አደገኛው የዚካ ቫይረስ በጥያቄና መልስ ሲፈተሽ

በአሸናፊ ዋቅቶላ (ዶ/ር)

የዚካ ቫይረስ ምንድን ነው?

ዚካ በቢንቢዎች የሚተላለፍ ቫይረስ ሲሆን፣ የሚገኝበት የቫይረስ ቤተሰብ ዌስት ናይል ቫይረስ፣ ደንጊ፣ ቲክ-ቦርን ኢንሰፋላይቲስና ((መዥገር-ተሸካሚ የአንጎል መቆጣት ቫይረስ)፣ ቢጫ ወባ (የሎው ፊቨር) ይገኙበታል። ፍላቪ በላቲን ቋንቋ ቢጫ ማለት ሲሆን፣ ስሙ የተገኘው ከቢጫ ትኩሳት (ቢጫ ወባ) ነው። ቢጫ የተባለውም ቢጫ ወባ ጉበትን አሳምሞ የዓይንን ቢጫነት (ጆንዲስ) ስለሚፈጥር ነው።

የቀድሞ ወረርሽኞች ታሪክ ምን ይመስላል?

ዚካ ቫይረስ በመጀመሪያ የተገኘው በአፍሪካ ኡጋንዳ ዚካ ጫካ ለቢጫ ወባ ምርምር የተቀመጠ ሪህሰስ 776 ተብሎ በተሰየመ አንድ ጦጣ ላይ ነበር። ከዚያ በኋላ ለብዙ ዓመታት በሰዎች ውስጥ አነስተኛ ወረርሽኞች ሲደርሱ ቆይተዋል። በዚህ ሁኔታ በ60 ዓመታት ጊዜ ውስጥ 14 ሰዎች ብቻ በበሽታው ሲያዙ፣ ተጨማሪ ሁለት ሰዎች ከምርምር ጋር የተገናኘ የዚካ በሽታ ይዟቸዋል። እነኚህ በሙሉ ያሳዩት ለአጭር ጊዜ የቆየ ያልጠና ሕመምና ከበሽታውም ሙሉ በሙሉ ድነው ነበር።

እ.ኤ.አ. በ2007 ፓስፊክ ውቅያኖስ በሚገኙት ማይክሮኔዥያ ፌደራላዊ ክፍለ አገሮች ያፕ ደሴት ውስጥ ትልቅ ወረርሽኝ ተከስቶ 5,000 የሚገመት ሕዝብን ይዞ ነበር። ይህ ደግሞ ከነዋሪዎች 70 በመቶ በላይ ማለት ነው። በዚህ ወረርሽኝ ምክንያት ሆስፒታል የተኛም ሆነ የሞተ አልነበረም።

የሚቀጥለው ወረርሽኝ የታየው እ.ኤ.አ. ከ2013 እስከ 2014 ሲሆን በፍሬንች ፖለኔዥያ ነበር። 30,000 ሰዎች ከመያዛቸው ሌላ ወደ ተጨማሪ ሰባት ደሴቶች ተሰራጭቷል። በወረርሽኙ የሞተ አልነበረም። ነገር ግን የነርቭ ሥርዓት መዛባቶች መታየት የጀመሩት በዚህ ጊዜ ከመሆኑ ሌላ 42 ሰዎች ጉሊያን ባሬ የተባለ የጠና የነርቭ ሥርዓት መዛባት ደርሶባቸው ነበር። 16 ሰዎች ሕመም በጣም የጠናባቸው መታከሚያ ውስጥ (ኢንቴንሲቭ ኬር) ውስጥ ሲታከሙ፣ 12ቱ የሰው ሠራሽ መተንፈሻ ዕርዳታ አስፈልጓቸው ነበር።

እ.ኤ.አ. በማርች 2014 ቺሌ በኢስተርን አይላንድ ውስጥ የዚካ መተላለፍ ሲዘገብ በሜይ 2015 በሰሜን ምሥራቅ ብራዚል ሥርጭቱ ተረጋግጦ ነበር። ክኦክቶበር 2015 በኋላ ብዙ አገሮችና ግዛቶች የቫይረሱን መኖር አሳውቀዋል።                             

የዚካ ቫይረስ የሚተላለፈው እንዴት ነው?

  • ቫይረሱ ወደ ሰዎች የሚተላለፍበት ዋነኛ መንገድ በቫይረሱ በተያዘች የኤዲስ ሴት ቢንቢ ንክሻ ነው። የኤዲስ ቢንቢዎች ቀን በቀን ከቤት ውጪና ውስጥ ኃይለኛ (አግረሲቭ) ተናካሾች ናቸው። ቢንቢዎቹ በምሽትም ይናከሳሉ።
  • የዚካ ቫይረስ በእርግዝና ጊዜና በወሊድ ጊዜ ከእናት ወደ ልጅ ይተላለፋል።
  • በግብረ-ሥጋ ግንኙነት ከወንድ ወደ ሴት ይተላለፋል።
  • የደም ከአንድ ሰው ወደ ሌላ ሰው መዘዋወር (ብለድ ትራንስፉዥን)፣ የክፍለ-አካልና የኅብረ-ሕዋስ መተካከል (ኦርጋን ኤንድ ቲሹ ትራንስፕላንቴሽን) ቫይረሱን ማስተላለፍ የሚችሉ መንገዶች ናቸው።

የዚካ ቫይረስን የሚያስተላልፉት ቢንቢዎች የትኞቹ ናቸው?

ኤዲስ ኢጂፕቲ ቢንቢዎች በምድር ወገብ አካባቢና በአንዳንድ ቀዝቀዝ ያሉ (ቴምፐሬት) አየር ንብረቶች ውስጥ ይኖራሉ። ዚካ፣ ደንጊ፣ ቺኩንጉንያና ሌሎች ቫይረሶችን የሚያስተላልፉት ዋነኛ ቢንቢዎች ኤዲስ ኢጂፕቲ ቢንቢዎች ናቸው። ሰዎችን ተጠግተው የሚኖሩና ከሌሎች እንስሳት የሚመርጡት ሰዎችን መንከስ ስለሆነ፣ ከሌሎች ቢንቢዎች ይበልጥ እነዚህን ቫይረሶች የማስተላለፍ ዕድል አላቸው።

ኤዲስ አልቦፒክተስ የተባሉት ቢንቢዎች በምድር ወገብ አካባቢና ቀዝቀዝ ያሉ ቦታዎች ውስጥ እንደ ኤዲስ ኢጂፕቲ ቢንቢዎች መኖር ከመቻላቸውም በላይ፣ ይበልጥ ስፋት ባላቸው አየር ንብረቶችና በጣም በቀዘቀዙ ቦታዎች ውስጥ መኖር ይችላሉ። እነዚህ ቢንቢዎች እንስሳትና ሰውን የሚነክሱና ከኤዲስ ኢጂፕቲ ቢንቢዎች ጋር ሲወዳደሩ ቫይረሶችን ወደ ሰው የማስተላለፍ ብቃታቸው አነስተኛ ነው።

ከኤዲስ ኢጂፕቲ ቢንቢዎች ውስጥ ምን ያህሉ ቢያዙ ነው አሁን በአሜሪካኖች የሚታየውን ዓይነት ትልቅ ወረርሽኝ ማስተላለፍ የሚችሉት?

ብራዚል ውስጥ በተደረገ ክትትል (ሰርቬላንስ) ምርመራዎች ከ1,000 ቢንቢዎች ውስጥ ሦስት ብቻ በዚካ ቫይረስ መያዛቸው ታውቋል። በሌሎችም የቢንቢ ወረርሽኞች በበሽታ አምጪው የሚያዙት በዚሁ ቁጥር አካባቢ ነው።

የኤዲስ ቢንቢ ከአገር ወደ አገር፣ ከክልል ወደ ክልል ሊበር ይችላል?

የኤዲስ ቢንቢ ደካማ በራሪ ነው። ከ400 ሜትር በላይ አይበርም። ነገር ግን በሰዎችና በተሽከርካሪዎች አማካይነት ከቦታ ቦታ እየተጓዘ አዳዲስ ቦታዎች ውስጥ መንሰራፋት ይችላል።

የዚካ ቫይረስ በሽታ መደላደል ጊዜ (ኢንኩቤሽን ፔሬድ) ምን ያህል ነው?

ቫይረሱ ሰውነት ወስጥ ከገባ በኋላ የመጀመሪያ የሕመም ስሜቶች እስኪከሰቱ ድረስ ያለው ጊዜ ማለትም የመደላደል ጊዜው (ኢንኩቤይሽን ፔሬድ) ከቢንቢ ንክሻ በኋላ ብዙ ጊዜ ከሦስት እስከ 12 ቀናት ነው።

የዚካ ቫይረስ በሽታ የሕመም ስሜቶች (ሲምፕቶምስ) ምንድን ናቸው?

ቫይረሱ ከያዛቸው 80 በመቶ የሚሆኑ ሰዎች ምንም የሕመም ስሜት ስለማይኖራቸው ቫይረሱ እንደያዛቸው እንኳን አያውቁም፡፡ በተቀሩት ላይ ይበልጥ ተዘውትረው የሚታዩት መለስተኛ (ያልጠኑ) የሕመም ስሜቶች ትኩሳት፣ የቆዳ ሽፍታ፣ የመገጣጠሚያ ሕመምና የዓይን መቅላት (ኮንጀንክቲቫይቲስ) ናቸው። ሌሎች የሕመም ስሜቶች ደግሞ የጡንቻ ሕመምና ራስ ምታት ይገኙባቸዋል። የዚካ ሕመም ስሜቶች ከሁለት እስከ ሰባት ቀናት ይቆያሉ።

የዚካ ቫይረስ በታማሚው ሰው ደም ውስጥ ብዙ ጊዜ የሚቆየው ለአንድ ሳምንት ብቻ ነው። በአንዳንድ ሰዎች ውስጥ ከዚያ ለረዘመ ጊዜ ሊቆይ ይችላል።

አንዴ በዚካ ቫይረስ የተያዘ ሰው ከዚያ በኋላ ወደፊት በዚካ ቫይረስ ደግሞ እንደማይያዝ ይታመናል።

የዚካ ቫይረስ በሽታ በምርመራ የሚለየው እንዴት ነው?

የዚካ ቫይረስን ማግኛ የሲሮሎጂና የሞለኩይላር ቴክኖሎጂ ዘዴዎች አሉ።

- የዚካ ቫይረስ በሽታ ከያዘ በኋላ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ከደም ውስጥ ስለሚጠፋ ወይም በጣም ስለሚቀንስ የሲረም ረቨርስ ትራንስክሪፕሽን ፖሊመሬዝ ሪአክሽን (አር ፒሲአር ) ላያገኘው ይችላል። ሽንት ውስጥ ግን እስከ ሁለት ሳምንት ስለሚቆይና በሽታው ከጀመረበት ጊዜ እስከ ሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ስለሚታይ የሽንት አር ፒሲ አር ሊያገለግል ይችላል፡፡ የደም ወይም የሽንት አር ፒሲ አር ምርመራ ‹‹አለ›› (ፖሲቲቭ) ካለ የዚካ ቫይረስ በሽታ ተረጋግጧል ማለት ነው።

- የዚካ ቫይረስ በሽታ ከያዘ ከአንድና ሁለት ሳምንታት በኋላ ሲረምና በሽንት ውስጥ የሚገኘው የቫይረስ መጠን በጣም ሲቀንስ በሽታው እያለ የፒ ሲ አር ምርመራ ፖሲቲቨ ላይሆን ይችላል። በዚህ ጊዜ ውስጥ የሲሮሎጂ (የፀረ-አካል) ምርመራ ሊደረግ ይችላል። ቢሆንም ምርመራው ከደንጊና ከቢጫ ወባ (የሎው ፊቨር) ከመሳሰሉ ሌሎች ፍላቪ ቫይረሶች ፀረ-አካሎች አጋር ሊያምታታ ይችላል። ይህንን ችግር ለመቀነስና በተለይ የዚካ ቫይረስን ፀረ አካሎች ለማግኘት ሌላ ምርመራ (ፕሌክ-ሪደክሽን ኒውትራላይዚንግ አንቲቦዲስ) ማድረግ ያስፈልጋል።

የዚካ ቫይረስ በሽታ ሕክምና እንዴት ነው?

በአሁኑ ጊዜ የተለየ የዚካ መድኃኒት ወይም ፀረ-ቫይረስ የለም። ሕክምናው የሚደረገው ቫይረሱ የሚያስከትላቸውን የሕመም ስሜቶች ለመቀነስ ነው። ብዙ ዕረፍት ማድረግ ይጠቅማል። ፈሳሾች በብዙ መጠጣት ያስፈልጋል። ሕመም ለማስታገስና ትኩሳትን ለመቀነስ አሲታሚኖፊን (ታይላኖል) እና ፓራሲታሞልን መውሰድ ነው።

አስፕሪን፣ አይቡፕሮፈን፣ ናፕሮክሰንና የመሳሰሉት መድኃኒቶች (ኖን ስትሮይዳል አንቲ ኢንፍላማቶሪ ድረግስ) የመድማትን ውስብስቦሽ ሊያስከትሉ ወይም ሊያባብሱ ስለሚችሉ አለመጠቀም ነው። በሽታው ከጠና የጤና ባለሙያን ማማከር ያስፈልጋል።

የዚካ ቫይረስ በሽታ ዋና ዋና ውስብስቦች የትኞቹ ናቸው?

የዚካይረስ በሽታ የነርቭ ሥርዓት ውስብስቦች ማይክሮኬፋሊ፣ ጉሊያን ባሬ ሲንድሮምና አኩይት ዲማይሊኔቲንግ ሜኒንጎ ኢንሰፋላይትስን ይጨምራሉ።

ማይክሮኬፋሊ ምንድነው?

ይህ ከሁሉ የዚካ ውስብስቦች ይበልጥ አሳሳቢና አሳዛኙ ነው። ማይክሮኬፋሊ የጭንቅላት መጠን መቀነስ ሲሆን የሚገለጠውም ከወሊድ ጋር በተያያዘ (ኒዮናታል) ከተመሳሳይ ፆታና ዕድሜ ጋር ካሉ ሌሎች ሕፃናት ጋር ሲወዳደር የራስ ቅል መጠን መቀነስ ነው። ይህ ከአንጎል በሚገባ አለማደግ ጋር ሲጣመር የአካልና የአምዕሮ ዕድገት ጉድለቶችን (ዲቨሎፕመንታል ዲሴቢሊቲስ) ሊያስከትል ይችላል። እነኚህም የመቀመጥ፣ የመነሳት፣ የመሄድ፣ የመንቀሳቀስ፣ ሚዛን የመጠበቅ ድክመቶች፣ የመብላትና የመዋጥ ችሎታ መቀነስ፣ የመማርና ዕለታዊ የሕይወት ሥራዎችን የመፈጸም ችግሮች ሊያጋጥሙቸው ይችላሉ። በተጨማሪም የሚጥል በሽታ (ሲዠርስ)፣ ያለመስማትና የማየት ድክመቶች ናቸው።

የማይክሮኬፋሊ መንስዔዎች ብዙ ሲሆኑ ምክንያቱ ከምርመራዎችም በኋላ ላይታወቅ ይችላል፡፡ የማሕፀን ሕመም (ቶክሶፕላዝሞሲስ፣ ሩቤላ፣ ኸርፒስ፣ ጨብጥ፣ ሳይቶሜጋሎ ቫይረስ፣ ኤችአይቪ)፣ ለመጥፎ ኬሚካሎች መጋለጥ፣ የእናቶች ለከባድ ብረቶች (ሄቪ ሜታልስ) መጋለጥ (አርሰኒክ፣ ሜርኩሪ)፣ በእርግዝና ጊዜ አልኮል ብዙ መጠጣት፣ ጨረር (ራዲኤሽን)፣ ሲጋራ ማጨስ፣ ዳውን ሲንድሮም የመሳሰሉ የአፈጣጠር ጉድለቶች (ጄኔቲክ አብኖርማሊቲስ)፣ በእርግዝና ጊዜ የጠና የምግብ ዕጥረት (ሲቨር ማልኑትሪሽን) መንስዔዎች ከሚሆኑት ውስጥ ናቸው።

ጉሊያን ባሬ ሲንድሮም ምንድነው?

የሰው የተፈጥሮ መከላከያ የራሱን ወይም የራሷን ነርቮች የሚያጠቃበት በጣም አልፎ አልፎ የሚታይ ሕመም ነው። በሁሉም የሰዎች ዕድሜ ክልሎች መታየት የሚችል ቢሆንም የሚበዛው አዋቂ (አደልት) ወንዶች ላይ ነው። ከ20 በመቶ እስከ 25 በመቶ በሚሆኑት ውስጥ የደረት ጡንቻዎችን አውኮ የመተንፈስ ችግርን ያስከትላል። በጣም የጠና ሲሆን ሽባነትንና (ፓራልይሲስ) ሞትን ሊያመጣ ይችላል።

አኩይት ዲማይሌቲንግ ሜኒንጎ ኢንሰፋላይቲስ ምንድነው?

ሰውነት በራሱ ላይ የሚመጣን ጥቃት ለመከላከል አንጎልንና ሰረሰርን (ስፓይናል ኮርድ) በስፋት የሚጎዳበት መቆጣት (ኢንፍላሜሽን) ነው፡፡ ይህ በሽታ በተለይም ኋይት ማተር የተባለውን የአንጎል ክፍል ያጠቃል፡፡ የዚህ በሽታ አቀራረብ መልቲፕል ስክሌሮሲስ የተባለ የነርቭ በሽታን እንደሚመስልና ስድስት ወራት ድረስ ሊቆዩ የሚችሉ የነርቭ ሥርዓት መዛባቶች ሊኖሩት እንደሚችሉ ተዘግቧል።

የዚካ ቫይረስ በሽታ ብዙ ጊዜ ሞት ያስከትላል ወይ?

ባለፉት ዓመታት የዚካ ቫይረስ በሽታ ወረርሽኞች የሚያጠቁት ሰዎች ቁጥር አነስተኛ ከመሆናቸው ሌላ፣ የዚካ ቫይረስ በሽታ የሞት አደጋም አድርሶ እንደነበረ የሚያሳይ መረጃ የለም። በአሁኑ ወቅት ወረርሽኙ እጅግ በጣም ተስፋፍቶ የሚገኝና አንዳንድ ጊዜ በጣም የጠና ሕመምና ሞትን ያስከትላል።

ሰዎች ራሳቸውን ከቢንቢ ንክሻ እንዴት ሊከላከሉ ይችላሉ?

ከሁሉ የሚበልጠው ዕርምጃ የቢንቢ ንክሻን መከላከል ነው፡፡ በተለይ እርጉዞች፣ ለማርገዝ ዕቅድ ያላቸው ሰዎችና የግብረ-ሥጋ ጓደኞቻቸው (ሴክሿል ፓርትነርስ) ከቢንቢ ንክሻ ራሳቸውን ይበልጥ መጠበቅ ይኖርባቸዋል።

  1. የሚለብሷቸው ልብሶች በተቻለ መጠን አብዛኛውን የሰውነት ክፍሎችን መሸፈን አለባቸው።
  2. ቢንቢ አባራሪ ኬሚካሎችን ባልተሸፈኑ የሰውነት ክፍሎች ወይም ልብሶች ላይ መቀባት፡፡ ኬሚካሎቹ ዳይኢታይልቶሉአማይድ ወይም አይአር 3535 የሚባሉትን ነገሮች የያዙ ከመሆናቸው ሌላ፣ የአጠቃቀም መመርያዎች በትክክል መጠቀም ያስፈልጋል። እነዚህ በእርጉዞች ላይ ጉዳት አያስከትሉም።
  3. አካላዊ ከለላዎች ማለትም የታከሙ ወንፊቶችን በበሮችና መስኮቶች ላይ መጠቀም።
  4. በቢንቢ መከላከያ አጎበሮች ሥር መተኛት፡፡
  5. ቢንቢዎች ሊራቡባቸው የሚችሉባቸውን ቦታዎችና ዕቃዎች መለየትና ማስወገድ ለምሳሌ ባልዲዎች፣ የአበባ ማስቀመጫዎችና የመኪና ጎማዎችን መክደን ወይም ማስወገድ።

ለዚካ ቫይረስ መክላለከያ ክትባት አለ?

በአሁኑ ጊዜ የዚካ ቫይረስ በሽታ መከላከያ ክትባት የለም።

እርጉዞች እንዴት ከቢንቢ ንክሻ ሊጠበቁ ይችላሉ?

ዚካ በሚተላለፍባቸው አገሮች ውስጥ ያሉ እርጉዞች እንደ ሌላው ሕዝብ የመከላከያ ዘዴዎችን መጠቀም ይገባቸዋል፡፡ መደበኛ የእርግዝና ክትትል ማድረግና የትኛውም የዚካ በሽታ ስሜት ቢያሳዩ ቶሎ የጤና ባለሙያዎች ክትትል ማድረግ ይገባቸዋል።

እርጉዞች በዚካ ቫይረስ ይበልጥ ይጠቃሉ?

የዚካ ቫይረስ እርጉዞችን ከሌሎች ይበልጥ ሊይዝ እንደሚችል፣ ወይም ከሌሎች ሰዎች ይበልጥ የጠና በሽታ እንደሚሰጣቸው የሚያሳይ መረጃ የለም፡፡

የዚካ ቫይረስ የተገኘባቸው እናቶች ጡት ሊያጠቡ ይችላሉ?

የዚካ ቫይረስ አርኤን ኤ በጡት ወተት ውስጥ ቢገኝም፣ በላቦራቶሪ ውስጥ ማሳደግ (ከልቸር ማድረግ) አልተቻለም፡፡ እስካሁን ድረስ ቫይረሱ ከእናት ወደ ልጅ በጡት መጥባት ምክንያት እንደተላለፈ የሚያሳይ መረጃ የለም፡፡ የዓለም የጤና ድርጅት ለመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ሕይወት የጡት ወተት ብቻ መጠቀምን ይመክራል፡፡

እርጉዞች ለዚካ ቫይረስ ሕክምና ሊወስዱ ይችላሉ?

በተለይ ለዚካ ቫይረስ የሚሆን ፀረ-ቫይረስ ሕክምና እስካሁን የለም። የዚካ ቫይረስ በሽታ ብዙ ጊዜ መለስተኛና ቶሎ የሚተው (ከሁለት እስከ ሰባት ቀናት) ነው። ሕመሙ ካስቸገረ እርጉዞች ብዙ ዕረፍት እንዲወስዱና በቂ ፈሳሾች እንዲጠጡ ይመከራል። ለሕመሙና ለትኩሳቱ ፓራሲታሞል ወይም አሲታሚኖፊን መውሰድና ሌሎችም ሰውነት ማቀዝቀዣዎችን ሊጠቀሙ ይችላሉ።

ፀረ-ሂስታሚኖች በእርግዝና ጊዜ መውሰድ ይቻላል?

ሽፍታው የሚያሳክክ ከሆነ እርጉዝ ሴት የጤና ባለሙያ አማክራ ፀረ-ሂስታሚን መውሰድ ትችላለች፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ክሎርፌኒራሚን፣ ሎራታዲን ወይም ሴቲሪዚን ይታዘዝላታል። እነኚህ ቆየት ያሉ ፀረ-ሂስታሚኖች ለብዙ ዓመታት በእርግዝና ጊዜ ስለተወሰዱ ጉዳት እንደማያስከትሉ ይታወቃል።

በግብረ-ሥጋ ግንኙነት የሚተላለፈውን ዚካ ቫይረስ መከላከል የሚቻለው እንዴት ነው?

በዚካ ቫይረስ የተያዙ ሰዎች በሙሉና የግብረ-ሥጋ ጓደኞቻቸው (በተለይ እርጉዝ ሴቶች) የዚካ ቫይረሰ በግብረ-ሥጋ ግንኙነት የመተላለፉን አደጋ፣ የእርግዝና መከላከያ ዘዴዎችንና ጉዳት የማያስከትሉ የግብረ-ሥጋ ግንኙነት ዘዴዎችን አስመልክቶ መረጃዎች ማግኘት ይኖርባቸዋል።

በሚቻልበት ጊዜ ኮንዶሞችን ማግኘት፣ በትክክልና የግብረ-ሥጋ ግንኙነት ባደረጉ ቁጥር እንዲጠቀሙበት ማስተማር ያስፈልጋል።

የእርጉዞች የግብረ-ሥጋ ጓደኞች የዚካ በሽታ እየተላለፈባቸው ባሉ ቦታዎች ውስጥ የሚኖሩ ወይም ወደዚያ የተጓዙ ከሆነ ጉዳት የማያስከትል የግብረ-ሥጋ ግንኙነት ማድረግ አለባቸው፡፡ ይህም ግንኙነት ባደረጉ ቁጥር ኮንዶምን ማጥለቅ ወይም እስከ እርግዝና ፍፃሜ ድረስ ከግብረ-ሥጋ ግንኙነት መቆጠብ ሊሆን ይችላል።

የዚካ ቫይረስ በሽታ በሚተላለፉባቸው ሥፍራዎች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ጉዳት የማያስከትሉ (ሴፍ) የግብረ-ሥጋ ግንኙነቶችን ማድረግ ወይም ከግብረ-ሥጋ ግንኙነት መቆጠብ አለባቸው።

መከላከያ የሌለው ግብረ-ሥጋ ግንኙነት የፈጸሙና በዚካ ቫይረስ መያዝ ሥጋት እርግዝና ባይፈልጉ ምን ማድረግ ይችላሉ?

ሕግ በሚፈቅደው ልክ ሙሉ ሁሉም ሴቶች የድንገተኛ እርግዝና መከላከያ፣ ትክክለኛ መረጃና አቅም የሚመጥን ዘዴዎችን መጠቀም እንዲችሉ መደረግ አለበት።

ዚካሚገኝባቸው ቦታዎች የሚሄዱ ምን ማድረግ አለባቸው?

እርጉዞች የዚካ ቫይረስ እየተላለፈባቸው ወዳሉ ቦታዎች እንዳይጓዙ መመከር ይገባቸዋል። የግብረ ሥጋ ጓደኞቻቸው (ሴክሽዋል ፓርትነርስ) ዚካ በሚተላለፍባቸው ቦታዎች ውስጥ የሚኖሩ ወይም ወደዚያ የሚጓዙ ከሆነ፣ እርግዝናው እስኪፈጸም ድረስ ከግብረ ሥጋ ግንኙነት መቆጠብ ወይም የዚካ ቫይረስ በሽታን የማያስተላልፍ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ዓይነትን (ለምሳሌ ኮንዶም) መጠቀም ይኖርባቸዋል።

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የሕክምና ዶክተር ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡