[ክቡር ሚኒስትሩ እሑድ ቀን ከቤታቸው ሊወጡ ሲሉ ልጃቸው አገኘቻቸው]

[ክቡር ሚኒስትሩ እሑድ ቀን ከቤታቸው ሊወጡ ሲሉ ልጃቸው አገኘቻቸው]

 • ወዴት እየሄድክ ነው ዳዲ?
 • ዘመድ ልጠይቅ፡፡
 • ምን ዓይነት ልብስ ነው የለበስከው?
 • ያው ዊኬንድ ስለሆነ ቱታ ነዋ ያደረኩት፡፡
 • እኔ የጠየቅኩህ ቀለሙን ነው?
 • ቀለሙማ እንደምታይው አረንጓዴ ነው፡፡
 • እሱ ነዋ ችግሩ፡፡
 • ይኼ ቀለምማ ችግር የለውም፡፡
 • በጣም አለው እንጂ፡፡
 • አረንጓዴ ለምን እንደምለብስ ታውቂያለሽ?
 • ለምንድን ነው የምትለብሰው?
 • አገሪቷ እየለመለመችና እያደገች ስለሆነ እሱን ላመላክት ነዋ፡፡
 • እየለመለመች?
 • አዎና፡፡
 • ድርቅ ገብቷል እየተባለ ሲወራ አልነበር እንዴ?
 • እ…
 • ለማንኛውም ዛሬ የሚለበሰው አረንጓዴ ሳይሆን ቀይ ነው፡፡
 • ለምን ተብሎ?
 • ቫላንታይንስ ዴይ ነዋ፡፡
 • ምንድን ነው ደግሞ እሱ?
 • የፍቅረኛሞች ቀን፡፡
 • መንግሥት የሚያከብረው ቀን ነው?
 • ኧረ በመላ ዓለም የሚከበር ነው፡፡
 • የኒዮሊብራሎች በዓል ነው አትይኝም ታዲያ?
 • እኔ እሱን አላውቅም፡፡
 • ለመሆኑ ቀኑ ምንድን ነው?
 • ፍቅረኛሞች ፍቅራቸውን የሚገልጹበት ቀን ነው፡፡
 • ምን ማለት ነው?
 • በቃ አንዳቸው ለአንዳቸው ፍቅራቸውን በዚህ ቀን ይገልጻሉዋ፡፡
 • በሌሎቹ ቀኖች ጥላቻቸውን ነው የሚገልጹት ማለት ነው?
 • እንደ እሱ ማለቴ አይደለም ዳዲ፡፡
 • ለነገሩ ተይው በዚህ በተወደደ ፍቅር በዓመት አንዴ እንኳን ሰው መዋደዱ ቀላል አይደለም፡፡
 • ለማንኛውም ዳዲ ዛሬ አንተም ማሚን እራት መጋበዝ አለብህ፡፡
 • ቤት ምግብ የለም እንዴ?
 • ነገርኩህ እኮ ዛሬ የፍቅረኛሞች ቀን ነው አልኩህ፡፡
 • ለእኔና ለእናትሽ ሁሉም ቀን የፍቅረኛሞች ቀን ነው፡፡
 • ለማንኛውም እኔ የቤቱን ዕቃ ቀለም ልቀይረው ነው፡፡
 • የቱን ዕቃ?
 • መጋረጃውን፣ ሶፋውን፣ ብቻ ሁሉንም ነገር፡፡
 • ምን ዓይነት ቀለም ልታደርጊው?
 • ቀይ ነዋ፡፡
 • እንግዲህ እንደፈለግሽ፡፡
 • እኮ ዳዲ አንተም ቱታህን ቀይረዋ፡፡
 • ምን ላድርግ?
 • ቀይ ቱታ፡፡
 • ለነገሩ ከቀይ ቀለም ጋር ችግር የለብኝም፡፡
 • ስለዚህ ትቀይረዋለህ?
 • አንቺን ካስደሰተሽ እቀይረዋለሁ፡፡
 • ታንኪው ዳዲ፡፡
 • የማልቀይረው ሌላ ዓይነት ቀለም ቢሆን ነበር፡፡
 • ምን ዓይነት ቀለም?
 • ሰማያዊ!

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚስታቸው ጋር ሆነው ቴሌቪዥን እየተመለከቱ ነው] 

 • ለምንድን ነው አንተ ዜና ላይ የማትቀርበው?
 • ምን ሠራሁ ብዬ?
 • ምንም እየሠራህ አይደለም እንዴ?
 • የዕለት ተዕለት ሥራዬን ነዋ እየሠራሁ ያለሁት፡፡
 • እኮ እሱም ቢሆን ለምን በዜና አይቀርብም?
 • ዜና እኮ አዲስ ነገር መሆን አለበት፡፡
 • ከመቼ ጀምሮ?
 • ሁሌም ቢሆን እንደዚህ ነው፡፡
 • ዛሬ ስከታተል አልነበር እንዴ ዜና?
 • እና ምን አየሽ?
 • ይኸው የአንተ ጓደኛ የቴሌቪዥን ጣቢያውን ጐበኙ ተብሎ አይደል እንዴ ዜና የተሠራላቸው?
 • እ…
 • ለዛውም መክፈቻ ዜና ነው፡፡
 • ምን ችግር አለው ታዲያ?
 • ጣቢያው እኮ የሕዝብ ነው፡፡
 • ማን አይደለም አለ?
 • አትመጻደቁ እባካችሁ?
 • እንዴት ማለት?
 • ጣቢያው ከዚህ በፊት የደርግ ፕሮፓጋንዳ መንፊያ ነበር ትላላችሁ፡፡
 • እና አልነበረም?
 • አሁንስ ምንድን ነው?
 • የሕዝብ ድምፅ የሚሰማበት ጣቢያ ነዋ፡፡
 • ኧረ ሰው እንዳይሰማህ?
 • ቢሰማስ ምን ያመጣል?
 • ይኼ ነገራችሁ እኮ ነው ችግር እየፈጠረ ያለው፡፡
 • እንዴት?
 • ሰው እንደማትሰሙ አውቆ በግድ እንድትሰሙ ያደርጋችኋላ፡፡
 • ምን ለማለት ፈልገሽ ነው?
 • ያልኩት በደንብ ስለገባህ ማብራራት አያስፈልገኝም፡፡
 • ከፀረ ሰላም ኃይሎች ጋር ገጥመሻል ማለት ነው?
 • በእናትህ እነዚህን ልማታዊ ቃላት ከመደርደር የሕዝቡን ድምፅ በሚገባ ብታዳምጡ መልካም ይመስለኛል፡፡
 • የሕዝቡን ድምፅ አታዳምጡም እያልሽኝ ነው?
 • ብታዳምጡማ ይኼ ሁሉ ባልተፈጠረ፡፡
 • የተቃዋሚዎቹን ጣቢያ ማዳመጥ ጀመርሽ እንዴ?
 • ሰውዬ እውነቱን ለምን ትሸሻለህ?
 • ለመሆኑ እውነቱ ምንድን ነው?
 • አሁን ጥሩ ጥያቄ አነሳህ፡፡
 • እኮ ንገሪኛ?
 • ሕዝቡን ካዳመጥክ እውነቱን ታገኛለህ፡፡
 • ሕዝቡንማ እያዳመጥነው ነው፡፡
 • እያላመጥነው ነው ያልከኝ?
 • የለም የለም፤ እያዳመጥነው ነው፡፡
 • ብታዳምጡትማ ይኼ ሁሉ ባልመጣ፡፡
 • ይኼ ሁላ ምን?
 • ብጥብጥ!

[ክቡር ሚኒስትሩ ቢሮ እንደገቡ አማካሪያቸውን አስጠሩት] 

 • አቤት ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምን ወሬ አለ?
 • ወሬ መቼ ይጠፋል ክቡር ሚኒስትር?
 • ለነገሩ የሚሠራ ሰው ነው ያጣነው፡፡
 • የሚሠራም አይጠፋም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ለማንኛውም ወሬውን ንገረኝ እስቲ?
 • ነጋዴዎች ደስተኞች አይደሉም፡፡
 • ደግሞ ለምን?
 • በዚህ በኤልሲ ጉዳይ ነዋ፡፡
 • ይኸው አንበሸበሽናቸው አይደል እንዴ?
 • አይ ብሔራዊ ባንክ አዲስ መመርያ አውጥቷል እኮ፡፡
 • የምን መመርያ?
 • በአንድ ጊዜ በተለያዩ ባንኮች ኤልሲ መክፈት አይቻልም የሚል መመርያ ወጥቷል፡፡
 • ለምን?
 • ፍትሐዊ የሆነ የውጭ ምንዛሪ ክፍፍል እንዲኖር ነዋ፡፡
 • ፍትሐዊ የሆነ የሀብት ክፍፍል ሳይኖር ይኼ እንዴት ሊሆን ይችላል?
 • ጥሩ ነጥብ ነው ያነሱት፡፡
 • እና አሁን ባንዴ ከአንድ ባንክ የምንጠይቀውን የውጭ ምንዛሪ ይሰጡናል?
 • ክቡር ሚኒስትር እርስዎ ይጠይቃሉ እንዴ?
 • ማለቴ ነጋዴዎች የሚጠይቁትን ይሰጧቸዋል?
 • እሱን የምናየው ጉዳይ ይሆናል፡፡
 • ለመሆኑ እኛን ለማጥፋት ነው እንዴ ቆርጠው የተነሱት?
 • እኛን ሲሉ አልገባኝም፡፡
 • ማለቴ ነጋዴዎችን ሊያጠፉ ማለቴ ነው፡፡
 • እንደዛ እንኳን አይመስለኝም፡፡
 • አለቀልን በለኛ፡፡
 • እርስዎ ነጋዴ ሆነዋል እንዴ?
 • ማለቴ አለቀላቸው ልልህ ፈልጌ ነው፡፡
 • አይ ራስዎትን እያስገቡ ሲያወሩ ግራ ገብቶኝ ነው፡፡
 • ያው ነጋዴዎች እኮ የእኛው አካል ናቸው ብዬ ነው፡፡

[ክቡር ሚኒስትሩ አንድ ነጋዴ ጋ ደወሉ] 

 • ከየት ተገኙ ክቡር ሚኒስትር?
 • ምንድን ነው የምሰማው እባክህ?
 • ምን ሰምተው ነው?
 • የኤልሲውን ጉዳይ፡፡
 • ቆየ እኮ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ታዲያ ምንድን ነው የምናደርገው?
 • መላ መቼ ይጠፋል ብለው ነው?
 • ምንድን ነው መላው?
 • በቃ 17 ኩባንያዎች መሥርቶ በየባንኩ ወረፋ ማስያዝ ነዋ፡፡
 • የምን ወረፋ?
 • የዶላር!

[ክቡር ሚኒስትሩ ወዲያው ሚስታቸው ጋ ደወሉ] 

 • እስቲ የምታምኛቸው ስንት ዘመዶች አሉሽ?
 • ምን እያልከኝ ነው?
 • የጠየኩሽን ለምን አትመልሺም?
 • ምን ሊያደርጉልህ?
 • በስማቸው ድርጅት ለመክፈት፡፡
 • ሁለት እህቶች አሉኝ፡፡
 • ሌላስ?
 • አገር ቤት ደግሞ ሁለት የአክስቶቼ ልጆች አሉ፡፡
 • በቃ በአስቸኳይ ይምጡ፡፡
 • ለምን?
 • በስማቸው ድርጅት እንከፍታለን፡፡
 • ያለን ድርጅት አይበቃንም?
 • እነዚህኞቹን ድርጅቶች ለሠልፍ ነው የምንፈልጋቸው?
 • ለሠልፍ?
 • አዎን፡፡
 • ተጣላህ እንዴ ሰውዬ?
 • የምን ጥል ነው?
 • ሰላማዊ ሠልፍ ተከልክሏል ብዬ ነዋ፡፡
 • አልገባሽም እባክሽ፡፡
 • ለነገሩ ሰላማዊ ያልሆነው ሠልፍ የበዛው ሰላማዊው ስለከተለከለ ይመስለኛል፡፡
 • እስቲ ፖለቲካውን ትተሽ በአስቸኳይ በዘመዶችሽ ስም አራቱ ድርጅቶች ይከፈቱ፡፡
 • ምን ያደርጉልናል?
 • ወረፋ ይይዛሉ፡፡
 • የምን ወረፋ?
 • የዶላር ወረፋ!

[አንድ ዳያስፖራ ለክቡር ሚኒስትሩ ደወለላቸው] 

 • ክቡር ሚኒስትር አንድ ሐሳብ ነበረኝ፡፡
 • የምን ሐሳብ?
 • አንድ ተቋም የመክፈት፡፡
 • የምን ተቋም?
 • የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋም፡፡
 • በአገሪቷ ውስጥ ምንም ዓይነት የሰብዓዊ መብት ችግር የለም፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር የእርስዎን ድፍረት እኮ አንበሳ ራሱ የሚቀናበት ይመስለኛል፡፡
 • ምን እያልከኝ ነው?
 • አገሪቱ በሰብዓዊ መብት ችግር የተንበሸበሸች አይደለች እንዴ?
 • ምን ይላል ይኼ?
 • ብቻ ይተውት፡፡
 • ለማንኛውም ችግሩ ቢኖርም በውጭ ገንዘብ እዚህ ላይ መሥራት አይቻልም፡፡
 • እኔ እኮ የምልዎት ሌላ ነገር ነው፡፡
 • በቃ ጨርሻለሁ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር…
 • ጢጢጢ…

[ዳያስፖራው መልሶ ደወለ] 

 • ክቡር ሚኒስትር…
 • አንተ ሰውዬ ለምን አተወኝም?
 • እኔ የምልዎት ሌላ ነው፡፡
 • ምንድን ነው የምትለኝ?
 • ማቋቋም የምፈልገው ተቋም ለውሾች የሰብዓዊ መብት የሚሟገት ነው፡፡
 • ለውሾች?
 • አዎን ለውሾች፤ ውሾች አሉን አይደል እንዴ?
 • ያውም ብዙ ውሾች ነዋ፡፡
 • ተቋሙ መጠለያ ለሌላቸው ውሾች፣ ጐዳና ለወጡ ውሾች፣ አሳዳጊ ለሌላቸው ውሾች መብት የሚሟገት ነው፡፡
 • ሥራ ፈተሃል ልበል?
 • ትልቅ ሥራ ይዤ ነው እንጂ የመጣሁት፡፡
 • እንዴት?
 • ክቡር ሚኒስትር ይኼ ጠቀም ያለ ዶላር የምናገኝበት ሥራ ነው፡፡
 • ዶላር?
 • አዎና ክቡር ሚኒስትር፣ ጠቀም ያለ ፈንድ እናገኝበታለን፡፡
 • በቃ የተቋሙ የበላይ ጠባቂ እሆናለዋ፡፡
 • ለዛ አይደል እንዴ አደዋወሌ?
 • ወይ ኒዮሊብራሎች እኛ ለሰው ዶላር አጥተናል እነሱ ለውሻ ይሰጣሉ?
 • ዶላር በሽበሽ ነው አልኩዎት እኮ፡፡
 • ዶላር ካለውማ እንኳን የውሻ መብት ተሟጋች የሌላም መክፈት ትችላለህ፡፡
 • የሌላ የምን?
 • የዝንብ!