አውቃለሁ ግን ችግሩ ዘርፈ ብዙ ነው፡፡ -የምን ችግር ነው? -ይኸው እኔ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት አልቻልኩም፡፡ -ለምን? -መክፈል አልቻልኩም፡፡ -ምንድን ነው መክፈል ያልቻልከው? -ጉርሻውን ነዋ፡፡ -የምን ጉርሻ? -የዶላር ጉርሻውን፡፡ -አልገባኝም አብራራልኝ፡፡ -ክቡር ሚኒስትር ለአንድ ዶላር ሦስት ብር መክፈል አለብኝ፡፡ -ለምን ሲባል? -ዶላሩን ለማግኘት ነዋ፡፡ -ካልከፈልክስ? -ዶላሩ አይታሰብም፡፡ -ትቀልዳልህ? -እኔም አንዳንዴ ቀልድ ቢሆን ደስ ይለኝ ነበር፡፡ -ወይ ጉድ፡፡ -ግን የምር ነው? -አገሪቷ የኪራይ ሰብሳቢ ሆናለቻ፡፡ -እኔም ይኼ አሳስቦኝ ነው የመጣሁት፡፡ -ምኑ? ኪራይ ሰብሳቢነቱ? -አዎ ክቡር ሚኒስትር በሚቀጥለው ሳምንት ሊጀመር ነው አይደል? -ምኑ? -ፓርላማው፡፡ -አዎን፡፡ -ብዙ ኃላፊነት አለባችሁ፡፡ -አውቃለሁ፡፡ -ሙሉ ፓርላማው የእናንተ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ -እ… -ስለዚህ ቅንና ቆራጥ አመራሮች ከሌሉን አለቀልን፡፡ -እንዴት ማለት? -አንድ የሰማሁትን ነገር ላጫውትዎት፡፡ -እሺ፡፡ -የኬንያ ኤርዌይስን ያውቁታል? -በሚገባ፡፡ -ከጥቂት ዓመታት በፊት ከእኛም አየር መንገድ የተሻለ ነበር፡፡ -አውቃለሁ፡፡ -አሁን ግን በአፍ ጢሙ እያሽቆለቆለ ነው፡፡ -ምን ይደረጋል? -ለምን እንደሆነ ያውቃሉ? -አላውቅም፡፡ -መንስዔው ሙስና ነው፡፡ -እንዴት? -አየር መንገዱ እየከሰረ ያለው ሆን ተብሎ ነው፡፡ -ለምን? -የኬንያ ባለሥልጣናት ከባለሀብቶች ጋር ተመሳጥረው አየር መንገዱ ከከሰረ በኋላ ባለሀብቶቹ እንዲገዙት ለማድረግ ነዋ፡፡ -ይኼማ ግፍ ነው፡፡ -ሙስና ግፍ አያውቅም፡፡ -እውነት ነው፡፡ -ስለዚህ እኛም ጋ እያቆጠቆጠ ያለው ሙስና ከአሁኑ ሃይ ካልተባለ መዘዙ የከፋ ነው፡፡ -ልክ ብለሃል፡፡ -ስለዚህ ሳይቃጠል በቅጠል ነው፡፡ -ሙሰኛማ ቅጠል ሳይሆን ቅጣት ነው የሚያስፈልገው፡፡ [ክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊያቸው ጋ ሄዱ] -ጨረሽልኝ? -ምኑን? -ሪፖርቱን፤ ለስብሰባው እፈልገዋለሁ እኮ? -አሁን እጨርሰዋለሁ፡፡ -እስካሁን ምን እያደረግሽ ነው? -ኢንተርኔት ላይ እያየሁ፡፡ -ምንድን ነው የምታይው? -አይድል ሾው፡፡ -አይድል እንዳትሆኚ መስሎኝ ይኼን ሥራ የሰጠሁሽ፡፡ -ሁሉም ሰው የሚከታተለው ሾው ነው እኮ? -የምን ሾው ነው ያልሽኝ? -ባላገሩ ሾው፡፡ -የከተማ ልጅ ትመስሊኝ ነበር እኮ? -ክቡር ሚኒስትር አልገባዎትም፣ የዘፋኞች ውድድር የሚካሄድበት ሾው ነው፡፡ -ዘፋኝም ልትሆኚ አስበሽልኛል? -አይ ክቡር ሚኒስትር፣ የአሸነፈውን ዘፋኝ በጣም ስለምወደው ነው፡፡ -ማን ነው ያሸነፈው? -ዳዊት ፅጌ፡፡ -ማን ፅጌ? የአሸባሪዎች ውድድር ነው እንዴ ያልሽኝ? -አይደለም አይደለም ክቡር ሚኒስትር፣ ዳዊት ፅጌ ነው ያልኩት፡፡ -ለመሆኑ እንዴት አሸነፈ? -ሕዝብ መርጦት ነዋ፡፡ -ከኢሕአዴግ ሌላ ሕዝብ የመረጠው አለ? -ይኼ እኮ የሙዚቃ ውድድር ነው፡፡ -አሁን አሸናፊው ምን ይሆናል? -ንጉሥ ነዋ፡፡ -እኛ የዘውድ አገዛዙ አገሪቷን ወደኋላ አስቀርቷታል እያልን፣ እናንተ በጐን ንጉሥ ልታነግሡ? -የሙዚቃ ንጉሥ ነው ያልኩት፡፡ -ለመሆኑ ሕዝብ በነቂስ ወጥቶ ነው የመረጠው? -በጣም በርካታ ሕዝብ ነው የመረጠው፡፡ -የምርጫ ኮሮጆዎቹስ የታሸጉ ነበሩ? -በሞባይል ቴክስት ነው የሚመረጠው፡፡ -የአመራርጥ ሒደቱ ከእኛ ይለያላ? -በዚህ ብቻ ሳይሆን በሌላም ይለያል፡፡ -በምን? -ምርጫው ፍትሐዊና ነፃ ነበር!