ሕገወጥ ዝውውርን ለመከላከል ሕግ እንደመፍትሔ

በዚህ ሰሞን በየዕለቱ የምንሰማቸው ዜናዎች ከስደት ጋር የተያያዙና ተጨማሪ የስቃይ መርዶዎች ናቸው፡፡ ከሊቢያ ወደ አውሮፓ ሲሄዱ በሜዲትራኒያን ባህር ከሰመጡት ውስጥ ሰባት ኢትዮጵያውያን መሞታቸውን የተረዳነውም በዚህ ሰሞን ነው፡፡ የሕገወጥ ስደት ገፈት ቀማሽ የሆነችው አገራችን ከምንጊዜውም በተሻለ ሰፊ ሥራ የሚጠበቅባት ጊዜ አሁን ነው፡፡ የማንኛውም መፍትሔ መነሻ ምክንያቱንና መሠረታዊ ችግሩን መርምሮ መረዳት ነው፡፡ ችግሩ ከታወቀ መፍትሔውን መፈለግ ብዙ አስቸጋሪ አይሆንም፡፡

ሰው የሚወደውን አገር የሚለቅበት ምክንያት ምንጭ ሁለት መልክ ሊኖረው ይችላል፡፡ የመጀመርያው ከአገር የሚገፉ ምክንያቶች ሲሆኑ ሁለተኛው ደግሞ ከውጭ የሚጠሩት ምክንያቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ‹Pushing and Pulling Factors› ብለን ልንጠራቸው የምንላቸው ናቸው፡፡ የመጀመርያው ምክንያት ኢትዮጵያውያን ብዙ መከራ መኖሩን እየሰሙና እያዩ አገር ለመልቀቅ ምን አነሳሳቸው?  በአገራቸው በሙሉ ክብር ለመሥራትና የተሻለች አገር ለማድረግ ለምን አይጥሩም? ለሚለው ጥያቄ መልስ መስጠት ነው፡፡ ለስደት መነሻ ሊሆኑ የሚችሉ ችግሮችን ለምሳሌ ድህነትን፣ ሥራ እጥነትን፣ መድልኦን፣ የሰብዓዊ መብት ረገጣንና የመልካም አስተዳደር እጦትን ወዘተ፣ መታገልና ማሸነፍ መፍትሔ መሆኑ አከራካሪ አይሆንም፡፡ ይህ በአንድ ጊዜ የማይሠራና በሒደት ሰፊ ጥረት የሚፈልግ በመሆኑ አሁን በዚህ ሰሞን የምንመለከተውን ሰቆቃ ወዲያውኑ ላያስቆም ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ ችግሩን ለዘመናት ተሸክመነው እንዳንኖር መንግሥት የተለየ ትኩረት በመስጠት የተሻለች ኢትዮጵያን፣ ዜጎቿ በአገራችው ለመኖር ተስፋ የሚያደርጉባትና ምቹ እንድትሆን ሰፊ ጥረት ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡

ሁለተኛው ምክንያት ከውስጥም ሆነ ከውጭ ያሉ ምክንያቶች የስደትን በጎ ገጽታ ብቻ የሚሰብኩ ሁኔታዎችን ማስተካከል ነው፡፡ ውጭ አገር መሄድ ድሎት እንደሆነ፣ ሀብት ላይ መውደቅ እንደሆነ የሚሥሉ ስደተኛ ዘመዶችን፣ ሕገወጥ ደላሎችንና ነጋዴዎችን መታገል ሁለተኛው አማራጭ ነው፡፡ የሕግ አስፈላጊነት ከዚህኛው የችግሩ ምንጭ ጋር በበለጠ ይያያዛል፡፡ የስደተኞቹን ሕጋዊና ሰብዓዊ መብቶች መጠበቅ፣ በውጭ አገር ሥራ ለመሥራት የሚሄዱ ወገኖችን ጉዳይ የሚከታተሉ ተቋማትን ማጠናከር፣ ለዜጎች የተሻለ ጥበቃ የሚሰጥ የፖሊሲና የሕግ ማዕቀፍ መቅረፅ፣ ሕገወጥ ደላሎችን መቅጣት፣ ችግሩን ለመቅረፍ ሥራ ላይ የሚወጡ ሕግ ተኮር መፍትሔዎች ናቸው፡፡ በዚህ ጽሑፍ ከሕግ ማዕቀፍ ጋር በተያያዘ ያሉንን መርሆች፣ አፈጻጸማቸውንና ክፍተታቸውን በመመልከት ወደፊት ችግሩ በመሠረታዊነት ለመቅረፍ የሚያስችሉ መፍትሔዎች ለመጠቆም እንሞክራለን፡፡

የሕግ መነሻ መለያየት

ሕገወጥ ስደተኞችን የተመለከቱ ሕግጋት መነሻ እንደ አገሮቹ ፖሊሲ የሚለያይ ሲሆን፣ ሁለት ዓይነት አቅጣጫ ሊይዝ እንደሚችል ምሁራን ይተነትናሉ፡፡ አንዳንድ ምሁራን ለሕገወጥ ስደት ምክንያት የሆኑ ደላሎችና አዘዋዋሪዎችን መቅጣት ላይ ያተኩራሉ፡፡ በዚህ መሠረት ደላሎቹ ወይም የሥራ ግንኙነትን የሚያሳልጡ ወገኖች በወንጀል እንዲጠየቁ የሚደረግበትን ጠንካራ የሕግ ማዕቀፍ እንዲቀረፅ ያቀነቅናሉ፡፡ ወንጀሎቹን በዓይነት በመለየት መደንገግ፣ ቅጣቶቹን ማጠናከርና ሕግ አስፈጻሚ አካላትን ጠንካራ አድርጎ ማደራጀት ላይ ቅድሚያ ይሰጣሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ወንጀሉን ከመቆጣጠር ጎን ለጎን የስደት መከላከል ፖሊሲን ጠንካራ በማድረግ ዜጎች ያላግባብ ከአገር እንዳይወጡ ቁጥጥር የሚደረግበትን ማዕቀፍ ያበጃሉ፡፡

ሁለተኛው ዘዴ ደግሞ መብትን መሠረት ያደረገ የሕግ ማዕቀፍ ማዘጋጀት ሲሆን ስደተኞች ከአገር የሚወጡት፣ በጉዞና በውጭ አገሮች የሚደርስባቸው ስቃይ የመብት ጥሰት በመሆኑ ሕገወጥነትን የመከላከሉም አቅጣጫ መነሻ ማድረግ ያለበት ስደተኞቹን ነው የሚል ነው፡፡ ከመጀመርያው አቅጣጫ አንፃር ይኼኛው ከስደት ጋር የተያያዙ ችግሮች በሙሉ ከሰብዓዊ መብት ጥሰት ጋር የሚያያዙ በመሆኑ የሚቀረፁ ፖሊሲዎችና ዕርምጃዎች ስደተኛውን መሠረት ያደረገ ሊሆን ይገባል ይላሉ፡፡ የመጀመርያው አቅጣጫ ስደተኞች የኢሚግሬሽን ሕግን የሚያነሱ፣ ለስደተኞች መብትና ጥቅም በቂ ቦታ የማይሰጥ ከመሆኑ በላይ ለስደት መነሻ የሚሆኑ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶችን የማያደርቅ ነው የሚል ትችት ይደርስበታል፡፡

ሰብዓዊ መብትን መሠረት በማድረግ ሕገወጥ ስደትንና ዝውውርን የመዋጋት አቅጣጫ ግን ሕገወጥ ደላሎችን በሕግ ተጠያቂ ከማድረግ ጎን ለጎን የስደተኛውን ምሉዕ የሰብዓዊ መብት ጥበቃ መስጠት ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት የአፈጻጸም ሥርዓት ጠንካራ አለመሆኑና በሕገወጥ ዝውውር ከመንግሥት ውጪ ያሉ ቡድኖች መሳተፋቸው ሁለተኛውንም አቅጣጫ ብቻውን ፍፁማዊ መፍትሔ እንዳይሆን ያደርገዋል፡፡ አሁን አሁን አገሮች ሁሉንም አቅጣጫዎች በማካተት ሕግጋታቸውንና የኢሚግሬሽን ፖሊሲያቸውን ይቀርፃሉ፡፡ የአገራችንም የሕግ ማዕቀፍ ምሉዕነት ቢጎድለውም ሁለቱንም ማለትም ሕገወጥ ደላላውንም በሕግ ተጠያቂ ማድረግ፣ ስደተኛውም መብቱ የሚከበርበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ጥረት ያደርጋል፡፡

የፖሊሲ ማዕቀፍ አስፈላጊነት

ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ውስብስብ ችግር እንደመሆኑ ሰፋ ያሉ ማኅበራዊ፣  ኢኮኖሚያዊና ሕጋዊ ጉዳዮችን ይዳስሳል፡፡ ከሥነ ጾታ፣ ከትምህርት፣ ከሥራ፣ ከስደት፣ ከጤና፣ ከባህል፣ ከሰብዓዊ መብት ብሔራዊ፣ አኅጉራዊና ዓለም አቀፍ አጀንዳዎች ጋር ይያያዛል፡፡ እነዚህን ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች በአግባቡ ወጥነት ባለው መልኩ ለማስተናገድ አገሮች ስደትን የተመለከተ የፖሊሲ ሰነድ ያዘጋጃሉ፡፡ በዚህ ረገድ በአገራችን ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለይቶ በስፋት የሚመለከት ፖሊሲ የለም፡፡ የተለያዩ ፖሊሲዎች በአንድም በሌላ ችግሩን ከመነካካት ውጪ አድምተው መነሻና መድረሻውን፣ አገሪቱ ቅድሚያ የምትሰጣቸውን ወሳኝ ነጥቦች ተራ በተራ የሚተነትን ሰነድ የላትም፡፡ ስለዚህ ችግሩን በዘለቄታው ለመፍታት የፖሊሲ አስፈላጊነት ቸል ሊባል አይገባም፡፡

የሕግ ማዕቀፍ ምሉዕነትና ጠንካራነት

ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን የተመለከቱ ዓለም አቀፍና ብሔራዊ ሕግጋት በአግባቡ ከተቀረፁ ችግሩን ለመቅረፍ ያላቸው አስተዋጽኦ የታመነ ነው፡፡ አገራችን ከስደተኞች መብቶች ጥበቃ አንፃር የሰዎችን መብቶች የሚያስጠብቁ ጠቅላላና ልዩ የሰብዓዊ መብቶች ስምምነት አፅድቃለች፡፡ ስምምነቶቹ በአገሪቱ የሕግ አውጭ አካል በልዩ ልዩ ዝርዝር ሕግጋት እንዲካተቱ ቢደረግና አፈጻጸማቸው ቢጠናከር ተፅዕኗቸው ቀላል አይደለም፡፡ ሕገ መንግሥቱም የሰብዓዊ መብቶችን ዕውቅና ከመስጠት ባለፈ በአንቀጽ 18 (2) ለማንኛውም ዓላማ በሰው የመነገድ ተግባር የተከለከለ መሆኑን መደንገጉ ለዝርዝር ሕግጋት ጠንካራ ሕገ መንግሥታዊ መሠረት ነው፡፡ በተጨባጭ መብቶቹን በመዘርዘርና በተደራሽነት ሕገወጥ ዝውውርን ለመከላከልና ለመቆጣጠር አስተዋጽኦ ያላቸው ሕግጋት የወንጀል ሕጉና የሥራና ሠራተኛ ማገናኘት አገልግሎት አዋጅ ቁጥር 639/2001 ዓ.ም. ናቸው፡፡ እነዚህ ሕግጋት እንደ ቅደም ተከተላቸው በሰዎች መነገድንና ሕገወጥ ዝውውርን ወንጀል በማድረግ፣ ለሥራ ውጭ አገር የሚሄዱ ዜጎችን መብትና የአገናኞቹን ግዴታ በመዘርዘር ከቀድሞዎቹ የተሻሉ ጠንካራ የሕግ ማዕቀፍ ናቸው፡፡

የወንጀል ሕጉ ሕገወጥ ዝውውርን የሚከለክሉና ፈጻሚዎቹን የሚቀጡ ድንጋጌዎችን አካቷል፡፡ አንቀጽ 596 (ሰውን አገልጋይ ማድረግ)፣ 597 (በሴቶችና በልጆች መነገድ)፣ 598 (በሕገወጥ መንገድ ኢትዮጵያውያንን ለሥራ ወደ ውጭ አገር መላክ)፣ 635 (ሴቶችንና ሕፃናትን ለሴት አዳሪነት በማቃጠር መነገድ) ድርጊቶችን ወንጀል በማድረግ፣ ከአምስት እስከ 20 ዓመት የጽኑ እስራት ቅጣት በመደንገግ ከቀደመው የወንጀል ሕግ የተሻለ ቢሆንም ሕጉ ክፍተት አለበት፡፡ ለሕገወጥ ዝውውር በምልዓት ፍቺ (ትርጉም) አለመስጠት፣ ከሴቶችና ከሕፃናት ውጪ በወንዶች ላይ ሲፈጸም ወንጀሉ በሕጉ ልዩ ድንጋጌ እንዲሸፈን አለማድረጉ፣ በሕጉ የተቀመጡት ቅጣቶችም ከሌሎች ወንጀሎች አንፃር የቅጣት መጠናቸው ጠንካራ አለመሆኑ እንደ ክፍተት ይነሳል፡፡

ከዚህ ሰሞኑ የሊቢያ እልቂትና የደቡብ አፍሪካ ጭፍጨፋ በኋላ በሕገወጥ ዝውውር ተሳታፊ የሚሆኑትን አካላት የሚቀጡ የወንጀል ድንጋጌዎችን ለማሻሻል የፍትሕ ሚኒስቴር ማሰቡ እነዚህን ክፍተቶች ለመሸፈን ይመስላል፡፡ እንደ ፍትሕ ሚኒስቴሩ ገለጻ የወንጀል ሕጉ ምሉዕ እንዲሆን ተደርጎ ይሻሻላል፣ በሕጉ የተቀመጠው ቅጣትም ጠንካራና ከወንጀሉ ጋር ተመጣጣኝ እንዲሆን ይደረጋል፡፡ ፍትሕ ሚኒስትሩ የሕግ ጥናቱ በመካሄድ ላይ እንዳለና በዚህ ወር መጨረሻ ረቂቁ ተዘጋጅቶ ለባለድርሻ አካላት ለውይይት እንደሚቀርብ የተናገሩ ቢሆንም ጉዳዩ ካለው አንገብጋቢነት፣ ትልቅነትና ውስብስብነት አንፃር በጥሞና መታየት ያለበት መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም፡፡

የሥራና ሠራተኛ ማገናኘት አገልግሎት አዋጅ ቁጥር 632/2009 ለኤጀንሲዎች ፈቃድ የሚሰጥበትን ሁኔታ በመዘርዘር፣ የሠራተኞችን መብቶች የሕግ ዋስትና በመስጠትና ሕገወጥ ዝውውር የሚያካሂዱትንና ሕግን የማያከብሩትን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ድንጋጌዎችን የያዘ በመሆኑ ከቀድሞዎች የተሻለ ነው፡፡ አዋጁን መሠረት አድርጎ መንግሥት ለ400 ያህል የግል ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ፈቃድ ሰጥቷል፡፡ ግለሰቦችም በመካከለኛው ምሥራቅ በተወሰኑ ደረጃ ለመቀጠር የቻሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ይሁን እንጂ በተደጋጋሚ እንዳስተዋልነው በሕጋዊም ሆነ በሕገወጥ መንገድ ከአገር እየወጡ ባሉ ኢትዮጵያውያን ላይ እየደረሰ ያለው አደጋ (የመብት ጥሰት፣ ብዝበዛ፣ ሞት፣ የአካል ጉዳትና የአካል መጓደልና እንግልት ወዘተ) ተባብሶ ቀጥሏል፡፡ ግለሰብ ነጋዴዎች በዜጎቹ ሰቆቃ መጠን የሌለው ትርፍ አጋብሰዋል፡፡ በሕጉ ይዘት የተደነገጉት አታሽ መመደብ፣ ካሳ መክፈል፣ የሠራተኞቹን ወጪ መሸፈን፣ ለሠራተኛው መረጃ መስጠት፣ ሠራተኛውን በሰላም ወደ አገር መመለስ ወዘተ፣ የማይፈጸሙ የወረቀት ማድመቂያ ሆነዋል፡፡ መንግሥት ሕጉን ማስተግበር ካለመቻሉ በላይ በተግባር የሚደርሰውን እልቂትና ጉዳት መቆጣጠር ባለመቻሉ ወደ ዓረብ አገሮች የሚደረገውን ዝውውር አግዶታል፡፡ ያም ሆኖ ግን አሁን ድረስ በሕገወጥ መንገድ ወደ ሞት የሚተሙት ኢትዮጵያውያን ቁጥር ብዙ ሆኗል፡፡

አዋጁን ለማሻሻል መንግሥት ጥረት በማድረግ ላይ ሲሆን፣ ረቂቅ ሕጉ በሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ተረቅቆ ባለፈው ወር ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ተልኳል፡፡ በረቂቁ ማብራሪያ ላይ እንደተቀመጠው ሕጉ ለማሻሻል ምክንያት ናቸው የተባሉ ምክንያቶች ተዘርዝረዋል፡፡ ምክንያቶቹ በኤጀንሲዎች ከታዩ ክፍተቶች፣ ሠራተኞቹ ሊያሟሉ ከሚገባቸው መሥፈርቶችና ከተቆጣጣሪው አካል ጥንካሬ ጋር የተያያዙ ነው፡፡ ኤጀንሲዎቹ ተገቢ ዕውቀትና ልምድ አለመኖራቸው፣ በዋስትና የሚያስይዙት ገንዘብ ማነሱ፣ ሲያጠፉ የሚወሰድባቸው ዕርምት ጠንካራ አለመሆኑ፣ ሠራተኞቹ የሙያ ሥልጠና አለመውሰዳቸው፣ የተቆጣጣሪው አካል ራሱን የቻለ አለመሆኑና ሕግጋትን በብቃት ለመፈጸም አለመቻሉ ለአዋጁ መረቀቅ ምክንያት መሆናቸው ተገልጿል፡፡ ረቂቅ ሕጉ የሌሎች አገሮችን (ፊሊፒንስ፣ ህንድ፣ ሲሪላንካና ባንግላዴሽ) ተሞክሮን ያካተተ ሲሆን፣ አዳዲስ ሐሳቦችን አካቷል፡፡ ከነዚህ ውስጥ በውጭ አገር ስምሪት አገልግሎት ከግሉ ሴክተር በተጨማሪ የመንግሥት ተሳትፎ ከፍተኛ መሆን፣ የግል ኤጀንሲዎች የሚያሟሉት መሥፈርቶች (100,000 ዶላር ለግል ኤጀንሲ ዋስትና ማስያዝን ጨምሮ) ጠንካራ ሆኗል፣ ሌበር አታሼዎችን መመደብ ግዴታ መሆኑ፣ ሠራተኛው በሚሰማራበት የሥራ መስክ ተገቢውን ሥልጠና የወሰደና የብቃት ማረጋገጫ ማቅረብ የሚችል፣ ቢያንስ ስምንተኛ ክፍልን ያጠናቀቀ መሆን እንዳለበት ወዘተ የተወሰኑት ናቸው፡፡

አዋጁ ለመንግሥት ሰፊና ከፍተኛ ሥልጣን ይሰጣል፣ ጥንካሬው ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን የማበረታታት ውጤት ይኖረዋል፣ ኤጀንሲዎችን ከሥራ ያስወጣል ወዘተ የሚሉ ትችቶች እየቀረቡበት ቢሆንም ሕጉ የመጀመርያ የረቂቅ ደረጃው ላይ በመሆኑ በሌላ ጊዜ ሲበስል በዝርዝር ሰፊ የሕዝብ አስተያየት ሊሰጥበት ይገባል፡፡ ዞሮ ዞሮ የአዋጅ ጠርካራና ምሉዕ ሆኖ መዘጋጀት ሁሉንም የሚያስማማ ነው፡፡

የመፈጸም ብቃት አስፈላጊነት

የሕግና የፖሊሲ ማዕቀፍ ከመቅረፅ እኩል የሚፈጽመውን አካል ጠንካራ አድርጎ ማቋቋም ለሕገወጥ ዝውውር መፍትሔነት ወሳኝ ነው፡፡ እስካሁን ያለውን የአፈጻጸም ሁኔታ ከገመገምን የአፈጻጸሙም ችግር ሕገወጥ ዝውውርን ማባባሱን ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ ሕገወጥ ደላሎችን በስፋትና በሕገወጥነት ለሕግ ማቅረብ፣ በሕገወጥ ዝውውር  የሚነግዱ ሰዎችን ጉዳት ከመፈጸማቸው በፊት መቆጣጠር፣ ሕገወጥ ዝውውር ሪፖርት የሚደረጉበትን መጠን መጨመር፣ የሕግ አስፈጻሚ አካላትን አቅም መገንባት፣ የማስረጃ አሰባሰብና አተናተንን ማጠናከር ለሕግጋቱ መፈጸም ወሳኝ በመሆናቸው አጽንኦት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡

ለማጠቃለል ያህል ሕግ ሕገወጥ ዝውውርን በመከላከል፣ ዜጎችን በመጠበቅና ሕገወጦችን ለሕግ በማቅረብ ረገድ ያለው አስተዋጽኦ ሰፊ ነው፡፡ ሕግጋቱ ወንጀለኞችን በመቅጣት ብቻ ላይ ሳይሆን ስደተኞች መብታቸው በሚጠበቅበት፣ ከአገራቸው ሳይወጡ ሰብዓዊ መብቶቻቸው በሚጠበቁበት ሁኔታ ላይ ሊያተኩሩ ይገባል፡፡ በዚህ ረገድ የወንጀል ሕጉና የግል ሥራና ሠራተኛ አገናኝ አዋጅ ከቀድሞዎቹ ሕግጋት የተሻለ ይዘት ቢኖራቸውም፣ ክፍተት ስላለባቸው በጥሞና ተመርምረው መሻሻለቸውም ወሳኝ ነው፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ የሚቀረፁ ሕግጋትን፣ የሚደራጁ ተቋማትንና ዘርፈ ብዙ ተያያዥ ጉዳዮችን አቅጣጫ የሚያመለክት የፖሊሲ ማዕቀፍ ካልተዘጋጀ ሕገወጥ ዝውውርን መዋጋት በዘለቄታውና በወጥነት መፍትሔ ላያገኝ ይችላል፡፡ በተወሰኑ ጊዜያት ልዩነት በዜጎች ስቃይና ሞት ከማዘን፣ በጥሞና ወጥነት ያለው የሕግና የፖሊሲ ማዕቀፍ አዘጋጅቶ ለጠንካራ ተፈጻሚነቱ መንቀሳቀስ ከትናንት የዘገዬ ለነገ የማይባል የመንግሥት ግዴታ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የሕግ ጠበቃና አማካሪ ሲሆኑ፣ በኢሜይል አድራሻቸው getukow [at] gmail.com  ማግኘት ይቻላል፡፡