አሁን እየታየ ባለው አያያዝ የከፋው ሌብነት ይቆማልን?

በመንግሥቱ መስፍን

ሙስና ዓለም አቀፍ ወንጀል ነው፡፡ በመንግሥት ሌቦችና ሕዝቡ ውስጥ በተወሸቁ ዘራፊዎች ትብብር የሚፈጸመው ይህ አስከፊ ወንጀል ዜጎችን እርቃን የሚያስቀር፣ ጥቂቶችን የሚያበለፅግ፣ የመንግሥትን ተዓማኒነት የሚሸረሽርና ሕዝብን የሚያማቅቅ  አደገኛ ችግር ነው፡፡ ከዚህ አንፃር በአገራችንም ዓይነቱና መጠኑ ቢለያይም ወንጀሉን በጥብቅ መታገል ካልተጀመረ ከፊት ለፊት የተደቀነው አደጋ የከፋ መሆኑ አይቀርም፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል አገሮች ከፍተኛ ባለሥልጣናት በሜክሲኮ ሜሪዳ ከተማ እ.ኤ.አ. ከዲሴምበር 9 እስከ 12 2003 ተወያይተው ባፀደቁትና 140 አገሮች ፊርማቸውን ባስቀመጡበት የፀረ ሙስና ኮንቬንሽን መሠረት፣ አገራችን የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ማቋቋሟ ያስመሰግናታል፡፡ በፌዴራል ብቻ ሳይሆን በክልል ደረጃም የሙስናን ወንጀል ለመከላከል የሚረዳ ተቋም ያውም በኮንፌዴሽን ስምንት ክፍሎችና 71 አንቀጾች መሠረት ለማዋቀር የተደረገው ጥረትም እየተጠናከረ ከሄደ መበረታታት ያለበት ነው፡፡

እንዲያም ሆኖ ግን በኢትዮጵያ ያለው የፀረ ሙስና ኮሚሽን በአብዛኛው ወንጀለኞችን ከማስያዝና የሕዝብ ሀብት ከማስመለስ ይልቅ ሒደት (Process) ላይ የሚያተኩር ነው ይሉታል፡፡ ‹‹ጥርስ የሌለው አንበሳ›› ከማለት አንስቶ በገለልተኛነቱና በአሠራር ነፃነቱ ላይ ጥያቄ የሚያነሱም ብዙዎች ናቸው፡፡ ኮሚሽኑ ከዚህ ቀደም የአገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር (አቶ ታምራት ላይኔ)፣ የመከላከያ ሚኒስትር (አቶ ስዬ አብርሃ)፣ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዳይሬክተሮችና የክልል ፕሬዚዳንቶችን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ሙስናን የተሸከሙ ነጋዴዎችን ከሶ ቢያስቀጣም፣ በአገሪቱ እየታየ ካለው በአንድ ጀንበር መበልፀግና የከፋ ሙስና አንፃር በቂ ሥራ እየሠራ አይደለም የሚለው መከራከሪያም ቅቡልነት ያለው ነው፡፡

በግሌ የፌዴራሉ ብቻ ሳይሆን የክልል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽኖች ለአስፈጻሚው ተጠሪ ሆነው በኢሕአዴግ ተሿሚዎች ብቻ እየተመሩ፣ የሠራተኛ የምርመራ ዋስትና ሳይኖራቸው እንዲሁም በካፒታል፣ በሰው ኃይልና በጥቆማ አቀባበልና ምርመራ በሚገባ ሳይጠናሩ ችግሩን ለመፍታት እንደማይችሉ አምናሁ፡፡ ሌላው ቀርቶ የሕዝቡን አመኔታ በተሟላ መንገድ ማግኘትም ቢሆን የሚቻል አይሆንም፡፡

እነዚህን መከራከሪያዎች በዓለም አቀፍ የዘርፍ ኮንፌዴሬሽንና በአፍሪካ ውስጥም በፀረ ሙስና ትግሉ ‹‹አንቱ›› በተባሉ አገሮች ተሞክሮና ልምድ ጋር እያነፃፀርኩ በማቅረብ ለመሞገት እሻለሁ፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀረ ሙስና ኮንቬንሽን በውስጡ አምስት ዋና ዋና ክፍሎችን ያካተተ ሲሆን፣ እነሱም የሙስና መከላከያ ድንጋጌዎች  (Preventive Measures)፣ የሕግ አፈጻጸም (Criminalization and Law Enforcement)፣ ዓለም አቀፍ ትብብር (International Cooperation) በሙስና የተገኘ ንብረትን ማስመለስ (Asset Recovery)፣ እንዲሁም ቴክኒካዊ ድጋፍና የመረጃ ልውጥጥ (Technical Assistance and Information Exchange) የሚሉት ናቸው፡፡

ከእነዚህ መሠረታዊ ነጥቦች አንፃር በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን አካሄድ መፈተሽና ጉድለቱን ለመለየት ያስችላል፡፡ በቀጣይም መንግሥትም ሆነ ሕዝብ ተጨማሪ ትኩረት መስጠት ያለባቸውን ጭብጦችን ለመለየትም ያስችላል፡፡

የሙስና መከላከያ መንገዶች

ሙስናን ለመከላከል ትልቁ ሥራ ሙስናን የማይሸከም ማኅበረሰብ መፍጠር ነው፡፡ ይህ ጉዳይ ምንም እንኳን በአንድ ጀንበር ዕውን የሚሆን ባይሆንም በሒደት በትውልዱ ውስጥ የሞራል፣ የሥነ ምግባርና አገራዊ ተቆርቋሪነት ስሜትን መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ‹‹ሲሾም ያልበላ …››  እያለ ጉቦን ከመሸከም የሚወጣ ጠያቂ፣ መብቱን አዋቂና ግዴታውን የለየ ሕዝብም ሊኖር ግድ ነው፡፡ እዚህ ላይ ያለፈው አልፎ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጭምር ሕዝቡ አልሰጥም ይበል፣ እምቢ ይበል፣ ይጩህ እስከማለት መድረሳቸው አንድ ዕርምጃ ነው፡፡ ያም ሆኖ ግን ሙስናን የሚፀየፍ ማኅበረሰብ ገና አልተፈጠረም፡፡

ሌላኛው ሙስናን ለመከላከል የሚያስችለው ብርታት የግል ፅናትና ተጠያቂነት ያለበት ሥርዓትን የማጠናከሩ አጀንዳ ነው፡፡ ይኼ ደግሞ መልካም አስተዳደር ማስፈን እሴቶች (Values) ከመተግበርም ሆነ የዴሞክራሲ ሥርዓትን በልበ ሙሉነት ከማስፈን ውጪ ሊታይ አይችልም፡፡ በዚህ ረገድ ሦስቱ የመንግሥት ክንፎች (ሕግ አውጭ፣ ሕግ ተርጓሚና አስፈጻሚ) አንዱ ሌላውን የሚጠይቅበት፣ የተጠናከሩ የሰላማዊ የፖለቲካ ተወዳዳሪዎች፣ የነፃ ፕሬስና የነፃ ማኅበራት መኖር ዕውን ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ራሱ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ገለልተኛነትና ልበ ሙሉነት የሚለካውም ከአጠቃላይ አስተሳሰብ አንፃር መሆን ስላለበት፡፡

ሙስናን የመከላከያ ሌላኛው መንገድ መሆን ያለበት የባለሥልጣናት፣ የተመራጮችና የሠራተኞች ሀብትና የገቢ ምንጭን የማረጋገጥ ጉዳይ ነው፡፡ ዜጎች በየትኛውም ደረጃ ሠርተው ሀብት የማፍራት የማይሸራረፍ መብት ቢኖራቸውም፣ በአንድ ጀንበር ሚሊየነር የሆኑ ባለሥልጣናት፣ የባለሥልጣን ዘመዶችና የጥቅም ተጋሪዎች ጉዳይ አሳሳቢ ነው፡፡ በአንድ በኩል ሕዝቡ እውነታውን በአደባባይ እየተገነዘበ በሌላ በኩል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ሀብት እንኳን መዝግቤያለሁ እያለ ይፋ ለማድረግም እየተናነቀ ረዥም ርቀት መሄድ አይቻልም፡፡

በዚሁ ንዑስ ርዕስ በመጨረሻ መነሳ ያለበት የፀረ ሙስና ኮሚሽን ሕዝብን ያሳተፈ የሙስና ትግል የማድረግ ጉዳይ ነው፡፡ በተለይ ሕዝቡ ሙስናን በማጋለጥና በመጠቆም መተማመን ፈጥሮ እንዲታገል ማድረግ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ረገድ አንዳንድ የአገር ተቆርቋዎች እጅ ከፍንጅ እስከማስያዝ የደረስ የፀረ ሙስና ትግል ባያደርግም ጠቁሞ መፍትሔ ያጣ፣ ቅሬታ አቅርቦ ምላሽ ያላገኘ ዜጋ ቁጥሩ ትንሽ አይደለም፡፡ ይህ በመሆኑም ሙስናን የመከላከያ ወሳኞቹ መንገዶች እንደ አዲስ ተጠናክረው መውጣት አለባቸው፡፡

በሙስና የተገኘን ንብረት ማስመለስ

ሙስና የሕዝብና የመንግሥት ሀብትን ሳይሠሩ መዝረፍ ነው፡፡ ሥልጣንን በመጠቀምም ይሁን በማጭበርበር ጥቂቶችን ለማበልፀግ የሚሰረቅ የአገር ሀብት በሕጉ መሠረት ተጣርቶ መልሶ ለሕዝብ ጥቅም እንዲውል ማድረግ፣ የዓለም አቀፍ የፀረ ሙስና ኮንቬንሽን ስምምነት አካል ነው፡፡

በዚህ ረገድ የኢፌዴሪ የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን የሚከተላቸውን የሙስና ተጠርጣሪዎች ያህል ሀብት ማስመለሱን የሚጠራጠሩ አሉ፡፡ እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ በብዙ ሚሊዮን ብሮች በሚገመቱ መሬቶች፣ የመንግሥት ሀብቶች የተከሰሱ ተጠርጣሪዎች ይህን ያህል ዓመትና 20,000 ወይም 10,000 ብር ተቀጥተዋል ሲባል እጅግ የሚያስቅ ፍርድ ነው፡፡ ለነገሩ የአገሪቱን የወንጀል ሕግና ፍርድ ቤቶችንም ትዝብት ላይ የሚጥል ነው፡፡

ለዚህም ይመስላል አንዳንድ ስግብግቦችና ከድህነት የሚብስ የለም በሚል ‹‹ይህን ያህል ሚሊዮን ገንዘብ አግኝቼ ለቅርብ ሰው አሳልፌ ብታሰር ምናለበት›› እስከማለት ውርደት የሚዘቅጡት፡፡

ከዚህ አንፃር በሙስና የተገኘን ንብረት ማስመለስ (Asset Recovery) እነ ቻይና በሄዱበት ደረጃ ሊታሰብበት የሚገባ ነው፡፡ በሙስና ወንጀል የሚንገሸገሹ አገሮች አይደለም በአገር ውስጥ ተሰርቆ የተደበቀን ገንዝብ፣ በሌሎች አገሮችና ዓለም አቀፍ ባንኮች ውስጥ የተሸሸገን ሀብት ጭምር እስከ ማስመለስ የሚደርሱት ሙስና አስከፊ ወንጀል በመሆኑ ነው፡፡

በእርግጥ በሙስና የተመዘበረን የሕዝብ ሀብት ለማስመለስ ገና ከመነሻው የባለሥልጣናትም ሆነ የዜጎች ሀብትና የገቢ ምንጭ መታወቅ አለበት፡፡ ንፋስ አመጣሽና የአቋራጭ ብልፅግና መንገዶችም ንፋስ እንዲመታቸው ማድረግ ሲቻል ነው፡፡

ከሁሉ በላይ የሕዝቡ የጠያቂነትና ታጋይነት ፍላጎት ሲጨምር ወይም እንደ መገናኛ ብዙኃን ያሉ የግልጽነት መሣሪያዎች የሙስና ወንጀሎችን በድፍረት ማጋለጥ ሲችሉ ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ ጉዳይ ላይ ራሱ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታው ዋና ማነቆ እንዳይሆን መፈተሽ ተገቢ ይሆናል፡፡

በጥቅሉ በሙስና የተመዘበረን ሀብት በተጨባጭ አጣርቶ ያለርህራሔ ወደ ሕዝብ የመመለስ ጉዳይ የአገሮች የፀረ ሙስና ድክመት ጥንካሬ ዋነኛ መለኪያ ነው፡፡ በመመርመጥና በእከክልኝ ልከክልህ ማድበስበስ መቀጠል ግን ከወንጀል ተባባሪነት የተለየ ተግባር አይደለም፡፡

በእርግጥ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ባለፉት አሥር ዓመታት ከስምንት ቢሊዮን ብር የማያንስ መሬት፣ በስርቆት የተዘጋጀ የግዥና ሽያጭ ጨረታና ያልተቀረጠበት ንብረት፣ ወዘተ ከሚመለከታቸው አጋር አካላት ጋር ሆኖ መታደግ እንደቻለ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ከዚህ ውስጥ ግን አብዛኛው መሬት ሲሆን፣ በአዲስ አበባና በዙሪያዋ፣ በመ<span style="font-size:12.0pt; mso-bidi-font-size:11.0pt;line-height:200%;font-family:&quot;Ge" ez-1="" numbers","sans-serif"'="">Gለ፣ በአዳማና በሐዋሳ በዝቶ ይታያል፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖ ግን አሁንም ተዘርፎ ሳይመለስ ለጥቂቶች መጠቀሚያ የሆነ የሕዝብ ሀብት ሥፍር ቁጥር እንደሌለው ይታመናል፡፡ በተለይ በትልልቅ ሜጋ ፕሮጀክቶችና በሪል ስቴት ስም ከውጭ ወደ አገር ውስጥ ከቀረጥ ነፃ ገብቶ ጥቂቶችን ቱጃር ያደረገ ብረት፣ ተሽከርካሪ፣ የኮንስትራክሽን ግብዓት ከሕዝብ የተደበቀ ነው ብሎ ማሰብ አደገኛ ነው፡፡

ዓለም አቀፍ ትብብርን ማጠናከር

በፀረ ሙስና ትግሉም ሆነ በሌሎች ደረቅ ወንጀሎች ዓለም የሚተባበርባቸው ኢንተርፖልን የመሳሰሉ ተቋማት እንዳሉ ይታወቃል፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀረ ሙስና ኮንቬንሽን መሠረት ግን አገሮች በሙስና የሚመዘበር የሕዝብ ሀብትን መረጃ የማሳወቅ፣ እንደየአገሮቹ የተናጠል ግንኙነትም ወንጀሎችን አሳልፎ የመስጠት ሥራ ሊያከናውኑ ይችላሉ፡፡

ከሁሉ በላይ የመልካም አስተዳደርና የዴሞክራሲ ባህልን በተለይ በታዳጊው ዓለም በመገንባት መንግሥትና ባለሥልጣን ተጠያቂነት ውስጥ የሚወድቁበትን ሥርዓት ለመፍጠር ይታገዛሉ፡፡ እዚህ ላይ ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናልን የመሳሰሉ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ማኅበራት የሚያካሂዱት ጥናት፣ ሥልጠናና የመረጃ ልውውጥ ለአብነት ይጠቀሳል፡፡

በዚህ ረገድ በየአገሩ ያሉ የፀረ ሙስና መሥሪያ ቤቶች የፀረ ሙስና ኮንቬንሽን አፅዳቂ አገሮች በወሰኑት መሠረት በየዓመቱ ዲሴምበር 9 ቀን የፀረ ሙስና ቀንን ያከብራሉ፡፡ በዚህም በየአገሮቹ የሚገኙ ሕዝቦች በሙስና ምንነትና በሚያስከትለው ጉዳት ላይ ያላቸውን ግንዛቤ በማሳደግ በፅናት ለመታገል ያስችላል፡፡

ይሁንና አንዳንድ ጊዜ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ከዓለም አቀፍ በተለየ መንገድ በዓሉን ለማክበር የሚያደርገው ጥረት ዘወትር ግርምትን የሚያጭር ነው፡፡ ለምሳሌ ዘንድሮ ዓለም ‹‹Break the Corruption Chain›› (የሙስናን ሰንሰለት እንበጥስ) ሲል ያከበረውን በዓል፣ በዚህ አገር የሚበጣጠስ የሙስና ሰንሰለት የሌለ ይመስል ‹‹ሕፃናትና ወጣቶችን በሥነ ምግባር መገንባት አገርን መገንባት ነው›› በሚል መሪ ቃል አክብሮታል፡፡

ይህ ‹‹አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱ አይሰማም›› አካሄድ ብዙዎችን ከማስገረም አልፎ እያሳዘነ ነው፡፡ በዚህ አገር ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት ‹‹ለያዥ ለገናዥ›› አስቸግሯል ብሎ ራሱ ገዥው ፓርቲ መንግሥት እየጮኸ፣ በፀረ ሙስና ትግሉ አስፈላጊውን መስዕዋትነት ከፍሎም ቢሆን ዜጎችን ይታደጋል የተባለው ፀረ ሙስና ተቋም ሕፃናትና ወጣቶችን እናስተምር እያለ ራሱን ይደልላል፡፡ ማስተማሩ ባልከፋ ነገር ግን የሙስና ሰንሰለትን መበጣጠስ መቅደም ነበረበት፡፡

በነገራችን ላይ በየዓመቱ ዓለም ቁልፍ የዓመቱ የፀረ ሙስና ተግባራት በሚል የሚያቀርባቸው መልዕክቶች በእኛ አገር ይቀየራሉ፡፡ ‹‹ይህ ለምን ይሆናል?  ይልቅ እኛንም እያሳሰበን ያለውን ይህን ችግር ሌላው አገር አጋግሎ እንደሚታገለው እኛስ ለምን በዚያው ድምፀት አንሄድበትም?›› ብዬ በአንድ ወቅት የጠየቅኳቸው የኮሚሽኑ አንድ የሥራ ኃላፊ፣ ‹‹የእኛ ዋናው ሥራ ማስተማር እንጂ ማጋለጥና ማሳሰር አይደለም፤›› በማለት ‹‹ነባራዊ ሁኔታውን እያጤን ነው የምንሠራው፤›› የሚል ውኃ እንዳፈሰሱብኝ አልዘነጋውም፡፡

ስለሆነም አገራችን በሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ዓለም አቀፍ ትብብርን በማጠናከር በተሻለ ደረጃ ውጤት ይኑራት ከተባለ በቀዳሚነት ትብብር ትጀምር፡፡ በመቀጠል ለትግሉ እውነተኛ ቁርጠኝነትና መስዕዋትነት የሚከፍል ሥርዓት ይኑራት፡፡ ‹‹ጥቂቶች በልፅገው እስኪጠግቡ ተወት፣ መመታት ያለበት እጁን ሲያነሳ መቁረጥ›› የሚል አካሄድ ዛሬም ድረስ እየተመዘበረች ላለችው አፍሪካ እየጠቀመ እንዳልሆነ እየታየ ነው፡፡ ስለዚህ ብርቱ ትብብርና ትግል ይደረግ፡፡

መደምደሚያ

የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽንም ሆነ የክልል ቢሮዎች በጀት ተመድቦላቸው፣ የሰው ኃይልና ግብዓት ከሞላ ጎደል አሟልተው፣ ኮሚሽነሮችን አሹመው መሥራታቸው አንድ ዕርምጃ ነው፡፡ ግን በቂ አይደለም፡፡

ይህች አገር ከፍተኛ ልማት እየተከናወነባት ያለች ግዙፍ ታዳጊ አገር ወደመሆን እየመጣች ነው፡፡ በ12 ዓመታት እስከ 17 ቢሊዮን ዶላር የውጭ አገር ብድርና ዕርዳታ ተገኝቷል፡፡ ታላቁ የህዳሴ ግድብና የስኳር ፕሮጀክትን ለመሰሉ የልማት ሥራዎች በጨረታ ሰነድም ይሁን በድርድር በአንድ ጊዜ እስከ ሁለት ቢሊዮን ዶላር የውጭ ግዥ የሚፈጽም፣ ለባቡርና የግዙፍ መንገድ ሥራዎች በርካታ ቢሊዮን ዶላሮች የሚገመት ጨረታ ይሰጣል፡፡

ይህ ሁሉ የሕዝብ ሀብት በቂ ጥበቃ፣ ጠንካራ የግልጽነትና ተጠያቂነት መርህ ተግባራዊነት፣ እንዲሁም የማያቅማማ የፀረ ሙስና ትግል ካላገኘ ምንም ቢባል ምንም ስርቆሽ አይቀርም፡፡ በጥቅም መደላደል፣ ወደ ሥልጣን የተጠጋን መጠቀም፣ ወዘተ  ሊኖር እንደሚችል ጥርጥር የለውም፡፡ ስለሆነም አሁን ባለው የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና አካሄድ ብቻ ችግሩን መፍታት አይቻልም፡፡ ሥጋቱንም ማስቆም ያዳግታል ባይ ነኝ፡፡ እናንተስ?

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው mm2oo [at] yahoo.com ማግኘት ይቻላል፡፡