አገርና ምርትን ለማስተዋወቅ እንዲህም ይደረጋል

ሰሞኑን የኦማን ኩባንያዎች ምርትና አገልግሎታቸውን የሚያስተዋውቁበት አንድ የንግድ ትርዒት በአዲስ አበባ በሚሊኒየም አዳራሽ አካሂደዋል፡፡ ወደ 115 የሚደርሱትን እነዚህን የኦማን ኩባንያዎች ያሰባሰብውና ‹‹ኦማን አምራቾች ኤግዚቢሽን›› የሚል መጠሪያ ያለው የንግድ ትርዒት ለአራት ተከታታይ ቀናት ተጎብኝቷል፡፡ ይህ የኦማናውያን የንግድ ትርዒት በየዓመቱ በተመረጡ የተለያዩ አገሮች እየተዘዋወረ የሚካሄድ ነው፡፡

በኦማን መንግሥትና በኦማን ንግድ ምክር ቤት በጥምረት የሚዘጋጀውና በአገሪቱ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስተባባሪነት የሚካሄደው የንግድ ትርዒት ዋነኛ ዓላማ የኦማን ኩባንያዎች ገበያቸውን እንዲያስፋፉና አዳዲስ ገበያዎችን እንዲፈጥሩ ለማድረግ ነው፡፡ ከዚህ ዓላማ ጎን ለጎን የኦማን ኩባንያዎች የንግድና ትርዒቱ በሚያካሂዱባቸው አገሮች ውስጥ ካሉ አገር በቀል ኩባንያዎች ጋር በጥምረት በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ላይ ለመሰማራት የሚችሉበትን ዕድል ለመፍጠር ጭምር ነው፡፡

የኦማን ኩባንያዎች በግላቸው ከሚያደርጉት ገበያ የማፈላለግ ሥራ በተጨማሪ የመንግሥታቸው እገዛ ታክሎበት፣ የኩባንያዎቹ ከፍታ እንዲጨምር ታስቦ የሚደረግ የተደራጀ ገበያ የማፈላለግ ሥልት ተደርጎም ይወሰዳል፡፡

የኦማን ኩባንያዎች የበለጠ እንዲያተርፉና የበለጠ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንዲሁም ለአገራቸው የሚያስገኙት የውጭ ምንዛሪ እንዲጨምር ይህንን የንግድ ትርዒት እንደ አንድ አማራጭ እየተጠቀሙበት ነው፡፡  ኦማኖች ከሰሞኑ እዩልንና ተመልከቱን ያሉዋቸውን ምርቶቻቸውን የበለጠ ለማስተዋወቅ፣ ከመሰንበቻውም ተመሳሳይ ፕሮግራም እዚሁ አዲስ አበባ ላይ እንደሚደግሙ አስታውቀዋል፡፡ በቀጣዩ ዓመትም አዲስ አበባ እንመላለሳለን ያሉት ኢትዮጵያን ለመጥቀም ብቻ እንዳልሆነ ይገባናል፡፡ እነሱ ምርቶቻቸውን ለመሸጥ የሚችሉበት ዕድል መኖሩን በማወቃቸውና የበለጠ እንጠቀማለን ብለው በማመናቸው ጭምር መሆኑ ከማንም የሚሰወር አይሆንም፡፡

እንዲህ ያለው የንግድ ትርዒት የሚሰጠውን ጥቅም በሚገባ የተረዱ  በመሆናቸው፣ ቀጣዩን ንግድ ትርዒታቸውን አዲስ አበባ ለማድረግ መወሰናቸው በራሱ የሚያስረዳን ነገር አለ፡፡ ይህ የኦማናውያን ጥረት በትክክል ዒላማውን መምታት የቻለ መሆኑን የሚመሰክርልን ደግሞ ሰሞኑን በኢትዮጵያ ውስጥ ባካሄዱት የመጀመርያ ንግድ ትርዒ ላይ ኩባንያዎቻቸው ምርቶቻቸውን በኢትዮጵያ ገበያ ለማስገባት የሚያስችል ስምምነቶችን ማድረጋቸው ምሳሌ ሊሆን ይችላል፡፡  

ከዚህ የንግድ ትርዒት ቢያንስ የተወሰኑት ኩባንያዎች እርግጠኛ የሚሆኑበትን አዲስ ገበያ እንዲያገኙ ዕድል ሰጥቷቸዋል፡፡ ከኢትዮጵያ ኩባንያዎች ጋር በጋራ የኮንስትራክሽን ዕቃዎች ማምረቻ ለማቋቋም የሚያስችል ስምምነት መፈረሙም ሌላ በአስረጅነት የሚቀርብ ምሳሌ ነው፡፡

ስለዚህ ይብዛም ይነስም ኦማናውያን ይዘውት የተነሱትን ዓላማ ማሳካት ችለዋል ሊባል ይችላል፡፡ ከሰሞነኛው የኦማናውያኑ ክንውን ብዙ ልንማርበት ይገባል፡፡ የአገራቸውን ምርት ለማስተዋወቅና እንዲህም መሥራት እንደሚቻል አሳይተዋል፡፡ ከዚህ አንፃር የእኛ አገር ኩባንያዎች ምርቶቻቸውንና አገልግሎታቸውን እንዴት እያስተዋወቁ ይሆን? ብለን እንድናስብ ያስገድደናል፡፡

ይህንን የኦማናውያን ሥልት ተከትሎ የኢትዮጵያን ኩባንያዎች ሰብስቦ ገበያ ይገኝባቸዋል ወደተባሉ አገሮች እየተዘዋወሩ የኢትዮጵያን ምርቶችንና አገልግሎቶችን ማስተዋወቅ እስካሁን ለምን አልተጀመረም? ለምንስ አልታሰበም? የሚሉት ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ቢከብድም፣ ከዚህ በኋላ ለሚሆነው ግን ማሰብ ያስፈልጋል፡፡

ከኦማናውያኑ መገንዘብ እንደተቻለው ሰሞኑን እንደተመለከትናቸው ያሉ የንግድ ትርዒቶችን ማዘጋጀት የቻሉት የአገራቸው የንግድ ምክር ቤት ከአገራቸው መንግሥት ጋር ተባብረው በመሥራታቸው ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ንግድ ምክር ቤቶችን ስንመዝን የእኛ የንግድ ምክር ቤቶች ያሉበትን ደረጃ እንድንታዘብ ያደርጋል፡፡ እውነት እናውራ ከተባለም እነዚህ ተቋማት እንዲህ ባለው አገራዊ ራዕይና አዳዲስ አሠራሮችን በማመንጨትና የውጭ ምንዛሪ እንዲመነደግ በሚያስችሉ የማስታወቂያ ሥራዎች ላይ ያላቸው አስተዋጽኦ እጅግ ሚጢጢ ነው፡፡ እንደውም ሐሳቡ ይኑር አይኑራቸው እንኳን አይታወቅም፡፡ ነገር ግን እንደ ኦማናውያኑ ለመሥራት የሚያግዳቸው ነገር እንዳልነበር እናስባለን፡፡ የንግድ ትርዒት አዘገጃጀትም ይጠፋቸዋል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ምክንያቱም በተለይ የአዲስ አበባና የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤቶች ዓመታዊ የንግድ ትርዒቶችን ያካሂዳሉ፡፡ ከውጭ ኩባንያዎችን ይጋብዛሉ፡፡ የተቋማቱ መሪዎች ወደተለያዩ አገሮች ይጓዛሉና ለጉዳዩ አዲስ አይሆኑም ተብሎ ይታሰባል፡፡  

ስለዚህ የኢትዮጵያን ኩባንያዎች ምርትና አገልግሎት የሚያስተዋውቅ አንድ ቋሚና ተዘዋዋሪ የንግድ ትርዒት እንዲኖራቸው ለማድረግ ከተፈለገ፣ አሁንም ኃላፊነት ያለባቸው እነዚሁ ንግድ ምክር ቤቶች ናቸው፡፡ በተናጠል ገበያ ከማፈላለግ በጋራ አገራዊ ምርትን በማስተዋወቅ ተጠቃሚ መሆን እንደሚቻል ከታመነበት፣ እንዲህ ያሉ ንግድ ምክር ቤቶች ከእንቅልፋቸው ነቅተው እንዲህ ባሉ የተመረጡ ሥራዎች ላይ ቢያተኩሩ ይመከራል፡፡

እንደ ኢትዮጵያና አዲስ አበባ ያሉ የንግድ ምክር ቤቶች በአገር ውስጥ የንግድ ትርዒቶችን ማዘጋጀታቸው ባይከፋም፣ እነዚህ የንግድ ትርዒቶች የውጭ ኩባንያዎችን በማስተዋወቅ ላይ የተመሠረቱ በመሆናቸው ከኢትዮጵያ ውጭም ዓይናቸውን ሊጥሉ ይገባል፡፡ የበለጠ የሚጠቅመውም ይኸው ነው፡፡ የተቋማቱን ቁመና የሚመጥነውም ይኸው ነው፡፡ የአገር ውስጥ ኩባንያዎችን ገበያ ሊያሳድጉ በሚችሉ ዓለም አቀፍና ተዘዋዋሪ የንግድ ትርዒቶች ላይ መሥራታቸውም፣ ለሚወክሉት የንግድ ኅብረተሰብም ሆነ ለአገር ባለውለታ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል፡፡ 

ተደጋግሞ እንደሚነገረው የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ እጥረት የሚያጋጥመው ለምርቶች ገበያ በማፈላለግ ባለመሸጡ ነው፡፡ አንዱ ምክንያት ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችም ሆኑ  አሁን የውጭ ምንዛሪ እያስገኙ ያሉት ምርቶች፣ ገዥ ያገኙት በዘመነ የማስተዋወቅ ሥልት ተጠቅመን እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡ ስለዚህ ራስን ለመሸጥ አሁን ኦማናውያኑ እንዳሳዩን ዓይነት የማስተዋወቂያ ሥልት መሞከርና መተግበር አለበት፡፡ ይህ ሥልት የተሻለ ተመራጭ የሚሆነው ደግሞ በጋራ ብዙ ምርቶችንና ኩባንያዎችን ማስተዋወቅ በማስቻሉ ነው፡፡ ነገሩን በጥቅሉ እንየው ከተባለም ለተሻለ ገበያ ማስተዋወቅ ሥራ ወሳኝ በመሆኑ፣ አገርን የሚያስተዋውቅ አገራዊ ተቋም መፍጠር የማይቻለውስ ለምንድነው? ምክንያቱም ሊኖረን ይገባል፡፡