ሩቋ ጋምቤላና የቅርብ ፈተናዎቿ

ባለፈው ኅዳር ወር ሞቃታማዋ የጋምቤላ ከተማ ከሌሎቹ የአገሪቱ ከተሞች የተለየ ትኩረትን ስባ ከርማለች፡፡ የመገናኛ ብዙኃኑ የወሬ ምንጭና የፌዴራል መንግሥቱ የትኩረት አቅጣጫ እንድትሆን ካበቋት ምክንያቶች ውስጥ ሦስት ዓበይት ክንውኖችን በአሥራ አምስት ቀን ጊዜ ውስጥ ማስተናገዷ ተጠቃሽ ነው፡፡ የፌዴራልና የክልል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽኖችን የጋራ ጉባዔ ከኅዳር 17 እስከ 19 ቀን 2008 ዓ.ም. ስታስተናግድ፣ የዓለም የሰብዓዊ መብት ቀንን ደግሞ ታኅሳስ 1 ቀን 2008 ዓ.ም. እንድታስተናግድ በተወሰነው መሠረት ተግባራዊ አድርጋለች፡፡ ከሁሉም በላይ ግን በየዓመቱ ኅዳር 29 የሚከበረውንና ግዙፉን የብሔር ብሔረሰቦች ቀን አስተናግዳለች፡፡

በሦስት ዞኖችና በአንድ ልዩ ወረዳ ሥር በሚገኙ 13 ወረዳዎች፣ በ241 ቀበሌዎችና በአንድ የከተማ አስተዳደር የተዋቀረችው ጋምቤላ ጠቅላላ የቆዳ ስፋቷ 30,065 ካሬ ኪሎ ሜትር ነው፡፡ ሃያ በመቶው የክልሉ መሬት በደን የተሸፈነ ነው፡፡ ጋምቤላ በሰሜንና በምሥራቅ ከኦሮሚያ ክልል ጋር ስትዋሰን፣ በደቡብ ምዕራብ ከአዲሲቱ ደቡብ ሱዳን ጋር በሰፊው ትዋሰናለች፡፡ ከአዲስ አበባ በ776 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው የጋምቤላ ከተማ በቅርቡ 100ኛ ዓመት የልደት በዓሏን ያከበረች ሲሆን፣ እንደ ብዙዎቹ የአገሪቱ ዕድሜ ጠገብ ከተሞች ዘርፈ ብዙ ችግሮችን የምትጋፈጥ የበረሃ ገነት ነች፡፡ ከ60 ሺሕ በላይ ነዋሪዎች ያላት ጋምቤላ በአብዛኛው የሚኖሩባት ከሰሜኑና ከመካከለኛው የአገሪቱ ክፍል የመጡ በአካባቢው ነዋሪዎች አጠራር ‹‹ሐበሻ›› የሚባሉት ሲሆኑ፣ በከተማዋ ያሉትን በርካታ የንግድ ቤቶች፣ የትራንስፖርት አገልግሎቶችንና ገበያዎችን በባለቤትነት የያዙ ናቸው፡፡

በተቃራኒው በከተማዋ እዚህም እዚያም በቡድን ሆኖ ሲንቀሳቀስ የሚታየው የአካባቢው ተወላጅ ወይም ስደተኛ ይህ ነው የሚባል መተዳደሪያ የሌለውና ከተለያዩ የገቢ ምንጮች የሚያገኘውን ገንዘብ በሸመታ ላይ የሚያውል የቱሪስትነት ባህሪይ የተላበሰ ነው፡፡ በከተማውም ሆነ በክልሉ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ስደተኛ ከመኖሩ ጋር ተያይዞም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽን ድጋፍ የሚደረግላቸው እጅግ በርካታ ናቸው፡፡ በክልሉ ለረዥም ዓመታት ሰፍኖ በቆየው አለመረጋጋት፣ ብጥብጥና እጅግ ሥር የሰደደ ድህነት የአካባቢው ነዋሪን አጠቃላይ የኑሮ ሁኔታ ጥላ ያጠላበት ይመስላል፡፡

እንግሊዞች በቅኝ ግዛት ዘመን ሱዳንን በሚያስተዳድሩበት ወቅት ለወታደራዊም ሆነ ለንግድ እንቅስቃሴው መናኸሪያ በማድረግ ሲጠቀሙባት እንደነበር በታሪክ የሚነገርላት ጋምቤላ፣ ከ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ጀምሮ የኢትዮጵያ አካል እንደነበረችና በኋላም ሱዳን እ.ኤ.አ በ1956 ነፃነቷን ስትቀዳጅ በኢትዮጵያ የአስተዳደር ክልል ሙሉ ለሙሉ መካተቷም በታሪክ ድርሳናት ተወስቷል፡፡ በክልሉ አምስት ብሔረሰቦች ይኖራሉ፡፡ ጋምቤላ በእነዚህ ብሔረሰቦች የእርስ በርስ ግጭትና በአካባቢው ድንበርተኛ በሆነችው ሱዳን ለረዥም ዓመታት በቆየው የእርስ በርስ ጦርነት ስትታመስ መኖሯም ይታወቃል፡፡

ቅድመ ደርግና ድኅረ ደርግ ጋምቤላ

በአንዳንድ የአካባቢው ተወላጆችና ጸሐፊዎች እንደሚወሳው በንጉሡ ዘመን በጋምቤላ አካባቢ የነበረው ሁኔታ ከባርነት ጋር የሚነፃፀር ነበር፡፡ ንጉሡ መላ አገሪቱን ለማዘመን በነበራቸው ሰፊ ዕቅድ በጋምቤላ ሕዝብ ላይ አዲስ ባህልና የአኗኗር ዘይቤን ለመጫን ሙከራ ማድረጋቸው ይነገራል፡፡ በሌላ በኩል ‹‹አድቬንቸር ኢን አፍሪካ›› በተሰኘውና በአሜሪካዊው ደራሲ ዶን ማክለር በተጻፈውና ‹‹ከካርቱም አዲስ አበባ በአምስት አሥርታት›› በተሰኘው መጽሐፉ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ለዘመናዊነትና ለሥልጣኔ በተሰጠው ትኩረት፣ ሚሲዮናውያን ከአገሪቱ ጫፍ እስከ ጫፍ በመንቀሳቀሳቸው ትምህርትንና ኃይማኖትን አስፋፍተዋል፡፡ ከእነዚህ የሚሲዮናውያን እንቅስቃሴ መዳረሻ ከመሆን ያላመለጠው የጋምቤላ ክልልም ቋንቋውና ባህሉ እንዲታወቅ በር የከፈተ ሲሆን፣ በአኝዋ ቋንቋ የተጻፈ መጽሐፍ ቅዱስም እንደነበረው ተገልጿል፡፡

በ1967 ዓ.ም. መንበረ ሥልጣኑን ከንጉሡ የነጠቀው አብዮት በአገሪቱ ተከስቶ በነበረው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ የተነሳ በጋምቤላ አካባቢ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሠፋሪዎችን በሠፈራ ፕሮግራሙ ሲያጓጉዝ፣ ከዓለም አቀፍ የመብትና የባህል ተሟጋቾች ከፍተኛ የማጥላላት ዘመቻ ተካሂዶበታል፡፡ በተለይ ለም የሆነውን የአካባቢውን መሬት በቆለኛ ሰፋሪዎች የማስወረስና የመሬቱ ባለቤት የሆኑትን ነዋሪዎች የማፈናቀል አጀንዳ አለው በሚል፣ እንደ ‹‹ካልቸር ሰርቫይቭ›› ያሉ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋማት አውግዘውት ነበር፡፡

ሆኖም የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት በአካባቢው ሊኖረው ከሚችለው ጂኦ ፖለቲካዊ አንድምታ የተነሳና ክልሉ በነበረው ዕምቅ የተፈጥሮ ሀብት ምክንያት፣ በአካባቢው ከፍተኛ ፍላጎት ያደረበት ደርግ በጆን ጋራንግ ይመራ የነበረውን የደቡብ ሱዳን አማፅያንን ከመደገፉና ከማስታጠቅ ጀምሮ፣ በአካባቢው ለየት ያለ የልማት መርሐ ግብሮችን ወጥኖ እንደነበር ይነገራል፡፡ ለዚህም ከአገሪቱ ታላላቅ ተፋሰሶች አንዱ በሆነው የባሮ ወንዝ ላይ ረዥም የተባለውን ድልድይ በመገንባት የአካባቢውን ሁኔታ ሲያረጋጋ፣ ለፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለ ማርያምም ለየት ያለ አድናቆትንና ፍቅርን ያስገኘላቸው አጋጣሚ እንደነበርም በአካባቢው ነዋሪዎች በስፋት ይወሳል፡፡ አሁንም ድረስ በከተማዋ ጋምቤላ አቋርጦ የሚያልፈው ባሮ ወንዝ ላይ በተገነባው ድልድይ በአንድ በኩል ብቻ በርከት ያለ ሕዝብ ሲጓጓዝ የተመለከተ ጎብኚ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ሲጠይቅ፣ ከነዋሪዎች ‹‹ኮሎኔሌ መንግሥቱ የተራመዱበት ጥግ ስለሆነ ነው›› የሚል ምላሽ ሊያገኝ ይችላል፡፡

በእርግጥ በተደጋጋሚ ጊዜ እንደሚደመጠው የቀድሞው መሪ በባሮ ወንዝ ላይ ባስገነቡት ድልድይ የአካባቢው ነዋሪዎች የእርስ በርስ ግንኙነታቸውን ከማጠናከር ባለፈ፣ በኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ተጠቃሚ በመሆናቸው እሳቸው ጥለው ያለፉት ከፍተኛ ቅርስ መሆኑን ይመሰክራሉ፡፡ በአንፃሩ የከተማው የትራፊክ አስተናባሪዎች እግረኞች ብቻ ሳይሆኑ ተሽከርካሪዎችም ጭምር በተራ የሚተላለፉት የድልድዩን ደኅንነት ለመጠበቅ ታስቦ እንደሆነ በመግለጽ የመጀመሪያውን አስተያየት ያጣጥሉታል፡፡ ‹‹መንግሥቱ የባሮን ድልድይ በማሠራቱ ዘለዓለማዊ ፍቅርን በእኛ ዘንድ አኑሯል፤›› ያሉት የዕድሜ ባለፀጋው አኩሉ ኦጆን፣ ምናልባትም ፕሬዚዳንቱ በቆዳ ቀለማቸው ለጋምቤላ ሕዝቦች ቅርብ ከመሆናቸው ጋር በተያያዘ ትክክለኛ የአገር መሪ እንደነበሩም በማወደስ ጭምር ፈገግታ የተሞላበት አስተያየታቸውን ይሰጣሉ፡፡

የቀድሞው መሪ በጋምቤላ የባሮ ወንዝ ድልድይን ብቻ ሳይሆን የጋምቤላ አውሮፕላን ማረፊያን ያስገነቡ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ በአካባቢው ሕዝብ የተለየ ቦታ እንዳላቸው ቢነገርም፣ በርካታ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እሳቸው ፈጽመዋቸዋል የሚሏቸውን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ ማፈናቀልና ግድያን በመዘርዘር ኃጢያታቸውን ከማብዛት አልተቆጠቡም፡፡ የደርግ መንግሥት ህልውና ባበቃበት 1983 ዓ.ም. ኢሕአዴግ አገሪቱን በመቆጣጠር ሒደት ወደ ጋምቤላ ሲገሰግስና የቀድሞውን ሥርዓት አሻራ ሲያፀዳ፣ በሌሎቹ አካባቢዎች እንደነበረው ሁሉ የቀድሞው መሪ ምሥልን ከከተማዋ መግቢያ ላይ ለማንሳት ባደረገው ጥረት ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር ግጭት ውስጥ ገብቶ እንደነበር የሚያስታውሱ ነዋሪዎች፣ ከለውጡ በኋላ ለዓመታት አዲሱን መንግሥት ለመቀበል ተቸግረው እንደነበርም ይገልጻሉ፡፡

ሥልጣኑን ከደርግ ተረክቦ አገሪቱን ማስተዳደር የጀመረው ኢሕአዴግ ለብሔር ብሔረሰቦች መብትና ነፃነት በሕገ መንግሥቱ በሰጠው ዕውቅና መሠረት፣ የጋምቤላ ክልል ራሱን በራስ እንዲያስተዳድር ዕድሉን አግኝቶ ለዘመናት የቆየውን የማንነት፣ የነፃነትና የእኩልነት ጥያቄን ለመፍታት የተሻለ አጋጣሚ ተመቻችተውለታል፡፡ ይሁንና በአካባቢውና በክልሉ ተደጋጋሚ ግጭቶች ስለሚከሰቱ አለመረጋጋት ሰፍኖ ቆይቷል የሚሉ ተቺዎች፣ ኢሕአዴግንም በተመሳሳይ እንደ ቀድሞ ሥርዓቶች ይተቹታል፡፡ የክልሉን አስተዳደር ሕገ መንግሥቱ በሰጣቸው ዕድል በእጃቸው ካስገቡ በኋላ፣ በአካባቢው ለዓመታት በኖሩ ሰፋሪዎች ላይ ጥቃት አድርሰዋል በሚል ምክንያት መንግሥት ተደጋጋሚ ዕርምጃዎችን መውሰዱን የሚጠቁሙ የመብት ተሟጋቾች፣ እ.ኤ.አ በ2003 በክልሉ ለተከሰተው ደም አፋሳሽ ግጭት መንግሥትን ተጠያቂ ያደርጋሉ፡፡

መንግሥት በበኩሉ በክልሉ የነበረውን ከፍተኛ የፀጥታ ችግር ለመቅረፍ ብሎም በአካባቢው ልማትንና ኢንቨስትመንትን ለማበራከት ብዙ መጣሩን በመግለጽ፣ በንፁኃን ዜጎች ላይ ሰርጎ ገቦች ያደረሱትን ጥቃት ለመመከት መጠነኛ ዕርምጃ መውሰዱን ዋቢ በማድረግ ክሶቹን ሲያጣጥል ቆይቷል፡፡ በተለይ በሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ላይ የታጠቁ ግለሰቦች ከጥቂት ዓመታት በፊት ያደረሱት ጥቃትና ግድያ፣ መንግሥት አካባቢው ከፍተኛ የፀጥታ ችግር የነበረበት እንደሆነ በመገንዘብ ጠንከር ያለ ዕርምጃ እንዲወስድ ሳያስገድደው እንዳልቀረም ይነገራል፡፡

ከእነዚህ ጥቃቶች የተረፈውና የ32 ዓመቱ የሕዝብ ማመላለሻ አሽከርካሪ አቶ ሀብቱ ተመስገን ጭር ባለውና ምንም ዓይነት የደኅንነት ዋስትና በሌለበት የጋምቤላ ክልል በሚያሽከርክርበት ወቅት፣ ከበስተቀኙ በተከፈተ ድንገተኛ ተኩስ ራሱን ጨምሮ በርካታ ተሳፋሪዎች ቆስለው መትረፋቸውንና የሞቱም መኖራቸውን ይናገራል፡፡ በአጋጣሚ የመከላከያ ሠራዊት አባል ከተሳፋሪዎች መካከል በመኖሩና በአፀፋዊ ምላሽ በመከላከሉ አደጋው መቃለሉን ይገልጻል፡፡ 

ከዚህም በተጨማሪ በኢትዮጵያ ሚሊኒየም መባቻ በጋምቤላ ከተማ ከፍተኛ አመፅ ተቀስቅሶ በከተማዋ የሚኖሩ የመሀል አገርና የሰሜን ተወላጆች ላይ ጥቃት መፈጸሙና የንብረት መውደም መከሰቱ፣ የመንግሥት ኃይሎች በከተማዋና በአካባቢው ጠበቅ ያለ ቁጥጥር እንዲያደርጉ እንዳስገደዳቸውም የከተማው ነዋሪዎች ይገልጻሉ፡፡ በተለይ ከአራት ዓመት በፊት በክልሉ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ በሩዝ ምርት በተሰማራው ሳዑዲ ስታር የተባለ ኩባንያ ሠራተኞች ላይ ታጠቂዎች በከፈቱት ድንገተኛ ተኩስ የውጭ ዜጎች ሳይቀሩ ሰለባ መሆናቸው፣ የጋምቤላ ክልልን የፀጥታ ሁኔታ በአደገኛነቱ እንዲያስፈርጀው ሆኗል፡፡

የዚህ ሁሉ የፀጥታ ችግር መንስዔ ነው የተባለውና ለአሥራ ሦስት ዓመታት ክልሉን ሲያስተዳድር የቆየው ፕሬዚዳንት ከአኝዋ ብሔረሰብ የተገኘ ሲሆን፣ ከሁለት ዓመት በፊት ከንዌር ብሔረሰብ መደረጉ አሁን በአንፃራዊነት ለሚታየው ሰላምና የልማት ጭላንጭል የማዕዘን ድንጋይ መሆኑ አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ፡፡ የጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጋትሉዋክ ቱት ኮት በቅርቡ በክልሉ የተከበረውን የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በማስመልከት ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፣ አሁን በክልሉ አስተማማኝ ፀጥታ ያለ በመሆኑ ጋምቤላ ሙሉ ለሙሉ ፊቷን ወደ ልማት አዙራለች፡፡ ርዕሰ መስተዳድሩ ቀደም ሲል በሥልጣን ላይ የነበረው ኃይል የአኝዋ ብሔርን ብቻ የሚወክል እንጂ ለሌሎቹ ብሔሮች ቦታ የማይሰጥ እንደነበር ይተቻሉ፡፡ አሁን በክልሉ ካለው የሕዝብ ስብጥር አንፃር ፍትሐዊ እንዳልነበር ጠቁመዋል፡፡ አቶ ጋትሉዋክ የሚወክሉት የንዌር ብሔር ከአጠቃላዩ ሕዝብ የ46.65 በመቶ ተዋጽኦ አለው፡፡

የብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀንና ጋምቤላ

ተግባር ላይ ከዋለ 20ኛ ዓመቱን በያዘው ሕገ መንግሥት ጉልህ ሥፍራ የተቸረው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ቀን ኅዳር 29 ቀን 2008 ዓ.ም. ለአሥረኛ ጊዜ በጋምቤላ ከተማ እንደሚከበር ሲነገር፣ ክብረ በዓሉ ካሉት በርካታ ፕሮግራሞችና ከሚጠይቀው ሰፊ መስተንግዶ አንፃር የመሠረተ ልማትና የሆቴሎች ችግር ያለባት የጋምቤላ ከተማ ይህንን ኃላፊነት ለመወጣት እንደምትቸገር የገለጹ አልጠፉም ነበር፡፡ ይህ የመሠረተ ልማትና የማረፊያ ቦታ እጥረት ከአካባቢው የማያስተማምን የፀጥታ ሁኔታ ጋር ተዳምሮ፣ አሥረኛውን የብሔር ብሔረሰቦች ቀን እንከን የማያጣው እንደሚሆንም ተገምቶ ነበር፡፡

ይሁንና በኢትዮጵያ የፌዴሬሽን አባላት መካከል የተመጣጠነ ልማት ለማምጣት ሁሉም ክልሎች ከበዓሉ ጋር የተያያዙ ጠቀሜታዎችን በእኩልነት እንዲጋሩ መደረግ ከተጀመረ በርካታ ዓመታት መቆጠራቸው ይነገራል፡፡

ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ በዚህ የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ክብረ በዓል ሳቢያ፣ የታዳጊ ክልሎችን አቅም ባላማከለ ሁኔታ በተቺዎቹ ላይ ፖለቲካዊ ድል እያስመዘገበ መሆኑን የሚኮንኑ አስተያየት ሰጪዎች አሉ፡፡ በግምት ከሦስት ሺሕ እስከ አራት ሺሕ የሚደርሱ የፌዴራልና የክልል እንግዶችን፣ ባለሥልጣናትን፣ የኪነት ቡድኖችንና የሚዲያ አባላትን በእነዚህ ኋላቀር ከተሞች እንዲስተናገዱ በማድረግ የከተሞቹን ነዋሪዎች ከማጨናነቅ ባለፈ በሚኖረው ከፍተኛ ጥበቃና ወታደራዊ እንቅስቃሴ፣ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴው እንደሚገታ በመግለጽ የዚህ ውጤት ናቸው የሚሏቸውን ሁኔታዎች ይዘረዝራሉ፡፡

ለአብነትም የትራንስፖርት ችግር፣ የአገልግሎት ሰጪ ደርጅቶችና ሆቴሎች መዘጋትና በጊዜ ገደብ መሥራትን ጨምሮ የሰዎችን በቡድን የመንቀሳቀስ፣ የመሰባሰብና የመወያየት ነፃነትን እንደሚገድብም ይገልጻሉ፡፡ በጋምቤላ በተካሄደው የአሥረኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ዋዜማ ሪፖርተር በከተማዋ ከወትሮ በተለየ ከፍተኛ የፀጥታ አጠባበቅ መኖሩንና የመሸታ ቤቶች በጊዜ እንዲዘጉ እንደተገደዱ ተገንዝቧል፡፡ በማግሥቱ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ባጃጆች ቀኑን ሙሉ ሥራ በማቆማቸው እንግልት እንደተፈጠረና የከተማዋ አጠቃላይ እንቅስቃሴ ባለበት እንዲረጋ መደረጉ እንዳላስደሰታቸው ገልጸዋል፡፡ ሆኖም ለረዥም ዓመታት እንዲህ ዓይነቱን አገራዊ ትዕይንት ከዚህ ቀደም በጋምቤላ አለመመልከታቸውን በመጠቆም፣ በመገንባት ላይ ያለው አዲሱ የጋምቤላ ዘመናዊ ስታዲየም ከአፍ እስከ ገደቡ ሞልቶ መመልከታቸውና ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች በባህላዊ አልባሳቶቻቸው አጊጠው ከጋምቤላ ሕዝቦች ጋር በኅብረት መታየታቸው እንዳስደሰታቸው ግን አልካዱም፡፡

አክዋት (የአባት ስሟን ያልገለጸች) ወጣት በክልሉም ሆነ በከተማው ባለው የመልካም አስተዳደር ችግር፣ ሥራ እጥነትና ኢፍትሐዊ አሠራር በእጅጉ ብታዝንም በከተማዋ ነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ ጫና የነበረውን የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ክብረ በዓልን ግን በጥሩ መንፈስ እንደተቀበለችው ገልጻለች፡፡ ‹‹እኔ አምቦ ዩኒቨርሲቲ በነበርኩበት ወቅት የደረሰብኝ መገለል ለድብድብ ጋብዞኛል፡፡ ዛሬ ግን ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እዚህ መጥተው የጋምቤላን ሕዝብ በማወቃቸው ደስ ብሎኛል፤›› በማለት የባህልና የአኗኗር ልዩነቱ በጋምቤላ ሕዝቦችና በተቀረው የአገሪቱ ክፍል የሚኖሩ ሕዝቦች መካከል ምን ያህል ክፍተት እንደፈጠረ ትናገራለች፡፡

የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በጎ ተፅዕኖ

የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓላት በአካባቢው ነዋሪዎችና በአጠቃላይ ኑሮ ላይ ለቀናትም ቢሆን ጫና ቢያሳድሩም፣ በበዓላቱ ምክንያት የተገነቡ መሠረተ ልማቶች፣ ሆቴሎችና የእንግዳ ማረፊያዎችን ጨምሮ ለክልሎቹ ልማት ልዩ መነቃቃትን ጥለው እንደሚያልፉ ብዙዎችን የሚያስማማ ጉዳይ እንደሆነ የሚሞግቱ ግለሰቦች፣ በጋምቤላ የታየውም ይኸው ነው በማለት አስተያየታቸውን ያጠናክራሉ፡፡ በዓሉ ከተማዋ ከ35,000 ሕዝብ በላይ የሚያስተናግድ ዘመናዊ የእግር ኳስ ስታዲየም በሰባት ወራት ጊዜ ውስጥ ለመጠናቀቅ ጥቂት ጊዜ በቀረው ደረጃ ላይ እንድታገኝ ሲያስችላት፣ በክልሉ ብቻ እንደሚገኝ በተነገረለት ‹‹ናይል ሊቺዊ›› የተሰኘ የዱር አጥቢ እንስሳ መልክ የተቀረፀ ሐውልት የተገነባበት አደባባይም አግኝታለች፡፡ በተጣደፈ ግንባታ ሙሉ ለሙሉ ሳይጠናቀቅ ሥራ የጀመረውንና የከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ማረፊያ የነበረ ዘመናዊ ሆቴል፣ ወደ አውሮፕላን ማረፊያው የሚወስድ የ18 ኪሎ ሜትር መንገድ ጥገናና ማሻሻያን ጨምሮ ሌሎች ተመሳሳይ ሥራዎች ቀኑን ምክንያት በማድረግ በፍጥነት ተከናውነዋል፡፡

ከሁሉም በላይ ግን ክልሉ ያለውን እምቅ የተፈጥሮ ሀብት በተለይም በተላበሰው አረንጓዴ መልክዓ ምድር ከዓመት ዓመት የሚፈሱ ወንዞቹን ይዞ ለግብርናና መሰል ኢንቨስትመንቶች ራሱን ያስተዋወቀበት አጋጣሚ የሚጠቀስ ሲሆን፣ በቅርብ ዓመታት ውስጥ በተደጋጋሚ ጊዜ ክልሉን የተፈታተኑት የፀጥታ ችግሮች ለጊዜውም ቢሆን ተወግደው መቆየታቸው ከክብረ በዓሉ የተገኙ ትሩፋቶች እንደሆኑ የክልሉ ባለሥልጣናት ይገልጻሉ፡፡ ከጎረቤት የደቡብ ሱዳን አካባቢ የሞርሌ ጎሳ አባላት በክልሉ ላይ ተደጋጋሚ የከብቶች ዝርፊያ፣ የቤት ማቃጠል፣ የግድያ ሙከራዎችን በማድረጋቸው ክልሉ በፌዴራሉ መንግሥት ድጋፍ የኢትዮ-ደቡብ ሱዳን ኮንፈረንስ በብሔር ብሔረሰቦች ቀን በዓል ዋዜማ መካሄዱን በመጠቆም፣ ክልሉ ባለፉት ሁለት ዓመታት የተሻለ መረጋጋትና የልማት አቅጣጫ ላይ መገኘቱን ባለሥልጣናቱ ይጠቁማሉ፡፡ ይሁንና በአኝዋና በንዌር ብሔረሰቦች መካከል አልፎ አልፎም ቢሆን የሚስተዋለውን ግጭትና የባላንጣነት ስሜት ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ክልሉ አሁንም ወደ አስተማማኝ መረጋጋት እንዳልመጣ የሚጠቁሙ ተንታኞች አሉ፡፡ በክልሉ የሚታየው ዝቅተኛ የኢንቨስትመንት ፍሰት፣ ሥራ አጥነትና የአቅም ውስንነት የክልሉ ከባድ ፈተናዎች ሆነው እንደሚቆዩም ይገልጻሉ፡፡ ለጊዜው ግን በብዙኃኑ የመሀል አገር ነዋሪዎች ዘንድ በመልክዓ ምድራዊ አቀማመጧ ሩቅ መስላ የምትታየው ጋምቤላ ከነቅርብ ፈተናዎቿ ጋር የሰላም አየር እያንዣበበባት መሆኑን በበዓሉ ታዳሚ በነበሩ በርካታ እንግዶች ተገልጿል፡፡