ሕገ መንግሥታዊ ዴሞክራሲ እንዴት የሕዝብ ይሁንታ ማግኘት ይችላል?

በጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር)

ከዚህ በቀደመው ጽሑፌ ሕገ መንግሥታዊ ዴሞክራሲ በሌለበት በመራሔ መንግሥት ሰብዕና፣ በባህል፣ በሃይማኖት ወይም በኢኮኖሚያዊ ዕድገት ላይ የተመሠረተ ሕዝባዊ ይሁንታና ተቀባይነት ዘላቂና አስተማማኝ እንዳልሆነ ለማሳየት ሞክሬያለሁ። ሕዝባዊ ይሁንታና ተቀባይነት ለአንድ መንግሥታዊ ሥርዓት እጅግ አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁሜያለሁ። በዚህ ጽሑፍ ደግሞ ሕገ መንግሥታዊ ዴሞክራሲ በተለይም የብሔርና የሃይማኖት ብዝኃነት ባለበት ማኅበረሰብ የተረጋጋና ዘላቂ መንግሥታዊ ሥርዓት ለመገንባት ሁነኛው መንገድ እንደሆነ ለማሳየት እጥራለሁ።

የሕዝብ ይሁንታና ተቀባይነት፣ ሕገ መንግሥታዊ ዴሞክራሲ የሚሉት ጽንሰ ሐሳቦች ምን ማለት እንደሆኑ ቀደም ባሉት ጽሑፎቼ ስለገለጽኩ፣ በዚህ ጽሑፍ የጽንሰ ሐሳቦቹን ትርጉም ለማብራራት አልሞክርም። ይልቁንም በቀጥታ ሕገ መንግሥታዊ ዴሞክራሲ እንዴት የሕዝብ ይሁንታና ተቀባይነትን እንደሚያስገኝ ለመግለጽ እሞክራለሁ።

ሕገ መንግሥታዊ ዴሞክራሲ ዜጎች በቀጥታና በተዘዋዋሪ ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ ከማስቻሉም በላይ፣ ለመሠረታዊ የሰው ልጅ መብቶች ዋስትና ይሰጣል። እንዲህ ባለው ሥርዓት ውስጥ ያለ መንግሥት ሥልጣኑን የሚያገኘው በጦር ሜዳ ድል ስላደረገ፣ በጉልበት ከሌላው ስለበለጠና ስላሸነፈ አይደለም። በሕገ መንግሥታዊ ዴሞክራሲ የመንግሥት ሥልጣን ምንጭ ሕዝቡ በፈቃዱ የሰጠው ውክልና ነው። አነፃፅሮ፣ አወዳድሮ፣ አማርጦ፣ እገሌ ወይም እነ እገሌ ይወክሉኝ ብሎ ሕዝቡ በምርጫው የእንደራሴነት መብት የሰጣቸው ሰዎች ናቸው በሕገ መንግሥታዊ ዴሞክራሲ ሕዝቡን የሚያስተዳድሩት። የሥልጣኑ ባለቤት ሕዝብ ነው። መንግሥታዊ ሥልጣን ለጊዜውና በአደራ፣ በውክልና የተሰጠ ነው። ባለሥልጣኑ ራሱን በራሱ መሾም አይችልም። ባለሥልጣኑን የሚሾመው ባለሥልጣኑ የሚያስተዳድረው ሕዝብ ነው።

ስለዚህ ባለሥልጣኑ በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነትና ይሁንታ የማግኘት ዕድሉ ሰፊ ነው። እኛው ራሳችን የሾምነው፣ አስተዳድረን ብለን የወከልነው ቡድን ሥልጣን ይዞ ሲያስተዳድረን በፈቃዳችንና በስምምነታችን ላይ የተመሠረተ መንግሥታዊ ሥልጣን ስለሆነ ይሁንታችንን አንነፍገውም። በዚህ መልክ የተመሠረተ መንግሥታዊ ሥልጣን በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት የማግኘት ዕድሉ ሰፊ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ መረሳት የሌለበት ነገር ሕዝባዊ ውክልናው በጊዜ የተገደበ እንደሆነ ነው። ለዘለዓለም፣ ያለጊዜ ገደብ የሚሰጥ ውክልና ሳይሆን የዘመን ልክና ወሰን የተበጀለት ውክልና ነው።

ለማንም ግልጽ እንደሆነው ‹‹ሕዝብ›› የሚባል በአንድ ዓይነት መንገድ የሚያስብ፣ አንድ ዓይነት ጥቅምና ፍላጎት ያለው፣ በአንድ ድምፅ እገሌ ወይም እነ እገሌ ይወክሉኛል ብሎ የሚናገር ፍጥረት የለም። ሕዝብ የብዙ ግለሰቦች ጥርቅም፣ በብዙ ቡድኖች የተከፋፈለና በልዩነት የተሞላ ስብስብ ነው። እናም በአንድ አገረ መንግሥት ውስጥ ያለ ሕዝብ ሁሉ ማን ሊወክለው እንደሚገባና ማን ሥልጣን መያዝ እንዳለበት አይስማማም። በሕገ መንግሥታዊ ዴሞክራሲ ውስጥ ባለ የውክልና ዴሞክራሲ ደግሞ፣ የብዙኃኑ ሕዝብ ተወካዮች ሥልጣን መያዛቸው የማይቀር ነው። ስለዚህ ከብሔራዊ ማዕከላዊ መንግሥት ጀምሮ በክልላዊና አካባቢያዊ መንግሥትም ውስጥ ወኪሎቻቸው ብዙም ሥልጣን የማያገኙ ቡድኖችና ግለሰቦች ይኖራሉ። ታዲያ እነዚህ ግለሰቦችና ቡድኖች በሥልጣን ላይ ላለው መንግሥት ለምን ይሁንታቸውን ይሰጣሉ? ለምን የእነሱ ተፎካካሪ ወይም ባለጋራ የሆነው ቡድን ሥልጣን ይዞ ሳለ ለመንግሥታዊ ሥርዓቱ ታማኝ ይሆናሉ? በምርጫ ለተሸነፉ፣ በድምፅ ብልጫ ለተረቱ ወይም ለሚረቱ ወገኖች ሕገ መንግሥታዊ ዴሞክራሲ ምን ፋይዳ አለው?

ለዚህ ጥያቄ ብዙ ምላሾች አሉ። በመጀመሪያ ሕገ መንግሥታዊ ዴሞክራሲ ውስጥ አሸናፊነትም ሆነ ተሸናፊነት ጊዜያዊና አንፃራዊ መሆኑ ነው። የዛሬ ተሸናፊ ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ አሸናፊ የመሆን ዕድል አለው። ይህ የማሸነፍ ተስፋ ደግሞ ዛሬ የተሸነፈበትን ሥርዓት ሙሉ ለሙሉ እንዳይከፋበት ያደርገዋል። ዛሬ ብሸነፍም ነገ ላሸንፍ እችላለሁ ብሎ ሥርዓቱንና የዛሬውን አሸናፊ ይቀበላል። ‘ይሁን’ ብሎ በሥርዓቱ ይቀጥላል። ሽንፈቱ አንፃራዊ ነው ስንል መቶ በመቶ ወይም ፍፁም በሆነ ሁኔታ አይሸነፍም ማለት ነው። በዴሞክራሲያዊ ፉክክር በድምፅ አሰጣጡ ሒደት ቀንቶት ሥልጣን ባይጨብጥና መንግሥት ባይመሠርትም፣ በተለያየ መንገድ የሥልጣን ተካፋይ መሆኑ አይቀርም። በብሔራዊ ደረጃ ቢሸነፍም በክልል ወይም በአካባቢያዊ ምርጫዎች ሊቀናውና አሸናፊ ሊሆን ይችላል። ወይም በየትኛውም ደረጃ መንግሥት ለመመሥረት የሚያስችል ድጋፍ ባያገኝም ‘ተሸናፊው’ ወገን በምክር ቤት ውስጥ መቀመጫ ኖሮት ድምፁን ማሰማት ይችላል።

በሕግ ማውጣት ሒደትም ሆነ በሌሎች ሕዝባዊ ጉዳዮች ላይ ‘ተሸናፊው’ የውይይቱ አካል ሆኖ አመለካከቱን ማንፀባረቅ ይችላል። በዚህ የውይይትና የምክክር ሒደት በሚኖረው ተሳትፎ የአገሪቷ አስተዳደር ላይ ተፅዕኖ ማሳደር ይችላል። ስለዚህም የተሸናፊው ወገን ሽንፈት ጊዜያዊና አንፃራዊ ነው። በሕገ መንግሥታዊ ዴሞክራሲ መቶ በመቶ ሽንፈት፣ ሁሌ ማሸነፍ ወይም መሸነፍ የለም። ስለዚህ ተሸናፊው ወገን እንኳን ሥርዓቱንና በሥርዓቱ ሥልጣን የያዘውን መንግሥት ይሁን ብሎ የሚቀበልበት ምክንያት አለው።

ከዚህም በተጨማሪ በሕገ መንግሥታዊ ዴሞክራሲ ዜጎች መንግሥታዊ ሥርዓቱን እንዲቀበሉ የሚያደርጋቸው ሌላ ዋነኛ ምክንያት አለ። ይህም ለብዙኃኑ በሚያደላው የውክልና ዴሞክራሲ ሥርዓት የተሸነፉት ወገኖች መሠረታዊ መብቶች በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ዋስትና ማግኘታቸው ነው። ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ልቅና ገደብ የሌለው ዴሞክራሲ አይደለም። በሕገ መንግሥታዊ ዴሞክራሲ የሕዝብ ወኪሎች ሆነው የተሾሙ ሰዎች የሚያገኙት ሥልጣን በጊዜ ብቻ ሳይሆን በሥልጣኑ ይዘትና ልክም የተገደበ ነው። ሕግ የማውጣትም ሆነ የማስፈጸምና የመተግበር ሥልጣን በሕገ መንግሥቱ የተደነገገ ገደብ ይበጅለታል። ሥልጣን በምን ሁኔታ ሥራ ላይ መዋል እንዳለበት፣ የሥልጣኑ ገደብና ወሰን እስከምን ድረስ እንደሆነ በሕገ መንግሥቱ ይገለጻል። ይህንን ገደብና ወሰን ለማስከበር ደግሞ ባለሥልጣናቱን መቆጣጠሪያ፣ ከሥልጣን ገደባቸው ሲያልፉ ‘ሃይ’ የሚባሉበት መዋቅርና አግባብ ይዘረጋል። ባለሥልጣናቱ ለሕግ እንዲገዙ ይደረጋል። ሕግ የሚያወጡት ባለሥልጣናት ሳይቀሩ፣ እነሱንም ሆነ የሚያወጧቸውን ሕጎች ለሚገዛ የበላይ ሕግ እንዲታዘዙ ይደረጋል። ይህ ሕግ ሕገ መንግሥቱ ነው። ይህ ሕገ መንግሥት መሠረታዊ መብቶቹን ስለሚያስከብርለት በሕገ መንግሥታዊ ዴሞክራሲ ውስጥ የዴሞክራሲ ሒደቱ ተሸናፊም ዋስትና አለው። ስለዚህ ሥርዓቱን ይቀበላል፡፡ በሥርዓቱ አግባብ ሥልጣን ለያዘውም መንግሥት ይሁንታውን ይሰጣል።

በአገራችን ኢትዮጵያ ከንጉሣዊው ሥርዓት ጀምሮ በተደጋጋሚ ለከፋ ፖለቲካዊ ቀውስና ግጭት የሚዳርገን ሰፊና ዘላቂ የሕዝብ ይሁኝታና ተቀባይነት ያገኘ መንግሥታዊ ሥርዓት ልንገነባ አለመቻላችን ነው። በአገራችን ብዙ ብሔር፣ ብዙ ባህል፣ ቋንቋና ሃይማኖት አለ። ታሪካችን ግጭት፣ ጦርነትና ጉልበተኝነት የበዛበት ነው። እንደ ኢትዮጵያ ባለች አገር ባህልን፣ ሃይማኖትን ወይም ታሪክን መሠረት ያደረገ መንግሥታዊ ሥርዓት መገንባት አስቸጋሪ ነው። የጋራ የሆነ፣ የሚያስማማን፣ ለመንግሥታዊ ሥርዓቱ የሕዝባዊ  ይሁንታ ምንጭ የሚሆን ታሪክ፣ ሃይማኖትም ሆነ የጋራ ባህል የለንም። ኢሕአዴግ ላለፉት አሥራ ሦስት ዓመታት የተያያዘው ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገትን የመንግሥታዊ ሥርዓቱ ዋነኛ የይሁንታ ምንጭ የማድረግ ጥረትም ብዙ እክል እያጋጠመው ነው። ሕገ መንግሥታዊ ዴሞክራሲ በሌለበት ፈጣን፣ ዘላቂና ፍትሐዊ ልማት እንደ ኢትዮጵያ ባለች የብዝኃነት አገር ማምጣት አዳጋች ይመስለኛል።

ገና ከመነሻው በሕገ መንግሥታዊ  ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሕዝብ ይሁኝታን ያላገኘ መንግሥት ከሃያ ዓመት በኋላ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ እንሠለፋለን ብሎ ሕዝብን ለማግባባት ሲሞክር ተግዳሮቶቹ ብዙ ናቸው። የብሔርና የሃይማኖት ብዝኃነት ባለበት አገር የሕዝብ ይሁንታ በዱቤ አይገዛም። እንደዚህ ባለ አገር ዕድገቱ እስኪመጣ አምባገነናዊ አስተዳደርን በፀጋ ለመቀበል ያለው ፍላጎትና አቅም ውሱን ነው። በተለይም ዕድገቱና የሀብት ክፍፍሉ ፍትሐዊ አይደለም የሚል ጥርጥሬ ካለ ችግሩ ይከፋል። በዚያ ላይ ሁሌ ፋሲካ፣ ሁሌ ፈጣን ዕድገት የለም። በመሀል ላይ ኢኮኖሚው ሲንገዳገድ፣ ቀውስ ሲያጋጥመው፣ የኢኮኖሚው ቀውስ ወደ ከፋ አገራዊ ቀውስ እንዳያመራ ከኢኮኖሚ ዕድገት ውጪ የሆነ ፖለቲካዊ መደላድል ያስፈልጋል። ያ መደላድል ሕገ መንግሥታዊ ዴሞክራሲ ነው።

ስለዚህ ሕገ መንግሥታዊ ዴሞክራሲ የሕዝብ ተቀባይነትና ይሁንታ ያለው፣ የተረጋጋ መንግሥታዊ ሥርዓት ለመገንባት እጅግ አስፈላጊና ጠቃሚ ነው ብለን መደምደም እንችላለን። የሕዝብ ተቀባይነትና ይሁንታ የሚያስገኝ ሥርዓት ከመሆኑ በተጨማሪ ሕገ መንግሥታዊ ዴሞክራሲን ከሌሎች መንግሥታዊ ሥርዓቶች ይልቅ ተመራጭ የሚያደርጉት ሌሎች ብዙ ምክንያቶችም አሉ። የዜጎችን ነፃነትና ፖለቲካዊ እኩልነት፣ ሰብዓዊ ክብርና መሠረታዊ መብቶች ለማስከበር የተሻለ ሁኔታን መፍጠሩ ሕገ መንግሥታዊ ዴሞክራሲን ተመራጭ የሚያደርገው ሌላ ሁነኛ ተጨማሪ ምክንያት ነው። ታድያ በእነዚህ ምክንያቶች ላይ ተመሥርተን የተሻለ ነው፣ ተመራጭ ነው የምንለው ሕገ መንግሥታዊ ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ ተግባራዊ መሆን ጀምሯል ከተባለ ከሃያ ዓመት በላይ ቢሆንም፣ በተጨባጭ ሕገ መንግሥታዊ ዴሞክራሲ በአገራችን አለ ማለት ዛሬም አንችልም። ለሕገ መንግሥታዊ ዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ መነሻ የሚሆን ሕገ መንግሥት አለን። ፍፁም ነው ባይልባልም፣ መሻሻልና መጠናከር የሚያስፈልጋቸው ነገሮች ቢኖሩም የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ሕገ መንግሥታዊ ዴሞክራሲ ለመገንባት መሠረት ሊሆን የሚችል ሰነድ ነው።

ሆኖም ሕገ መንግሥቱ  በሚገባ በሥራ ላይ ውሎ፣ በበቂ ሁኔታ ተተግብሮና ተከብሮ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ልንገነባ አልቻልንም። ሕገ መንግሥቱ ያካተታቸውና ሕገ መንግሥታዊ ዋስትና ተሰጣቸው የሚባሉት መብቶች በስፋት እየተጣሱ ይገኛሉ። ሕገ መንግሥቱ ሁሉም ሰው በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደኅንነት መበት፣ የነፃነት መብት፣ ጭካኔ ከተሞላበት፣ ኢሰብዓዊ ከሆነ ወይም ክብሩን ከሚያዋርድ አያያዝ ወይም ቅጣት የመጠበቅ መብት አለው ይላል። የግል ሕይወት የመከበር መብት (በስልክና በኢንተርኔት የሚደረጉ ግንኙነቶች ግላዊነት አለመደፈርን ጨምሮ)፣ የሃይማኖት፣ የእምነትና የአመለካከት ነፃነት የማንኛውም ሰው መብቶች ናቸው ይላል፡፡ ሕገ መንግሥቱ ከዚያም አልፎ ዜጎች የፈለጉትን አመለካከትና ሐሳብ በነፃ የመያዝና ሐሳባቸውን የመግለጽ መብት አላቸው፡፡ የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሠልፍ የማድረግ፣ አቤቱታ የማቅረብ መብት አላቸው፡፡ የመደራጀት፣ ፍትሕ የማግኘት፣ የመመረጥና የመምረጥ መብት አላቸው ይላላል፡፡ ሕገ መንግሥቱ።

 እነዚህ መብቶችን በተጨባጭ በእውነትም እንዲከበሩ ያስደረገ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት በኢትዮጵያ ተገንብቶዋል ብሎ ከልቡ የሚያምን፣ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ የሚከታተል ብዙ ሰው ያለ አይመስለኝም። የሚጣሱት መብቶች መብዛትና የመብት ጥሰቱ ልክና ተደጋጋሚነት በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጡት መሠረታዊ መብቶች በተጨባጭ መብቶቻችን ናቸው ማለትን አዳጋች አድርጎታል። ይህንን እውነታ በአፋችን የምንክድ ሰዎች ሳንቀር ሀቁን በውስጣችን ስለምናውቀውና ኅሊናችን የሚመሰክርልን  ስለሆነ፣ ሕገ መንግሥታዊ መብቶች በስፋት ቸል አየተባሉና እየተጣሱ ስለመሆኑ ብዙ ሐተታ ማብዛት የሚያስፈልግ አይመስለኝም። እነዚህ መብቶች መጣሳቸው ብቻ ሳይሆን መብቱ የተጣሰበት ግለሰብ ወይም ቡድን አቤቱታ አቅርቦ ፍትሕ የሚያገኝበት ነፃ የፍርድ አደባባይ አለመኖሩም ግልጽ ነው። ይኼውም በሃያ ምናምን ዓመታት መንግሥት ሕገ መንግሥታዊ መብቴን ጣሰብኝ ብሎ ተሟግቶ የረታ፣ መብቱ የተከበረለት፣ ኢሕገ መንግሥታዊ የሆነን ሕግና አስተዳደራዊ ውሳኔ በፍርድ አደባባይ፣ በሕግ ሙግት  ያስለወጠ ሰው እስከዛሬ የለም ማለት በሚያስችል ደረጃ እጅግ ብርቅ መሆኑ ነው። አካሄድህ፣ ያወጣሃው ሕግ ወይም አስተዳደራዊ ውሳኔ ከሕገ መንግሥቱ ይጣረሳል ተብሎ መንግሥት ሲወሰንበት አይታይም። በአጠቃላይ ሕገ መንግሥቱ ለመንግሥታዊ ሥልጣን ልጓም ሆኖ ሥልጣን ሲገድብና መብት ሲጠብቅ አናይም።

ከዚህም በተጨማሪ ‹‹ዴሞክራሲ›› እንደናፈቀን፣ እንዳማረን የውኃ ሽታ ሆኖ ቀርቷል። የተለያዩ አመለካከቶች፣ አስተሳሰቦችና ፍላጎቶች ባሉበት አገር የሕዝብ ተወካዮች ምርጫ ሲካሄድ በአካባቢ ምርጫ፣ በክልልና በፌደራል ምክር ቤት ምርጫዎች ሁሉ አንድ ግንባርና አጋሮቹ ብቻ ‹‹አሸናፊ›› ሆነው ሕዝብ የሚሳተፍበትና  የሚወከልበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አለን ማለት ዘበት ነው። የፓርቲዎች ቁጥር ስልሳ ነው፣ ሰባ ነው በሚባልበት የዘጠና ምናምን ሚሊዮን ሕዝብ አገር አንድም የገዥው ግንባር ተቀናቃኝ የሐዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል መሆን አቅቶት፣  ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ላይ ነን ማለት ስለበቅሎ ምጥ ማውራት ነው። የማይመስል፣ የማይዋጥ፣ ደረቅ ፕሮፓሰጋንዳ ነው። ሕገ መንግሥታዊ ዴሞክራሲ በተግባር፣ በተጨባጭ የለንም። ይልቁን ይህንን እውነታ አምነን ሕገ መንግሥታዊ ዴሞክራሲ የሌለን ለምንድነው? ሕገ መንግሥታዊ ዴሞክራሲ በእውነት ያስፈልገናል ወይ? የሚያስፈልገን ለምንድነው? ይጠቅመናል ወይ? ሕገ መንግሥታዊ ዴሞክራሲን እንዴት መገንባት እንችላለን? በሚሉት ጥያቄዎች ዙሪያ ብንወያይ ሳይሻል አይቀርም። በኢትዮጵያ ለሕገ መንግሥታዊ ዴሞክራሲ የማይመቹና ተግዳሮት የሆኑ ብዙ ነገሮች አሉ። እናም ጎራ ለይተን ከመወጋገንና ከመጠፋፋት ይልቅ ልበ ሰፊ ሆነን ብንወያይ፣ ብንመካከር ለብዙ ችግሮቻችን መፍትሔ ማግኘትና በአገራችን ጠንካራ ሕገ መንግሥታዊ ዴሞክራሲ መገንባትም እንችላለን።

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የሕገ መንግሥት ኤክስፐርትና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት መምህር ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው gediontim [at] gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡