እልቂቱን ከማውገዝ ከማልቀስም ያለፈ ዕርምጃ

በዚህ ሰሞን የኢስላማዊ መንግሥት አቀንቃኞች (አይኤስ) በወገኖቻችን ላይ የፈጸሙት እልቂት ከህሊና በላይ ነው፡፡ በእምነታቸው ብቻ አንገታቸው እንዲሰየፍ፣ በጥይት ተደብድበው እንዲገደሉ መደረጉ የሰዎቹን እምነት የለሽነትና እንስሳዊነት የሚያሳይ ነው፡፡ ሐዘኑ ብዙ ነገሮችን እንድናስብ አድርጎናል፡፡

ዓለም አቀፍ ሚዲያ ኢትዮጵያዊነታቸውን ለይቶ ማፅናኛ ሲልክ፣ እንስሳውም የገደልኩት ጠላቴ የሆኑትን ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖችን ነው ባለበት ወቅት፣ የመንግሥት የመጀመርያው መግለጫ የዜጎቹን ማንነት አለማወቁ መሆኑ አስገርሞናል፡፡ ሕዝቡ መንግሥትን ቀድሞ ሲያዝን በየኤሌክትሮኒክስ ሚዲያው ሕዝብ ቁጣውን ሲገልጽ፣ አራት ኪሎ ላይ ስብሰባ ተጀመረ፡፡ ፓርላማውም ብሔራዊ የሐዘን ቀን፣ ቤተክህነቱም ጸሎትና ፍትሐቱን አስከተሉ፡፡

 የሕዝብ ሠልፍ በመስቀል አደባባይ ሲደረግም ሕዝቡ በቁጭትና በሐዘን ድርጊቱን ለማውገዝ ተመመ፡፡ በዕለቱ ከሐዘን ይልቅ የፀረ ሽብርተኝነት ዲስኩር የመንግሥት መገናኛ ብዙኃንን አጨናንቆ ዋለ፡፡ ፀረ ስደት መፈክሮች በብዛት ተስተጋቡ፡፡ ኩነቱ በሽብርተኝነትና ከሕገ ወጥ ስደት ጋር መያያዙ አመክንዮው ትክክል ቢሆንም ዕለቱ ግን የሐዘን ቀን በመሆኑ፣ ሕዝቡን በማፅናናት ላይ ብቻ ማተኮር ነበረበት፡፡ ለዚህ ነው የሠልፉ ፍጻሜም ያላማረው፡፡ መንግሥትና ለመኖራቸው ብቸኛ ዋቢ ራሱ መንግሥት የሆነላቸው ተቃዋሚዎች ዕለቱን ከዓላማው ውጭ አዋሉት፡፡ ሐዘኑ ተረስቶ መንግሥት ለሁከቱ ተጠያቂው ሰማያዊው፣ አስራችኋለሁ ወዘተ. በማለት ንትርክ ውስጥ መግባቱ የዜጎችንም ዋጋ ያሳጣል፣ የፖለቲካ ኪሳራውም ቀላል አይሆንም፡፡

ከእንዲህ ዓይነት ሕዝቡን ወዳልተፈለገ መስመር ከሚወስድ ንትርክ መንግሥትም ሆነ ሌላ ባለድርሻ አካላት ለዜጎቻችን ሊሠሯቸው ስለሚገቡ ነገሮች ቢያስቡ የተሻለ ነበር፡፡ በተለይ መንግሥት መንግሥትነቱ በተግባር የሚረጋገጠው ለዜጎቹ ያለበትን ግዴታ ሲወጣ፣ የዜጎቹን መሠረታዊ ችግር ከፖለቲካ ስሌት በወጣ መልኩ በማሰብ መፍትሔ ለማበጀት ሲጥር ነው፡፡ ሁሌም እንደሚባለው መንግሥት ሲሄድ መንግሥት ይተካል፡፡ የማይሄደው ሁሌም የሚኖረው ሕዝብ ነውና ለሕዝብ ጥቅም መሠረታዊ የሆኑ ብሔራዊ ችግሮች ላይ ወጥሮ መሥራት ሕገ መንግሥታዊ ግዴታ ነው፡፡ በዚህ ረገድ አይኤስ (Islamic State) ለፈጸመው ግፍ ምን ዓይነት ሕጋዊ የበቀል ዕርምጃ ሊወሰድ ይችላል? ዜጎች አገራቸውን ትተው በየአቅጣጫው የሚያስኮበልላቸው መሠረታዊ ችግር ምንድን ነው? በውጭ ያሉቱ ለተመሳሳይ አረመኔያዊ ድርጊት ሰለባ እንዳይሆኑ ከመንግሥት ምን ይጠበቃል? የሚሉትን የሌሎቹን አገሮች ተሞክሮ ጭምር መነሻ በማድረግ ምልከታ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡

ከአገር የመውጣት ችግር

ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ክፍሎች አደጋ በደረሰ ቁጥር ሰለባዎች ሆነዋል፡፡ በዚህ ሰሞን እንኳን በሊቢያ፣ በደቡብ አፍሪካና በየመን ባሉ ቀውሶች ኢትዮጵያውያን ተገድለዋል፣ ተጎድተዋል፣ ተዘርፈዋል፡፡ አንድ ሰው ከአገር የሚወጣው ወይ ኑሮውን ለማሻሻል በማሰብ ስደተኛ (Migrant) ሆኖ አልያም የሰብዓዊ መብት ረገጣ ደረሰብኝ ብሎ ጥገኝነት (Asylum) ለመጠየቅ ነው፡፡ በዚህ ረገድ በሁለቱም አኳኋን የአገራችን ዜጎች በስደት ሲንከራተቱ እናስተውላለን፡፡ ጥገኝነት የሚጠይቁት የተሻለ ኑሮ (ሕይወትን ለማቆየት) ከሚሰደዱት አኳያ ቁጥራቸው አነስተኛ ቢሆንም፣ ከዚህ ሁሉ ግን አገር ለዜጎቿ እንድትመች መሠረታዊ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ሕይወትን ለመለወጥ ለሚሄዱትም ከተቻለ አገራቸው ላይ ተመቻችተው እንዲሠሩ ነገሮችን ማመቻቸት፣ ካልሆነ ደግሞ በሚሄዱበት አገር የሰብዓዊ መብታቸው ተጠብቆ የመንግሥት ጥበቃ ሳይለያቸው የሚሠሩበትን መንግድ መፍጠር ግድ ነው፡፡

በዚህ ረገድ ችግሩን ለመለየት መንግሥት ብሔራዊ ጥናት በማድረግ ሁሉንም ያሳተፈ ውይይት ሊያደርግ ይገባል፡፡ ባለፈው ጊዜ ከተለያዩ የዓረብ አገሮች በተለይም ከሳዑዲ ዓረቢያ ተባረው የወጡ ዜጎችን በአግባቡ ለማቋቋም የተጀመረው እንቅስቃሴ ወቅታዊ ብቻ ሳይሆን በዘላቂነት ሊሠራበት ይገባል፡፡ የውጭ የሥራ ግንኙነትን ለማስተዳደር እየተረቀቀ ያው ሕግ በሕዝቡ ሰፊ ውይይት ተደርጎበት ለዜጎች የተመቸ መሆኑ ሊረጋገጥ ይገባል፡፡ መንግሥት በያመቱ እፈጥራቸዋለሁ የሚላቸው የሥራ ዕድሎች ለሁሉም ያለምንም መድልዎ የሚዳረሱ፣ በቁጥርና በዓይነት እየጨመሩ መሄዳቸውም በተግባር የሚረጋገጥበት ሥርዓት መፈጠር ይኖርበታል፡፡

እስላማዊ መንግሥትን የመታገል ፈተና

በዚህ ሰሞን ሕዝቡ ከሚያንፀባርቃቸው ሀሳቦች አንዱ ግብፅ እንዳደረገችው መንግሥት ለምን አይኤስን አይዋጋም? አይኤስን ለማጥፋት ከሚሠሩ አገሮች ጋር አይተባበርም የሚለው አንዱ ነው፡፡ በዚህ ረገድ መንግሥት በግልጽ ያስቀመጠው (ለሕዝብ የገለጸው) ነገር ባይኖርም ጉዳዩ መንግሥት ዜጎችቸን ከሚጠብቅባቸው መንገዶች አንዱ በመሆኑ ቸል ሊባል የማይገባው ነው፡፡ አይኤስን መዋጋት፣ ምንጩን ማድረቅ፣ ለአክራሪነት የተጋለጡ ኩነቶችን አጥንቶ ዕርምጃ መውሰድ ወዘተ. መንግሥት ሊያስበው ከሚገባው መፍትሔ አንዱ ነው፡፡ ኤይኤስን ሊቢያ ድረስ ሄዶ የመዋጋት ሀሳብ ከዓለም አቀፍ ሕግ ፈቃጅነት፣ ከአቅምና ከውጤታማ ስትራቴጂ መረጣ ጋር የሚያያዝ ሲሆን፣ በጉዳዩ ላይ የተለያዩ አቋሞች ሲንፀባረቁ ይስተዋላሉ፡፡

  ለምሳሌ በፋና የመረጃ መረብ አስተያየታቸውን የሰጡትና ዶ/ር ምፅላል ክፍለኢየሱስ የተባሉ የወታደራዊ ሳይንስ ባለሙያ፣ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ኢትዮጵያዊ በአይኤስ ላይ ወታደራዊ ዕርምጃ ለመውሰድ እንደሚከብዳት ይገልጻሉ፡፡ እንደርሳቸው ገለጻ ‹‹ኢትዮጵያ እንደ አንድ አገር በሌላ አገር ወታደራዊ ዕርምጃ የምትወስደው ድንበሯ ሲነካባት ነው፡፡ ከሰሞኑ የተፈጸመው ጥቃት ግን በአሸባሪ ቡድኑ እንጂ በሊቢያ መንግሥት በኢትዮጵያውያን ላይ የተቃጣ ባለመሆኑ፣ አገሪቱ በቀጥታ በሊቢያ ላይ ዕርምጃ እንዳትወስድ ያደርጋታል፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ከደኅንነት ሥጋት አንፃር ዓለም የተስማማበት ሥጋት በግዛትና በመከላከያ ኃይል ላይ የተደቀነ ሥጋት ሲኖር ነው፤ ኢትዮጵያ ውጭ ባሉ ዜጎቼ ላይ የደኅንነት ሥጋት ተፈጥሯል ብትል እንኳን በሰዎች ላይ የተፈጠረ የደኅንነት ሥጋት ለጦርነት እንደ መንስዔ ተደርጎ አይቆጠርም፤›› ሲሉ ነው  ዶ/ር ምፅላል አብራርተዋል፡፡

የአይኤስ ተጠቂ የሆኑ አገሮች ከወሰዱት ዕርምጃ አኳያ ከተነሳን ግን ወታደራዊ ዕርምጃ መውሰድ የአቅም ፀጥያቄ ተግዳሮት ካልሆነ በቀር፣ ዓለም አቀፍ ሕግን በመተርጎም አቋሙን መደገፍ ይቻል ይሆናል፡፡ እንደሚታወቀው ዜጎቻቸው ተጠቂ የሆኑባቸውና የእስላማዊ መንግሥትን አረመኔያዊ ሥራ የሚቃወሙ መንግሥታት አይኤስን ለመዋጋት ጊዜ አልወሰዱም፡፡ በዚህ ረገድ አሜሪካን፣ ካናዳን፣ አውስትራሊያንና ግብፅን ለአብነት መውሰድ ይቻላል፡፡ እነዚህ አገሮች ብሔራዊ የመንግሥት አካላቸውን ከማስፈቀድ ባለፈ ዓለም አቀፍ ሕግ ወደ ኋላ አላስቀራቸውም፡፡ የዓለም አቀፍ ሕግ ደካማነት (ልዕለ ኃያላን አገሮች ለራሳቸው እንዲጠቅማቸው እየረጉ የሚጠቀሙበት/የሚጥሱት) እንደተጠበቀ ሆኖ እነዚህ አገሮች ለድርጊታቸው የዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት አልነበራቸውም ወይም የላቸውም ማለት አይቻልም፡፡

እንደሚታወቀው የተባበሩት መንግሥታት ቻርተር፣ አገሮች በሌሎች አገሮች ክልልና ፖለቲካዊ ሉዓላዊነት ላይ ኃይል መጠቀምን አይፈቅድም፡፡ የዚህ ክልከላ ልዩ ሁኔታ ሁለት ምክንያቶች ናቸው፡፡ የመጀመርያው የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት አገሪቱ ኃይል እንደትጠቀም ሲፈቅድ ወይም በተባበሩት መንግሥታት ቻርተር አንቀጽ 51 መሠረት ከመጣ ኃይል (መንግሥት) ራስን ለመከላከል ሲባል ብቻ ኃይል መጠቀም ሊፈቀድ ይችላል፡፡ አሜሪካ ጉዳዩን ለፀጥታው ምክር ቤት ብታቀርብ ውሳኔን በውሳኔ የመሻር መብቷ ሩህያ ላትፈቅድላት ስለምትችል፣ ራስን የመከላከል ምክንያትን ተጠቅማለች፡፡ በዚህ ረገድ አሜሪካ በግል ወይም በጋራ ራስን መከላከል መሠረት አድርጋ ልትከራከር ትችላለች፡፡ በዚሁ መሠረት የተረጋጋ መንግሥት በሌለባቸው እገዳ ኢራቅ ያሉ አገሮች ራሳቸውን ለመከላከል ባለመቻላቸው የተነሳ በአሸባሪዎች ላይ ዕርምጃ በመውሰድ ራሷን ለመከላከል ትችላለች፡፡ ይህ የሙግት መስመር እጅጉን አከራካሪ መሆኑን ከተለያዩ ምሁራዊ ጽሑፎች መረዳት ይቻላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሚላና ስቴሮ የተባሉ ምሁር ሁለት የአሜሪካ ዜጎች በእስላማዊ መንግሥት መገደላቸው አሜሪካ በተባበሩት መንግሥታት ቻርተር አንቀጽ 51 መሠረት የጦር ጥቃት  ዜጎች ላይ መፈጸሙ ራሴን ለመከላከል ምክንያት ሆኖኛል ለማለት እንደሚያስችላት ይከራከራሉ፡፡ ሆኖም ይኼ አቋም ራስን መከላከል ከሉዓላዊ አገሮች አንፃር እንጂ ከሌሎች ቡድኖች አንፃር ባልተደነገገው ቻርተር ትርጉም የሚያዋጣ ላይሆን ይችላል፡፡

ከእነዚህ ሙግቶች አንፃር ለአገራችን ወታደራዊ ዕርምጃ አማራጭ ከሆነ፣ መቻኰል እንዳይኖር የዓለም አቀፍ ሕግ ምሁራን ሊመክሩበት ይገባል፡፡ የተለመደውና ጤነኛው አካሄዱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አሻባሪ ቡድኑ ላይ ዕርምጃ እንዲወሰድ ሊቢያ የውሳኔ ሐሳብ እንድታመንጭና እንዲያፀድቅ መጠየቅ ሊሆን ይችላል፡፡ ሊቢያ ባልተረጋጋችበት ሁኔታ ይህ ጥያቄ በአገሪቷ ሊቀርብ እንደማይችል ቢታመንም፣ የወታደራዊ ሳይንስ ባለሙያዋ ዶ/ር ምፅላል ክፍለእየሱስ ያህንን ሐሳብ ይደግፋሉ፡፡ የሰላምና ደኅንነት ምርምር ባለሙያው አቶ አበበ አይነቴ ግን ለፋና በሰጡት አስተያየት ኢትዮጵያ ከሊቢያ ጋር ካላት ጂኦግራፊያዊ ርቀት አንፃር ኢትዮጵያ በቀጣናው ግብፅን ከመሰሉና የአይኤስ ሰለባ ከሆኑ አገራት ጋር ተባብራ የቡድኑን መስፋፋት መግታት መፍትሔ ነው ብለው ያስቀምጣሉ፡፡

ውስጣዊ ብቃትን የማጠናከር የቤት ሥራ

የአይኤስ ሰለባ የሆኑ ዜጎች በአገራችን መሠረት እንዲያገኙ፣ ተቻችሎ የመኖር ባህላችን ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማድረግ ሌላው መንግሥት ሊያጠናክረው የሚገባው የቤት ሥራ ነው፡፡ የሃይማኖት አክራሪነት የአገራችን የቅርብና ዋና ፈተና መሆኑን የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር በየዓመቱ በአፅንኦት የሚናገረው ሲሆን፣ በቅርብ ታሪካችንም አይተነዋል፡፡ በጅማ ከተማ በክርስቲያኖች ላይ የደረሰው ጭፍጨፋ ለዚህ ዓቢይ ማሳያ ነው፡፡ ችግሩ የትልቅነቱን ያህል ግን በቂና ጠንካራ፣ ሕጋዊና ተቋማዊ ለውጥ ካላደረግን በቀር የውጭ ኃይሎች ተፅዕኖ ወደፊት እንዳይፈትነን ሥጋት አለ፡፡ ከሕገመንግሥቱ በተጨማሪ የሃይማኖትና የመንግሥት መለያየትን በዝርዝር የሚደነግግ ሕግ መቅረፅ፣ በተለያዩ ጊዜያት የተከሰቱ ጉዳዮች ላይ ሕዝቡ ግንባቤ እንዲያገኝ ማድረግ ለዘመናት ይዘናቸው የመጣናቸውን የመቻቻል ባህሎች የማጠናከር ሥራ ከመንግሥት፣ ከሃይማኖት ተቋማትና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅ ይሆናል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የሕግ ጠበቃና አማካሪ ሲሆኑ፣ በኢሜይል አድራሻቸው getukow [at] gmail.com  ማግኘት ይቻላል፡፡