ክቡር ሚኒስትር

[ክቡር ሚኒስትሩ ቢሯቸው ሆነው ዜና እየተከታሉ ነው፡፡ በአልጄዚራ የሚተላለፈውን ዘገባ ግን ማመን አቅቷቸዋል፡፡ ስልካቸውን አንስተው አማካሪያቸው ጋ ደወሉ]

 

 • ሄሎ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • የት ነው ያለኸው?
 • ቢሮ ነኝ፡፡
 • እያየህልኝ ነው?
 • ምኑን?
 • ዜናውን ነዋ፡፡
 • ምን ላይ?
 • አልጄዚራ ላይ፡፡
 • ኧረ ቲቪ አልከፈትኩም፡፡
 • አሁን በአፋጣኝ ቢሮ ና፡፡
 • እሺ፡፡

[አማካሪያቸው ቢሮ መጣ] 

 • ሥራህን ረሳኸው እንዴ?
 • ኧረ ሥራ እየሠራሁ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ታዲያ ዜናውን እንዴት አላየኸውም?
 • ያው ሥራ ላይ ስለነበርኩ ቲቪ አልከፈትኩም፡፡
 • አንተ ሥራ የለህም እያልከኝ ነው?
 • ኧረ በፍጹም፡፡
 • ሥራማ ትተሃል ማለት ነው?
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • መረጃ መሰብሰብ እኮ የሥራህ አንዱ ክፍል ነው፡፡
 • አውቃለሁ ክቡር ሚኒስትር ግን ሌላ አጣዳፊ ሥራ ይዤ ነው፡፡
 • በጣም እኮ ነው የሚገርመው?
 • ምን ዓይተው ነው?
 • ጉድ ሊያፈሉ ነው፡፡
 • እነማን?
 • እነዚህ አልጄዚራዎች፡፡
 • እንዴት?
 • ይኼው ሚስጥራዊ ዶክመንቶች ይፋ ሊያደርጉ ነው፡፡
 • ምን?
 • አዎን አሁን ማስታወቂያውን እያሳዩ ነበር፡፡
 • ወይ ጣጣ፡፡ የምን ዶክመንት ነው ያዩት?
 • ከእኛ የደኅንነት ቢሮ የወጣ ዶክመንት ነው፡፡
 • ዊኪሊክስ ነው እንዴ?
 • ኧረ ይኼ ሌላ ነው፡፡
 • ደግሞ ማን ነው?
 • ብቻ ከደቡብ አፍሪካ የወጣ ዶክመንት መሰለኝ፡፡
 • ሚስጥራዊ ነገር ነው?
 • ማስታወቂያው ላይ እንዳየሁት ገና ብዙ ጉድ ሊያወጡ ይችላሉ፡፡
 • ምን ተሻለ?
 • ይከሰሱ፡፡
 • እነማን?
 • አልጄዚራዎች፡፡
 • እ…
 • አዎ በቃ መክሰስ አለብን፡፡
 • የት ነው የምንከሳቸው?
 • ፍርድ ቤት ነዋ፡፡
 • የትኛው?
 • እኔ እንጃ ብቻ ይከሰሱ፡፡
 • እ…
 • እኔ እኮ የሚገርመኝ አንድ ነገር ነው፡፡
 • ምንድነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ልክ ጠብቀው ምርጫ ሲደርስ ነገር ይፈልጉናል፡፡
 • አይደል?
 • ከኒዮሊብራሊስቶች ድሮስ ምን ይጠበቃል?
 • ምንም፡፡
 • ስለዚህ ምን ይደረግ?
 • እኛም ፍርድ ቤት ቢሆን እንክሰሳቸው፡፡
 • ይመጣሉ ብለው ነው?
 • ተወካይ የላቸውም እንዴ?
 • እዚህ ተወካይ ያላቸው አይመስለኝም፤ ቢኖራቸውም ግን…
 • እሱን ብቻ አጣራልኝ እንጂ ካላቸውማ አለቀ፡፡
 • እንዴት?
 • በቃ እስር ቤት እንወረውረዋለን ከዛ ያርፉታል፡፡
 • እንደዚያማ ማድረግ አንችልም፡፡
 • እኔ የምለው አንተም ኒዮሊብራሊስት ነህ እንዴ?
 • አይ አይደለም፡፡
 • በቃ!
 • እሺ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ለመሆኑ የምን ሥራ ነው የያዝከው?
 • የምርጫ፡፡
 • እኮ የምርጫ ምን?
 • አይ ለቅስቀሳ እየተዘጋጀን ነው፡፡
 • ምን እየተሠራ ነው?
 • ያው እርስዎን ላማክርዎት አስቤ ነበር፡፡
 • እኔ እኮ የሚገርመኝ ያለኔ ሥራ አትሠራም እንዴ?
 • ያው ዳይሬክሽን እንዲሰጡኝ ብዬ ነው፡፡
 • ለነገሩ እኔም ይኼ ገብቶኝ ነው ያዘጋጀሁት፤ እንካ!
 • ምንድነው?
 • የምርጫ ቅስቀሳችን ስትራቴጂ፡፡
 • እሺ ምን ምን ታስቧል?
 • አንብበዋ?
 • እሺ፡፡
 • ጥያቄ አለህ?
 • አዎ፡፡
 • ቀጥል፡፡
 • በሞባይል ቴክስት ሜሴጅ መላክ ይላል፡፡
 • አዎን፡፡
 • ቲሸርትም እናሳትማለን?
 • እንዲቀር ፈለግክ?
 • ኧረ በፍጹም፡፡
 • ታዲያ ምንድነው?
 • ቢልቦርዶችና ፖስተሮችም እናሳትማለን፡፡
 • ችግር አለ?
 • አይ ጥያቄ አለኝ፡፡
 • እኮ ምን?
 • እነዚህን ነገሮች ለማስፈጸም ከፍተኛ በጀት ነው የሚያስፈልገን፡፡
 • ሰባት ሚሊዮን አባላት እንዳሉን አትርሳ፡፡
 • በአባላት መዋጮ ነው የሚሠራው?
 • በፍፁም፤ የአባላት መዋጮ ለሌላ ነገር ነው የሚውለው፡፡
 • ታዲያ በምንድነው የሚሠራው?
 • እኔ እኮ ትገርመኛለህ፡፡
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • ስንቱ አይደል እንዴ የሚለምነው?
 • ምን እያለ?
 • በልማቱ መሳተፍ እንፈልጋለን እያለ፡፡
 • እ…
 • ይህቺን አገር እኛ ከመረከባችን በፊት የነበረችበትን አስታውስ፡፡
 • እ…
 • አሁን የግሉ ዘርፍ የደረሰበትን ተመልከት፡፡
 • በእርግጥ የግል ዘርፉ አድጓል፡፡
 • አገሩ ሁሉ ባንክና የቢዝነስ ተቋም ሆኗል አይደል እንዴ?
 • ታዲያ ቢሆንስ?
 • ጠይቃቸዋ፡፡
 • ምን?
 • ለቅስቀሳው ማስፈጸሚያ በጀት፡፡
 • ምን?
 • ምን አትበለኝ፡፡ ሁሌም በልማቱ ካልተሳተፍን የሚሉት ራሳቸው ናቸው፡፡
 • ይህ እኮ ልማት አይደለም፡፡
 • ምን አልክ?
 • የምርጫ ጉዳይ ነው፡፡
 • ለሕዝቡ የሚበጀውን የምናውቀው እኛ ነን፡፡
 • ኧረ ይኼ አካሄድ አያዋጣንም ክቡር ሚኒስትር?
 • ይኼን ዲስኩርህን እዚያው አረቄ ቤት አውራ፡፡
 • እ…
 • እንዲያውም የምትጠይቀውን ዋጋ ልንገርህ፡፡
 • እሺ፡፡
 • ከፍተኛ ገንዘብ የሚያንቀሳቅሱትን አንድ አንድ ሚሊዮን ጠይቅ፡፡
 • እሺ፡፡
 • መለስተኛ ገንዘብ የሚንቀሳቀሱትን 500 ሺሕ ጠይቅ፡፡
 • እሺ፡፡
 • አነስተኛ ገንዘብ የሚንቀሳቀሱትን 100 ሺሕ ጠይቅ፡፡
 • እሺ፡፡
 • አሁኑኑ ደብዳቤው ይዘጋጅ፡፡
 • የትኛው?
 • ለድርጅቶቹ የሚጻፈው፡፡
 • ግን ክቡር ሚኒስትር…
 • ግን የሚል ነገር ከዚህ በኋላ መስማት አልፈለግም፡፡
 • እሺ ክቡር ሚኒስትር፡፡

[ክቡር ሚኒስትር ቤት ሲገቡ ባለቤታቸው ቴሌቪዥን ሲመለከቱ አገኟቸው] 

 • ምን እያየሽ ነው?
 • አልጄዚራ፡፡
 • ይኼን ቲቪ አጥፊልኝ፡፡
 • ለምን?
 • የኒዮሊብራሊስት ጣቢያ ነው፡፡
 • እ…
 • አዎን እኛን ለማጥፋት የተነሱ ናቸው፡፡
 • ኧረ ተው፡፡
 • በቃ አጥፊልኝ፡፡
 • የፕሬስ ነፃነት እያልክ ትደሰኩራለህ አይደል እንዴ?
 • እነዚህ የእኛ ጠላቶች ናቸው፡፡
 • እንዴት?
 • አስተላለፉት እንዴ?
 • ምኑን?
 • የሚስጥራዊ ዶክመንቶቹን ጉዳይ?
 • እስካሁን ምንም አላየሁም፡፡
 • ለመሆኑ ውጭ ያስቀመጥነው ገንዘብ እንዴት ነው?
 • ምን ማለት ነው እንዴት ነው?
 • በማን ስም ነው ያለው?
 • በልጃችን ስም ነዋ፡፡
 • አሜሪካ ባለችው ነው?
 • አዎን፡፡
 • ባንኩ እንዴት ነው?
 • አልገባኝም፡፡
 • መቼም መረጃ አሳልፈው አይሰጡም አይደል?
 • ምነው ፈራህ?
 • ለምን አልፈራ?
 • ተው አላልኩህም ነበር?
 • ለምንድነው የምተወው?
 • ብቻ ለእኛም እንዳትተርፍ፡፡
 • እ…
 • አሁን ከአልጄዚራ ጋር ይኼ ምን አገናኘው?
 • ሚስጥራዊ ዶክመቶችን ይፋ አደርጋለሁ እያለ ነው፡፡
 • ምን?
 • አዎን፡፡
 • ከየት የመጡ?
 • እኔም ብዙ አላውቅም፡፡
 • ፈርተህ ነው?
 • ለምን?
 • እንዳያጋልጡህ፡፡
 • ምን ብለው?
 • አባ ኮራፕት!