ኑሮና ዴሞክራሲ በኢሕአዴግ ዘመን

ሰሞኑን በማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ ስለ ግንቦት 20 የብር ኢዮቤልዩ 25ኛ ዓመት ብዙ ነገሮች እየተባሉ ነው፡፡ በመገናኛ ብዙኃኑ፣ በየቤቱና በየካፍቴሪያውም እንዲሁ እየተባለ ነው፡፡ ግንቦት 20ን ምክንያት በማድረግ በየተቋማት የሚደረጉት ውይይቶች፣ የመንገድ ላይ ባዛሮች፣ ኤግዚቢሽኖችና ሌሎችም ስለግንቦት 20 እንዲያስቡ የግድ ይላል፡፡ ‹‹ግንቦት 20 ለምን ይከበራል?›› የሚል ጥያቄ ተነስቶ በተለያየ መንገድ በብዙ ማስረጃዎች ተደግፎ ተቀምጧል፡፡ ለእንዲህ ያለው ጥያቄ ብዙዎች በመደገፍና በመቃወም አስተያየታቸውንም ሰጥተዋል፡፡ ‹‹ዕለቱ መከበር የለበትም አለበት›› የሚለው ክርክር ባለበት ቢተው፣ እንዲህ ያነጋገረው ምን ዓይነት ለውጦችን አስከተለ? የሚለው ጥያቄ ግን ቢፈልጉም ሳያነሱ የሚተውት አይሆንም፡፡

ጥያቄው የአፄ በኃይለ ሥላሴን፣ የደርግ ሥርዓትን ባለፉ፣ እንዲሁም በኢሕአዴግ ሥርዓት አድገው ተምረው በምርጫ ድምፅ ለመስጠት በበቁ ወጣቶች ጭምር የሚነሳ ነው፡፡ በእነዚህ ሥርዓቶች ውስጥ ያለፉ፣ የተማሩና የአገሪቱን ፖለቲካና ኢኮኖሚ የሚከታተሉ፣ ፊደል ያልቆጠሩና መረጃ የሌላቸው ሁሉም በየፊናቸው ግንቦት 20ን እና ግንቦት 20 መሠረት የሆነውን ሥርዓት በተለያየ መነፅር ይመለከታሉ፡፡ በአንድ በኩል ባለፉት 25 ዓመታት በሕዝቡ ኑሮ ላይ ምን ለውጥ ተገኘ የሚለው በሌላ በኩል፣ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን መሠረት ያደረገ የብዙኃን ፖለቲካ ስለመፈጠሩ ጥያቄ ይነሳበታል፡፡

ኢሕአዴግና ማኅበራዊ ኑሮ

ባለፉት 25 ዓመታት አዎንታዊ ለውጦች መኖራቸውን ይህም በኢኮኖሚ ዕድገት፣ በትምህርትና በጤና ሽፋን እንዲሁም በመሠረተ ልማት መስፋፋት እንደሚገለጽ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ ነገር ግን ዕድገቱ ‹‹በግለሰቦች ሕይወት ላይ ምን ጠብ አደረገ?›› የሚለው ጥያቄ የብዙዎች ነው፡፡

የ75 ዓመቷ ወይዘሮ ግርማነሽ ወልደ ጻዲቅ ከኑሮ ጥሩነት አንፃር የአፄ ኃይለ ሥላሴ ሥርዓት ጥሩ ነበር ብለው ያምናሉ፡፡ የደርግ ስም እንዲነሳቸው አይፈልጉም፡፡ ‹‹ለወጣቱ ሰላም ማደር ለሴቶች እኩልነት ግን ኢሕአዴግ ይሁን፤›› ይላሉ፡፡ የኑሮ ሁኔታን በማነፃፀር ዛሬ ያለው የኑሮ ውድነት እጅግ ከባድ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ‹‹እንደ መንገድ ያሉ መሠረተ ልማቶች መስፋፋታቸው ትልቅ ነገር ቢሆንም፣ አንድ ኪሎ ምስር 60 ብር በሚሸጥበት ገበያ ደሃ ምን በልቶ ያድራል?›› በማለት ይጠይቃሉ፡፡ ‹‹ነፃ ገበያ ብሎ ነጋዴ ይጫወትብናል፡፡ ይኼ መንግሥት ገበያ አይቆጣጠርም፡፡ መንገድ ቢሠራ ቢታይ ቢታይ ምን ያደርጋል? ምግብ አይሆን፤›› ይላሉ፡፡

በሌላ በኩል የትምህርት ተደራሽነት የጨመረ ቢሆንም የትምህርት ጥራት ወደቀ የሚባልበት ደረጃ ላይ መድረሱን፣ በየክልሉ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ማስፋፋት ከፖለቲካ ፋይዳ ውጪ ምንም ዓይነት ትርጉም እንደሌለው የሚያስረዱ አሉ፡፡ በተመሳሳይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ቅበላ 70/30 መሆን በአገሪቱ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ሊኖራቸው የሚችሉ፣ ጥልቅ አሳቢዎች፣ የማኅበራዊና የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራንና ተንታኞችን በማፍራት ረገድ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳለው የሚገልጹ ጥቂት አይደሉም፡፡

ምንም እንኳ የአፄ ኃይለ ሥላሴ ሥርዓትን የሚያውቁት በትንሹ ቢሆንም፣ በወቅቱ ሰዎች የሚያገኙት ገቢ በጥሩ ሁኔታ ያኖራቸው እንደነበር የሚናገሩት አዛውንት ዛሬ ስልሳዎቹ አጋማሽን ተሻግረዋል፡፡ ዛሬም ግን በአንድ የግል ድርጅት ውስጥ ተቀጥረው በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡ ‹‹የደርግ ሥርዓት ፖለቲካው የማያራምድ ነበር›› ቢሉም ሠርተፊኬት፣ ዲፕሎማ ወይም ዲግሪ ለነበረው ሰው ሥራ ማግኘት ከባድ ችግር እንዳልነበር ያስታውሳሉ፡፡ በተመሳሳይ ተቀጣሪዎች የሚያገኙት ገንዘብም በወቅቱ ጥሩ የሚያኖር እንደነበር ይገልጻሉ፡፡

መንግሥት ከችርቻሮ ጀምሮ እስከ ላይ ያለውን የሸቀጥ ማከፋፈል ተቆጣጥሮት የነበረ ቢሆንም፣ ‹‹ሰዎች ተሠልፈው የሚፈልጉትን ነገር ያገኙ ነበር›› በማለት የሰዎች ገቢ ኑሮን የሚሸከም እንደነበር ይመሰክራሉ፡፡

ዛሬ ሸቀጥ (እንደ ስኳርና ዘይት)፣ ታክሲና ሌሎችም በሠልፍ መሆናቸውን በመጥቀስ ‹‹ዕድገቱ የታለ›› ዓይነት ጥያቄ የሚያነሱ ጥቂት አይደሉም፡፡ በቀድሞ ሥርዓት (የመንግሥት ሠራተኛ ነበሩ) የመስክ ሥራ አበላቸው 16 ብር እንደነበር በማስታወስ፣ ዛሬ በግል ድርጅት ተቀጥረው እያገኙ ያሉት ደመወዝ ምንም እንኳ በንፅፅር ከፍተኛ ሊባል ቢችልም ኑሮን የማይሸከም እንደሆነ፣ ‹‹የኢኮኖሚ ዕድገት ቢኖርም ዕድገቱ በግለሰብ የሚመነዘር አይደለም፤›› በማለትም ይገልጻሉ፡፡

የመሠረተ ልማቶች መስፋፋት፣ የፈጠራዎች መበረታታትና የግሉ ዘርፍ መስፋፋት የዚህ ሥርዓት አዎንታዊ ገጽታ ብለው የሚያነሷቸው ናቸው፡፡ የሰዎችን ገቢና የኑሮ ሁኔታን በሚመለከት የእሳቸውን ሐሳብ የሚጋሩትና በ1960ዎቹ መጀመሪያ ላይ የሚገኙት አቶ መኮንን የተማረ የሰው ኃይል ብዙ ቢሆንም፣ ይህን የሰው ኃይል የሚቀበል የሥራ ገበያ አለመኖር የዚህ ሥርዓት ከባድ ችግር ነው ይላሉ፡፡ በሌላ በኩል የፖለቲካ አመለካከት ሥራ ለማግኘት መሥፈርት መሆኑ የሙያና የብቃትን ዋጋ ያወረደ አደገኛ የሥርዓቱ መገለጫ እንደሆነ፣ በአቋራጭ መክበርም የማይካደው የኢኮኖሚ ዕድገት ማሳያ ነው ብለው ያምናሉ፡፡

‹‹በተለይም ከ1997 ዓ.ም. ወዲህ በኢኮኖሚው ዘርፍ ዕድገት ተመዝግቧል፡፡ ዕድገቱ የሥርዓቱ ጥንካሬ ያስከተለው ሳይሆን ዓለም አቀፍ ሁኔታዎች በተለይም በኢኮኖሚው ዘርፍ ለኢትዮጵያ ምቹ በመሆኑ ነው፤›› የሚል አስተያየት የሚሰነዝረው ሔኖክ ፀሐዬ የ26 ዓመት ወጣት ነው፡፡ የመጀመርያ ዲግሪውን በታሪክ ሁለተኛውን ደግሞ በኮሙዩኒኬሽን ሠርቷል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ የቻይና በኢኮኖሚው ወደ ላይ መምጣትና ያለቅድመ ሁኔታዎች ለኢትዮጵያ ድጋፍ መስጠት በኢኮኖሚው ዘርፍ ተመዝግቧል ከተባለው ዕድገት ጀርባ አለ የሚለው ምቹ ዓለም አቀፍ ሁኔታ ነው፡፡

ለአማራጭ ድምፆች በር መዝጋት ከመቼውም በበለጠ የሥርዓቱ ወቅታዊ መገለጫ ሆኗል የሚለው ሔኖክ፣ ከተመዘገበው ዕድገትም እየተጠቀሙ ያሉት ጥቂቶች እንጂ ብዙኃን አይደሉም የሚል አቋም አለው፡፡ ‹‹ሥርዓቱ እያገለገለ ያለው ላይ ላሉ ጥቂቶች ነው፤›› ይላል፡፡

ኑሮውን በአሜሪካ ለማድረግ ከአገር ከወጣ ዓመት ሊሞላ ነው፡፡ ብዙዎች የተሻለ ነገር ፍለጋ እንደ ሔኖክ በተለያየ አጋጣሚ ከአገር እየወጡ ነው፡፡ ሰዎች ሁሌም የተሻለ ነገርን በማሰብ መሰደዳቸው የማያቋርጥ የስደት ዑደት አካል ቢሆንም፣ ሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪ እስከ መሥራት የደረሱና ጥሩ የሚባል ሥራ ያላቸውም ከመቼውም የበለጠ ስደትን ምርጫ እያደረጉ መሆኑ ግን ስለአገሪቱ ኢኮናሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ሁለንተና የሚናገረው ብዙ ነገር መኖሩ የሚጠረጠር አይሆንም በማለት ይሞግታል፡፡

በማኅበራዊና በኢኮኖሚው ዘርፍ ጉልህ ስኬቶች ተመዝግበዋል የሚሉት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞ የጋዜጠኝነትና የኮሙዩኒኬሽን ትምህርት ቤት ዲን ዶ/ር አብዲሳ ዘርዓይ በዚህ ረገድ ትምህርት፣ ጤናና ሌሎች የማኅበራዊ አገልግሎት ዘርፎችን ይጠቅሳሉ፡፡ የጥራት ችግር ግን በሁሉም ዘርፎች እንዳለ መሆኑንም ያነሳሉ፡፡ በመሠረተ ልማት መስፋፋትም ጉልህ ዕድገት መታየቱንና የጠቀሷቸውን ነጥቦች መሠረት በማድረግ ባለፈው አሠርት ጉልህና ጠንካራ የኢኮኖሚ ዕድገት ተመዝግቧል ሲሉ ይደመድማሉ፡፡

ስለአጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕድገቱና ልማቱ ይህን ቢሉም ግን ዕድገቱና ልማቱ በተጨባጭ ትርጉም የሚኖረው በሰዎች ሕይወት ላይ በሚያመጣው አዎንታዊ ለውጥ ነው ይላሉ፡፡ ነገር ግን መሬት ላይ ያለው እውነታ ከኢኮኖሚ ዕድገቱና ከልማቱ ጋር አብሮ እየሄደ እንዳልሆነ፣ የድህነት ሥር መስደድ፣ የትምህርት ዕድል ያላገኙ በርካታ መሆን ብዙ እየተወራላት ያለው የማኅበራዊና ኢኮናሚያዊ ስኬት በዜጎች ሕይወት ላይ ይህ ነው የሚባል ለውጥ እንዳላመጣ ማሳያ መሆናቸውን ያስረዳሉ፡፡

ኢሕአዴግና ዴሞክራሲ

የዛሬ 25 ዓመት ኢሕአዴግ ሥልጣን ላይ ሲወጣ፣ በሽግግር ዘመኑ በተለያዩ መንገዶች የትጥቅ ትግል ሲያካሂዱ የነበሩ ድርጅቶች ሳይቀር በፓርላማ እንዲሳተፉ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ከፀደቀ በኋላም በተካሄዱት ሁለት ምርጫዎች ማሸነፍ ባይቻልም፣ በኢሕአዴግ ተቃራኒ የተሠለፉ ድርጅቶች በፓርላማ ውክልና እያገኙ ሥልጣን ላይ ካለው ገዢው ፓርቲ ውጪ የተለየ ሐሳብ ያለውን የኅብረተሰብ ክፍል የሚመለከቱ የመንግሥት አፈጻጸምና የሕገ መንግሥት ጥሰትን በተመለከተ የሚያነሱዋቸው ጉዳዮች፣ ፓርላማው ቢያንስ የሕዝብ ውክልና የሚንፀባረቅበት ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ዛሬስ?

ዶ/ር አብዲሳ ዘርዓይ የብሔር ብሔረሰቦችን መብት እስከ መገንጠል የሚያከብረው፣ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓትን፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽን፣ የመሰብሰብን፣ የኢኮኖሚ ነፃነትን (Economic Liberalization) እና ሌሎችንም የሚያስቀምጠው ሕገ መንግሥት የሥርዓቱ የመጀመርያው አዎንታዊ ዕርምጃ እንደሆነ ይጠቅሳሉ፡፡ ‹‹ሕገ መንግሥቱ ስለሆንነው ላይሆን መድረስና መሆን ስለምንፈልገው የሚናገር ነው፡፡ ስለዚህም በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያችን ምን ያህል እየሄድን ነው የሚለውን ያንፀባርቃል፤›› ይላሉ፡፡ ስለዚህም እንደ እሳቸው ምልከታ ያለፉት 25 ዓመታት እንዴት ናቸው የሚለው ከዚህ አንፃር የሚገመገም ይሆናል፡፡

ኢሕአዴግ ገና ሥልጣን በያዘ የመጀመርያ ዓመት የተጻፉ ‹‹የአብዮታዊ ዴሞክራሲና የአንድነት ጥያቄ›› ውስጥ የኢሕአዴግና የተቃዋሚዎች ዋና ልዩነት፣ የግዛት አንድነትና የሕዝቦች አንድነት አቀንቃኝነት ሆኖ እንደሚቀጥል ያብራራል፡፡ የኢሕአዴግ ልሳን በሆነው ኅትመት በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የተጻፈ እንደሆነ የሚገመት መጣጥፍ፣ የኢሕአዴግ ፌዴራላዊና አብዮታዊ አስተሳሰብ ሕዝቡ ውስጥ ገዢ ሆኖ ከመስረፁ በፊት፣ የያዘውን አዲስ ሥርዓት ካለፉት መሣፍንታዊና ወታደራዊ ሥርዓት የሚቃረን በመሆኑ፣ ‹‹የቀድሞ ሥርዓት ናፋቂዎች›› የሚላቸውን ሥርዓቱን በማጥላላትና በሰፊው ሕዝብ ተቀባይነት እንዳይኖረው ለማድረግ እንደሚጥሩ ያትታል፡፡ ይህንን በመፍራት ግን ሐሳብን በነፃነት የመግለጽና የመደራጀት መሠረታዊ መብት እንደማይገድብ ሰነዱ ያትታል፡፡ በድምዳሜውም፤ ‹‹የቀድሞ ሥርዓት ናፋቂዎች›› የሚላቸው እነዚህ አካላት በሦስት ክንፍ ተደራጅተው ይመጣሉ ይላል፡፡ በተቃዋሚነት፣ በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችና በነፃ ፕሬስ፡፡ እነዚህ አካላት ጥምር በመፍጠር ‹‹የሦስትዮሽ›› ሲመስላቸው የዘር ጥላቻን በመንዛት ጭምር፣ አንድ ቀን አንድ ላይ በመተባበር ሥርዓቱን ለመገዝገዝ የተባበሩ ጊዜ ይህንን ፀረ ዴሞክራቲክ አስተሳሰብ ለማሸነፍ የሚደረግ ትግል የመጨረሻ ፈተና እንደሚሆን ጽሑፉ ይተነብያል፡፡

እስከ 97 ምርጫ ጥላቻንና የእርስ በርስ ግጭትን የሚቀሰቅሱ ያላቸውን ‹‹ነፃ›› ሚዲያዎች ሳይቀር ገዢው ፓርቲ የታገሳቸው መሆኑን፣ በምርጫው ማግሥት ለተፈጠረው ቀውስ ተጠያቂ አድርጎ ከተቃዋሚዎች አመራሮች ጋር ዕርምጃ በመውሰድ ለእስር እንደዳረጋቸው መግለጹ ይታወሳል፡፡ በይቅርታ ከወጡም በኋላ ብዙዎቹ ከኅትመት ውጪ ሆነዋል፡፡ ብዙዎቹ ተሰደዋል፡፡ አሊያም ሙያቸውን ትተዋል፡፡ ሌሎችም ሲንገዳገዱ ቆይተዋል፡፡

አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት፣ የ1997 ምርጫ እንዲህ ዓይነት ትግል የተካሄደበት ነው፡፡ በዚህ ፈታኝ ምርጫ ከቅስቀሳው ጊዜ ጀምሮ ተበታትነውና በግል ሲንቀሳቀሱ የቆዩት ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሁለት ትልልቅ ጎራዎች ተሰባስበው ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ንብረትና ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ በሚሉ ስያሜዎች ገዢውን ፓርቲ ተፈታትነዋል፡፡ በሁለቱ ድምር ውጤትም ገዥውን ፓርቲ ማሸነፋቸውንም እስከማሳወቅ ደርሰው ነበር፡፡ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው የአዲስ አበባ መስተዳድርን ሙሉ ለሙሉ ቅንጅት ማሸነፉ አይዘነጋም፡፡

ኢሕአዴግ በመጀመርያው (በ1987) ምርጫ ከ547 የፓርላማ መቀመጫዎች 490 አግኝቶ የነበረ ሲሆን፣ በሦስተኛ ጠቅላላ ምርጫ ወደ 365 ዝቅ ሲል ተቃዋሚዎች ደግሞ 236 መቀመጫዎችን አግኝተው ነበር፡፡ የምርጫ ውጤቱን ያልተቀበሉ ተቃዋሚዎች ተሰረቀ ያሉትን ድምፅ ለማስመለስ በአመፅና በኃይል ለማስመለስ እንቅስቃሴ አድርገው የአዲስ አበባ አስተዳደርንም ሳይረከቡ፣ ቀላል የማይባል የፓርላማ መቀመጫንም ትተውታል፡፡ ለአንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት፣ በሁለቱም ወገኖች ጥፋት ተከፍቶ የነበረው የዴሞክራሲ ጭላንጭል ተቀልብሷል፡፡

ኬቲል ትሮንቮል የተባሉት ተመራማሪ በኢትዮጵያና በሌሎች አገሮች የምርጫ ሒደት በማጥናት የሚታወቁ ሲሆኑ፣ “Ambiguous Elections: The Influence of non-electroal Politics in Ethiopian Elections” በሚለው ጥናታዊ ጽሑፋቸው ምርጫውን ተከትለው የተወሰዱ ዕርምጃዎችን የዳሰሱ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ጉዞ የኋሊት ሊጓዝ እንደሚችልም ደምድመው ነበር፡፡ በተለይ ደግሞ ከኢሕአዴግ ውጪ ሐሳቦች የሚንፀባረቁባቸው ነፃ ፕሬሶች፣ ሲቪክ ማኅበረሰቦችና ተቃዋሚ ፓርቲዎችን የሚመለከቱ ሕጎች በመፅደቃቸው ሳቢያ የአደጋው ቀይ መብራት መታየት ጀምሯል ብለዋል፡፡

ስቲቪን ሌቪስኪና ሌሎች “Competitive Authoritarianism” በማለት የሚጠሩት ካምፕ አለ፡፡ በዚሁ ካምፕ የሚካተቱ አገሮች ምርጫ ቦርድና የፍትሕ ተቋማት ያሉዋቸው ቢሆንም ነፃ አይደሉም፡፡ ሚዲያው በገዢው ፓርቲ ቁጥጥር ሥር ይውላል፡፡ ምርጫ በየጊዜው ይካሄዳል፡፡ ሜዳው ግን ለሁሉም እኩል አይደረግም፡፡ ተቃዋሚዎች እንዲኖሩ ይደረጋል፡፡ ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በተለያዩ መንገዶች እንዲዳከሙ ይደረጋል፡፡ በርካታ ፓርቲዎች ቢኖሩም ቀድሞ የተገመተው ገዢው ፓርቲ ያሸንፋል፡፡

ከ2002 ምርጫ ውጤት በኋላ የፖለቲካ ተመራማሪዎቹ ኢትዮጵያ ይኼንን ካምፕ መቀላቀሏን አምነዋል፡፡ የሥርዓቱ ባህርያት ከአንድ ፓርቲ ሻል ያለ ቢሆንም በመሠረቱ እምብዛም አይደለም በማለት፡፡

ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ ወደ አውራ ፓርቲ

የ2002 ምርጫ ቅስቀሳ ከመጀመሩ በፊት የፕሬስ፣ የፀረ ሽብርና እንዲሁም የሲቪክ ማኅበረሰብ አዋጆች ዴሞክራሲያዊ ምኅዳሩን እንዲታፈን አድርገውታል ተብሎ በብዙዎች የተተቸ ሲሆን፣ ለተቃዋሚዎች ቅርበት ያላቸው ተብሎ የሚታመንባቸው የመምህራን ማኅበር፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና ሌሎች ነፃ ማኅበራት እንዲበተኑ ተደርገዋል ተብሏል፡፡ ኢሕአዴግ በራሱ አነሳሽነት በአገር አቀፍ ደረጃ የወጣቶች ማኅበር፣ የሴቶች ማኅበርና የነጋዴዎችና የነዋሪዎች ፎረም የሚባሉ የተለያዩ ደጋፊ ማኅበራት እንዲቋቋሙ አድርጓል፡፡ አንዲሁም ከ1997 ዓ.ም. በፊት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ አባላት ያልነበሩት ኢሕአዴግ እስከ ሰባት ሚሊዮን የሚሆኑ በተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች እየተደለሉ አባል እንዲሆኑ ስለመደረጋቸው ብዙ ተብሏል፡፡

ይኼም ብቻ ሳይሆን እንደ ዋና የምርጫ ስትራቴጂ በልማት አደረጃጀት ስም ሕዝቡ በአንድ ለአምስት እንዲደራጅ የተደረገ መሆኑ፣ በዋናነት የፖለቲካ መሣሪያ ሆኖ ጥቅም ላይ መዋሉም በስፋት ይነገራል፡፡ የቀድሞ የኢትዮጵያ አየር ኃይል አዛዥ ሜጀር ጄኔራል አበበ ተክለ ሃይማኖት (ጆቤ) ይኼ አደረጃጀት ደንበኛ የስለላ መዋቅር እየሆነ መመጣቱንና ለዘመናት የቆዩ ባህላዊ እሴቶች ሊበታትን እንደሚችል ሥጋታቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ምርጫ 2002 በዚሁ ድባብ የተገባ ሲሆን፣ በወቅቱ ጠንካራ የተባለው መድረክ አንድ ወንበር የግል ተወዳዳሪ የሆኑት ዶ/ር አሸብር ወልደ ጊዮርጊስም አንድ ወንበር ከማግኘት ውጪ ኢሕአዴግና አጋሮቹ 99 በመቶ የፓርላማውን መቀመጫዎች ተቆጣጥረዋል፡፡ በቀጣዩ ማለትም ባለፈው ዓመት በተካሄደው አምስተኛ ዙርም ይባስ ብሎ ሙሉ በሙሉ ኢሕአዴግ ከነአጋሮቹ የፓርላማውን ወንበሮች ተቆጣጥሯል፡፡

የምርጫ ተመራማሪዎች በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ዓይነት የተለያዩ አስተሳሰቦችና ብሔሮች ባሉባቸው አገሮች አንድ ፓርቲ ከ60 በመቶ በላይ ካሸነፈ፣ የውጤቱ ታማኝነትና የሒደቱ አግባብነትን ጥያቄ ውስጥ ይከቱታል ይላሉ፡፡

ዶ/ር አብዲሳ የፖለቲካ ፓርቲዎች መኖርና የምርጫ በየጊዜው መካሄድ ሥርዓቱን ተቀባይነት ያለው ከማስመሰል (Legitimizing the System) ውጪ በፖለቲካው ምኅዳር ይህ ነው የሚባል ለውጥ እንዳላመጣና ከጊዜ ወደ ጊዜ የፖለቲካው ምኅዳር እየጠበበ መሄዱን ይገልጻሉ፡፡ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽና የተቃውሞ ድምፅ የማሰማት ነገርም አስቸጋሪ እየሆነ እንደመጣ፣ ይህ በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየበረታ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ይህም ኢሕአዴግ በቅርብ ያደረገው የፖለቲካዊና የኢኮኖሚያዊ ቅኝት ለውጥ ውጤት እንደሆነም ይገልጻሉ፡፡

ነገር ግን እንደ ኢትዮጵያ ባለ ፅንፍ የወጡ አቋሞች በሚንፀባረቁበት የፖለቲካ ምኅዳር ግን የአውራ ፓርቲ ሥርዓት መዘርጋት ቀላል አይሆንም አይቻልም ማለት ባይቻል እንኳን፣ አስቸጋሪ መሆኑን ዶ/ር አብዲሳ ይገልጻሉ፡፡ ስለዚህም እየታየ ያለው ነገር መንግሥት ኃይል የመጠቀም አማራጭን እየወሰደ የመሆኑ ምስክር ነው ያስብላል፡፡ በተጨማሪም በኢኮኖሚው ውስጥ ያሉ አዎንታዊ ለውጦችን በማስቀጠል ተቀባይነቱን የማስቀጠል ፍላጎት አለው የሚሉት ኢሕአዴግ፣ ይህን የሚያደርገው በዴሞክራሲ ረገድ ያለው ነገር ምንም ይሁን ምን የኢኮኖሚ ዕድገቱ እስከቀጠለ ድረስ በዜጎች ዘንድ ተቀባይነት ይኖረኛል በሚል ሥሌት እንደሆነም ያስረዳሉ፡፡

ሰማያዊ፣ መኢአድ፣ ኢዴፓና መድረክ እርስ በርሳቸው በምርጫው ባይተባበሩም በሁለቱ ምርጫዎቹ ውጤት ላይ ተመሳሳይ አቋም በመያዝ በአገሪቱ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት አደጋ ላይ መውደቁን ይገልጻሉ፡፡ ቢሆንም አሜሪካን ጨምሮ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ አቀንቃኝ ተብለው የሚታመንባቸው ለጋሽ አገሮች እምብዛም ተቃውሞ አላሰሙም፡፡ ለአንዳንድ ተመልካቾች በኢትዮጵያ ኢሕአዴግ በነፍጥ እንጂ በምርጫ ከሥልጣን አይወርድም በማለት የትጥቅ ትግል ላወጁ ድርጅቶች ትልቅ ብሥራት ቢሆንም፣ ኢሕአዴግ ግን ውጤቱን በተለየ መንገድ ይተነትናል፡፡

አውራ ልማታዊ መንግሥት

ኢሕአዴግ በ1993 ዓ.ም. ካጋጠመው ክፍፍል በኋላ አዲስ የመጣው አስተሳሰብ ‹‹ተሃድሶ›› የሚባል ሲሆን፣ ከመበስበስ አደጋ ለመውጣት እንደተጠቀመበት ይገልጻል፡፡ ከ1997 ዓ.ም. በኋላ ዳግም ከላይ የተጠቃቀሱት ዕርምጃዎችን ከመውሰድ ጎን ለጎን ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት የሚል መርህ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብን እየተካ መጣ፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ለዶክትሬት ዲግሪያቸው የሠሩት ጥናት የሚያጠነጥነው ይኼ አስተሳሰብ ላይ ነው፡፡ የምሥራቅ እስያን የልማት ጉዞ በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ ለመድገም ያለመ ነበር፡፡ እናም ደቡብ ኮሪያና ጃፓንን የመሳሰሉት አገሮች በፍጥነት ያደጉበት ይኼው መንገድ በመሆኑ፣ የእነዚህ አገሮች ዴሞክራሲያዊነት ግን ሁሌም ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ነው፡፡ ለመድበለ ፓርቲ ሥርዓትና ሐሳብን በነፃነት ለመግለጽ መብት ለአብነት የሚጠቀሱ አገሮች አይደሉም፡፡ አንዳንድ ተንታኞች ግን በእነዚህ አገሮች ያሉት መብቶች በኢትዮጵያ እንደሌሉ ያስረዳሉ፡፡

የኢሕአዴግ የንድፈ ሐሳብ ትንታኔ መጽሔት የሆነው አዲስ ራዕይ በ2002 ምርጫ ማግሥት ሐምሌ ወር ላይ ለኅትመት የበቃ ሲሆን፣ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ እንደተጻፈ የሚነገርለት ‹‹የምርጫ 2002 ስትራቴጂያዊ ፋይዳ›› በሚል ርዕስ የቀረበው ሐተታ የገዢውን ፓርቲ አቅጣጫ አመላካች ነበር፡፡ በመግቢያው ኢሕአዴግ በዚህ ደረጃ በምርጫ አሸንፎ እንደማያውቅ አስረድቶ፣ ከሁሉም በላይ ምርጫው በሰላም መጠናቀቁ ትልቅ ትርጉም እንደሚሰጠው ይገልጻል፡፡

‹‹ተቃዋሚ ፓርቲዎች የዛሬውን ዓይነት ሁሉን አቀፍ ጠቅላላ ውድቀት አጋጥሟቸው አያውቅም፤›› በማለት፣ ‹‹ምርጫ 2002 በአገራችን የህዳሴ ጉዞ ውስጥ አንድ አዲስ ስትራቴጂካዊ ምዕራፍ የከፈተ ፍፃሜ ነው፤›› የሚለው የታዛቢዎች እምነት እንደሆነ ያስረዳል፡፡

ተቃዋሚዎችና የፖለቲካ ተንታኞች የምርጫ ውጤቱን አስመልክተው ከያዙት አቋም በተቃራኒ፣ ኢሕአዴግ አጠቃላይ አሸናፊ የሆነበት ምክንያት፣ ‹‹ልማታዊ መስመራችን የኪራይ ሰብሳቢነት መስመርን በልማት ትግል በማሸነፉ ነው፤›› ይላል፡፡ በ1994 ዓ.ም. ‹‹የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ››ን በተመለከተ የቀረበው የስትራቴጂ ውጤት መሆኑንም ያስረዳል፡፡ የምርጫ 97 ቀውስም ይህንን በደንብ ተግባራዊ ያለማድረግ ውጤት መሆኑን ይኼው ሰነድ ያብራራል፡፡ ፓርላማ የገቡ ተቃዋሚዎችም የሚያራምዱት የጥላቻና የቂም በቀል ፖለቲካ እንደሚሆን ያትታል፡፡ ኢሕአዴግ በዚህ ሰነድ ዴሞክራሲ በዋናነት ከፖለቲካዊ መብት አንፃር ይልቅ፣ ከመረጋጋትና ከደኅንነት አንፃር የቃኘው ሲሆን፣ ‹‹ፍልሚያው የተረጋጋና ሰላማዊ ሆኖ ሊዘልቅ የሚችለው ፀረ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት የሆኑ ኃይሎች ሰፋ ያለ ኅብረተሰብ ክፍል የማያንቀሳቅሱ፣ በፖለቲካ ጨዋታ የሚኖራቸው ድርሻም አነስተኛ (ማርጂናል) ሲሆን ብቻ ነው፤›› ይላል፡፡

ሰነዱ ፀረ ዴሞክራሲ ኃይሎች ያላቸው ተቃዋሚዎችን ሲሆን፣ የተረጋጋ ዴሞከራሲ ልምድ የተወሰደው የቬይመር ሪፐብሊክ አሳዛኝ ክስተትን በመጥቀስ ነው፡፡ ጀርመን እ.ኤ.አ. በ1918 በአንደኛው የዓለም ጦርነት ስትሸነፍ በኢዴሞክራሲያዋ ሥርዓት ምትክ የተተካው ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ነበር፡፡ ለ15 ዓመታት የቆየው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ቬይመር ሪፐብሊክ እየተባለ ነበር የሚጠራው፡፡ በግራና በቀኝ ሕገ መንግሥቱን የማይቀበሉ ድርጅቶች በዚሁ ሕጋዊ ምርጫ ሥልጣን ላይ በመውጣታቸው፣ ከእነዚህም የናዚ ፓርቲ ነጥሮ የወጣ መሆኑንና የፋሽስቱ ሥርዓት ያደረሰው ዕልቂት ይታወሳል፡፡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከሆነ፣ በናዚ ፓርቲ ሥርዓት ዙሪያ የጥንት ሥርዓት ናፋቂዎች የተሰበሰቡበት በመሆናቸው ከኢትዮጵያ ጋር ለማነፃፀርያ የቀረበ ነበር፡፡

‹‹የአገራችን የምርጫ 97 ልምድም ይህንኑ ሀቅ የሚያረጋግጥ ነው፤›› በማለት፣ ‹‹ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ሕገ መንግሥቱ ከሚፈቅደው ሥርዓት ውጪ ለመቀየርና ቀደው ለመጣል የተዘጋጁ ነበሩ፤›› በማለት እየማሉና እየገዘቱ በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ሽፋን ተመሳሳይ ተግባር ለመፈጸም ያደረጉት ጥረት በማስረጃ የተረጋገጠ እነደሆነ ያስረዳል፡፡ ሰነዱ እንደሚለው ሆኖም ገና ለገና እንዲህ ዓይነት ዘረኛ አቋም አላቸው በማለት መብታቸውን ከመከልከል መቆጠብ እንዳለበት ተሰምሮበታል፡፡

ሰነዱ ምርጫ 2002 የዚህ ፀረ ዴሞክራሲ ኃይሎች የሚላቸው ለሥርዓቱ አደጋ የማይሆኑበት ደረጃ ላይ መድረሳቸው አመላካች መሆኑን ያስረዳል፡፡ የተወሰደውም ተሞክሮ ከ60 ዓመታት በላይ በሥልጣን ላይ የቆየው የጃፓንና የስዊድን በተከታታይ ምርጫን በማሸነፍ ሥልጣን ላይ የቆዩትን ድርጅቱ በምሳሌነት ይወስዳል፡፡ ይህ የአውራ ፓርቲ ሥርዓት ተብሎ የሚታወቀው የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት አንድ ገጽታ መሆኑን ሰነዱ ያስረዳል፡፡

የአውራ ፓርቲ ዴሞክራሲ

ወጣት ናሁሰናይ በላይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌዴራሊዝም ተቋም መምህርና የዶክትሬት ተማሪ ነው፡፡ ጥናቱ የሚያጠነጥነው አብዮታዊ ዴሞክራሲ ላይ ሲሆን፣ በሽግግር ዘመን ሌሎችን ለማካተት የተደረገ ጥረት መጥፎውን ጊዜ ለማለፍ ረድቷል ይላል፡፡ ‹‹አገር ትበተናለች›› የሚለው ሥጋት የፈጠረውን አገላለጽ በድጋሚ መስማት እንደማይፈልግ ገልጾ፣ አሁን ላይ ተሁኖ ሲታይ የፓርላማው ዴሞክራሲ ከሽግግር ጊዜም የባሰ መሆኑ ይገልጻል፡፡

በ1997 ዓ.ም. ሥልጣን ላይ ሊወጡ የነበሩት ኃይሎች ፀረ ዴሞክራሲ መሆናቸውን ያምናል፡፡ ነገር ግን መንግሥት እነዚህን ኃይሎች ማዳከም ያለበት በሐሳብ በመብለጥ እንጂ፣ ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን በመጣስና ሌሎች ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች አንድ ላይ እንዲጠፉ በማድረግ አይደለም ይላል፡፡

የወጣት ናሁሰናይ ሥጋት ግን ከዚህም በላይ ነው፡፡ ‹‹ኢሕአዴግ በ1997 ዓ.ም. ምርጫ ከደነገጠ በኋላ መረጋጋት የቻለ አይመስለኝም፤›› በማለት ያንን ቀውስ ተከትሎ በአገሪቱ የተጀመረው የዴሞክራሲ ጉዞ ቀስ በቀስ ደረጃ በደረጃ ወደ አደገኛ ሁኔታ እየገባ መሆኑን ያስረዳል፡፡

በአሁኑ ወቅት ኢሕአዴግ በኪራይ ሰብሳቢነት ላይ የልማታዊ አስተሳሰብ የበላይነት አረጋግጫለሁ ማለቱን እንደማይበቀልና የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብ የበላይነቱን እየያዘ መምጣቱን ይናገራል፡፡

በአሁኑ ወቅት በገዢው ፓርቲ ውስጥ ፖለቲካዊ የመበስበስ አደጋ እንዳይኖርም ሥጋት አለው፡፡ ምክንያቱም የሕዝቡ ፍላጎትና የድርጅቱ የፖለቲካ አስተሳሰብ ሊገጥም አልቻለም ይላል፡፡ በተለይ የወጣቱ ጥያቄ፡፡ በአገሪቱ ፖለቲካ ወጣቱ የበለጠ ተሳትፎ እንዲኖረው የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ለመግታት መሞከር፣ እኔ አውቃለሁ የሚል አስተሳሰብ፣ እንዲሁም የወጣቱን ዘመናዊ ፍላጎት በ60ዎች አስተሳሰብ ለመመለስ መሞከርን ይተቻል፡፡ ነፃነትን፣ ፍትሕን፣ መደራጀትን የመሳሰሉ የወጣቶት ፍላጎቶች ለመመለስ የሚችል፣ ይህንን ትውልድ የሚመስልና የሚረዳ የፖለቲካ አመራር ስለመኖሩ ጥርጣሬ ያድርበታል፡፡

ተቋማዊ አሠራር

ገዢው ፓርቲ ሥልጣን ከያዘ ጊዜ ጀምሮ ባሳለፋቸው 25 ዓመታት ውስጥ ከሚተችባቸው ዋነኛ ጉዳዮች መካከል ጠንካራ ተቋም በመፍጠር ረገድ ያለው ዳተኝነት አንዱ ነው፡፡ ባለሙያዎች ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በኢትዮጵያ ለመገንባት ከሚያስፈልጉ ጉዳዮች መካከል ጠንካራ የዴሞክራሲ ተቋማትን በዘላቂነት መገንባት ቢሆንም፣ ገዢው ፓርቲ ግን የፈጠራቸው የዴሞክራሲ ተቋማት በገዢው ፓርቲ ላይ የሚሰነዘሩ የሰብዓዊ መብት ጉዳዮችን ለመከላከል የቆሙ እንደሚመስሉ ይናገራሉ፡፡ የሚዲያ ተቋማት የአንድ አገር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለማጠናከር ከፍተኛ ሚና የሚጫወቱ ቢሆንም፣ ገዢው ፓርቲ ግን ነፃነታቸው የተጠበቀና ያለ ጣልቃ ገብነት ፈተና የሚንቀሳቀሱ የሚዲያ ተቋማትን በአገሪቱ እስካሁን አለመፍጠሩ፣ የአገሪቱ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ በኅብረተሰቡ ፍላጎት ላይ የተመሠረተ ሳይሆን ተለክቶ የሚሰጥ እንዲሆን አድርጎታል ሲሉ ባለሙያዎች ይወቅሳሉ፡፡

ይህ ትችት ገዢው ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ተቋማትን በመገንባት ረገድ በሚያሳየው ዳተኝነት ላይ የተሰነዘረ ቢሆንም፣ በተመሳሳይ ኋላቀር የቢሮክራሲ ሥርዓትና ተቋማዊ ትውስታ የሌላቸውን ተቋማት በመቁጠርም ይወቀሳል፡፡ በቅርብ ዓመታት ብቻ እየገነባ የሚያፈርሳቸው ወይም የሚበትናቸው ተቋማት በሚንቀሳቀሱበት የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ዘርፍ፣ ለረዥም ዓመታት የተደራጀ ተቋማዊ ትውስታ እንዳይኖራቸው አድርጓል ሲሉም ይተቻሉ፡፡

የግብርናና ገጠር ልማት ሚኒስቴር፣ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመሳሰሉትና በአሁኑ ወቅት ለሁለት እንዲከፈሉ የተደረጉ ተቋማትን ማንሳት ይቻላል፡፡ (ዮሐንስ አንበርብር ለዚህ ጽሑፍ አስተዋጽኦ አድርጓል)