ሙስናን የት ድረስ ታግለነዋል?

በሒሩት ደበበ

ሙስናና ያልሠሩበትን የመሻት ዓለም አቀፍ ችግር ነው፡፡ ባደጉትም ይሁን ባላደጉት አገሮች የሚከሰት የሕዝብ ተጠቃሚነትና የአገር መለወጥ እንቅፋት መሆኑም ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ያም ሆኖ የግልጽነትና የተጠያቂነት ባህላቸው ዝቅተኛ በሆነ፣ የዴሞክራሲ ሥርዓትን ከልብ እየገነቡ ባልሆኑ፤ የሕግ የበላይነት ጥርስ በወለቀባቸው አገሮች ሙስና አንበሳ ሆኖ ይታያል፡፡

ለዚህም ነው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እ.ኤ.አ. ዲሴምበር 4 ቀን 2000 ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ሙስና በአገሮች ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመከላከል ጥረት የጀመረው፡፡ ይኼውም የዓለም አገሮችን የሚያሳትፍ ዝርዝርና ሁሉን አቀፍ የፀረ ሙስና ስምምነት አስፈላጊ መሆኑን በመደንገግ ውሳኔ ቁጥር 55161 ይፋ ማድረጉ በቀጣይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን የፀረ ሙና ኮንቬሽንን ለማፅደቅ መሠረት ጥሏል፡፡ ቢያንስ ለሁለት ዓመታት የተመከረበት ስምምነትም እ.ኤ.አ. ኦክቶበር 31 ቀን 2003 በተካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ በውሳኔ ቁጥር 5814 መፅደቁ ይታወቃል፡፡

ወደ ኢትዮጵያ ሁኔታም ስንመጣ በአሁኑ ወቅት 178 የዓለም አገሮች ያፀደቁትን ዓለም አቀፍ የፀረ ሙና ኮንቬሽንን ተቀብላ ወደ ሥራ ከገባች ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በዚሁ መሠረት በአገሪቱ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በፌዴራልና በክልሎች ደረጃ ተቋቁመው ወንጀሉን ለመከላከል የሚረዱ ልዩ ልዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው፡፡ በአገሪቱ ወንጀለኛ መቅጫ ሕግም ሆነ በፀረ ሙስና ሕጎች ላይ ማሻሻያ ተደርጎ ወደ ሥራ በመገባቱም ቀላል የማይባሉ ዕርምጃዎች ተወስደዋል፡፡

ያም ሆኖ አሁንም ሙስናን ከኢትዮጵያ ነቅሎ መጣልም ሆነ በሚታይ ደረጃ መቀነስ አልተቻለም፡፡ እንዲያውም መልኩና መጠኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተለዋወጠ የሕዝብን ሀብት እየበላና ሕዝቡንም እያስመረረ ለመምጣቱ ራሱ መንግሥት ያደረገው ጥናት በቅርቡ አረጋግጧል፡፡ ለሕዝቡም ይፋ ሆኗል፡፡

በእርግጥ ሙስና በዓለም አቀፍ ‹‹ስታተሱም›› ሆነ በአፍሪካ ደረጃ የመጨመር እንጂ የመቀነስ ምልክት አልታየበትም፡፡ ለምሳሌ ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የተሰኘው በሙስና ላይ ትኩረቱን አድርጎ የሚንቀሳቀሰው ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆነ ተቋም፣ አፍሮ ሜትር ተብሎ ከሚጠራው ተቋም ጋር በቅንጅት ባካሄደው ጥናት እ.ኤ.አ. በ2015 ከሰሐራ በታች ከሚገኙ የአፍሪካ አገሮች ከ75 ሚሊዮን የሚልቁ ሰዎች ጉቦ መስጠታቸውን አረጋግጧል፡፡

ይህ ግርድፍ ጥናት የአፍሪካ አኅጉር ሕዝቦች ጉቦ የሚሰጡበትንና የሙስና ወንጀልን የሚያበረታቱበትን መሠረታዊ ምክንያትንም አስቀምጧል፡፡ በቀዳሚነት ወንጀል ሠርተው ለማምለጥና የቅጣት ጊዜያቸውን ለማሳጠር ለፖሊስና ለፍርድ ቤቶች (ዳኞችና ዓቃብያነ ሕግ) የሚከፍሉት ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ መሠረታዊ የሕዝብ አገልግሎት (መብራት፣ ውኃ፣ መሬት፣ ስልክን … ጨምሮ በአንዳንድ አገሮች እንደ ቤት፣ ምግብና የመሳሰሉትን) ለማግኘት የሚከፈል ነው፡፡ የግሉን ዘርፍ አገልግሎቶችና ምርቶች ለማግኘትም ከፍትሐዊ ግብይት ይልቅ ሙስናና አጭበርባሪነትን ማለፍ ግድ ብሏል፡፡

አገራችን ያለችበት ሁኔታም ከዚህ የተለየ ነው ሊባል አይችልም፡፡ እርግጥ እንደ ደቡብ አፍሪካና ላይቤሪያ ባሉት አገሮች ሙስና ዓይን ያወጣ  ላይባል ይችላል፡፡ ግን ቀስ በቀስ አደጋው አፈሩን እየገለጠ፣ ጥቂቶችን እያደለበ፣ ብዙኃንን እያማረረና እያንገላታ መሆኑን ደጋግሞ ማጤን አስፈልጓል፡፡ በእርግጥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግሥት የችግሩን መጠን ለሕዝቡ አሳይቶ ‹‹የመልካም አስተዳደር ዕጦትና ሙስናን ለማስተካከል እሠራለሁ፤›› ብሎ ተነስቷል፡፡ ግን አሁንም ሙስናን የት ድረስ ታግለነዋል? መጠየቅ ነው የዚህ ጽሑፍ ዓላማ፡፡

አሠራር ያልፈታቸው የሙስና ጉድጓዶች

ሙስናን መፈክር ስለደረደርን፣ ሌላው ቀርቶ ራሱ ፀረ ሙስና ኮሚሽንን በተቆጣጣሪ ብዛት ስላጥለቀለቅነው አናስወግደውም፡፡ ይልቁንም በግልጽነት፣ በተጠያቂነትና በቅልጥፍና ላይ የተመሠረተ አሠራር በመዘርጋት ለማዳከም ይቻላል፡፡

ለዚህ ሲባል በሲቪል ሰርቪሱ ውስጥ የሥነ ምግባር መርሆች ተነድፈዋል፡፡ እንደ ቢፒአር፣ ቢኤስሲ፣ የለውጥ ሥራ አመራርና የካይዘን ዘዴን የመሳሰሉ የማሻሻያ ሥራዎች በየጊዜው እየመጡ ተተግብረዋል፡፡ በአንዳንዱ አካባቢም ተለፍቶባቸው፣ ብዙ ሀብት ወጥቶባቸው በጎንዮሽ አልፈዋል፡፡ ስለዚህ በእነዚህ የለውጥና የዘመናዊነት አቅጣጫዎች የትኞቹ መሥሪያ ቤቶችና ባለሙያዎች ተቀይረዋል? እንዴት ያሉ የሥራ መሪዎች ተፈጥረዋል? ብሎ መመርመር ነው ተገቢ የሚሆነው፡፡

በቅርቡ የመንገድ ትራንስፖርት ጉዳይ አጋጥሞኝ በአዲስ አበባ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፋይልና ዋናው መሥሪያ ቤት በሚገኝበት ለገሐር ትራንስፖርት ባለሥልጣን ተገኝቼ ነበር፡፡ ይህ ነባር ሕንፃ እንደ ወትሮው ሁሉ በባለጉዳይ ከመሞላቱ በተጨማሪ ሊብሬ ዕድሳት፣ ሰሌዳ ማውጣት፣ ተላላፊ መጠየቅ፣ ሰሌዳ መቀየርና ቴክኒክ ማስወሰን … የመሳሰሉትን አገልግሎቶች የፈለጉ ዜጎች ትዕግሥት አጥተው በየቦታው ይቁነጠነጣሉ፡፡

በዚያ ተቋም በየመስኮቱ ተቀምጠው አገልግሎት የሚሰጡ አንዳንድ ወጣቶችና ካኪ ካፖርት ደርበው ወዲያ ወዲህ የሚሉት የቴክኒክ ምርመራ አረጋጋጮች ‹‹ይህን አምጣ!››  ሲሉ ይሉኝታ እንኳን አላየሁባቸውም፡፡ ማን ነው? ምንድነው? እንኳን ሳይሉ ወደ ተቋሙ የመጣውን ተገልጋይ እንደ ልጥ ይሞሸልቁት ይዘዋል፡፡ ያስገረመኝ ነገር ግን እጅግ ኋላቀር በሆነ የፋይል አያያዝ በመዝገብ ቤት የተደረደረው የክላሰር ፋይልን ለማግኘት (ለማውጣት ብቻ) ገንዘብ ወይም ልመናና ምልጃ የሚያስፈልገው መሆኑ ነው፡፡ እንግዲህ አስቡት በዚህ ኮምፒውተራይዝድ ዘመን አሠራሩ እንዴት ለሙስና አመቺ የሆነ ፉካ እንደፈጠረ፡፡

የአሠራር ነገር ሲነሳ እንደ አገር ዋነኛ የሙስና ምንጭ በሆነው የከተማ መሬት አስተዳደርና ማስተላለፍ ላይ ያለውን ችግር እንዲመለከት የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ በሥራዬ አጋጣሚ የሲቪል ሰርቪስ ተገልጋዮችን እርካታና ቅሬታ የሚያረጋግጥ ግብረ መልስ እሠራለሁ፡፡ በብዛትም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ክፍለ ከተማዎች በመገኘት ያለውን ሁኔታ የማጤን ዕድሉ አለኝ፡፡

ከመሬትና መሬት ነክ መረጃና አወሳሰን ጋር ያለው ችግር ታጥቦ የማይጠራ፣ ቀዳዳው ተደፍኖ የማያልቅ ይመስላል፡፡ ተገልጋዩም ጉቦ ሳይሰጥ የመሬት ጉዳይን እንደማይጨርስ ውስጡን አሳምኖ በአብዛኛው በሕጋዊ መንገድ ለሚያልቀው መብት ሁሉ በአሥር ሺዎች እየገፈገፈ መስተናገድን መርጧል፡፡

በቦሌ ክፍለ ከተማ የታዘብኩት ሁኔታ ይህን አባባል ያጠናክርልኛል፡፡ በክፍለ ከተማው አንዳንድ ወረዳዎች የአየር ካርታ ላይ የለም፣ መሬቱ በሕገወጥ የተያዘ ነው የተባሉት ቦታዎች ላይ ካርታና ስም ወጥቶባቸዋል (በተለይ ወረዳ 8 እና 10)፡፡ ሌሎች በተመሳሳይ የካርታና የግንባታ ፈቃድ ሲጠይቁ ግን ሊስተናገዱ አልቻሉም (ተገልጋሎዮች እንደሚሉት በመቶ ሺሕና በሚሊዮኖች ጉቦ ተጠይቀዋል)፡፡  በማኅበር በጋራ በወጣ የግንባታ መሠረት ላይ አንዳንድ ጉልበተኞችና ‹‹ጉቦ አቀባዮች›› ከፕላን ውጪ ወለል ጨምረው ፎቅ ይሠራሉ፡፡ እጅግ ያስገረመኝ ደግሞ በመንገድና በመልሶ ማልማት ዓይነት ሥራዎች ‹‹ይፈርሳል›› በሚል ማስፈራሪያ ቦታን በእጅ አዙር በማሸጥ የጥቅም ተጋሪ እየተሆነበት ያለው የወሮበላ አካሄድ ነው፡፡

እንደ ቂርቆስ፣ አራዳና የካ ባሉ ክፍለ ከተሞችም በቅርቡ በዚሁ በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ እንዳነበብነው መንግሥትን በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ያሳጡ የመሬት አስተዳደር ሙያተኞች ተከሰዋል፡፡ የወንጀላቸው መንስዔም በካሳ ክፍያ አሻጥር፣ የቀበሌ ቤትና ይዞታን በመሸጥ፣ ካርታ በማውጣት፣ ስም በማዞር፣ ሕገወጥ ይዞታዎችን ሕጋዊ በማድረግና የሕዝብ መሬትን በጉቦ ወደ ግል የማዞር … ዓይነት ዓይን ያወጡ ወንጀሎችን በመሥራት ነው፡፡

ታዲያ እነዚህ ወንጀሎች የሚሠሩት በዋናነት መረጃን በማጥፋት፣ በመደበቅና ተገልጋይን በማጉላላት ነው (በላቀ ጉዳይ ላይ ገንዘብ ለመቀበል ብቻ ለወራት የሚያመላልሱ አሁንም አሉ)፡፡ ሲቀጥል ከላይ እስከ ታች ሕገወጥ የጥቅም ትስስር በመዘርጋት ነው፡፡ ይኼም ባይሆን ባለጉዳይ ተበደልኩ ብሎ በመረጃ አስደግፎ ለኃላፊዎች ቅሬታ ሲያቀርብ እንዴት ሊፈታ የሚችል ይጠፋል? ስለዚህ ወይ የጥቅም ተጋሪነት አለ ወይም ፍርኃት ውሳኔ ሰጪነትን በቁሙ ቀብሮታል፡፡

ከእነዚህ ማሳያዎች አንፃር በሁሉም መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች አሠራር፣ አደረጃጀት፣ የሰው ኃይልና መመርያ የሚባሉት ነቁጦች ላይ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ሁሉም ቢሆኑ በግልጽነት፣ በተጠያቂነት፣ በቅልጥፍናና በፍትሐዊነት እንዲመሩ ማድረግ ካልተቻለ ያለጥርጥር ሙስና ፈቀቅ ሊል አይችልም፡፡ በነገራችን ላይ ፒውፕል ኤንድ ኮራፕሽን አፍሪካ ሰርቬይ 2015 የተባለው የትራንስፓረንሲ ጥራት እንደ ላይቤሪያ፣ ናይጄሪያ፣ ኬንያ፣ ቻድና ኮንጎ ባሉት አገሮች 69 በመቶ የሚሆነው ሙስና ያውም በደሃው ሕዝብ ላይ እየተፈጸመ ያለው በእነዚህ ችግሮች መሆኑን አረጋግጧል፡፡ የኢትዮጵያም ከዚህ ማነሱን እንጃ!?

ስግብግብነት ቅጥ አጥቷል

ሰው ሲበዛ መሬት ይጠባል፡፡ አገልግሎትና አቅርቦትም ያንሳል፡፡ በዚህ ላይ ስግብግብነትና አልጠግብ ባይነት ሲበረታ ሽሚያ፣ ንጥቂያና የሌላውን ድርሻ መብላት ይበረታል፡፡ ኢትዮጵያውያን ምንም እንኳን በሃይማኖቶቻችንና በባህሎቻችን ፈሪኃ ፈጣሪና ሞራላዊ ማንነት ያለን ቢሆንም፣ በተለይ በከተሞች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያቆጠቆጠ የመጣው በአቋራጭ የመክበርና ሕግና ሥርዓትን በገንዘብ የመጠምዘዝ ድርጊት ፈር እያሳተን ነው፡፡ ‹‹ሲሻም ያልበላን …›› ከማበረታታም በላይ የሄደ ነው፡፡

ከትንሿ የአሽከርካሪ ቅጣት አንስቶ እስከ ትልልቅ የኩባንያ ድርጅቶች የታክስና የጉምሩክ ሥራዎች ድረስ በጉቦ ለማስፈጸም የማይቋምጥ እስኪ ማነው? በእርግጥ አንዳንዱ ባለሥልጣን (ባለሙያ) ዓይኑን እያስለመለመ የ‹‹ስጡኝ›› ጥያቄውን በእጅ አዙር ሊያቀርብ ይችላል፡፡ እኛ ግን ስንቶቻችን ነን ‹‹ይኼ መብቴ ስለሆነ በዚህ ጊዜ ሠርተህ ስጠኝ፤›› ብለን በድፍረት የምንታገል?

 ለነገሩ በገቢዎችና ጉምሩክ፣ በመሬት አስተዳደር በድርጅቶች፣ በፈቃድ ዕድሳትና ብቃት ማረጋገጫ፣ በኤሌክትሪክ ኃይል ማከፋፈል … ሕገወጥ አካሄድን የሚከተሉ ባለጉዳዮች ሁሉ ጉቦ ካልከፈሉ ሕጉን እንደማይጥሱት ያውቃሉ፡፡ ለዚህም ሲባል ለድርድርና በእጅ ለመሄድ በራቸውን ክፍት ከማድረግ ባሻገር ‹‹ጉዳይ ገዳይ›› እና ደላላ እስከ መቅጠር የሚሄዱ ጥገኞች በርክተዋል፣ በዝተዋል፡፡

አሁን በቅርቡ ኢትዮጵያ ውስጥ በአንድ ጊዜ ‹‹የፓራሹት ቱጃር›› ስለሆኑ ሰዎች እየተጨዋወትን ነበር፡፡ ጉዳዩን በአርምሞ የሚታዘብ አንድ ወዳጄ ያስቀመጠልኝ ትዝብት ግን ‹‹እንዴት አይከበር›› እንድል ነው ያደረገኝ፡፡ ሰውየው በገቢዎች፣ በውልና ማስረጃ፣ በባንኮችና በመሬት አስተዳደር … ሁሉ በየጊዜው እንደ ወር ደመወዝ ጉቦ ተቆራጭ የሚያደርግላቸው ሠራተኞችና ኃላፊዎችን ‹‹ቅጥረኞች›› አድርጓል፡፡

ስለሆነም ምንም ዓይነት ጉዳይ ሲገጥመው እነዚያን የሕገወጥ ተባባሪ ሌቦች መሠረት አደርጎ በመንቀሳቀስ ‹‹ሀብት በሀብት ላይ›› ይደርባል፡፡ ለምሳሌ አንድ ሕንፃ ሲገዛ ወይም አንድ ድርጅት በድርድር ሲወስድ ውልና ማስረጃ የሚሄደው ለእሱ የሚመቸው አንድ ቅርንጫፍ ብቻ ነው፡፡ ይህን የሚያደርገው ደግሞ ከገቢዎች፣ ከመሬት አስተዳደርና ከባንክ … ማጣሪያ አምጣ የሚባሉ የተለያዩ ሰነዶች ባይሟሉ እንኳን ውሉ በቀላሉ ስለሚፀድቅለት ነው፡፡

እንግዲህ ተመልከቱት አንድ ሰው ከሀብታምነት ደረጃ በላይ አልፎ ተረጋግቶ ሕጋዊ ሥራ በመሥራት ለአገር የሚበጀውን መፈጸም ነው የሚጠቅመው? ወይስ ዕድሜ ልክ እየተሰቀቀ በሙስና ጭቃ ውስጥ መቡካካት፡፡

በዚህ የቱባ ጉበኞችን ገመና ጠቀስን እንጂ በሁላችንም አዕምሮ ውስጥ ጉቦ የመስጠት ልክፍት በምን ያህል ደረጃ አለ? የሚለውን ነው መጫን ያለብን፡፡ ስንቶቻችንን መብትና ግዴታችንን አውቀን እንወጣለን? ብንል ነው የሚጠቅመው፡፡ ሌላው ይቅር ጉቦ በመጠየቅ ያልሠሩበትን ለመዝረፍ መቆሚያ መቀመጫ የሚያሳጡን የመንግሥት ሌቦችን ደፍረን ለማስያዝ አስበን እናውቃለን? ወደ ሁላችንም አዕምሮ መምጣት ያለበት ጥያቄ ነው፡፡

በአጠቃላይ የሙስና ወንጀል ጎጂነት ላይ የምንስማማውን ያህል በጋራ መታገሉ ላይ ካልበረታን ለነገው ትውልድ የተሻለች አገር ልናስተላልፍ አንችልም፡፡ ስለዚህ ከወዲሁ በላቀ ሞራልና ሥነ ምግባር፣ በታታሪነትና ትጋት እንዲሁም በፀረ ሌብነትና በፀረ ሙስና ባህል ውስጥ ሆነን ቤታችንን እንሥራ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊዋን በኢሜይል አድራሻቸው hdebebe [at] yahoo.com ማግኘት ይቻላል፡፡