ክቡር ሚኒስትር

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ ስልክ ደወለችላቸው]

 

 • ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • አቤት?
 • ስልክ ይፈልግዎታል፡፡
 • ማንን?
 • እርስዎን ነዋ፡፡
 • እየቀለድሽ ነው?
 • ኧረ በፍጹም፡፡
 • ሥራ እንደያዝኩ እያወቅሽ?
 • አዎን ግን አስቸኳይ ነው ተብዬ ነው፡፡
 • ከበላይ አለቃ ነው እንዴ የተደወለው?
 • አይ አይደለም፡፡
 • ታዲያ ማን ነው?
 • ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ነው፡፡
 • ምን?
 • አዎን፣ ክቡር ሚኒስትሩን እንፈልጋቸዋለን እያሉ ነው፡፡
 • ለምን ሥራ ላይ ነው አትይም?
 • ብያቸው ነበር፣ ግን በጣም አስቸኳይ ነው ብለውኝ ነው፡፡
 • እሺ አገናኚኝ፡፡
 • እሺ፡፡

[በስልክ አገናኘቻቸው]

 • ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ሰላም እንዴት ናችሁ?
 • ሰላምማ እናንተ ጋ ነው እንጂ እኛ ጋ መቼ አለ?
 • ኧረ ተው አንዳንዴ እንኳን አመስግኑ፡፡
 • ማንን? እናንተን?
 • እኛን እንኳን ባታመሰግኑ ፈጣሪያችሁን አመስግኑ፡፡
 • እሱንማ ባናመሰግን ዛሬ ላይ አንደርስም ነበር፡፡
 • እሺ ምን ልርዳችሁ?
 • በጣም ጠቧል፡፡
 • ምን?
 • በጣም እየጠበበ ነው፡፡
 • ምኑ ነው የጠበበው?
 • ሁሉ ነገር፡፡
 • ይኼው እኛ እንግዲህ ሰፋፊ መንገዶች እያስገነባን ነው፡፡
 • ኧረ ፖለቲካውን ነው የምልዎት፡፡
 • ምን ሆናችሁ ደግሞ?
 • ይኸው አባሎቻችን በየጊዜው እየታሰሩ ነው፡፡
 • የትኞቹ?
 • የተቃዋሚ ፓርቲዎች አባሎች ናቸዋ፡፡
 • እኮ ምን ሲያደርጉ?
 • እ…
 • በሕጋዊ መንገድ ሲንቀሳቀሱ ነው የታሰሩት?
 • እነማን?
 • አባሎቻችሁ ናቸዋ?
 • አልሰማሁዎትም?
 • ሕግ አይከበር እያልከኝ ነው?
 • እንዴት?
 • ከሕግ ውጪ ማንም ከተንቀሳቀሰ ተጠያቂ መሆኑ አይቀርም፡፡
 • አሁን ማን ይሙት እናንተ በሕግ ነው የምትንቀሳቀሱት?
 • እንዴታ?
 • አሁን ሕግ ብትከተሉ ይህ ሁሉ ሙስና አገሪቷ ውስጥ ይኖር ነበር?
 • ይኸው ባለፈው ዕርምጃ ወሰድን አይደለ እንዴ?
 • ማን ላይ?
 • የራሳችን ሌቦች ላይ ነዋ፡፡
 • ዋናው ጥያቄው እኮ ሌቦቹ እነሱ ብቻ ናቸው ወይ? የሚለው ነው፡፡
 • እ…
 • ለነገሩ ሁሉም ሌቦች ቢታሰሩ መንግሥት አይኖርም ነበር፡፡
 • እንዴት?
 • ንፁኃን እጅግ ጥቂት ብቻ ናቸው፡፡
 • ሌባ ነህ እያልከኝ ነው?
 • እሱን እርስዎ አሉ፡፡
 • ይህ ራሱ የሚያሳየው ሆደ ሰፊነታችንን ነው፡፡
 • አይ ሆደ ሰፊነት?
 • እየሰደባችሁን ዝም እንላለን፡፡
 • ለማንኛውም ክቡር ሚኒስትር ምኅዳሩ ጠቧል፡፡
 • አንድ ነገር ልንገርህ?
 • እሺ፡፡
 • ኳስ ትወዳለህ?
 • ብዙም አይደለሁም፡፡
 • እኔ ግን በጣም እወዳለሁ፡፡
 • እሺ፡፡
 • አንድም ጨዋታ አያመልጠኝም፡፡
 • ለዚያ ነው ሥራ የማይሠሩት?
 • እንግዲህ አትዘባርቅ!
 • እሺ ይቀጥሉ፡፡
 • አርሴናልና ማንችስተር ቀንደኛ ተፎካካሪ ክለቦች ናቸው፡፡
 • አውቃለሁ፡፡
 • እናም የአርሴናል አሠልጣኝ ለማንቸስተሩ አሠልጣኝ ደውሎ የጨዋታ ፎርሜሽንህን ንገረኝ ቢለው ምን እንደሚለው ታውቃለህ?
 • አላውቅም፡፡
 • ልክ አንተ ላይ አሁን እኔ ስልኩን እንደምዘጋብህ ይዘጋዋል፡፡
 • ጢጢጢ…

[የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ ቢሯቸው ገባ]

 • እሺ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንዴት ነህ እባክህ?
 • እግዚአብሔር ይመስገን፡፡
 • ሥራ እንዴት ይዞሃል?
 • ይኸው የህዳሴ ግድቡ የመሠረት ድንጋይ የተጣለበትን አራተኛ ዓመት ለማክበር እየወጣን እየወረድን ነው፡፡
 • እኔም ሰሞኑን በዚሁ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ተወጥሬያለሁ፡፡
 • አንድ ነገር ልንገርዎት ብዬ ነው፡፡
 • ምን?
 • እርስዎን መርጬዎት ነበር፡፡
 • ለምኑ?
 • የባለሥልጣናትን የእግር ኳስ ቡድን እንዲያስተባብሩ፡፡
 • ተው ተው እባክህ?
 • እግር ኳስ በጣም ጐበዝ ስለሆኑ ነው፡፡
 • አውቃለሁ ግን…
 • በዚያ ላይ ባለፈው ዓመትም ሕዝቡ በጣም ሲያደንቅዎት ነበር፡፡
 • አዎ ቢሆንም?
 • ኳስ ደግሞ በጣም ይወዳሉ፡፡
 • ልክ ነህ ግን እኔ በአሁኑ ተቀያሪ ብሆን ደስ ይለኛል፡፡
 • ለምን ክቡር ሚኒስትር?
 • በቃ ለሌሎቹም ዕድል መስጠት አለብና፡፡
 • እ…
 • አዎ እኔ የእኛ ቡድን ሲደክም ተቀይሬ ገብቼ ባግዝ ይሻለኛል፡፡
 • እና በአሁኑ ቋሚ ተሰላፊ አይሆኑም?
 • አዎን፡፡
 • ፖለቲካውም ላይ እንዲህ ቢሆን ጥሩ ነበር፡፡
 • ምን ማለትህ ነው?
 • ያው ለአዲሱና ለወጣቱ ትውልድ ዕድል ቢሰጠው ማለቴ ነው፡፡
 • ይኸው መተካካት ላይ አይደለን እንዴ?
 • መተካካትማ ተብሎ ነበር፡፡
 • ታዲያ ምን ሆነ?
 • በርካቶች እኮ በመጪው ምርጫ አይወዳደሩም ተብሎ ነበር፡፡
 • እ…
 • ማለቴ በመተካካቱ ፖሊሲ መሠረት የቀድሞ አመራሮች በመጪው ምርጫ አይወዳደሩም ተብሎ ነበር፡፡
 • ልክ ነው፡፡
 • እና ባለፈውም ምርጫ በርካቶቹ የተጠባባቂ ወንበር ላይ ተቀምጠው ነበር፡፡
 • ምን እያልክ ነው?
 • በዚህኛው ምርጫ ግን ራሳቸውን ማግለል ሲገባቸው ቋሚ ተሰላፊ ሆነው መጥተዋል፡፡
 • እ…
 • ለዚያ ነው ምነው ፖለቲካው ላይም ተጠባባቂ ወንበር ላይ በተቀመጣችሁ ያልነው፡፡
 • አትሳሳት፡፡
 • እንዴት?
 • እነፖል ስኮልስ ራሳቸውን ከኳስ ካገለሉ በኋላም ቡድናቸው ሲቸገር ተመልሰው ይጫወቱ ነበር፡፡
 • እኮ አትሊስት ሞክረን ሲያቅተን ለምን አትረዱንም?
 • እ…
 • ለእኛም ዕድል ስጡን፡፡
 • ዛሬ ምነው እንደዚህ ለፍላፊ ሆንክ?
 • ይቅርታ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ለማንኛውም እኔ የዓባይን የፖለቲካ ጉዳይ ብከታተል ይሻለኛል፡፡
 • እሺ እንዳሉ፡፡
 • መቼም አንተ የጂኦፖለቲክስ ጉዳይ አይገባህም፡፡
 • እንዴት?
 • ያለነው ቀንድ ላይ ነው፡፡
 • አውቃለሁ፡፡
 • ይህ ቦታ ደግሞ ሰላም የለበትም፡፡
 • ቀንድ ላይማ መቼ ሰላም ኖሮ ያውቃል?
 • ከሰሜን ሻዕቢያ፣ ከምሥራቅ አልሸባብ፣ ከምዕራብ ደግሞ ደቡብ ሱዳን አሉ፡፡
 • ልክ ነው፡፡
 • ስለዚህ ግብፅ እዚህ ከእኛ ጋ እየተስማማች ከጐን ልማታችንን ለማደናቀፍ ትሠራለች፡፡
 • እሱማ ልክ ነው፡፡
 • ስለዚህ የግብፅ ጉዳይ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚሻ ጉዳይ ነው፡፡
 • ልክ ብለዋል ክቡር ሚኒስትር፡፡

[የክቡር ሚኒስትሩ ወዳጅ ደወለ] 

 • እንዴት ነህ?
 • አለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ሥራ እንዴት ነው?
 • ያው በልተን ካደርን ተመስገን ነው፡፡
 • ቀልደኛ ሆነሃል ልበል?
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • አንተም በልተን ካደርን ትላለህ?
 • ታዲያስ?
 • አንተ በልተህ፣ አስበልተህ፣ ተበላልተህ አይደል እንዴ የምታድረው?
 • ኧረ የለም፡፡
 • ምን?
 • ምንም የለም እኮ?
 • ምኑ?
 • ዶላር፡፡
 • የምን ዶላር?
 • ይኸው ወረፋ መጠበቅ ከጀመርኩ ወራት አለፉ፡፡
 • የምን ወረፋ?
 • የዶላር ወረፋ፡፡
 • ጥፋቱ የራሳችሁ ነው፡፡
 • እንዴት?
 • ዶላሩን የምታሸሹት ራሳችሁ፡፡
 • እኔም መናገር ይፈቀድልኛል?
 • ቀጥል፡፡
 • ዶላሩን እንድናሸሽ መንገዱን የምታመቻቹልን ራሳችሁ፡፡
 • እ…
 • አዎና፣ ለማንኛውም ምንም ዶላር የለም፡፡
 • በቃ አጣራለሁ እስቲ፡፡

[የክቡር ሚኒስትሩ ሚስት ደወሉ] 

 • የለም እኮ፡፡
 • ምንድነው የሌለው?
 • ዶላር የለም፡፡
 • የምን ዶላር?
 • እህቴ ከነገወዲያ ወደ ውጭ ጉዞ እንዳላት ታውቃለህ አይደል?
 • አዎን አውቃለሁ፡፡
 • ለመንገድ እንኳን የሚሆናት ዶላር ማግኘት አልቻለችም፡፡
 • ከብላክ ማርኬት ለምን አትገዛም?
 • ምን? ትልቅ ባለሥልጣን መሆንህን ረሳኸው እንዴ?
 • እኔ የመፍትሔ ሰው እንደሆንኩ ታውቂያለሽ?
 • ቢሆንስ?
 • ችግር ነገርሽኝ፣ መፍትሔ ነገርኩሽ፡፡
 • ድንቄም መፍትሔ?
 • ሁሌም መፍትሔ ስለምናሰላስል ነው አገሪቱ እዚህ የደረሰችው፡፡
 • ሌላ የለህም?
 • ሃያ አራት ሰዓት ሠርተን፣ አገሪቷን ሃያ አራት ዓመት መርተናታል፡፡
 • እ…
 • አሁን ደግሞ አርባ ስምንት ሰዓት ሠርተን፣ አርባ ስምንት ዓመት እንመራለን፡፡
 • ያድርግላችሁ!