ለወሲባዊ ትንኮሳ የሕግ ማዕቀፍ አስፈላጊነት

በዚህ ሳምንት የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር የሥራ ኃላፊዎች ለመገናኛ ብዙኃን ከሰጧቸው አስተያየቶች አንዱ የኢትዮጵያ የሕግ ማዕቀፍ ስለማይሸፍናቸው በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃችን ይመለከታል፡፡ እንደማኅበሩ አቋም የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥትና የተሻሻለው የወንጀል ሕግ ሴቶችን ከጥቃት የሚከላከሉ የሕግ ማዕቀፎችን ቢቀርጹም፣ እስካሁን ድረስ በዝርዝር ሕግጋት ያልተሸፈኑ ግን በተጨባጭ በሴቶች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያስከትሉ ጥቃቶች መኖራቸውን ነው፡፡ ማኅበሩ ከሚያነሳቸው ጥቃቶች ውስጥ የቤት ውስጥ ጥቃትና ወሲባዊ ትንኮሳ በሕግ ማዕቀፋችን ተገቢውን ቦታ ያልተሰጣቸው ናቸው፡፡ የቤት ውስጥ ጥቃትን በተመለከተ የወንጀል ሕጉ ጠቅላላ ድንጋጌ ቢኖረውም ለወንጀሉ ትርጉም የማይሰጥ፣ የቤት ውስጥ ጥቃት ድርጊቶችና መገለጫዎችን በምልዓት የማይዘረዝር፣ ፈጻሚዎቹን በገደብ የሚገልጽ በመሆኑ ለሴቶች በቂ ጥበቃ እንደማይሰጥ ማኅበሩ ይገልጻል፡፡ ወሲባዊ ትንኮሳን በተመለከተ ደግሞ የማኅበሩ አቋም በስፋት ከቤት ውስጥ እስከ አደባባይ ተንሰራፍቶ የሚገኝ ቢሆንም፣ ሕግጋቱ በተገቢው ሁኔታ እንደማይሸፍኑት ይገልጻል፡፡ ማኅበሩ ስለ ወሲባዊ ትንኮሳ የሕግ ማዕቀፍ አስፈላጊነት የውትወታ ሥራ መሥራት ከጀመረ ከ15 ዓመታት በላይ ቢሆነውም፣ እስካሁን ሰሚ ያገኘ አይመስልም፡፡ በተቋማት (በመሥሪያ ቤቶችና ትምህርት ቤቶች) አልፎ አልፎ በሚታይ ወሲባዊ ትንኮሳ ከሚመለከቱ መመርያዎች (ደንቦች) ውጪ፣ በሕግ ረገድ የተሠራ ሥራ አለመኖሩ በወሲባዊ ትንኮሳ መልክ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች መፍትሔ አላገኙም፡፡ በዚህ ጽሑፍ ማኅበሩ ‹‹ወሲባዊ ትንኮሳ በኢትዮጵያ፡- ለሴቶች ዕድገት ተግዳሮትነቱ›› በሚል የሠራውን ጥናት መሠረት አድርገን ለወሲባዊ ትንኮሳ የሕግ ማዕቀፍ አስፈላጊ ስለመሆኑ የሚቀርቡ ምክንያቶችን ባጭሩ ለመዳሰስ እንሞክራለን፡፡ ጥናቱ ወሲባዊ ትንኮሳን አንድና ሁሉንም የሚያስማማ ትርጉም መስጠት አስቸጋሪ መሆኑን በመጥቀስ፣ ማናቸውም ያለ ሴቷ ተቀባይነት ወይም እየተቃወመችው ወይም ፍርሃትን በሚፈጥር፣ በማስገደድ፣ በማቅረብ ወይም በመንገድ ላይ ወሲብን ዓላማ አድርጎ በቃል/በንግግር ወይም አካላዊ ንክኪን ጨምሮ ያለንግግር የሚፈጸም ትንኮሳን እንደሚያካትት ይገልጻል፡፡ ብዙውን ጊዜ በተቋማት ውስጥ የሚታወቁት የወሲባዊ ትንኮሳ ዓይነቶች ሁለት ናቸው፡፡ የመጀመሪያው የሚያስፈራ አካባቢ የመፍጠር (Hostile Environment) ሲሆን የማይፈለግ ወሲባዊ ውለታን መጠየቅ፣ ወሲባዊ ገጸ በረከት መጠየቅንና በግለሰቧ ሥራ ወይም ትምህርት አፈጻጸም ላይ ምክንያታዊ ያልሆነ ጣልቃ ገብነት ዓላማ/ውጤት ያለው ፍራቻን፣ ጥላቻን ወይም ጥቃትን የሚፈጥር በንግግር ወይም በአካል የሚገለጽ ድርጊትን የሚመለከት ነው፡፡ የሰውነት አካልን ማድነቅ፣ አፍጥጦ ማየት፣ የተወሰኑ አካሎችን መንካት፣ ወሲባዊ ይዘት ያላቸውን ርዕሰ ጉዳዮች ማንሳት ወዘተ. በዚህ ምድብ ይወድቃሉ፡፡ ሁለተኛው ዓይነት ወሲባዊ ትንኮሳ አድርጊልኝ ላድርግልሽ (Quid Pro quo) ሲሆን ትንኮሳ ፈጻሚው ከተጠቂዋ ለትምህርት ወይም ለሥራ ቅጥር ጥቅማ ጥቅሞች ለውጥ የሚሆን ወሲባዊ ገጸ በረከት የሚጠብቅ ሲሆን ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ትንኮሳ ድርጊቱን ፈጻሚው ብዙውን ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ ላይ ያለ ስለሚሆንና የተጠቂዋና ትምህርት ወይም ሥራ ለመጉዳት ስለሚችል የሥልጣን መኖር ቁልፍ ሚና ይጫወታል፡፡ ከመጀመሪያው ዓይነት ትንኮሳ የሚለየው ወሲባዊ ጥያቄው ተቀባይነት ካላገኘ በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ የሚፈጸም ዛቻን ወይም መጉዳትን ወይም ወሲባዊ ግንኙነቱን ታሳቢ ተደርጎ ሠራተኛዋን ለመጥቀም የተገባውን የተስፋ ቃል መንፈግን ስለሚጨምር ነው፡፡ ዝቅተኛ የሥራ ግምገማ ውጤት መስጠት፣ የማይጠቅም የማበረታቻ ክፍያ (Bonus) መተመን፣ ተግባራዊ የማይሆን የሥራ ማጠናቀቂያ ጊዜ ገደብ ማስቀመጥ፣ ከሥልጣን/ከሥራ ደረጃ ዝቅ ማድረግ ወዘተ. የተለመዱት የበቀል ዕርምጃዎች ናቸው፡፡

የሕግ መውጣት አስፈላጊነት

የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር ባስጠናው ጥናት ወሲባዊ ትንኮሳን በተመለከተ ሕጋችን ተሻሽሎ ወይም አንድ ወጥ ሕግ መውጣት ይገባዋል ሲል ይደመድማል፡፡ እዚህ መደምደሚያ ላይ ለመድረስ ጥናቱ ሦስት ዓይነት መንገዶችን ተጠቅሟል፡፡ የመጀመሪያው ወሲባዊ ትንኮሳ ሴቶች በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ስምምነት የተደነገጉ የሴቶች መብቶች የሚጥስ መሆኑን መነሻ የሚያደርግ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በፈረመቻቸው ሰብዓዊ መብቶች ስምምነቶች መሠረት ወሲባዊ ትንኮሳን ወንጀል የሚያደርግ ድንጋጌ በሕግ ቀርጻ ካላስፈጸመች ዓለም አቀፍ ግዴታዋን እንደማትወጣ ጥናቱ ይተነትናል፡፡ ሁለተኛው ዘዴ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሕግጋት ወሲባዊ ትንኮሳን በተመለከተ መሉዕነት ያለው ድንጋጌ የሌላቸው መሆኑን በመተንተን የሕግጋቱ ክፍተት እንዲሞላ ውትወታ ያደርጋል፡፡ ሕግጋቱ ያለባቸውን ክፍተት በሚቀጥለው የጽሑፍ ክፍል የምንመለከተው ይሆናል፡፡ ሦስተኛው ጥናቱ በሴቶች ላይ ሰፊ የዳሰሳ መረጃን መሠረት አድርጎ ወሲባዊ ትንኮሳ የሴቶች መሠረታዊ ችግር መሆኑን፣ በሴቶች ላይ ያሉትን የተለያዩ አሉታዊ ተፅዕኖዎች በመተንተን ወሲባዊ ትንኮሳ በምን መልኩ በሕግጋቱ ውስጥ መካተት እንደሚገባው ይገልጻል፡፡ በጥናት ዳሰሳው 5000 የሚደርሱ ሰዎች የተካተቱ ሲሆን፣ በተለያዩ የክልል ከተሞችና በአዲስ አበባ ውስጥ የሚገኙ 11 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን፣ 18 ኮሌጆችን፣ ዩኒቨርሲቲዎችን፣ 36 ድርጅቶችን በመሸፈን ከ640 ሴቶች መረጃ ተሰብስቧል፡፡ በተጨማሪም በ68 የግልና የመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ 1500፣ በግልና በመንግሥት ተቋማት ውስጥ 1600፣ በመንገድ ላይ ያለውን የወሲባዊ ትንኮሳ ለመዳሰስ 1600 መጠይቆች ተሞልተዋል፡፡ የዳሰሳው ጥናት ወሲባዊ ትንኮሳ የሴቶችን መብት እጅጉን እየጣሰ መሆኑን፣ በሴቶች ላይ ሰፊ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያደርስና የሕግ መውጣት አስፈላጊ መሆኑን ይተነትናል፡፡

የሕግጋቱ ክፍተት

በማኅበሩ ጥናት መሠረት ወሲባዊ ትንኮሳ በሕገ መንግሥት የተቀመጡ የሴቶች መሠረታዊ መብቶች የሚጥስ መሆኑ ቢታወቅም፣ ብሔራዊ ዝርዝር ሕግጋቱ ወሲባዊ ትንኮሳን ለመከላከል ለማስቀረት የሚያስችሉ ምሉዕ ድንጋጌ የላቸውም፡፡ በጥናቱ የተፈተሹትና ክፍተት የታየባቸው ሕግጋት የወንጀል ሕጉ፣ የአሠሪና ሠራተኛ አዋጁና ከውል ውጪ ኃላፊነት ሕግ ናቸው፡፡ በጥናቱ የተዳሰሱትን ክፍተቶች ባጭሩ ለማቅረብ እንሞክር፡፡

የወንጀል ሕጉ

የተሻሻለው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 625 የወሲባዊ ትንኮሳን ጭብጥ በከፊል አካትቷል፡፡ አንቀጽ 625 ‹‹አንድ ሴት ያለባትን ከፍ ያለ ችግር ወይም ጥገኝነትዋን ምክንያት በማድረግ የሚፈጸም ድርጊት›› በሚል ርዕስ

‹‹…ማንም ሰው በአንዲት ሴት ላይ የደረሰውን ከፍ ያለ ቁሳዊ ችግር ወይም የህሊና ሐዘን ምክንያት በማድረግ ወይም በጠባቂነት፣ በአስተማሪነት፣ በአሳዳሪነት፣ በአሠሪነት ወይም ይህን በመሰለ በማናቸውም ሌላ ግንኙነት ምክንያት ያገኘውን ሥልጣን፣ ኃላፊነት ወይም ችሎት በመጠቀም ከተባለችው ሴት ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት የፈጸመ ወይም የግብረ ሥጋ ግንኙነትን የመሰለ ድርጊት ወይም ለንጽሕና ተቃራኒ የሆነ ማናቸውም ሌላ ዓይነት ድርጊት የፈጸመ እንደሆነ የግል አቤቱታ ሲቀርብበት በቀላል እሥራት ይቀጣል፡፡››

ይህ ድንጋጌ በማናቸውም የሥልጣን ሁኔታ የሚፈጽም አድርጊልኝ ላድርግልሽ የወሲባዊ ትንኮሳን የሚሸፍን ቢሆንም የተወሰኑ ክፍተቶች አሉበት፡፡ የመጀመሪያው ጉድለቱ፣ ድንጋጌው የሚሸፍነው በሥልጣን ላይ ባሉ ግለሰቦች የሚፈጸም ትንኮሳን ብቻ መሆኑ ላይ ነው፡፡ ድንጋጌው ሥልጣን በሌላቸው ግለሰቦች ለምሳሌ በሥራ ባልደረቦች፣ በትምህርት ቤት የክፍል ጓደኞች የሚፈጸሙትን አያካትትም፡፡ በመንገድ ላይ ከሚፈጸም ወሲባዊ ትንኮሳም ጥበቃ አያደርግም፡፡ ሁለተኛው ወሲባዊ ትንኮሳ በድንጋጌው ከተገለጹት ድርጊቶች በላይ ድርጊቶችን/ባህሪያትን የሚሸፍን ነው፡፡ በወሲባዊ ጥቃት በቀልድ፣ በተደጋጋሚ ለመገናኘት በመጠየቅ ወዘተ. በንግግርና ያለንግግር የሚፈጸሙ የወሲባዊ ትንኮሳ ድርጊቶችን አይሸፍንም፡፡ በሦስተኛ ደረጃ የድንጋጌው አጻጻፍም በተወሰነ ደረጃ አሻሚና ግልጽነት የሚጎድለው ነው፡፡ ‹ለንጽህና ተቃራኒ የሆነ ድርጊት› የሚለው ግልጽ አይደለም፡፡ ‹‹ከፍ ያለ ቁሳዊ ችግር ወይም የህሊና ሐዘን›› የሚለውም ትርጉሙንና አተገባበሩን በጣም ውሱን ያደርገዋል፡፡ በተማሪም በድንጋጌው ተቋማዊ ኃላፊነትና ተጠያቂነት አልተሸፈነም፡፡

የአሠሪና ሠራተኛ ሕጉ

አዋጅ ቁጥር 377/1996 በአንቀጽ 32(1)(ሀ) ‹‹አሠሪው በሠራተኛው ላይ ማንኛውንም ለሰው ልጅ ክብርና ለሞራል ተቃራኒ የሆነ ድርጊት ወይም ሌላ በወንጀል ሕጉ ሥር የሚያስቀጣ ድርጊት ከፈጸመበት ሠራተኛው ምክንያቱን በመናገር የሥራ ቅጥር ውሉን ያለማስጠንቀቂያ ማቋረጥ ይችላል፡፡›› ይህ ድንጋጌ ከሠራተኛና አሠሪ ግንኙነት ጋር በተያያዘ ፍርድ ቤቶች በትንኮሳ ምክንያት ሥራ ለለቀቀች ሴት ጉዳይ ተፈጻሚ ለማድረግ የሚችሉ ቢሆንም፣ የሕጉን መጣስ ለማስረዳት የሚያስፈልጉት ቅድመ ሁኔታዎች የድንጋጌውን ተፈጻሚነት አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡ አንድ አሠሪን በሠራተኛው ላይ በተፈጸመ ‹‹ለሰው ልጅ ክብርና ለሞራል ተቃራኒ የሆነ ድርጊት›› ኃላፊ ለማድረግ የሚያስፈልጉት ሁኔታዎች በግልጽ መቀመጥ ይኖርባቸዋል፡፡ በሌላ በኩል ሴቶች በትንኮሳ ሥራ ሲለቁ የሥራ ስንብት ክፍያ እንደሚያገኙ ሕጉ ቢደነግግም፣ የሴቶችን የሥራ ዋስትና የሚያረጋግጥ ወይም ከወሲባዊ ትንኮሳ ጥበቃ የሚያደርግ አይደለም፡፡ ከሕጉ ዓላማም አንፃር የውል መቋረጥ ከሚያስከትለው በቀር ትንኮሳውን የሚቀጣ አይደለም፡፡ ሥራቸውን መልቀቃቸው በራሱም በሴቶች ላይ የሚፈጸመውን ልዩነት እጥፍ ድርብ ያደርገዋል፡፡ ይህ ሁኔታ ለሴቶች የሚያስተላልፈው መልዕክት ወሲባዊ ትንኮሳውን መታገስ ወይም ሥራችሁን መተው አለባችሁ የሚል ሲሆን፣ ሁለቱም ምርጫዎች ለሴቶች ሠራተኞች ምክንያታዊ አማራጮች አይደሉም፡፡

ከውል ውጪ ኃላፊነት ሕጉ

ከውል ውጪ ኃላፊነት ሕጉ ለወሲባዊ ትንኮሳ አቤቱታዎች ተፈጻሚነት ሊኖረው ይችላል፡፡ ተገቢነት የሌለው ድርጊት፣ ለምሳሌ አንድን ሰው ያለፈቃዱ መንካት፣ በአንቀጽ 2038(1)፣ ከአንቀጽ 2027 እስከ 2178 በተደነገጉት መሠረት በፍትሐ ብሔር ጥፋተኝነት ያስጠይቃል፡፡ በዚህ የሕጉ ክፍል መሠረት ጥቃት መፈጸሙን ለማስረዳት በቁጥር 2039(ሀ) እስከ (ሠ) ተከሳሹ በልዩ ሁኔታ ጥፋተኛ የማይባልበትን በቂ ምክንያት ማስተባበልን ይጠይቃል፡፡ በቂ ምክንያቶች የተባሉት በጣም በጥቅሉ የተቀመጡና ምክንያታዊ በሆነ/አዕምሮ ባለው ሰው ዓይን መረጋገጥ የማይችሉ ማናቸውንም ነገር ያካተቱ ናቸው፡፡ ከዚህ አንፃር ይላል የማኅበሩ ጥናት፣ ‹‹የምክንያታዊ ሴትን አስተያየት ለማንፀባረቅ ይቻል ዘንድ የምክንያታዊ ሰውን መለኪያ ማሻሻሉ የተሻለ ይሆናል፡፡›› የዚህ ድንጋዎች ጥቃትን ብቻ የሚያካትቱ ከሆነ፣ ወሲባዊ ትንኮሳን ሙሉ በሙሉ አላካተተም ለማለት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም ወሲባዊ ትንኮሳ ከጥቃት ደረጃ ሳይደርስ ነገር ግን ከጥቃት ባልተናነሰ ሁኔታ ጎጂ በሆነ መልኩ ሊፈጸም ይችላል፡፡ በተጨማሪም ሕጉ አሠሪዎች በሠራተኞቻቸው አማካይነት ለሚፈጸም ወሲባዊ ትንኮሳ ያለጥፋት ኃላፊ እንዳይሆኑ በግልጽ ነፃ ተደርገዋል፡፡ አንቀጽ 2129፣ 2130 እና 2133 ይመለከቷል፡፡ በሌሎች አገሮች አሠሪዎችን ያለጥፋት ኃላፊ የሚያደርጋቸው ለትንኮሳ ፈጻማዎቹ ባደረጉት አስተዋጽኦ ነው፡፡

ሕግ እንዲወጣ የመወትወት ተግዳሮቶች

ሴቶች የኅብረተሰቡ ግማሽ ክፍል ናቸው፡፡ ሕገ መንግሥቱና ዓለም አቀፍ ስምምነቶች መብቶቻቸውን ቢደነግጉላቸውም፣ በዝርዝር ሕግጋት መቅረጽ በአገራችን ዐውድ አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ እንኳን ሴቶችን በተናጠል የሚመለከቱ ለኅብረተሰቡ በሙሉ ተፈጻሚ እንደሚሆኑ የሚጠበቁት የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕግ፣ የውርስ ሕግ፣ የማስረጃ ሕግ ወዘተ ወትዋች፣ አርቃቂና ሕግ አውጪ ያጡ ይመስላሉ፡፡ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበርም ባለፉት 15 ዓመታት ጥናትን መሠረት አድርጎ ሕግጋት እንዲሻሻሉ ወይም እንዲወጡ መጠየቅ የተለያዩ ፈተናዎች/ጋሬጣዎች ሐሳቡን ስለሚያደናቅፉ ነው፡፡ ከሁሉም ዋናው ተግዳሮት ወሲባዊ ትንኮሳ ቀዳሚ የሴቶች መብት አጀንዳ አይደለም፣ በሕግ ሥርዓቱ በቂ ጥበቃ ተደርጎለታል፣ ባህላዊ መሠረት ያለውና ሴቶች ራሳቸው እንደሚቀበሉት ግምት በመውሰድ የተለያዩ አካላት የሕጉን አስፈላጊነት ይቃወማሉ፡፡ አንዳንድ ሰዎች ችግሩ መኖሩን፣ ወሲባዊ ትንኮሳ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መሆኑን ቢያምኑም፣ ሴቶች በትምህርትና በሥራ ውጤታማነታቸው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳለው ቢረዱም በሕግ ደረጃ አዋጅ እንደሚያስፈልገው አያምኑም፡፡ ሕግ ቢወጣ ከችግሩ ብዛትና ስፋት አንፃር የተፈጻሚነቱን ውጤታማነት የሚጠራጠሩ አሉ፡፡ መንገደኛ ወንድ ሴትን እንደልቡ ያለገደብ በቃልና በድርጊት በሚለክፍበት አገር ሕግ አውጥቶ መተግበር አስቸጋሪ ነው፤ መንገደኛውን ሁሉ እንደ ማሰር ነው የሚሉ ወገኖች አይጠፉም፡፡

እንደ ጸሐፊው እምነት ከጥናቱና ሕግ እንዲወጣ ከመወትወቱ ጎን ለጎን አመለካከትን የመቀየር ሥራው ተደራጅቶና በወጥነት ሊሠራ ይገባል፡፡ አንደኛ፣ አጀንዳው የማኅበሩ ብቻ ባለመሆኑ ከሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ሚኒስቴር፣ በፓርላማ ከሴቶች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴና ከኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጋር የተቀናጀ ግንኙነት መፍጠር ተገቢ ነው፡፡ የጋራ ሥራው ወሲባዊ ትንኮሳ በተገቢው ቦታ እንዲሰጠውና የሕግ መፍትሔው እንዲመጣ ያስችለዋል፡፡ ሁለተኛ፡- የሕግ እንዲወጣ የመወትወት ሥራውን ደረጃ በደረጃ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ በተቋማት ደረጃ ወሲባዊ ትንኮሳን የሚከለክል፣ ዕርምጃውንና አካሄዱን የሚገልጽ ፖሊሲ አሠራር እንዲፈጠር ማስቻል ሊቀድም ይገባል፡፡ በዚህ ረገድ ትምህርት ሚኒስቴር በከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና በትምህርት ቤቶች የጀመረው ሥራ ድጋፍ ሊያገኝና ሊጠናከር የሚባው ነው፡፡ በመጨረሻው፣ ማኅበሩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ወሲባዊ ትንኮሳና የማይታገስ ብሎም የሚቃወም ኅብረተሰቡ እንዲፈጠር የተለያዩ ሥልጠናዎች፣ የምክክር ጉባዔዎችና የማኅበረሰብ ውይይቶች ሊያዘጋጅ ይገባል፡፡ የኅብረተሰቡ አመለካከት ከተቀየረ ሕግ ማውጣቱ በሁሉም የሚደገፍ ያደርገዋል፡፡ የመብቱ ተጠቃሚዎች (ሴቶች) ራሳቸው የሕጉን መውጣት በሙሉ ዕውቀትና ድጋፍ ባልተቀበሉበት ሁኔታ ሕግ የማውጣትን ውትወታ ከባድ ሥራ መጀመር 15 ዓመት አይደለም ምዕተ ዓመትም ይፈልጋል፡፡ ‹‹ካልተለከፍኩ ደስ አይለኝም››፣ ‹‹እናቶቻችንም ከአባቶቻችን ጋር ትዳር የመሠረቱት በትንኮሳ ነው››፣ ‹‹ለጥምቀት ሎሚ ካልተወረወረብኝ ደስ አይለኝም›› ወዘተ. የሚሉ ሴቶች ባሉበት ስለ ወሲባዊ ትንኮሳ ሕግ መውጣት አስቸጋሪ ነው፡፡

አዘጋጁ ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው getukow [at] gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡