ለማደግ አቅደን ላለመራብ ሳናቅድ ቀረን

በጌታቸው አስፋው

የዕቅድ ሰዎች እንደ ቀልድ አድርገው አዘውትረው የሚናገሩት ቁምነገር አለ፡፡ ይህም ያቀዱም ያላቀዱም አቅደዋል ነው፡፡ ዕደገታቸውን ያላቀዱ ውድቀታቸውን አቅደዋል፣ የማይቻለውን ያቀዱ በጊዜ እጥረት የሚቻለውን አላቀዱም፣ እንዳይራቡ ያላቀዱ መራባቸውን አቅደዋል ማለት ነው፡፡ ለምን እንራባለን ጥያቄ መልሱ ላለመራብ ስላላቀድን ለመራብ አቅደናል ነው፡፡

ጳጳሱም ሼሁም የሰበኩላቸው፣ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ምሁራን የዘመሩላቸው፣ ከጥቁር እስከ ነጭ ባዕዳን ያራገቡላቸው ዕቅዶች ከረሃብ እንዳላስጣሉን በዓይናችን አየን፡፡ እውነት የሚለካው ባሳመኑት ሰው ብዛት ልክ ሳይሆን በእውነትነቱ ብቻ ስለሆነ፣ ዕቅዶቹ ከረሃብ እንዳላስጣሉን ፀሐይ የሞቀው ሀቅ ሆነ፡፡

ለውጥ የሚመጣው በለውጥ ግብረ ኃይሎች (Change Factors) መስተጋብር ነው፡፡ ግብረ ኃይሎችም ውስጣዊና ውጫዊ በመባል በሁለት የሚከፈሉ ሲሆን፣ ውስጣዊ ግብረ ኃይሎች ዋናዎቹ ሲሆኑ ውጫዊ ግብረ ኃይሎች አጋዥ ብቻ ናቸው፡፡

እንደ ዕቅድ ባለሙያ በዕድገትና በትራንስፎርሜሽን ዕቅዶቹ ላይ የሚታየኝ ችግር፣ ለኢኮኖሚ ዕድገትና ብልጽግና ዕቅድ ትንታኔ ኢኮኖሚክስን እንደ የለውጥ ውስጣዊ ግብረ ኃይል (Endogenous Factor)፣ ልማትን እንደ ውጪያዊ ግብረ ኃይል (Exogenous Factor) አድርጐ አለመመልከቱ ነው፡፡

በለውጥ የውስጥ ግብረ ኃይል ባለቤት ሆኖ የሚሳተፈው እያንዳንዱና ጠቅላላው ሕዝብ ሲሆን፣ በአጋዥነት የለውጥ ውጫዊ ግብረ ኃይል ሆነው የሚሳተፉት በጥቂት ሺዎች የሚቆጠሩ የመንግሥትን ፖሊሲ የሚያስፈጽሙ ሰዎች ናቸው፡፡

የለውጥ ውጫዊ ግብረ ኃይሎች የሚያቅዱት የራሳቸውን አገልግሎት ብቻ ነው፡፡ ዋናውን ባለቤት የዕቅዱ ተሳፋሪ መንገደኛ እንጂ የዕቅዱ ሾፌር (ነጂ) አላደረጉትም፡፡ በሌላ አነጋገር ፍላጐትህን የማያውቅ ጐረቤትህ ለአንተ ያቅዳል ማለት ነው፡፡ ረሃቡ አቃጆቹ ጎረቤቶች ገበሬውን እንደማያውቁ ማስረጃ ሆነ፡፡ ተሳፋሪ መንገደኛው በሚያንገላታው ጐረቤት የዕቅድ ሾፌር የተቆጣ ለታ የታቀደውም ያልታቀደውም ይበለሻሻል፡፡

ሠርቶና ነግዶ ለማትረፍ ከውስጥ መነሳሳት (Internal Dynamism) የራሱ የአምራቹ ከውስጥ የሚመነጭ የለውጥ ውስጣዊ ግብረ ኃይል ሲሆን አባብሎ፣ መክሮ፣ ሰብኮና ድጋፍ ሰጥቶ እንቅፋቶችን አስወግዶና ሁኔታዎች አመቻችቶ እንዲሠራ መገፋፋትና ማነቃቃት የለውጥ ውጫዊ ግብረ ኃይል ነው፡፡

ሰዎች የማምረት ፍላጐታቸው እንዲነሳሳ የውጭ ድጋፍ ከማግኘታቸው አስቀድሞ፣ ከአጥንትና ከደማቸው ከሰውነታቸው ውስጥ የተነጠቁት የለውጥ መነሳሳት ሊመለስላቸው ይገባል፡፡ ይህ በተፈጥሮ ያገኙትና የራሳቸው የሆነ የለውጥ መነሳሳት በራስ መተማመን ወይም በእኩል ሜዳ በውድድር ለማሸነፍ መፎካከር (Self-esteem or Human Ego Behavior) ይሆናል፡፡

ይህን በፉክክር መኖርና ለሥራ መነሳሳት ደርግ በሶሻሊዝም እምነት በጠመንጃ ጉልበት ከሰው ሰውነት ውስጥ አላቆ አወጣ፡፡ ኢሕአዴግም በዚያው እምነትና በዚያው ጉልበት ቀጠለበት፡፡ ወጣቶችም ድህነትንና ባለፀጋነትን፣ ተስፋ መሰነቅንና ተስፋ መቁረጥን በቀጥታ ከወላጆቻቸው እየወረሱ ነው፡፡

መስተካከል የሚገባው በጊዜ ካልተስተካከለ አፍርሶ በመገንባት ሜዳውን እኩል የሚያደርግ ጎርፍ በራሱ ጊዜ ይመጣል፡፡

የብሔራዊ ኢኮኖሚ ዕቅድ ውስጣዊ ግብረ ኃይሎች

የብሔራዊ ኢኮኖሚ ዕቅድ ለማቀድ ከሁኔታዎችና ከፖሊሲዎች ትንታኔ ባሻገር፣ የማክሮ ኢኮኖሚ መለኪያዎችን የመደጋገፍና የመቃረን ወይም የመሳሳብና የመገፋፋት ተያያዥነትም (Linkage) መረዳት ያስፈልጋል፡፡

ለምሳሌ የዋጋ ንረትን የመቀነስ ግብና የኢኮኖሚ ዕድገትን የማፋጠን ግብ አብረው አይሄዱም፡፡ ሥራ አጥነትን መቀነስና የዋጋ ንረትን መቀነስም እንደዚሁ፡፡ የኢኮኖሚና የኢንዱስትሪ ዕድገት ብዙ የኢምፖርት ግብዓተ ምርቶችን ስለሚፈልግ፣ የውጭ ምንዛሪን አሟጦ የክፍያ ሚዛን ጉድለትን ያስከትላል፡፡

ከዚህ በላይ የተጠቀሱት ዋናዎቹ ውስጣዊ የለውጥ ግብረ ኃይሎች ሲሆኑ፣ በሰው የሚሰጡ ብሔራዊ ኢኮኖሚውን ለማሳደግ በክፍላተ ኢኮኖሚዎች ደረጃ ለግብርናው፣ ለኢንዱስትሪውና ለአገልግሎት ዘርፉ የሚሰጡት ድጋፎች ውጫዊ የለውጥ ግብረ ኃይሎች ናቸው፡፡

ዕቅዶች ከአንድ በላይ በሆኑ አማራጮች (Different Scenarios) ሲታቀዱ፣ የመሠረታዊው ዕቅድ ፖሊሲዎች ሳይለወጡ በሚደርስ ግብ ይታቀድና ሌሎቹ አማራጮች ከፖሊሲ ለውጦች ጋር የሚኖሩ ልዩነቶችን በማጤን በሌሎች ግቦች ይታቀዳሉ፡፡

የፖሊሲ ለውጥ ሳይጠቁም ወይም ሳያመለክት መሠረታዊና ከፍተኛ ብሎ በመክፈል በሁለት አማራጮች የታቀደው የተገባደደው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አንዳንድ ግቦች፣ ለምሳሌ በኤክስፖርት ንግድ ከመሠረታዊው እጅግ በጣም በታች በሌሎች ግቦች ለምሳሌ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት ከፍተኛ ዕድገት ውጤት ታይቶበታል፡፡ የዋጋ ንረትና የውጭ ምንዛሪ እጥረትም ጎልተው ታይተዋል፡፡ ይህ የሚያመለክተው ውስጣዊ የለውጥ ግብረ ኃይሎች መስተጋብር አለመተንተኑን ነው፡፡

የገበያውን ከገበያው ወስዶ ሞግዚት በመሆን ድጋፍ እየለገሱት የሥራ ማበረታቻ ማድረግ አምራቹን ያለሞግዚት የማይንቀሳቀስ ሰነፍ ማድረግ ነው፡፡ ሰዎች ከሞግዚት የሚያገኙትን ድጋፍ ከማግኘታቸው በፊት፣ የተነጠቁትን የውስጥ መነሳሳት የሚፈጥርላቸውን ውስጣዊ የለውጥ ግብረ ኃይል (Change Factor) መልሰው ማግኘት አለባቸው፡፡

ከዚህ ቀጥሎ ከዕድገት ውስጣዊ የለውጥ ግብረ ኃይሎች ውስጥ ከኢኮኖሚ ዕድገት ጋር ከሁሉም በላይ ቁርኝት ስላለው የቋሚ ካፒታል ክምችትን ከረሃብ እንዳንላቀቅ ምክንያት ከመሆኑ ጋር በማገናኘት፣ ዕቅዶቹም የዘነጉት መሆኑን በመጠቆም በአገር አቀፍ ገጠርና በከተሞች በመከፋፈል እገልጻለሁ፡፡

የግል ቋሚ ካፒታል ክምችት በአገር አቀፍ ደረጃ

በኢኮኖሚ ጽንሰ ሐሳቦችና ሞዴሎች ከዕድገት ለውጥ ውስጣዊ ግብረ ኃይሎች ዋናዎቹ የቋሚ ካፒታል ክምችትና የካፒታል ምርታማነት፣ የሰው ኃይል ምርታማነትና የቴክኖሎጂ ሥርፀት ናቸው፡፡ የካፒታልና የምርት ተዛምዶ ጥምርታን (Capital Output Ratio) ሙያውና መረጃ ካለ መለካት ይቻላል፡፡ መለካት ካልተቻለም ያለፉትን ዓመታት ዝንባሌ (Trend) መረጃ በማድረግ መተንተንና የዕቅድ መነሻ ማድረግ ይቻላል፡፡

የመነሻ ካፒታል እጥረት ችግር በኢትዮጵያ ውስጥ ሥር የሰደደ እንደሆነ ይነገራል፡፡ የካፒታል ችግር ብቻ ሳይሆን የካፒታል ምርታማነትም ትልቅ ችግር ነው፡፡ ዕቅዶቹም የግሉን ተሳትፎ ለማነቃቃትና ወደ ምርት ለማስገባት የፋይናንስ ችግርን እናቃልላለን፣ የባንክ ብድር እናመቻቻለን፣ መሬት እናቀርባለን የሚሉትን ነገሮች ነው እንደ ታሳቢ አድርገው የሚያቀርቡት፡፡

በነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ገንዘብም መሬትም የገበያ ሸቀጦች እንጂ የመንግሥት ንብረት አልነበሩም፡፡ የገበያውን ንብረት ከገበያው ነጥቆ ወደ ምርት እንድትገባ አመቻችልሃለሁ ማለት፣ የግብይት ሥርዓቱን የለውጥ ውስጣዊ ግብረ ኃይል ወደ የለውጥ ውጫዊ ግብረ ኃይልነት ቀይሮ ሁኔታዎችን ከማመቻቸት ይልቅ እንቅፋት መፍጠር ነው፡፡

ውስጣዊ የለውጥ ግብረ ኃይሉን በዚህም በዚያም ብሎ አደናቅፎ በውጭ የለውጥ ግብረ ኃይል በመተካት አመቻች ሁኔታ ቢፈጠርም፣ ወደ ማኑፋክቸሪንግ ምርት ተገብቶ የኢንዱስትሪ ዕድገት ሊመጣ ባለመቻሉ የውጭ ቀጥታ መዋዕለ ንዋይን እንደ አማራጭ በመጠቀም ግብዣ ተዥጐድጉዶለታል፡፡

የውጭ ቀጥታ መዋዕለ ንዋይ ዕዳ ውስጥ ሳይገባ ከውጭ ወደ ውስጥ የሚፈስ ካፒታል ስለሆነ፣ የካፒታል ክምችትን አበርክቶ የኢኮኖሚ ዕድገትን እንደሚያመጣ ስለሚታወቅ በሌጣ ዓይን ሲታይ ሳያንገራግሩ የሚቀበሉት ጉዳይ ነው፡፡

በአመለካከት ደረጃ አንዳንድ ሰዎች እንደ አዲስ ዓይነት ቅኝ አገዛዝ አድርገው ሲመለከቱ ሌሎች ታዳጊ አገሮች ያለእሱ መልማት እንደማይችሉ አድርገው ይመለከታሉ፡፡

ብዙ ሰዎችም የውስጥ ድርጅቶችን ያቀጭጫል፣ ዘመናዊ ማሽነሪዎችን በመጠቀም ሥራ አጥነትን ያበዛል፣ የውጭ ንግድ ሚዛንን ያዛባል ይላሉ፡፡ ለአገሮች ሉዓላዊነት እንደሚያሰጋና ብሔራዊ ደኅንነትን አደጋ ላይ እንደሚጥል የሚቆጥሩም አሉ፡፡

የውጭ ቀጥታ መዋዕለ ንዋይ አዲስ ጅማሮ (Green Field) ወይም (Accusition and Merger) ወይም በጥምረት መሥራት (Joint Venture) ሊሆን ይችላል፡፡

የውጭ ቀጥታ መዋዕለ ንዋይ ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞቹና ጉዳቶቹ ማክሮና ማይክሮ ተብለው በሁለት ሊከፈሉ ይችላሉ፡፡

ዋናው የማክሮ ጥቅም የካፒታል ከውጭ ወደ ውስጥ ፍሰት (Capital Inflow) በውጭ ምንዛሪ ግኝት የውጭ ኢኮኖሚ ክፍያ ሚዛንን ማሻሻል ነው፡፡ ከቀጥታ መዋዕለ ንዋይ ትርፍ ቀረጥም ማክሮ ኢኮኖሚው ይጠቀማል፡፡ በወለድና በዋና ገንዘብ ዕዳ ከሚያስቆልለው አገራዊ ብድርም (Sovereign Loan) ሆነ ወላዋይ ባህሪይ ካለው የኮሮጆ (ሰነዶች) ካፒታል የውስጥ ፍሰት (Portfolio Capital Inflow) የተሻለ ተደርጐ ይወሰዳል፡፡

በግለሰቦችና በኢንዱስትሪዎች ላይ የሚንፀባረቅ የማይክሮ ኢኮኖሚው ለውጥ የሚታዩባቸው መንገዶች፣ በገበያ ውድድር የአገር ውስጥ አምራች በውጭ ቀጥታ መዋዕለ ንዋይ ለመተካት (Substitution) የሚጋለጥበትና በአሟይነት (Complementarily) የሚደጋገፍበት አጋጣሚዎች ነው፡፡

የውጭ ቀጥታ መዋዕለ ንዋይ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የምርት መጠንን እንደሚያሳድግ ቢታወቅም፣ ይህን ቴክኖሎጂ መጠቀም የሚችል ተመጣጣኝ የተማረ የሰው ኃይል መኖር ግድ ይላል፡፡

የውጭ ቀጥታ መዋዕለ ንዋይ ጥቅም ብቻ ሳይሆን ጉዳቶችም አሉት፡፡ በገንዘብ ፍሰት ረገድ የውጭ ቀጥታ መዋዕለ ንዋይ የተወሰነ የውጭ ገንዘብ ብቻ ይዞ መጥቶ ከአገር ውስጥ ባንክ ብዙ በመበደር የዋጋ ንረት እንዲባባስ ያደርጋል፡፡ የአገር ውስጥ አምራቾችን የመበደር አቅምም በመሻማት ይገድባል፡፡

ሌላው የውጭ ቀጥታ መዋዕለ ንዋይ ጉዳት በወለድ፣ በትርፍ ክፍፍል፣ በሐዋላ መላክና በከፊል የተፈበረኩ ምርቶችን ለማስመጣት በሚጠይቀው የውጭ ምንዛሪ ምክንያቶች ይዞት ከገባው የውጭ ምንዛሪ በላይ ከአገር ውስጥ ማስወጣት ነው፡፡

በአዲስ መዋዕለ ንዋይ ካልተተካ በቀር የቀድሞ መዋዕለ ንዋይ ቀስ በቀስ በእነዚህ ሁኔታዎች ከአገር መውጣት የተጣራ የገንዘብ ፍሰቱ ከውጭ ወደ ውስጥ (Inflow) መሆኑ ቀርቶ፣ ከውስጥ ወደ ውጭ (Outflow) ሆኖ የቋሚ ካፒታል ክምችትን ይቀንሳል፡፡

በጥናቶች እንደታየው ታዳጊ አገሮች ከማዕድን ዘርፍ ቀጥታ የውጭ መዋዕለ ንዋይ የተጣራ የውጭ ምንዛሪ ወደ ውስጥ ፍሰት (Net Inflow) ሲያገኙ፣ ከማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የውጭ ቀጥታ መዋዕለ ንዋይ በኢምፖርት ግብዓተ ምርት ምክንያት የተጣራ የውጭ ምንዛሪ ወደ ውጭ ፍሰት (Net Inflow) ይገጥማቸዋል፡፡

ከዚህ በላይ ከተጠቀሱት ውጪም ሌሎች የውጭ ቀጥታ መዋዕለ ንዋይ ጉዳቶች ተብለው የሚጠቀሱ ሁኔታዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ሕግንና ስምምነትን ጠብቆ አለመሥራት፣ የሠራተኛ መብቶችና የአካባቢ ጥበቃ ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችን ወደጐን መተው፣ በተለያዩ የውጭ ሽያጭ ዋጋ ማጭበርበሪያ ዘዴዎች ገንዘብ ማሸሽ የመሳሰሉት ይገኙባቸዋል፡፡

የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዶቹ በጊዜ ብዛት ለአገር ኢኮኖሚ ተጨማሪ ቋሚ ካፒታል ከመፍጠር አንፃር የውጭ ቀጥታ መዋዕለ ንዋይ ውስጣዊ ባህሪያትን ምን ያህል አጥንተው፣ ‘በሬ ሆይ ሣሩን አየህና ገደሉን ሳታይ’ እንዳይሆን ጥንቃቄ አድርገዋል?

የግል ቋሚ ካፒታል ክምችት በገጠሪቱ ኢትዮጵያ

ኢሕአዴግ በገጠር ቋሚ ካፒታል እንዳይከማችና ምርታማ እንዳይሆን እንቅፋት መሆኑን ቢያውቅ፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ ሁሉንም ታቦቶች ተሸክሞ ይቅርታ በጠየቀ ነበር፡፡

ባለሙያዎች ግብርናው ይዘምን ሲሉ መንግሥት 15 ሚሊዮን የሚሆኑት አነስተኛ ገበሬዎችን የሚተካ ምንም ዓይነት ፖሊሲ ሊመጣ አይገባም ይላል፡፡ እንደ ባለሙያዎቹ ግብርናውን ማዘመን ገበሬው በሙሉ በትራክተር ይረስ ማለት አይደለም፡፡ ከዚህ በመለስም ብዙ ዓይነት መዘመኖች ይኖራሉ፡፡

ግብርናውን ማዘመን ለምን የገጠሩ ሕዝብ በሙሉ እርፍ ይጨብጣል ማለትም ነው፡፡ አንዱ የከብት መኖ በማምረት፣ ሌላው ወተት በማለብ፣ ሌላው የወተት ተዋዕፆዎችን በማምረት፣ ሌላው ዳቦ በመጋገር በራሱ በግብርናው ውስጥ የሥራ ክፍፍል በመፍጠር ግብርናውን ማዘመን አይቻልም ነበርን?

ስለ የደርግ ዘመኑ የትኖራ ሁለገብ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ አግሮ ኢንዱስትሪ ያልሰማ ይኖራል ብዬ አልገምትም፡፡ እኔም ወደ ጐጃም ጉዞ ሳደርግ ቦታው ድረስ ሄጄ ያለሥራ የቆሙትን ሕንፃዎች ጐብኝቼአለሁ፡፡ ተቋሙ ኢሕአዴግ እንደገባ ነው የፈራረሰው፡፡

የትኖራን ከተተበተበበት ርዕዮተ ዓለማዊ አደረጃጀት አላቆ ወደ ነፃ ገበያ ኢኮኖሚ አደረጃጀት ቢቀይሩትና በ25 ዓመታት ውስጥ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የትኖራዎች ተፈጥረው ቢሆን ኖሮ፣ በየዓመቱ ድርቅ መጣ እያልን ወደ ነፍስ አባቶቻችን አውሮፓውያን ባልጮህን ነበር፡፡

የአየር ንብረት ለውጥና ድርቅ የተፈጥሮ ክስተቶች ስለሆኑ ማስቀረት ባይቻልም፣ በገጠር በቂ ቋሚ ካፒታል ተፈጥሮ ቢሆን ኖሮ ወደ ረሃብነት አይቀየሩም ነበር፡፡

በአንድ ጥማድ በሬና በግማሽ ሔክታር መሬት አርሶ ዕድሜ ለምርት ገበያ ድርጅት የሸመታ አቅም የሌላቸውን ከተሜ ኢትዮጵያውያን በአየር ላይ ዘሎ ከአውሮፓ ሸማች ጋር ተገናኝቶ በኩንታል ምርት በሺዎች ቤት ሸጦ፣ በጥቂት ዓመታት የሚሊዮኖች ጌታ ሆነ የተባለው ገበሬ ገንዘብም በንግድ ባንኮች አማካይነት ቦሌና ልደታ መጥቶ ለሕንፃ ግንባታ እንጂ ለገጠሩ ኢኮኖሚ ዕድገት ቋሚ ካፒታል አልሆነም፡፡

አውሮፓና አሜሪካ አራትና አምስት ወራት በበረዶ ሲሸፈኑ ሣር ቅጠል የሚባል ነገር ለዓይን አይታይም፡፡ ከብቶች የሚግጡት ከመስክ ስላልሆነ ሣር ቅጠል ጠፍቶ ከብት አለቀብን ብለው አይጮሁም፡፡ እኛ የበልግ ወይም የመኸር ዝናብ አንድ ወር ዘገየ ብለን የከብት በድን መቁጠር እንጀምራለን፡፡ ቀንና ዓመታት ሲቆጠሩ የተፈጥሮ ላይ ጥገኝነታችንን በመቀነስ ፈንታ የጨመረበትን ሁኔታ ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እንላለን፡፡

የግል ቋሚ ካፒታል ክምችት በከተሞች

አንደኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ስላልተሳካለት፣ ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በተለይ በከተሞች የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በመገንባት ከፍተኛ የውጭ መዋዕለ ንዋይን ለመሳብ የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረት ተሰጥቶት ነጋሪት እየተጎሸመ ነው፡፡

የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ በተለይ ያተኮረው ደግሞ በኤክስፖርት ሸቀጦች ምርት ላይ ነው፡፡ ቻይና ለእኛ መቶ ሚሊዮን ሕዝብ የማፋክቸሪንግ ምርት ስታቅድ፣ እኛ ብዙ ሺሕ ኪሎ ሜትሮች አጓጉዘን ለመቶ ሺሕ የውጭ ዜጐች የማፋክቸሪንግ ምርቶች ቅድሚያ ትኩረት ሰጥተን ለማምረት አቅደናል፡፡

በመጀመሪያው ዕቅድ ዘመን በከተሞች በተገነቡ ሕንፃዎችና መንገዶች ብዛት ቋሚ ካፒታል እንደተፈጠረ ምንም ጥርጥር የለም፡፡ ጥያቄው ግን ምርትን ከማሳደግ አንፃር የእነዚህ ቋሚ ካፒታሎች ምርታማነት ምን ያህል ነው የሚለው ነው፡፡

ከነቦሌና ሲኤምሲ መገናኛ ቀጥሎ በሕንፃ ግንባታ በቅርቡ እያበበ ያለው ልደታ ሠፈር ነው፡፡ ከልደታ ወደ ጌጃ ሠፈር ጠምዘዝ ሲሉ ከዚያም ወደ አብነት ሲያቀኑ፣ ያንንም አልፈው ሰባተኛ ሲደርሱ፣ ጉዞ ቀጥለው ወደ አውቶቡስ ተራ፣ ሰፈረሰላም፣ ጨው በረንዳ፣ ጉለሌ፣ ሸጎሌ፣ ቀጨኔ፣ አፍንጮ በር፣ ሽሮ ሜዳ፣ ቀበና፣ አቧሬ… እያሉ መሀል አዲስ አበባን ያስተውሉ፡፡

ከመሀል አዲስ አበባ የቆዳ ስፋት ምን ያህሉ ነው በሕንፃ የተያዘው ብለው አስበው ይህንን ከኢትዮጵያ ቆዳ ስፋት ጋ ቢያነፃፅሩት እንዲያው ለነገሩ በአዲስ አበባና በአንዳንድ ከተሞች ሕንፃ ቆጠራ የኢትዮጵያን ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን መለካት ይቻላል እንዴ ይላሉ፡፡ በድፍን ሩብ ምዕተ ዓመት አገሪቱ ፈጠረች የሚባለው የግል ቋሚ ካፒታል ክምችት ይኸው ነው፡፡

አስተሳሰባችን ሕንፃዎቹ ከያዙት ቦታ ሰፋ ካላለ እንዴት ነው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ያመጣልን ለውጥ አገራዊ ነው ልንል የምንችለው? ዕድሜ ለቴክኖሎጂ በመረጃ ቅርበት ምክንያት የሰው ልጅ ጭንቅላት እኮ ዛሬ ዓለምን ከአጥናፍ አጥናፍ እያየ ነው፡፡ እኛም ከቦሌና ከልደታ ፈቀቅ ብለን እንይ፡፡

በከተማም በገጠርም ያመለጠ ዕድል

በጂቡቲ በር በኩል ወደ ውጭ ሸቀጥ ልከን ከምናገኘው የውጭ ምንዛሪ አራት እጥፍ በገቢ ሸቀጦች የምናወጣው የውጭ ምንዛሪ ስለሚበልጥ፣ በባቡር ሐዲዱ ከፍተኛ ተጠቃሚ የሆነችው ቻይና ምን ያህል ወጪ ተጋርታለች የሚሉ አንዳንድ ጥያቄዎች ብልጭ ቢሉብኝም፣ በአጠቃላይ በመንግሥት ደረጃ የተፈጠረው አዕምሯዊና ቁሳዊ ካፒታል ለታሰበው የኢኮኖሚ ዕድገት አንሷል የምልበት ምክንያት የለኝም፡፡

ሆኖም በጊዜ ሒደት ከግል ቋሚ ካፒታል የመንግሥት ቋሚ ካፒታል እየበጠለ፣ ከካፒታሊዝም ወደ ሶሻሊዝም ጉዞ እየተደረገ ይመስለኛል፡፡ ሶቭየት ኅብረት ገና በመጀመሪያዎቹ ሁለት የአምስት ዓመታት ዕቅዶች ዘመን አገር ምድሩን በኤሌክትሪክ ኃይል አጥለቀለቀች፡፡ ሌሎችንም መሠረተ ልማቶች በሚያስደንቅ ፍጥነት ገነባች፡፡ በሰባ ዓመታት የሶሻሊዝም አመራር ልዕለ ኃያል አገርም ሆነች፡፡ ሮጣ ሮጣ በመጨረሻ ፈራረሰች፡፡

በቋሚ ካፒታል ክምችት መጠንና ይዞታ የኢትዮጵያ ጉዞ የሶቭየት ኅብረትን ያልመሰለው፣ ሶቭየት ኅብረት በገጠር በስፋት በአምራቾች ማኅበራት የተደራጁ አግሮ ኢንዱስትሪ ፋብሪካዎች በማቋቋም የገጠሩን ቋሚ ካፒታል መገንባቷ ብቻ ነው፡፡

የሩብ ምዕተ ዓመቱ የኢሕአዴግ ዘመን እንደባከነ የሚቆጠረውና ዕድገታችን በግል ቋሚ ካፒታል ክምችት ጠንክሮ በተፋጠነና አስተማማኝ መሠረት በያዘ ኖሮ ብለን ልንቆጭበት የሚገባን፣ በራስ ካፒታል የማደግ ዕድልን አለመጠቀም ነው፡፡

በራስ ካፒታል (Equity Capital) ትልልቅ ማምረቻ ድርጅቶች ማቋቋም እንደሚቻል ከሌሎች አገሮች ልምድ ብቻ ሳይሆን፣ በኢትዮጵያ ንግድ ባንኮችና ኢንሹራንሶች በአክሲዮን ኩባንያነት በመደራጀት በተቋቋሙ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዴት እንዳደጉ አይተናል፡፡ ሕግ ባለመውጣቱ ምክንያት ከባንክ ውጪ የሆኑ በአክሲዮን የተደራጁ የማጭበርበር ሙከራዎች አጋጥመዋቸዋል፡፡

በአክሲዮን መደራጀት ችግር ኖሮት ሳይሆን መንግሥት እንደ መሬቱ ሁሉ ገንዘብ ነክ ጉዳዮች ከእጁ እንዳያፈተልኩ ስለፈለገ፣ በአክሲዮን ተደራጅቶ በራስ ገንዘብ ወይም ከንግድ ባንክ ብድር ውጪ በሰነድ ንግድ (Securities Trading) ወይም የካፒታልና የጥሬ ገንዘብ በጥቅሉ የገንዘብ ገበያ (Financial Market) የገንዘብ ምንጭ ተደራጅቶ ማምረትን ስላበረታታ ነው፡፡

ለንግድ ቅልጥፍናና ለኢኮኖሚ ዕድገት የገንዘብ ምንጭና ገበያ ሊሆኑ ከሚችሉት ውስጥ የካፒታል ገበያ (Capital Market)፣ የጥሬ ገንዘብ ገበያ (Money Market)፣ የውጭ ምንዛሪ ገበያ (Foreign Exchange Market)፣ የሰነድ ገበያ (Derivatives Market)፣ የስምምነት ውል ገበያ (Futures Market) በኢኮኖሚው ውስጥ እንዳያቆጠቁጡ ሆን ተብሎ ዕቀባ ተደርጎባቸዋል፡፡ ለግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ መቀጨጭም ዋነኞቹ ምክንያቶች ናቸው፡፡

በተቆጣጣሪ ባለሥልጣን ክትትል አማካይነት የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ድርጅት (Ethiopian Commodity Exchange) ምን ያህል ውጤታማ እንደሆነ ለመንግሥት ሚስጥር አይደለም፡፡ ሌሎቹ የገንዘብ ገበያዎችም (Financial Markets) በገጠርና በከተማ ተቋቁመው ቢሆን ኖሮ ዛሬ በባለሙያ አደራጅነትና አመራር (Professional Organization and Management) የሚለመልሙ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የአክሲዮን ኩባንያዎች፣ በገጠርና በከተማ ኖረውን በሚሊዮን ለሚቆጠሩ የማኅበራዊ ሳይንስ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን ዕድልም በፈጠሩ ነበር፡፡

በዚህ ጽሑፍ መሥፈርት ላለመራብ አልታቀደም ለዕድገትም በትክክል አልታቀደም፡፡ ለዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ማቀድ ጥሩ ቢሆንም አስቀድሞ ከረሃብ ለመውጣት፣ በረሃብተኝነት ላለመጠራት፣ በዓለም ዙሪያ ለሕፃናት ሳይቀር በስማችን ገንዘብ እንዳይለመን ዕናቅድ፡፡ ‘ዝንጀሮ መጀመሪያ የመቀመጫዬን’ ብላ የለ እንማርበትና በቅድሚያ አንጀታችንን በቁራሽ እናርስ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው Getachewasfaw240 [at] gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡