ኢ ፍትሐዊ አሠራር በመልሶ ማልማት ፕሮጀክት

በከተማችን አዲስ አበባ ምቹ የመኖሪያ አካባቢ ለመፍጠር የተጎሳቆሉ የከተማዋን ክፍሎች መልሶ የማልማት እንቅስቃሴ ከተጀመረ ዓመታት አስቆጥሯል፡፡ መልሶ ማልማት ከተካሄደባቸው አካባቢዎች መካከል የልደታ፣ የባሻ ወልዴ ችሎት፣ እንዲሁም የሰንጋ ተራ መልሶ ማልማቶች ለአብነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅትም በከተማችን በተለያዩ ክፍለ ከተሞች የመልሶ ማልማት እንቅስቃሴዎች እየተካሄዱ ሲሆን፣ ከሚኖሩበት ቦታ ለሚነሱ ነዋሪዎች የሚስተናገዱበት ወጥ የሆነ የሕግ አግባብ መኖሩ ይታወቃል፡፡

ሆኖም በአስፈጻሚ አካላት በኩል ሕጉ በተደጋጋሚ በግልጽ የሚጣስበት ሁኔታ ይታያል፡፡ እነዚህ የሕግ ጥሰቶች ከሚታዩባቸው አካባቢዎች አንዱ ከተክለሃይማኖት እስከ ዲአፍሪክ ሆቴል ድረስ በሚካሄደው የመልሶ ማልማት ፕሮጀክት ውስጥ ነው፡፡

የኮንዶሚኒየም አሰጣጡ በነዋሪዎች ምርጫና አንድ ወጥ በሆነ አካሄድ ላይ የተመሠረተ አይደለም፡፡ ሲጀመርም ነዋሪዎች በአንድ ዓይነት ዕይታ አይታዩም፡፡ ለግማሹ እንደ ምርጫው፣ ማለትም ባለ ሦስት መኝታ ቤት ለመረጠው ባለሦስት መኝታ ቤት ሲሰጥ ለግማሹ ባለሁለት ውሰዱ፣ አልወስድም ካላችሁ ባለአንድ እንድትወስዱ ይደረጋል በማለትና በማስፈራራት በኃላፊዎች ጫና ያለምርጫቸው እንዲወስዱ ተደርገዋል፡፡ በወቅቱ ባለሦስት መኝታ ቤት በየሳይቱ ባለበት ተጨባጭ ሁኔታ ቤቶቹ የሉም ብሎ መደምደሙ እጅግ በጣም የሚያሳዝን ነው፡፡ ለምሳሌ መካኒሳ ቆጣሪ ተብሎ በሚጠራው ሳይት ውስጥ ባለሦስት መኝታ ክፍሎች እንደነበሩ ለመጥቀስ ይቻላል፡፡

ሌላው እንቆቅልሽ የሆነው አሠራር ደግሞ በአንድ ቀን በተመሳሳይ ወቅት ፎርም የሞሉና ከቤቶች ኤጀንሲ ቤት ተከራይተው ከሚኖሩ ነዋሪዎች መካከል የተወሰኑት ብቻ ተመርጠው ዕጣ እንዲያወጡ ያውም ያለምርጫቸው እንዲስተናገዱ ሲደረግ፣ ቀሪዎች ግን ይኸው ከዓመት በላይ ቆይተውም ዕጣ እንዲያወጡ አልተደረገም፡፡ ዕጣ ካወጡትም መካከል እንደገና የተወሰኑት ተመርጠው በቀደመ ምርጫቸው መሠረት ባለሦስት መኝታ ክፍል እንዲሰጣቸው ጥረት እየተደረገ መሆኑ ታውቋል፡፡

 ይህ ሁኔታ ሲታይ የተወሰኑ ነዋሪዎችን ብቻ ለይቶ በቅድሚያ ለማንሳት ታስቦ የተደረገ አካሄድ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡

ይህም አሠራር መንግሥት በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ከሚያካሂደው መልካም አስተዳደርን የማስፈን እንቅስቃሴ ጋር የሚቃረን ስለሆነ፣ የሚመለከታቸው አካላት ተገቢ የእርምት ዕርምጃ በመውሰድ የመልሶ ማልማቱ ሥራ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ እንዲከናወን ቢያደርጉ የተሻለ ነው፡፡

(ሰለሞን አምባቸው፣ ከአዲስ አበባ)

* * *

በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ስለሐዋሳ ጨርቃ ጨርቅ የቀረበው ዘገባ እውነታውን አያሳይም

ከአንድ ዓመት በፊት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ስለሐዋሳ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ አንዲት ጋዜጠኛ ባቀረበችው ዘገባ፣ ‹‹ፋብሪካው ወደ ግል ይዞታ ከተዛወረ በኋላ እጅግ ውጤታማ መሆኑንና ቀደም ሲል ለሠራተኛው ደመወዝ እንኳን መክፈል ያልቻለበት ሁኔታ እንደነበር አሁን ግን ሠራተኛው ተጠቃሚ መሆኑንና ፋብሪካው ከሁለት ወራት በኋላ ምርቱን ለውጭ ገበያ እንደሚያቀርብ…›› በማለት የሠራችው ዘገባ በፋብሪካው ሥራ አስኪያጅ መገለጹ ይታወሳል፡፡

በዕለቱ በቴሌቪዥን ይታዩ የነበሩት የፋብሪካው የማምረቻ መሣሪያዎች የፈትል ክፍሉን ብቻ የሚያሳዩ ነበሩ፡፡ በወቅቱ በሽመናና በማጠናቀቂያ ክፍል ከአገልግሎት ውጪ የነበሩ ማሽኖች ካሜራ ዕይታ ውስጥ እንዲገቡ አልተደረጉም፡፡ ለመሆኑ ምርቱን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ በዝግጅት ላይ ነኝ ያለውና በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የተሞካሸው ፋብሪካ ዛሬ በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል?

በአሁኑ ወቅት የሐዋሳ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ የሽመናና የማጠናቀቂያ ክፍሉ ተዘግቶ ሠራተኛው ሥራ ካቆመ ከአምስት ወራት በላይ ሆኖታል፡፡ ፋብሪካው የኤሌክትሪክ ኃይል ፍጆታ 17 ሚሊዮን ብር ባለመከፈሉ ከመብራት ኃይል ጋር ፍጥጫ ውስጥ ይገኛል፡፡ ፋብሪካው በአሁኑ ወቅት ለውጭ አገር ገበያ አይደለም ለአገር ውስጥ እንኳን አንድ ሜትር ጨርቅ ማምረት ያልቻለበት ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ ስለሆነም ዛሬ ሊዘጋ ቀናትን የሚጠብቅና ሠራተኛው ሊበተን በሥጋት ላይ ያለውን የዚህን ፋብሪካ ዘገባ፣ የውስጡን ጉድ በመሸፋፈን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ለምን ለሕዝብ አቀረበው?

(ማቴዎስ ሽመሎ፣ ከሐዋሳ)

* * *

ኪራይ ስብሰባ በአርባ ስልሳም

መቼም የቤት ነገር ሲነሳ እንደሚታወቀው በዚህች አገር እንደ ሦስተኛ ዜጋ ሆኖ የሚኖረው በግለሰቦች ቤት ተከራይቶ የሚኖር ሰው ነው፡፡ ይህን ለማለት ያበቃኝ በመንግሥት፣ በቀበሌ ቤት፣ እንዲሁም በግለሰብ ቤት ተከራይቶም ተመድቦም የሚኖረው ሁሉም የዚህች አገር ዜጋ በመሆኑ ነው፡፡ ግን ልዩነታቸው የሰማይና የመሬት ነው፡፡

በመንግሥት ቤት የሚኖረው ላለፉት 40 ዓመታት አንድም የኪራይ ጭማሪ ሳይደረግበት ነፃ በሚያሰኝ ኪራይ ይኖራል፡፡ ኧረ እንደውም አንዳንድ ቀበሌዎች አካባቢ ከሰሞኑ ያየሁት ማስታወቂያ ለረጅም ዓመታት የቤት ኪራይ ያልከፈሉ ግለሰቦች ስማቸው ተለጥፎ ልመና ቀረሽ በሆነ መልኩ እንዲከፍሉ ያሳስባል፡፡ አንዱ የማውቀው ግለሰብ የተለጠፈው ውዝፍ የቤት ኪራይ የብዙ ዓመታት ሲሆን፣ እኔ በወር የምከፍለው ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ እሱ ተለምኖ ይከፍለዋል እኔ ደግሞ ወር በገባ በሁለተኛው ቀን ስንት ግልምጫ ደርሶብኝ እከፍላለሁ፡፡ ይኼ ነው እንግዲህ የዜግነት ልዩነት፡፡ ወደ ዋናው ቁም ነገሬ ልመለስና ይኼን የግለሰቦች ቤት ኪራይን ስቃይ ለመገላገል ስል የዛሬ ሁለት ዓመት ከስምንት ወር በፊት በ40/60 ቤቶች መርሐ ግብር ተመዝግቤ ያለችኝን ጥሪት እንደምንም አድርጌ 100 በመቶ በመክፈል እየተጠባበቅሁ እገኛለሁ፡፡ የሚሠሩትንም ሕንፃዎች ምን ላይ ደረሱ እያልኩ ሁሌ እቃኛቸዋለሁ፡፡ ከሰዎችም ጋር ስለቤቶቹ አወራባቸዋለሁ፡፡ ከጉጉት የተነሳና በአንድ ወቅት ደላላ ልበለው ኪራይ ሰብሳቢ ወይም አቀባባይ ምን ይለኛል 100 በመቶ መክፈል ቤት ቢዝነስ አለው አለኝ፡፡ ዕጢዬ ዱብ አለና እንዴት ብለው ቅድሚያ ለማግኘትና ዕጣው ውስጥ ለመካተት ቅብብሎሽ አለው አለኝ ምን ስለው ‹‹ገንዘብ›› አለኝና በጣም ገርሞኝ ኪራይ ሰብሳቢም በአርባ ስልሳም ገብተዋል አልኩኝ፡፡ እንግዲህ ይህ ነገር ትክክለኛ ይሁን አይሁን፣ ይፈጸም አይፈጸም ወደፊት የምናየው ይሆናል፡፡

ይኼን ካለኝ አሁን ወደ ሁለት ወር ተኩል ይሆነዋል፡፡ በጊዜው በጣም አሳስቦኛል፡፡ ኪራይ ሰብሳቢዎች የማይገቡበት ጓዳ ጐድጓዳ የለም፡፡ እና የቤቶች ኤጀንሲና ገንዘብ አደራ ብለን የሰጠንህ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም ከእነዚህ ኪራይ ሰብሳቢዎችና አቀባባዮች ተጠንቅቃችሁ አምነን የሰጠናችሁን ጥሪት በሙሉ እምነትና ፍትሕ በሚወጣው ዕጣ መሠረት ቤቶቹን እንድታከፋፍሉን አደራ ስል አሳስባለሁ፡፡    

(ተስፋዬ አበበ፣ ከአዲስ አበባ)

* * *

በዘገባው የተላለፈው ሐሳብ የእኔ አይደለም

በሚያዝያ 23 ቀን 2008 ዓ.ም. የሪፖርተር ጋዜጣ ዕትም በፖለቲካ ዓምድ ‹የኮምፒዩተር ወንጀል አዋጅ ሥጋቶች› በሚል ርዕስ በወጣው ጽሑፍ በረቂቁ አዋጅ ላይ የሠራሁትን ጥናት አንድ ቦታ ላይ የተጠቀሰው ያላግባብ ነው፡፡ ‹‹አቶ ሀለፎም በረቂቁ አዋጅ ባደረጉት ምርመራ የዜጐች መብትን የሚፃረሩ አንቀጾችን ለይተዋል፡፡ ከላይ የተጠቀሱት ድንጋጌዎችና ሌሎችም ሕገ መንግሥታዊ ከሆነው የመናገር ነፃነት ጋር በቀጥታ የሚጋጩ በመሆናቸው፣ ወንጀል የሚሆኑት በምን ሁኔታ እንደሆነ በጥልቀት በረቂቁ መብራራት ሲገባው፣ ጥቅል ሆኖ መቅረቡ ለትርጉም የተጋለጠ ያደርገዋል ብለዋል፤›› ተብሎ የተጻፈው የእኔ ሐሳብ እንዳልሆነ ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡

(ሀለፎም ኃይሉ አብርሃ፣ የሳይበር ሕግና ፖሊሲ ተመራማሪና

በኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ የሕግና ፖሊሲ ጉዳዮች

ምክትል ዳይሬክተር)