ክቡር ሚኒስትር

[ክቡር ሚኒስትሩ አማካሪያቸው ዘንድ ደውለው ጠሩት]

 

 • አቤት ክቡር ሚኒስትር ፈለጉኝ?
 • አንዳንድ ነገር አፕዴት እንድታደርገኝ ብዬ ነው፡፡
 • ስለምን አፕዴት ላድርግዎት?
 • በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ስላሉት ዝግጅቶች፡፡
 • እንግዲህ ጋዜጠኞች ወደ ሥፍራው መጓዝ ጀምረዋል፡፡
 • በጣም ጥሩ፡፡
 • አራተኛ ዓመቱን ለመዘከርም የተለያዩ የእግር ኳስ ውድድሮች ተካሂደዋል፡፡
 • እሺ፡፡
 • በአጠቃላይ ነገሮች እንዳቀድናቸው እየተጓዙ ናቸው፡፡
 • ይኼ ነው የሚፈለገው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ይህ እኮ ታሪካዊ ፕሮጀክት ነው፡፡
 • ምን ታሪካዊ ብቻ ተዓምራዊም ነው እንጂ፡፡
 • ይኸው እንግዲህ 40 በመቶው አካባቢ ግንባታው ተጠናቋል፡፡
 • እንደጀመርነው እንጨርሰዋለን፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር እንኳን ይኼን ሌላም እንጀምራለን፡፡
 • እንግዲህ ጉራህን አትንፋ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር የእርስዎ አመራር እኮ አስደናቂ ነው፡፡
 • እስቲ ፉገራህን ተወው፡፡
 • ፉገራ አይደለም ክቡር ሚኒስትር፣ ገና ሌላ ብዙ ተዓምር መሥራት እንችላለን፡፡
 • ለነገሩ በዚህ አንታማም፣ ገና ሌላ ብዙ ነገር መሥራት እንችላለን፡፡
 • ይኼን እኮ ነው የምልዎት፡፡
 • ዓባይ ይገደባል፡፡
 • በሚገባ፡፡
 • ከዓባይ ውጪ ግን የሚገደቡ ሌሎችም አሉ፡፡
 • ደግሞ የትኛው ወንዝ ሊገደብ ነው?
 • ወንዝ አይደለም፡፡
 • ምንድነው ታዲያ?
 • ፖለቲከኞች!
 • እ…
 • ሙሰኞች!
 • እእእ…
 • እንዲሁም ሞላጮች፡፡
 • እነሱስ ይገደቡ፡፡
 • ከዚያ በቃ ይህን ሕዝብ እናንበሸብሸዋለን፡፡
 • በምን? በግድብ?
 • የአንተም አፍ ይገደባል፡፡
 • ይቅርታ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ሌላ ምን ወሬ አለ?
 • ያው ጂቲፒ 2 እየተዘጋጀ ነው፡፡
 • የእኛ መሥሪያ ቤት ዕቅድ ተዘጋጅቷል?
 • ቀን ተሌት እሱ ላይ ነው የምንሠራው፡፡
 • በኋላ አመድ አፋሽ እንዳታደርገኝ፡፡
 • አያስቡ ክቡር ሚኒስትር ሁሉን ነገር እናዘጋጀዋለን፡፡
 • ብቻ እንዳታሳፍረኝ፡፡
 • እርስዎ ያለእኔ፣ እኔም ያለእርስዎ እንደማንሠራ አውቃለሁ፡፡
 • ምን አልክ?
 • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
 • እኔ ማንም ላይ አልተደገፍኩም፣ ራሴን ችዬ ነው የቆምኩት፡፡
 • ማለቴ የቡድን ሥራ ነው ማለቴ ነው፡፡
 • የምን የቡድን ሥራ ነው?
 • እ…
 • ሁላችሁም እዚህ የደረሳችሁት በእኔ መሆኑን አትርሱ፡፡
 • እ…
 • በቃ ሰምተሃል አሥሬ እ…አትበል፡፡
 • እሺ፡፡
 • ምርጫውስ እንዴት ነው?
 • ያው እንግዲህ እሱንም ተያይዘነዋል፡፡
 • ሕዝቡ እኮ ከእኛ ጋር ነው፡፡
 • ምን አሉኝ?
 • ሕዝቡ የሚፈልገውን እየሠራን ስለሆነ ከእኛ ውጪ ማን አለው?
 • ያው እሱ የሕዝቡ ውሳኔ ነው የሚሆነው፡፡
 • ስለእሱ ሐሳብ አይግባህ፡፡
 • መቸኮል ግን አያስፈልግም፡፡

[የክቡር ሚኒስትሩ ጓደኛ የሆኑ ሌላ ሚኒስትር ደወሉ] 

 • ሰላም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ሰላም እንዴት ነህ?
 • የህዳሴው ግድብ ዝግጅት እንዴት ነው?
 • እንኳን ደስ አለህ፡፡
 • ለምኑ?
 • ይኸው ሰሞኑን ከግብፅ ጋር ተፈራረምን አይደል እንዴ?
 • ምኑ ነው ደስታው አልገባኝም?
 • ከግብፅ ጋር እኮ ከአሥር ዓመት በላይ የፈጀ ድርድር አድርገናል፡፡
 • ሲኤፍኤውን ፈረመች እንዴ?
 • ኧረ በፍጹም፡፡
 • ታዲያ ከአሥር ዓመት በላይ የፈጀው ድርድር እኮ እሱን ለማስፈረም ነው፡፡
 • ቢሆንም ይኼኛው ወደዚያው መንገድ የሚወስደን ነው፡፡
 • አልመሰለኝም፡፡
 • እንዴት?
 • አዲሱ ስምምነት ማንን እንደሚጠቅም ብዙም አልገባኝም፡፡
 • እኛን ነዋ የሚጠቅመን፡፡
 • እኔ ግን አልመሰለኝም፡፡
 • እንዴት?
 • ግድቡን ለመስኖ መጠቀም አንችልም አይደል?
 • ማን አለ?
 • ይኼው በየሚዲያው ኢትዮጵያ ግድቡን ለመስኖ መጠቀም እንደማትችል አረጋገጠች እያሉ ነው፡፡
 • እንደዚያ የሚል ስምምነት አልተፈራረምንም፡፡
 • እኔም ሳነበው ግን ግድቡ ለመስኖ ጥቅም ይውላል የሚል ነገር አላገኘሁበትም፡፡
 • ለመስኖ ባንለውም ለኢኮኖሚክ ዴቨሎፕመንት ይውላል ይላል፡፡
 • ይህ ምን ማለት ነው ታዲያ?
 • መስኖ እዚህ ውስጥ ሊካተት ይችላል ማለት ነው፡፡
 • ለምን መስኖ ተብሎ አልገባም?
 • ዲፕሎማሲ ነዋ፡፡
 • እኔ ግን ብዙም አላማረኝም፡፡
 • ለምን?
 • እንደ ውጫሌ ውልና እንደ ዘ ሔግ ውሳኔ እንዳይሆን ብዬ ነው፡፡
 • ያ ሌላ ይኼ ሌላ፡፡
 • የግብፅ ፕሬዚዳንትን ንግግር ሰምተውታል?
 • በሚገባ፡፡
 • ይህ መርህ እኮ ሕግ ሆኖ እንዲፀድቅ ነው የሚፈልገው፡፡
 • እሱ ፈለገ ማለት ሕግ ይሆናል ማለት አይደለም፡፡
 • እና ይህ መርህ በፓርላማ ቀርቦ አይፀድቅም እያሉኝ ነው?
 • ፓርላማ ሊቀርብ ይችላል፡፡
 • ከቀረበማ ይፀድቃል፡፡
 • ቀርቦ ባይፀድቅስ?
 • ቀርቦ ያልፀደቀው የመጀመሪያው ሕግ ሊሆን ነው ማለት ነው?
 • እሱን ነው የምልህ፡፡
 • እንዲያ ከሆነ ጥሩ፡፡
 • በዚያ ላይ ግብፆች በአንዴ ሲኤፍኤውን ከሚፈርሙ በዚህ እያሟሟቁ ሊጠብቁን በማሰብም ሊሆን ይችላል፡፡
 • የእኔም ዋናው ጥያቄ ከሲኤፍኤው ውጪ ሌላ ስምምነት አያስፈልገንም የሚል ነው፡፡
 • በዚህ ስምምነት ያስመዘገብነውን ሌላ ድል አትርሳ፡፡
 • የምን ድል?
 • በኢንተርናሽናል ማኅበረሰብ ከፍተኛ ተቀባይነትን አትርፈንበታል፡፡
 • እሱ እንዳለ ሆኖ አሁንም ስምምነቱ ጥንቃቄ ያሻዋል፡፡
 • እንግዲህ እንዳልኩህ ይህ ስምምነት በፓርላማ ላይፀድቅ ይችላል፡፡
 • የእኔም ፀሎት እሱ ነው፡፡
 • ግድቡንማ ለፈለግነው ነገር መጠቀም እንችላለን፡፡
 • እኔም ይህን ዕድል ሳናውቅም አሳልፈን እንዳንሰጥ ብዬ ነው፡፡
 • ስለእሱ አታስብ፡፡

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሾፌራቸው ጋር ወደ ቤት እየሄዱ ነው] 

 • ደረሰህ?
 • ምኑ ክቡር ሚኒስትር?
 • የቤት ዕጣው ነዋ፡፡
 • ኧረ በጣም ተናድጃለሁ፤ በዚህኛውም ዙር አለፈኝ፡፡
 • ዕድል የለህም ልበል?
 • ሰው ሁሉ እንዴት አልወጣልህም? ለዚያውም የሚኒስትር ሾፌር ሆነህ እያለኝ ነው፡፡
 • እኔን እኮ ሁሌም ግራ ታጋባኛለህ፡፡
 • በምን ክቡር ሚኒስትር?
 • ወደ እኛ ትሆን ወይስ ወደ ተቃዋሚዎች ጎራ?
 • ለዚያ ነው ዕጣ ያልወጣልኝ?
 • እኔ እንደዚያ አልወጣኝም፡፡
 • ታዲያ ምን እያሉ ነው?
 • የመንግሥት ሠራተኞች ኮታ ስለነበር እንዴት በዚያ አልወጣልህም ብዬ ነው?
 • አያስታውሱኝ በቃ ይተዉት፡፡
 • ለመሆኑ ምርጫው እንዴት ነው?
 • እርስዎን ልጠይቅዎት እንጂ፣ ምርጫው እንዴት ነው?
 • ያው በዚህም ምርጫ እንደምናሸንፍ ይታወቃል፡፡
 • ምንም አያስጨንቅዎትማ?
 • የሚያስጨንቀኝ ሌላ ነው፡፡
 • ምንድነው የሚያስጨንቅዎት?
 • ፐርሰንቱ፡፡
 • የምን ፐርሰንት?
 • ባለፈው 99 ነበር አሁን ስንት ይሆናል ብዬ ነዋ፡፡
 • ለምን 70/30 አትካፈሉም?
 • ምን አልክ አንተ?
 • እናንተ 70 ፐርሰንት ተቃዋሚዎች ደግሞ 30 ፐርሰንት ውሰዱ፡፡
 • ይኼን ቁጥር ከየት አመጣኸው?
 • አፌ ላይ መጥቶ ነው፡፡
 • ከማን ጋር እንደምትውል አጣራልሃለሁ፡፡
 • ወይ ጣጣ፡፡
 • 70/30 አልከኝ?
 • ኧረ ይቅርታ፡፡

[ክቡር ሚኒስትሩ ቤት ሲገቡ ሚስታቸውን አገኟቸው] 

 • ምን እያየሽ ነው?
 • ይህን የጀርመን አውሮፕላንን የከሰከሰው ሰውዬ ዜና አስገርሞኝ ነው፡፡
 • ምኑ ይገርማል?
 • አይ በአውሮፓውያን አውሮፕላን መጠቀም ራሱ እያስፈራ መጣ፡፡
 • የእኛ አየር መንገድ አለ አይደል እንዴ?
 • አሁን ከአውሮፓውያኖቹ የበለጠ ሆኖ ነው?
 • የአፍሪካ ኩራት መሆኑን እንዳትረሺ፡፡
 • ዋናው ጥያቄ እኮ ፓይለቶች እንዴት ይታመኑ የሚለው ነው?
 • የእኛ ፓይለቶች ታማኞች ናቸው፡፡  
 • ይኼው ባለፈው የእኛስ ቢሆን አውሮፕላኑን ጠልፎት አልነበር?
 • ጠለፈው እንጂ አልከሰከሰውማ?
 • ለነገሩ አሁን አዲስ ሕግ አውጥተዋል፡፡
 • የምን ሕግ?
 • 2 ለ 1 የሚል፡፡
 • ምንድነው 2 ለ 1?
 • ከሁለቱ ፓይለቶች ተጨማሪ አንድ ሌላ አብራሪ ኮክፒት ውስጥ ይኖራል፡፡
 • እኛም ለነገሩ ቀደም ብለን ሕግ አውጥተናል፡፡
 • ምን የሚሉት?
 • 1 ለ 5!