ክቡር ሚኒስትር

[ክቡር ሚኒስትሩ ጉንፋን ይዟቸዋል፡፡ ቢሮ ከጸሐፊያቸው ጋር እያወሩ ነው]

 

 • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ምነው?
 • ድምፅዎት ተዘግቷል፡፡
 • ምን ይመስልሻል?
 • እዚያ ውጭ ለምርጫ ቅስቀሳው ብዙ አውርተው ነው?
 • ምን ትቀባጥሪያሽ?
 • እውነቴን እኮ ነው፡፡
 • ኧረ ጉንፋን ይዞኝ ነው፡፡
 • እንዴ እርስዎን ክቡር ሚኒስትር?
 • አዎና፣ እኔም እኮ እንደ አንቺ ሰው ነኝ፡፡
 • አይ ያው የሚውሉት ጥሩና የፀዳ ቦታ ነው ብዬ ነው፡፡
 • አሽሙር መሆኑ ነው?
 • ኧረ የምሬን ነው፡፡
 • አታይም እንዴ? አየሩ ተቀይሯል፡፡
 • ስለሱማ አያንሱ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንዴት?
 • መዓት ሊወርድብን ነው እኮ የሚመስለው፡፡
 • የምን መዓት?
 • ሙቀቱ ነዋ፡፡
 • ግሎባል ዋርሚንግ ነው፡፡
 • እሱ ብቻ ነው ብለው ነው?
 • ሌላ ታዲያ ምን አለ?
 • የፈጣሪ ቁጣ ነው እባክዎት፡፡
 • ፈጣሪ ደግሞ ማን ላይ ነው የሚቆጣው?
 • እኛ ላይ ነዋ፡፡
 • ለምን?
 • እዚህ አገር አይኖሩም እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
 • ምን ማለት ነው?
 • እስቲ ይመልከቱ፡፡
 • ምኑን?
 • ግፉን፣ ሙስናውን፣ ጭካኔውን፣ ስግብግብነት፣ ኧረ ስንቱ ቅጡ፡፡
 • ለዚያ ነው አየሩ የተቀየረው?
 • የእግዚአብሔር ቁጣ ነው ስልዎት፡፡
 • በይ እኔ እንደሰማሁሽ ሌላ ሰው እንዳይሰማሽ፡፡
 • እ…
 • አየሩ የተቀየረው በግሎባል ዋርሚንግ ምክንያት ነው፡፡
 • በእሱ ብቻ እንደዚህ በአንዴ አይቀየርም ብዬ ነው፡፡
 • ለዚያ ነው እኮ ከምዕራቡ ዓለም መሪዎች ጋር የምንደራደረው፡፡
 • ምን እያልን?
 • ካሳ ክፈሉን ብለን ነዋ፡፡
 • ካሳ ቢከፍሉን አየሩ ካልተለወጠ ምን ይጠቅመናል?
 • ካሳውን እኮ የምንጠቀምበት ዛፍ ለመትከያ ነው፡፡
 • ካሳ ባይከፍሉንም እኮ እኛ ዛፍ መትከል እንችላለን፡፡
 • እሱማ እየተከልን ነው፡፡
 • በእሱ ዙሪያ ግን መሥራት ያለብንን ያህል እየሠራን አይደለም፡፡
 • እንዴት?
 • ዛፍ መትከል ግዴታ መሆን አለበት፡፡
 • እሱስ ልክ ብለሻል፡፡
 • የእኛ ሠፈር ለዚህ ጥሩ ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡
 • እንዴት?
 • ከጥቂት ዓመታት በፊት ከእኔ መኖሪያ በላይ ያለው ተራራ መላጣ ነበር፡፡
 • እሺ፡፡
 • ነፍሳቸውን በገነት ያኑረውና …
 • የማንን?
 • የጠቅላይ ሚኒስትር መለስን ነዋ፡፡
 • ለምን?
 • እሳቸው ያረፉ ጊዜ ሁሉም ሰው በስማቸው ዛፍ መትከል ጀመረ፡፡
 • እ…
 • በቃ ድርጅት በሉ፣ ግለሰብ ማን ቀረ?
 • እሺ፡፡
 • ይኸው አሁን ያ ተራራ በዛፍ ተሸፍኗል፡፡
 • በጣም ደስ ይላል፡፡
 • የዚያ አካባቢ ሰዎችም በእጅጉ ተጠቃሚ ሆነናል፡፡
 • ይህ በጣም የሚያስደስት ነገር ነው፡፡
 • ግን ክቡር ሚኒስትር፣ ሌላው አካባቢ እኮ እየነደደ ነው፡፡
 • እሱማ አሳሳቢ ነው፡፡
 • እኔማ በድጋሚ ሰው ዛፍ መትከል እንዲጀምር ሌላ መሪ መሞት አለበት ወይ እያልኩ ነው፡፡
 • ምን አልሽ?
 • እውነቴን ነው ክቡር ሚኒስትር፣ ሌላ መሪ ካልሞተ ዛፍ መትከል አንጀምርም እንዴ?
 • አንቺ አፍ ለቆብሻል፡፡
 • ዛፍ መትከል ግዴታ መሆን አለበት፡፡
 • በእሱ እስማማለሁ፡፡
 • በዚያ ላይ ደግሞ ሕንፃዎችም ሲሠሩ አየሩ ላይ ጉዳት የማያደርሱ መሆናቸው ሊረጋገጥ ይገባል፡፡
 • ትክክል፡፡
 • ባለሀብቱ ሕንፃ መትከል ብቻ ሳይሆን ዛፍ መትከልንም ይማር፡፡
 • ሌላ ፖለቲካሽን ተይ፡፡
 • ይቅርታ ክቡር ሚኒስትር፣ ሌላም የሚያሳስበኝ ነገር አለ፡፡
 • ምን?
 • የመናፈሻ ሥፍራ እኮ በከተማችን የለም፡፡
 • መኖር እንኳን አለ፡፡
 • ሰዎች ገብተው ካላረፉበት ቢኖርስ ምን ይጠቅማል?
 • እ…
 • በዚያ ላይ አምስት ሚሊዮን ሕዝብ በሚኖርበት ከተማ በጣት ብቻ የሚቆጠሩ መናፈሻዎች ይበቃሉን?
 • እሱስ አይበቁም፡፡
 • ይኼም በጣም ሊታሰብበት ይገባል፡፡
 • ሐሳብሽን ተቀብያለሁ፡፡

[የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ ቢሯቸው ገባ] 

 • እንዴት ነበር ጉዞ ክቡር ሚኒስትር?
 • ስኬታማ ነበር፡፡
 • ዳያስፖራው እንዴት ነው?
 • ከእኛ ጋር እንደሚሠለፉ አረጋግጠውለናል፡፡
 • በጣም ደስ ይላል፡፡
 • በርካቶች ከእኛ ጋር ለመሥራት ተስማምተዋል፡፡
 • ዋናው እዚህ ያለውን የቤት ሥራችንን መሥራታችን ነው፡፡
 • እሱማ ግድ ነው፡፡
 • አሁን ያው የምርጫ ክርክሩ ተጀምሯል፡፡
 • የእኔ ተራ መቼ ነው?
 • በቅርብ ጊዜ ነው፡፡
 • ያው እኔ የገበሬ ልጅም ስለሆንኩ ግብርናን አስመልክቼ ተቃዋሚዎችን ወጥሬ ነው የምከራከራቸው፡፡
 • እሱ ጥሩ ነው፤ ግን…
 • ግን ምን?
 • ክርክሩ ግብርና ብቻ ላይ ያተኮረ አይደለማ፡፡
 • እ…
 • በዚያ ላይ ኢኮኖሚያችን ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መር ተቀይሯል፡፡
 • አውቃለሁ፡፡
 • በተጨማሪም የሰብዓዊ መብት ጉዳይም መነሳቱ አይቀርም፡፡
 • እሱ ነው እኮ የሚያስጨንቀኝ፡፡
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • በወረቀት ላይ ያሰፈርነውና በመሬት ላይ ያለው ሰፊ ልዩነት አለው፡፡
 • ቢሆንም ወጥተን መከራከራችን አይቀርም፡፡
 • በቃ እየሠራን ነው፣ እየተለወጥን ነው ማለት ነው ቢከፋ፡፡
 • ሌላማ ምን እንላለን?
 • ችግሩ እኮ እንዳለ እኔም አውቃለሁ፡፡
 • እንዴት?
 • ባለፈው ባለቤቴ አንድ ነገር ፈልጋ ያጋጠማትን የመልካም አስተዳደር ችግር እኔ ነኝ የማውቀው?
 • ታዲያ ለምን አንፈታውም?
 • ከምርጫው በኋላ፡፡
 • ባለፈውም ምርጫ እኮ እንዲህ ብለን ነበር፡፡
 • አሁንም እንደግመዋለና፡፡
 • ለማንኛውም ጸሐፊዬን ጥራልኝ፡፡
 • እሺ፡፡

[ጸሐፊያቸው መጣች] 

 • ፈለጉኝ ክቡር ሚኒስትር?
 • የምርጫ ካርድ አውጥተሻል?
 • አላወጣሁም፡፡
 • ለምን?
 • ጊዜው አለፈብኝ፡፡
 • ባለቤትሽስ?
 • እሱም አላወጣም፡፡
 • ሄዳችሁ አውጡ እንጂ ምንድነው የምትጠብቁት?
 • ጊዜው እኮ አልፎብናል፡፡
 • በመብትሽ ትቀልጃለሽ?
 • ያው ነው እባክዎት፡፡
 • ምኑ ነው ያው?
 • መረጥኩም አልመረጥኩም ለውጥ የለውም፡፡

[የክቡር ሚኒስትሩ ወዳጅ የሆነ ባለሀብት ቢሯቸው መጣ]

 • ሰላም ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንዴት ነህ ወዳጄ?
 • ምርጫ እንዴት ይዟችኋል?
 • ይኸው ተያይዘነዋል፡፡
 • እኛም ተያይዘነዋል፡፡
 • ስለሁሉም ነገር አታስብ፡፡
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • በቃ መሬት በል፣ የታክስ ጉዳይ በል ብቻ ሁሉንም ነገር እኛ እንጨርስልሃለን፡፡
 • ይኸው እኔም ሥራዬን ትቼ እኮ የምርጫ ዘመቻ ላይ ነው ያለሁት፡፡
 • እሱን ነው እኔ የምልህ፡፡
 • ሁሉንም ነጋዴ እየቀሰቀስኩ ነው፡፡
 • ዋናው መመረጣችን ነው፡፡
 • ስለሱ አያስቡ ክቡር ሚኒስትር፣ ዛሬ የመጣሁት ግን ለሌላ ነገር ነበር፡፡
 • ምን ገጠመህ?
 • አንድ ዘመዴ እናንተ ጋ መሥራት ይፈልጋል፡፡
 • አምጣው ችግር የለም፣ አንድ ቦታ እወሽቀዋለሁ፡፡
 • ልጁ ያለው የትምህርት ደረጃ…
 • ዝም ብለህ ላከው ስልህ?
 • እሺ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • በነገራችን ላይ አንድ የእኔም ዘመድ እናንታ ጋ መሥራት ይፈልጋል፡፡
 • ዝም ብለው ይላኩት፡፡
 • እሺ፡፡

[የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ ቢሯቸው ገባ] 

 • ይኸው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምንድነው?
 • በምርጫ ክርክሩ የሚያነሷቸው ነጥቦች፡፡
 • እኔ የምልህ ከክርክሩ በፊት አንድ ነገር ማድረግ አለብን፡፡
 • ምን?
 • የሆነ ፕሮጀክት መመረቅ አለብኝ፡፡
 • ባለፉት ጊዜያት እኮ በርካታ ፕሮጀክቶች መርቀዋል፡፡
 • አሁን ሌላ ልመርቃ፡፡
 • ምንም አዲስ ፕሮጀክት የለንማ፡፡
 • ሁሉም ተመርቀው አልቀዋል?
 • አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ከክርክሩ በፊት ግን የግድ መመረቅ አለብኝ፡፡
 • ታዲያ ምን ተሻለ?
 • ያንን ፕሮጀክት…
 • ምን?
 • ደግሜ ልመርቀው!