ተክለ ጻድቅ መኩሪያ የአሮጌይቱና የአዲሲቱ ኢትዮጵያ መስታወት

በገብሩ ታረቀ  (የታሪክ ኢመሪተስ ፕሮፌሰር)

‹‹ፊደል እያለን ጸሐፊም ሳይጠፋ የገዛ ታሪካችንን ለገዛ ወጣቶቻችን የውጭ አገር ሰዎች በየቋንቋቸው እንደምን ማስተማር ቻሉ?›› ሲሉ አቶ ተክለ ጻድቅ መኩሪያ በለጋ ዕድሜያቸው ላነሱት ቀናዒና መሠረታዊ ጥያቄ በ1936 ዓ.ም. የታተመውና እስከ ዛሬ ደረስ በስፋት የሚነበበው፣ ከአፄ ቴዎድሮስ እስከ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የተሰኘው መጽሐፋቸው የመጀመርያው መልሳቸው ነበር፡፡ ከዚያም ሳይታክቱ ጥናታቸውን ለ30 ዓመታት በመቀጠል ከደርዘን በላይ፣ በተለይ የኢትዮጵያ ታሪክ ላይ የሚያተኩሩ መጻሕፍትን አበርክተዋል፡፡ የሚያስደንቀው ወደ ማምሻው ከደረሷቸው ሦስት ወፍራም ቅጾች በስተቀር ሌሎቹን የጻፏቸው የዕረፍት ጊዜያቸውንና ገንዘባቸውን በመሰዋት መሆኑ ነው፡፡

ከብዛት አንፃር አስተዋጽኦዋቸው እጅግ ብዙ ከመሆኑም  በላይ በአማርኛ መጻፋቸው ደግሞ የሥራቸውን ፋይዳነት የበለጠ ከፍ ያደርገዋል፣ ተጠቃሚው ብዙ ነውና፡፡ ካለፉት ሦስት ትውልድ ኢትዮጵያውያን ውስጥ በተለይ በዘመናዊ ትምህርት ቤት ያለፈ ሰው ከመጻሕፍቶቻቸው ውስጥ አንዱን ያልዳሰሰ ይገኛል ብሎ መገመት ያስቸግራል፡፡ የሚያስገርመው ጸሐፊው ትምህርት ቤት ገብተው የታሪክ ትምህርትን ያልገበዩ ከመሆናቸውም በላይ፣ የመደበኛ ትምህርት ደረጃቸው ዝቅተኛ የነበረ መሆኑ ነው፡፡ ስለሆነም የታሪክ አቀራረብ ሥልታቸው ከነገሥታቱ ዜና መዋዕል የተለየና የተሻለ ቢሆንም፣ ዘመናዊው የታሪክ  ጸሐፊነት ሙያ የሚጠይቀውን መሥፈርት አያሟላም፡፡ ነገር ግን ለነገሥታትና ለመሳፍንት ቅድሚያ ከሚሰጠው ተራ ትረካ ወደ ዘርፈ ብዙ ማኅበራዊ ትንተና የሚያሸጋግረውን የታሪክ አጻጻፍ ድልድይ የከፈቱት ፋና ወጊዎች ተክለ ጻድቅና ቀደምታቸው ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ ናቸው ቢባል ስህተት አይሆንም፡፡ ሁለቱ ደራሲያን ከቤተ ክህነትና ከዘመናዊው ትምህርት ያገኙትን ዕውቀት በመጠቀም፣ አሮጌውንና አዲሱን የታሪክ አጻጻፍ ሥልት ለማጣመር የማይናቅ ሙከራ አድርገዋል፡፡ ጥረታቸው የሽግግር ዘመኑ ነፀብራቅ ነው፡፡ እንዲያውም ተክለ ጻድቅ ራሳቸው የሁለት ዓለም ሰው ነበሩ፡፡ በመሆኑም የአሮጌይቱና የአዲሲቱ ኢትዮጵያ መስተዋት ናቸው፡፡ ከተለያየ መነሻ የሥራቸውን ሚዛናዊነት የሚተቹ ሊኖሩ እንደሚችሉ ቢገመትም፣ ኢትዮጵያውያን ያለተክለ ጻድቅ ጽሑፎች ስለራሳቸውና አገራቸው፣ ማለትም ከየት ተነስተው ወዴትና እንዴት እንደደረሱ ያላቸው ዕውቀት በእጅጉ የሳሳ ይሆን ነበር፡፡ አስተዋጽኦዋቸውም የሚደነቅም የሚከበርም ነው፡፡ ከጉድለቱ ይልቅ ትሩፋቱ ያመዝናል፡፡

ስመ ጥር ታሪክ ጸሐፊ ተክለ ጻድቅ መኩሪያ ጽፈው ያስቀመጡት የሕይወቴ ታሪክ የተሰኘ መጽሐፍ በቅርቡ ታትሞ ገበያ ላይ ውሏል፡፡

የተክለ ጻድቅ መኩሪያ የሕይወት ታሪክ ሁለት ገጽታዎች ነበሩት፡፡ እነዚህም መንግሥታዊ አገልግሎትና ጸሐፊነት ናቸው፡፡ ታዋቂነታቸው ይበልጥ በታሪክ ጸሐፊነታቸው እንጂ ለአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት በሰጡት የረዥም ዘመን አገልግሎት አልነበረም፡፡ ይህ ድርሰታቸው ከማናውቀው ገጽታቸው ማለትም ከፖለቲካ ሕይወታቸው ጋር ያስተዋውቀናል፡፡ የሕይወቴ ታሪክ የተክለ ጻድቅ ግለ ታሪክ ቢሆንም፣ ትኩረቱና በውስጡ የሚዳሰሱት ቁምነገሮች ሰፊ ናቸው፡፡ ደራሲው ጽሑፉን ያዘጋጁት ከልጅነት ጀምሮ ይህን ድርሰት እስከጨረሱበት ያለውን ዘመን፣ የጊዜ ወሰንና የራሳቸውን የሕይወት ታሪክ መሠረት አድርገው በመከፋፈል ነው፡፡

አንደኛው የመጽሐፉ እምብርት የታሪኩ ዋናው ተዋናይ ራሳቸው ጸሐፊው ከመሆናቸው ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ተክለ ጻድቅ በጸሐፊነታቸው ግዙፍ ሰው ቢሆኑም፣ ሰብዕናቸውና ፖለቲካዊ አስተያየታቸው በአደባባይ እምብዛም የሚታወቅ አልነበረም፡፡ ይህ መጽሐፍ በበለጠ እንድናውቃቸው፣ እንድንተቻቸው ወይም እንድናደንቃቸው ብሎም እንድናከብራቸው የሚጋብዙንን ብዙ ቁም ነገሮች አዝሏል፡፡ የደራሲውን ሰብዕና፣ የሕይወት ገጠመኞችና ፖለቲካዊ ሚና በቅንነትና በድፍረት ያቀርብልናል፡፡

ሁለተኛው ጸሐፊው ለአራት አሠርት ዓመታት በትጋትና በቅንነት ያገለገሉትን የአፄ ኃይላ ሥላሴን መንግሥት የውስጥ አወቃቀርና አሠራር ግልጽ በሆነ ቋንቋ ቁልጭ አድርገው አቅርበውታል፡፡ የወቀሳና የትችቱ ጥንካሬ ለአንዳንድ አንባቢያን ግርታን የሚፈጥር ቢሆንም ተገቢነቱ ግን አጠያያቂ አይደለም፡፡ በመንግሥታዊው መዋቅር ቁልፍ ቦታዎችን ከያዙት ባለሥልጣናት መካከል ጥቂቶችንም ቢሆን ይጠቅሳሉ፡፡ ሲያሞግሱም ሆነ ሲወቅሱ በስም ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነቱን ትውስታ ካቀረቡልን የውስጥ አዋቂዎች ዋነኛው ተክለ ጻድቅ ሲሆኑ፣ የሚመስሏቸው ፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት ተክለ ማርያምና አቶ ብርሃኑ ብርሃኑ ናቸው፡፡

ሦስተኛው፣ ምንም እንኳን ይህ መጽሐፍ እንደማንኛውም ግለ ታሪክ በግለሰቡ ዙሪያ የሚያጠነጥን ቢሆንም ጉልታዊውን ሥርዓት፣ ማኅበራዊ ቅራኔዎችን፣ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ ለውጦችን፣ በየጊዜው የተከሰቱትን ፀረ መንግሥት አመጾች፣ የፋሺስት ኢጣሊያ ወረራን፣ የመደበኛ ትምህርት ዕድገትና የእንግሊዞችን ሴራ፣ የ1966ቱን ሕዝባዊ እንቅስቃሴና የወታደራዊ አምባገነንነት መስፈንን ይዳስሳል፡፡

ተክለ ጻድቅ መኩሪያ እስከ ሕልፈተ ሕይወታቸው ያልተለዩዋቸውን ትጉህነትና ብልኃትን ያሳዩት ገና ‹‹ሀ ሁ››ን ከቆጠሩበት ሰባት ዓመታቸው ጀምሮ ነበር፡፡ ትጋታቸውንና ንቁነታቸውን ያስመሰከሩት በአሥር ዓመታቸው ዳዊትን ደግመው ዜማን ሲጀምሩ ሲሆን፣ የወሰደባቸውም ጊዜ ሦስት ዓመት ብቻ ነው፡፡ በ‹‹ለምን አይሆንም/ይቻላል›› አስተሳሰብ የሚመሩ፣ ለጊዜ፣ ለዕውቀትና ለሥራ የተለየ ክብር ያላቸው፣ ነፃነትንና ፍትሕን የሚወዱና በአንፃሩ ዘገምተኝነትንና ስንፍናን የሚጠሉ፣ አገራቸውንና ሕዝባቸውን የሚያፈቅሩ ሰው እንደነበሩ ግለ ታሪካቸው ያመለክታል፡፡  በባህሪያቸው ‹‹ክስና ወቀሳ፣ ክርክርና ሁካታ›› እንዲሁም ሴረኛነትን እንደሚጠሉ ‹‹አኩራፊነትና መራርነት›› ያጠቋቸው እንደነበር ያምናሉ፡፡ የወዳጅነት ክልላቸው ጠባብ ይመስላል፡፡ ለምን ብቸኝነትንና ገለልተኝነትን እንደመረጡ ሲገልጹ፣ ‹‹መሠረታዊ ዓላማ አድርጌ የያዝኩት ያለምንም  ጭቅጭቅ በሰላም መኖርን ብቻ ነው፤›› ይላሉ፡፡

የተክለ ጻድቅ ትምህርትና ዕውቀት ፍለጋ ጉዞ ብዙ እክሎችና መሰናክሎች ነበሩት፡፡ ለምሳሌ የቤተ ክህነቱን ትምህርት እየተከታተሉ በነበሩበት ጊዜ በአንድ የቤተሰብ ወዳጅ  አማካይነት በአሊያንስ ፍራንሴዝ ፈረንሣይኛ ቋንቋ መማር ጀመሩ፡፡ ‹‹በስድስት ሰዓት ጓደኞቼ ለምሳ ወደ ቤታቸው ሲበታተኑ እኔ የምሄድበትና የምበላበት ቤት ስለሌለኝ፣ በዚያ በተማሪ ቤትና በእስላም መስጊድ አካባቢ እየተንጎራደድሁ፣ በባዶ ሆዴ ስንቃቃ ቆይቼ በስምንት ሰዓት ሲደወል ከበሉት ጋር አብሬ ገብቼ እማራለሁ፤›› ከዚያም በአባታቸው ግፊት ትምህርቱን  አቋርጠው በልጅነታቸው በጎተራ ጸሐፊነት ደጃዝማች ወልደ ጻድቅ ጎሹን (የአገር ግዛት ሚኒስትር፣ የአርሲ አውራጃ ገዥና የአዲስ ዓለም ማርያም ንቡረዕድ) ማገልገል ጀመሩ፡፡ ዋናው ሥራቸው ከየገባሩ የሚሰበሰበውን ጥሬ እህልና ዱቄት፣ ማርና ቅቤ በአንድ በኩል፣ ለእንጀራ ወጥ፣ ለጠጅና ጠላ የሚወጣውን ደግሞ በሌላ በኩል መመዝገብ ነበር፡፡ የ15 ዓመቱ ወጣት አስተዋይነቱንና ቀልጣፋነቱን ለማስመስከር ጊዜ አልወሰደበትም፡፡ በተከታታይ የፍርድ ቀላጤና መልዕክት ጸሐፊ ከዚያም የሚስጥር ጸሐፊ ይሆኑና አበላቸውም ከአንድ ወደ ሦስት ብር አደገ፡፡ የግብር መሶባቸውም ‹‹ከአሽከሮች ጋር መሆኑ ቀርቶ ከሹማምንት ጋር ሆነ፤›› በዚህ  ጊዜ ስለ ገባሩ ኑሮና እሮሮ ያስተዋሉትን በየሕይወቴ ታሪክ እንደሚከተለው ገልጸውታል፡፡       

ካሩሲ ግዛታቸው ከሌላም ግዛት ይህ ተበደልሁ ወንድሜ ወይም አባቴ አለዚያም ልጄ ታሰረብኝ ወይም ርስቴን ተቀማሁ፣ ምስለኔዎች አላግባብ ፈረዱብኝ ብሎ የቻለውን መታያ እንጨት ጥሬ ብር ወይም ሠንጋ እንደ ችሎቱ ይዞ በአጋፋሪዎችና በእልፍኝ አስከልካዮች በኩል ከደጃዝማች ቀርቦ ያመለክታል፡፡ ነገር  ግን መከረኛው ነገረተኛ ወጪው በዚህ አይወሰንም፡፡ ወደ ጌቶቹ ለመቅረብ ላጋፋሪዎችና ለልፍኝ አስከልካዮች ካንድ እስከ አምስት ብር እንደ ችሎቱ ይከፍላል፡፡ ከዚያ ለጌቶቹ እላይ እንደተባለው የቻለውን ከሁለት እስከ 100 ብር ወይ እንጨት ወይም ሠንጋ መታያ ያቀርባል፡፡ ከዚያ ጸሐፊው ሳይዘገይ በቶሎ ጽፎ እንዲሰጠው ከቀላጤው ሩብ በቀር ካንድ እስከ አምስት ወይም አሥር ብር ይከፍላል፡፡ አዲስ አበባ ነገሩ ሲዛወር በችሎት በሚታይበት ጊዜ ለወንበሮችና ለአጋፋሪዎች፣ ለፍርድ ጸሐፊዎች የሚከፍለው በዚሁ አካባቢ እንደነገሩና እንደ ኃጢያቱ ክብደትና ቅለት ነው፡፡

በመሠረቱ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝና አፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ ከገለጹት የአርሶ አደሩ መከራና እንግልት እምብዛም የተለየ አይደለም፡፡ ይህንን ሲታዘቡ ያደጉት ጸሐፊ በዚህኛውም ሆነ በሌሎች መጻሕፍቶቻቸው ውስጥ የሥርዓቱን አስከፊነት አጉልተው ማውጣት አለመቻላቸው ለአንባቢ ግር ሊል ይችላል፡፡ ሆኖም የታሪክ ዕይታቸውም ሆነ ትኩረታቸው በገዥው መደብ አሠራርና አካሄድ ላይ ስለነበረና የዚህ ዓይነቱ ዕይታና ትኩረት እስከዛሬም በብዙ የታሪክ ጸሐፍት ዘንድ ስላለ ብዙም ሊያስገርመን አይገባም፡፡ ይልቁንም አንባቢው የዚህ ዓይነቱን የዜጎች መቸገርና መሰቃየት ሲያነብ፣ ‹‹ዛሬስ የዜጎቻችን ሸክምና ብሶት ምን ያህል ቀሏል? አሁንስ በምድረ ኢትዮጵያ ያለው የአስተዳደርና የፍትሕ ሁኔታ ከዚህ ጋር እንደምን ይመሳሰላል? ወይም ይነፃፀራል?›› ማለቱ ስለማይቀር የተክለ ጻድቅ ትውስታ መጠቀሱ አሁንም ትልቅ ጠቀሜታ አለው፡፡

እንደ የሕይወቴ ታሪክ ከሆነ ተክለ ጻድቅ ህሊናቸው ግፍን፣ ጭቆናንና ኢፍትሐዊነትን ስለሚኮንን ሁሌም በልባቸውና በመንፈሳቸው እንዳመፁ ነበር፡፡ ነገር ግን በሐሳብ (በምኞት) እና በተግባር መካከል ያለውን አጣብቂኝ ሊፈቱ ወይም ሊያስታርቁ አለመቻላቸውን እንገነዘባለን፡፡ ከታች ቁልጭ አድርገው እንዳቀረቡት ይህ የብዙኃን ችግር ወይም ድክመት መሆኑ የተረጋገጠ ነው፡፡ የተክለ ጻድቅ ጥንካሬ መለኪያው ባላሳዩት ፖለቲካዊ ጥንካሬ ሳይሆን፣ በዕምነት ፅናትና በሥነ ምግባር አለመምከን ነው፡፡

ተክለ ጻድቅ በዋና ጸሐፊነት፣ በቆንስላነትና በአምባሳዳርነት በተለያዩ አገሮች  ለ17 ዓመታት የቆዩበት ጊዜ ዕውቀታቸውን፣ የፖለቲካ ዕይታቸውንና አቋማቸውን እንዳዳበረውና እንዳጠናከረው መገንዘብ ይቻላል፡፡ በእስራኤላውያንና በፍልስጤማውያን መካከል ያለው የረዥም ጊዜ የፖለቲካ ውዝግብ ምንኛ አካባቢውንና ዓለምን እንዳስቸገረ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ ለኢትዮጵያ መንግሥት ደግሞ ብዙ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን የፈጠረ የእግር እሾህ ስለነበር፣ ጸሐፊው በፅሞናና በጥንቃቄ ካጠኑት በኋላ አስተያየት ሰጥተውበታል፡፡ በየሕይወቴ ታሪክ ውስጥ የሚከተለውን አስፍረዋል፡-

ከሥራ ሰዓት ውጪ ወይም ቅዳሜ እሑድ በእየሩሳሌም፣ ከዚያም ራቅ ብዬ በልዳ፣ በጋዛ ከተሞች እየተዘዋወርሁ ስጎበኝ፣ ‹‹ይኸ ሕንፃ የማን ነው?›› ስል ቀድሞ የፓላስቲን ተወላጅ እንደነበረ አሁን ከአውሮፓ፣ ከጀርመንና ከፖላንድ ወይም ከመስኮብ የመጣ ይሁዲ እንዳለበት፣ ባለቤቱ ግን እስራኤሎች በ፲፱፵፯ እና ፲፱፵፰ ዓ.ም በተደረገው ጦርነት ያሸነፉ ጊዜ ተሰዶ በዦርደን ወይም በሶርያ በረሃ በድንኳን እንደሚኖር በብዛት ተረዳሁ፡፡ ወደ ዦርደን ተሻግሬ፣ ኢያሪኮ አጠገብ ያለውን በበረሃ የታመቀውን የስደተኛ ብዛት፣ የሽማግሌውን የሕፃኑን የወንድና የሴቱን አኗኗር ዓይቼ በመንፈሴ ተበሳጨሁ፡፡ በዓለም ላይ የዕውቀት የገንዘብና የጉልበት ኃይል እንጂ፣ ትክክለኛ ሕግ እውነትና ፍትሕ እንደሌለ ቀድሞ የማውቀው የበለጠ እየተብራራልኝ ሄደ፡፡ . . . እኔ ይኸን ሁሉ በመመልከት መንፈሴና ህሊናዬ ለፓለስቲኖቹ ሲያደላ እኔ ወኪል የሆንሁበት የዛን ጊዜ የኢትዮጵያ መንግሥት ደግሞ ከእስራኤል ወገን ቆሟል፡፡ . . . የእስራኤልንና የፓለስቲንን ሁኔታ ለመንግሥቴ በራፖር ስገልጥ አብዛኛውን ጊዜ ለመንግሥቴ መሪዎች የማቀርበው አስተያየት ባጭር ጊዜ ከእስራኤል ጋር መወዳጀቱ፣ በወታደር ማሠልጠን፣ በኢኮኖሚ ረገድ፣ የስለላ ሥራ በማከናወን ቢጠቅመንም፣ በረዥም ጊዜ ግን በአንድ እስራኤል የተነሳ ከብዙዎቹ የዓረብ መንግሥታት ጎረቤቶቻችን ጋር ስለሚያጣላን በተቻለ መጠን ከእስራኤል ራቅ እያልን ከጎረቤቶቻችን የዓረብ መንግሥታት ጋር መቀራረቡ ለኢትዮጵያ ጠቃሚ ነው የሚል ነው፡፡

የኢትየጵያና የእስራኤል መንግሥታት ከነበራቸው ቁርኝት፣እንዲሁም ክርስቲያን ኢትዮጵያውያን ለእስራኤል ከነበራቸው የዋህ ወገናዊነት አንፃር ሲታይ፣ የዲፕሎማቱ አስተውሎ፣ ሀቀኝነት፣ ድፍረትና ፍትሐዊነት ያስደንቃል፣ ሊያስከብራቸውም ይገባል፡፡

የፈረንሣይ ቆይታቸውም እንደዚሁ ዓይነ ህሊናቸውን እያሰፋ፣ ፖለቲካዊ ሐሳባቸውንና ራዕያቸውን እያበሰለና እያጎለበተ ለነፃነትና ለዴሞክራሲ የነበራቸውን ጥማትና ናፍቆት አጠንክሮታል፡፡ የሪፐብሊኩ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ውይይትና ሙግት በማዳመጣቸው፣ እንዲሁም ጋዜጦቻቸውን በማንበባቸው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚሰጠው መብትና ነፃነት አስቀናቸው፣ ተመኙትም፡፡ በሕግ ላልተገደበው የአገራቸው መለኮታዊ መንግሥት ያደረባቸው ጥላቻ እየበረታ መጣ፡፡

የዚህ ዓይነት አስተዳደር ካገራችን መራቁን፣ ንጉሠ ነገሥቱ ብቻ ፈላጭ ቆራጭ ሆነው የልባቸውን መሥራታቸውን፣ የአገሪቱን ሀብታምነትና በደህና አስተዳደር ዕጦት የተነሳም የሕዝቡን ድህነት እያመዛዘንሁ ባገሬ መንግሥት አስተዳደር ላይ ያለኝ ጥላቻ እየባሰብኝ ሄደ፡፡ . . .  የኢትዮጵያን  የአሁኑን አስተዳደርና በፈረንሣይ አብዮት ዋዜማ የነበረውን የፈረንሣይ የነገሥታት  አስተዳደር እያመዛዘንሁ በኢትዮጵያም ሽብር መነሳቱ አይቀርም የሚል ስሜት አደረብኝ፡፡

ይህ ሥጋት የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታዎችና ታሪካዊ ኩነቶች ባጤነ ግንዛቤ ላይ የተመሠረተ መሆኑን ጠንቃቃ አንባቢ የሚስተው አይመስለኝም፡፡ ይሁን እንጂ የሚመኙትንም ሽብር ቀስቃሽ ከመሆን እንደማይቆጠቡ ይጠቁማሉ፡፡ ‹‹በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አስተዳደር ላይ የፖለቲካና የመቃወም ንቅናቄ መፍጠሬ አይቀርም በሚል ስሜት የመንግሥቱን ያስተዳደር ብልሹነት፣ የንጉሠ ነገሥቱን ባለጉልትነት፣ ገንዘብ ሰብሳቢነት የሚገልጽ ጽሑፍ በፈረንሣይኛ እያዘጋጀሁ . . . መሥራት ጀምሬ ነበር፤›› ለማንኛውም ተክለ ጻድቅ የተመኙት የንጉሠ ነገሥቱ ፍፁማዊ መንግሥት ውድቀትን እንጂ፣ የዘውዱን አብሮ መጥፋት እንዳልነበር ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡

ይሁንና ይህ ሁሉ ኑዛዜ በዚያን ጊዜ የነበራቸውን ስሜት በትክክል የሚገልጽ ነው ወይስ የሚጠሉት መንግሥት ከተገረሰሰ በኋላ ‹ታሪክን የኋሊት እየተመለከቱ ያለሙትን ይሆን ያቀናጁት?› ብሎ ዕውነትነቱን የሚጠራጠር አንባቢ አይታጣም፡፡ ከባለታሪኩ ረዥም ጉዞና የተፈጥሮ አፈንጋጭነት አንፃር ሲታይ ተራ ፈጠራ ነው ለማለት በጣም ይከብዳል፡፡

የተክለ ጻድቅን አስተዋይ፣ ተቆርቋሪና እምቢተኛ ህሊና በተጨማሪ ያመለክታሉ ያልኳቸውን ሁለት ክስተቶችን ልጠቁም፡፡ በነፃነት ማግሥት ለ‹‹አርበኝነታቸው›› ኒሻን ቢሰጣቸው ‹‹የማይገባህን በሰጡህ ጊዜ የሚገባህን ካስቀሩብህ የበለጠ ልትቸገርበት ይገባል፤›› በሚል እሳቤ ‹‹ዓርበኛም፣ የውስጥ ዓርበኛም፣ ስደተኛም አይደለሁ፤ እስረኛነትም አያሸልምም፤›› ብለው ኒሻኑን በድፍረት መለሱት፡፡ ወልቂጤ አካባቢ ከመንግሥት የተሰጣቸው ‹‹አራት ጋሻ መሬት አለአግባብ መሆኑን፤›› ሲረዱ ሳይጠቀሙበት እንደቀሩ አመልክተዋል፡፡

ተክለ ጻድቅ መኩሪያ በ40 ዓመት የአገልግሎት ዘመን የሠሩትን፣ ያለሙትን፣ ካዩትና ከታዘቡት በዝርዝርና በማያሻማ ቋንቋ ይተርኩልናል፡፡ የግል ታሪካቸውንና ትዝታቸውን በጽሑፍ በማስፈር በበለጠ እንድናውቃቸው ስላደረጉ ጥሩ ዜጋ መሆናቸውን አስመስክረዋል፡፡ ሆኖም የግለ ታሪክ ፋይዳ  ባለ ታሪኩ ለነበሩበት ዘመን፣ ማኅበረሰብና መንግሥታዊ ሥርዓት መስተዋት ሲሆን ነው፡፡ ስለሆነም ተክለ ጻድቅ የራሳቸውን የሕይወት ታሪክ፣ ገጠመኞችና እሴቶች ሲተርኩ ስለአገራቸውም ታሪካዊ ሒደትና ማኅበራዊ ዕድገት፣ በተለይም ስለአገሪቱ ጉልታዊ የፖለቲካ ሥርዓት፣ ስለአፄ ኃይለ ሥላሴ  አገዛዝ  ዘይቤ፣ ‹የተዘባረቀና አስቀያሚ›› ወይም ‹‹አስከፊ አስተዳደር›› የሚሉትን፣ በማደግ ላይ ስለነበረው የቢሮክራሲ አወቃቀርና ጉልህ ችግሮች ሰፋ አድርገው ይተነትናሉ፡፡ እንደሳቸው አገላለጽ ከሆነ የቄሳሩ መንግሥት ተጠያቂነትና ግልጽነት ያልነበረው፣ አድሏዊነት የሰፈነበት፣ ግለኝነትና የዝምድና  አሠራር የተንፀባረቀበት፣ የሥልጣን ሽኩቻ የበዛበት፣ የሀብት ምዝበራ የበረከተበትና ፖለቲካውም የጓዳ ፖለቲካ እንደነበር አስረግጠው ይናገራሉ፡፡ ባለሥልጣነቱም በአፄው አምሳያ የተፈጠሩና እንደ አፄው በተጠራጣሪነትና በተንኮል የተካኑ እንደነበሩ ያወጉናል፡፡ ለምሳሌ ጸሐፌ ትዕዛዝ ወልደ ጊዮርጊስ ወልደ ዮሐንስ በሰባቱ ዓመት የሥልጣን ዘመናቸው ከጃንሆይ ባላነሰ ሁኔታ ‹‹አድራጊ፣ ፈጣሪ፣ በለሙሉ ሥልጣን›› መሆናቸውን ‹‹ወደ እሳቸው ተጠግቶ ‹የርስዎ ነኝ› ያለውን አሳዳጊ፣ በጠባዩ ወይም በትምህርት ገለል ብሎ ‘በራሴ ችሎታ እኖራለሁ›  የሚለውን ጊዜ እየጠበቁ በመኮርኮም  (በመሻር) የሚያዋርዱ ነበሩ፡፡ ጸሐፌ ትዕዛዝ ብዙ ጊዜ ሲያጠቁ አንዱን ባንዱ  ነው፡፡ ይኸውም ‹‹የጠሉትን በሚያፈቅሩት፤›› ሲያጠቃልሉም፣ ‹‹ንጉሠ ነገሥቱ ከነጸሐፌ ትዕዛዛቸው ለአገርና ለወገን አሳቢዎች ያልሆኑ፣ ዳኝነት የማይጠብቁ መሆናቸው ገባኝና በልቤ አቄምሁ፤›› ይላሉ፡፡ በተለይም ንጉሠ ነገሥቱን በሥነ ምግባር ድክመት፣ በአፍቅሮተ ነዋይ፣ በንፉግነትና በራስ ወዳድነት ይኮንኗቸዋል፡፡ በንፅፅር የአፄ ምኒልክን ደግነትና  ቸርነት፣ ሕዝብ ወዳድነትና መልካም ሥነ ምግባር ያደንቃሉ፡፡

በዚህም ባለፉት በዳግማዊ ምኒልክና አሁን ባሉት ንጉሠ ነገሥት መካከል ያለውን የፀባይ ልዩነት እያመዛዘንሁ ሁለቱ ነገሥታት በመራራቃቸው እደነቃለሁ፡፡ ምኒልክ ከአባቶቻቸው እንደወረሱት ከመኳንንትም ከሕዝቡም እንደ ዘመኑ ደንብ መታያና እጅ መንሻ ይቀበላሉ፡፡ የተቀበሉትን ለሕዝብ ለወታደር መልሰው ያከፋፍሉታል፡፡ ግብር ከማብላት፣ ከመሸለም መንግሥታቸውን ከማደርጀት ላይ ያፈሱታል፡፡ ያፈሰሱትንም እምዬ ምኒልክ ተብለው በመወደድ መልሰው ያገኙታል፡፡ ይህን አርዓያቸውን የማይከተል መስፍንና መኮንን በፊታቸው ሞገሥና ባለሟልነትን አግኝቶ በሹመትና በደረጃ  አያድግም፡፡ . . .  ምኒልክ ያገኘኸውን ለሕዝብ አብላ ሲሉ ኃይለ ሥላሴ ቋጥር ይላሉ፡፡ ምኒልክ መሳፍንቶቻቸውን፣  የጦር  አለቆቻቸውን የምኗቸዋል፣ ይወዷቸዋል፣ እንዲያድጉ ይገፋፏቸዋል፡፡ ስመጥር ታጃቢ፣ ሕዝብ ሰብሳቢ ግብር አብሊ በመሆን ስመ ጥሩ ሲሆኑላቸው ይደሰታሉ ይባላል፡፡ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መሳፍንቶቻቸውን ታማኞቹን ሳይቀር ይጠራጠራሉ፣ ያቆረቁዛሉ፡፡ እገሌን ሰው ይከተለዋል፣ ያበላል፣ ያጠጣል በተባለ ጊዜ  እስኪጥሉት ድረስ እንቅልፍ አይወስዳቸውም፡፡ ምኒልክ የንጉሥ ርስቱ ዘውዱና ዙፋኑ ነው በሚል ንፁህ ፍልስፍና ሲጠመዱ፣ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በኢትዮጵያ ያለው የለመለመው መሬት ሁሉ በስማቸው ተመዝግቦ ቤተ ርስታቸው ቢሆን ይወዳሉ፡፡ ምኒልክ በንጉሠ ነገሥታቸው ካልሆነ የግል አንጡራ ገንዘብ ባገርም ካገርም ውጪ ባለ ባንክ ማስቀመጥ  አይወዱም፡፡ አስቀምጧል ተብሎ የታማውንም ይጠሉታል ይባላል፡፡ ስለራስ መኮንን ሞት በጣም አዝነው በሚያለቅሱበት ጊዜ እቴጌ ጣይቱ ‹‹ይህን ያህል ምን አሳዘነዎ፣ እሱ እኮ ገንዘብ እንግሊዝ አገር አስቀምጧል፤›› ቢሏቸው እንባቸው ደረቀ ይባላል፡፡ በአንፃሩ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ለመንግሥት በቀጥታ ገቢ ሆኖ ለሕዝብ ጉዳይ የሚውለውን ሁሉ በሰበብ አሳብቦ በባለሟል አማካይነት ወደ ግል ግምጃ ቤታቸው መሰብሰብ ዓይነተኛ ሥራቸው ነው፡፡ ከውጭ አገር ነጋዴ ጋር እየተሻረኩ ትርፍ መካፈል፣ በውጭ ባንኮች ብዙ ገንዘብ ማስቀመጥ፣  አክሲዮንና መኖሪያ ቤት መግዛት፣ የወደዷቸው የቤተሰብ  አባሎችም ይህንኑ  አርዓያ እንዲከተሉ ማድረግ ልማዳቸው ነው፡፡  

ይህን ያገናዘቡት  በአፍላ ዕድሜያቸው ቢሆንም ከዚያ በኋላ አስተያየታቸውን ስለማሻሻላቸው ወይም ስለመቀየራቸው ምልክት አይታይም፡፡ መቼም የሰው የተፈጥሮ በህሪ የተለያየ ከመሆኑም በላይ በአስተዳደግ፣ በአካባቢ ሁኔታዎች፣ በትምህርትና በሥራ ልምድ ከሰፊው ዓለም ጋር በመተዋወቅ አዕምሮንና ዕይታን በማስፋት ሊለወጥ እንደሚችል ተክለ ጻድቅ ይስቱታል ብዬ አልገምትም፡፡ ስለአፄ ምኒልክና አፄ ኃይለ ሥላሴ የየግል ባህሪያትና የአስተዳደር ዘዴዎች የተገለጹት ጠቀሜታ ቢኖራቸውም፣ ከቀጥታ  ንፅፅር ይልቅ የሁለቱን ነገሥታት ልዩነቶች የሚገልጹና የሚያስረዱ ብዙ የአስተዳደግና የአካባቢ ሁኔታዎች እንዳሉ አንባቢ ቢረዳ የበለጠ ጠቀሜታ የሚኖረው መሆኑን መጠቆም የሚበቃ ይመስለኛል፡፡ አንዲት ጉዳይ ግን ማከል አስፈላጊ ይሆናል፡፡ ይኸውም ጊዜው የሽግግር መኖሩና የንግድ (መርካንታይሊስት) ካፒታሊዝም እየተስፋፋ ጉልታዊውን ሥርዓት መሸርሸር የጀመረበት ዘመን እንደነበር ከግምት አላስገቡትም፡፡ ከጅምር ካፒታሊዝም የመጀመርያዎቹ ተጠቃሚዎችና መናኸሪያ በሆነቸው ሐረር ተወልደው ዘመናዊነትን ከተቀበሉት የመጀመርያዎቹ መሳፍንት ቀዳሚ ከሆኑት አባታቸው ስለንግድና የገንዘብ አያያዝ የማይናቅ ትምህርትን ቀስመዋል፡፡ በተፈጥሮ ብልህነትና ቀልጣፋነት ላይ ተመርኩዘው ማኪያቬላዊ የፖለቲካ ጥበብ ተከናንበው፣ ገደብ በሌለው ሥልጣን ተንተርሰው፣ ዘመን ያመጣውን የኢኮኖሚ ለውጥ ለግልም  ለአገርም ተጠቅመውበታል፡፡ ከንዋይ አፍቃሪነትና አትራፊነት አንፃር ዋና ተቀናቃኛቸው የጎጃሙ ራስ ኃይሉ ተክለ ሃይማኖት እንደነበሩ ይታወቃል፡፡ ተክለ ጻድቅ እንደጠቆሙት፣ ንጉሠ ነገሥቱ ልክ እንደ ራስ ኃይሉ በስግብግብነታቸውና በዝባዥነታቸው ሊወገዙ ቢገባም፣ በኢኮኖሚው ዘርፍ ላሳዩት ተሳትፎና በጎ አርዓያነት ቢወደሱ ምን ይከፋል? ነጋዴ የኢኮኖሚ ብሎም የማኅበራዊ ለውጥ አንቀሳቃሽ ኃይል ወይም ሞተር ነው፡፡ በአውሮፓና በጃፓን እንደታየው የጉልታዊውንና ባላባታዊውን ሥርዓት በማናጋት ብሔርተኛ ከበርቴ እንዲፀነስ (እንዲወለድ) የኢንዱስትሪ ካፒታልን መሠረት ከጣሉት የማኅበራዊ አካላት ነጋዴ አንዱና ዋናው ነው፡፡ አውቀውም ይሁን ሳያውቁ አፄ ኃይለ ሥላሴ በዚህ ረገድ የተጫወቱት ሚና የሚናቅ አልነበረም፡፡

ደራሲው ከዚሁ ጋር አያይዘው ስለመንግሥት ባለሥልጣናት ብልሹነትና የሞራል ዝቅጠት የሰነዘሩት ነቀፋ ትክክለኛና ለጊዜያችንም መልካም አስተምህሮ የሚሰጥ መሆኑን አምንበታለሁ፡፡

‹ወጣቶች ሚኒስትሮች ከንጉሠ ነገሥቱ የቅርብ ባለሟሎች አንዳንድ ወጣት ነጋዴዎች ጋር  በየቪላው ውስኪ እንደ ውኃ እያፈሰሱ፣ ጮማና ክትፎ እየበሉ፣ አዝማሪ እያቆሙ ከየሴቱ ወጣት ጋር ሆነው ዓለማቸውን ያያሉ› የሚባለው ወሬ ከሚነፍሰው ጋር እያንዳንዱ የተቻለው በየቤቱ፣ በየምክንያቱ የሚደግሰው የድግሱ፣ የመብሉና የመጠጡ ዓይነትና ብዛት በውጭ ካለው የሥራ ፈትና የደሃ ኑሮ ጋር ሲመዛዘን ልዩነቱ ዓይን ይመታል፡፡

የአፄው  ሥርዓት ከተገረሰሰ በኋላ አገሪቱና ኅብረተሰሰቡ ባሳለፏቸው ዓመታት ከነበረውና ዛሬም ካለው ሁኔታ ጋር አንባቢ እያነፃፀረ ቢመለከት፣ ብዙዎቹ የአስተዳደርና የማኅበራዊ ፍትሕ ችግሮች ለረጅም ጊዜ አብረውን የቆዩ መሆናቸውን ከመረዳቱም ባሻገር፣ እንዲያውም በብዙ መልኩ የባሰ መሆኑን ስለሚገነዘብ ጠቀሜታው ሰፊ ነው፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ አንባቢ ለባለ ግለ ታሪኩ ሁለት ተገቢና  አስፈላጊ ጥያቄዎችን ማንሳት ይችላል፡፡ አንደኛው ‹እንደዚህ ሥርዓቱን የሚወቅሱና የሚኮንኑ ሆነው ሳለ ለምን ያን ያህል ጊዜ ፍፁማዊ መንግሥቱን በትዕግሥትና በታማኝነት አገለገሉ?›  የሚል ሲሆን፣ ‹ሁለተኛው ደግሞ በንጉሡ ላይስ የሰነዘሩት ሰፋ ያለ ወቀሳና ትችት ቂም በቀል ቢኖራቸው ይሆን?› የሚል ይሆናል፡፡ የመጀመርያው ጥያቄ ህሊናቸው ውስጥ ስለመኖሩ ከዚህ በታች ያስቀመጡት በግልጽ ያሳየናል፡፡

ይህ ዓለም ተሸፋፍኖ ተቻችሎ የሚኖሩበት ዓለም ነው፡፡ ሀቀኞች ደረቆች መስዕዋትነትን መክፈል የሚችሉ ቁጥራቸው ትንሽ ነው፡፡ እኔ ያለሁት ቁጥራቸው ከበዛው ውስጥ መሆኑን በግልጽም በሥውርም መናዘዝ አለብኝ፡፡ የአካሉን ትግል ወደ መንፈስ ትግል ለውጨዋለሁ፡፡ ይኸም የደካሞች መሣሪያ መሆኑ ነው፡፡ ነገር ግን ከቀጥታ አድርባዮች ይሻላል፡፡ አድርባዮች ሹመቱን፣ ሽልማቱን በትጋት ፈልገው በደስታ ተቀብለው ሲኮሩበት የኔው ዓይነት ደግሞ በግድ የለሽነት ይቀበለዋል፡፡ እንደ ዕውነቱ ወደዚህ አስተዳደር በፈቃዴ በመግባቴና በመሾሜ ከመነቀፍ ለማምለጥ አልችልም፡፡

የኑዛዜውን ሀቀኝነት የሚጠራጠሩ አንባቢያን እንኳን በቀላሉ የሚያጣጥሉት አይመስልም፡፡ እርግጥ ነው የተክለ ጻድቅ ተቃውሞ ውስጣዊ (ልባዊ) እንጂ ውጫዊ (ገሃዳዊ) አልነበረም፡፡ እንዲያም ሆኖ ደራሲው ደጋግመው እንደተናገሩት አጋጣሚውን ቢያገኙ ኖሮ ከማመጽ ወደኋላ እንደማይሉ ነበር ፡፡

ለሁለተኛው ጥያቄ የሚሰጡት ቀጥተኛ መልስ ባይኖርም፣ የሁለቱ የሥራ ግንኙነት የሻከረና በጥርጣሬ፣ ባለመተማመንና መፈራራት ላይ የተመሠረተ እንደነበር አንዳንድ አመልካቾች አሉ፡፡ ተክለ ጻድቅ በንጉሠ ነገሥቱ ላይ ቂምና ቁርሾ ባይሆንም ትልቅ ቅሬታ እንደነበራቸው የሚጠቁሙ ሦስት አብነቶችን ማመልከት በቂ ነው፡፡ ‹‹የካቢኔ ሚኒስትር እንዳልሆን፣ በሀብት ከፍ እንዳልል፣ በኢትዮጵያ ጥናት ተሸልሜ ስም እንዳላገኝ ማድረጋቸው በትክክል ይታወቀኛል፤›› ምናልባት ዋነኛው የቅሬታቸው ምክንያት ይህ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ሌላው ደግሞ በእሳቸውና በአቶ ከበደ ሚካኤል መካከል ሥር የሰደደ ፉክክርና መቀናናት የነበረ ይመስላል፡፡ ጃንሆይም ይህንን ለግል ፍላጎታቸው እንደተጠቀሙበት ጸሐፊው በግልጽ አስቀምጠውታል፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ ‹‹የምናደድበትን የምቀናበትን ሁኔታ ሲፈጥሩብኝ ይታያል፡፡ እንዳጋጣሚ  እኔንና ከበደ ሚካኤልን ማፎካከርና ማበላለጥ ይወዳሉ፤›› አቶ ከበደ ሚካኤል ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሽልማት ድርጅት በኢትዮጵያ ጥናት ተሸላሚ ሲሆኑ፣ ተክለ ጻድቅ ምንም እንኳ ለሽልማቱ በተዳጋጋሚ ቢታጩም ሊጎናጸፉት ግን አልቻሉም፡፡ ይህ ለዘለቄታው ቅሬታንና ምሬትን መፍጠሩ አልቀረም፡፡ ሦስተኛ በአንድ ወቅት ተክለ ጻድቅ በገንዘብ እጥረት ተወጥረው በተመሳሳይ ሁኔታ ላይ ከነበሩት ፕሮፌሰር ታምራት አማኑኤል ጋር ሆነው ጃንሆይን ገንዘብ ለመለመን  ወደ ድሬዳዋ ይጓዛሉ፡፡ ፕሮፌሰሩ 10,000 ብር ተሸክመው ሲመለሱ፣ ተክለ ጻድቅ ግን  የአምስት መቶ ብር ተመጽዋች ሆኑ፡፡ ሰብዓዊ ክብራቸው በመነካቱ አዘኑ፡፡ ፍፁማዊ አገዛዝ በሰፈነበት ሥርዓት፣ ነፃነትና ፍትሕን መውደድ፣ ከአሽቃባጭነት ይልቅ በራስ ተማምኖ መቆምና ለሥልጣን አለማጎብደድ በትንሹ ዋጋው እንዲያ መሆኑን በይበልጥ ሳያስገነዝባቸው አልቀረም፡፡

እንደ ታሪክ ተመራማሪ ተክለ ጻድቅን ካንገበገቧቸውና ካስከፏቸው ጉዳዮች ውስጥ ሁለቱን እንዳመለክት ይፈቀድልኝ፡፡ በቅርሶቿ ጥንታዊነት፣ ብዛትና አስደናቂነት ከግብፅ በስተቀር በምድረ አፍሪቃ ኢትዮጵያን የሚስተካከላት አገር እንደሌለ በሰፊው የተዘገበ ሀቅ ነው፡፡ እነዚህ ቅርሶች በተማከለ አስተዳደር አስፈላጊው ጥበቃና እንክብካቤ ይደረግላቸው ዘንድ ሚኒስትሩ ያደረጉት ሰፊ ጥረት አርኪ ምላሽ አለማግኘቱን በአጽንኦት ዘግበውታል፡፡ በዚህ ጉዳይ ቀዳሚው ተወቃሽ ንጉሠ ነገሥቱን አድርገው፣ ነገር ግን ባለሥልጣናቱም እንቅፋት ፈጣሪዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ምሬታቸውንም እንደሚከተለው ይገልጻሉ፡፡

እኛ ባሁኑ ጊዜ ያለነው ባለሥልጣኖች ለብሔራዊና ለሚያኮራ ቅርስ ዋጋ መስጠት የማንችል፣ ይሉኝታንና ትዝብትን የማንፈራ፣ ሐሜትን የማንሳቀቅ፣ ለዚህችም ታሪክና ቅርስ ለመላባት አገር ዜግነት የማንመጥን ዝቅተኞች ነን የሚል ስሜት አደረብኝ፡፡

ለተክለ ጻድቅ መከፋት ሌላኛው ምክንያት እንደ አገርና ኅብረተሰብ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ የሆነ የሥርዓት ለውጥ ማድረግ አለመቻሉ ነበር፡፡ አብዮቱ እንደፈነዳ በርሳቸው ሊቀመንበርነት የሚመራ አዲስ ሕገ መንግሥት አርቃቂ ጉባዔ ተሰይሞ ሥራውን አጠናቆ ነበር፡፡ ሳይተገበር በቀረው ሕገ መንግሥት ረቂቅ ላይ የተደነገገውም የንጉሠ ነገሥቱ ፍፁማዊ ሥልጣን ሕጋዊ ገደብ ተበጅቶለት፣ በሕዝብ ቀጥተኛ ተሳታፊነት የተመረጠና በአፄው የፀደቀ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር የሚመራ የፓርላማ ሥርዓት ነበር፡፡ ማለትም ሕገ መንግሥታዊ ዘውዳዊ ሥርዓት፡፡ ሆኖም በወቅቱ በተካሄደው አብዮታዊ ትግል ግራ ዘመሙ ክፍል በማሸነፉና በዚህም ምክንያት በተፈጠረው ሥርዓታዊ ቀውስ ወታደራዊ ጁንታ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለመቆጣጠር ቻለ፡፡ ባለ ግለ ታሪኩ ምሬታቸውን ተስፋ በቆረጠ ስሜት የሚከተለውን ጽፈዋል፡፡

እኛ በዚህ ዘመን የተገኘን ሰዎች ለነፃነት፣ ለእኩልነትና ለወንድማማችነት አልታደልንም፡፡ እንደ ነፃው አገር ያሰብነውን ጽፈን፣ ተናግረን፣ ተወያይተንና በነፃ ምርጫ የመተዳደር ዕድል እግዚአብሔር ሊሰጠን አልፈቀደም የሚል ተስፋ አስቆራጭ ዕምነት አደረብኝ፡፡ በዕውነትም በዚህ የትምህርትና የሥልጣኔ ደረጃ ላይ እያለን ቢሰጠንም እንደ ምዕራባውያን አናውቅበትም፣ አንችለውም፡፡ እኛም ትምህርትና ሥልጣኔ ሳይቀድም፣ ጎሳ በበዛበት አገር ነፃውን አስተዳደር የተመኘነው ሐሳባችንና ምኞታችን ያለጊዜው ቀድመው ጠውልገዋል ማለት ነው፡፡

ማለፊያ ገለጻ ነው፡፡ ሆኖም የባህላዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገታችን ዝቅተኝነት እንጂ መለኮታዊ እርግማን አለመሆኑን ለምንገነዘብ ሁሉ የጸሐፊው አስተያየት ምናልባት እጅግ ጨለምተኛ ሊመስል ይችላል፡፡ ጸሐፊው በወቅቱ የተመኙት የመንግሥት ሥርዓት ተቋቁሞ ቢሆንም ኑሮ አገሪቱ ዛሬ ካለችበት ሁኔታ በተለየና በተሻለ ደረጃ ላይ ትገኝ ነበር ለማለት የምንችልበት በቂ መሠረት ባይኖርም፣ የደርግ አገዛዝ ያስከተለውን መከራና እሮሮ ስንመለከትና በወቅቱም በብዙ ወገኖች ላይ የፈጠረውን ተስፋ መቁረጥ ስንመዝን የጸሐፊውን አገላለጽ አክብዶ መተቸት ያስቸግራል፡፡

ታላቅነነት አይወረስም፣ ይቀዳጁታል እንጂ፡፡ ተክለ ጻድቅ መኩሪያ ከጎተራ ጸሐፊነትና የመዝገብ አለቃነት እስከ ሚኒስትርነት፣ ከዚያም ዕውቅ ደራሲ እስከመሆን የበቁት በመንፈስ ጽናትና ብርታት፣ በግል ጥረትና ቁርጠኝነት መሆኑ ግለ ታሪካቸውን ለሚያነብ ሁሉ ግልጽ ነው፡፡ እኝህ ሰው ሰሜን ሸዋ ውስጥ በምትገኘው አሳግርት ወረዳ አቆዳዳ ወይም ሳር አምባ መንደር መስከረም 1 ቀን 1906 ዓ.ም. ተወልደው ሐምሌ 16 ቀን 1992 ዓ.ም ይችን ዓለም ሲለይዋት፣ ኢትዮጵያ ከብርቅዬ ልጆቿ አንዱን አጣች፡፡ ተክለ ጻድቅን የመሰለ ታላቅ ዜጋ አረፈ እንጂ ሞተ አይባልም፡፡ ድርሳኖቻቸው ለዘለዓለሙ ሕያውነታቸውን ሲያወሱላቸው፣ ሲያስመሰግኗቸውና ሲያስተቿቸው ይኖራሉ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡