ሲጨንቅ እርጉዝ የማግባት አሠራር በዛ

በአብዱ ዓሊ ሒጂራ

ፍትሕ ሚኒስቴርን የሚያፈርስ በምትኩ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ተብሎ የሚጠራ መሥሪያ ቤት የሚያቋቁም የሕግ ሐሳብ መጋቢት 13 ቀን 2003 ዓ.ም. ለፓርላማ መቅረቡን የሰማነው ከተግተለተሉ ልዩ ልዩ የአፀፋ ምላሾች ጋር ነው፡፡ ‹‹አፈረሱት አሉ ውቤ በረሃን…›› ዜማ ያንጎራጎሩ አሉ፡፡

በዚህም ላይ እንደማንኛውም ሌላ የአገር ጉዳይ ከግልጽ ውይይት ይልቅ፣ ጥርጣሬና ፍርኃትን የተንተራሱ በሹክሹክታና በአሉባልታ የገለሙ ወቀሳዎች፣ ክሶችና ሐሜቶች ነግሠዋል፡፡

በመንግሥትም በኩል በአጠቃላይ የዴሞክራሲና በተለይም ደግሞ የሕግ የበላይነት ኃይል ሆኖ መውጣት መፈለጉን የሚያሳይ፣ በ‹‹ሳስበው ሳስበው ደከመኝና ተውኩት›› ወይም ‹‹በአዲስ መልክ ሥራ ጀምረናል›› ዓይነት የጥፋተኝነት የእምነት ክህደት ቃል ሰጪነት የማያሳማ የሕግና የፖለቲካ ጥራት ብልጫ አምጥቶ፣ ጉዳዩን የሚያስረዳ የፖሊሲ ማብራሪያና መከራከሪያ አልቀረበም፡፡ በገዛ ራሱ ውስጥ በቅጡ የተጠናና በውይይት የዳበረ የተለያዩ አማራጮችን አገላብጦ ያየና ያሳየ ፖሊሲ አለኝ አላለም፡፡ ቀደም ሲል የጠቀስናቸውን ወንጀለኞችንና ክሶች እያመከነ የሚታገል ብልጫ ያለው አማራጭ ነው የሚለውን አዲሱን የኢትዮጵያ የወንጀል የፍትሕ ሥርዓት አደረጃጀት አብጠርጥሮና አፍረጥርጦ የሚያሳይ ሥራ አልሠራም፡፡

‹‹ውቤ በረሃን አፈረሱት…›› ብሎ አንጀት እየበላ የሚያንጎራጉረው ‹‹መከራከሪያ›› በመንሰፍሰፍ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ስሜት ነዘራንና የቋንቋ ውበትን ይዞ በብስጭትና በድንገተኛ የደፈረሰና የፈላ ስሜት መታወርን ጋብዞ፣ የሌላውን ሰው ስሜት የመጋለብ ዓላማ ያለው ነው፡፡ እንዲህ ያለ እንጉርጉሮ ለምን ውቤ በረሃ መፍረስ እንደሌለበት በትክክል አያሳይም፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ አገር አለኝ በምትለው የከተማ ፕላን የሕግ ማዕቀፍ መሠረት፣ የልማት ሥራም ሆነ የማፍረስ ሥራ የቢሻኝ ውሳኔ የማይሽረው ነባራዊ አስገዳጅነት ያለው ክልከላዎች አሉት፡፡ በመሬት ላይ ወይም ከመሬት በታች የሚካሄድ የግንባታ፣ የምህንድስናና ወይም ሌላ ሥራ ወይም በማናቸውም መዋቅሮች (ስትራክቸርስ) ወይም መንደሮች የሕይወት ዘመን ላይ የሚደረግ ከፍተኛ ለውጥ ማለት ልማት ማለት ነው፡፡ አስቀድሞ የልማት ፈቃድ ካልተሰጠ በስተቀር የልማት እንቅስቃሴ ማካሄድ የተከለከለ ነው፡፡

በማናቸውም መዋቅሮች (ስትራክቸርስ) ወይም መንደሮች የአገልግሎት ወይም የሕይወት ዘመን ላይ የሚደረግ ከፍተኛ ለውጥ እንደ የልማት ሥራነቱም ቅድሚያ ፈቃድ ያስፈልገዋል፡፡ በማንኛውም ከተማ ክልል የሚከናወን መዋቅሮችን ወይም መንደሮችን የማፍረስ ተግባርም ፈቃድ ያስፈልገዋል፡፡ ውቤ በረሃን ለማፍረስ ፈቃድ ያስፈልጋል፡፡ በአገርና በከተማው መዋቅራዊ ፕላንና የልማት ዕቅድ ማዕቀፍ ውስጥ ፈቃዱ የሚሰጥባቸውም ሆነ የሚከለከልባቸው ሁኔታዎች፣ ምክንያቶችና ሥርዓቶች በዝርዝር ሕግ ተወስነው የአገር ሁሉ የአገር ልጅ ሁሉ ዕውቀት ይሆናሉ፡፡

ውቤ በረሃ መፍረስ የለበትም ሆነ መፍረስ አለበት የሚል ጠብና ጭቅጭቅ ካለም፣ መገዛት ያለበት በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ነው፡፡ በተራ ውርርድም ሆነ ቤት እሠራለሁ አትሠራም፣ አፈርሳለሁ አታፈርስም ውስጥ የሚነሳ አለመግባባት የሚፈታበት ሥርዓት መዘርጋት የአብሮ መኖር ዝቅተኛውና ዝቅተኛው (መንዕስ) ቅድመ ሁኔታ ነው፡፡ በሕግና በሥርዓት መተዳደር ማለት ትርጉሙ ይኸው ነው፡፡ በሕግና በሥርዓት መተዳደርን ከሕግ የበላይነት፣ ከመልካም አስተዳደርና ከዴሞክራሲ ጋር ማመሳሰልና ማሳሳት ግን የለብንም፡፡

የፖለቲካ ጠቦች የሕዝብ ቅሬታዎች ወደ ጠመንጃ የሚሄዱበት ዕድል፣ ሲሆን በተዘጋበት አለዚያም በጠበበበት፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መስተንግዶና ስብስቦሽ እየፋፋና እየሰፋ ሄዶ አጠቃላይ የእሰይታና የአዲስ አገር ግንባታ ሥነ ልቦናዊ ምልዓት በተፈጠረበት፣ የዚህም ታህታይና ላዕላይ መዋቅር መሠረት ይዞ ግንባታው በተጧጧፈበት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተለይ ነባሮቹና ሥልጣን ላይ ያሉቱ እንደማሉትና እንደተገዘቱት ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ ተፎካካሪነት በተለወጡበት፣ ይህም የሚጠይቀውን አስተሳሰብና ምግባር በያዙበት፣ ምርጫና የሕዝብ ፈቃድ በተግባቡበት የምርጫ ወቅት ማለት በሕዝብ ፈቃድና ውሳኔ መንግሥት የሚለወጥበት እንጂ፣ መንግሥት በሥልጣን ለመቆየት ሕግ የሚለውጥበት አሠራር ባልሆነበት አገር፣ በሕግና በሥርዓት ከመተዳደር በላይ፣ ስለመልካም አስተዳደር፣ ስለሕግ የበላይነትና ስለዴሞክራሲ መናገር ይቻላል፡፡

ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያ የ‹‹በሕግ አምላክ››፣ የ‹‹አደራ ሕጊ››› የ‹‹ዝባን መንግሥቲ›› አገር ሆና ብቻ ኖራለች፡፡ አገሬው በሕግ አምላክ ሲል፣ የንጉሡን ስም ጠርቶ በስሙ ሲማፀን፣ የመንግሥት ያለህ ብሎ አቤት ሲል፣ መንግሥትን የገዛ ራስህን ሕግ አስከብር ማለቱ ነው፡፡ ሕግ በማውጣት ሥልጣንህ ሕግ አወጣህ፣ ይህን ይህን አታድርጉ ብለህ ከለከልክ፣ ይህንን ደግሞ አድርጉ ብለህ አዘዝክ፣ ሕጉን አለማስከበርና አለማስፈጸም ደግሞ የከለከሉትን መፍቀድ፣ ግዴታ አድርገው ያዘዙትን መሻር ነው አለ፡፡ የ‹‹በሕግ አምላክ›› አቤቱታ ትርጉም ይህ ነው፡፡

ከዚህ በላይ በሕጉ ይዘትና አወጣጥ ሒደት ላይ በመንግሥት በራሱ ተፈጻሚ በሚሆን የሕግ ገደብ ላይ የሚለው ነገር የለውም፡፡ ሁሉም ነገር ቀርቶብን በሕግና በሥርዓት በተዳደርኩ ማለት ድረስ የሚኬደው በዚህ ምክንያት ነው፡፡

ዘመናዊት ኢትዮጵያ በጣም የተስፋፋውን፣ ወሰን የሌለውን፣ በሥጋዊውም በመንፈሳዊውም ሥራ ሁሉ የሚገባውን የንጉሠ ነገሥቱን ሥልጣን በሕግ አውጪው፣ በሕግ ተርጓሚውና በሕግ አስፈጻሚው ዘርፍ አከፋፍያለሁ ካለች ጀምሮ፣ አሁንም ድረስ አስፈጻሚው አካል የትኛውም ዘርፍ የማይገዳደረውና የማይናገረው ዋነኛው ባለጡንቻው አካል ሆኖ ኖሯል፡፡ ሕግ የማውጣት የመንግሥት ሥልጣን የፓርላማ ነው ከተባለበትና ምርጫም መካሄድ ከጀመረበት ከ1949 ዓ.ም. ወዲህ እንዲሁም የዳኝነት ሥልጣን የፍርድ ቤቶች ብቻ ነው ከተባለ በኋላም የኢትዮጵያ የረዥም ጊዜ ችግር ማገጃ ያልተደረገለት፣ ቢደረግለትም በተግባር የማይውል ያሻውን የሚያደርግ የአስፈጻሚው ዘርፍ መሆኑ ነው፡፡

አስፈጻሚው አካል ማለትም መስተዳድሩ የአገሪቷ ከፍተኛ አስፈጻሚና አስተዳደራዊ አካል ነው፡፡ የሕግ ማስከበር ሥራ የሚከናወነውም ይኸው አካል በሚያደራጃቸው በሚመራቸው ሚኒስትሮች፣ ኮሚሽኖች፣ ባለሥልጣናት በሚባሉ መሥሪያ ቤቶች አማካይነት ነው፡፡ ይህንን የፌዴራሉን መንግሥት የሕግ አስፈጻሚ አካል ራሱን የሚያደራጀውና የሚመራው በምርጫ በተወካዮች ምክር ቤት አብላጫ መቀመጫ ያገኘ የፖለቲካ ፓርቲ ነው፡፡

አሁን የምነጋገርበትና የዚህ ጽሑፍ ዋነኛ ጉዳይ የሆነው የሕግ ማስከበር የመንግሥት ሥራ የሚከናወንበት የአስፈጻሚው አካል ትልቅና ግዙፍ ቢሮክራሲ ነው፡፡ የአገሪቷን ሕጎች የሚያስተዳድረውና የሚያስፈጽመው እጅግ በጣም አብዛኛው የአገር ዓመታዊ በጀት የሚከሰከሰው ለዚህ የመንግሥት ዘርፍ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ከፍተኛው የአስፈጻሚውና አስተዳደሪያው አካል ዋነኛ አሀዶች ማኒስቴሮች ናቸው፡፡ በሚኒስቴሮች ቁጥር መጠን ላይ የተጣለ የሕግ ገደብ አገራችን አይታ አትውቅም፡፡ በመስከረም 2008 ዓ.ም. የታወጀው የአስፈጻሚ አካላት አዋጅ ከሱ ቀደም ሲል 20 የነበሩትን ማኒስቴሮች 25 አድርጎታል፡፡ የመስተዳድር አካላት ወይም የአስፈጻሚው አካል አካላት ግን ሚኒስቴሮች ብቻ አይደሉም፡፡ ሌሎችም ለቁጥር የሚያታክቱና በልክና በመልካቸውም በስያሜያቸውም ፈርጅ አሟጦና ዘርዝሮ ጠርቶ ለመገላገል የማይመቹ በርካታ አስፈጻሚ አካላት አሉ፡፡ ኮሚሽኖች፣ ኤጀንሲዎች፣ ባለሥልጣኖች (አውቶሪቲዎች)፣ ቦርዶች ማዕከሎች፣ አስተዳደሮች፣ ምክር ቤቶች፣ ኢንስቲትዩቶችና ኢንስቲትዩሽኖች ይባላሉ፡፡

ስያሜያቸው ብቻ ሳይሆን ተጠሪነታቸውም በየጊዜው የሚለዋወጥ አካላትም አሉ፡፡ ለአዋጅ ቁጥር 916/2008 መታወጅ ምክንያት የሆነው የአስፈጻሚ አካላት አደረጃጀት ማሻሻያ ጥናት እንደሚለው እንኳን፣ የማቋቋሚያ ደንብ ወይም አዋጅ የሌላቸው አራት ተቋማት ተገኝተዋል፡፡ ከ1984 ዓ.ም. የሽግግር መንግሥቱ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሕግ መውጣት ጀምሮ፣ ‹‹በተለምዶ›› የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን ጽሕፈት ቤት በመባል ይታወቅ የነበረው አካል በሕግ የተቋቋመው በ1994 ዓ.ም. በአዋጅ ቁጥር 277/1994 ነው፡፡

በ2003 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ ‹‹ራሱን የቻለ የሕግ ሰውነት ያለው የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤት›› ሆኖ ከተቋቋመው ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ጀምሮ፣ ብሔራዊ የሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲን፣ ብሔራዊ የመጠባበቂያ ነዳጅ ዲፖዎች አስተዳደርን፣ እንዲሁም የብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ኤጀንሲን፣ የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደርን፣ የብሔራዊ ባንክን ጨምሮ እስከ የብሔራዊ የመረጃና ደኅንነት አገልግሎት ድረስ ያሉት ልዩ ልዩ አካላት ሁሉ ‹‹የአስፈጻሚው የመንግሥት የሥልጣን አካል›› የሆኑ ተቋማት ናቸው፡፡

አንዳንዴ ለምሳሌ ብሔራዊ ቴአትርን፣ የኢትዮጵያ የስብሰባ ማዕከልን፣ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅን አሁን ምን የመንግሥት የአስተዳደር የሥልጣን አካላት አደረጋቸው ብለን ተደመንና  ጠይቀን ሳናበቃ፣ በግልጽና በሕግ የልማት ድርጅት ተብለው የተቋቋሙትን ለምሳሌ እንደ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ‹‹የኢፌዲሪ›› ማለትም የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪነግ ኮርፖሬሽን ብለው ሲጠሩ እንሰማለን፡፡ የኢፌዲሪ ብሔራዊ ባንክ ተብሎ አያውቅም፡፡ ቢባል ግን ነውርም ስህተትም አይደለም፡፡ የኢፌዲሪ ንግድ ባንክ፣ የኢፌዲሪ ኢትዮ ቴሌኮም፣ የኢፌዲሪ ኢትዮጵያ ሆቴል፣ የኢፌዲሪ ሙገር ሲሚንቶ ማለት ግን ነውር ብቻ ሳይሆን የመንግሥትን የአስተዳደርና የአስፈጻሚነት ሥራ አላዋቂነት ያጋልጣል፡፡

ሚኒስቴሮችን ጨምሮ ኮሚሽኖችን፣ ባለሥልጣኖችን፣ ኤጀንሲዎችን በሚያካትተው አካላት የተገነባው የአስፈጻሚው አካል ዋነኛ ተግባር ሕግ አስፈጻሚነት ነው፡፡ ሕግ አስከባሪነት ነው፡፡ ሕግ የማስከበርና የአስፈጻሚው አካል ሥልጣንና ተግባር በዋነኛነት ተለይተውና የአገር የሕግና የሥርዓት ‹‹አውጋርና አድባር›› ተደርገው በሚታወቁት ‹‹ሕግ አስከባሪዎች›› ተብለው በሚጠሩት ተቋማት ላይ ቢሆንም፣ ይህ ተግባር ሁሉም የመንግሥት የሥልጣን አባላት አካላት ጋር አለ፡፡ እንደ አዲስ አበባ ቄራዎች ያለ፣ የቄራ አገልግሎት የሚሰጥ የንግድና የነጋዴ ተቋም በመንግሥት ባለቤትነት ውስጥ የታቀፈውን ኩራትና ትዕቢት ሞቆ ራሱን የሕገወጥ ዕርድ ሕግ አስከባሪ ሲያደርግ ማየት ከ1967 ዓ.ም. ወዲህ የመጣ አሁንም ያልዳነ፣ የአገር የሕግና የሥርዓት ማስከበር ደዌ አካል ቢሆንም፡፡

የቄራዎች ድርጅት ራሱን የሾመበት የዕርድ ሥጋን ጤንነት የመቆጣጠር የመንግሥት ሕግ የማስከበር ሥራ ግን እንደ ሁኔታው ለአንዱ ወይም ለሌላው የመንግሥት የአስፈጻሚ አካል ወይም ቅርንጫፍ ወይም ወኪል ሊሰጥ ይችላል፡፡ እንዲህ ያለ መንግሥት ለአጠቃላዩ የሕዝብ ደኅንነትና ጤንነት ሲል በዜጎችና በሰዎች መብቶችና ነፃነቶች ላይ ያለው ገደብ የመጣል ሥልጣን የፖሊስ ሥልጣን (ፖሊስ ፓወር) ይባላል፡፡ ይህ ሥልጣኔና ሕግ የማስከበር ሥርዓት ‹‹ፖሊስ ፓወር›› ብሎ የጠራው ሥልጣንና ተግባር ግን ለፖሊስ ብቻ የተሰጠ አይደለም፡፡

አንድ ምሳሌ ላቅርብ፡፡ የአባለዘርዕ በሽታ ዛሬም የአገር ችግር ነው፡፡ የ21ኛው ምዕት ዓመት ኡትዮጵያ ችግር ኤችአይቪ/ኤድስ ብቻ ሳይሆን የጥንቱ የጥዋቱ የአባለዘርዕ ጭምር ስለመሆኑ የወቅቱ (መጋቢት 2008) የመንግሥት ቴሌቪዥን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ማስታወቂያ ጭንቅ ጥብብ ያሳያል፡፡ ኢትዮጵያ ዝሙትንና አመንዝራነትን ጨርሶ መከልከል አለመቻሏን ከመገንዘብ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ጋር እነዚህን በሽታዎች በነፃና በግዴታ የማከም ሕግ ያወጣችው ከ1943 ዓ.ም. ጀምሮ ነው፡፡ መጠጥ በሚሸጥበት ወይም በሚሸመትበት ቦታ/ሱቅ ወይም ከሱቅ ጋር በተያያዘው ክፍል ውስጥ የዝሙት ሥራ መሥራት ክልክል ነው፡፡ ከሃያ ዓመት ዕድሜ ያነሰ ካላቸው ወጣቶች ጋር አንዲት አመንዝራ የዝሙት ሥራ መሥራት አይገባትም ማለትን የመሰለ ሕግ ለሕክምና ባለሙያዎች ከተሰጠ፣ ከማስገደድ ሥልጣን ጋር የመጣው ዘመናዊ የሕዝብ ጤና ጥበቃ አገራችን ከገባ ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡

ስለዚህም የመንግሥት የፖሊስ ሥልጣን የሐኪምም ነው፣ የጤና ጥበቃ ባለሥልጣንም ነው፡፡ የኢትዮጵያ ደረጃዎችን የመመደብ፣ የመለኪያ መሣሪያዎችን የመወሰን ሥልጣን የተሰጠው አካልም ጭምር ነው፡፡ በእነዚህ ከተጠቀሱት ዘርፎች ከፍ ያሉና ጎልተው የሚታዩና የሚታወቁ ሕግ አስከባሪዎች ምሳሌዎችም በኢሚግሬሽን ቁጥጥር፣ በደንና ዱር አራዊት ጥበቃ፣ በዓሣ ሀብት ልማት ዘርፍ ያሉት ናቸው፡፡ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡትንና ከኢትዮጵያ የሚወጡትን ሰዎች የኢትዮጵያን የመግቢያና የመውጫ በሮች የሚቆጣጠሩ የኢሚግሬሽን ኦፊሰሮች ናቸው፡፡ የደን ጥበቃ ሕጎችንና ደንቦቻቸውን ሥራ ላይ የሚያውሉ መለዮ የሚለብሱና መሣሪያ የሚይዙ የደን ጥበቃ ኃላፊዎች (ሬንጀር) የሚባሉ አሉ፡፡ የአገሪቷ የዓሣ ሀብት ልማት አጠቃቀም ሕግም አስቁሞ የሚፈትሽ፣ የማስጊሪያ መሣሪያ የሚመረምር፣ ወዘተ ሥልጣን ያለው የዓሣ ሀብት ተቆጣጣሪ (ኢንስፔክተር) አለው፡፡

ዋነኛው ሁሉም የሚያውቀው ሕግ አስከባሪ ፖሊስ ነው፡፡ በንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት ዘመን የወጣው የፖሊስ ሠራዊት ኦርኬስትራ ዘፈን ‹‹ፖሊስ ለነፃነት የሰላም ሰንሰለት›› ይለዋል፡፡ ሜክሲኮ አደባባይን አካልሎ የተገነባው የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ጠቅላይ መምርያ ሕንፃ ሲመረቅ ኮሚሽነሩ ሕንፃውን ‹‹የሕግ የበላይነት ምልክት›› ብለው የገለጹት የመሰየምና ሐውልት የማቆም ያህል ነው፡፡ ከሚኒስቴሮች መቋቋም ጀምሮ ፖሊስ በአገር ግዛት ሚኒስቴር ሥር ሆኖ ሲተዳደር ቆይቷል፡፡ የፖሊስ ኃይልን የመምራትና የመቆጣጠር ተግባር የአገር ግዛት፣ ኋላም የአገር አስተዳደር ኋላም፣ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ሆኖ ቆይቷል፡፡ በ1972 ዓ.ም. ፖሊስ ሠራዊትን በበላይነት የመምራት ሥልጣን ለአገር አስተዳደር ሚኒስቴር የሰጠው ሕግ ራሱ በፖሊስ ሠራዊት የመጠቀምን ሥልጣን ለአገርና የሕዝብ ደኅንነት ጥበቃ ጨምሮ ሰጥቶ ነበረ፡፡ በሽግግሩ ወቅት ጭምር የማዕከላዊ መንግሥት የፖሊስ ኃይል የማደራጀትና በበላይነት የመምራት ሥልጣን የአገር ውስጥ ጉዳይ ማኒስቴር ነበር፡፡

የ1987 ዓ.ም. ሕገ መንግሥት ከፀና በኋላ ወዲያውኑ የወጣው የአስፈጻሚው ዘርፍ መወሰኛ ሕግ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የፌዴራል ፖሊስ ኃይልንና የፌዴራል እስር ቤት አስተዳደርን በበላይነት የመምራትና የመቆጣጠርን ሥልጣን ለፍትሕ ሚኒስቴር ሰጠ፡፡ በ1994 ዓ.ም. ጥቅምት ውስጥ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር በተቋቋመበት አዋጅ ግን፣ የፖሊስንና የእስር ቤትን በበላይነት የመምራት ሥልጣን ለዚህ አዲስ መሥሪያ ቤት ተሰጠ፡፡

በፍርድ ቤቶች ዘንድ ለሚቀርበው የወንጀል ክስ ሕግ አስከባሪ ጠበቃ ሆኖ በፍርድ ሚኒስቴር ሥር የተቋቋመው ዓቃቤ ሕግ፣ በተለይም ከ1954 ዓ.ም. ጀምሮ ሥራ ላይ በዋለው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነ ሥርዓት አዋጅ አማካይነት አሁን የሚታወቀውን የዓቃቤ ሕግ ምሥል/ገጽታ ሥልጣንና አሠራር አቋቋመ፡፡ በመካከሉ በተለይ በ1980 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት መቋቋም ጋር የሕግ መከበርን፣ የደንቦች፣ የትዕዛዛትና የመመርያዎችን ሕጋዊነት ጭምር የሚመራመርና የሚቆጣጠር፣ የወንጀል ምርመራ ክፍሎችን የሚቆጣጠር፣ የፍርድ ሥራ ሕጋዊነትን የሚከታተል፣ የእስረኞችንና የተያዙ ሰዎችን አስተዳደርና የተያዙበትን ሁኔታ ሕጋዊነት የሚቆጣጠር የዓቃቤ ሕግ መሥሪያ ቤት የሚባል ተቋም ተመሠረተ፡፡ የጠቅላይ ፍርድ ቤትን ካቋቋመውና አስተዳደርና አሠራሩን አዲስ ከደነገገው አዋጅ ጋር ይህ የዓቃቤ ሕግ መሥሪያ ቤት ማቋቋሚያ ሕግ የፍትሕ ሚኒስቴርን ስሙ ብቻ የቀየረ ባለበጀት መሥሪያ ቤት አደረገው፡፡ አዲሱና በ‹‹ሶሻሊስት›› አገሮች ርዕዮተ ዓለምና ባህል አምሳል የተቀረፀው የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ መሥሪያ ቤት፣ በተለይ አመራር ላይ በተቀመጡት ዓቃቤ ሕግ ረገድ አንቱ የተባሉ ባለሙያዎችን ቢጎናፀፍም የኅብረተሰቡ የሕግ ሥርዓትና የሥነ ምግባር ውቅራቶች ፍልስልሳቸው በወጣበት፣ በሕይወት በተገኘው ማንኛውም አቋራጭና አጋጣሚ ሁሉ የመጠቀም ታላቅ ቁማር በሆነበት በዚያ ወቅት አዲሱ ለውጥ የፈየደው ነገር አልነበረም፡፡ እንዲያውም የፍርድ ሥራን ሕጋዊነት በመከታተል ስም ፍርድ ቤቶች የስም ነፃነታቸውን እንኳን አጡ፡፡

ኢሕአዴግ እንደመጣ በሽግግሩ ወቅት የኢሕዲሪን ዓቃቤ ሕግ መሥሪያ ቤት አዋጅ ለመሻር፣ ኋላም ፍትሕ ሚኒስትሩን ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ለማድረግ ጊዜ ባይፈጅም፣ አስፈጻሚው የመንግሥት የሥልጣን አካል የሕግ ማስከበር ሥራ ማቀናጀት፣ ማግባባትና ተጠያቂነት ያለበት ማድረግ አልቻለም፡፡

በዚህ ምክንያት ዛሬ ከ25 ዓመት በኋላ የአገር ሕግ የማስከበር ተግባር የዓቃቤ ሕግ መሥሪያ ቤት ሆኖ ይጠቃለል ሲባል፣ ጥያቄውና ክርክሩ የተባለው የሕግ ማስከበር ሥራ መሰባሰብና መጠቃለል ያለበት በዓቃቤ ሕግ መሥሪያ ቤት ሳይሆን በፍትሕ ሚኒስቴር ነው የሚለው በጭራሽ አይደለም፡፡ የአንድ አገር ዋና የሕግ ባለሥልጣን የመንግሥቱም ዋነኛና የበላይ የሕግ አማካሪ ስያሜ የፍትሕ ሚኒስቴር ሆነ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ፣ የዛሬዋ ኢትዮጵያ ያን ያህል ደልቷትና ያንን ያህል መቀናጣት ችላ የምታዋቅረው ጭብጥ አይደለም፡፡

አገራችን በሕግ አምላክ ብሎ መንግሥት ሕጉን እንዲያስከብርለት ብቻ ሳይሆን፣ መንግሥት ራሱ ከሕግ በላይ እየሆነ ማስቸገሩ ዋናው አደጋ መሆኑን አውቆ ሰላማዊና ሕጋዊ ንቅናቄ የሚያቀጣጥል ተሃድሶ ጠይቃለች፡፡

ሕግ የማስፈጸም በተለይም ሕግ የማስከበር የመንግሥት ሥልጣን እንደገና ፈርሶ መሠራት ያለበት መሆኑም አያጠርጥርም፡፡ ዋናው ችግር ግን አሁን ለፓርላማ የቀረበው የሕግ ረቂቅ ሲጨንቅ እርጉዝ የማግባት ዓይነት ሙከራ? ወይስ ከጥንቱ፣ ከቆየውና ከትኩሱ የአገራችን የሕግ ማስከበር ታሪክና ድክመት ተምረን የአዲስ አካሄድ ጥንስስ የማደረግ አደራ የተሸከመ ቁርጠኝነት?

ስንት ጊዜ ወስዶ ተሠራ የተባለው ለአዋጅ ቁጥር 916/2008 የአስፈጻሚ አካላት አዲስ አዋጅ መነሻ የሆነው ጥናትና የውሳኔ ሐሳብ የፍትሕ ሚኒስቴርን ህልውና አስቀድሞ ማሰብ ቀርቶ፣ በተከታታይ የአስፈጻሚ አካላት ሥልጣንና ተግባር መወሰኛ ሕጎች ጭማሪ ሥልጣን መስጠትን መልሶ መላልሶ የመሰከረ መሆኑን እንኳን ጥፋት አድርጎ አልጣለውም፡፡ የጥፋተኛነትን ድርድር የመወሰን፣ ከተከሳሽ ጋር የጥፋተኝነት ድርድር የማድረግ ሥልጣን የሚሰጠው ለፍትሕ ሚኒስቴር ይሁን ለፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ዋናው ጥያቄ ይህ አይደለም፡፡ ሰው በመግደል ወንጀል ከተከሰሰና ድርጊቱን አልፈጸምኩም ብሎ ክዶ ከሚከራከር ሰው ጋር ዓቃቤ ሕግም ሆነ ፍትሕ ሚኒስቴር የሚደረደረው መቼ በወጣ? የት ተመከሮበት በፀደቀ ሕግ ነው? ለማንም የሕግ አስከባሪ አካል ይህን የመደራደር የሥራ ድርሻ የሚመደበው መጀመሪያ እንዲህ ያለ ዓይነተኛ ሕግ ሲኖር ነው፡፡

ለዓቃቤ ሕግ መሥሪያ ቤት ተጠናክሮ መቋቋም በቅድሚያ የተወሳውና ዋነኛ መነሻ የሆነው የዓቃቤ ሕግነት ሥራ በተለያዩ ተቋማት ተበታትኖ የሚሠራበት መሆኑ ነው፡፡ ለዚህም የፀረ ሙስና ኮሚሽን ዓቃቤ ሕግ፣ የጉምሩክ ዓቃቤ ሕግና የሸማቾች ዓቃቤ ሕግ በምሳሌነት ተጠቅሰዋል፡፡ የዓቃቤ ሕግነት ሥልጣን ዋነኛ ባለቤትና ባለመብት ከሆነው የመንግሥት የሥልጣን አካል በውክልና ለጉምሩክ ዓይነት ድርጅቶች ይሰጥ የነበረበትን የጥንት የጠዋት አሠራራችንን ረስተንና ገደል ከተን፣ ለዚህ በውክልና ሥልጣን የማደላደል ተግባር ዋስትና የሆነውን የማዕከላዊ ተጠሪነትን፣ ተጠያቂነትንና  አስፈላጊነትን የቢሻን ሕግ አድርገን፣ ሁሉም መሥሪያ ቤት ውስጥ ዓቃቤ ሕግ በድንገተኛ ስሜት እየተነሳን ሕግ የማውጣት አሠራራችን፣ የኮፒ ራይት ዓቃቤ ሕግና የአስገድዶ መደፈር ዓቃቤ ሕግ እንዲቋቋም ከመፍቀዳችን በፊት መደንገጣችን ጥሩ ቢሆንም፣ ይህ የአደጋ ደወል የተነገረን ግን አንድ የደች ተቋም ለአቅም ግንባታ ሚኒስቴር ባጠናው ጥናት ነበር፡፡

በፖሊስና በዓቃብያነ ሕግ መካከል፣ እንዲሁም በተለያዩ የዓቃብያነ ሕግ እንክትካች ሥልጣኖች መካከል ያለውን ችግር የመረመረውና የገዛ ራሱን የመፍትሔ ሐሳብ ያቀረበው ጥናት ተመልሶ ሊታይና የሕዝብ መወያያ ሊሆን ይገባል፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግን የሚያቋቁመው የአዋጅ ረቂቅና በተጓዳኝ ተረቀው የቀረቡት የአስፈጻሚው አካላት ማቋቋሚያ ማሻሻያዎች፣ አዲስ የሚቋቋመው መሥሪያ ቤት የካቢኔው (ማለትም የሚኒስትሮች ምክር ቤት) አባል ስለመሆኑ ተስማምተው አይናገሩም፡፡ የማቋቋሚያ አዋጅ ፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ እየተባለ የሚጠራ ራሱን የቻለ የሕግ ሰውነት ያለው የፌዴራል መንግሥት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ሆኖ በዚህ አዋጅ ተቋቁሟል ይላል፡፡ በተመሳሳይ ቀን ለምክር ቤቱ የቀረበው የመጀመሪያ አዋጅ ቁጥር 916/2008 ማሻሻያ ደግሞ በመስከረም 2008 ዓ.ም. ከፀደቀው የአስፈጻሚ አካላት ሥልጣንና ተግባር መወሰኛ አዋጅ ውስጥ የፍትሕ ሚኒስቴርን ለመሰረዝ እንጂ፣ በፍትሕ ሚኒስቴር ምትክ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግን ለመተካት አይደለም፡፡

ፓርላማው በሕገ መንግሥቱ እንደተደነገገው የፌዴራል መንግሥቱ ከፍተኛው የሥልጣን አካል ነው፡፡ በአንፃሩ ደግሞ ተኮልኩሎ እጅ የማውጣት/የመስቀል ወግ ከማሟላት የበለጠ ሥራ የሌለበት ነው እየተባለ የሚታማው በአፍ፣ በጽሑፍ፣ እንዲሁም በምሥል ጭምር መሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ይህ ረቂቅ አዋጅ በተያያዝነው የመልካም አስተዳደርና የሕግ የበላይነት የንቅናቄ ወቅት ውስጥ በፓርላማው ላይ የሚሰነዘረውን ስሞታ ማምከኛ አጋጣሚ እንዲሆን መልካም ምኞታችን ነው፡፡

  ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡