ከአሥር ዓመት በኋላ ዕውቅናና ሽልማት ያገኘው የአክሱም ሐውልት አስመላሽ ኮሚቴ

በሻሂዳ ሁሴን

የጥንታዊት ኢትዮጵያን ሥልጣኔ ከሚያንፀባርቁ ቅርሶች መካከል የአክሱም ሐውልት ቀዳሚው ነው፡፡ ሌሎችም የጥበብ ሥራዎች ይጠቀሳሉ፡፡ ይሁንና በተለያዩ ጊዜያት በውጭ ኃይሎች ተሰርቀው ከአገር የወጡ በርካታ ቅርሶች ሲኖሩ ጥቂቶቹ ደግሞ ተመልሰዋል፡፡ ከእነዚህም ከተመለሱት መካከል የአገሪቱ የሥልጣኔ አሻራ የሆነው የአክሱም ሐውልት ይገኝበታል፡፡

ሐውልቱ ከአገር የወጣው በፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ (1928 - 1933) ጊዜ ነበር፡፡ በኢጣሊያንና በኢትዮጵያ መካከል በተደረገ የአምስት ዓመታት ጦርነት ፋሽስቶች የተለያዩ ግፎችን ፈጽመዋል፣ ልዩ ልዩ ቅርሶችና ንብረቶችም ዘርፈዋል፡፡ ከሦስቱ የአክሱም ሐውልቶች መካከል አንደኛውን ዘርፎ ወደ አገሩ የወሰደውም በዚሁ ወቅት በ1929 ዓ.ም. ነበር፡፡ አገሪቱ ከድል በኋላ በርካታ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ምሁራን፣ ዲፕሎማቶች፣ አምባሳደሮች፣ ታዋቂ ግለሰቦችና አርቲስቶች ይህንን ኃይልን መሠረት ተደርጐ የተፈጸመ ድርጊትን በመቃወም ሐውልቱ ወደ ነበረበት ለማስመለስ ጥረት አድርገዋል፡፡

በ1983 ዓ.ም. የአክሱም ሐውልት አስመላሽ ኮሚቴ ተመሥርቶ በተደራጀ መልኩ ቅርሱን የማስመለስ ጥረት ተጀምሮም ነበር፡፡ እንቅስቃሴው ከመቼውም ጊዜ ጠንካራ ነበር፡፡ በአፍሪካ አንድነት ድርጅትም ዕውቅና አግኝቶ ነበር፡፡ ድርጅቱ ሐውልቱ እንዲመለስ ድጋፍ እንዲያደርግ ጠንካራ ግፊት ይደረግበትም ነበር፡፡ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ግን ከ1985 ዓ.ም. ጀምሮ ጉዳዩን በበላይነት የኢትዮጵያ መንግሥት ይከታተለው ጀመር፡፡ የቴክኒክ አጥኚ ኮሚቴ በማቋቋምም ወደ ተግባር እንዲገባ ተደረገ፡፡

ነሐሴ 30 ቀን 1988 ዓ.ም. ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በተጻፈ ደብዳቤ ለማስታወቂያና ባህል ሚኒስቴር ሐውልቱን ለማስመለስ የሚረዳ ብሔራዊ አስተባባሪ አካል እንዲቋቋም በተጠየቀው መሠረት፣ ሐውልት አስመላሽ ብሔራዊ ኮሚቴ ተቋቋመ፡፡ ከዓመታት በኋላም የተቋቋመበት ዓላማም ሰምሮ በሮም አደባባይ ከስድስት አሠርታት በላይ የቆመው የአክሱም ሐውልት በታኅሣሥ 1996 ዓ.ም. ወደ አገሩ ሊገባ ቻለ፡፡

በወቅቱ ሐውልቱን አገር ቤት ለማስገባት በተቋቋመው ኮሚቴ አባል ከነበሩት መካከል አቶ ታደለ ዓለምሰገድ ይገኙበታል፡፡

‹‹የአክሱም ሐውልት አስመላሽ ብሔራዊ ኮሚቴ አባል ሆኜ የተመረጥኩት ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተመርጬ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ምርጫውን ተቀብለው በጻፉልኝ የአባልነት ደብዳቤ ነበር፤›› የሚሉት አቶ ታደለ፣ ሐውልቱን ለማስመለስ ከባድ ፈተናዎች እንደነበሩና ስምንት ዓመታት ፈጅቶ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ በወቅቱ የበዓል ዝግጅት ኮሚቴ ምክትል ሊቀመንበር ሆነው ይሠሩ ነበር፡፡ በተለያዩ ክልሎች ተዘዋውሮ ቅስቀሳ የማድረግ ሥራ በተለይ በአማራ ክልል በባህርዳርና በጐንደር ሠርተዋል፡፡

‹‹ነገሮች ሁሉ አስቸጋሪ ነበሩ፡፡ ይመጣል አይመጣም የሚል ጥርጣሬ የነበረባቸው ሰዎችም ነበሩ፡፡ ነገር ግን አንዳንዶች ‹ከተጠራ ውሻ ያልቀጠሩት ቀን ይፈጥናል› እያሉ ተስፋ ሳንቆርጥ እንድንሠራ ያበረቱን ነበር፤›› ሲሉ ሐውልቱ ወደ አገሩ እንዲመለስ ለማድረግ የነበረውን ውጣ ውረድ ያስታውሳሉ፡፡

የአቶ ታደለና የሌሎች የብሔራዊ ኮሚቴው አባላት ጥረት የአክሱምን ገጽታ ምሉዕ አድርጎታል፡፡ ለዚህም ግንቦት 27 ቀን 2008 ዓ.ም. በብሔራዊ ቤተ መንግሥት በተዘጋጀ የእራት ፕሮግራም ላይ አገራዊ እውቅናና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡

በዕለቱ የክብር እንግዳ የነበሩት ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ በመክፈቻ ንግግራቸው፣ ሌሎች ከአገር ውስጥ የተወሰዱ ቅርሶችን ለማስመለስ በሚደረጉ ጥረቶች ሁሉ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በትጋት መሥራት ግድ እንደሚል አሳስበዋል፡፡

በአገራዊ እውቅናና በሽልማት ፕሮግራሙ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ጨምሮ ሌሎች ለሐውልቱ መመለስ ጥረት ያደረጉ የኮሚቴው አባላትና ባለሀብቶች ተካተዋል፡፡   

ፕሮግራሙ የተዘጋጀው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በሰጠው ውሳኔ መሠረት ሲሆን ያዘጋጀው ደግሞ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከብሔራዊ ቤተ መንግሥት ጋር በመተባበር ነው፡፡