ስለሚያረፍዱና ስለሚቀሩ ሠራተኞች

በአሠሪና ሠራተኛ ግንኙነት ለስንብት ምክንያት ከሚሆኑ ጉዳዮች መካከል ከሥራ ገበታ ላይ እያረፈዱ መገኘትና ከሥራ መቅረት የተለመዱት ናቸው፡፡ ከየዕለቱ ተሞክሯችን እንደምናስተውለው ሠራተኞች በተለያዩ ምክንያቶች ከሥራ ያረፍዳሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ የሥራ መግቢያ የሚባለው ሰዓት በተለምዶ (በተግባር ተሻሽሎ) ከ30 ደቂቃ እስከ አንድ ሰዓት እያረፈዱ ሲገቡ የማይሳቀቁ ሠራተኞችም አሉ፡፡

የሥራ ግንኙነቱን ባያሻክረውም ሠራተኛው በሰዓቱ እንዲገኝለትና ውጤታማ ሥራ እንዲሠራለት ለሚጠብቅ አሠሪ ማርፈድ እጅጉን አሳሳቢ ጉዳይ ነው፡፡ ሕጉ ማንኛውም ሠራተኛ በቀን ስምንት ሰዓት የመሥራት ግዴታን ሲጥል ሠራተኛው ሥራ ገበታው ላይ ከተገኘበት ሰዓት ጀምሮ ሥራውን አጠናቆ እስከሚሄድበት ሰዓት ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ሙሉ አግልግሎት እንዲሰጥ ነው፡፡ ይህማ ባይሆን ሰዓት መገደብ፣ የሥራ መጀመሪያውና መጨረሻውን ጊዜ መወሰን ባላስፈለገ ነበር፡፡ በዚህ ሰሞን በአንድ የግል ባንክ የሚሠራ ወዳጄ ቢሮ በሰዓቱ (ለመግቢያ በተወሰነው የሥራ ሰዓት) ገብቼ ጠረጴዛ መታቀፌ አሠሪውን አይጎዳውም በሚል ብሂል የሥራ ሰዓት አለማክበር በእርሱና በሥራ ባልደረቦቹ የተለመደ መሆኑን አጫወተኝ፡፡ ነገሩ ቢደንቀኝም ብዙኃኑ በሐሳቡ ሳይስማማበት አይቀርም፡፡ ለመሆኑ የሥራ ሰዓት ያለማክበር ውጤቱ በሕግ ምን ይመስላል? ከማርፈድ በዘለለ አንዳንድ ሠራተኞች ጭርሱኑ ከሥራ ገበታቸው በመቅረት ከአሠሪ ጋር አታካራ ውስጥ የሚገቡ አሉ፡፡ ከአሠሪው ፈቃድ ሳይኖረው ከሥራ ቦታው ያልተገኘ ሠራተኛ ጉዳይና ውጤቱ በሕጉ ምን ይመስላል? በዚህ ጽሑፍ እነዚህን ነጥቦች በአጭሩ ለመመልከት እንሞክራለን፡፡

መነሻ ጉዳዮች

ለዚህ ጽሑፍ መነሻ እንዲሆኑ ሁለት የሰበር ፍርዶችን መርጠናል፡፡ ፍርዶቹ ከሥራ መቅረት ጋር የተያያዙ ሲሆኑ፣ አሠሪው ሠራተኛው በመቅረቱ ከሥራ ያሰናበተበትና ሠራተኛው ስንብቱ ተገቢ አይደለም በማለት ፍርድ ቤት ክስ ያቀረበባቸው ናቸው፡፡

የመጀመርያው በ1999 ዓ.ም. ሠራተኛው ከድርጅቱ የዓመት ዕረፍት ፈቃድ ወስዷል፡፡ ዕረፍቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ግን ወደ ሥራው ሳይመለስ ይቀራል፡፡ ሠራተኛው ያቀረበው ምክንያት ዕረፍት ከወጣሁ በኋላ በድሬዳዋ ጎርፍ አደጋ የተጠቁ ዘመዶቼን ለመጠየቅ ሄጄ ነው ይላል፡፡ ሠራተኛው ይኼን ይበል እንጂ ፍርድ ቤት ይኼ ጉዳይ ተከስቶ በአስቸኳይ ስለመሄዱ እንኳ ያቀረበው ማስረጃ አለመኖሩ ተረጋግጧል፡፡ አሠሪው የሚያቀርበው ክርክር ደግሞ እንዲህ ዓይነት ጉዳይ አልገጠመውም፤ ቢገጥመውም ከሥራ ለመቅረት በቂ ምክንያት አይደለም፡፡ ዕረፍት ከወጣ በኋላ ስላጋጠመው ነገር በቃልም ሆነ በጽሑፍ ለአሠሪው አላሳወቀም፡፡ ስለሆነም ከሥራ የተሰናበተው በአግባቡ ነው ሲል አሠሪው ይከራከራል፡፡ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ለጉዳዩ በመ/ቁ 32822 የሰጠውን ፍርድ ወደ ኋላ እንመለስበታለን፡፡

ሁለተኛው ጉዳይ በሰበር መ/ቁ 37402 ውሳኔ ያገኘ ሲሆን፣ ከኮንስትራክሽን ሥራ ጋር ይገናኛል፡፡ ሠራተኛው በሎደር ኦፕሬተርነት ከሚሠራበት ድርጅት ከሥራ ገበታው ላይ ከአሠሪው ፈቃድ ሳያገኝ ለአምስት ቀናት ይቀራል፡፡ አሠሪው ደግሞ ከሥራ በመቅረቱ ምክንያት ያሰናብተዋል፡፡ ሠራተኛው ከሥራ የቀረሁት ታምሜ ነው፤ የሕክምና ማስረጃዬን ለአሠሪው ለማቅረብ ወደ መሥሪያ ቤት በምሄድበት ጊዜ የድርጅቱ ጥበቃዎች ወደ ግቢው አትገባም ስላሉኝ የሕክምናውን ማስረጃ መስጠት አልቻልኩም ይላል፡፡ የስር ፍርድ ቤቶች በጉዳዩ ላይ ተመሳሳይ ፍርድ ሰጥተዋል፡፡ ሠራተኛው ያለአግባብ የተሰናበተ መሆኑን በመግለጽ ወደ ሥራ ቢመለስ ግን መልካም የሥራ ግንኙነት አይፈጠርም በማለት የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች እንዲከፈሉት ወስነዋል፡፡ ሰበር ችሎቱ ግን ተቃራኒ ፍርድ ሰጥቷል፡፡ የሰበሩን የፍርድ ምክንያት በጽሑፉ የመጨረሻ ክፍል እንመለስበታለን፡፡

በተጨባጭ በፍርድ ቤት ከታዩት ጉዳዮች ለመረዳት እንደምንችለው ሠራተኞች ለአሠሪያቸው ሳያሳውቁ ከሥራ በሚቀሩበት አጋጣሚ አሠሪው ከሥራ የሚያሰናብት ሲሆን፣ ሠራተኛው ፍርድ ቤቱን የሚያሳምን በቂ ምክንያት በማስረጃ አስደግፎ ካላቀረበ የሥራ ዋስትናውን ያጣል፡፡ በተግባር ከተለመዱት የመቅረት ምክንያቶች የተወሰኑትን ለመጥቀስ እንሞክር፡፡ ሠራተኛው የዓመት ዕረፍት ፈቃድ ፎርም ሞልቶ የአሠሪውን ፈቃድ ሳያገኝ ከሥራ መቅረት፣ ከአቅም በላይ የሆነ ምክንያት (ሕመምን ጨምሮ) አጋጥሞት ከሥራ ሲቀር ሠራተኛው መረጃውን በተቻለ ፍጥነት ለአሠሪው አለማሳወቅ፣ አሠሪው የከፋ ዕርምጃ እንደማይወስድ በማሰብ፣ በቸልተኝነት ከሥራ መቅረት፣ አሠሪው ሠራተኛውን ለማሰናበት የሚገደድባቸው ምክንያቶች ናቸው፡፡ ለመሆኑ የአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 377/96 በዚህ ረገድ ምን ይላል የሚለውን እንመልከት፡፡

ሕጉ ምን ይላል?

የሥራ ሰዓትን አለማክበርና ከሥራ መቅረት በአዋጁ አሠሪው ሠራተኛውን ያለማስጠንቀቂያ ለማሰናበት ከሚችልባቸው ምክንያቶች ውስጥ እንደሚመደቡ በአንቀጽ 27(1) ላይ ደንግጓል፡፡ ሕጉ እነዚህ ምክንያቶች ሠራተኛውን ለማሰናበት በቂ የሚሆኑባቸውን ቅድመ ሁኔታዎች በጥንቃቄ ቀርጿል፡፡ የሕጉ መነሻ የአሠሪውንና የሠራተኛውን ንጽጽራዊ ጥቅም ፍትሃዊና ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ማስታረቅን ተገን ያደረገ ነው፡፡ በአንድ በኩል ሠራተኛው በተለያዩ ምክንያቶች (አሳማኝ በሆኑ) ከሥራ ሰዓት ሊያረፍድ ወይም ሊቀር ስለሚችል አንዴ አርፍደሃል ወይም ቀርተሃል በማለት አሠሪው በግብታዊነት እንዳያሰናብተው ሕጉ ጥንቃቄ ያደርጋል፡፡ ሠራተኛውን አሳማኝ ባልሆኑ ትንንሽ ምክንያቶች ማሰናበት ሕገ መንግሥታዊና ሰብዓዊ መብት የሆነውን የሠራተኛውን የመሥራት መብት ይጋፋል፡፡ በሌላ በኩል አሠሪው ትርፋማ ሆኖ እንዲቀጥል የቀጠረው ሠራተኛ በተገቢው ሰዓት ሥራ ላይ ተገኝቶ በሥራ ውሉ መሠረት አገልግሎቱን መስጠት ይገባዋል፡፡ ሠራተኛው ያላአግባብ እያረፈደና እየቀረ ዝም ብለህ ይዘህ ቀጥል የሚል የሕግ መርህ የቀጣሪውን መሠረታዊ መብት ይጋፋል፡፡ ሕጉ በአንቀጽ 27 ስለ ማርፈድና ከሥራ ስለመቅረት ሲደነግግ እነዚህን አንፃራዊ ጥቅሞች አቻችሎ ነው፡፡

በአንቀጽ 27(1) (ሀ) መሠረት ‹‹ያለበቂ ምክንያት ማስጠንቀቂያ እየተሰጠው በተደጋጋሚ የሥራ ሰዓት አለማክበር፤›› ሠራተኛውን ያለማስጠንቀቂያ ለማሰናበት በቂ ምክንያት ነው፡፡ ከዚህ ድንጋጌ ይዘት ለመረዳት እንደሚቻለው፣ ሠራተኛው በቂ ምክንያት እያለው በተደጋጋሚ የሥራ ሰዓት ባያከብር እንኳ ላይሰናበት ይችላል፡፡ ‹‹በቂ ምክንያት›› የሚለው ለትርጉም የተጋለጠ በመሆኑ ሠራተኛው ከአቅሙ በላይ በሆኑ እክል፣ ኩነት ወይም አጋጣሚ ያረፈደበትን ሁኔታ ብቻ የሚያካትት አድርጎ መተርጎም ፍትሃዊ ነው፡፡ የታክሲ ወይም የትራንስፖርት ችግር መኖሩ ለማንም በታወቀበት ከተማ፣ ‹‹ታክሲ አጥቼ፣ ትራንስፖርት ዘግይቶ፤›› ወዘተ የሚሉ ምክንያቶች በቂ ሊባሉ ይችላሉ ወይ? የሚለው አከራካሪ ነው፡፡

ሌላው ነጥብ ለአንድ ወይም ለሁለት ቀን የሥራ ሰዓት አለማክበር ከሥራ ያለማስጠንቀቂያ ለማሰናበት ምክንያት አይሆንም፡፡ የሥራ ሰዓት አለማክበሩ ‹‹በተደጋጋሚ›› ከሁለት ጊዜ በላይ የተፈጸመና አሠሪው በግልጽ በጽሑፍ ወይም በቃል ማስጠንቀቂያ እየሰጠው ሊሆን ይገባል፡፡ ለምሳሌ በተደጋጋሚ መቅረቱን እንዲሁ በዝምታ ሲታገስ የቆየ አሠሪ፣ ማስጠንቀቂያ ሳይሰጥ ሠራተኛውን ሊያሰናብተው አይችልም፡፡ አሠሪው የሚሰጠው ማስጠንቀቂያ ‹‹በተደጋጋሚ የሥራ ሰዓት እያከበርክ ባለመሆኑ ከአሁን በኋላ ካረፈድክ ከሥራህ ያለማስጠንቀቂያ እንደማሰናብትህ ዕወቅ›› የሚል ሐሳብ ያለው ነው፡፡ ለዚህ እንዲረዳ አሠሪው የሰዓት ፊርማ መቆጣጠሪያ ዘዴዎችን (ለምሳሌ በጣት አሻራ ወይም በመታወቂያ የኤሌክትሮኒክስ ምዝገባ ሊሆን ይችላል) ሊያዘጋጅ ይገባዋል፡፡ አሠሪው ሠራተኛውን አሰናብቶ ጉዳዩ በፍርድ ቤት ሙግት ከተደረገበት የሰዓት ፊርማው ሠራተኛው የሥራ ሰዓቱን በተደጋጋሚ ላለማክበሩ አስረጅ ይሆናል፡፡

የአዋጁ አንቀጽ 27 በንዑስ አንቀጽ 27(1) (ለ) ‹‹በመደበኛው ለአምስት የሥራ ቀናት ወይም በአንድ ወር ውስጥ በጠቅላላው ለአሥር ቀናት ወይም በአንድ ዓመት ውስጥ በጠቅላላው ለሰላሳ የሥራ ቀናት ያለበቂ ምክንያት ከሥራ መቅረት፤›› ያለማስጠንቀቂያ ሠራተኛን ለማሰናበት ምክንያት እንደሚሆን ደንግጓል፡፡ ከሥራ መቅረትም ለስንብት ምክንያት የሚሆነው ሁለት ሁኔታዎች ሲሟሉ ነው፡፡ የመጀመርያው የቀረበት ጊዜ መጠን ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ መቅረቱ ያለ በቂ ምክንያት ከሆነ ነው፡፡

በተግባር የተለመደው ሠራተኛው በመደዳው ለአምስት የሥራ ቀናት ሲቀር፣ የቀረበት ጉዳይ (ምክንያት) በቂ የሚባል ካልሆነ መሰናበቱን ሕግ ይደግፈዋል፡፡ ሠራተኛው ከሐሙስ ጀምሮ እስከ ሰኞ ቀርቶ ማክሰኞ ቢመጣ ቅዳሜ ለማይሠራበት ድርጅት ሦስት የሥራ ቀናት በመደዳው ቀርቷል እንጂ አምስት ቀናት ቀረ አያሰኘውም፡፡ አሠሪው ለሦስት ቀናት ያልሠራበትን ከደመወዙ ከሚቀንስ ወይም በኅብረት ስምምነት ከተደነገገ ከማሰናበት መልስ ዕርምጃ ከሚወስድ በቀር ሠራተኛውን ሊያሰናብተው አይገባም፡፡ ሠራተኛው አንድ የሥራ ቀን እየመጣ፣ ቀጣዩን ቀን የሚቀር ከሆነም የቀረበት አምስቱ የሥራ ቀናት ስለማይሟላ፣ አሠሪው ያለው አማራጭ በአንድ ወር ውስጥ በጠቅላላው ለአሥር ቀናት መቅረቱን በማስረጃ አስደግፎ ያለማስጠንቀቂያ ማሰናበት መብቱ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ግን ሠራተኛው የቀረበት ቀናት ተከታታይ መሆን አይጠበቅበትም፡፡ ‹‹በቂ ምክንያት›› የሚለው በሕጉ ያልተዘረዘረ/ያልተገለጸ በተግባር ግን እጅጉን አካራካሪ የሆነ ሐረግ ነው፡፡ ሰበር ችሎቱም ማሳያ የሚሆኑ ምክንያቶችን አልገለጸም (በፍርዱ) አልተነተነም፡፡ በደምሳሳው ሠራተኛው ከአቅም በላይ የሆነ ምክንያት አጋጥሞት፣ ከአሠሪው የዓመት ፈቃድ ወይም ሌላ ፈቃድ ለመውሰድ ባልቻለበት መልኩ ወይም በማናቸውም መልኩ የገጠመውን ጉዳይ ለአሠሪው ለማሳወቅ ባልቻለበት ጊዜ ምክንያቶቹ በቂ ሊሆኑ እንደሚችሉ ማሰብ ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ከቤቱ በሰላም ወጥቶ ከተማ ውስጥ በተፈጠረ ግርግር በጅምላ ከሌሎች ጋር አምስት ቀናት ታስሮ የተፈታ ሠራተኛ ይህንን ምክንያቱን ለአሠሪው ቢያቀርብ ‹‹በቂ ምክንያት›› የማይሆንበት ምክንያት አይኖርም፡፡

ሁሉም ምክንያቶች ግን እንደዚህ በቀላል ለመለየት የሚያስችሉ ላይሆኑ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ ሠራተኛው የቅርብ ዘመዱ ታሞበት ፀበል በመውሰዱ ቢቀር፣ ታክሞ የሕክምናውን ማስረጃ እስከ አምስት ቀናት ባይልክ በቂ ምክንያት ነው ወይ? የሚለው አከራካሪ መሆኑ አይቀርም፡፡ አሠሪው ሠራተኛው ለአምስት ቀናት ሲቀርበት ወዲያው ከሚያባርረው፣ ሠራተኛው ሲመለስ የሚያቀርበውን ምክንያት ሰምቶና መዝኖ አሳማኝ ካልሆነ ቢያሰናብተው በፍርድ ቤት የሚቀርቡ ክሶችን በጥሩ ሁኔታ ለመከላከል ያስችለዋል፡፡ ሠራተኛውም ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ከሥራ ሲቀር በሚችለው መንገድ ምክንያቱን ገልጾ ለአሠሪው ቢያሳውቅ መብቱን ለማስከበር ይረዳዋል፡፡

የፍርድ ቤቶች ተሞክሮ ምን ይመስላል?

የሥራ ክርክርን በተመለከተ ከፍርድ ቤቶች የተደራጀና ለሁሉም የቀረበ ፍርድን ማግኘት ያስቸገራል፡፡ የመጀመርያ ደረጃና ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች ፍርዶቻቸው ተጠርዘው ለጥናት ወይም ለትምህርት የተዘጋጁበት ሥርዓት ባለመኖሩ ሕግ ነክ ጉዳዮችን የሚያጠና ሰው መረጃ ያጥረዋል፡፡ በግል የሚሰበሰቡትም ምሉዕነት ስለሚጎድላቸው ሁሉንም ለመግለጽ ጥንካሬ ያንሳቸዋል፡፡ ለጥናትና ለምርምር የተሻለ ግብዓት የሚሆኑት የሰበር ሰሚ ፍርዶች መጻሕፍት ናቸው፡፡ ከላይ በመግቢያችን የጠቀስናቸው ሁለት መዛግብትም ከሰበር መዛግብት የተገኙ ሲሆን፣ ከሠራተኛ መቅረት ጋር የተያያዙ በመሆናቸው የፍርድ ቤቶችን ተሞክሮ ለማሳየት ይረዳናል፡፡

ከሠራተኛ መቅረት ጋር በተያያዘ የሚነሱት ጉዳዮች ዋና ጭብጥ ሠራተኛው ለአምስት ተከታታይ የሥራ ቀናት የቀረው በበቂ ምክንያት ነው አይደለም የሚለው ነው፡፡ አንዳንድ ዳኞች ዋና ምክንያቱን ከማስረጃ ጋር በአግባቡ በመመዘን በቂ መሆን አለመሆኑ ላይ ይፈርዳሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ አሠሪው ሠራተኛው በምን ምክንያት እንደቀረ ሳይጠይቁ ስንብቱን በመተንተን ዋናውን ምክንያት ሳያመዝኑ ስንብቱ ሕገወጥ ስለመሆኑ አቋም ይይዛሉ፡፡ ከላይ በገለጽነው የመጀመርያ መዝገብ (32822) የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ሠራተኛው የዓመት እረፍት እንዲወጣ ለተከሳሽ ሳያሳውቅ ያለ በቂ ምክንያት ለአምስት የሥራ ቀናት የቀረ በመሆኑ፣ አሠሪው የሥራ ውሉን ማቋረጡ አግባብ ነው በሚል ፈረደ፡፡ ይግባኝ ሰሚው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ደግሞ በማስረጃ ባያረጋግጥም ሠራተኛው በጎርፍ አደጋ የተጠቁትን ዘመዶቼን ልጠይቅ ነው ሲል ያቀረበው ምክንያት ለመቅረቱ በቂ ስለሆነ ስንብቱ ሕገወጥ ነው አለ፡፡ ሰበር ችሎቱ ደግሞ ሠራተኛው ለአምስት ቀናት መቅረቱ በግራ ቀኙ የታመነ መሆኑን በመግለጽ ሠራተኛው ያቀረበው ምክንያት በቃል በሠራተኛው ከመገለጹ ውጭ በማስረጃ ያልተረጋገጠ በመሆኑ ለመቅረቱ በቂ ምክንያት የለውም በማለት ለአሠሪው ፈርዶለታል፡፡

በሁለተኛው መዝገብ (37402) አሠሪው መልሱን ያላቀረበ ሲሆን፣ የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤቱ ሠራተኛው ያለበቂ ምክንያት ነው የተሰናበተው ግን ወደ ሥራ መመለሱ ለግንኙነቱ መልካም አይደለም በሚል ሳይመልሰው ቀረ፡፡ ይግባኝ የቀረበለት ከፍተኛ ፍርድ ቤትም ይህንኑ ፍርድ አፀና፡፡ ሰበር ችሎቱ ሠራተኛው የሕክምና ማስረጃ ለአሠሪው ለማቅረብ የድርጅቱ ዘበኛ ከለከለኝ ሲል ያቀረበው ክርክር በማስረጃ ያልተደገፈ መሆኑን በማተት ማስረጃ ባልቀረበበት ሁኔታ ለመቅረት በቂ ምክንያት ነበረ ለማለት አይቻልም ብሏል፡፡ ሰበር ችሎቱ በሰጠው የሕግ ትንተና አሠሪ በአንቀጽ 27(1) (ለ) መሠረት ለአምስት ቀናት የቀረን ሠራተኛ የማሰናበት መብት ያለው ሲሆን፣ ይህን መብት ሠራተኛው ሊቃወም የሚችለው በቂ ምክንያት ኖሮት ተቀባይነት ሲያጣ ብቻ ነው፡፡ ከሥራ ገበታው መቅረቱ አከራካሪ ባልሆነበት ሁኔታ በቂ ምክንያት ስለመኖሩ የማስረዳት ሸክም ከሥራ ገበታው መቅረቱን ያልከዳው ሠራተኛ እንጂ አሠሪ ሊሆን አይችልም፡፡ ከዚህ የሰበር ፍርድ በመነሳት ሠራተኛው በአንቀጽ 27(1) (ለ) ያለበቂ ምክንያት ተሰናበትኩ የሚል ክስ በሚያቀርብበት ወቅት የማስረዳት ሸክም ስላለበት ምክንያቱን ከነማስረጃው ለፍርድ ቤቱ ማቅረብ ይጠበቅበታል፡፡

በአጠቃላይ ሕጋችን ከሥራ መቅረትና የሥራ ሰዓትን አለማክበርን በተመለከተ ያስቀመጣቸው ድንጋጌዎች የአሠሪውንና የሠራተኛውን አንፃራዊ ጥቅም የሚያስጠብቁ በመሆኑ ሁሉም አውቆ ሊተገብራቸው ይገባል፡፡ አሠሪው ሁኔታዎቹ ሳይሟሉና በቂ ምክንያት አለመኖሩን ሳያጣራ አለማሰናበት፣ ሠራተኛው ያጋጠመው እክል ወይም ጉዳይ ለአሠሪው በማስረጃ በማረጋገጥ፣ ተገቢውንም መረጃ በመስጠት ሥራው እንዳይበደል ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ በግራ ቀኝ የቀረቡ ፍሬ ነገሮች ‹‹በቂ ምክንያት›› መኖር አለመኖሩን በእርግጠኝነት ለመረዳት ባላስቻሉበት ጊዜ ግን ፍርድ ቤቶች የሕጉን መንፈስ ግንዛቤ ውስጥ አስገብተው ይወስናሉ፡፡

አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው getukow [at] gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡