ክቡር ሚኒስትር

[ክቡር ሚኒስትሩ ጠዋት ቢሮ ውለው ምሳ ለመብላት ከሾፌራቸው ጋር ወደ ቤት እያመሩ ነው፡፡ በመንገዳቸው ላይም አዲስ የተመረቀውን የባቡር መንገድ እያዩ ስለነበር ከሾፌራቸው ጋር ወሬ ጀመሩ]

 

 • አየኸው?
 • ምኑን ክቡር ሚኒስትር?
 • አሁን እዚህ ጋ ምን ሌላ ነገር ይታያል?
 • አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር?
 • አሁን ምን ይታይሃል?
 • አሮጌ ቤቶች፡፡
 • እ…
 • የተቆፋፈረ መንገድ፡፡
 • ወይኔ?
 • ትራንስፖርት አጥቶ የተሠለፈ ሕዝብ፡፡
 • እኔ ጠፋሁ?
 • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ይኼ ብቻ ነው የሚታይህ?
 • ልቀጥል ክቡር ሚኒስትር?
 • በቃህ!
 • ይቅርታ ክቡር ሚኒስትር፡፡ ምነው ተቆጡ?
 • እንዴት አልቆጣ?
 • ኧረ ምን አጠፋሁ?
 • ልማታዊ ትመስለኝ ነበር?
 • አይደለሁም እንዴ?
 • አንተማ አፍራሽ መሆንህን ዛሬ አወቅኩ፡፡
 • እንዴት አወቁ?
 • በቃ ዕይታህ አፍራሽ መሆኑ ያስታውቃል፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር፣ ‹‹ምን ታያለህ?›› አሉኝ፡፡ እኔ ያየሁትን ነገርኩዎት፡፡ ታዲያ ምኑ ነው ጥፋቴ?
 • ዓይንህ አፍራሽ ነው ልበል?
 • ደግሞ ከሰውነት ክፍላችንም አፍራሽና ልማታዊ የሆነ አለ ማለት ነው?
 • በሚገባ እንጂ?
 • እንግዲህ ይቅርታ፡፡
 • አሁን ይኼ የባቡር ሐዲድ አይታይህም?
 • ይታየኛል እንጂ፡፡
 • ታዲያ ቀድመህ እሱን እንዴት አልጠራኸውም?
 • ለዚያ ነው አፍራሽ ነህ ያሉኝ?
 • አፍራሽ መሆንህንማ ዛሬ አወቅኩ፡፡
 • ያው ይኼ ባቡር ስላማረረኝ እኮ ነው፡፡
 • ቢያማርርህም አሁን እኮ ይኸው ተጠናቀቀ፡፡
 • እኔም መጠናቀቂያውን ቀን በጉጉት እየጠበቅኩ ነው፡፡
 • ባለፈው ተመረቀ አይደል?
 • ማለቴ ሙሉ ለሙሉ የሚያልቅበትን ጊዜ ማለቴ ነው፡፡
 • በጥቂት ወራት ይጠናቀቃል፡፡
 • እስቲ እናያለን፡፡
 • እስካሁን አላመንክም ማለት ነው?
 • ያው ረጅም ጊዜ ስላሰቃየኝ፣ የሚጠናቀቅበት ቀን ናፍቆኝ ነው፡፡
 • ስነግርህ አትሰማም እንዴ?
 • ግን እንደታሰበው የከተማዋን የትራንስፖርት ችግር ይቀርፋል?
 • ምን ጥያቄ አለው?
 • እኔንም ገላገለኛ፡፡
 • ከአሁን በኋላማ አንተም ምን እንደሚውጥህ እናያለን፡፡
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • የማርፈድ ሰበብህ ሊቀር ነዋ፡፡
 • ለምን ይቀራል?
 • ይኸው ባቡሩ ሥራ ሊጀምር ነዋ፡፡
 • የባቡሩ ሥራ መጀመር ቢያስደስተኝም፣ የኃይል ጉዳይ ግን አሁንም ያሳስበኛል፡፡
 • ለምን?
 • እየመጣሁ መሀል ላይ ኃይል ቢቋረጥስ?
 • ስለእሱ አታስብ፡፡
 • መቼም ተሳፋሪው ወርዶ አይገፋው?
 • መሳለቅህ ነው?
 • ኧረ በፍጹም፡፡
 • ለማንኛውም ከአሁኑ አስብበት፡፡
 • እርስዎ ግን ባቡሩን ይጠቀማሉ?
 • ማን እኔ?
 • አዎና ምን አለበት?
 • እየቀለድክ ነው?
 • ኧረ እውነቴን ነው፡፡ እንዲያውም ባለፈው ሬዲዮ ላይ ስሰማ የጉግል መሥራች ባቡር ይጠቀማሉ እኮ?
 • እነሱ ኒዮ ሊብራሊስቶች ስለሆኑ ተዋቸው፡፡
 • እ…
 • ባቡሩን የሠራነው ለሕዝቡ ነው፡፡
 • እርስዎም የሕዝቡ አካል ነዎት ብዬ ነው፡፡
 • ለእኔ ቪ8 ይበቃኛል፡፡
 • እሺ፡፡

[ክቡር ሚኒስትሩ ቤታቸው ሲደርሱ ባለቤታቸው ጋዜጣ እያነበቡ ነበር] 

 • ምን እያደረግሽ ነው?
 • ምን እያደረኩ ይመስልሃል?
 • ማለቴ ምን ዓይነት ጋዜጣ ነው የምታነቢው?
 • የአገራችንን ጋዜጣ ነዋ፡፡
 • እኮ የትኛው?
 • ይኼው፡፡
 • እኔ የምልሽ?
 • ምንድነው የምትለኝ?
 • የሚኒስትር ሚስት መሆንሽን ትረሽዋለሽ ልበል?
 • አልገባኝም?
 • ለምንድነው የግል ጋዜጣ የምታነቢው?
 • ምን?
 • ሰምተሻል፡፡
 • አንተ ግን የምር ሚኒስትር ነህ?
 • ትጠራጠሪያለሽ እንዴ?
 • አሁን ልጠራጠርህ ነው፡፡
 • ለምን?
 • እንዴት ጋዜጣ አታንብቢ ትለኛለህ?
 • እኔ የግል ነው ያልኩት?
 • ቢሆንስ?
 • እነሱ አፍራሾች ናቸዋ?
 • ተሳስተሃል፡፡
 • እንዴት?
 • እናንተው አይደላችሁ እንዴ ሚዲያው ሊያድግ ይገባል እያላችሁ ዲስኩር የምታሰሙት?
 • ሚዲያውማ ማደግ አለበት፡፡
 • እንዴት ይደግ?
 • አገር ስታድግ ሚዲያውም ያድጋል፡፡
 • ይኸው አታንብቢ እያልከኝ?
 • እኔ የመንግሥትን አንብቢ ነው ያልኩት፡፡
 • ስማ ሚዲያ አራተኛው መንግሥት መሆኑን አታውቅም?
 • ይኼ እባክሽ የኒዮ ሊብራሊስቶች አመለካከት ነው፡፡
 • አትሳሳት፣ ሚዲያ መንግሥትና ሕዝብን የሚያገናኝ ድልድይ መሆኑን አትርሳ፡፡
 • እነዚህ ግን አፍራሾች ናቸው፡፡
 • ሥራችሁን ስለሚገመግሙና ለሕዝብ ስለሚያቀርቡ ነው አይደል እንደዚህ የምትለው?
 • የምንሠራውንማ አይዘግቡም፡፡
 • እኔ ይኼን ጋዜጣ በደንብ እከታተለዋለሁ፤ እወደዋለሁም፡፡
 • እ…
 • ለምን እንደሆነ ታውቃለህ?  
 • አላውቅልሽም፡፡
 • የሠራውን ሠራ ይላል፤ ሌባውንም ያጋልጣል፡፡
 • አየሽ አመለካከትሽን በርዞታል፡፡
 • እንዴት?  
 • በቃ አፍራሽ ሆነሻል፡፡
 • ዝም ብለህ በጭፍን አትመራ፡፡
 • እ…
 • ገደል ውስጥ እንዳትገባ፡፡
 • አሁን ጭቅጭቁን ትተሽ ምሳ አስቀርቢልኝ፡፡
 • ያው ቀርቧል፡፡
 • አንቺ አትበይም?  
 • ይኸው እየበላሁ ነው፡፡
 • ምን? ጋዜጣ?  
 • የራበኝ ሆዴን ሳይሆን ጭንቅላቴን ነው፡፡
 • ዛሬ ተነስቶብሻል፡፡
 • በል ሁለታችንም እንብላ፡፡

[ክቡር ሚኒስትሩ ቢሮ ገብተው ከአማካሪያቸው ጋር ወሬ ጀመሩ] 

 • ምን ይደረግ ነው የሚሉት?  
 • እነማን ናቸው ክቡር ሚኒስትር?  
 • እነዚህ ተቃዋሚዎች ናቸው፡፡
 • ምን አሉ ክቡር ሚኒስትር?  
 • እንዴት ነው ምርጫ ቦርድ ገለልተኛ አይደለም የሚሉት?  
 • እነሱ ብቻ አይደሉም እኮ ገለልተኛ አይደለም እያሉ ያሉት፡፡
 • ደግሞ ሌላ ማን አለ?  
 • ሕዝቡም፡፡
 • እ…
 • አዎ ምርጫ ቦርድ ለእኛ የሚጠቅመውን ፓርቲ የመምረጥ ሥልጣን የለውም እያለ ነው፡፡
 • ምርጫ ቦርድ ፍጹም ገለልተኛ ነው፡፡
 • ምን አሉኝ?  
 • ገለልተኛ ነው፡፡
 • ገለልተኛም ብቻ ሳይሆን ሆደ ሰፊም ነው፡፡
 • ማለት?  
 • ይኸው እንደዚህ ሲተች ዝም ማለቱ ሆደ ሰፊነቱን በሚገባ ያሳያል፡፡
 • ታዲያ ይህ ምርጫ ቦርድ ሆደ ሰፊ ብቻ ነው መባሉ አያንሰውም?  
 • ተቃዋሚዎችማ ሌላ ነው የሚሉት፡፡
 • እንዴት?  
 • ይኸው ምርጫ ቦርድ ሆደ ሰፊ ሆኖ ብዙ ፓርቲዎችን እየዋጠ ነው ይላሉ፡፡
 • አሁን ቢከሰሱ ደግሞ ሌላ ጣጣ ነው፡፡
 • ለምን ይከሰሳሉ?  
 • እንደዚህ እየተሳደቡ?  
 • የመናገር መብት ግን ያላቸው መሰለኝ?  
 • ማን ፈቀደላቸው?  
 • ሕገ መንግሥቱ ነዋ፡፡
 • ቢፈቀድላቸውም፣ ፈር ሲለቁ ዝም ማለት የለብንም፡፡
 • ያለበለዚያማ ምኅዳሩ ይጠባል?  
 • ሲሰፋ ሊውጠን ነው ይላሉ፣ ሲጠብ ተጨነቅን ይላሉ፣ ግራ አጋቡን እኮ?
 • ትዕግሥት ይጠይቃል፡፡
 • ለመሆኑ አሁን ምን ሊያደርጉ ነው?  
 • እነማን?  
 • ምርጫ ቦርድ ዕውቅና የነሳቸው፡፡
 • አልሰሙም እንዴ?  
 • ምኑን?  
 • በሌላ ባርኔጣ መጡ እኮ? 
 • በምን ባርኔጣ?  
 • በሰማያዊ፡፡
 • ከሰማይ ነው ያልከኝ?  
 • ያው ነው በሰማይ ቀለም መጥተዋል፡፡
 • ከሰማይም ይምጡ ከምድር፣

መቼም እንደ እኛ አይሠሩም ባቡር፡፡

 • ወቸ ጉድ?