ለመሆኑ ስንት ትበላላችሁ? አገር ስንት ትከፍላችኋለች?

በበሪሁን ተሻለ

የዓለም አቀፍ የምርመራ ጋዜጠኞች ጥምረት የሚባል አንድ ማኅበር ‹‹የፓናማ ሰነዶች›› ብሎ የሰየመውን ሚስጥርና ጉድ እንደ አዋጅ ቅዳጅ ዘክዝኮና ዘርግፎ ካጋለጠ በኋላ፣ በዚህ ምክንያት በመላው ዓለም ብዙ ጉዳት ደርሷል፡፡ ብዙ ጥያቄ ተነስቷል፡፡ የአይስላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር በሕዝብ የተቃውሞ ግፊት ከሥልጣናቸው ለቀዋል፡፡ የታላቋ ብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ‹‹አልጋ›› ተነቃንቋል እየተባለ ነው፡፡ በርካታዎቹ ታክስ የከፈሉበትን ሪፖርት ለሕዝብ ይፋ እያደረጉ ነው፡፡ የፓናማ ሰነዶች ሚስጥር እያጋለጠ በጉድ ያወጣቸው በየአገሩና እንደየአገሩ በሰውና በሚዲያው አፍ ገብተዋል፡፡ አገር ባበጀው ሥርዓትም ውስጥ ተጠየቁ እየተባሉ ነው፡፡

የፓናማ ሰነዶች ውስጥ ኢትዮጵያን የሚያስደነግጥና የሚያስደንቅ፣ የኢትዮጵያን ወይም የኢትዮጵያዊን ስም የሚጠራ አንዳች ነገር ስለመኖሩ ገና ባናውቅም ጉዳዩ ግን እኛም በአቅማችን አንድ መሠረታዊ ግን ተራ ጥያቄ እንድናነሳ ያስገድደናል፡፡ የመሪዎቻችን ገቢ ምን ያህል ነው? ገቢስ ማለት ምንድነው? ሹሞቻችን ስንት ይበላሉ? ወይም የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት አገራችንን ስንትና ምን ያህል ይበሏታል? አለዚያም ኢትዮጵያ ሹሞቿንና ባለሥልጣኖቿን ምን ያህል ትክሳቸዋለች? ምን ያህል ታበላቸዋለች?

የዚህ ጽሑፍ ዕይታ የሚዘረጋበትን ዳር ድንበር ለመወሰንና የጽሑፉን ጭብጥ ቢጤ ነገር ለማዋቀር፣ ከተዋቀሩት ጥያቄዎች መካከል አንዱ ሹሞቻችን ስንት ይበላሉ የሚለው ጥያቄ ዛሬ ለብዙው ወጣትና ከተሜ ክፋት ያረገዘ፣ ነገር ነገር የሚሸተው፣ ቀኝ አውለኝ ብሎ ያልተነሳ ጥያቄ የሚባል መሆኑ ብዙ አያጠራጥርም፡፡ ስንት ይበላል? ብቻ ሳይሆን ስንት ትበላለህ? ብሎ መጠየቅ ግን ደመወዝህ ስንት ነው የማለት ያህል ንፁህና ገለልተኛ ጥያቄ ነበር፡፡ በተለይ ከመንግሥት የደመወዝ መክፈያ ሰነድ ዝርዝር ውስጥ ከተተከለው ደመወዝተኛ ውጪ ያለው የ‹‹ሰፊው ሕዝብ›› ደመወዝህ ስንት ነው ቋንቋ ስንት ትበላለህ ነበር፡፡

ከጣሊያን ወረራ በኋላና ከነፃነት ወዲህ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ አስተዳደር ሲመሠረት፣ አገሪቷ በጠቅላይ አገረ ገዢዎች በሚተዳደሩ የአውራጃ ግዛቶች ተከፋፈለች፡፡ የአውራጃ ግዛቱ የመንግሥት እንደራሴ ጠቅላይ አገር ገዢው ሲሆን፣ በእያንዳንዱ አውራጃ ግዛት ውስጥ፣ ወይም በአንድ ጠቅላይ አገር ገዢ ሥር የወረዳ ግዛቶችና የወረዳ ገዢዎች አሉ፡፡ በወረዳ ውስጥ ደግሞ ምስለኔዎች የሚያስተዳድሯቸው የምስለኔ ግዛቶች ተቋቋሙ፡፡ አውራጃ ግዛት ይባል የነበረው ጠቅላይ ግዛት፣ የወረዳ ግዛት ይባል የነበረው የአውራጃ ግዛት፣ የምስለኔ ግዛት ይባል የነበው የወረዳ ግዛት የተባለው እያንዳንዱ ወረዳም በምክትል ወረዳ ግዛት እንዲከፋፈል የተደረገው በ1938 ዓ.ም. ነው፡፡ ይህም አከፋፈልና አጠራር ጠቅላይ ግዛትን ክፍለ አገር፣ ጠቅላይ አገረ ገዢውን ወይም እንደራሴውን ዋና አስተዳዳሪ ብሎ ከሰየመው ለውጥ ጋር እስከ 1980 ዓ.ም. መጀመሪያ የደርግ (ወታደራዊ መንግሥት) ዘመን ድረስ ዘልቋል፡፡

በዚያ አዲስ የአስተዳደር ሕግ እንደ አዲሱ አስተዳደር ደንብ ‹‹ጠቅላይ አገረ ገዢዎች፣ ዳይሬክተሮች፣ አገረ ገዢዎች፣ ዳኞች፣ ምስለኔዎች፣ ወታደሮች፣ የዘበኛ አለቆችና ዘበኞች፣ ሌሎችም የመንግሥት ሠራተኞች ሁሉ የንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት በመደበው የወር ደመወዝ አዳሪ ናቸው፡፡ መንግሥት ከወሰነላቸው ደመወዝ በላይ ከሕዝብ ላይ ገንዘብ እንዳይቀበሉ ክልክል ነው፤›› ሲል ደነገገ፡፡

የንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት በ1967 ዓ.ም. ከተወገደ በኋላ በወታደራዊ መንግሥት የመጀመሪያ አፍላ ዘመን ውስጥ የወጣ አንድ ሙዚቃ ‹‹ጉቦና አድልኦ በአዋጅ ሊወጣ ጥቂት ሲቀረው ነው ይኼ ለውጥ የመጣ›› ቢልም፣ ጠቅላይ አገረ ገዢው እንደራሴው በተሾመበት ግዛት ውስጥ ሲዘዋወር ‹‹መጥን፣ መተያያ፣ መስተንግዶ፣ እጅ መንሻ፣ ይህንንም የመሰለ ስጦታ ሁሉ እንዳይቀበል በፍጹም ክልክል ነው፤›› የተባለው ከ1934 ዓ.ም. ጀምሮ ነው፡፡

ከላይ እንደጠቀስነው ምስለኔ ሦስተኛውና የመጨረሻው የአገር አስተዳዳሪ እርከን ሹም መሆኑ ቀርቶ፣ ከነስያሜው የጠፋው የምስለኔ ግዛት ይባል የነበረውም የወረዳ ግዛት የተባለው ገና በ1938 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ ቢሆንም፣ ተሳካም አልተሳካም የእንደራሴነትና የምስለኔነት አስተዳደር ጀመርኩ ያለው ያን ጊዜ ነው፡፡ አንድን የአገር ክፍል ወይም ያኔ ይባል እንደነበረው ‹‹አንዱን አገር›› ማስገዛትና በግዛት ለአንድ ሹም መስጠትና ያንኑ አገር በእንደራሴነት ወይም በምስለኔነት እንዲያስተዳድር ወክሎ መላክ ማለት በጣም የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ እንደራሴም ሆነ ምስለኔ የሚሉት ቃላት ከዘመን ዘመን እየነተቡ የመጡ፣ የሥር የመሠረት ትርጉማቸውንና ጽንሰ ሐሳባቸውን ያጡ ቢሆንም አጀማመራቸው ግን ውክልናን፣ ተጠሪነትን፣ እንደኔ፣ እንደራሴ ሆነህ፣ እኔን መስለህ፣ እኔን አክለህ ሥራ ማለትን የሚያቋቁሙ ነበሩ፡፡

የእንደራሴነትና የውክልና ጉዳይ ግን እንኳንስ በፖለቲካውና በመንግሥት አስተዳደር ጉዳይ ውስጥ ይቅርና በዕለት ተዕለት የማኅበራዊና የንግድ ሥራ ውስጥ እንኳን የጠራ ግንዛቤ ያልተመዘገበበት ባዕድ ጉዳይ ነው፡፡ ግማሽ ምዕተ ዓመት ያለፈው (ከ1953 ዓ.ም. መስከረም 1 ቀን ጀምሮ የፀናው) የፍትሐ ብሔር ሕጉ ፍጥርጥርና አፈጻጸሙ የዚህ አንድ ማሳያ ነው፡፡

የሌላ ሰው እንደራሴ ወይም ወኪል በመሆን ሥራዎችን የመፈጸም ከውል ወይም ከሕግ የሚገኝ ይህ ሥልጣን በሕጉ የእንግሊዝኛው ቅጅ ተጀምሮ እስኪጨረስ ኤጀንሲ ይባላል፡፡ የፍትሐ ብሔሩ የአማርኛ ሕግ ቅጅ ግን እንደራሴነትም ውክልናም ይለዋል፡፡ አማርኛ የግዱን የራሱ ያደረገው ኤጀንሲ ደግሞ በኢትዮጵያ የአብዛኛዎቹ የመንግሥት የአስተዳደር መሥሪያ ቤቶች መጠሪያ ነው፡፡ በግሉ ዘርፍ ደግሞ ከግል ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲ ጀምሮ የንግድ ሕጉ የንግድ ወኪሎች ብሎ የሚያውቃቸው የንግድ ወኪሎች እስከ ‹‹ኮሚሽን ኤጀንቶች›› ድረስ ያለ የሰፋ መጠሪያ ነው፡፡ ከይዘት አንፃር ደግሞ ሕጉ እንደሚለው እንደራሴው የዋናው ባለቤትና ባለመብት ወኪል መሆኑ ቀርቶ ወኪሉ ዋናው የሚሆንበትና በኃላፊነት የማይጠየቅበት ነው፡፡ ሥዕሉ በብዙ ውክልና በሚሰጡ ሰዎች ሕይወት ውስጥ በስፋት የሚታይ ነው፡፡

የወኪልና የተወካይ ግንኙነት ከውል መነጨም ከሕግ በተለይ ለተወካዩ ከሚያስከትላቸው ግዴታዎች አንዱ ለእንደራሴው የሚከፈለው የድካም ዋጋ ነው፡፡ በመንግሥት አስተዳደር ውስጥ ወካዩ ሕዝብ በተደራጀው ዓውደ መንግሥቱ አማካይነት የተለያየ ሥልጣንና ደረጃ፣ እንዲሁም የሥራ መደብ ላላቸው እንደራሴዎቹ የሚከፍለው የድካም ዋጋ ደመወዝ ይባላል፡፡ መንግሥት በኢትዮጵያ ጭምር ትልቁና ግዙፉ ቀጣሪ መሥሪያ ቤት ነው፡፡ የመንግሥት ተቀጣሪዎች ደግሞ በጣም ልዩ ልዩነት አላቸው፡፡ መንግሥት በአመዛኙ የመንግሥትን አስተዳደርና ጠቅላላ ድርጅት በአንድ ዓይነት ደንብና መሠረታዊ ሐሳብ መመራት አለበት ብሎ ሲጀምር፣ የመንግሥት ሠራተኞች ማስተዳደሪያ ጠቅላይ መሥሪያ ቤት፣ ኋላ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ቆየት ብሎ ሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር የሚባል መሥሪያ ቤት ቢኖረውም ሁሉም የመንግሥት ሠራተኛ ግን በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ አይሸፈንም፡፡ ስለዚህም የተለያዩ የመንግሥት ተቀጣሪዎችን በተለይ የሚሸፍኑ ልዩ ልዩ ዓይነት ፈርጆች አሉ፡፡ ለምሳሌ በሲቪል ሰርቪስ ሕጉ መሠረት እንኳን ሚኒስትር ዴኤታዎችን፣ እንዲሁም በተመሳሳይ ደረጃና ከዚያ በላይ የሆኑ ኃላፊዎችን፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላትን፣ የፌዴራል ፍርድ ቤት ዳኞችንና ዓቃብያነ ሕጎችን፣ የመከላከያ ሠራዊትና የፌዴራል ፖሊስ አባላትን፣ እንዲሁም በመከላከያ ወይም በፖሊስ ደንብ የሚተዳደሩ ሌሎች ሠራተኞችን የሲቪል ሰርቪሱ ሕግ አያካትታቸውም፡፡

የተጠቀሱትን የሥራ ክፍሎች (የሚኒስትሮችን፣ የዳኞችን፣ የእንደራሴዎችን፣ ወዘተ) የሲቪል ሰርቪሱ ሕግ አይመለከታቸውም ማለት፣ የእነዚህ ከዚህ አዋጅ/ሕግ ውጪ የተደረጉ የመንግሥት ቅጥር ሠራተኞች የሥራ ሁኔታና የደመወዝ መደብ አይመለከታቸውም ማለት ነው፡፡ የሲቪል ሰርቪሱ የሥራ ሁኔታና የደመወዝ መደብ የማይሸፍናቸው የሠራተኛ ዓይነቶች ግን እነዚህ የታወቁት ብቻ አይደሉም፡፡ በዚህ ረገድ የሲቪል ሰርቪስ ሕጉ እንደሚደነግገው፣ ‹‹አግባብ ባለው ሌላ ሕግ በዚህ አዋጅ እንዳይሸፈኑ የተደረጉ ሠራተኞች›› በርካታ ናቸው፡፡ ለምሳሌ እንደ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ያሉ ሠራተኞች  በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ የራሳቸው የተለየ አስተዳደርና ልዩ የደመወዝ መደብና ስኬል ያላቸው ሠራተኞች አሉ፡፡ የእነዚህ የባለሥልጣኑን ሠራተኞች የሚስተካከልና ምናልባትም የሚያስከነዳ የሚባል አዲሱና የተለየ የደመወዝ መደብ የፈጠረው ደግሞ መጋቢት 2007 ዓ.ም. የወጣው የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ሠራተኞች አስተዳደር ደንብ ነው፡፡

የሚገርመው ግን የተለየ መደብ ሆነው የወጡት የመንግሥት ሠራተኞችም ሆኑ የሌሎች ከመንግሥት ሠራተኞች አስተዳደር ሕግ ሽፋን ውጪ ያሉ የተለያዩ ክፍሎች የተለየ የደመወዝ መደብ ያስፈልጋቸዋል ተብሎ የተወሰነው በሕግ ቢሆንም፣ የደመወዛቸውን መደብ ዝርዝር ግን ለሕዝብ ይፋ ያደረገ ሕግ/ደንብ የለም፡፡ ከመቀጠር ከሚገኝ የወር ደመወዝ አሁን እስከ 150 ብር ድረስ ያለው ገቢ ከግብር ነፃ ቢሆንም፣ የአገራችን የመንግሥት ሠራተኞች ምን ያህል እንደሚበሉ በነጠላም ሆነ በድምሩ ማወቅ የአገር የማወቅ መብት አካል አይደለም፡፡ የአደባባይ ሚስጥርም አይደለም፡፡ ቀድሞ ከነምህፃረ ቃላቱ የፕሮፌሽንና የሳይንስ አገልግሎት (ፕሳ) የአስተዳደር አገልግሎት (አስ) የመለስተኛ ፕሮፌሽን አገልግሎት (መፕ) የጽሕፈትና ሒሳብ አገልግሎት (ጽሒ) የእጅ ጥበብ አገልግሎት (እጥ) የጥበቃና የጉልበት አገልግሎት (ጥጉ) እየተባሉ ከነመነሻ ደመወዛቸውና ከነእርከናቸው የሚታወቁት የሥራ ዓይነቶች፣ ዛሬ ከውስጥ ለውስጥ ዕውቀትነታቸው አልፈው የሕዝብ ሀብትና የዕለት ተዕለት የዕውቀት አካል ሊሆኑ አልቻሉም፡፡

ከመደበኛ የመንግሥት ሠራተኞች ሽፋን ውጪ ያሉት የሚኒስትሮች፣ የአገር መሪዎች ደመወዝና ገቢ ምን ያህል እንደሆነ የሚያውቀው ዛሬም እንደ ድሮው ባለደመወዙና ደመወዝ ከፋዩ ነው፡፡ ከደመወዝ በተጨማሪ የሚከፈሉት ሌሎች ወጪዎች ሲደማመሩ ደግሞ ባለሥልጣኖቻችን የሚበሉትን መጠንና የገቢያቸውን ልክ ለማንም ራሳቸውን ጨምሮ ከዕይታ ውጭ ያደርገዋል፡፡ በሥልጣን የደረጃ ከፍታ መሰላል ላይ ሽቅብ ከፍ እያልን በወጣን ቁጥር ሚስጥሩ ይበልጥ እየጠበቀና ግልጹና አገር ሊያውቀው ፀሐይ ሊሞቀው የሚገባው ጉዳይ ይበልጥ ውስብስብ እየሆነ ይሄዳል፡፡ በአገራችን ደግሞ ሥልጣን በሕግ የተወሰነና የተገደበ ሆነም አልሆነም፣ እስካሁንም ሁልጊዜም ዋናው ባለሥልጣንና ‹‹ፈላጩ ቆራጩ›› አስፈጻሚው አካል ነው፡፡

በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን መሪው የሚቀበሉት ገቢ በሕገ መንግሥቱ በራሱ ‹ሲቪል ሊስት› ይባል ነበር፡፡ በወቅቱ የነበረው ሕገ መንግሥት የንጉሠ ነገሥቱ ቤተ ዘመዶች የማዕረግ ሁኔታ፣ ተግባርና ኃላፊነት፣ መብት፣ ደመወዝ፣ ወደ ውጭ አገር አካሄዳቸውና አኗኗራቸው በየጊዜው በዘውድ ምክር ቤት እየተጠና በሥራ ላይ እንዲውል የምክር ቤቱ አስተያየት ለንጉሠ ነገሥቱ ይቀርባል ማለት ድረስ መደንገጉ፣ ዛሬ ጭምር በላቀ አሠራርና ሥርዓት ዋጋ አጥቶ የተዘጋ ጉዳይ አይደለም፡፡ የ1948 ዓ.ም. ሕገ መንግሥት ንጉሠ ነገሥቱ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ላለበት ለንጉሠ ነገሥትነት ተግባሩ መፈጸሚያ ከተግባሩ ጋር ተመዛዛኝ የሆነውን ገንዘብ፣ ከንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት ግምጃ ቤት በሕግ የተወሰነውን ገንዘብ (ሲቪል ሊስት) በየዓመቱ እየተቀበለ ያዝበታል በማለት ይደነግጋል፡፡ ሲቪል ሊስት ማለት መንግሥት የንጉሠ ነገሥቱንና የንጉሣዊ ቤተ ዘመዱን ወጪ ለመሸፈን የሚከፍለው/የሚያወጣው ገንዘብ ቢሆንም፣ በወቅቱ በቤተ መንግሥቱ ወጪና በንጉሠ ነገሥቱ ደመወዝ መካከል ልዩነት ማበጀት የሚችል ወግ ስለመኖሩ ማስረዳት ቀርቶ መጠርጠር እንኳን የሚቻል አይመስለኝም፡፡

እንዲህ ያለ ለወግ የተቀዳ ሕግም እያለ ‹‹አገሩ የንጉሥ ነው›› እያልን እየዘመርን እንዳልሆነ አድርገን አሰናብተን ደርግ መጣ፡፡ ደርግ የርዕሰ ብሔሩን (የደርግን) ሊቀመንበርና አባላት የደመወዝ ጉዳይ እንደ ተወገደው መንግሥት እንኳን ለወግ ያህል የሕግ ርዕሰ ጉዳይ የማድረግ ጨዋነት ሳይፈጥርበት በዚያው ተሰናበተ፡፡ ስለመንግሥቱ ኃይለ ማርያም ደመወዝ ሲነገር በሕግ ሳይሆን በአጋጣሚ ምክንያትና በእነሱ መልካም ፈቃድ የተነሳ፣ ሰውየው በአንድ ኮሎኔል ደመወዝ የሚተዳደሩ፣ ስለዚህም ለኢትዮጵያ ሕዝብ ውለታ የሠሩ መሆኑ ሲነገረን ነበር፡፡                             

ደርግ ከተወገደና ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘ ወዲህ ሃያ አምስት ዓመታችንን ግንቦት ላይ እናከብራለን፡፡ በዚህ ዘመን ውስጥ በ2001 ዓ.ም. ከኃላፊነት የሚነሱ የአገርና የመንግሥት መሪዎች (ፕሬዚዳንት፣ ጠቅላይ ሚኒስትርና፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር)፣ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች (ሚኒስትሮች፣ ሚኒስትር ዴኤታዎችና በእነሱ ደረጃ የሚገኙ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች) ስለሚያገኙዋቸው ጥቅሞች የሚደነግግ ሕግ ወጣ፡፡ ይህም ሕግ ከኃላፊነት የተነሳ የአገር መሪ ለምሳሌ በኃላፊነት ላይ በነበረበት ጊዜ ይከፈለው የነበረው የወር ደመወዝና አበል ከኃላፊነት ሲነሳም እንደማይቋረጥበት፣ በሥልጣን ላይ ያለ የአገር መሪ የደመወዝና አበል ማስተካከያ ሲደረግ ከኃላፊነት ለተነሳውም የአገር መሪ የግል ወጪና የአበል ማስተካከያ እንደሚደረግለት፣ ወዘተ ደነገገ፡፡ በጣም ጥሩ ነው፡፡ ሥልጣን ላይ ያለው የአገር መሪ (ፕሬዚዳንት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩና ምክትሉ) የሚከፈላቸው ደመወዝና አበል ግን ምን ያህል እንደሆነ አናውቅም፡፡ አልተነገረንም፡፡ አሁንም የመሪያችንን ደመወዝ ግምት በዚህ ጊዜ ውስጥ እንደ አጋጣሚ ያወቅነው ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር በአንድ ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ‹‹ተገድደው›› ሲናገሩ ነው፡፡ በዚያ መሠረት አሁንም የምናውቀው የጠቅላይ ሚኒስትራችን ደመወዝ ስድስት ሺሕ ብር መሆኑን ነው፡፡ ስለአበላቸው በጭራሽ አንድም ነገር አይታወቅም፡፡

ከዚህ የመንግሥት ዘርፍ የተሻለ ግልጽ ሆኖ የጀመረው ፓርላማው ነው፡፡ በዚህ ረገድ የ1948 ዓ.ም. ሕገ መንግሥት እስካሁን ድረስ ወደር ያላገኘ በመርህ ላይ የተመሠረተ የደመወዝ ድንጋጌ ነበረው፡፡ የፓርላማ አባላት በሕግ የተወሰነውን ደመወዝ ይቀበላሉ፡፡ ፓርላማ የአባላቱን ደመወዝ የሚያሳድግ ማናቸውንም ሕግ ያወጣ እንደሆነ ያ ሕግ ሊሠራበት የሚችለው ቀጥሎ የሚመረጠው ፓርላሜንት ከተሰበሰበ በኋላ ወይም የሚቀጥለው ፓርላማ ከተመረጠ በኋላ ነው ይላል፡፡ የዚህ ትርጉም አንድ ለአራት ዓመት የሥራ ዘመን የሚመረጡ የፓርላማ አባላት የራሳቸውን የግለሰብ አባላቱን ደመወዝ የሚጨምር ሕግ ሊያወጡ አይችሉም፡፡ የሕጉ ተፈጻሚነት የሚጀምረው የዚያ ፓርላማ አባላት የአራት ዓመት የሥራ ዘመን ካበቃ በኋላ በሚቀጥለው ምርጫ ለተመረጡ አባላት ነው ማለት ነው፡፡

በዚህ መሠረት ከ1954 ዓ.ም. ጀምሮ የፀናው የፓርላማ አማካሪዎች ደመወዝ አዋጅ የእያንዳንዱ የፓርላማ አማካሪ የወር ደመወዝ አምስት መቶ ብር እንዲሆን ወሰነ፡፡ ሁለተኛውንና የፓርላማ አባላት የወር ደመወዝ ወደ አንድ ሺሕ ብር ከፍ አድርጎ የወሰነው የፓርላማ አባላት የደመወዝ ጭማሪ አዋጅ የወጣው በ1965 ዓ.ም. ሲሆን፣ የአዋጁ ተፈጻሚነት የጀመረው ደግሞ በ1965 ዓ.ም. አምስተኛ ምርጫ ለተመረጡትና ሥራቸውን ከጥቅምት 23 ቀን 1966 ዓ.ም. ለጀመሩት አዲስ ተመራጭ የፓርላማ አባላት ነው፡፡ የንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት የፓርላማ አባላት የሚበሉት ስንት ነው? የሚለው ጥያቄ ከላይ እንደተመለከትነው የሕግና የአዋጅ መልስ ያገኛል፡፡ የ500 ብር እና የአንድ ሺሕ ብር ደመወዝተኛ መሆናቸውን ለውስጥ አዋቂ ብቻ አይተውም፡፡ ሥርዓቱ ሲጀመር የያዘው አያያዝ ሌላም ውበትና ልቀት ነበረው፡፡ የፓርላማ አባላት ደመወዝ የሚወሰነው በሕግ በመሆኑና ሕግ አውጭው ደግሞ ፓርላማው ስለሆነ፣ የፓርላማ አባላት የደመወዝ ሕግ ተፈጻሚነት የሚጀምረው ሕጉን ያወጣው ፓርላማ የሥራ ዘመን ካበቃ በኋላ ነው ማለት የመሰለ የጥበቃ ሥርዓት ተቋቋመ፡፡ እንደሚታወቀው ይህ አሠራር አልቀጠለም፡፡ ሥራውን በ1966 ዓ.ም. የጀመረው የ1965 ዓ.ም. ብሔራዊ ምርጫ ውጤት የሆነው ፓርላማ በ1967 ዓ.ም. መፈንቅለ መንግሥት ተበተነ፡፡ ሕገ መንግሥቱም ታገደ፡፡

የደርግ አባላቱንም ሆነ የብሔራዊ ሸንጎ እንደራሴዎች ደመወዝ በሕግ ቀርቶ አደባባይ በወጣ ሰነድ ሳናውቅ ደርግ ተወገደ፡፡ የሽግግሩ መንግሥት ተቋቋመ፡፡ የተወካዮች ምክር ቤት በተቋቋመ በዚያው ዓመት ውስጥ ከነሐሴ 30 ቀን 1983 ዓ.ም. ጀምሮ በፀና አዋጅ የተወካዮች ምክር ቤት አባላት ደመወዝና አበል ተወሰነ፡፡ በዚህ መሠረት የተወካዮች ምክር ቤት ደመወዝ አበል 750 ብር ሆኖ ተወሰነ፡፡ ስለዚህም በሽግግሩ ቻርተር እንደተወሰነው ከብሔራዊ ነፃነት ንቅናቄዎች፣ ከሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች ተውጣጥተው ለተወከሉት ከ87 ለማይበልጡ አባላት የሚከፈለው የአንድ እንደራሴ አባል ደመወዝ 750 ብር ሆነ ማለት ነው፡፡

የ1983 ዓ.ም. የተወካዮች ምክር ቤት የአባላት ደመወዝና አበል መወሰኛ አዋጅ ግን በዚህ አያበቃም፡፡ አንድ የተወካዮች ምክር ቤት አባል የተወሰነውን የወር ደመወዝ ወይም የምክር ቤቱ አባል እስኪሆን ሲሠራ በነበረበት የመንግሥት መሥሪያ ቤት ወይም የመንግሥት ተቋም ይከፈለው የነበረውን የወር ደመወዝ የመምረጥ መብት ተሰጠው፡፡ የተወካዮች ምክር ቤት ምክትል ሊቀ መንበርና ጸሐፊው እያንዳንዳቸው 1,500 ብር የወር ደመወዝ እንዲከፈላቸውም በሕግ ተወሰነ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የ1983ቱ ሕግ የተወካዮች ምክር ቤት አባላትን አበል ወሰነ፡፡ እያንዳንዱ አባል 500 ብር ታክስ የማይከፈልበት የቤት አበል እንዲከፈለው ወሰነ፡፡ ይህ የቤት ኪራይ አበል ግን ለተወካዮች ምክር ቤት ምክትል ሊቀ መንበር፣ ለጸሐፊው፣ የሚኖርበት የግል ቤት ላለው አባል፣ ኪራይ ሳይከፍል የሚኖርበት የመንግሥት ቤት ለተሰጠው አባልና የምክር ቤቱ አባል ከመሆኑ በፊት፣ ሲሠራ በነበረበት የመንግሥት መሥሪያ ቤት ወይም ተቋም ይከፈለው የነበረውን የወር ደመወዝ ለማግኘት ለመረጠ አባል ተፈጻሚ እንደማይሆን ተደነገገ፡፡

የሽግግሩን መንግሥት የተወካዮች ምክር ቤት ተራ አባላት የወር ደመወዝ 750 ብር ያደረገው፣ የተወካዮች ምክር ቤት ምክትል ሊቀ መንበሩንና የምክር ቤቱን ጸሐፊ ደመወዝ ደግሞ ወደ 1,500 ብር ከፍ አድርጎ የወሰነው አዋጅ የተወካዮች ምክር ቤትን ሊቀ መንበር ደመወዝና አበል መኖሪያ በዝምታ ያለፈው ያላንዳች ‹‹ይሉኝታ›› ያላንዳች ማንገራገር ነው፡፡ በቻርተሩ መሠረት (አንቀጽ 9) የተወካዮች ምክር ቤት ዋና ሊቀመንበር ማለት የአገሪቷ ርዕሰ ብሔር ነው፡፡ የሽግግሩ መንግሥት ፕሬዚዳንት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ነው፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በላይ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩን የሚሾመው እሱ ነው፡፡ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ነው፡፡ የተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ የሚመራው፣ ምክር ቤቱን የሚወክለውና የሚያስተባብረው የምክር ቤቱ ሊቀመንበር የአገሪቷ ርዕሰ ብሔርና ፕሬዚዳንት ነው፡፡ የምክር ቤቱ ሊቀመንበር ደግሞ የምክር ቤቱ አባል ነው፡፡

የተወካዮች ምክር ቤት አባላትን ደመወዝና አበል ለመወሰን የወጣው የነሐሴ 30 ቀን 1983 ዓ.ም. ሕግ ዝም ብሎ ያለፈው፣ ሆን ብሎ የዘለለው የተወካዮች ምክር ቤት ሊቀመንበርን ደመወዝ ብቻ አይደለም፡፡ አበሉንና የመኖሪያ ቤቱን ጉዳይ ጭምር ነው፡፡ ‹‹ተራሮችን ያንቀጠቀጠው ትውልድ›› አባላትም እንደተለመደው እዚህ የግልጽነት ጣጣ ውስጥ መግባት አልፈለጉም፡፡

ከዚያ ወዲህና ከዚያ በኋላም በአዋጅ ተቆርጦ መወሰን የጀመረው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ደመወዝ ራሱ በዚያው አምሮበት አልቀጠለም፡፡ ቁጥራቸው ከ87 እንደማይበልጥ ከተወሰነው ከሽግግሩ መንግሥት የተወካዮች ምክር ቤት በኋላ አምስት መደበኛ ጠቅላላ ምርጫ ተካሂዷል፡፡ አምስት ምክር ቤትም ተመሥርቷል፡፡ የእያንዳንዱ ምክር ቤት አባል ቁጥር ደግሞ 547 ያህል ነው፡፡ የምክር ቤቱን አባላት ደመወዝ፣ አበልና ጥቅማ ጥቅም የሚወስነው የሥልጣን አካል ማነው? ራሱ ምክር ቤቱ ነው? የአሁኑ የአምስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ደመወዝ ስንት ነው? ይህንን ሁሉ ዛሬም እንደገና በሕግ አናውቅም፡፡

ከኃላፊነት የተነሱ የአገርና የመንግሥት መሪዎችን፣ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎችን፣ የምክር ቤት አባላትና ዳኞችን መብቶችና ጥቅሞች የወሰነው አዋጅ የምክር ቤት አባላት ከጡረታ መብታቸው በተጨማሪ የመቋቋሚያ አበል፣ የሥራ ስንብት ክፍያ፣ የመኖሪያ ቤትና የተሽከርካሪ አበል፣ የሕክምና አገልግሎትና የግል ደኅንነት ጥበቃ እንደሚያገኙ ይደነግጋል፡፡ የዚህ ልክና መጠን በመደበኛ ደመወዝ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ፣ ኢትዮጵያ የአንድ ወቅት አገልጋዮቿን ምን ያህል እንደምትክስም ሆነ የአገሪቱ ኢኮኖሚ በዚህ ረገድ በየጊዜው የሚጨመርበትን ጫና ለማወቅ ማንም አይችልም፡፡

ቀደም ሲል የ1948 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ስለፓርላማ አባላት የደመወዝ አወሳሰን የደነገገውን ገልጸናል፡፡ የፓርላማ አባላት በሕግ የተወሰነውን ደመወዝ ይቀበላሉ ይላል፡፡ የፓርላማ አባላት ደመወዝ በሕግ መወሰን አለበት ማለት ነው፡፡ የፓርላማ አባላት ደመወዝ የፔይሮል ዝግጅት፣ የአስተዳደር ውሳኔ፣ የሰርኩላርና የቢሮ ውስጥ ማስታወሻ ነገር አይደለም ማለት ነው፡፡ በሕገ መንግሥት ደረጃ የተወሰነው የፓርላማ አባላት ደመወዝ ጉዳይ ሌላም የሚገርም የመርህ ጉዳይ አስተጋብቶ ያቋቁማል፡፡ ፓርላማው የአባላቱን ደመወዝ የሚያሳድግ ማናቸውንም ሕግ ያወጣ እንደሆነ ያ ሕግ ሊሠራበት የሚችለው ቀጥሎ የሚመረጠው ፓርላማ ከተሰበሰበ በኋላ ነው ይላል፡፡

ከ60 ዓመታት በፊት የወጣውን ሕገ መንግሥትና በእሱ መሠረት ተቋቋመ የተባለውን ሥርዓት የተዋጋውና የታገለው ትውልድ ግን ይህንንም መርህ ጭምር አላምንበትም ሊል አይችልም፡፡ ያልተሠራበትና በተግባር ላይ ያልዋለ መሆኑ ሊያስቆጨው ይገባል እንጂ፡፡ በተግባር የሆነው ግን ሌላ ነው፡፡ የ1987 ዓ.ም. ሕገ መንግሥት የዚህ አቻ ድንጋጌ ሳይኖረው መቅረቱ ብዙ ባያስደንቅም፣ በሕገ መንግሥቱ ሥር የወጡ ሌሎች ሕጎች ይህንን ሊስቱትና ሊያልፉት ባልተገባ ነበር፡፡ እንደምናውቀውና የሆነው ግን ከዚያ የባሰና የበለጠ ነው፡፡ የዚህ ማሳያ ከኃላፊነት የተነሱ የአገርና የመንግሥት መሪዎች፣ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች፣ የምክር ቤት አባላትና ዳኞች የሚያገኙዋቸውን መብቶችና ጥቅሞች ለመወሰን የወጣው አዋጅ የተፈጻሚነት ጊዜ ነው፡፡

ይህ አዋጅ የ2001 ዓ.ም. አዋጅ ነው፡፡ በ2001 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ ጳጉሜን 4 ቀን የታወጀ ሕግ ነው፡፡ ተፈጸሚነቱን የጀመረው ግን ከሐምሌ 1 ቀን 2000 ዓ.ም. ጀምሮ ነው፡፡ ይህ አዋጅ አሁን የካቲት 8 ቀን 2008 ዓ.ም. እንደገና ተሻሽሏል፡፡ የተሻሻለውም በዋነኝነት የፌዴሬሽን ምክር ቤት በቋሚነት የሚሠራ የምክር ቤቱን ቋሚ ኮሚቴ አባላትን ለማካተት ነው፡፡ በማሻሻያው አዋጅ የተፈጻሚነት ድንጋጌ መሠረት አዋጁ በሥራ ላይ ከዋለበት ከሐምሌ 1 ቀን 2000 ዓ.ም. ጀምሮ በፌዴሬሽን ምክር ቤት በቋሚነት ላገለገሉና ለተሰናበቱ የቋሚ ኮሚቴ አባላትም ጥቅሙ ተፈጻሚ እንዲሆን በየካቲት 2008 ዓ.ም. ሕግ ተወሰነ፡፡

ሥልጣን ላይ ያሉ ወኪሎቻችን፣ እንደራሴዎቻችን፣ ምስለኔዎቻችን፣ በሰጠናቸው የውክልና ሥልጣን መሠረት መፈጸማቸውን የማረጋገጥ ግዴታ አለባቸው፡፡ እኛም የመጠየቅ መብትና ሥልጣን አለን ማለት እንኳን በእኛ አገር ምራቃቸውን በዋጡ፣ ጠያፋቸውን በከተቱ ዴሞክራሲዎችም ውስጥ ገና የ‹‹ደላው›› ወሬ ነው፡፡ ለመሪዎቻችን በግልጽ የሰጠነውና የምናዝበት የውክልና ሥልጣን ኖረም አልኖረም፣ ሕግና ሥርዓት የማስከበር መነሻ ግዴታና ግዳጅ ያለባቸው ሹማምንት ከዚህ በተጨማሪ ለአገልግሎታቸው የሚያስከፍሉንን ዋጋ በግልጽ ሊነግሩን ይገባል፡፡ ደመወዛቸውን፣ አበላቸውንና ወጪያቸውን በዝርዝር መተሳሰብና ሒሳብ ማወራረድ አለባቸው፡፡

በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በሆነ አጋጣሚ ጉዳዩ ተነስቶ ስለበጀት ሲናገሩ፣ በዓለም ላይ የታተመ በጀት የሌለው ብቸኛው መንግሥት ያሉት የኤርትራን መንግሥት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ቢያንስ ከሐምሌ 1 ቀን ጀምሮ አለዚያም ከዚያ በፊት በጀቷን በኦፊሴል ጋዜጣዋ አትማ የማውጣት ባህልና ሕግ ያላት አገር ናት፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን ለሹማምንቶቻችን የምንከፍለው ደመወዝና ሌላም ሌላም ወጪ በየመንግሥት መሥሪያ ቤቱ የበጀት ኮድና የወጪ አርዕስት በ‹‹አስተዳደርና ጠቅላላ አገልግሎት›› ውስጥ ብቻ ተግበስብሶና ተደባብሶ መቀመጥ የለበትም፡፡

በእያንዳንዱ የበጀት አዋጅ ላይ እንደሚነበበው ጠቅላላ የተፈቀደ በጀት አለ፡፡ ለምሳሌ ከሐምሌ 1 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2008 ዓ.ም. ድረስ ባለው በአንድ የበጀት ዓመት ጊዜ ውስጥ የፌዴራል መንግሥቱ ከሚያገኘው ገቢና ከሌላም ገንዘብ (የውጭ አገር ዕርዳታና ብድር) ለተጠቀሱት ሥራዎችና አገልግሎቶች 223.3 ቢሊዮን ብር ለፌዴራል መንግሥት ወጪ ሆኖ እንዲከፈል በአዋጅ ታዟል ሲባል፣ እዚያ ውስጥ ያለውን የሹማምንት ክፍያና ሌላም ወጪ ማየትና ማሽተት አለብን፡፡

መንግሥት ይህን ሁሉ ገንዘብ የሚሰበስብበት አንደኛ ምንጩ የገቢ ግብር ነው፡፡ ከመቀጠር ከሚገኝ ገቢ ጭምር ነው፡፡ ባለሥልጣኖቻችን ግብር የሚከፍሉበት ቢያንስ ቢያንስ ከመቀጠር የሚገኝ ገቢ አላቸው፡፡ አሠሪያቸው መንግሥት ነው፡፡ ለተራው ሰውም ለእነሱም በሚያገለግል የግብር ሕግ መገዛት አለባቸው፡፡ የምናውቃቸው አሠራሮችና ሕጎች ግን ከዚህ ክስና ሐሜት የሚጠብቁ አይደሉም፡፡ ለምሳሌ ለግብር ዓላማ ሲባል የመዘዋወሪያ አበል ከሠራተኛው ደመወዝ አንድ አራተኛ የውሎ አበል ደግሞ ከአራት በመቶ መብለጥ የለበትም የሚለው የገቢ ግብር ሥርዓት ግን፣ በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ወይም በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ቦርድ አባል ወይም ጸሐፊ፣ እንዲሁም የፌዴራልና የክልል መንግሥታት ወይም የከተማ መስተዳድሮች በሚያቋቁሟቸው የጥናት ቡድኖች አባል ወይም ጸሐፊ በመሆን የሚከፈል አበል ከግብር ነፃ ነው፡፡ ከግብር ነፃ መሆኑ ብቻ ሳይሆን የግብር አስገቢው ባለሥልጣን ክፍያ መጠን ላይ የመወሰን ሥልጣን የለውም፡፡ እነዚህ ቦታዎች ላይ ያለ የቦርድ አባልነት ደግሞ ለመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት የተከለለና የቀበጠ ቦነስ የሚያስገኝ፣ እነዚሁ ባለሥልጣናት እየተለዩ የሚሠሩበት ቦታ ነው፡፡

የመንግሥት ባለሥልጣናት ገቢ ግን ፔይሮል ላይ የሚተከለውና ከቦርድ አባልነት የሚገኘው ክፍያ ብቻ አይደለም፡፡ በአስፈጻሚው አካል ውስጥ በተወሰኑ የተለያዩ መመርያዎች መሠረት በርካታና ጥቃቅን የሚመስሉ ለአገር ኢኮኖሚ ግን ከፍተኛ ጫና የሚፈጥሩ ጥቅማ ጥቅሞች አሉ፡፡ የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ የሚያስተዳድራቸው ቤቶች የባለሥልጣናት ቤተ ርስቶች ናቸው ከተባለ ቆይቷል፡፡ በ2006 ዓ.ም. ለተወካዮች ምክር ቤት በድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ የቀረበው ሪፖርት መነሻ ሆኖ እንደተገለጸው፣ እነዚህ ቤቶች በ1998 ዓ.ም. በወጣ መመርያ መሠረት ለአካል ጉዳተኞች፣ ለኤችአይቪ/ኤድስ ታማሚዎችና ለመንግሥት ባለሥልጣናት የተከለሉ ለሌላ የተከለከሉ ናቸው፡፡ በእንዲህ ዓይነት አሠራር 1.3 ትሪሊዮን ብር ዋጋ ያለው የመንግሥት የመኖሪያ ቤት የመንግሥት ባለሥልጣናት ነው ማለት ነው፡፡ እንዲያም ሆኖ ሪፖርቱን ያቀረቡት ባለሥልጣን ለፓርላማ አማረው እንደተናገሩት የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ መልካም ተከራዮች (ጭሰኞች) የሉትም፡፡ በቀን በአማካይ 49 የጽሑፍ መልዕክት ይደርሳቸዋል፡፡ ብዙዎቹ ምሬቶች አስፋልት ይሠራልን ዓይነት ትዕዛዞች ናቸው፡፡

ለባለሥልጣናት የተሰጡ ቤቶች የስልክ፣ የመብራትና የውኃ ወጪም ሹሙ የሚሠራበት ባለበጀት መሥሪያ ቤት ነው፡፡ ለቤትና ለቤተሰብ አገልግሎትም የመኪና ምደባ አለ፡፡ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የውስጥ የአሠራር መመርያ መሠረት ደግሞ የሚኒስትሮች የውጭ አገር ጉዞ የቤተሰብ አባላትን ሊያካትትና ይህም ሊፈቀድ እንደሚችል ይወስናል፡፡ የኢትዮጵያ የኢሚግሬሽን፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብም የዲፕሎማቲክ ፓስፖርት ለተሰጣቸው ሰዎች የቤተሰብ አባላት የሰርቪስ ፓስፖርት እንደሚሰጥ ይደነግጋል፡፡

ይህ ሁሉ ግን አነሰም በዛም ጥቅምም ወጪም ነው፡፡ አገር ረዥም የባካናነትና የዝርፊያ ዘመን አሳልፋለች፡፡ አሥራ ሰባት ዓመት ከፈጀው ጦርነት በኋላም እነሆ ሃያ አምስት ሊሞላን ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ሌላው ቢቀር የነፃነትና የእኩልነት ንቃቱና የትግል ፍላጎቱ በውስጣችን ማደግ አለበት፡፡ ከእነዚህ መካከል አንዱ የአስተዳደራችን ወጪ ነው፡፡ የውክልና ሥልጣን ለሰጠናቸው ወይም በሆነ ምክንያት የውክልና ሥልጣኑን ወስደው በእጃቸው ለያዙት የምናወጣው ወጪ ምን ያህል ነው? በዚህ ላይ ገና ግልጽነት የለንም፡፡ ሥርዓት አላበጀንም፡፡ እንዲያውም ከመፈራራቱ ከዱሮው ባህል አልወጣንም፡፡ ሁለት አጉልቶ ማሳያ ምሳሌዎችን እንመልከት፡፡

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሴት ልጃቸውን መዳራቸውን የሩቅ ዜና ሆኖ ሰምተናል፡፡ የማንኛውም የመንግሥት ሚዲያ ዜና ግን አልሆነም፡፡ የዚህ ምክንያት ጉዳዩ በሚዲያ ዓይን አልሞላ ብሎ የዜና ፋይዳ ጎድሎት ሳይሆን፣ ሲወርድ ሲዋረድ በመጣው የመንግሥት ሚዲያን በሚገዛው ደንብ መሠረት ጉዳዩን ‹‹እርም›› ወይም ‹‹ሀራም›› ስላደረግነው ነው፡፡ የአንድ አገር ጠቅላይ ሚኒስትር በተለይ ደግሞ የእኛ የአገር መሪ ልጅ መዳር፣ የልጅን አበባ ማየት ጉዳይ ግን የግል ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ ይህን የግል ጉዳያቸውን ከመንግሥቱ ሥልጣንና ሚና ጋር ‹‹ሳያጠቃቅሱ›› እንዴት አድርገው ተወጡት? ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሪፖርት ሊያደርጉበት ሌላው ቢቀር ሪፖርት ሊደረግበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ አባትና እናት ልጃቸውን የሚድሩት ከመደበኛ መኖሪያ ቤታቸው ነው፡፡ በአጋጣሚ ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትሩ መደበኛ መኖሪያ ቦታ ‹‹የግል ቤት›› ብቻ አይደለም፡፡ የግል ቤትም ነው፡፡ የመሥሪያ ቤቱን የግል ገጽታ ከሌላው ገጽታው ጋር እንዴት እንዴት አድርገው አጣጣሙት? መመለስ ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ አዳዲስ አሠራሮችን ለማስተዋወቅ ነባሮችን ለማስወገድም ይጠቅማል፡፡

ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ጉዳይና ምሳሌ ሳንወጣ አንድ ተጨማሪ ማሳያችን የቀዳማዊት እመቤቷ ሚና ነው፡፡ በዚህ ረገድ በአቶ ኃይለ ማርያም ዘመን የቀዳማዊት እመቤቷን ሚና ተቋማዊ ልክና መልክ ለመስጠት በሚደረግ፣ ቢያንስ ቢያንስ በመታየት ላይ ያለው ሁሉ የሚደፋፈርና የሚመረቅ ነው፡፡ የቀዳማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤት ሲባልም በይፋ መስማት ጀምረናል፡፡ ይህ በጎና ቅን ጥረት ግን በሕግ መታገዝ አለበት፡፡ የሕግ ድጋፍ ሊያገኝ ይገባዋል፡፡ በዚህ አማካይነት የአንድን ሰው የግል ጉዳይና የመንግሥት አስተዳደር ወጪያችንን መለየት እንችላለን፡፡

እስካሁን ወደ ሥልጣን የመጡት መሪዎቻችን በአጋጣሚና በአብዛኛው የግል የንግድ ሥራቸውን ትተው ሀብታቸው ላይ ቆልፈው የመጡ አይደሉም፡፡ እንዲያውም በአብዛኛው ይህ ስለመኖሩ የሚያውቁ አይደሉም፡፡ እስከዛሬ ድረስ ስንፈራው የኖርነውና መላም ያላበጀንለት አደጋ የመንግሥት ሥልጣንን የግል ርስተ ጉልት ማድረግን ነው፡፡ ከሌላ ማዕዘን ለግል ሀብትና ድርጅት ጥቅም የመንግሥትን ሥልጣን በ‹‹ሊዝ›› የመውሰድ ዓይነት ዘዴም አለ፡፡ ለምሳሌ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ እሱ በተደጋጋሚ ሲለው እንደነበረው ፕሬዚዳንት ሳይሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሆን፣ አሁን ዋነኛው ሥራው አድርጎ የሚያካሂደውን የንግድ፣ የኢንዱስትሪና የኢንቨስትመንት ሥራውን ምን አድርገው እንለዋለን? ውክልና ሰጥቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊሆን? እንዲህ ያለ ጉዳይ የሚገዛ ሕግና ሥርዓት ቀርቶ አስፈላጊነቱንስ እናውቃለን?

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በቅርቡ ከምሁራንና ከመምህራን ጋር ባደረጉት ውይይት የወር ደመወዝዋ 150,000 ብር ስለሆነ የአንድ ማኅበር ሊቀ መንበር አንስተው ነበር፡፡ በወር 150 ሺሕ ብር ማለት በቀን አምስት ሺሕ ብር ማለት ነው፡፡ የተለያዩ የዓለም መሪዎችን ደመወዝ በነገረኝ አንድ ዌብሳይት መሠረት የእኛ የማኅበር ሊቀመንበር ደመወዝ ከግብፅና ከላይቤሪያ ፕሬዚዳንቶች፣ እንዲሁም ከስፔን ጠቅላይ ሚኒስትር ደመወዝ ይበልጣል፡፡ የቻይናውን ፕሬዚዳንት ደመወዝማ ከአራት ጊዜ በላይ ይበልጣል፡፡ ዋናው ጉዳያችን ግን የእኛን መሪዎች ደመወዝ እንኳን ለማነፃፀር ለወሬ ያህል እንኳን የማናውቅ መሆናችን ነው፡፡ ስንት ትበላላችሁ? አገር ስንት ትከፍላችኋለች? ሹሞቻችን አገራችንን ስንት ይበሏታል? በሹክሹክታ የሚቀርብ ጥያቄ መሆን የለበትም፡፡ የአገር ዕውቀት ሊሆን ይገባል፡፡

  ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡