ክቡር ሚኒስትር

[ክቡር ሚኒስትሩ ከአማካሪያቸው ጋር ቢሯቸው እያወሩ ነው]

 • ሪፖርቱን አዘጋጀህልኝ?
 • የትኛውን ሪፖርት ክቡር ሚኒስትር?
 • አጠቃላይ ሪፖርቱን ነዋ?
 • አዎን ግን ማጠቃለያው ይቀረዋል፡፡
 • በል በአፋጣኝ ይጠቃለል፡፡
 • ምነው? ምን ተፈጠረ?
 • አንድ ጉዞ ስላለኝ ከዚያ በፊት ማየት ፈልጌ ነው፡፡
 • እኔ የማላውቀው የምን ጉዞ ነው?
 • አይ ለግል ጉዳይ ነው፡፡
 • ክፍለ ሀገር ወጥተው ዘመድ ሊጠይቁ ነው እንዴ?
 • የለም ከአገር ውጭ ነው የምሄደው፡፡
 • ምነው አመመዎት እንዴ?
 • ኧረ በፍጹም ለግል ጉዳዬ ነው የምሄደው፡፡
 • በዚህ ወቅት?
 • ምን ማለት ነው በዚህ ወቅት?
 • ብዙ ሥራ ያለበት የምርጫ ወቅት ነው ብዬ ነዋ፡፡
 • ያልተጠየከውን አትዘባርቅ፡፡

[በመሀል ጸሐፊያቸው ደወለች] 

 • ያዘዝኩሽን አስፈጸምሽ?
 • የትኛውን ክቡር ሚኒስትር?
 • የትኬቱን ጉዳይ ነዋ፡፡
 • እኔም ለእሱ ነው የደወልኩት፡፡
 • እሺ ምን አደረግሽው?
 • ሁሉም አየር መንገዶች ደወልኩኝ፡፡
 • ሴትዮ ፍሬ ነገሩን ብቻ ንገሪኝ፡፡
 • እኮ ልነግርዎት ነው፡፡
 • ቀጥዪ፡፡
 • ቢዝነስ ክላስ ቦታ የላቸውም፡፡
 • ምን ማለት ነው?
 • ቢዝነስ ክላሳቸው በሙሉ ተይዟል፡፡
 • እና?
 • ትኬቱን በኢኮኖሚ ክላስ ልቁረጠው ወይ?
 • ምን አልሽ?
 • ምን ይሻላል ታዲያ ክቡር ሚኒስትር?
 • ሚኒስትር እኮ ነኝ፡፡
 • አውቃለሁ ግን…
 • ለዚያውም የተከበርኩ፣ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር በጣም ጨንቆኝ ነው የደወልኩልዎት፡፡
 • ተጨነቂ ሳይሆን ትኬት ቁረጪ ነው ያልኩሽ፡፡
 • አሁን እንደገባኝ ትኬት ከመቁረጥ ተስፋ መቁረጥ ቀላል ነው፡፡
 • ምን አልሽ?
 • ቀኑን መቀየር ይችላሉ?
 • አንቺን ማን አማካሪ አደረገሽ? የተነገረሽን አስፈጽሚ ነው የተባልሽው፡፡
 • ምን ተሻለኝ?
 • የጉዞ አበሌንስ ምን አደረግሽ?
 • ለግል ጉዳይዎት መስሎኝ የሚሄዱት?
 • ቢሆንስ?
 • ማለት መሥሪያ ቤቱ እንዴት አበል ይከፍልዎታል?
 • እኔ የምልሽ?
 • አቤት?
 • ኩምታ አስበሻል እንዴ?
 • የምን ኩምታ?
 • እኔ ሳላውቅ የእኔን ቦታ ወስደሻል ማለቴ ነው፡፡
 • እንደሱ አይደለም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ዝም በይ!
 • እ…
 • ለሚመለከተው መሥሪያ ቤት ነግረሽ በአፋጣኝ አበሌን አስጨርሺ፡፡
 • እሺ፡፡
 • ያሉኝ አማካሪዎች ራሳቸው ጤና ነስተውኛልና አንቺ ራስሽን ምከሪ፡፡
 • ይቅርታ፡፡

[ከአማካሪያቸው ጋር ማውራት ቀጠሉ] 

 • ወይ ጣጣ፡፡
 • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
 • የሚነገራትን አትሰማም፡፡
 • እ…
 • ለማንኛውም አንተ ዶላር ፈልግ፡፡
 • የምን ዶላር?
 • ለጉዞ የሚያስፈልገኝን ነዋ፡፡
 • ዶላር እኮ የለም እየተባለ ነው፡፡
 • እኔ እኮ አለቃህ ነኝ፡፡
 • አውቃለሁ፡፡
 • የለም ለእኔ መልስ አይሆንም፡፡
 • ከየት ላምጣ ታዲያ?
 • መፈንቀል ያለብህን ጉድጓድ ሁሉ ፈንቅል፡፡
 • እሱንማ አደርጋለሁ ግን ከጠፋ ብዬ ነው፡፡
 • ብቻ አንተ ፈንቅል፡፡
 • እሺ፡፡

[ክቡር ሚኒስትሩ ሚስታቸው ጋ ደወሉ] 

 • ጨራረስክ?
 • ኧረ ሊጨርሱኝ ነው፡፡
 • እነማ?
 • ሁሉም፡፡
 • ዶላር ተገኘ?
 • ምን ይገኛል?
 • ምን ማለት ነው?
 • ግራ ገብቶኛል እባክሽ፡፡
 • ቀረህ እንዴ?
 • እንዴት እቀራለሁ?
 • ያለዶላር ሄደህ ምን ልታደርግ ነው ታዲያ?
 • እየፈለግኩኝ ነው፡፡
 • የቀረህ እኮ ጥቂት ቀን ነው፡፡
 • አውቃለሁ ግን ምን ላድርግ?
 • ወዳጆችህ ጋ ደውላ፡፡
 • እ…
 • ለዚህ ያልደረሱልህ ለመቼ ሊደርሱልህ ነው?
 • እስቲ አንቺም ደዋውይ፡፡
 • እኔማ እየሞከርኩ ነው፡፡
 • እስቲ ይቅናሽ፡፡
 • በል ቻው፡፡

[ክቡር ሚኒስትሩ አንድ የባንክ ፕሬዚዳንት ዘንድ ደወሉ] 

 • ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንዴት ነህ ወዳጄ?
 • ሥራ እንዴት ይዞአችኋል?
 • ተያይዘነዋል፣ እናንተስ እንዴት ናችሁ?
 • ይኸው ወጥረን ይዘናል፡፡
 • ያለፈው ስጦታችሁ ደርሶናል፡፡
 • የትኛው ስጦታ ክቡር ሚኒስትር?
 • ለ40ኛ ዓመት በዓላችን የላካችሁት፡፡
 • ኧረ ከዚህም በላይ ብናደርግ ደስ ይለናል፡፡
 • አንድ ላይ ነው ተያይዘን ማደግ ያለብን፡፡
 • እኛም ከእናንተ ጋር በመሥራታችን ደስተኞች ነን፡፡
 • ገና ብዙ ሥራ እንሠራለን፡፡
 • ምን ልታዘዝ ታዲያ ዛሬ?
 • ዶላር ፈለጌ ነው፡፡
 • ምን ችግር አለው ታዲያ? በቃ በቢሮ ደብዳቤ ጻፉልን፡፡
 • አሁኑኑ እንዲጻፍልህ አደርጋለሁ፡፡
 • ያው አንድ ሦስት ወር ግን መጠበቅ አለባችሁ፡፡
 • ምን?
 • ወረፋ አለ፤ ቢያንስ ሦስት ወር መጠበቅ አለባችሁ፡፡
 • ኧረ እኔ በሦስት ቀን ውስጥ ነው የምፈልገው፡፡
 • ሦስት ቀን ነው ያሉኝ?
 • አዎን ሦስት ቀን፡፡
 • አይ ክቡር ሚኒስትር፣ ቢሆን ደስ ይለኝ ነበር ግን…
 • ግን ምን?
 • በሦስት ወር ከደረስዎት ራሱ ጥሩ ነው፡፡
 • ወይ ጣጣ፡፡

[ክቡር ሚኒስትሩ ለምሳ ወጡ፤ በመንገድ ላይ ከሾፌራቸው ጋር እያወሩ ነው] 

 • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ምንድነው ምነው ማለት?
 • ፊትዎ ላይ ሐዘን ይታያል፡፡
 • ምን የሚያስደስት ነገር አለ ብለህ ነው?
 • እንዴ ግድቡ፣ ባቡሩ፣ ኧረ ስንቱ?
 • እ…
 • ምን የሌለ ነገር አለ?
 • ዶላር ነዋ!
 • ዶላር?
 • አዎን ዶላር፡፡
 • እኔ ገንዘብ አጥቼም ደስተኛ ነኝ፣ እርስዎ ዶላር የለም ብለው አዝነዋል?
 • አሽሙርህን እስቲ እዚያው፡፡
 • ምን አሽሙር ነው፣ ይኼማ እውነታው ነው፡፡
 • ዶላሩን እኮ ለሥራ ነው የምፈልገው?
 • እናቱ የሞተችበትና ገበያ የሄደችበት እኩል ያለቅሳሉ አሉ፡፡
 • ምን ማለት ነው?
 • እኔ እኮ ገንዘቡን የምፈልገው ለመኖር ነው፡፡
 • በገንዘብ አይኖርም አላልኩህም?
 • አይ እንዲያው ነገሩን ማለቴ ነው፡፡
 • ነገረኛ ሆነሃል ልበል?
 • ይቅርታ ክቡር ሚኒስትር፡፡

[ክቡር ሚኒስትሩ ምሳ የሚበሉበት ሆቴል አንድ ኤክስፖርተር ወዳጃቸውን አገኙ] 

 • ስፈልግዎት ነው ያገኘሁዎት ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ሥራ እንዴት ነው እባክህ?
 • በጣም ጥሩ ነው፣ እናንተስ ጋ እንዴት ነው?
 • ምን እባክህ?
 • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
 • እኛው ባወጣነው ሕግ እኛው እንቸገራለን፡፡
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • ዶላር አጥቼ ተቸግሬያለሁ፡፡
 • የምን ዶላር ክቡር ሚኒስትር?
 • ለሥራ ፈልጌ ነው፡፡
 • ምን ችግር አለው ታዲያ?
 • ባንክም የለም ብለውኝ ነዋ፡፡
 • እነሱ መቼ ሥራቸውን ይሠራሉ ብለው ነው?
 • እ…
 • ምንም አያስቡ፡፡
 • እኔንማ በጣም አሳስቦኛል፡፡
 • ለማንኛውም ምን ያህል ነው የፈለጉት?

[ክቡር ሚኒስትሩ ጠጋ ብለው በጆሮው ነገሩት] 

 • ምንም ችግር የለውም እኔ እሰጥዎታለሁ፡፡
 • ምን አልከኝ?
 • ቢሮዬ ሻንጣ ይዘው ይምጡ፡፡
 • እሱ ግን ችግር አለው፡፡
 • የምን ችግር?
 • እንዴት አወጣዋለሁ ብለህ ነው?
 • ስለእሱ አያስቡ፡፡
 • እንዴት?
 • እኔ በስልክ እጨርሰዋለሁ፡፡
 • አንተ ብቻ ተወልደህ ሌላው ቢቀር ይሻል ነበር፡፡

[ክቡር ሚኒስትሩ ሚስታቸው ጋ ደወሉ] 

 • ምነው ሳቅ በሳቅ ሆንክ? አገኘህ እንዴ?
 • እኔ እኮ የሰው መውደድ እንዳለኝ ታውቂያለሽ?
 • የፈለግነው ዶላር ተገኘ?
 • ድሮስ?
 • እኔም ወደድኩህ አሁን፡፡
 • እስከ ዛሬ አትወጂኝም ነበር?
 • ስማ ለማንኛውም የዓመት በዓል መዋያ የሚሆን ብር ያስፈልገኛል፡፡
 • ምን ያህል?
 • ሃምሳ ሺሕ ብር፡፡
 • ይህ ሁላ ብር ምን ያደርግልሻል?
 • ይኼን ቤት ማስተዳደር እንዲህ ቀላል መስሎሃል?
 • አካውንታንት ይቀጠርልሽ?
 • አድርገኸው ነው?
 • በይ አንድ ልጅ አለ እሱን አመጣልሻለሁ፡፡
 • በቃ በኋላ፡፡

[ክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊያቸው ጋ ደወሉ] 

 • ያዘዝኩሽን ጨረስሽ?
 • በእሱ ላይ ተወጥሬ ነው ያለሁት፡፡
 • አሁን ብር እፈልጋለሁ፡፡
 • የምን ብር?
 • የዓመት በዓል መዋያ፡፡
 • ምን አሉኝ?
 • ለበዓል መዋያ፡፡
 • ከቢሮ ነው?
 • አዎና፣ የመስተንግዶ ብለሽ አስፈቅጂ፡፡
 • ለቤትዎ ወጪ እንዴት መሥሪያ ቤቱ ይከፍላል?
 • አንቺና እኔ ግን እንዴት ነው የተናናቅነው?
 • ትንሽ ግን አልበዛም ክቡር ሚኒስትር?
 • አንቺ ሥራሽ ማስፈጸም ብቻ ነው፡፡
 • በቃ እሺ በባንክ ልላክልዎታ?
 • በየትኛው ቅርንጫፍ?
 • በአባ ኮራን፡፡
 • ምን አልሽኝ?
 • በአባ ኮራፕት!