ክቡር ሚኒስትር

[ክቡር ሚኒስትሩ አማካሪያቸውን ቢሯቸው አስጠሩት]

 

 • እንዴት ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ዘመኑ የፌሽታ ነው፡፡
 • ሰሞኑን በበዓላት ተጨናነቅን፡፡
 • የካቲት እኮ እንደዚህ ነው፡፡
 • እንዴት ነው?
 • በቃ ታሪካዊ ወር ነው፡፡
 • ታሪካዊ ሲሉ?
 • የአድዋ በዓልን የምንዘክርበት፡፡
 • ጣሊያንን ከኢትዮጵያ ያባረርንበትን ነው የሚሉኝ?
 • ምን እሱ ብቻ?
 • ሌላ ደግሞ ምን አለ?
 • ዋናውን ረሳኸው እንዴ?
 • ዋናው ደግሞ ምንድነው?
 • እኛ የተወለድንበት ነዋ፡፡
 • በዚህ ወር ነው እንዴ የተወለዱት?
 • እኔም ለነገሩ በዚህ ወር ነው የተወለድኩት፣ ግን ያኛውን ነው ያልኩህ፡፡
 • የትኛውን?
 • ሕወሓትን ነዋ፡፡
 • እእእ….
 • በቃ የፌሽታ ወር ነው፡፡
 • ለነገሩ ፌሽታ የበዛ ይመስለኛል፡፡
 • ይብዛ እንጂ፡፡
 • ሌላም ፌሽታ ሳይኖር አይቀርም፡፡
 • ደግሞ ሌላ ምን ተገኘ?
 • አልሰማሁም እንዳይሉኝ ክቡር ሚኒስትር?
 • ኧረ በፍጹም፡፡
 • ከሁሉም የሚበልጠው ፌሽታ እንዲያውም ይኼኛው ሳይሆን አይቀርም፡፡
 • ኧረ ምን ሰምተህ ነው?
 • የሚወራውን አልሰሙም?
 • ምን ተወራ?
 • ሹመት አለ፡፡
 • ሹመት?
 • አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • የምን ሹመት?
 • ብቻ ቃል ይግቡልኝ?
 • ምን ብዬ?
 • ይዘውኝ እንደሚሄዱ፡፡
 • የት ነው የምሄደው?
 • ሲሾሙ ነዋ፡፡
 • እኮ የት ነው የምሾመው?
 • ለከፍተኛ ኃላፊነት መታጨትዎን ሰምቻለሁ፡፡
 • የምን ከፍተኛ ኃላፊነት?
 • እንጃ ግን ከፍተኛ መሆኑን ሰምቻለሁ፡፡
 • እየቀለድክብኝ ነው?
 • የምን ቀልድ አመጡ? እውነቴን ነው፡፡
 • ኧረ እንቅልፍ አትንሳኝ?
 • እስካሁን ይተኛሉ እንዴ?
 • እሱማ መቼም እንቅልፍ ኖሮኝ አያውቅም፡፡
 • ብቻ እንዳይረሱኝ?
 • ለምን እረሳሃለሁ?
 • ሲሾሙ፡፡
 • እንደ አፍህ ያድርግልኝ፡፡
 • ሆኖልዎታል፡፡
 • አሜን!

[የክቡር ሚኒስትሩ ወዳጅ ከውጭ አገር ደወለ] 

 • ሄሎ ክቡር ሚኒስትር!
 • ሄሎ!
 • እንዴት ሰነበቱ?
 • በጣም ደህና ነኝ፡፡
 • በዓል እንዴት ነው?
 • በጣም ደስ ይላል፡፡
 • እኔም ስላልቻልኩ ነው እንጂ መምጣት ፈልጌ ነበር፡፡
 • ብትመጣ ጥሩ ነበር፡፡
 • ምን አዲስ ነገር አለ?
 • ብዙ አዲስ ነገር አለ፡፡
 • እኮ ምን አለ?
 • ሹመት እየመጣ ነው፡፡
 • ሹመት ነው ያሉኝ?
 • አዎ ወዳጄ፡፡
 • በጣም ደስ ይላል፡፡
 • እናም የምትፈልገውን ነገር ይዘህ ና፡፡
 • ምን ችግር አለ?
 • አሁን ብዙ ነገር እያሰብን ነው፡፡
 • ምን ታስቧል?
 • የኢንዱስትሪ ዞን በየቦታው እያስገነባን ስለሆነ በዚያም ላይ መሳተፍ ትችላለህ፡፡
 • በጣም ደስ ይለኛል፡፡
 • ለአንተ ብቻ ሳይሆን ለሌሎቹም ዕድሉ አለ፡፡
 • አስተባብራለሁ በቃ፡፡
 • ታሪክ መሥራት አለብን፡፡
 • ልክ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ብዙ ሥራ ነው ያለው፡፡
 • በቻልነው መጠን እንሳተፋለን፡፡
 • ከሠራን ደግሞ ማደጋችን አይቀርም፡፡
 • እኔ የምለው ግን ክቡር ሚኒስትር…
 • ምን አልክ?
 • ባለፈው እኮ በቃኝ ብለውኝ ነበር፡፡
 • ምኑን?
 • ሥልጣን ላይ መቀመጥ ነዋ፡፡
 • ልሾም ነዋ፡፡
 • ቢሆንስ?
 • እኔ ሕዝቡን ማገልገል ደስ ይለኛል፡፡
 • በሕዝቡ መገልገል አሉኝ?
 • ኧረ ሕዝቡን ማገልገል ደስ ይለኛል ነው ያልኩት፡፡
 • ለነገሩ ከዚያ ውጪ ምን እርካታ አለ ብለው ነው?
 • ምንም ነገር የለም፡፡
 • በጣም ታላቅ ሰው ነዎት፡፡
 • በጣም አመሰግናለሁ፡፡
 • ለማንኛውም ስላሉኝ ጉዳይ በደንብ አስብበታለሁ፡፡
 • እሱ ላይ ፍጠን፤ ተረቱ እንዳይፈጸምብን፡፡
 • የቱ ተረት?
 • ሲሾም ያልበላ፣ ሲሻር ይቆጨዋል የሚለው ነዋ፡፡
 • እ…
 • ዕድል ካተጠቀምክባት ትበድልሃለች፡፡
 • አይደል?
 • እውነቴን ነው የምልህ፡፡
 • በቃ ክቡር ሚኒስትር አመሰግናለሁ፡፡
 • በል ቻው፡፡

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ ቤታቸው ከሾፌራቸው ጋር እያመሩ ነው፡፡ በመኪናው ውስጥ የተከፈተውን ሙዚቃ ያንጐራጉራሉ] 

 • ምን ተገኘ ክቡር ሚኒስትር?
 • ምነው?
 • በጣም ደስ ብሎዎታል፡፡
 • እንዴት ደስ አይበለኝ?
 • እኮ ምን ተገኘ?
 • አታይም እንዴ?
 • ምኑን?
 • ባቡር በል፣ ግድብ በል፣ መንገድ በል፣ ኧረ ስንቱን ልጥራ?
 • ምን ሆኑ?
 • ይህን ነገር ሁሉ ሠርተን ካልተደሰትን ሌላ በምን እንደሰት?
 • አይ የዛሬው ለየት ያለ ይመስላል፡፡
 • እንዴት?
 • ከቅድም ጀምሮ እያንጐራጐሩ ነዋ፡፡
 • እዚች አገር ላይ ያመጣነው ለውጥ እንኳን ማንጐራጐር አያስጨፍርም ወይ?
 • ለውጥ?
 • አዎና፣ ተመልከት እንጂ ዕድገቱን?
 • ዕድገቱ ግን ሁሉንም እኮ ያማከለ አይደለም፡፡
 • እንዴት ማለት?
 • ዕድገቱ የጠቀመው ከላይ ያሉትን ብቻ ነው፡፡
 • ከላይ ካልወረደ እንዴት ታች ይደርሳል?
 • አይደል?
 • ወይስ እንደ ካሮት ወደ ታች እንደግልህ?
 • አይ እንዲያው ይኼ ዕድገት ለእኛ መቼ ይደርሳል ብዬ ነው፡፡
 • አታስብ፣ እኛን ካረሰረሰ በኋላ ወደ እናንተ ይደርሳል፡፡
 • ይሁና፡፡
 • ለማንኛውም ተዘጋጅ፡፡
 • ለምኑ?
 • ለአዲሱ ሥራ፡፡
 • የምን አዲስ ሥራ?
 • አዲስ ሹመት እየመጣ ነው፡፡
 • መቼም ያኔም እኔን ይወስዱኛል?
 • ተዘጋጅ እኮ እያልኩህ ነው፡፡
 • መቼ ነው ሹመቱ?
 • ሁሉም እንቅስቃሴዬ ወደ ሹመት ነው የሚያመራኝ፡፡
 • አይደል?
 • መንገዶች ሁሉ ወደ ሮም ያመራሉ ብሏል አሪስጣጣሊስ፡፡
 • ይኼ አሪስጣጣሊስ ስለሁሉም ነገር ተናግሯል ማለት ነው?
 • ከእሱ ውጪ ማን ይላል ብለህ ነው?
 • ያው ሁሌም እሱን ስለሚጠቅሱት ብዬ ነው፡፡
 • አሁን ሌላ ነገር አትዘባርቅ፡፡
 • ይቅርታ ክቡር ሚኒስትር፡፡

[ክቡር ሚኒስትሩ ቤት ሲገቡ ባለቤታቸውን አገኙ] 

 • ሰላም ዋልክ?
 • ሁሉ ነገር ሰላም ነው፡፡
 • ምን ተገኘ ደግሞ?
 • ምን አጥቼ አውቃለሁ?
 • ዛሬ ደስ ያለህ ትመስላለህ፡፡
 • በጣም ደስ ብሎኛል፡፡
 • እኮ ምን ተገኘ?
 • ሹመት፡፡
 • ሹመት?
 • አዎን፣ ሹመት፡፡
 • እኮ የምን ሹመት?
 • አዲስ ሹመት ነዋ፡፡
 • በቃኝ አላልክም እንዴ?
 • ማን ሲበቃው አይተሻል?
 • ከራሳችሁ ፖሊሲ ጋር ይጋጫል ብዬ ነዋ፡፡
 • ከየትኛው?
 • ይኼ መነካካት ነው መተካካት ከምትሉት ጋር ነዋ፡፡
 • ይኸው ከአንድ ቦታ ወደ ሌላው እየተዘዋወርን አይደል እንዴ?
 • ቀየራችሁት ማለት ነው?
 • ምኑን?
 • ፖሊሲውን ነዋ፡፡
 • ከምን ወደ ምን?
 • ከመተካካት ወደ መዘዋወር!