አገር በቀሉ ብረት ፋብሪካ ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ ጨረታ አሸነፈ

- የአዲስ አበባ ቁጠባ ቤቶች ከሦስት ቢሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ ብረት ለመግዛት ተዘጋጅቷል

የአዲስ አበባ ቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ ላወጣው 220 ሺሕ ቶን የብረት ግዥ ጨረታ፣ ዝቅተኛውን ዋጋ በማቅረቡ ሲ እና ኢ ወንድማማቾች የተባለው አገር በቀል ብረት አምራች ኩባንያ አሸናፊ መሆኑ ታወቀ፡፡

ኩባንያው ለጨረታ ከቀረበው ጠቅላላ የብረት መጠን ውስጥ ከ126 ሺሕ ቶን በላይ በ2.2 ቢሊዮን ብር ለማቅረብ መዘጋጀቱን ለመረዳት ተችሏል፡፡

የኤጀንሲው ምክትል ኃላፊ አቶ ተክሉ ቢያሞ ለሪፖርተር በሰጡት ማብራሪያ መሠረት፣ ከዚህ ቀደም ወጥቶ የነበረው ጨረታ እንዲሰረዝ የተደረገው በዓለም አቀፍ ገበያው ላይ የብረት ዋጋ ባስመዘገበው ቅናሽ ሳቢያ ነው፡፡ እንደ አቶ ተክሉ ማብራሪያ ከሆነ በዓለም ገበያ በታየው ዋጋ ቅናሽ ሳቢያ ኢንተርፕራይዙ 320 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ለማዳን በመቻሉ ጨረታውን በድጋሚ ለማውጣት ተገዷል፡፡ ይህም ተከትሎም ከዚህ ቀደም በወጣው ጨረታ ሊገዛ የታሰበው 150 ሺሕ ቶን ብረት ላይ ተጨማሪ 70 ሺሕ ቶን ለማከል እንዳስቻለ ገልጸዋል፡፡

በሚያዝያ ወር የነበረው የዓለም ገበያ ዋጋ ለአንድ ቶን 90 ዶላር የተጠየቀበት ሲሆን፣ ይህ መጠን ግን ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወር ላይ 295 ዶላር እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ከዚህ በኋላ ሲ እና ኢ ወንድማማቾች
ድጋሚ በተካሄደው ጨረታ መሠረት መጠናቸው ከአሥር እስከ 20 ሚሊ ሜትር የሆኑ አርማታ ብረቶችን ለማቅረብ በሰጠው ዋጋ መሠረት አሸናፊ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ 

ከሲ እና ኢ ወንድማማቾች ባሻገር አምስት ያህል ተወዳዳሪዎች መሳተፋቸውን መረጃዎች ሲጠቁሙ፣ ከአምስቱ ሦስቱ ባቀረቡት ዋጋና መጠን መሠረት ግዥ ለመፈጸም የሚያስችል ስምምነት ሰሞኑን ይፈረማል ተብሎ እንደሚጠበቅ አቶ ተክሉ ገልጸዋል፡፡ የቻይናው ኢስት ስቲል፣ አቢሲንያ ኢንተግሬትድ ስቲል፣ ሐበሻ ስቲል እንዲሁም ስቲሊ አርኤምአይ በጨረታው ሒደት መሳተፋቸው ታውቋል፡፡

ከሲ እና ኢ ወንድማማቾች በመቀጠል 39.4 ሺሕ ቶን የአርማታ ብረት በ718 ሚሊዮን ብር ያቀርባል ተብሎ የሚጠበቀው ኢስት ስቲል ሲሆን፣ ስቲሊ አርኤምአይ በበኩሉ 45.9 ሺሕ ቶን ብረት በ832 ሚሊዮን ብር ለቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ ያቀርባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከኢንተርፕራይዙ በተገኘው መረጃ መሠረት፣ ሐበሻና አቢሲንያ በጨረታው ቢሳተፉም የሚያቀርቡት የብረት መጠንም ሆነ የሚሸጡበት ዋጋ አልተጠቀሰም፡፡

ከዚህ ቀደም ሦስት ቢሊዮን ብር በሚጠጋ ወጪ 150 ሺሕ ቶን ብረት ለመግዛት ጨረታ ያወጣው ኢንተርፕራይዙ፣ በአሁኑ ጊዜ ለሚገዛው 220 ሺሕ ቶን 3.6 ቢሊዮን ብር በጠቅላላው ሊያወጣ እንደሚችል ይጠበቃል፡፡ በቀደመው ጨረታ መሠረት አሸናፊ ለመሆን የቻለው ኢስት ስቲል ሲሆን፣ ከ150 ሺሕ ቶን ውስጥ 124 ሺሕ ለማቅረብ የጠየቀው ዋጋ 2.4 ቢሊዮን ብር ገደማ እንደነበር ይታወሳል፡፡

ከሁለት ወራት በፊት ወጥቶ በዓለም ዋጋ ለውጥ ምክንያት የተሰረዘው ጨረታም ሆነ ግንቦት 24 ቀን 2008 ዓ.ም. ይፋ የወጣው ጨረታ ዓለም አቀፍ ተጫራቾችን አላሳተፉም፡፡ ይህ የሆነውም የአገር ውስጥ አምራቾችን ለማበረታት በሚል የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ባወጣው መመርያ መሠረት ነው፡፡ የግዥ ሕጉ ማናቸውም ከሦስት ሚሊዮን ብር በላይ ግዥ የሚፈጸምባቸው ዕቃዎችና አገልግሎቶች ዓለም አቀፍ ጨረታ እንዲወጣባቸው ያስገድዳል፡፡