በዓለ ጥምቀትም እንደ በዓለ መስቀል ተራው ደረሰ

በአገራችን በአደባባይ ደምቀው ከሚከበሩ በዓላት አንዱና ዋነኛው የጥምቀት በዓል ስለመሆኑ መናገር ክርክር አያስነሳም፡፡ በየዓመቱ ጥር 11 የሚከበረው ይህ በዓል ሃይማኖታዊና ባህላዊ በዓል ከመሆን ባለፈ ማኅበራዊ ትስስርን የሚያጠናክር መድረክ ሆኗል፡፡ ሃይማኖታዊነቱ ከኢየሱስ ክርስቶስ መጠመቅ ጋር የሚያያዝ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ ጥር 10 ታቦታት ወደ ወንዝ፣ መጠመቂያ ቦታ ወይም ገንዳ በሕዝብ ታጅበው ወርደው ካደሩ በኋላ በማግስቱ ጥር 11 ወደየአጥቢያቸው የሚመለሱበት ሥርዓት ነው፡፡ ካህናት ጥንግ ድርብ፣ ልብሰ ተክህኖ ለብሰው፣ የሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን በተለያዩ ቀለማት አሸብርቀው በዝማሬ በየአደባባዩ ታቦታቱን አጅበው ይጓዛሉ፡፡ በአዲስ አበባ፣ በጐንደርና በላሊበላ በዓሉ እጅጉን አሸብርቆ ሲከበር ቱሪስቶችን እጅጉን ይማርካል፡፡ ከሃይማኖታዊ ይዘቱ ጐን ለጐን ባህላዊነት በስፋት ይስተዋላል፡፡ የተለያዩ የብሔር ብሔረሰቦችን አልባሳት የለበሱ ሰዎች እየዘፈኑ፣ እየጨፈሩ፣ ባህላቸውንና ወጋቸውን በዓሉን ለሚያከብረው ሰው ያሳያሉ፡፡ አማራው፣ ኦሮሞው፣ ትግሬው፣ ጉራጌው ሌሎቹም በየዓውድ በየዓውዳቸው በሥርዓቱ ሲጨፍሩ ላስተዋለ በዓሉ ኅብረ ብሔራዊነት የሚንፀባረቅበት ስለመሆኑ በቀላሉ ይረዳል፡፡ የባህል ጎኑ አንዱ መገለጫ ደግሞ በዚህ ወቅት ሴቶችና ልጃገረዶች ከሌላው ቀን በተለየ አጊጠውና አምረው በአደባባይ የሚታዩበትና ወንዱም ለጋብቻም ሆነ ለሌላ ግንኙነት ልቡ የሚሸፍትበት ጊዜ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ‹‹ለጥምቀት ያልሆነ ልብስ ይበጣጠስ›› እንዲል ብሂሉ በበዓለ ጥምቀት ሁሉም ያማረ ለብሶ ቆንጆ ሆኖ የሚውልበት ነው፡፡ ጥምቀትን መሠረት አድርጎ ትዳር የመሠረተ ብዙ ሰው መኖሩን ከጥንት ጀምሮ የምንሰማው ነገር ነው፡፡ ከቅርብ ዓመታት ጀምሮ ደግሞ ጥምቀት የወጣቱ ኅብረትና ለአንድ ዓላማ በጽናት የሚቆምበት በዓል ሆኗል፡፡ ታቦታቱ የሚያልፉበትን መንገዶች በሰንደቅ ዓላማ ማሸብረቅ፣ መንገዱን ማጠብ፣ ቆሻሻውን ማንሳት፣ ምንጣፍ ማንጠፍ፣ ሕዝቡን ማስተናበር፣ ለሕዝቡ ፀበል ጻድቅ ማዘጋጀት፣ ወዘተ. እጀጉን የሚማርክ የበዓሉ ክፍል ሆኗል፡፡ መንፈሳዊነት፣ ባህልና ማኅበራዊ ትስስር በስፋት የሚስተዋልበት ይህ በዓል በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት ማስመዝገብ ቢያንስበት እንጂ የሚበዛበት አይሆንም፡፡ አገራችን የመስቀል በዓልንና ጫንበላላ የሲዳማ የአዲስ ዓመት አከባበርን ግዙፍነት የሌላቸው ባህላዊ ቅርሶችን በዩኔስኮ ያስመዘገበች ሲሆን፣ የጥምቀት በዓል ቀጣዩ ዓለም ሊያውቀው የሚገባ ተመዝጋቢ ቅርስ መሆኑን ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡

ግዙፍነት የሌለው ባህላዊ ቅርስ

ከቅርስ አንፃር የዩኔስኮ ዋና ዓላማ ግዙፍነት ያላቸውንና የሌላቸው ቅርሶች ዓለም አቀፍ ጥበቃ እንዲያገኙና ጠቀሜታቸውም በዓለም ሁሉ እንዲታወቅ ማድረግ ነው፡፡ ይህን ዓላማውን ለማስፈጸም ግዙፍነት የሌላቸውን ባህላዊ ቅርሶች በተመለከተ ዩኔስኮ ሁለት ዓይነት ምዝገባዎችን (List) ቀርጾ ይፈጽማል፡፡ የመጀመርያው ግዙፍነት የሌላቸው ባህላዊ ቅርሶችን በሰው ዘር ቅርስነት መመዝገብ (List of intangible cultural heritage of humanity) ሲሆን፣ ይህም የቅርሱን ብዙኃነትና ጠቀሜታው ጋር የሚያተኩር ነው፡፡ ሁለተኛው አስቸኳይ ጥበቃ የሚያስፈልጋቸው ግዙፍነት የሌላቸው ቅርሶች ምዝገባ (List of intangible cultural heritage in need of urgent safeguarding) ሲሆን፣ ዋና ዓላማው አገሮችና ኅብረተሰብ ያሉት መንፈሳዊ ሀብቶች እንዳይጠፉ በምዝገባ ጥበቃ መስጠት ነው፡፡ የጥምቀት በዓል አከባበር በመጀመሪያው ምዝገባ ሥር ሊታይ የሚችል ሲሆን፣ በዩኔስኮ የወጡትን መሥፈርቶች ማሟላቱ በዩኔስኮ ኮሚቴ ከተረጋገጠ መመዝገቡ እውን ይሆናል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2003 የወጣውና ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2006 የፈረመችው ግዙፍነት የሌላቸው ባህላዊ ቅርሶች ጥበቃ ኮንቬንሽን ሊሟሉ የሚገባቸውን መሥፈርቶች ደንግጓል፡፡ በዚህ ስምምነት መሠረት ግዙፋዊነት የሌለው ባህላዊ ቅርስ የሚከተሉትን ኩነቶች ሊያካትት ይችላል፡፡

የመጀመርያው በቃል ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፉ ትውፊቶችና ንግግሮች (Oral traditions and expressions) ናቸው፡፡ በዚህ ምድብ የሚወድቁት በኅብረተሰቡ ውስጥ ባህልና ኅብረተሰባዊ ዋጋ (Values) ለማስተላለፍ የምንጠቀምባቸው ንግግሮችና ትውፊቶች ናቸው፡፡ ምሳሌያዊ ንግግሮች፣ ፈሊጣዊ ንግግሮች፣ ግጥሞች፣ አፈታሪኮች፣ ዘፈኖችና መዝሙሮች፣ ሥነቃል፣ ተረት፣ ታሪኮች፣ ፀሎት የድራማ ኩነቶች ወዘተ. በዚህ ምድብ ይጠቃለላሉ፡፡

ሁለተኛው የሚከወኑ ትዕይንቶች (Performing arts) ናቸው፡፡ እነዚህ በኅብረተሰቡ ውስጥ በተለያዩ ዓላማዎችና ምክንያቶች የሚከናወኑ ዘፈኖች፣ ድርሰትና ቴአትሮችን ያካትታል፡፡ እጅጉን የተለመደው የዘፈን ሥርዓት ሲሆን፣ የኅብረተሰቡን ባህል፣ ታሪክ፣ ፖለቲካዊ እሳቤ ወዘተ. የሚያንፀባርቅ በመሆኑ ግዙፋዊነት በሌለው ባህላዊ ቅርስ ይመዘገባል፡፡ በጋብቻ፣ በለቅሶ፣ በባህላዊ በዓላት፣ ፌስቲቫሎችና ሌሎች ኩነቶች የሚወጡ ግጥሞች፣ የሚታዩ ትዕይንቶችና ባህላዊ መሣሪያዎቹም ጭምር የዚሁ ቅርስ አካል ተደርገው ይቆጠራሉ፡፡

ሦስተኛው ማኅበራዊ ድርጊቶች፣ በዓላትና የሕዝብ ትዕይንቶች (Social practice, rituals and festive events) ናቸው፡፡ እነዚህ ቅርሶች በኅብረተሰቡ ለዘመናት እየተፈጸሙ ያሉ የባህልና የሃይማኖት ሥርዓቶች ሲሆኑ የኅብረተሰቡ መለያ ተደርገው ይቆጠራሉ፡፡ የጥምቀት በዓልም በዚህ ምድብ የሚወድቅ ነው፡፡

አራተኛው ተፈጥሮንና ዓለምን የተመለከቱ ዕውቀቶችና ልማዶች (Knowledge and practices concerning nature and the universe) ናቸው፡፡ ባህላዊ ዕውቀቶች፣ ስለተፈጥሮ የሚገለጹ አካባቢያዊ ዕውቀቶች፣ ትውፊታዊ መድኃኒቶች፣ ባህላዊ አደረጃጀቶች ወዘተ. በዚህ ምድብ ይወድቃሉ፡፡

አምስተኛውና የመጨረሻው ትውፊታዊ የዕደ ጥበብ ዕውቀት (Traditional Craftsmanship) ናቸው፡፡ እነዚህ ቅርሶች ከዕደ ጥበብ ውጤቶች ይልቅ ዕውቀቱና ክህሎቱ ላይ የሚያተኩር በመሆኑ መሣርያዎች፣ ልብሶች፣ ጌጣጌጦች፣ መኖሪያ ቤቶች፣ የትምህርት መረጃዎች ወዘተ. የሚሠሩባቸውን ዕውቀቶችና ክህሎቶች ያጠቃልላል፡፡ቅርሱ ግዙፋዊነት የሌለው የባህል ቅርስ መሆኑ ከተረጋገጠ ሌሎች መሥፈርቶች መሟላት ይኖርባቸዋል፡፡ ቅርሱ የባህል ብዙኃነትን የሚያንፀባርቅ፣ ቅርሱን ለመጠበቅ የሚያስችሉ ጠንካራ አሠራሮች፣ ሰፊ የኅብረተሰብ ፈቃድና ተሳትፎ ያገኘ ሊሆን ይገባል፡፡

አንድ ቅርስ የዓለም ቅርስ የሚባለው ምን ሲያሟላ ነው?

ቅርስን የዓለም ቅርስ በሚል የመወሰን ሥልጣን ያለው የዓለም የቅርስ ኮሚቴ (The World Heritage Committee) ሲሆን፣ 21 አባላትን የያዘና በአገሮች የሚመረጥ ነው፡፡ ኮሚቴው ፍትሐዊ ውክልና እንዲኖረው የአኅጉራቱ ስብጥር እንዲጠበቅ ያደርጋል፡፡ አንድን ቅርስ በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ አቤቱታ የሚያቀርበው የዩኔስኮ አባል አገር ሲሆን፣ ኮሚቴው ጥያቄውን መርምሮ ዕውቅና ሊሰጠው ይችላል፡፡ አንድ ቅርስ የዓለም ቅርስ ለመባል በአንቀጽ 11(2) መሠረት በኮሚቴው ልዩ ዓለም አቀፋዊ እሴት (Outstanding Universal Value) እንዳለው ሊታመንበት ይገባል፡፡ ኮሚቴው ለዓለም ቅርስነት የሚያበቁ መሥፈርቶችን በየጊዜው የሚያሳውቅ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ባለው መሥፈርት አንድ ቅርስ አራት መሥፈርቶችን ካሟላ የዓለም ቅርስ ሊባል ይችላል፡፡ 

የመጀመርያው በዩኔስኮ ከወጡት አሥር መሥፈርቶች (ቅድመ ሁኔታዎች) ውስጥ አንዱን ሊያሟላ ይገባል፡፡ ከእነዚህ መሥፈርቶች ውስጥ ከመስቀል በዓል ጋር የሚያያዙትን ሁለቱን መሥፈርትን እንመልከት፡፡ አንዱ ኩነቱ ልዩ የሆነ ባህል ወይም ትውፊት ወይም ዘመናዊነት ያለው ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ በቀጥታ ወይም በተለምዶ ዓለም አቀፋዊ ጠቀሜታ ካለው ኩነት ወይም ትውፊት ጋር የተገናኘ የኪነ ጥበብና የጽሑፍ ሥራ ሊሆን ይገባል፡፡

ሁለተኛው ወጥነት (Integrity) ያለው መሆን አለበት። ወጥነት ሲባል የቅርሱ ባለቤት የሆነው ኅብረተሰብ በተመሳሳይ ሁኔታ ሲተገብረው ነው፡፡ በኅብረተሰቡ የባህሉ፣ ትውፊቱ ወይም ሥርዓቱ ባለቤት ወቅቱን ጠብቆ የሚተገብረው ከሆነ እሴቱን ለዘመናት ይዞት የሚኖር መሆኑ ከተረጋገጠና ሥርዓቱ ከሚደርስበት ፈተና ለመታደግ ኅብረተሰቡ በጋራ የሚሠራ ከሆነ ለወጥነቱ በቂ አስረጅ ነው፡፡

ሦስተኛው መሥፈርት ትክክለኛነት (Authenticity) ነው፡፡ ይህም ቅርሱ የኅብረተሰቡ የራሱ የሆነና እውነተኛ መገለጫው መሆኑ ላይ ነው፡፡ ቅርሱ የተኮረጀ ትውስት ወይም ኮፒ ከሆነ ትክክለኛ ስለማይሆን ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ የዚህ መገለጫው በሦስት መልኩ ይታወቃል፡፡ መጀመርያ ግዙፍነት የሌለውና የቅርሱ አተገባበር ለሌላ ባዕድ ኅብረተሰብ አዲስ የመሆኑ ጉዳይና አዲስነቱ (The Creative Process) ነው፡፡ ሌላው የጽሑፍ የታሪክ መረጃ ሊኖረው ይገባል፡፡ የጽሑፍ መረጃው መሠረት የሚያደርገው ለዘመናት የቆየውን ልማድ እንደሚሆን ይታሰባል፡፡ ሦስተኛው ደግሞ የማኅበራዊ አውዱ (The Social Context) ነፀብራቅ ነው፡፡ ኅብረተሰቡ ቅርሱን ሀብቱ ስለማድረጉ በተግባሩ፣ በዘፈኑ፣ በአመጋገቡ፣ በአለባበሱ በአጠቃላይ በአኗኗሩ ከገለጸው ትክክለኛነቱ በቂ አስረጅ ነው፡፡

አራተኛው መሥፈርት ቅርሱን የሚጠብቅና የሚያስተዳድር አካል የመኖሩ ጉዳይ ነው፡፡ ይህ በቅርሱ ባለቤት አገር የአስተዳደር መዋቅር የሚዘረጋ ሲሆን፣ ራሱን የቻለ ቅርስን የሚንከባከብና የሚያስተዳድር ተቋም ያስፈልገዋል፡፡ በአገራችን በአዋጅ ቁጥር 209/1992 የኢትዮጵያ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን የተቋቋመ በመሆኑ ቅርሶች ጠባቂና አስተዳዳሪ አላቸው፡፡

ጥምቀት መሥፈርቶቹን ስለማሟላቱ

የጥምቀት በዓል ከላይ የተጠቀሱትን መሥፈርቶች በአግባቡ የሚያሟላ ስለመሆኑ ብዙ ምክንያቶችን ማቅረብ ይቻላል፡፡ የመጀመሪያው በዓሉ ከሌላው ዓለም በተለየና በወጥነት ለብዙ ዘመናት ሲተገበር የቆየ መሆኑ ነው፡፡ በሁሉም ዓለም የክርስቶስ ጥምቀት በተለያየ መልኩ ቢከበርም ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚከበረው ሰፊ፣ ሁሉን ያሳተፈና ደማቅ አለመሆኑ ሁሉንም ያስማማል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት አድርጐ የሚከበረው የጥምቀት በዓል ለማያምነው ሳይቀር የክርስቶስን ጥምቀት ሒደቱን፣ ዓላማውንና መንፈሳዊ ትምህርቱን ለሁሉም የሚያሳውቅ በዓል ነው፡፡ አከባበሩም ወጥነት አለው፡፡ በጐንደርም ሆነ በአዲስ አበባ፣ በመቀሌም ሆነ በወላይታ በመላው ኢትዮጵያ ተመሳሳይ በሆነ ሥርዓትና ቅርጽ ይተገበራል፡፡ በዓሉም የኢትዮጵያውያን የራሳቸው የሆነና ከሌላው ያልተቀዳ ሃይማኖታዊ ዳራ አለው፡፡ የጥምቀት በዓል በመጽሐፍ ቅዱስ ሰፍሮ የምናገኘውን የክርስቶስን ጥምቀት በድርጊታዊ ኩነቶች የሚያሳይ ለዘመናት በአገራችን የሚተገበር፣ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን በእጅጉ የሚያሳትፍ በዓል የመሆኑ ጉዳይ ነው፡፡ በሦስተኛነት ሊጠቀስ የሚችለው ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍበት ሁኔታ፣ ማራኪነቱና ማኅበራዊ ፋይዳው ነው፡፡ በበዓሉ ወቅት የሚታየው ዝማሬው፣ የባህል ጭፈራው ማራኪነት፣ በወጥነት የሚፈጸመው ሥርዓትና በዓሉን በሚገባ ለመፈጸም የሚያስችለው አደረጃጀት በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ነው፡፡ ሌላው በዓሉ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፈው በመንፈሳዊ ቁርጠኝነት መሆኑና ዕድሜ፣ ፆታ፣ ብሔር ሳይለይ ሁሉም ተሳታፊ የሚሆንበት ነው፡፡ ማኅበራዊ ፋይዳውም ሰፊና ለሁሉም የተገለጠ ነው፡፡ በአገሪቱ ማኅበራዊ አንድነትና የእርስ በርስ ትስስርን፣ ብዝኃነትን የሚያንፀባርቅ፣ በበርካታ ብሔረሰቦች ባህሎች መካከል ትስስርን የፈጠረ በመሆኑ ዓለም አቀፍ መሥፈርቱን በአግባቡ ማሟላቱን ሁሉም ሊመሰክረው የሚችል ሐቅ ነው፡፡

በዓለ መስቀል በቅርስነት በተመዘገበበት መልኩ በዓለ ጥምቀትም እንዲሁ መመዝገቡ ብዙም ሩቅ አይሆንም፡፡ ምዝገባው አገራችንን ያሳውቃል፣ ማንነታችንን ይገልጻል፣ የቅርሱ ባለቤት ያደርጋል፣ የቱሪዝምን ገቢ ያሳድጋል፡፡ እናም መንግሥትና ቤተ ክርስቲያን የጀመሩትን አጠራክረው ሊቀጥሉ፣ አገራችን በምታስተናግደው የዩኔስኮ ጉባዔ ላይም ብስራቱን እንደምንሰማ ተስፋ አለን፡፡ ሌሎቹም መንፈሳዊ ሀብቶች ቅኔው፣ዝማሬው፣ መወድሱ፣ ሰዓታቱ ወዘተ. ሁሉም ተራውን ጠብቆ ይመዘገባል፡፡ ዓለምም የአገራችንን ሀብት ያውቃል፡፡

አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው getukow [at] gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡