መልካም አስተዳደር እንዳይሰፍን የሚያለባብሱ የዴሞክራሲ አረሞች

በአሳምነው ጎርፉ

ኢትዮጵያ እንደ ጀመረችው የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ዕድገት ሁሉ አልሳካ ያላት መልካም አስተዳደርን ማስፈን ነው፡፡ አስተዳደርን መልካም ለማድረግ ደግሞ ዴሞክራሲያዊነት፣ የሕግ የበላይነትና ፈጠን ብሎም ፍትሐዊ ልማትን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡

ገዢው ፓርቲ ባለፈው ክረምት ባካሄደው ድርጅታዊ ጉባዔው የፀረ ሙስና ትግልን በማጠናከር፣ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባራትን በመፋለም መልካም አስተዳደርን ማስፈን አለብኝ ብሎ አቅዷል፡፡ ማቀድ ብቻ ሳይሆን ይህን ተግባር አለማሳካት ህልውናን ለአደጋ የሚያጋልጥ ክብተት ያስከትላል የሚል አቋም ወስዷል፡፡ ከዚያም ወዲህ በመንግሥታዊ መዋቅሩ ዕርምጃዎችን እየወሰደ፣ የጎላ ባይሆንም የማሻሻያ ፍላጎትን እየቀረፀ ስለመምጣቱም መንግሥት ይናገራል፡፡ ሕዝቡ በጎ ጅምር የሚላቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ ነገር ግን በሚፈለገው መጠን የሚታይ ነገር አለ?

አገሪቱ በዚህ ሒደት ውስጥ ብትሆንም አደገኛ ሊባሉ የሚችሉ አለመረጋጋት የፈጠሩ ሁከቶችና ቀውሶች ታይተዋል፡፡ በተለይ በኦሮሚያ ክልል ከአራት ወራት ላላነሰ ጊዜ የቀጠለው የሕዝብ ተቃውሞና ቁጣ ተቀስቅሷል፡፡ ይህን ተከትሎም ንብረት ያወደመና ውድ የሕይወት ዋጋ ያስከፈለ ብጥብጥና ውድመት አጋጥሟል፡፡ በትግራይና በአማራ ክልሎች አቤቱታዎች ተሰምተዋል፡፡ እንዲሁም በጋምቤላ ክልል መጠኑና ዓይነቱ ይለያይ እንጂ የበርካቶችን ሕይወት የቀጠፈ አደጋ ታይቷል፡፡

ይህ ከ1997 ዓ.ም. ወዲህ የመጀመሪያው ሊባል የሚችል ክስተት ብዙዎችን አሥግቷል፡፡ ለሞትና ለእስራት ከተዳረጉትም ሌላ ለሥጋትና ለጥርጣሬ የተጋለጡ ዜጎች እንዲኖሩም አድርጓል፡፡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አምስተኛ ዘመን አንደኛ ዓመት 14ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ የመንግሥታቸውን የስድስት ወራት ሪፖርት ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በአገሪቷ ለተፈጠረው ቀውስ ዋነኛው መንስዔ የመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ የሕዝብ አለመርካትና መንገላታት መበራከት መሆኑን በግልጽ ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ስለዚህም ወደዚያና ወደዚህ ስናስብ ኃላፊነቱን እንደ መንግሥት ወስደን ፈጥነን ከችግሩ ለመውጣት በቁርጠኝነት መነሳት አለብን ነው፤›› ያሉት፡፡

‹‹ሕዝቡ ፍላጎቱ እያደገ የመጣና ያለመርካት ደረጃ ላይ እየደረሰ ነው፡፡ መንግሥታዊ መዋቅሩ ደግሞ በሚፈለገው ደረጃ አገልግሎት ካለመስጠት ባሻገር፣ የሚታይበት የሙስናና ኢፍትሐዊ አካሄድ አለ፡፡ ይህን ለማሻሻል እየሠራን ቢሆንም ሕዝቡ ግን ቅሬታውን እየገለጸ ነው፡፡ በአንዳንድ አካባቢ በአፍ ብቻ፣ በሌላ አካባቢ ደግሞ በእጅ መገፍተርም ጀምሯል፡፡ … ስለዚህ ችግሩ በኦሮሚያ አካባቢ ብቻ ሳይሆን ከትግራይ ጫፍ እስከ ደቡብ ጫፍ የታየ ነው፤›› በማለት በግልጽ የተናገሩትም በዚሁ መድረክ ነው፡፡ ስለሆነው ሁሉ መንግሥት ይቅርታ እንደሚጠይቅ እስከማስረዳትን ጨምሮ፡፡

ከዚህ ውይይት በኋላ ለዚህ ጽሑፍ ዝግጅት ሲባል የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ለመናገር ሞክሬያለሁ፡፡ በተለይ ምሁራንና የፖለቲካ ሰዎችንም አስተያየት ከተለያዩ የመረጃ ምንጮች ለመውሰድ ጥረት አድርጌያለሁ፡፡

ከረዥም የፖለቲካ ዝምታ በኋላ በተከታታይ ወደ ኅትመት ሚዲያው እየወጡ ያሉት የቀድሞው የኢዴፓ ሊቀመንበርና የታዋቂው ፖለቲከኛ አቶ ልደቱ አያሌው ሐሳብ ግን በቀዳሚነት የሚወሰድ ነው፡፡ አቶ ልደቱ አሁን የተፈጠረውን የሕዝብ አለመርካት፣ ቅሬታና ብሶት የሚያያይዙት ከመልካም አስተዳደርና ከመንግሥት የአገልግሎት አሰጣጥ ብቻ ጋር አይደለም፡፡ ይልቁንም በአገሪቱ እየተዳከመ ከመጣው የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታና የሐሳብ ብዝኃነትን የማስተናገድ ብልህነት ከማጣት ጋር ነው ይላሉ፡፡

‹‹ገዢው ፓርቲ በአገር አቀፍ ደረጃ ከአባልና ከአጋር ፓርቲዎቹ ጋር ከሞላ ጎደል ሙሉ በሙሉ በሕዝብ ምርጫ አሸነፍኩ ብሎ ሥልጣን ላይ ደግሞ በቀጠለበት ጊዜ፣ ባሉት ጥቂት ወራት ውስጥ ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን ሕዝብ በዚህ ደረጃ ቅሬታ ሲያነሳ እርስ በርሱ የሚጋጭ እውነት አለ፤›› ነው ያሉት፡፡ በብሔር፣ በሃይማኖት፣ በታሪክ፣ በባህልና በተለያዩ ማኅበራዊ ፍላጎቶች የተለያየ ማኅበረሰብ አንድ የፖለቲካ አመለካከት ሊኖረው አይችልም፡፡ የአስተሳሰብ ብዝኃነት ብቻ ሳይሆን የአመለካከት ግጭትም ባለበት ሁኔታ ደግሞ ልዩነት ሆደ ሰፊ ሆኖ ማስተናገድ ካልተቻለ ቀውስ መጋበዙ እንደማይቀር አስምረውበታል፡፡

ይህንኑ ሐሳብ የሚጋሩት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁራንም አሉ፡፡ ዶ/ር ካሳሁን ብርሃኑና ወጣቱ የታሪክ ተመራማሪ አበባው አያሌው በቅርቡ ከአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ ጋር ባደረጉት ውይይት በአገሪቱ የሐሳብ ነፃነት፣ የመደራጀትና የፖለቲካ አስተሳሰብን በሕጋዊና ሰላማዊ መንገድ የማራመድ ዴሞክራሲያዊ መብቶች ማጠናከር ያስፈልገል፡፡ በዋናነትም ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድን ተከትሎ ሐሳብን ማራመድ ብቻ ሳይሆን፣ በሕዝብ ውሳኔ መመረጥ የሚቻልበት ቀስ በቀስም ሥልጣን እስከመያዝ የሚወስድ ሥርዓት ሥር እንዲሰድ መደረግ አለበት፡፡

ይህ የሥልጠና ባህል መጠናከር ካልጀመረ ለመንግሥት ብቸ ሳይሆን ለአገሪቱም ፈተና የሚጋርጥባት ሁኔታ ያጋጥማል ነው የሚሉት፡፡ በአንድ በኩል የመንግሥታዊ መዋቅሩን የግልጽነትና ተጠያቂነት፣ የሕግ የበላይነትና የሕዝብ ወገንተኝነት ለማረጋገጥና ለመሔስ የሚቻልበት ባህል እንዳይኖር ያደርጋል፡፡ ይህም መልካም አስተዳደር የሚባለውን ትልቅ ዕሴት ጥያቄ ውስጥ እየከተተው ይሄዳል፡፡ በሌላ በኩል መንገሥት ራሱ እንደ ተቋም የሚጠይቀውንና የሚገዳደረውን ሰላማዊ ኃይልና አማራጭ እያጣ፣ ሳይጠረጥርና ሳይገምት ወደሚገነፍል የሕዝብ ቁጣና ቅሬታ መጋፈጥ እንደሚወርድ አስምረው አስረድተዋል፡፡

በእርግጥም አሁን ላይ ሲታይ መልካም አስተዳደርን የማስፈን ተግባር ብቻውን ተነጥሎ የሚታይ አልሆነም፡፡ በመንግሥት የተለያዩ የሥራ ኃላፊዎች የሚገለጸውም ሆነ፣ በተለያዩ ሰነዶች ላይ የተጻፈው ልማትን በፍትሐዊነት ከማዳረስና የዴሞክራሲ ባህልን እየገነቡ ከመሄድ ውጪ ተነጥሎ የሚታይ የመልካም አስተዳደር ሥራ የለም የሚል ነው፡፡ ይሁንና ግን ወደ ተግባር ሲገባ መንግሥት በተለይ የዴሞክራሲ ምኅዳሩን ለማስፋትና የአስተሳሰብ ብዝሐነትን ለማስተናገድ የሚያስችሉ የፖሊሲ ማሻሻያዎችንም ሆነ የማስተካከያ ዕርምጃዎችን አልወሰደም፡፡

ብዙዎቹ የፖለቲካ ሰዎችና ምሁራን (በቅርቡ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የተወያዩትን ጨምሮ) የሚስማሙባቸው የዴሞክራሲ ሒደቱን የሚያደናቅፉ ችግሮችን እዚህ ላይ ማንሳት ለውጥ ለማምጣት ያግዛል፡፡ አንደኛው በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ እየነጠፈ የመጣው የአካዴሚ ነፃነት (Academic Freedom) ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ዓለም አቀፍ የትምህርት መርሆ ዜጎች በነፃነትና በገለልተኝነት ብቻ ሳይሆን፣ በፈጠራና በምርምር ብሎም በተወዳዳሪነት መንፈስ አገራቸውን እንዲገነቡ ሊያነሳሳ የሚችል እሳቤ ነው፡፡

‹‹በእኛ አገር ግን ይኼ የለም!›› ብለው የሚሞግቱ ጥቂት አይደሉም፡፡ መከራከሪያቸውም የየተቋማቱ የሥራ ኃላፊዎች ሹመት ብሔርና ፖለቲካዊ ታማኝነት መሆኑ፣ ተማሪዎችም ይሁኑ መምህራን በገዢው ፓርቲ አባልነት ሲደራጁ ሌላ የፖለቲካ አስተሳሰብን ማራመድ ወንጀል ተደርጎ መውሰዱ፣ ነፃና የተጠናከሩ የተማሪዎች አደረጃጀቶች አለመኖራቸው (እነዚህ በተለይ ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ትኩሳት አንፃር የነበራቸው ሚና ይታወቃል)፣ የሐሳብ ነፃነትን ለማረጋገጥ የሚረዱ ኅትመቶችና መድረኮች መጥፋት፣ ብሔር ተኮር ቡድንተኝነት እንጂ ዴሞክራሲያዊነትን የተላበሰ አገራዊ አንድነት በየተቋማቱ እንዲገነባ አለመፈለጉን በቁጭት ያነሳሉ፡፡ የፖለቲካ ካድሬዎች፣ ደኅንነቶችና የገዢው ፓርቲ ጽሕፈት ቤቶች (አስተባባሪዎች) በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ እንዳሉም ዶ/ር መረራ ጉዲና በቅርቡ ከጻፉት መጽሐፍ አንብበናል፡፡

ሌላው የዴሞክራሲ ባህል ግንባታውን እያወኩ ነው የሚባሉት በተለይ ከምርጫ 97 በኋላ ተነድፈው በሥራ ላይ የዋሉት ሕግጋቶች ጉዳይ ነው፡፡ የፕሬስ አዋጅ፣ የፀረ ሽብር ሕግ፣ የሲቪል ማኅበራትና በጎ አድራጎት ድርጅቶች አዋጅ ጋር በተያያዘ ለዓመታት እየተገለጹት ያሉት ሒሶች፣ መንግሥት የፖለቲካ ተገዳዳሪዎቹን ለማፈን፣ የሐሳብ ነፃነትና ብዝኃነትን ላለማስተናገድና የተለያዩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ግንባታ ጉዞ ማበርከት ያለባቸውን አስተዋጽኦ እንዳይወጡ የሚያደርጉ ናቸው የሚል ነው፡፡ በእርግጥ እነዚህን ሕግጋት አስመልክቶ መንግሥት የሚያነሳቸው መከራከሪያዎችም ከንቱ የሚደረጉ አይደሉም፡፡

‹‹በአገሪቱ የተረጋጋ ሰላምና አገራዊ ደኅንነት እንዲኖር ጠንካራ የፀረ ሽብር ሥራ መከናወን አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ የሕጉ መውጣት ወሳኝ ከመሆኑ ባሻገር ከተለያዩ ዓለም አገሮችም የተቀዳ ነው፤›› ይላል መንግሥት በቀዳሚነት፡፡ ይህ ብቻ ሰይሆን የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት ሕጉም ተጠያቂነትና ግልጽነትን ያዳብር እንደሆነ እንጂ ሊገድብ አይችልም በማለት፡፡ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም ሆኑ ዓለም አቀፍ ማኅበራት ለዜጎች ብቻ በተፈቀደው የፖለቲካ ተሳትፎ ውስጥ ‹‹ገብተው መፈትፈታቸውን›› መንግሥት እንደማይቀበል የሚያስረዳውም በይፋ ነው፡፡

ከእነዚህ እውነቶች ጀርባ ግን በጥልቀት መፈተሽ ያለባቸው የዴሞክራሲ አረሞች አሉ፡፡ አንደኛው የፀረ ሽብር ሕጉ ለአገራችን ደኅንነት ወሳኝ ቢሆንም ከዜጎች ነፃነት፣ ሐሳብን የመግለጽና የመንቀሳቀስ መብት ጋር እንዳይጋጭ የማጤኑ ጉዳይ አንድ ነገር ነው፡፡ በሽብርተኝነት የተጠረጠሩ ሰዎች አያያዝ፣ ፍተሻና እስርም ቢሆን ፍትሐዊና ቀልጣፋ የፍትሕ ሥርዓት ካላጀበው ሕጉ ራሱ ሌሎች እንደሚሉት አስፈራሪና ‹‹አሸባሪ›› መሆኑ አይቀርም፡፡ የዚህ ሕግ መውጣት በሰላማዊና በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለመታገል በሚዳክሩ የፖለቲካ ኃይሎችና በሕዝቡ በራሱ ውስጥ የፈጠረው አንድምታም ሊጤን ይገባዋል፡፡

ከመረጃ ነፃነትና ከፕሬስ ጋር በተያያዘም ከሙያ ሥነ ምግባሩና ከመርሆዎቹ ጋር የሚጋጩ የስም ማጥፋት፣ ብሔራዊ ጥቅምን መጉዳት፣ የሕዝቦች አንድነትን መሸርሸር … ዓይነት ድርጊቶች እንዲገቱ ሕጉ መርዳቱ አይታበልም፡፡ ያለጥርጥር ግን በተለይ የመገናኛ ብዙኃንን ኃላፊዎችንና ዋና አዘጋጆችን አጣብቂኝና ሥጋት ውስጥ ከትቷል፡፡ በተለይ ከፀረ ሽብር ሕጉ ጋር ተዳምሮ ሲታይ ብዙዎችን አስደንብሮ ከጨዋታ ሜዳው እንዳስወጣ የሚታወቅ ነው፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ መንግሥት ለሕዝብ መስጠት ያለበትን መረጃ በአግባቡ ከሕጉ አንፃር ይሰጥ ዘንድ የተቀመጡ ድንጋጌዎች አለመከበራቸው አሳሳቢ ሆኖ ዘልቋል፡፡ የመረጃ መስጫ ጊዜ፣ የተከለከሉና ያልተከለከሉ መረጃዎች፣ ከልካይ የሥራ ኃላፊዎችና ሙያተኞች ላይ መውሰድ ስላለበት ዕርምጃ … በግልጽ ቋንቋ የሠፈሩ አንቀጾች ቢኖሩም፣ በዚህ ጉዳይ ላይ የመጣው መሻሻል ይህን ያህል ደረት የሚያስነፋ አይደለም፡፡ ይህን ሕግ ለማስፈጸም የተቋቋመው የዕንባ ጠባቂ ተቋምም እስካሁን ‹‹ግንዛቤ ማስጨበጥ›› የተባለው ሥራ ላይ እንደቆመ ነው፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት በአገሪቱ ‹‹የልማታዊ ዴሞክራሲ አስተሳሰብ ልዕልናን አረጋግጣለሁ›› ብሎ የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ ነው፡፡ ነገር ግን የተለያዩ ፖለቲከኞችና ምሁራንን ጥያቄ እያስነሳ ያለው የ‹‹ልማታዊ›› መንግሥታዊ ሥሪት ዴሞክራሲያዊ ተባለም አልተባለም፣ ግራ ዘመምና የሊብራል አስተሳሰብን የሚፃረር ነው የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ ሲከራከሩም እሳቤው ነፃ ሐሳብ፣ ነፃ ማኅበር፣ ነፃ የፖለቲካ ድርጅቶች ነፃ ገበያ …. የሚባሉ የዴሞክራሲያዊነት ምሰሶዎችን በአንድም ይሁን በሌላ እንደሚገድብ ያሰምሩበታለ፡፡ ስለሆነም ነው ገዢው ፓርቲ እንደ ጨው የሌለበት ምንም ነገር የለም በማለት የሚተቹት፡፡

እዚህም ላይ ምሁራን የሚሰነዝሩት ምክረ ሐሳብ አለ፡፡ ባለፉት 25 ዓመታት (ሩብ ክፍለ ዘመን) በተለያየ መንገድ አገሪቱን እየመራ እዚህ ያደረሳት ኢሕአዴግ ነው፡፡ በሒደቱም በርካታ ጠቃሚና አበረታች ጅምሮችና የተገኙ በተለይ የልማት ፍሬዎች አሉ፡፡ በዚያው ልክም እንደ አገር ያጣናቸው (ወደብና የብሔራዊ አንድነት ዓይነቶቹን ያነሳሉ) ጉዳዮችም አሉ፡፡ ምንም ቢሆን ግን ከዚህ በኋላ ለሚነሱ የልማት፣ የዴሞክራሲም ሆነ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች እስካሁን በዘለቀው አካሄድ ብቻ መልስ ለመስጠት አይቻልም፡፡ ያለጥርጥር ማሻሻያዎች ያስፈልጋሉ ነው የሚሉት፡፡

የኢዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው ዶ/ር ካሳሁን ራሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሕዝቡ ፍላጎት ያለው መሆኑን፣ ስለሆነም በአገልግሎትና አስተዳደራችን አለመርካት ብቻ ሳይሆን እንደ ሙስናና ብልሹ አሠራር ይሉትን ያልተገቡ ድርጊቶች አልቀበልም የማለትና የመግፋት ተግባር ውስጥ ገብቷል ማለታቸው የለውጥን አስፈላጊነት ያመላክታል ነው ያሉት፡፡ እዚህ ላይ የሚያስፈልገው ማሻሻያ ግን በነካ ነካና ጥገናዊ ለውጥ ብቻ እንዲመጣ የሚፈለግ ሳይሆን፣ ሥርዓት ባለውና እያደገ በሚሄድ ብሎም ሁሉን አሳታፊ በሆነ አኳኋን ሊሆን ይገባል ባይ ናቸው፡፡

በቅርቡ በመልካም አስተዳደር ሰበብ በየአካባቢው የተነሳው የማስተር ፕላን፣ የማንነትም ይሁን የሥራ ዕድል ፈጠራ ጥያቄ ያለጥርጥር የሕዝብ ነው፡፡ ምንም እንኳን ከሰላማዊ ጥያቄነት እየወጣ ወደ ግጭትና ሁከት የሄደባቸው አካባቢዎች የደረሰው ጉዳት ብዙዎችን ቢያሳዝንም መነሻው የሕዝቡ ምሬት ነው፡፡ ይህን መንግሥትም ሳያቅማማ ተቀብሎታል፡፡ (በእርግጥም ህልውናቸው እንኳን ስለመኖሩ የማይታወቁት እነ ኦነግን ወይም አሜሪካና አውሮፓ ተኮልኩለው በማኅበራዊ ድረ ገጽ አሉባልታ የሚነዙት ቀሰቀሱት ብሎ ሙሉ በሙሉ መደምደም የሚጠቅም አይደለም፡፡ ሕዝቡንም መናቅ ይሆናል፡፡

ስለሆነም የሕዝብ ጥያቄ አሁንም በዴሞክራሲያዊ መንገድ ማዳመጥና ሕዝብን ባሳተፈ መንገድ መፈታት አለበት፡፡ በአንድ በኩል አሁን እንደተጀመረው የግጭት አካባቢዎችን ማረጋጋት፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ካለ አረጋግጦ ፈጣንና ሕዝብን የሚያሳምን ዕርምት መውሰድ፣ እንዲሁም ለወደመው የሕዝብና የዜጎች ሀብት የካሳና መሰል ሥራዎች መሥራት አለባቸው፡፡ በሌላ በኩል ከነካ ነካና ቁጥቁጥ ወጥቶ ሥር ነቀል የመልካም አስተዳደር ለውጥ ማስፈን ሥራ ውስጥ መገባት አለበት፡፡ አሠራርን በማሻሻልና በማዘመን፣ አደረጃጀትን በመፈተሽና በማጠናከር ብሎም ፈጻሚና አመራር በሆነው የሰው ኃይል ላይ ጠበቅ ያለ ብርበራ በማድረግ ለውጥ ማምጣት ያስፈልጋል፡፡

የዴሞክራሲያዊ ምኅዳሩን ለማስፋትም ሆነ በፌደራል ሥርዓቱ ውስጥ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር የሚያስችሉ ዕርምጃዎችም የግድ የሚያስፈልጉበት ጊዜ መጥቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት እስከ 40 ሚሊዮን የሚደርስ ወጣት (በኢሕአዴግ ዘመን የተወለደ) ይዘን ያለፈውን የታሪክ እድፍ በማውራት፣ የኢሕአዴግን የትጥቅ ትግል ድል ብቻ በመንገር ማርካት አይቻልም፡፡ የቀደሙትን ክፉና ፀረ ዴሞክራሲያዊ ዘመናት የቀመሳቸው ትውልድ የአሁኑን እንደሚያጣጥመው፣ የአሁኑ ትውልድ በእርካታ ሊንበሸበሽ አይችልም፡፡ እንዲያውም አንዳንዴ በባህላችንም ሥር ሰዶ እንዳለው ድሮን ናፋቂነት (ድሮ ቀረን ልብ ይሏል) የቀደሙትን ሥርዓት በጎነት እየመዘዘ አጀንዳ ሊያደርገው ይቻላል፡፡ በነገራችን ላይ ወደ መቃብር የወረደው የደርግ ሥርዓት ቁንጮ ሌተና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያምን እንኳን የሚያወድሱ ወጣቶች በማኅበራዊ ድረገጾች እንደ አሸን መፍላታቸውን አይታችኋልን?!

ከእነዚህ ደረቅ ሀቆች አንፃር ኢሕአዴግ ውስጡን ይፈትሽ፡፡ ካለ ዴሞክራሲያዊ ባህል ግንባታ መልካም አስተዳደር ሊታሰብ እንደማይችልም ይገንዘብ፡፡ ሁሉንም የፖለቲካ ኃይሎችን የሚያሳትፈበትን ምኅዳር ከምር ያስፋ፡፡ የዜጎችን ነፃ ሐሳብ፣ መደራጀት፣ መንቀሳቀስና የአመለካከት ብዝኃነትም ሳይዘነጋ ያስተናግድ፡፡ በፌዴራላዊ ሥርዓቱ ውስጥ እየተደነቀሩ የመጡ ፈተናዎችንም እየለየ ዴሞክራሲያዊ ኅብረ ብሔራዊነትን ያጠናክር፡፡ በዚህ ሒደት ዋነኛ ባለቤት የሆነው ሕዝብም ተሳትፎውን ያጠናክር፡፡ በዚህ ሁኔታ መንቀሳቀስ ሲቻል ነው ለመልካም አስተዳደር መስፈን እንቅፋት የሚሆኑ የዴሞክራሲ አረሞች የሚወገዱት፡፡

   ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡