በአገራችን የሕክምና ሙያ ጥፋቶች እየተደጋገሙ ስለሆነ መላ ሊፈለግላቸው ይገባል!

በኢዮቤድ ጥበቡ ልሳነወርቅ

          በዘውዲቱ ሆስፒታል የእንቅርት ታካሚዋ ለሐሞት ከረጢት ጠጠር ሆዷ በቀዶ ጥገና መከፈቱን በተመለከተ አስደናቂ ዜና ተዘግቧል፡፡ የሕክምና ሙያ ጥፋቱን የፈጸሙት ሐኪም ከሥራ መታገዳቸውን፣ ተጎጂዋ በሽተኛም  "የሐሞት ጠጠሩ በነፃ ስለወጣልሽ ዕድለኛ ነሽ" መባሏ ጭምር ተሰምቷል፡፡ የእንቅርት ታካሚዋና የሐሞት ጠጠር ታካሚዋ በቅደም ተከተል "ሰላም ደሞዜ" እና  "ሰላም ኪሮስ" ይባላሉ፡፡ ሁለቱም ታካሚዎች ለየግል ሕክምናቸው ከሆስፒታሉ የተገኙት የወረፋ ቀጠሮ  ስለደረሳቸው ከሕመማቸው የሚፈውሳቸውን ሕክምና ለማግኘት ብለው ነው፡፡ በስም መመሳሰል የእንቅርት ታካሚዋ የሰላም ደሞዜ ሆድ በስህተት በቀዶ ጥገና ሕክምና ተከፍቷል፡፡ በስህተት ያልጠበቀችውና ያልተዘጋጀችበት ቀዶ ጥገና ሲደረግላት በሕይወቷ ላይ ከፍተኛ አደጋ ሊያጋጥማት ይችል እንደነበር ግልጽ ነው፡፡

የኢቢሲ ዜና አገልግሎት ለተጎጂ ግለሰቧና ለሆስፒታሉ ኃላፊዎች ቃለ መጠይቅ  ሲያደርግላቸው በቴሌቪዥን መስኮት ተመልክተናል፡፡ በቃለ መጠይቁ ሆስፒታሉ የሚያስተዳድራቸው ሐኪሞች በሕክምና አፈጻጸማቸው ላይ ጥፋት ከሠሩ በእነሱ ድርጊት ሆስፒታሉም የፍትሐ ብሔር ኃላፊነት ያለበት መሆኑን ሳይገልጽ፣ ጥፋቱ የተፈጸመው በዋናው ሐኪምና በረዳቶቻቸው ጥንቃቄ ጉድለት መሆኑን ብቻ ገልጾአል፡፡ ትልቁንም ጥፋት የፈጸሙት የቀዶ ጥገና ሐኪሙ ስለሆኑ ከሥራና ከደመወዝ ማገዱን፣ የተጎጂዋን በሽተኛ ጤንነት እየተከታተለ እንዳስፈላጊነቱ በነፃ ሕክምና ይሰጣታል ሲል ሆስፒታሉ በተጨማሪ ገልጾአል፡፡

የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ በዚህ ጉዳይ ላይ ብዕሩን ሊያነሳ የቻለበት ምክንያት   ስለጉዳት ሥጋትና መድን ግንዛቤ ለኅብረተሰቡ የሚያስጨብጥ መጽሐፍ በአማርኛ ሲያዘጋጅ ባደረጋቸው ጥናቶችና ምርምሮች፣ በአገራችንም ሆነ በውጭ አገሮች በሕክምና ሙያ ላይ በተደጋጋሚ የተፈጸሙ ጥፋቶችን መዝግቦ በመያዙ ነው፡፡  በዚህ አጋጣሚ ለአብነት ያህል ጥቂቶቹ በዚህ ጽሑፍ ይነሳሉ፡፡ በእግረ መንገድም ሆስፒታሎች በማወቅም ሆነ ባለማወቅ በሕክምና ሙያ ጥፋት ኃላፊነቱ እንደሚመለከታቸው   ለሕዝብ ሳይገልጹ የሚሰጧቸው አስተያየቶች ትክክል እንዳልሆኑ እውነታውን ሕዝብ እንዲገነዘበው ይደረጋል፡፡

ባለሙያዎችን ቀጥሮ የሚያሠራ ሆስፒታል/የሕክምና ተቋም እንደ ጲላጦስ እጁን ታጥቦ ከደሙ ንፁህ ነኝ ሊል አይችልም፡፡ ሕሙማን ከአንድ የሕክምና ባለሙያ ወይም ሆስፒታል/የሕክምና ተቋም ጋር ከሕመማቸው ለመፈወስ ሲሉ የሚፈጥሩት ግንኙነት በ1952 ዓ.ም. የፍትሐ ብሔር ሕግ መሠረት ውል ነው፡፡ አንቀጽ 2641 ይህንኑ እንደሚከተለው ይደነግጋል፡፡

አንቀጽ 2641 የሆስፒታል ውል ትርጓሜ፡፡

የሆስፒታል ውል ማለት አንድ የሆስፒታሉ መሥሪያ ቤት ስለአንድ የታወቀ በሽታ ብዙ ሐኪሞች አንድ ሆኖ ለአንድ ሰው የሕክምና ሥራዎች ሊያደርግለት የሚደረግ ውል ነው"፡፡ የዚህ ድንጋጌ እንግሊዘኛው ትርጉም፡ "Definition of contract of hospitalization. A contract of hospitalization is a contract whereby a medical institution undertakes to provide a person with medical care from one or several physicians in connection with a given illness!"

          ሕዝብ የሕክምና ባለሙያዎችን ምጡቅ የኅብረተሰብ አባላት (the smartest members of society) አድርጎ እንደሚመለከታቸው ግልጽ ነው፡፡ አመለካከቱ  ያለምክንያት የተፈጠረ አይደለም፡፡ አንድ ሐኪም ጥሩ ሐኪም ሆኖ የሚመረቀው በረጅም ጊዜ የትምህርትና የሥልጠና ጥረቱና ድካሙ ብቁ ሐኪም ስለመሆኑም በምዘና ተረጋግጦለት ነው፡፡ በሥራ ዓለምም ከተሰማራ በኋላ ሙያውን በተከታታይ ሥልጠና፣ በአዳዲስ ክህሎቶችና ቴክኖሎጂዎች እውቀቱን ለማዳበርና ለማዘመን ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ ብቃቱን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻሻለ ስለሚሄድ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ሐኪሞች ሰው እንጂ  መለኮታዊ ባህሪ የላቸውም፡፡ እንደ ማንኛውም ሰው በስህተት ወይም በቸልተኝነት በሕክምና ሥራቸው ላይ ማድረግ የሚገባቸውን ባለማድረግ ወይም ማድረግ የማይገባቸውን በማድረግ ስህተቶችን ሊፈጽሙ ይችላሉ፡፡

የዚህ አጭር ጽሑፍ ዓላማ በጥፋት ላይ ስለተመሠረተ ኃላፊነት የፍትሐ ብሔር ድንጋጌዎችን ለማንሳትና በዓለም ላይ በሌሎች አገሮች እንደሚሠራበት ሁሉ፣ ለአገራችን ባለሙያዎችም "የሙያ ሕጋዊ ኃላፊነት መድን ዋስትና" (Professional Indemnity/Liability Insurance) ለባለሙያውም ሆነ ለተጎጂው ወገን አለኝታ ሆኖ ሊያገልግል እንደሚችል አንድ ሁነኛ መላ ለመጠቆም ነው፡፡ ስለአጠቃላይ ጥፋት በፍትሐ ብሔር ሕጉ የተደነገጉ ሁለት አናቅጽት አሉ፡፡

አንቀጽ 2028 ጠቅላላ መሠረት

ማንኛውም ሰው ከራሱ ጥፋት የተነሳ በሌላ ሰው ላይ ጉዳት ካደረሰ ላደረገው ጥፋት ኪሳራ መክፈል አለበት (Who so ever causes damage to another by an offense shall make it good)"፡፡

አንቀጽ 2029  የጥፋት ልዩ ልዩነት

(1) አስቦ ወይም በቸልተኝነት በሚሠራ ተግባር ጥፋት ሊደረግ ይችላል፣

(2) እንዲሁም አንድ ተግባርን መፈጸም ወይም ተግባርን አለመፈጸም ጥፋት ሊሆን ይችላል የሚሉ ናቸው፡፡

(የዚህ አንቀጽ ርዕስ የእንግሊዝኛ ትርጉም "Types of Offence" ነው፡፡ ምናልባት የአማርኛው ርዕስ የአጻጻፍ ግድፈት ይኖርበት ይሆን በማለት ጸሐፊው ከመጽሐፉ መጨረሻ ላይ እርማት ቢፈልግ አላገኘም፡፡ ስለዚህ አባባሉን ከእንግሊዝኛው ትርጉም አንፃር አንባቢ እንዲረዳው ያስፈልጋል)

ስለሕክምናና ስለሆስፒታል ውል በፍትሐ ብሔር ሕጉ ከአንቀጽ 2639 እስከ 2652 ዝርዝር ነገሮች ተደንግገዋል፡፡ ሁሉንም በጋዜጣ ዓምድ ላይ መዘርዘር ስለማይቻል፣ ከእነዚያ መካከል በተለይ ሁለቱን አናቅጽት ብቻ ለግንዛቤ እንዲበጅ ይጠቀሳሉ፡፡

"አንቀጽ 2651 ስለ ሆስፒታሉ መሥሪያ ቤት ኃላፊነትና ስለሕክምናው አፈጻጸም፡፡ በሐኪሞች ወይም እነሱ ባሰማሩዋቸው ረዳት ሠራተኞች ጥፋት በበሽተኛው ላይ ለደረሰው ጉዳት የሆስፒታሉ መሥሪያ ቤት በፍትሐ ብሔር ረገድ ኃላፊ ነው"፡፡ (Liability of medical institutions. 1. Medical Treatment. The medical institution shall be civilly liable for the damage caused to a sick person by the fault of the physician or auxiliary staff, which it employs).

አንቀጽ 2652 ስለሆቴሉ ሥራ አፈጻጸም ጥንቃቄ

በሽተኛው ስለሕክምናው ጥቅም በማለት በሆስፒታሉ ውስጥ የተመገበና የተቀመጠ እንደሆነ ስለዚሁ መቀመጥና ስለዚሁ መመገብ ኃላፊነቱንና ግዴታዎቹን የሚመለከት የሆቴል ሥራን ውል በሚመሩት በዚህ ሕግ ደንቦች ጽሑፎች መሠረት ተፈጻሚ ይሆናሉ (ከአንቀጽ 2653 እስከ 2671 ተመልከት)፡፡ (Board and lodging. Where the sick person, for the purpose of his treatment, is lodged and fed by the medical institution, such institution shall, as regards its obligations and responsibility arising from loging and feeding, be subject to the provisions regarding to innkeepers’ contracts፡ Art. 2653-2671). (የአማርኛው ርዕስ አጻጻፍ "ስለሆቴሉ ሥራ አፈጻጸም ጥንቃቄ" የሚለው ከእንግሊዝኛው ትርጉም አንፃር "ስለሆስፒታሉ ሥራ አፈጻጸም ጥንቃቄ" ማለቱ እንደሆነ ልብ ይሏል፡፡)

በዚህ ድንጋጌ መሠረት አንድ ሕመምተኛ በሆስፒታል ውስጥ ተኝቶ በሚታከምበት ጊዜ የመኝታ ምቾቱና አመጋገቡ የሆቴል ሥራ በሚመራበት ደንብና ሥርዓት ተፈጻሚ መሆን እንዳለበት የፍትሐ ብሔር ሕጉ ደንግጓል፡፡

እ.ኤ.አ. በጥር ወር 2015 በወጣው ኢትዮጵያ የሜዲካል መጽሔት (Ethiopian Medical Journal) ላይ የኢትዮጵያ ጤና ባለሙያዎች ሥነ ምግባር ፌዴራል ኮሚቴ (Health Professionals Ethics Federal Committee of Ethiopia) እ.ኤ.አ ከጥር 2011 እስከ ታኅሳስ 2013 ባቀረበው የሦስት ዓመት ሪፖርት በሕክምና ሙያ ላይ ከቀረቡት አቤቱታዎች መካከል 23.3 በመቶ ያህሉ በትክክል ጥፋት ሆነው መረጋገጣቸውን፣ 76.7 በመቶ ያህሉ አቤቱታዎች በትክክል ጥፋት ሆነው እንዳላገኛቸው ተገልጾአል፡፡ ኮሚቴውም ሆስፒታሎች ሕሙማን ላይ ጉዳት እንዳይደርስ በማድረግ ረገድ ግንባር ቀደም ሚና ያለባቸው መሆኑን እንዲሁም ለኦብስቴትሪስ፣ ለጋይናኮሎጂ፣ ለጄኔራልና ለኦርቶፔዲክስ ቀዶ ጥገና ሐኪሞች ስለሕክምና ሙያ ስህተቶች ማነቃቂያ ሥራ እንደሚያስፈልግ (Creation of more awareness) ወደ እነዚህ ሙያዎች ለሚገቡትም ልዩ ሥልጠና እንደሚያስፈልጋቸው ምክሩን ለግሷል፡፡

ስለ ልዩ ሙያ የፍትሐ ብሔር ሕጉ የሚከተለውን ይደነግጋል፡፡ 

አንቀጽ 2031 በሙያ ሥራ ስለሚደረግ ጥፋት

(1) በልዩ ሙያው አንድ ሥራ የሚፈጽም ሰው ወይም በዚህ በሙያው የሥራ ተግባሩን የሚያካሂድ ሰው፣ የዚሁ የሙያ ሥራው የሚመራበትን ደንብ መጠበቅ ይገባዋል፡፡

(2) በሥነ ጥበብ ወይም ራሱ በሚሠራው ኪነ ጥበብ ደንቦች መሠረት ያሉበትን ግዴታዎች አለመከተሉ ሲገለጽ ባለመንጠንቀቅ ወይም በቸልተኝነት ጥፋተኛ ሆኖ በተገኘ ጊዜ ኃላፊ ይሆናል፡፡

ባለሙያዎች እነማን ናቸው? ለሚለው ጥያቄ ከላይ የተጠቀሰው ድንጋጌ መልስ ይሰጠናል፡፡ በዚሁ ድንጋጌ ንዑስ አንቀጽ (1) መሠረት በቅድሚያ በሙያው አስፈላጊውን እውቀት፣ ልዩ ልምድና ሥልጠና (special skills, experience and knowledge) አግኝቶ የሙያ ተግባሩ የሚመራበትን ደንብና ሥርዓት ጠብቆ መሥራት ያለበት ሰው ባለሙያ ነው፡፡ የሙያ ሥራው የሚመራበትን ደንብና ሥርዓት ሳይጠብቅ በስህተት ወይም በቸልተኝነት ለፈጸመው የሙያ ስህተት ጥፋተኛ ይሆናል፡፡ ንዑስ አንቀጽ (2) ደግሞ በሥነ ጥበብ ወይም ራሱ በሚሠራው ኪነ ጥበብ መሠረት ያሉበትን ግዴታዎች ሳይጠብቅ ተገቢውን ጥንቃቄ አጉድሎ በቸልተኝነት ለሚሠራው የሙያ ተግባር ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ ኃላፊ መሆኑን ሰይገልጻል፡፡

ስለዚህ ልዩ ልዩ የሙያ ተግባራትን የሚያከናውኑ የሙያ ተቋማትና ባለሙያ ሰዎች፣ ለምሳሌ ሆስፒታሎች፣ ሐኪሞች፣ ነርሶች፣ ፋርማሲስቶች፣ አዋላጆች፣ ኢንጂነሮች፣ አርኪቴክቶች፣ የሕግ አማካሪዎች፣ ጠበቆች፣ አካውንታንቶች፣ ኦዲተሮች/ሒሳብ መርማሪዎች፣ የፋይናንስ፣ የማኔጅመንትና ሌሎች አማካሪዎች፣ "የውስጥ አስዋቢዎች" (Internal Decorators)፣ ወዘተ ባለሙያዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ባለሙያዎች ከላይ እንደተመለከተው ተግባራቸውን ሲያከናውኑ የሙያቸውን ደንብና ሥርዓት እንዲሁም አግባብነት ያላቸውን ሕግጋት ሳይከተሉ በቸልተኝነት ለፈጸሙት ጥፋት፣ የፍትሐ ብሔር ኃላፊነት ስላለባቸው ጉዳት ለደረሰባቸው  ወገኖች ተገቢውን የጉዳት ካሳ የመክፈል ግዴታ አለባቸው፡፡

በሪፖርተር ጋዜጣ ቅጽ 21 ቁ. ጥር1677 ግንቦት 17 ቀን 2008 "ምን እየሠሩ ነው?" በሚለው ዓምድ የኢትዮጵያ የግሉ ዘርፍ ሐኪሞች ማኅበር ፕሬዚዳንት በሰጡት ቃለ ምልልስ "አንድ ሐኪም የሕክምና ስህተት ሠራ ተብሎ እጁ ላይ ካቴና ማስገባት ተገቢ አይመስለኝም" ሲሉ የሰጡት አስተያየት አነጋጋሪ ይመስላል፡፡ ፕሬዚዳንቱ አባባላቸውን በደንብ ስላላብራሩት ከፍትሐ ብሔር ወይም ከወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ አንፃር አስተያየት ለመስጠት ይቸግራል፡፡

ይሁን እንጂ ስለሙያ ሕጋዊ ኃላፊነት መድን አንዳንድ ነጥቦችን ከማንሳታችን በፊት፣ በዚህ ጽሑፍ መጀመሪያ ላይ የተገለጸውን ዓይነት የሕክምና ሙያ ጥፋቶች መደጋገማቸው አሌ አይባልም፡፡ ለአብነት ያህል በአገራችን የተከሰቱትን ሁለት  የሕክምና ሙያ ጥፋቶችን፣ እንዲሁም አንድ በውጭ አገር የተከሰተን የሙያ ጥፋት በዚህ ጽሑፍ ላይ ማንሳት የጉዳዩን አሳሳቢነት ሊያጎላው እንደሚችል ጸሐፊው  ያምናል፡፡ የተጠቀሱት የሕክምና ሙያ ጥፋቶች ልብ ወለድ ሳይሆኑ በእውነት የተፈጸሙና በመገናኛ ብዙኃንም በወቅቱ ለሕዝብ የተገለጹ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ የተፈጸሙት ጥፋቶች ቀደም ብለው የተፈጸሙ በመሆናቸው  ፈጻሚዎቹን ሆስፒታሎች በዚህ ጽሑፍ በስም መጥቀስ አላስፈለገም፡፡

"የመሬዋ ልጃገረድ"      

          ከወደ መራቤቴ አንዲት ልጃገረድ ለሕክምና ወደ አዲስ አበባ ትመጣና ከአንድ ታዋቂ ሆስፒታል ውስጥ የማህፀን ሕክምና ትጀምራለች፡፡ የማህፀን ሐኪሙ ተገቢውን ምርመራ ካደረገላት በኋላ "የማህፀን ደጃፍ ፈሳሽ" (Vaginal Smear) ናሙና ተወስዶ በላብራቶሪ እንዲመረመር ያዛል፡፡ የማህፀን ሐኪሙ ረዳት ወይም በዜናው ድሬሰር የተባለው ባለሙያ ናሙናውን በሚወስድበት ጊዜ ያላግባብ የልጅቷን ስሱ ገላ ስለጠነቆለባት ክፉኛ ስትጮህ ሐኪሞች ተረባርበው ሲመረምሯት ክብረ ንጽፅህናዋ ላይ ጉዳት እንደደረሰባትና በዚህ ምክንያትም ደም እንደፈሰሳት ተገልጾ የመጀመሪያ ዕርዳታ ያደርጉላታል፡፡ ጉዳቱን ያደረሰባት መጀመሪያ ካያት ሐኪም ቀጥሎ ከማህፀኗ ናሙናውን የወሰደው ረዳት ባለሙያ መሆኑን፣ እርሱም ከሥራ ታግዶ የገንዘብ ቅጣት እንደተወሰነበት የሆስፒታሉ የወቅቱ ሜዲካል ዳይሬክተር የነበሩት በቴሌቪዥን በተደረገላቸው ቃለ መጠይቅ ገልጸዋል፡፡ ሆስፒታሉና ምርምራውን ያካሄዱት ባለሙያዎች ልጅቷ ለደረሰባት የሕክምና አገልግሎት የሕክምና ሙያ ጥፋት ተጠያቂ መሆናቸው አያከራክርም፡፡ እንደዚያ ባለው ስስ ገላ ላይ የምርመራ ሒደቱን በጥንቃቄ መፈጸም የነበረበት ዋና ሐኪሙ ራሱ ነው ወይስ ረዳቱ  የሚል ጥያቄም በጊዜውም ተነስቷል፡፡ ጉዳዩ ፖሊስ እጅ እንደደረሰና ከዚያ በኋላ የተደረሰበትን ውጤት በተመለከተ በቂ ማስረጃ ማግኘት አልተቻለም፡፡ ቁም ነገሩ ኅብረተሰቡ በሌሎች ሰዎች ጥፋት ጉዳት ሲደርስበት እንደ ቀድሞው "የአርባ ቀን ዕድሌ ነው፣ መቼስ ምን ይደረጋል?" ብሎ በአርምሞ የሚተወው ነገር እንዳልሆነ የመሬዋ ልጃገረድ አረጋግጣለች፡፡

የሞተው ሾፌር

          በደርግ ጊዜ የነበረውን የቀበሌ መጠሪያ ስም ጸሐፊው ማስታወስ ቢቸግረውም፣ አካባቢው በዛሬው ስሙ የየካ ክፍለ ከተማ ከእንግሊዝ ኤምባሲ ጀርባ ከፍ ብሎ ባለው ዳገታማ ቦታ በዘልማድ "ብቅ እንቅ" ከሚባለው ሰፈር፣ አንድ የአዕምሮ ሕመም የነበረበት ሰው ዘጠኝ ልጆቹን፣ ባለቤቱንና እሱን ጨምሮ አሥራ አንድ ቤተሰብ በከባድ መኪና ሾፌርነት ሙያ ያስተዳድር ነበር፡፡ ሕመሙ ሲነሳበት ወደ ተለመደው ሆስፒታል ሄዶ ይታከምና ሲሻለው ወደ ሥራው ይሰማራል፡፡

ከዕለታት አንድ ቀን አዘውትሮ ይታከምበት የነበረው ሆስፒታል ለቀበሌ ስልክ ይደውልና "አቶ እገሌ ሞቷልና ቤተሰቡ መጥቶ አስከሬኑን ይውሰድ" ብሎ መርዶ ይነግራል፡፡ ሞቷል የተባለውም ሰው በሠፈሩ በመልካም ባህሪው የሚታወቅ፣ ሰው አክባሪና ደግ ስለነበረ የቀበሌው ሰዎች በጣም ተደናግጠው ለሠፈሩ ዕድር ዳኞች ይነግራሉ፡፡ መርዶውን የሰሙ ጎረቤቶች ሁሉ ሟች ሾፌር ቤት ይሄዱና ባለቤቱን "ወ/ሮ እገሊት ተነሽ፣ ልበሽ፣ አቶ እገሌ ሕመሙ ፀንቶበታል ተብሎ ከሆስፒታል ተደውሏልና ሄደን እንየው፤" ብለው ይነግሯታል፡፡ ሴትዮዋም በጣም ተደናግጣ፣ "እንዴ ምንድንው የምትሉት? እሱኮ ድኖ ከሆስፒታል ወጥቶ ወደ ሥራው ተመልሷል፡፡ ክፍለ ሀገር ከሄደ አንድ ወር ሊሞላው ነው፤" ብላ መልስ ብትሰጥም፣ "አይ ብቻ ተነሽ ልበሽ" ባዩ ስለበዛባትና በድንጋጤም ስለተዋከበች በሠፈር ሰዎች ታጅባ ሆስፒታሉ ዘንድ ትደርሳለች፡፡

የሆስፒታሉም ሰዎች እሷንና አጃቢዎቿን ወደ አስከሬን ማቆያ ክፍል ይወስዷቸውና አስከሬኑን ያሳዩዋቸዋል፡፡ ሞተ የተባለው ሰው ሚስት አስከሬኑን አይታ "እንዴ ይኼ እኮ እሱ አይደለም ምነው ጠቆረብኝ?" ትላለች፡፡  "ሴትዮ ሬሳ ሲቆይ ይጠቁራል ብትወስጂ ውሰጂ አለበለዚያ ማዘጋጃ ቤት ወስዶ እንዲቀብረው እናደርጋለን፤" የሚል ኃይለ ቃል ከሆስፒታሉ ሠራተኞች ይሰነዘርባታል፡፡ አጃቢ ሠፈርተኞችም  በሁኔታው ግራ ቢጋቡም አስከሬኑ ከቆየ ይበልጥ ይበላሻል በሚል ፍራቻና ድንጋጤ  በሳጥን አድርገው አስከሬኑን ሠፈር ያደርሳሉ፡፡ ከዚያም ሟች አቶ እገሌን ቤተ ዘመዱ፣ ልጆቹና ወዳጆቹ እንባ በእንባ እየተራጩ የካ ደብረ ሳህል ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ወስደው ይቀብሩታል፡፡

          ሞተ ተብሎ የተቀበረው ሾፌር አቶ እገሌ በ12ኛ ቀኑ ለተቃረበው የዘመን መለወጫ ቅዱስ ዮሐንስ ዓመት በዓል መዋያ የሚሆኑ ዶሮዎች፣ ቅቤ፣ ከሰል፣ ለልጆቹም ሸንኮራ አገዳውን፣ ወዘተ ይዞ ገና ሲነጋጋ ከቤቱ ከች ይላል፡፡ ዘመዶቹና ልጆቹ ከፍራሽ ላይ ሳሎን ተኝተው ሲያገኛቸው በጣም ደንገጦ፣ "ማነው የሞተው ንገሩኝ ማነው የሞተብኝ ልጅ፤" ብሎ ራሱን ይዞ እዬዬ በማለት መጮህ ይጀምራል፡፡  "ኧረ! አንተ ነህ ሞትክ የተባልከውና የተቀበርከው፤" ቢሉትም አልሰማ ብሎ ጩኸቱን ይቀጥላል፡፡ በስንት ሆይ ሆይታ ለቅሶውም ይቆምና ግርግሩም ይረግብና ‘እግዘአብሔር ያጥናሽ’ ያላት የሠፈር ሰውና ወዳጅ ዘመድ ሁሉ በአግራሞት ቀኑን ሙሉ እየመጣ ‘እንኳን ደሽ ያለሽ’ ይላት ገባ፡፡

          የኋላ ኋላ ጉዳዩ አደባባይ የወጣው ዕድሩ ለሴትዮዋ የከፈላትን ብር 300 መልሽ በማለቱ ነው እንጂ፣ ይኼንን የሚያህል ትልቅ በደል በአንድ ቤተሰብ ላይ ደርሶ  "ጉድ አንድ ሰሞን ነው" እንዲሉ የሠፈር ወሬ ከመሆን አያልፍም ነበር፡፡ ‘የበላሽውን ብር መልሽ’፣ ‘አልመልስም’ የሚል ትልቅ ወዝግብ በዕድሩና በሴትዮዋ መካከል ይነሳል፡፡ በተነሳው ውዝግብም ከፊሉ ሰው ሴትዮዋ ባልዋ ባይሞትም ሞተ ተብሎ በምትኩ የሌላ ሰው ቀብር መፈጸሙና ቤተሰቡም በስህተት በመጣ እክል ተሰቃይቷልና ሴትዮዋ ገንዘቡን መመለስ አይገባትም ሲል፣ ከፊሉ ደግሞ የዕድሩ ገንዘብ እንዴት ሊወራረድ ነው? የሕዝብ ገንዘብ ስለሆነ መመለስ አለባት ይላል፡፡

በዚህ ምስኪን ቤተሰብ ላይ ያን ያህል ጉዳት ከደረሰ በኋላ ከዕድሩ የተከፈላትን ገንዘብ መልሽ መባሏ አግባብ ነው? አይደለም? በሚል በተነሳው ውዝግብ መካከል "ይህ ሁሉ ነገር የደረሰው በማን ጥፋት ነው?" ለሚለው ጥያቄ መልስ ለማግኘት ጥረት የሚያደርጉ የሠፈር ሽማግሌዎችና የዕድሩ ዳኞች ከሴትዮዋ ጋር ሄደው ሆስፒታሉን ለመጠየቅ ይስማማሉ፡፡

"የመጣነው ከዚህ ቀበሌና ዕድር ነው፡፡ በዚህ ቀን በስህተት የዕድራችን አባል የሆነ እገሌ የተባለ ሰው ሞተ ብላችሁ ስልክ ደውላችሁልን ከሬሳ ማቆያ ቦታ ገብተን ስናየው እሱ ለመሆኑ ጥርጣሬ ቢገባንም፣ እዚህ ቆይቶ ሬሳው ከሚበላሽ ብለን ወስደን ቀብረን በኋላ ሞተ የተባለው የዕድራችን አባል ደህና ሆኖ ተገኘ፡፡ ዛሬ የመጣነው ሳይሞት ሞተ የተባለውን የዕድርተኛችን ጉዳይ ለማጣራት ነው፤" በማለት  የዕድሩ ተወካዮች የመጡበትን ጉዳይ ዘርዝረው ለሆስፒታሉ ኃላፊዎች ያስረዳሉ፡፡ የሆስፒታሉ አስተዳደርም "ሲደወልላችሁ መጥታችሁ አስከሬኑን በዓይናችሁ አይታችሁ የእኛ ነው ብላችሁ ወስዳችኋል፡፡ ከዚህ ውጪ እኛ የምናውቀው ነገር የለም፤"  በማለት ቁርጥ ያለ መልስ ይሰጣቸዋል፡፡

          ‘ይህ አስደናቂ ነገር መጀመሪያውኑ እንዴት ሊከሰት ቻለ?’ ተብሎ ነገሩ ሲጣራ እንደተደረሰበት ሞተ የተባለው የሴትዮዋ ባል የተኛበት አልጋ ካርድ ሳይለወጥ ሌላ በድንገት ታሞ የመጣ በሽተኛ ተኝቶ ሲታከም ይቆይና ይሞታል፡፡ ለቀበሌውም አስከሬን ውሰዱ ተብሎ ከሆስፒታሉ የተደወለው በእውነተኛው ሟች አድራሻ ሳይሆን፣ ከእሱ በፊት ተኝቶ ድኖ በወጣው ሾፌር ካርድ ላይ ከተገኘው የቀበሌ ስልክ አድራሻ ነበር፡፡ ጉዳዩ ፖሊስ እጅ የደረሰ ቢሆንም በእውነት የሞተውን ሰው ማንነት ፖሊስ ስለማጣራቱ ወይም በአካራካሪው ነጥብ ላይ የተሰጠ ውሳኔ ስለመኖሩ የተገኘ ተጨማሪ ማስረጃ የለም፡፡ ጉዳዩ በዚያው ተድበስብሶ የቀረ ይመስላል፡፡ ሞተ በተባለው ሾፌር ቤተሰብ ላይ የደረሰው "የአካልና የሞራል ጉዳት፣ እንዲሁም የገንዘብ ኪሳራ" በጣም ከፍተኛ መሆኑ አይካድም፡፡

ከላይ በጠቀስናቸው ሕግጋት መሠረት እነዚህ ጉዳዮች ከፍርድ ቤት ቢደርሱ ለተጎጂ ወገኖች የጉዳት ካሳ ሊከፈላቸው እንደሚችል አያጠራጥርም፡፡ ድርጊቶቹ የተከሰቱት በአደጉት አገሮች፣ በተለይም በአገረ አሜሪካ ቢሆን ኖሮ በሕክምና ሙያ ጥፋት ሕጋዊ ኃላፊነት ሆስፒታሎቹና በውስጡ የሚሠሩ ሠራተኞች በሙያ ቸልተኝነት ተከስሰው ለተጎዱ ወገኖች በብዙ ሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ ካሳ በከፈሉ ነበር፡፡ የሕክምና ሙያ ጥፋት ለተጎጂው ወገን የጉዳት ካሳ በመክፈል ብቻ የሚወሰን ሳይሆን፣ እንደ ጥፋቱ ክብደት የሙያ ሥራ ፈቃድን ሊያስነጥቅ ይችላል፡፡

የአንጎል ቀዶ ጥገና (Brain Surgery)

የሕክምና ሙያ ስህተቶች የሚፈጸሙት በአገራችን ብቻ ሳይሆን በበለጸጉት አገሮች ሳይቀር እንደሚፈጸሙ ከላይ ገልጸናል፡፡  በአገረ አሜሪካ ሮድ አይላንድ ክፍለ ግዛት በታዋቂውና የሐኪሞች ማሠልጠኛ በሆነው ሮድ አይላንድ ሆስፒታል ውስጥ፣ በአንድ ዓመት ሦስት ያህል የአንጎል ቀዶ ጥገና ስህተቶች ተፈጽመዋል፡፡ የመጀመሪያው  ስህተት የግራ ጎኑን የአንጎል ክፍል በቀዶ ጥገና ለመክፈት ታስቦ በስህተት የቀኙን  የአንጎል ክፍል ሐኪሞቹ ከፍተውታል፡፡ ስህተቱ ሲመረመር ቀዳጅ ሐኪሞቹም ሆኑ ነርሶቹ የሥራ ቅደም ተከተል ማጣሪያ ዝርዝር (Checklist) አጠቃቀም ሥልጠና እንደሌላቸው ታውቋል፡፡ በቀዶ ጥገና ሥራ አፈጻጸም ይቅርና ከግሮሰሪ ዕቃዎችን ለመግዛት አንኳን የዕቃዎች ዝርዝር በቅድሚያ ማዘጋጀት ወሳኝነቱ አይስተባበልም፡፡

የሙያ ሕጋዊ ኃላፊነት መድን

ባለሙያ ግለሰቦች/ቡድኖች ወይም የሙያ ሥራ የሚሠሩ ተቋማት በሙያቸው አግባብ ሥራ በሚሠሩበት ወይም አገልግሎት በሚሰጡበት ጊዜ "ስህተቶች" (Errors)፣ ወይም "ግድፈቶች" (Omissions) በቸልተኝነት ፈጽመው ሲገኙና ጥፋታቸውም በሰዎች ላይ ጉዳት ካደረሰ፣ የድርጊቱ ፈጻሚ ባለሙያዎች በሕግ ተጠያቂዎች እንደሚሆኑ ከላይ ተገልጾአል፡፡ አጥፊዎቹ በፍርድ ቤት ተከሰው ለተጎጂው ወገን ካሳ መክፈል ግዴታቸው ነው፡፡ ለዚህ ዓይነቱ የጉዳት ሥጋት ተጋላጭነት (Exposure to Risk) ለባለሙያዎቹ አለኝታ ሆኖ ሊያገለግላቸው የሚችለው የመድን ዋስትና ዓይነት "የሙያ ሕጋዊ ኃላፊነት መድን ዋስትና ውል" ነው፡፡ ዋስትናው ለተጎጂው ወገን የሚከፈለውን ካሳ መክፈል ብቻ ሳይሆን ክስን ለመከላከል የሚወጣውን ወጪ ጭምር ይሸፍናል፡፡ በተለይ በአሜሪካ ይህ ዓይነቱ የመድን ውል "የስህተቶችና ግድፈቶች መድን ውል" (Errors and Omissions Insurance) በሚል ስያሜ ይታወቃል፡፡

ልዩ ልዩ የሙያ ሕጋዊ ኃላፊነት መድን ዋስትና ውሎች አሉ፡፡ እንደ ባለሙያው ፍላጎትና እንደሚሰጠውም የሙያ አገልግሎት ዓይነት ውሉን መድን ሰጪው ለደንበኛው እንደሚስማማው አድርጎ ሊቀርፅለት ይችላል፡፡ አንዳንድ በውጭ አገሮች የሚገኙ  የመድን ሰጪዎች  የሙያ ሕጋዊ ኃላፊነት መድን ውል በተከታታይ የሚታደስ ከሆነ፣  በቀደመው የውል ዘመን የቀረቡ የጉዳት ካሳ ጥያቄዎችን ጭምር በመሸፈን ለመድን ገቢዎች ጥቅም ይሰጣሉ፡፡ የሙያ ሕጋዊ ኃላፊነት መድን ዋስትናን ተመሳሳይ ሙያ ያላቸው ሰዎች በቡድን አንድ ላይ ሆነው ሲገዙት የዓረቦን ቅናሽ ያስገኝላቸዋል፡፡

የሙያ ሕጋዊ ኃላፊነት መድን ውል የገንዘብ መጠን  ወሰን (Professional Liability Policy Limit)

የሕጋዊ ኃላፊነት መድን ውል የኃላፊነት መጠን ወሰን  አለው፡፡ የውል ኃላፊነት መጠን ወሰን ምን ማለት ነው? በተለይ በሕጋዊ ኃላፊነት መድን ውሎች የኃላፊነት መጠን ወሰን ሲባል "መድን ሰጪው በአንድ የውል ዘመን ውስጥ ለጉዳት ካሳ ለመክፈል የተስማማው ከፍተኛ የገንዘብ ካሳ ኃላፊነት መጠን ወሰን" ማለት ነው (Indemnity or policy limit is the maximum amount that an insurer will pay out for any one claim and usually within any one-policy year (assuming a yearly insurance policy)፡፡

ስለሆነም እንደ ሙያ ሕጋዊ ኃላፊነት መድን ውል "የካሳ ገንዘብ ኃላፊነት መጠን ወሰን" ያላቸው የሕጋዊ ኃላፊነት የመድን ዋስትና  ዓይነቶች፡

  • "የምርት ሕጋዊ ኃላፊነት መድን" (Products Liability)፤
  • "የሕዝብ ሕጋዊ ኃላፊነት መድን" (Public Liability) እና
  • "የሠራተኞች ጉዳት ሕጋዊ ኃላፊነት መድን" (Workers’ Compensation/Employers Liability/Indemnity insurance) ለአብነት ይጠቀሳሉ፡፡

ከሌሎች የመድን ዋስትናዎች መግቢያ ገንዘብ መጠን (Sum Insured) የሕጋዊ ኃላፊነት ገንዘብ መጠን ወሰን የሚለየው በእያንዳንዱ በደረሰ አደጋ ወሰን ወይም  በዓመቱ ጠቅላላ የኃላፊነት መጠን ወሰን መሠረት ሊገደብ ስለሚችል ነው፡፡ ስለዚህም የሌሎች የመድን ዋስትና ውሎች መድን ዋስትና ገንዘብ መጠን የሙያ ኃላፊነት መድን ውል ገንዘብ መጠን ወሰን አተማመን ለየት እንደሚል ልብ ሊባል ይገባል፡፡  የሚወሰነውም "በደረሰ አደጋ መጠን" (Any One Accident (AOA) Limit) ወይም "በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በደረሰ አደጋ መጠን" (Any One Year (AOY) Limit) ሊሆን ይችላል፡፡

"በደረሰ አደጋ መጠን" የኃላፊነት ገንዘብ ወሰን በውሉ ዘመን ውስጥ በደረሱ አደጋዎች ለእያንዳንዳቸው የሚከፈለውን "ከፍተኛ የገንዘብ መጠን" የሚወስን ነው፡፡ አወሳሰኑም የመድን ገቢውን የሙያ ሥራ ኃላፊነት በባለሙያው የሥራ አፈጻጸም ሊጎዱ የሚችሉትን የሰዎች ብዛትና የሚጠቀምባቸውን መሣሪያዎች ዓይነት ወይም ብልሽት በአንድነት ሊደርስ የሚችለውን ከፍተኛ የኃላፊነት ወሰን መጠን በቅድሚያ በማስላት ነው፡፡

የሚገርመው በታዳጊ አገሮች በተለይም በአገራችን የሚገኙ ባለሙያዎችና ተቋማት ለሙያ ግዴታቸው የሚሰጡት ትኩረት እጅግ አነስተኛ ነው፡፡ ሕዝብ ግን በጉዳዩ ላይ እያደር እየነቃ እንደሚሄድና ለደረሰበት ጉዳት ካሳ በሕግ አግባብ ጉዳት ፈጻሚውን እንደሚጠይቅ ሊታወቅ ይገባል፡፡

ስለዚህ "በሬ ሆይ ሣሩን አየህና ገደሉን ሳታይ" እንዳይሆን ባለሙያዎች የሆኑ ሰዎችና ተቋማት ሁሉ የሙያ ሕጋዊ ኃላፊነት መድን ዋስትና እንዲገዙ ይመከራሉ፡፡ በተለይ የሕክምና ባለሙያዎች ከሚሠሩበት ሆስፒታል ወይም ክሊኒክ ውጪ ለምሳሌ በድንገተኛ ዕርዳታ ወቅት የበጎ ሥነ ምግባር ግዴታቸውን ሲፈጽሙ ስህተት ሊያደርጉ ስለሚችሉ ሊጠነቀቁ ይገባል፡፡

ብዙ አገሮች በተለይ "የሕክምና ሙያ ሕጋዊ ኃላፊነት መድንን" እንደ "ሦስተኛ ወገን አስገዳጅ የተሽከርካሪ መድን ዋስትና" አስገዳጅ አድርገውታል፡፡ በእኛ አገርም ሊታሰብበት እንደሚገባ በተከታታይ የተከሰቱት የሕክምና ሙያ ጥፋቶች ህያው ምስክሮች ናቸው፡፡ አስገዳጅ አዋጁን ለመደንገግ ብዙ ሰዎች እስኪጎዱ መጠበቅ የለበትም።

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው [BA, LLB (GD), Post Graduate Dipl. in Development Administration (India), ACII, Chartered Insurer (UK), ACS (USA)] ለረጅም ዓመታት በመድን ሥራ፣ በሥልጠና፣ በመድን ምርምርና ሥነ ጽሑፍ ልምድና ዕውቀት ያላቸው ናቸው፡፡ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው eyosono [at] gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡