ምሉዕ የሕግ ጥበቃ ለመንፈሳዊ ሀብቶቻችን

የትንሳዔ በዓል ሲከበር የበዓሉ አካል የሆኑ መንፈሳዊ ሀብቶችን እንዘክራለን፡፡ በዚህ ወቅት የምንመለከተው ዝማሬው፣ ቁመቱ፣ አለባበሱ፣ ስግደቱ፣ መጽሐፍቱ፣ የዜማ መሣሪያዎቹ ወዘተ. በአገልግሎታቸው በዓሉን ያበስራሉ፤ ምስጢሩን ይገልጣሉ፡፡ ከሃይማኖት መገለጫ ባለፈ የኢትዮጵያዊነት መገለጫ ከሆኑ ምዕተ ዓመታት ተቆጠሩ፡፡ ጥንግ ድርብ መልበስ፣ ያሬዳዊ ዜማን መዘመር፣ መሰንቆ፣ ከበሮ ፀናጽልና መቋሚያውን ሲመለከት ሐሴት ማድረግ፤ ከደስታ የመነጨ እንባ ማውጣት ኢትዮጵያዊነት ሆኗል፡፡ እነዚህ ሀብታት ፈጣሪ የሚመለክባቸው በመሆናቸው ‹‹መንፈሳዊ›› ብንላቸውም በምድር ሥነ ሕግ ቅርስ የምንላቸው ናቸው፡፡ እነዚህ ቅርሶች የሚታዩ፣ የሚዳሰሱ (Tangibles) እንደ መስቀል፣ ቅዱሳት መጽሐፍት፣ አቢያተ ክርስቲያናት ያሉ ወይም የማይታዩ፣ የማይዳሰሱ (Intangibles) እንደ ቅኔ፣ መዝሙር፣ ቅኔ ማህሌት፣ ቅዳሴ ያሉት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ቅርሶች በአገራችን ሕጎች በሕገ መንግሥቱ፣ በተለያዩ አዋጆችና ደንቦች ጥበቃ ይደረግላቸዋል፡፡ በዚህ ረገድ የቅርስ ጥበቃ አዋጅ፣ የተዘረፉ ቅርሶችን ለማስመለስና በጦርነት ጊዜ ቅርሶችን ለመጠበቅ የወጡ አዋጆች፣ በቅርስ ላይ ለሚፈጸሙ ወንጀሎች ቅጣት የሚደነግገው የወንጀል ሕጉ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በዚህ ጽሑፍ የምንመለከተው የሕግ ጥበቃ ግን በእነዚህ ሕጎች የማይሸፈን ነው፡፡ ይህ ጽሑፍ መንፈሳዊ ሀብቶች የመጡበትን ሥርዓት ጠብቀው ሳይበረዙ እዲቀጥሉ የሚያደርግና ሦስተኛ ወገን ያለፈቃድ መጽሐፍቱን ቢተረጉም፣ ቢያሳትም፣ ወደ ሌላ ቋንቋ ቢለውጥ ወይም ዜማውን ከእምነቱ ሥርዓት ውጪ ቢጠቀም፣ ሥርዓቱን ቢተገብር ሊኖረው ስለሚችለው ውጤት ጥበቃ የሚደነግግ የሕግ ማዕቀፍ ስለመኖሩ መፈተሽ ነው፡፡

የመንፈሳዊ ሀብቶቹ ባለቤት ማነው?

የመንፈሳዊ ሀብቶቹ ባለቤትን መለየት የባለቤቱን መብት ዓይነትና መጠን ለመተንተን ይረዳል፡፡ ከዚህ በላይ የተገለጹት መንፈሳዊ ሀብቶች የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ስለመሆናቸው መናገር የተሻለ ተቀባይነት አለው፡፡ ምክንያቱም የእነዚህ መንፈሳዊ ሀብቶች ደራስያን የሃይማኖት አባቶች በመሆናቸውና የሃይማኖት አባቶችም ሥራዎቹን የፈጠሩዋቸው በቤተ ክርስቲኒቱ ውስጥ አምላክ እየተመለከ እንዲኖር ለማድረግ በሚል ዓላማ በመሆኑ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ እነዚህ ሀብቶች ለዘመናት በየአቢያተ ክርስቲያናቱ ለመንፈሳዊ ዓላማ በመዋል ላይ ያሉና ሌላ ባለቤት ነኝ የሚል አካል ሲጠይቃቸው ስለማይስተዋል ነው፡፡ በተጨማሪም ስለ ቅርስ ጥናትና አጠባበቅ የወጣው አዋጅ ቁጥር 209/92 ቅርሶች በመንግሥት ወይም በማናቸውም ሰው ባለቤትነት ሊያዙ ይችላሉ በማለት ስለሚደነግግና ሰው የሚለው እንደ እምነት ተቋማት ያሉ በሕግ የሰውነት መብት የተሰጠው አካልን ስለሚጨምሩ የሃይማኖት ተቋማት የቅርስ ባለቤቶች ናቸው፡፡ ቅርሶቹ በስማቸው የተመዘገቡ ከሆነ ደግሞ የባለቤትነት የተሻለ ማስረጃ ነው፡፡ ይህ ማለት ግን ግለሰቦች ባለቤት የሚሆኑበት ቅርስ አይኖርም ማለት አይደለም፡፡ ሆኖም ግለሰቦች የመንፈሳዊ ሀብቶች (ቅርሶች) ባለቤት የሚሆኑባቸው አጋጣሚ በእኛ አገር ነባራዊ ሁኔታ የለም፡፡ ስለዚህ በዚህ ጽሑፍ ምልከታ የተደረገባቸው መንፈሳዊ ሀብቶች የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሀብቶች ናቸው፡፡

የመንፈሳዊ ሀብቶቹ ባለቤት መብት ምን ድረስ ነው?

የሃይማኖት ተቋማት የመንፈሳዊ ሀብቶች ባለቤት ከሆኑ በፍትሐ ብሔር ሕጉ የተቀመጡ ሰፊ የባለቤትነት መብት ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ ይኼውም መንፈሳዊ ሀብቶቹን የመጠቀም፣ ሌላው እንዲጠቀም የመፍቀድ ወይም የማስተላለፍ መብት ይኖራቸዋል፡፡ ከዚህ ሰፊ መብት በመነሳት የእምነት ተቋማት አምልኳቸውን የሚፈጽሙባቸውን ሥርዓቶች ሌላው (በእምነት የማይመስለው) በተጠቀመ ጊዜ የመቃወምና የማስቆም መብት ይኖራቸዋል ማለት ነው፡፡ ሆኖም እምነት የውስጥ በመሆኑ ይህን መብት መተግበር አስቸጋሪ መሆኑ አጠያያቂ አይሆንም፡፡ ማንም ሰው የአምልኮ ሥርዓቱን ስለማምንበት ነው የምጠቀመው የሚል ክርክር ቢያቀርብ ተቀባይነት ማግኘቱ አይቀርም፡፡ በሌላ በኩል ግን የአምልኮ ሥርዓቱን የሚጠቀመው አካል ወይም ኅብረት በግልጽ ከባለቤቱ አስተምህሮ ጋር ተቃርኖ ካለው የባለቤትነት መብቱ መጣሱ አካራካሪ አይሆንም፡፡

የመንፈሳዊ ሀብቶቹ ባለቤት በቅርስ ጥናትና አጠባበቅ አዋጅ ያለው መብትና ግዴታ

የቅርስ ጥናትና አጠባበቅ አዋጅ ቅርስ በባለቤትነት የያዘ ሰው ስላሉበት ግዴታዎች እንጂ ስላሉት መብቶች በግልጽ አይደነግግም፡፡ ግዴታዎችን በተመለከተ የአዋጁ አንቀጽ 18 በራሱ ወጪ ለቅርስ ተገቢውን ጥበቃና እንክብካቤ ማድረግ፣ ቅርሱን ለኤግዚቢሽን ወይም በሌላ ሁኔታ ለሕዝብ እንዲታይ በባለሥልጣኑ መፍቀድ፣ ስለቅርሱ አያያዝና አጠቃቀም የሚመለከቱ ደንቦችንና መመርያዎችን ማክበር በሚል ይደነግጋል፡፡ አዋጁ ከመብት ይልቅ ግዴታ ላይ ማተኮሩ የመንፈሳዊ ሀብቶች ባለቤት የሆኑ የሃይማኖት ተቋማት ያላቸውን መብት በዝርዝር ለማየት አያስችልም፡፡

ሆኖም አዋጁ የቅርሱ ባለቤት ሀብቶቹን እንዲጠቀም የማይከለክሉ መሆኑን ከአጠቃላይ መንፈሱ መረዳት ይቻላል፡፡ በተጨማሪም የአዋጁ አንቀጽ 23 የቅርስ ባለቤት ባለቤትነቱን ለሦስተኛ ወገን የማስተላለፍ መብትን ያጎናጽፋል፡፡ ሆኖም ቅርሶቹ ሲተላለፉ ሁለቱም ወገኖች በቅድሚያ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣንን በጽሑፍ የማሳወቅ ግዴታ ያለባቸው ሲሆን፣ ባለሥልጣኑም ለሽያጭ የቀረቡ ቅርሶችን የመግዛት ቅድሚያ መብት ይኖረዋል፡፡ ከዚህ ውጪ አዋጁ የቅርስ ባለቤት ከእርሱ ውጪ ያሉ ተጠቃሚዎችን የመከልከል ወይም ሲጠቀሙ የማስቆም ሥልጣን ያለው ስለመሆኑ በአንድምታ ካልሆነ በግልጽ አንመለከትም፡፡ በተለይ ቅርሱ ግዙፍነት የሌለው (intangible) ቅርስ በሆነ ጊዜ የምዝገባ ሥርዓትም በባለሥልጣኑ ባለመጀመሩ ባለቤትነት አረጋግጦ የመብት ጥሰቱን ለማረም የሚያስቸግር ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ የቅርሶቹ ምዝገባ ከባለሥልጣኑ ባለፈ በዩኔስኮ ቢፈጸም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በቅርሱ ላይ ያላትን መብት በዓለም አቀፍ ደረጃ ሳይቀር ለመጠየቅና ለማስከበር ያስቻላታል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን የመንፈሳዊ ሀብቶቹ ባለቤት ያልሆኑ ሌሎች የውጭ ተቋማት ቅርሶቹን በዓለም አቀፍ ደረጃ በማስመዝገብ የአገራችንን መብት ሊያጣብቡ መቻላቸው አከራካሪ አይሆንም፡፡

በአጠቃላይ የቅርስ ጥናትና አጠባበቅ አዋጅ ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የመንፈሳዊ ሀብቶች የባለቤትነት መብት መሠረት ቢደነግግም፣ በተግባር ግዙፍነት የሌለው ቅርስ የመመዝገብ ተሞክሮ ባለመኖሩ ይህን የባለቤትነት መብት በአገር ውስጥና ከአገር ውጭ ከሃይማኖት ሥርዓት ውጪ የሚጠቀሙ አካላትን ለመከልከል ወይም ለማስቆም በሚያስችል መልኩ ግልጽ አልተደረገም፡፡ ይህ ክፍተት ለመብት ጠያቂውም ሆነ ለግዴታ ፈጻሚው ዝርዝር ድንጋጌዎን አለመያዙ የመንፈሳዊ ሀብቶቹ ቢበረዙ ለማስተካከል የሚያስችል ፈጣን ዕርምጃን ለመውሰድ አያስችልም፡፡

የቅጅና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ አዋጅ ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የተሻለ ጥበቃ ይሰጥ ይሆን?

ቅዱሳት መጽሐፍት ያለ ኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ፈቃድ ሲተረጎሙ፣ ዜማዎች ከጥንት መሠረታቸው ተፋልሰው ሲቀርቡ፣ ዝማሬ፣ ወረብ ወዘተ ሥራዎች በአዕምሯዊ ንብረት ጽንሰ ሐሳብ ክዋኔ (Performance) የሚሉባት ያለፈቃድ ሲተገበሩ የቅጂና ተዛማች መብቶች ጥበቃ አዋጅ መፍትሔ እንደሚሰጥ ይጠበቃል፡፡ በእርግጥ ይህ አዋጅ ከእነዚህ ጥበቃዎች የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ለመጠቀም በሚያስችልበት መልኩ ተቀርፀዋል ወይ? የሚለው በአግባቡ ሊታይ የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡

የቅጅና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ አዋጅ ለሥራ አመንጪ ለሆነ የተፈጥሮ ሰው ወይም በሕግ ሰውነት ለተሰጠው አካል በሥራው ላይ የቅጅ መብት ማለትም ከሥራው የሚመነጭ የኢኮኖሚ ጥቅም (የሞራልን መብት ጨምሮ) የሚሰጥ ሲሆን፣ ለሥራው አመንጪው ወይም እርሱ ለሚፈቅድለት ለሌላ አካል ሥራውን የማባዛት፣ የመተርጎም ወደ ሌላ የመቀየር፣ በይፋ የመከወን፣ የማከፋፈል ወዘተ መብቶችን ይሰጣል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አዋጁ ለተዛማች መብቶች ማለትም ለከዋኝ፣ የድምጽ ሪከርዲንግ ፕሮዲውሰር፣ የብሮድካስቲንግ ድርጅት በሥራቸው ላይ ጥበቃ ይሰጣል፡፡

አዋጁ ጥበቃ የሚሰጠው ‹‹ሥራ›› በአንቀጽ 2 (30) በግልጽ እንደተቀመጠው መጽሐፍትን፣ የሃይማኖት ስብከትን፣ የኪነ ሕንፃ ሥራና ሥዕላትን ስለሚያጠቃልል የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የሥራ አመንጪ በሆነችባቸው ወይም ለቤተ ክርስቲያኗ በስጦታ በተቀበለቻቸው ወይም መብቱ ተላልፎላት ከሆነ የቅጅ መብት ባለቤት ትሆናለች፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በቅጥር የተከናወነ ሥራ ማለትም በቅጥር ወይም በአገልግሎት ውል መሠረት ተከፋይ በሆነ የሥራ አመንጪ የተፈጠረ ሥራም ከሆነ በአዋጁ ጥበቃ ይደረግላታል፡፡

በአዋጁ መሠረት ጥበቃ የሚያገኘው ሥራ ሁለት መመዘኛዎችን ማለፍ ይጠበቅባታል፡፡ አንቀጽ 6 ይኼን ይደነግጋል፡፡ ይኸውም ሥራው ወጥ (ኦሪጅናል) ከሆነና ከተቀረፀ ወይም ግዙፍነት ካገኘ ሥራውን በማውጣት ምክንያት ብቻ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ጥበቃ ያገኛል፡፡ በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሥራዎች ወጥነት ያላቸውና በድምጽ፣ በክወና፣ በጽሑፍ የሚገለጽ አንዳንዴም ተቀርፀው የሚገኙ በመሆናቸው የጥበቃው ተጠቃሚ መሆን ይችላሉ፡፡ በዚህ ረገድ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቤተ ክርስቲያኒቱ አማኞች የሚወጡ መጻሕፍት፣ ስብከቶችና መዝሙራት የሥራ አመንጪዎቹ ተላልፈው ሲገኙም ቤተ ክርስቲያኒቱ የቅጅ መብት ተጠቃሚ መሆኗ አጠያያቂ አይሆንም፡፡ አከራካሪ የሚሆነው ጥያቄ ዕድሜ ጠገብ የሆኑት መንፈሳዊ ሀብቶችን በተመለከተ ያለው ጥበቃ ነው፡፡ ለምሳሌ የቅዱስ ያሬድ ድጓ፣ ፆመ ድጓ፣ መዋሲት ወይም አቋቋም ወይም ዜማ በአዋጁ ያለው ጥበቃ ምን ድረስ ነው? የሚለው ነው፡፡

በመጀመሪያ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የእነዚህ የቅዱስ ያሬድና የሌሎች አባቶች ሥራዎች የእርሷ እንደሆነ በታሪክ፣ አመክንዮ ወይም በአጠቃላይ ልማድ የሚታወቅ ቢሆንም በአዋጅ ጥበቃ እንዲያገኙ ግን ቅዱስ ያሬድ ሥራዎቹን ለቤተ ክርስቲያንት መሥራቱን ወይም በስጦታ ወይም በማናቸውም መንገድ ማስተላለፍ፣ ማስረዳት ይጠይቃል፡፡ አዋጁ የስጦታ ወይም የማስተላለፍ ወይም ፍቃድ የመስጠት ጉዳይ በጽሑፍ ካልተደረገ የተላለፈለት ሰው የቅጂ መብት ኢኮኖሚያዊ መብት ተጠቃሚ እንደማይሆን በአንቀጽ 23 ላይ በግልጽ ደንግጓል፡፡ የቤተ ክርስቲያኗ ቅዱሳን ደግሞ እንኳን በጽሑፍ ውል ሥራዎቻቸውን ለቤተ ክርስቲያን ሊያስተላልፉ ስማቸውን እንኳን በሥራዎቻቸው ላይ ለመግለጽ መንፈሳዊነታቸው አልፈቀደላቸውም፡፡ ጸሐፍቱ፣ ዘማሪያኑ፣ ሠዓሊያኑም ቢሆን ከቤተ ክርስቲያኗ ጋር የቅጥር ውል ነበራቸው ብሎ ለመከራከር የሚያስችል ሁኔታ አልነበረም፡፡ እነዚህ ሰዎች የራሳቸውን ገንዘብ፣ ሰውነትና ዕውቀት ይሰጣሉ እንጂ ከቤተ ክርስቲያኗ በምድራዊ ሚዛን የሚለካ ልዋጭ (Return) ደመወዝን ጨምሮ ስለማያገኙ ሥራዎቹን ቤተ ክርስቲያኗ በቅጥር ውል ያሠራቻቸው ስለመሆናቸው መናገር አይቻልም፡፡

በሁለተኛ ደረጃ ሊታይ የሚገባው ቤተ ክርስቲያኗ በአዋጅ መሠረት የእነዚህ ዕድሜ ጠገብ መንፈሳዊ ሀብቶች ሥራ አመንጪ መሆኗ ቢረጋገጥ ወይም ሥራዎቹ በስጦታ ወይም ለረጅም ዘመናት ከመጠቀም ተላልፎላታል ብንል እንኳን መብቱን ለመጠቀም ሌላ ገደብ በአዋጁ ተቀምጧል፡፡ ይኸውም የአዋጅ አንቀጽ 20 የኢኮኖሚ መብቶች ፀንተውም የሚቆዩበት ጊዜ የሥራ አመንጪው በሕይወት በሚቆይበት ዘመንና ከሞተ በኋላ ለወራሾቹ እስከ 50 ዓመት ፀንተው ይቆያሉ ሲል መግለጹ ነው፡፡ በዚህ ድንጋጌ መሠረት የቅጅ መብት የኢኮኖሚ ጥቅም (ማለትም ማባዛት፣ መተርጎም፣ ወደ ሌላ የመቀየር፣ በይፋ የመከወን ወዘተ.) የሥራ አመንጪው በሕይወት እስካለ ድረስ ወይም ከሞተ በኋላ እስከ 50 ዓመት ብቻ ተፈጻሚ ይሆናል፡፡ ይህ የ50 ዓመት ገደብ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከዘመናት በፊት በሥጋ ከተለዩት የቤተ ክርስቲያኗ አባቶች የተላለፈላትን መብቶች ለመጠቀም አያስችላትም፡፡

የመንፈሳዊ ሀብቶቹ የሕግ ጥበቃ እንዴት ሊሸፈን ይችላል?

ግዙፍነት የሌላቸው መንፈሳዊ ሀብቶች በባህሪያቸው በቀላሉ የሚሸጋገሩ (Susceptible for diffusion) በመሆናቸው ለጥበቃ አስቸጋሪ ይሆናሉ፡፡ ጥበቃዎቹን ለማስተካከል የሁሉንም ሃይማኖቶች መንፈሳዊ ሀብቶች ሊያስተዳድር የሚችል የኅብረተሰብ ዕውቀት ጥበቃ አዋጅ (Community knowledge protection proclamation) ሊወጣ ይገባል፡፡ ይህ አዋጅ የእምነት ተቋማት፣ የባህል ሽማግሌዎች ወይም ማኅበራት የሚፈጥሩዋቸው ሥራዎች ላይ ወይም አሁን ተቋማቱ ይዘዋቸው ያሉ ግዙፍነት የሌላቸው መንፈሳዊ ሀብቶች (እንደ ቅኔ፣ ቅዳሴ፣ ዝማሬ ወዘተ ያሉትን) ዝርዝር ጥበቃ የሚሰጥ ሊሆን ይገባል፡፡ ጥበቃው የተቋማቱን ሰፊ የባለቤትነት መብት የሚያረጋግጥ (መጠቀምን መፍቀድ፣ መከልከልና ማስቆም የሚያስችል)፣ መንፈሳዊ ሀብቶች ሳይበረዙ የሚቆዩበትን ሁኔታ የሚያመቻች እንዲሁም ጥበቃው በጊዜ ገደብ ያልተወሰነ ሊሆን ይገባል፡፡

በሌላ በኩል የሕግ ክፍተቱን ለመሸፈን አሁን ያሉትን የሕግ ጥበቃዎች ማስፋትና በግልጽ የተቀመጡትን ወደ ተግባር መለወጥ ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ትውፊቷን ልትጠብቅ በምትችልበት መልኩ ያለፍቃዷ የሚከወኑ ዝማሬዎችን፣ ሥዕላትን፣ ክዋኔዎችን፣ የመጽሐፍት ትርጉሞችን ለመከልከል ወይም ሲፈጸሙ ለማስቆም የሚያስችላትን የባለቤት መብት በግልጽና በዝርዝር በደንብ (በመመርያ) መደንገግ ይገባል፡፡ ግልጽ የሆኑትንም ግዴታዎች መፈጸም ጥበቃውን ያጠናክራል፡፡ በዚህ ረገድ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ግዙፍነት ያላቸውንም ሆነ የሌላቸውን መንፈሳዊ ሀብቶች በአግባቡ ለማስመዝገብ መንቀሳቀስ ይገባዋል፡፡ በተለይ ግዙፍነት የሌላቸው ቅርሶች በዩኔስኮ እንዲመዘገቡ በማድረግ የቅርሶችን ዓለም አቀፋዊ ጥበቃ ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ የቅርስ ምዝገባ የባለቤትነት መብት ከማረጋገጥ ባለፈ በቀዳሚነት  የመታወቅ መብት የሚሰጥ በመሆኑ፣ ሌሎች ባዕዳን ቅርሶቹን በማስመዝገብ የኢትዮጵያዊነት አሻራ እንዳይሰርዙ መንቀሳቀስ ይገባል፡፡ ለአገር ኩራት የሆኑ መንፈሳዊ በዓላትን ስናከብር ሳይበረዙ የሚቀጥሉበትን የሕግ ሥርዓት በመደንገግ ከሆነ ኢትዮጵያዊነትን እንታደጋለን፡፡   

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የሕግ ጠበቃና አማካሪ ሲሆኑ፣ በኢሜይል አድራሻቸው getukow [at] gmail.com  ማግኘት ይቻላል፡፡