በኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት ላይ የሚያጠሉ ሥጋቶች

በየማነ ናግሽ

በወርኃ ግንቦት 2007 ዓ.ም. አምስተኛ ዙር ጠቅላላ ምርጫ ተከናውኖ ‹‹አዲሱ›› መንግሥት በተያዘው ዓመት የመጀመሪያ ወር (መስከረም) የመጨረሻው ሳምንት በይፋ ተቋቋመ፡፡ የፓርላማው መቀመጫዎችን ከአጋሮቹ ጋር ሙሉ በሙሉ የተቆጣጠረው ኢሕአዴግ፣ በአዲሱ መንግሥት ምሥረታ በዋናነት የዚህ ዓመት ፈተና አድርጎ የተመለከተው በኤልኒኖ ሳቢያ የተከሰተውን ድርቅ ነበር፡፡ ችግሩ ከቁጥጥር ውጪ እንዳይሆን መንግሥት ሙሉ ኃይሉን በመጠቀም ምላሽ በመስጠት ላይ ተሰማራ፡፡

የተለያዩ ፍላጎቶችና አስተሳሰቦች ባሉባት አገር የሕዝቡን ሙሉ ይሁንታ በማግኘት በምርጫ አሸናፊ መሆኑን የገለጸው ገዥው ፓርቲ ግን፣ መንግሥት መሥርቶ ድርቅ ለመቋቋም መንቀሳቀስ በጀመረባቸው ቀዳሚ ወራት ውስጥ ነበር ያልተገመተውና ያልታሰበው ሕዝባዊ አመፅ ከኦሮሚያ ክልል ብቅ ያለው፡፡

ምናልባትም ከ1997 ዓ.ም. ምርጫ ማግሥት በኋላ ከተከሰተው ብጥብጥ ወዲህ ባለፉት አሥር ዓመታት እንደዚህ ዓይነት ሕዝባዊ አመፅ ሲከሰት በአገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሆን፣ መጀመሪያ አካባቢ የአመፁን መነሻ ወደ ውጭ ለመግፋት ሲደረግ የነበረውን ጥረት የሚቀለብስ ሪፖርት ለፓርላማ መቅረቡ ይታወሳል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ቀውሱን አስመልክተው ከኢሕአዴግ ያልተለመደና ወጣ ያለ ተብሎ በታሰበ መንገድ፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ ጠይቀው የችግሩ ምንጭ የአስተዳደር ጉድለት መሆኑን ገልጸው ነበር፡፡

በእርግጥ አንዳንዶች እንዳሉት ችግሩ በኦሮሚያ ክልል ነዋሪዎች ብሶት ተጋለጠ እንጂ፣ ይኼ ሕዝብን ያስለቀሰ የመልካም አስተዳደር ዕጦት ውስጥ ለውስጥ እየተብላላና ወደ መጨረሻ ጫፍ አካባቢ መድረሱን፣ የኢትዮጵያ ፖሊሲና ጥናት ማዕከል ያቀረበው ሪፖርት ያመለክታል፡፡

በኦሮሚያ የተከሰተውን አመፅን ለማብረድ መንግሥት ከመጠን በላይ ኃይል መጠቀሙን የአሜሪካ መንግሥትን ጨምሮ አንዳንድ ወገኖች የገለጹ ሲሆን፣ ከፍተኛ የሆነ የንብረት መውደሙና በርካታ ቁጥር ያለው የሰው ሕይወት ለማለፉ ምክንያት ሆኗል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩን ይቅርታ ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል የተከሰተው ችግር ቀዝቀዝ ያለ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያን የተረጋጋ ድባብ የሚረብሹ ክስተቶች ተከታትለው እየታዩ ይመስላል፡፡

በየመን የተከሰተው ሥጋት

በዚህ ዓመት የውስጥ ሁኔታ ብቻ አልነበረም አሳሳቢ የሆነው፡፡ መንግሥት በቂ ትኩረት እንደሰጠው ምንም ማረጋገጫ ባይገኝም፣ የመን ውስጥ የተከሰተውን የእርስ በርስ ግጭት በመጠቀም ሁቲ የሚባለውን ቡድን ለመምታት በሚል ሰበብ በኢትዮጵያ ላይ እንቅልፍ አይወስዳቸውም ተብለው የሚገመቱት ግብፅና ሳዑዲ ዓረቢያ በግንባር ቀደምትነት የሚመሩት፣ የጎረቤት ጠላት የሆነው የኤርትራ መንግሥት የተቀላቀለበት ቅንጅት መፈጠሩ አይዘነጋም፡፡

ከኢትዮጵያ ጋር በከፈተው ጦርነት አሁንም ድረስ ከመፍትሔ ይልቅ ችግር የሚፈጥረው የኤርትራ መንግሥት በፈጠረው ቅንጅት በርከት ያሉ ወታደሮች ያወጣ ሲሆን፣ እጅግ ስትራቴጂካዊ የሚባለውንና ለኢትዮጵያ የደኅንነት ሥጋት ይሆናል ተብሎ የሚታመንበትን የቀይ ባህር ለቅንጅቱ ‹‹ነፃ የበረራ ዞን›› እንዲሆን ፈቅዷል፡፡

በተጨማሪም በኢትዮጵያ መንግሥት ‹‹የግመል መጠጪያ›› ይሆናል ተብሎ ዝቅ የተደረገው የአሰብ ወደብ እጅግ ከፍ ባለ ምናልባትም በብዙ ቢሊዮን ዶላር በሚገመት ስምምነት፣ ለተባበሩት የዓረብ ኤምሬትስ ለ30 ዓመታት መከራየቱ ይፋ ተደርጓል፡፡

ሳውዝ ፍሮንት በመባል የሚታወቀው አንድ መርማሪ ሪፖርት የቅንጅቱ ዓላማ በጊዜያዊነት የሁቲ አማፂ ቡድንን ለመምታት ይምሰል እንጂ፣ ቅንጅቱ በዘላቂነት ለኢትዮጵያ የደኅንነት ሥጋት ሊሆን እንደሚችል ጠቁሞ ነበር፡፡

ለአንዳንድ የፖለቲካ ታዛቢዎች ሁኔታውን አሳሳቢ የሚያደርገው፣ የኤርትራ መንግሥት ከዚህ የወደብ ኪራይና ከዓረብ አገሮች ቅንጅት የሚያገኘው ገንዘብና ወታደራዊ ድጋፍ እንደ ዋና ጠላት የምትታየው ኢትዮጵያን ለማጥቃት ሊውል ይችላል የሚል ጥርጣሬ ነው፡፡ ይኼም እየሆነ ያለው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የፀጥታው ምክር ቤት ከአንዴም ሁለቴ የጦር መሣሪያ ዝውውር ማዕቀብ በተጣለባት አገር ነው፡፡ አንድ ስማቸውን እንዲገለጽ ያልፈለጉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ ኃላፊ፣ ‹‹መንግሥት በቅርበት የሚከታተለው ነው፤›› ቢሉም፣ በዝርዝር ምን ዓይነት ዕርምጃ እየተወሰደ እንደሆነ ግን ለመግለጽ አልፈለጉም፡፡

በሚስጥር የሚሠራ ነገር ከሌለ በስተቀር በተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ሆነ በሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ የመንግሥትን አንዳችም ዕርምጃ በመረጃ ማግኘት አልተቻለም፡፡

በምሥራቅ አፍሪካ አካባቢ ፀጥታና ሽብርን ለማጥናት፣ ለመተንበይና ለመከላከል ታስቦ በኢጋድ ሥር የተቋቋመው የደኅንነት ዘርፍ ፕሮግራም ዳይሬክተር የሆኑት ኮማንደር አበበ ሙሉነህ ግን፣ ሳዑዲ ዓረቢያ የምትመራው ቅንጅት በየመን ሊሰማራ አካባቢ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ወደ ሳዑዲ ዓረቢያና ወደ የተባበሩት የዓረብ ኤምሬትስ መጓዛቸው ያለምክንያት እንዳልነበረ ለሪፖርተር ይናገራሉ፡፡ አሁንም ቢሆን የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴዎች ይፋ አለመሆናቸውንና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አካባቢ ከፍተኛ ዲፕሎማቶች መኖራቸውን ገልጸው፣ ‹‹ምንም እየተሠራ አይደለም ብሎ ማመን ይከብዳል፤›› ሲሉ ግምታቸውን ይናገራሉ፡፡

‹‹ኤርትራ ውስጥ ያለው መንግሥት ደንበኛ የቢዝነስ ቡድን ነው፤›› በማለት በቅፅበት ከኢራን ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ ደጋፊነት የተመለሰበት ምክንያት ገንዘብ ፍለጋ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡

የመን ላይ ያነጣጠረው በሳዑዲ ዓረቢያ አነሳሽነት የተቋቋመው ቅንጅት፣ በኢትዮጵያ ላይ ቅያሜ ያላቸው አገሮችን ከመያዙ በተጨማሪ የጦረኝነት ባህሪ ያላቸውን አገሮች ያቀፈ በመሆኑ ችላ መባል የለበትም ይላሉ፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት ቁጭ ብሎ ይመለከታል ብዬ አላምንም፤›› በማለት፡፡  

ሳውዝ ፍሮንት አናሊስት እንደሚለው፣ ‹‹ኤርትራ አጋጣሚውን ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የደረሰባትን የመነጠል አደጋ ለመላቀቅ ትጠቀምበታለች፡፡ ኢትዮጵያና ጂቡቲ በአፍሪካ ኅብረት አማካይነት በኤርትራ ያለው የአካባቢው ሕገወጥ ሥርዓት መሆኑን ለማሳየት ጥረት ሲያደርጉ ነበር፡፡ በመሆኑም የሳዑዲንና የኤምሬትስን ገንዘብ መቀበል ምክንያታዊ ነው፤›› ብሏል፡፡

ከትግራይ እስከ ጋምቤላ

የኤርትራ መንግሥት ይህንን ገንዘብ ባገኘ ጥቂት ወራት ውስጥ ታጣቂ ኃይሎችን በመላክ፣ ከትግራይ ክልል በባህላዊ መንገድ ወርቅ በማውጣት ላይ የነበሩ ቁጥራቸው 85 የሚደርስ ወጣቶች አፍኖ መውሰዱ ይታወሳል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትም በጉዳዩ ላይ ለሁለት ሳምንት ያህል ዝም ካለ በኋላ መረጃው በጥቂት የግል ሚዲያዎች ይፋ በመውጣቱ ምክንያት የኤርትራን መንግሥት በማስፈራራት የተወሰኑት መመለሳቸው ታውቋል፡፡ የተቀሩት ግን እስከዛሬ የገቡበት አልታወቀም፡፡ መንግሥትም የገለጸው ነገር የለም፡፡

እምብዛም ሳይቆይ ሁለት ወራት ባልሞላ ጊዜ የደቡብ ሱዳን የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች መሆናቸው የተነገረላቸው አንድ ሺሕ የሚደርሱ ታጣቂ ኃይሎች ከደቡብ ሱዳን ወደ ጋምቤላ ክልል በመግባት፣ በርካቶችን ገድለው ከ100 በላይ ሕፃናትን አፍነው ወስደዋል፡፡ በርካታ ከብቶችም ዘርፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል ሕፃናቱን ለማስለቀቅ ደቡብ ሱዳን ዘልቆ የገባ ሲሆን፣ የተወሰኑትን በድርድር ከማስመለስ ውጪ ስለተቀሩት ዜጎች ግልጽ የሆነ መረጃ አልተገኘም፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፡፡ የጋምቤላ የጥቃት ዜና በተሰማ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሱዳን ድንበርን ጥሰው የገቡ የታጠቁ ኃይሎች በእርሻ ላይ የነበሩ ዜጎችን አፍነው መውሰዳቸው እየተነገረ ነው፡፡ እንዲሁም የኤርትራ መንግሥት እንደላካቸው የተገለጸ በደቡብ ክልል በኩል በኢትዮጵያ ላይ የሽብር ጥቃት ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ፣ በኢትዮጵያ ፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር መዋላቸው ተሰምቷል፡፡

የፀጥታ ባለሙያው ኮማንደር አበበ፣ ከኦሮሚያ ግጭት በኋላ እየታዩ ያሉ ተከታታይ የፀጥታ ክስተቶች በጥንቃቄ መመርመር እንዳለባቸው ያሳስባሉ፡፡ ከደቡብ ሱዳን ተነስተው በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ ጥቃት የፈጸሙ ኃይሎች ከጀርባቸው የሆነ ገፊ ሌላ ኃይል ሊኖር እንደሚችል ይገምታሉ፡፡ የከብት ዘረፋ የተለመደ ቢሆንም፣ እንዲህ እስከ አፍንጫቸው ታጥቀው የተደራጀ ጥቃት መፈጸማቸውን ግን ጥርጣሬውን ከፍ እንደሚያደርገው ያስባሉ፡፡

በእርግጠኝነት መናገር ባይቻልም ሁለት ነገር መገመት ይቻላል ይላሉ፡፡ አንድም የዶ/ር ሪክ ማቻር ወደ ጁባ መመለስ በአንድ ሳምንት ከመዘግየት ጋር በተያያዘ፣ አሊያም ሁኔታውን ለማባባስ ከደቡብ ሱዳን ውጪ ሌላ አገር ከጀርባ ሊኖርበት እንደሚችል ይናገራሉ፡፡ ጥቃት የተፈጸመበት የኑዌር ጎሳ ሲሆን፣ ማቻር የኑዌር ጎሳ አባል መሆናቸው አይዘነጋም፡፡

በሌላ በኩል በኢትዮጵያ የታላቁ የህዳሴ ግድብ መገንባት ምክንያት ቅሬታ ያላት ግብፅ በየመን የተሠማራውን ቅንጅታዊ ኃይል ለመርዳት ይውል ዘንድ፣ በሶማሊላንድ አካባቢ ቁጥሩ ያልታወቀ የታጠቀ እግረኛ ኃይል መላኳ እየተነገረ ነው፡፡ በኦጋዴን አካባቢም ሆነ ግድቡ በሚገነባበት በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተፈጠረው የውጭ ኃይል ጥቃት የግብፅ እጅ ይኑርበት አይኑርበት ማረጋገጥ አልተቻለም፡፡  

በሌላ በኩል የኦጋዴን ነፃ አውጪ ግንባር መሥራችና ቃል አቀባይ እንደሆኑ የተነገረላቸው አብዱራህማን ማህዲ በቅርቡ ከአልጄዚራ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ድርጅታቸው የሚያራምደው የመገንጠል ዓላማ ሳይሆን የሕዝቡን ‹‹የራስን ዕድል በራስ የመወሰን›› መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ተገንጣይ›› የሚለው የኢትዮጵያ መንግሥት ፕሮፓጋንዳ ነው በማለት፡፡

አቶ አብዱራህማን እንደሚሉት፣ የኦጋዴን አካባቢ በልማት ኋላ የቀረና ሕዝቡም በድህነት እየማቀቀ ይገኛል፡፡ ‹‹መቀናጀታችን ዛሬ እየሰፋ ነው፤›› የሚሉት አቶ አብዱራህማን፣ ከሌሎች የኢትዮጵያ አማፂ ኃይሎች ጋር ለመተባበር መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡

‹‹ኢትዮጵያ አሁን እየተነቃነቀች ትገኛለች፡፡ ሥርዓቱም የተከፋፈለ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብም ተነስቷል፡፡ እንደ የዓረብ ፀደይ ትግሉን እናቀጣጥለዋለን፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡ በኤርትራ መንግሥት ይደገፉ እንደሆነ ተጠይቀው ቢክዱም በአስመራ ጽሕፈት ቤት እንዳላቸው ግን አምነዋል፡፡ የኦጋዴን ነፃ አውጪ ግንባር በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት ከተሰየሙ የአገር ውስጥ ድርጅቶች አንዱ ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜ እዚህ ግባ የሚባል ኃይል እንደሌለው ይነገራል፡፡ የአቶ አብዱራህማንን ንግግር ‹‹አለሁ አልሞትኩም›› ዓይነት መፈራገጥ አድርገው የሚመለከቱት አሉ፡፡   

በኢትዮጵያ ስትራተጂካዊ ጥናት ተቋም ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት አቶ አበበ ዓይነቴ፣ በአሁኑ ወቅት እዚያም እዚህም እየተከሰተ ያለው የፀጥታ ችግር የፀጥታ ሥጋት ባህሪው እየተቀየረ ለመምጣቱ አመላካች መሆኑን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ የፀጥታ ሥጋት መከላከል በአብዛኛው ሽብር ላይ ያተኮረ መሆኑን፣ አሁን እየታየ ያለው ግን መልኩን እየቀየረ መምጣቱን ይናገራሉ፡፡ የኢትዮጵያ ትኩረት በአሮጌ ትንታኔ ላይ የቆመ እንዳይሆን በማሳሰብ፣ በየመን እየሆነ ያለው ወቅታዊ ሁኔታ ከፍተኛ ትኩረት የሚስብ ነው ይላሉ፡፡ በተለይ የግብፅንና የኤርትራን እንቅስቃሴ በቅርበት እየተከታተሉ አስቀድሞ ዕርምጃ እንዲወሰድም ያሳስባሉ፡፡

ኮማንደር አበበ ሙሉነህ በበኩላቸው፣ ከውጭ እየተሰነዘሩ ያሉ ጥቃቶች ኢትዮጵያ በውጭ እንዴት እየታየች እንደሆነ አመላካች እንደሆኑ አስረድተው፣ ‹‹የፌዴራል መንግሥት ከክልል፣ ታች ካሉ አስተዳደሮችና የፀጥታ መዋቅሮች ጋር በቅንጅት መሥራት ይጠበቅበታል፤›› ብለዋል፡፡