ክቡር ሚኒስትር

[ክቡር ሚኒስትሩ ቤት ውስጥ ከባለቤታቸው ጋር እያወሩ ነው]

 

 • ምን ተገኝቶ ነው ዛሬ?
 • ምን ሆነሃል?
 • እንደዚህ የዘነጥሽው?
 • ዓይን ተከፍቶ ነው እባክህ?
 • እንዴት ማለት?
 • ሁሌም ቢሆን እኔ ሚስትህ ዘናጭ ነኝ፡፡
 • እሱን ተይውና አሁን ምን ተገኘ ነው ያልኩሽ?
 • በዓላችን እኮ ነው ዛሬ?
 • የምን በዓል?
 • የእኛ በዓል ነዋ!
 • እኮ እናንተ እነማን ናችሁ?
 • እኛ ሴቶች፡፡
 • እ…
 • አዎን፣ የምን እ… ነው?
 • ገርሞኝ ነዋ!
 • ምኑ?
 • እንዲህ መዘነጥሽ፡፡
 • ምኑ ነው የሚያስገርመው?
 • ባለፈው ወር ያን ሁሉ በዓል ስናከብር ምነው እንደዚህ አልዘነጥሽ?
 • ወዴት? ወዴት?
 • የምሬን ነው፡፡
 • ያ ሌላ ይኼ ሌላ፡፡
 • እንዴት?
 • ያ የራሳችሁ ነው፤ ይኼ ደግሞ የእኔ ነው፡፡
 • እንዴት ነው የራሳችን የሆነው? የሁላችንም ነው እንጂ፡፡
 • ሰው የሚነግርህን ስማ የታገልከው ለራስህ ነው፡፡
 • ምን?
 • አዎን እና ደግሞ እንደፈለግህ ስትሆን ነበር፤ አሁን ይኼ የእኔ ነው፡፡
 • አልገባኝም፡፡
 • ምኑ ነው ያልገባህ?
 • የታገልከው ለራስህ ነው ያልሽው?
 • ታዲያስ?
 • ይኼን ከሚያሰማኝ ምነው…?
 • በል ግፍ እንዳታወራ፡፡
 • ያን ሁሉ ትግል ከንቱ አደረግሽው?
 • እኔ ከንቱ ነው አላልኩም፡፡
 • አልሽ እንጂ?
 • አልወጣኝም፡፡
 • አንድ ነገር ግን ስሚ?
 • ምን?
 • የሁሉ ነገር መሠረት የእኛ ትግል ነው፡፡
 • ማለት?
 • ዛሬ እንዲህ እንድትዘንጪ ያደረገሽ ራሱ የእኛ ትግል ነው፡፡
 • ዛሬ የዘነጥኩትማ በገዛሁት ልብስ ነው፡፡
 • የምልሽን ስሚ፡፡
 • ምን አልክ?
 • ለሴቶች እኩልነት እኮ የታገልነው እኛ ነን፡፡
 • አቤት፡፡
 • አዎን ሴቶች ከወንዶች ጋር እኩል እንዲቆጠሩ ያደረገው የእኛው ሕገ መንግሥት ነው፡፡
 • እባክህ አትሳሳት፡፡
 • እንዴት?
 • እኩልማ ያደረገን ፈጣሪያችን ነው፡፡
 • ቢሆንም የቀድሞዎቹ መንግሥታት እሱንም ነፍገዋችሁ ነበር፡፡
 • አሁንም ቢሆን ሙሉ በሙሉ መብታችንን እየተጠቀምን አይደለም፡፡
 • ቀስ በቀስ ግን ታገኙታላችሁ፡፡
 • በል ዲስኩርህን ተው፤ ለማንኛውም ዛሬ እራት ውጪ ስለምበላ እንዳትጠብቀኝ፡፡
 • ምን?
 • አዎን፣ ራት አልመጣም፡፡
 • ከማን ጋር ነው የምትበይው?
 • ከሴቶቹ ጋር፡፡
 • ለነገሩ እኔም ቢሮ አመሻለሁ፡፡
 • ለምን?
 • ብዙ ሥራ አለኝ፡፡
 • አዲስ ሥራ አለ?
 • ሰሞኑን ጉዞ አለኝ፡፡
 • የምን ጉዞ?
 • ወደ ውጭ እሄዳለሁ፡፡
 • ለምን?
 • ለምርጫ ቅስቀሳ፡፡
 • ለምርጫ ቅስቀሳ?
 • አዎና፡፡
 • መራጩ እኮ እዚህ ነው ያለው?
 • እዚያ ደግሞ አስመራጮቹ አሉ፡፡
 • አልገባኝም፡፡
 • ያው በየሶሻል ሚዲያው የሚያብጠለጥሉንን ለማለሳለስ ነዋ፡፡
 • ምን ያመጣሉ ብለህ ነው?
 • ሚዲያ ከባድ ነው፤ እኛ ወደን እኮ አይደለም ቲቪውንም፣ ሬዲዮኑንም፣ ጋዜጣውንም የያዝነው፡፡
 • እነሱ ምን ይዘዋል ታዲያ?
 • ሶሻል ሚዲያ፡፡
 • ያን ያህል ተሰሚነት አላቸው ብለህ ነው?
 • ሁሉንም ቀዳዳ መድፈን አለብሽ፡፡
 • መልካም ሥራ፡፡
 • መልካም ራት፡፡

[ክቡር ሚኒስትሩ ቢሮ ገብተው ከአማካሪያቸው ጋር እያወሩ ነው]

 • ሁሉም ነገር ተዘጋጀ?
 • በሚገባ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ስንት ቀን ነው የምቆየው?
 • አሥር ቀን፡፡
 • ብዙ አይደለም?
 • ብዙ ነው፤ ግን ቢሆንም የግድ መሆን ስላለበት ነው፡፡
 • ለነገሩ አንተም ስላለህ ችግር የለውም፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር …
 • አቤት?
 • እኔ እኮ አብሬዎት አልመጣም፡፡
 • ምን?
 • አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምን ማለት ነው?
 • አያስቡ ሁሉም ነገር በሚገባ ተዘጋጅቷል፡፡
 • ብቻዬን ሜዳ ላይ ልትጥሉኝ?
 • እዚህም ያለው ሥራ መሠራት ስላለበት ነው፡፡
 •  አይይይ…
 • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ዳያስፖራው በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡
 • አያስቡ ሁሉም ነገር ተዘጋጅቷል ስልዎት?
 • በቃ ሊወርዱብኝ ነዋ?
 • እነማን?
 • እነሱ ናቸዋ፡፡
 • የለመድነው ነገር እኮ ነው? ብዙም አያስቸግርዎትም፡፡
 • አሁንስ ሰለቸኝ፡፡
 • ምኑ?
 • ስድብ፡፡
 • አያስቡ የሚያግዝዎት ሰዎች እዚያ ተዘጋጅተዋል፡፡
 • ለማንኛውም ልደውል?
 • ማን ጋ?
 • ወዳጄ ጋ፡፡
 • ይችላሉ፡፡

[ክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊያቸው ጋ ደወሉ]

 • አቤት ክቡር ሚኒስትር?
 • ለምንድን ነው ስልኩን የማታነሽው?
 • እንግዶች እያስተናገድኩ ነበር፡፡
 • የማን ጸሐፊ ነሽ?
 • ማለት?
 • የእንግዶቹ ነሽ? ወይስ የእኔ?
 • ኧረ የእርስዎ ነኝ፡፡
 • ይኼኔ እዚያ ፌስቡክ ላይ ሆነሽ ነው?
 • ኧረ አይደለሁም፡፡
 • እስቲ ደውዪ እና አገናኚኝ፡፡
 • ማንን?
 • ወዳጄን፡፡
 • የትኛውን?
 • ውጭ ያለውን ወዳጄን ነዋ፡፡
 • ይቅርታ ብዙ ወዳጅ አለዎት ብዬ ነው፡፡
 • አሁን ያልተጠየቅሽውን አትቀባጥሪ፡፡
 • እሺ ይቅርታ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ቶሎ በይ፡፡
 • እኔ የምለው ክቡር ሚኒስትር …
 • ውጭ ሊሄዱ ነው እንዴ?
 • አዎን ምነው?
 • አይ በየፌስቡኩ ላይ አይቼዎት ነው፡፡
 • እ…
 • አዎን ሊመጡ ነው፤ ተዘጋጁ ሲባባሉ ነበር፡፡
 • እነማን?
 • ዳያስፖራዎቹ፡፡
 • ወይ ጣጣ፡፡
 • ይቅናዎት እንግዲህ፡፡
 • አሁን ቶሎ ደውይልኝ፡፡
 • እሺ፡፡

[ክቡር ሚኒስትሩ ከወዳጃቸው ጋር በስልክ ተገናኙ]

 • ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንዴት ነህ ወዳጄ?
 • አለሁ፤ ሁሉ ሰላም ነው?
 • ልመጣ ነው፡፡
 • ምን?
 • እናንተ ጋ ልመጣ ነው፡፡
 • ምን ሊያደርጉ?
 • ለምርጫ ቅስቀሳ፡፡
 • ምርጫው እኮ አገር ቤት ነው ያለው፡፡
 • እዚያም ላሉት ዜጐች የግድ መደረግ አለበት ተብሏል፡፡
 • ይቅናዎት እንግዲህ፡፡
 • ምርቃቱን ተወውና እፈልግሃለሁ፡፡
 • ማንን? እኔን?
 • አዎን፡፡
 • ለምን?
 • እንድታግዘኝ ነዋ፡፡
 • አያስቡት ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምነው?
 • ፖለቲካ ትቻለሁ፡፡
 • ምነው?
 • እዚህ እኮ ሁሉ ነገር ከሯል፡፡
 • እንዴት ማለት?
 • በቃ ከፍተኛ ጥላቻ ነው ያለው፡፡
 • እኔ የምመጣው እኮ እንድንፋቀር ነው፡፡
 • ኧረ አይቀልዱ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እየቀለድኩ አይደለም፤ እውነቴን ነው፡፡
 • እኔ በየሶሻል ሚዲያው መሰደቡ ሰልችቶኛል፡፡
 • እ…
 • ቤተሰቦቼ ራሱ ተገልለዋል፡፡
 • እ…
 • ስለዚህ ፖለቲካ በቃኝ ብያለሁ፡፡
 • ምን ተሻለኝ?
 • አይምጡ፡፡
 • እ…
 • ይቅርብዎት፡፡
 • መምጣቴማ ግድ ነው፡፡
 • እንግዲያው አንድ ነገር ይቅርብዎት፡፡
 • ምን?
 • ሾፒንግ!