ሁሉም የሚኮመኩመው ሚዲያ ዛሬም ሹክሹክታ ነው

በአብዱ አሊ ሒጅራ

ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ባለአደራና ተጠሪ ዩኔስኮ ነው፡፡ ዩኔስኮ ማለት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት ነው፡፡ አገራችን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል፣ ከአባልም መሥራች አባል ናት፡፡ ከዚህም በላይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት ብሔራዊ ኮሚሽንን በኢትዮጵያ በሕግ ያቋቋመች አገር ናት፡፡ የዩኔስኮን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ኮሚሽን ያቋቋመውና ከጥር 23 ቀን 1961 ዓ.ም. ጀምሮ የፀናው ይህ ሕግ (ትዕዛዝ ቁጥር 55) ዛሬም ሕጉ ካቋቋመው ኮሚሽን ጋር ሥራ ላይ አለ፡፡ እንደ ዩኔስኮ ያለ የመንግሥታቱ ድርጅት አስተዳደርና ሥርዓት ክፋይ (ወይም የዩናይትድ ኔሽንስ ኤጀንሲ) የሆነ ራሱን ችሎ ብሔራዊ ኮሚሽን የተቋቋመለት ሌላ አካል ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ አይመስለኝም፡፡ የዩኔስኮ ብሔራዊ ኮሚሽን ብቸኛው ነው፡፡

የዩኔስኮ ብሔራዊ ኮሚሽን አቋቋምና የዋና ዋና የሥልጣን አካላቱ (የጠቅላላ ጉባዔውና የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤቱ) አወቃቀር አጉልቶ እንደሚያመለክተው፣ የዩኔስኮ የትምህርት ጎን ከሌሎች የሳይንስና የባህል የበለጠና የገነነ ሥፍራ ነበረው፡፡ የማቋቋሚያ ሕጉ ግን ዩኔስኮ እያደገና እየበለፀገ ሄዶ ዛሬ በደረሰበት የዕድገት ደረጃ ላይ ሥራዬ ብሎ የሚሯሯጥበትን የኢንፎርሜሽን ጉዳይ አላወቀም የሚል አይደለም፡፡ ለዚህም የብሔራዊ ኮሚሽኑን የማቋቋሚያ ሕግ መግቢያ ልብ ብለን እንመልከት፡-

‹‹ዓለም በትምህርት፣ በሳይንስና በባህል ረገድ የሚያደርገውን ጠቃሚ ዕርምጃ ሕዝባችን ለአዕምሮው ማጎልመሻና ለኑሮው ማዳበሪያ እንዲያውለውና እንዲሁም ኢትዮጵያ በትምህርት፣ በሳይንስና በባህል ረገድ ስለምታደርጋቸው ዕርምጃ መረጃዎች በሚገባ እንዲሰበሰቡ፣ እንደጠበቁና ለዓለም እንዲሠራጩ ለማድረግ የዘወትር ዓላማችንና ሐሳባችን ስለሆነ …›› ይላል፡፡

በማቋቋሚያ ሕጉ የተገለጸውና እኛም ያሰመርንበት መረጃ በሚገባ የመሰብሰብ፣ የመጠበቅና የማሠራጨት ጉዳይ በማቋቋሚያ ሕጉ የተገለጸበት መልክ ኢትዮጵያ ለዓለም ስለዕድገቷ ለምታሠራጨው መረጃ ቢያደላም፣ የዩኔስኮ ዋና ሥራና ተግባር በዚሁ በኢንፎርሜሽን ነፃነት ላይ ያነጣጠረና ያተኮረ ነው፡፡ የመንግሥታቱ ድርጅት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት የተመድ የሐሳብን የመግለጽ ነፃነት ዋና እንደራሴና ባለአደራ ነው ብለናል፡፡ የኢንፎርሜሽን ነፃነት መሠረታዊ ሰብዓዊ መብት ነው፡፡ ተመድ ለታመነባቸውና ለተፈጠመባቸው ነፃነቶች ሁሉም ማመሳከሪያና መለኪያም የኢንፎርሜሽን ነፃነት ነው ያለውም የመንግሥታቱ ድርጅት ራሱ ገና ከመነሻውና ከጅምሩ እ.ኤ.አ. በ1946 ዓ.ም. ነው፡፡ እ.ኤ.አ. የ1948 የዩኒቨርሳል ዲክላሬሽንና የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ዓለም አቀፍ ኮቨነንት አንቀጽ 19 ድንጋጌዎች ምንጭና መነሻም ይኸው የኢንፎርሜሽን ነፃነት ነው፡፡

‹‹የኢንፎርሜሽን ነፃነት›› የዘንድሮው የዓለም የፕሬስ ቀን ማቀንቀኛ ኃይለ ቃል ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. በ2015 መጨረሻ በ11ኛው የኖቬምበር ወር ውስጥ የዩኔስኮ አባል አገሮች ባደረጉት ስምምነት መሠረት፣ ሴፕቴምበር 28 ወይም መስከረም 18 ላይ ተመድ የሚያከብረው አዲስ ዓለም አቀፍ ቀን ይቋቋማል፡፡ ይህም ኢንፎርሜሽን የማግኘት (ሁለንተናዊ) ዓለም አቀፋዊ ቀን ይባላል፡፡

በዩኔስኮ ፊታውራሪነት በመንግሥታቱ ማኅበር ሥርዓት ውስጥ የሚከበሩት ተመሳሳይነት ያላቸው ጉዳዮች ግን የፕሬስ ነፃነት ቀንና አሁን አዲስ የተጨመረው የኢንፎርሜሽን ነፃነት ቀን ብቻ አይደለም፡፡ በጣም በርካታ ናቸው፡፡ በአውሮጳውያን ወራት ቅደም ተከተል መሠረት የዓለም የሬዲዮ ቀን የካቲት 6 ላይ ይውላል፡፡ ሬዲዮና ወደኋላ በተራው የምናገኘው የዓለም የቴሌቪዥን ቀን የሚያከብረው ቴሌቪዥን፣ ፕሬስ ቀንም ውስጥ አሉ፡፡ የካቲት 14 የአፍ መፍቻ ቋንቋ (ማዘር ላንጉዌጅ) ዓለም አቀፋዊ ቀን ነው፡፡ ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት ከቋንቋ መብት ጋር ይገጥማል፡፡ የንግግር ወይም ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት በአንድ ቋንቋ ብቻ አይባልም፡፡ ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት በቋንቋ እንደማይገደብ ሁሉ በሌላም የአንድ ቋንቋ ውስጥ የአነጋገር ልክና መልክ ላይ አይታከልም፡፡ መጋቢት 12 የዓለም የግጥም ቀንን የሚያከብረው በዚህ ምክንያት ነው፡፡ የወሩንና የቀናቱን ቅደም ተከተል እዚህ ላይ (አሁን) ይፋለስብናል እንጂ ሚያዝያ 22ም ዓለም አቀፍ የጃዝ ቀን ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 28 ውስጥ በሰብዕና ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ብሎ ለይቶ ያወጣቸው ዓይነት ወንጀሎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ሕገ መንግሥቱ የዘር ማጥፋት ወንጀልን፣ ያለ ፍርድ የምት ቅጣት ዕርምጃ መውሰድ፣ በአስገዳጅ ሰውን መሰወር (ማለትም አድራሻውንና ድራሹን ማጥፋት) ወይም ሰቆቃና ድብደባ በመሳሰሉት ኢትዮጵያ ባፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶችና በሌሎች የኢትዮጵያ ሕጐች ላይ በሰው ልጅ ላይ የሚፈጽሙ ወንጀሎች የሚባሉት ክሶች በይርጋ አይታገድም፡፡ በፍርድ ቤት የሚሰጡ ውሳኔዎችም በየትኛውም የመንግሥት የሥልጣን አካል ምሕረት ወይም ይቅርታ አይሰጥባቸውም፡፡ የመንግሥታቱ ድርጅት ሥርዓት ካሌንደርም መጋቢት 15ን (ማርች 24) የሚያከብረው እውነቱን የማወቅ መብት ቀን የሚባል አለው፡፡ በሰብዓዊ መብት ላይ የተፈጸሙ ድርጊቶችን የማወቅ መብት ነው፡፡ የዚህ ፋይዳ ወንጀል የፈጸሙ ሰዎችን ለፍርድ ከማቅረብ የታወቀ (የታወቀ ነው ከሚባለው) ጠቀሜታው በተጨማሪ/ወይም ከዚህ ጎን ለጎን በድብቅ የተፈጸመውን ማን አባቱ ያውቃል ተብሎ የተከናወነውን አገር እንዲያውቀው ያደርጋል፡፡ ወንጀል ፈጽመው ሳይጠየቁ መኖር አይቻልምን ይሰብካል፡፡

ሚያዝያ ወር ውስጥ የመጻሕፍትና የኮፒ ራይት ቀን (ሚያዝያ 15)፣ የአዕምሯዊ ንብረት ቀን (ሚያዝያ 18) እንዲሁም ቅድም የጠቀስነው የጃዝ ቀን አሉ፡፡ የዓለም የፕሬስ ቀን ሚያዝያ 25፣ የዓለም የቴሌኮሙዩኒኬሽንና የኢንፎርሜሽን ሶሳይቲ ቀን (ግንቦት 9) የሚውሉ በዓላት ናቸው፡፡

በሚገርም አጋጣሚ ግንቦት 13 ቀንና ግንቦት 14 እንደ ቅደም ተከተላቸው የብዝኃነት ቀን ናቸው፡፡ የመጀመርያው የባህል ብዝኃነት ቀን ሁለተኛው የሕይወታዊ ሀብት ብዝኃነት ቀን ወይም የብዝኃ ሕይወት ቀን፡፡ ለሁለቱ የተሰጠው ትኩረትና የመታመን ልክ ግን የሚያስተዛዝብ ነው፡፡ ብዝኃ ሕይወትን የመንከባከብ የማበልፀግና የመጠበቅ ጉዳይ በአንፃራዊነት ያስቀናል፡፡ የኢትዮጵያ የብዝኃ ሕይወት ፀጋ ለአገርና ለሕዝቦቿ ጥቅምና ብልጽግና ይውላል ብሎ ያምናል፡፡ ስለዚህም የአደይ አበባም የጽጌረዳ አበባም እኩል ህልውና እኩል ጥበቃ አላቸው ይላል፡፡ የባህልና የአመለካከት ብዝኃነት የንቅናቄው ጎራ ግን ከዚህ የተለየ ነው፡፡ ተቃራኒም ነው፡፡ መጀመሪያ ነገር ጽጌረዳ አበባ እንጂ አደይ አበባ ብሎ ነገር የለም ይላል፡፡ አለዚያም አደይ አበባ፣ ጽጌረዳ አበባ ካልሸተተ አትኖርም ይላል፡፡ የ‹‹ብዝኃነት›› ስም በሚነገድበት ቦታ ሁሉ የተለየ ሐሳብ ቦታ የለውም፡፡

ጳጉሜን የሚከበረው የመሠረተ ትምህርት ቀን፣ መስከረም 18 (አዲስ) የሚውለው የኢንፎርሜሽን ነፃነት ቀን፣ የጥቅምት 14 የዓለም የልማት ኢንፎርሜሽን ቀን፣ የጥቅምት 17 የዓለም የኦዲዮ ቪዥዋል ቅርስ (ሔሪቴጅ) ቀን ሁሉ ይህንን ያልነውንና የተባለውን ሐሳብን የመግለጽ ነፃነትን አንድ ወይም ሌላ ገጽታ ወይም ጎን የሚያከብሩ፣ ጠቀሜታውን ደጋግመው እየወቀጡ የሚያስተምሩ ናቸው፡፡

ኖቬምበር 2 (ጥቅምት 23) የሚውል ሳይጠየቁ መኖር መቻልን ለመታገልና ለመዋጋት የተሰየመ ቀን አለ፡፡ በጋዜጠኞች ላይ ወንጀል ሠርቶ ሳይጠየቁ መቅረትን የሚታገልና የሚዋጋ ዓለም አቀፋዊ ቀን ነው፡፡ ዓለም በመንግሥታቱ ድርጅት ሥርዓትና በሥልጣን አካላቱ አማካይነት ጋዜጠኞችን ብቻ ለይቶ በእነሱ ላይ የሚፈጸም ወንጀል ሠርቶ ሳይጠየቁ መቅረት (Impunity) በፍፁም አይቻልም ያለው፣ በጋዜጠኝነት ላይ የሚሠራ ወንጀል የአንድ ሰው ብቻ ጥቃት አይደለም፡፡ ራሱን ንግግርን፣ ሐሳብ መግለጽን፣ ለጋዜጠኛ መናገርን፣ የጋዜጠኛ ምንጭ መሆንን፣ ኢንፎርሜሽንን ስለሚያጠቃ ነው፡፡ በዚህ ላይ የሚፈጸም ወንጀል ነው ብሎ ነው፡፡

የዘንድሮው የፕሬስ ነፃነት ቀን ዋና መሪ ቃል ኢንፎርሜሽን መሠረታዊ ነፃነት ነው የሚል መሆኑን፣ መስከረም 18 ደግሞ ከዚህ በኋላ በየዓመቱ የሚከበር የኢንፎርሜሽን ነፃነት ቀን ሆኖ መወሰኑን አይተናል፡፡ የፕሬስ ነፃነትንና የኢንፎርሜሽን ነፃነትን ግንኙነት ይበልጥ ጠጋ ብለን መመርመር ያስፈልገናል፡፡

የኢንፎርሜሽን ነፃነት በገዛ ራሱ ምክንያት መሠረታዊ ነፃነት ነው፡፡ ሰብዓዊ መብትም ነው፡፡ በገዛ ራሱ ምክንያት ማለት ሌላ ምንም በውጤትነት የሚያስከትለው ፋይዳና ጠቀሜታ መኖሩን ማስመስከር ሳይኖርበት ማለት ነው፡፡ የኢንፎርሜሽን መብትና ነፃነት ‹‹ሰባ፣ ካልተበላ ምን ሊረባ›› አይባልም ማለት ነው፡፡ በገዛ ራሱ ምክንያት ብቻ መብትና ነፃነት ነው ማለት ትርጉሙ ይኸው ነው፡፡ በገዛ ራሱ ምክንያት ብቻ ማለት ግን ሌላ ጥቅም የለውም ማለት አይደለም፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ገና ከጅምሩ እ.ኤ.አ. በ1946 ጉባዔው፣

“Freedom of information is a fundamental human right and the touchstone of all the freedoms to which the UN is consecrated.” ያለው ሌላ ጥቅሙም የገዘፈና የማይተካ በመሆኑ ነው፡፡

የኢንፎርሜሽን ነፃነት ሰፋ ካለው ሐሳብን ከመግለጽ ነፃነት ጋር በተፈጥሮውና በባህርይው የተሳሰረ መሠረታዊ ነፃነትና ሰብዓዊ መብት ነው፡፡ ኢንፎርሜሽን የመሻትንና የመቀበልን መብት ያካትታል፡፡ እንዲሁም ኢንፎርሜሽን የማሠራጨት መብትን ሙሉ ያደርጋል፡፡ ኢንፎርሜሽን የማቀበል፣ የመስጠትና የማሠራጨት መብት ማለት በፕሬስ ነፃነት መብት አማካይነት ኢንፎርሜሽንን አደባባይ የማውጣት ነፃነት ማለት ነው፡፡

እስቲ የአንቀጽ 29 ድንጋጌን ቃል በቃል እንመልከት፡፡ አንቀጽ 29(2) ማንኛውም ሰው ያለምንም ጣልቃ ገብነት ሐሳቡን የመግለጽ ነፃነት አለው ይላል፡፡ ቀጥሎ ይህ ነፃነት ይልና ሐሳብን የመግለጽ ነፃነትን ትርጉም ይደነግጋል፡፡

ይህ ነፃነት ይልና ይጀምራል፡-

ይህ ነፃነት በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጪ ወሰን ሳይደረግበት በቃልም ሆነ በጽሑፍ ወይም በሕትመት በሥነ ጥበብ መልክ ወይም በመረጠው በማንኛውም የማሠራጫ ዘዴ፣ ማንኛውንም ዓይነት መረጃና ሐሳብ የመሰብሰብ፣ የመቀበልና የማሠራጨት ነፃነቶችን ያካትታል ይላል፡፡

በዚህ ትርጉም መሠረት ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት የኢንፎርሜሽን ነፃነት ነው፡፡ ኢንፎርማሽን የመሻትና የመሰብሰብ፣ የመቀበል፣ ኢንፎርሜሽን የመስጠትና የማሠራጨት መብት ነው፡፡ ማንኛውንም ዓይነት ኢንፎርሜሽንንና በማንኛውም የማሠራጫ ዘዴ ማለት ነው፡፡

ስለዚህም የኢንፎርሜሽን ነፃነት በአንድ ኅብረተሰብ ውስጥ የሚገኘውን የክፍትነትና የግልጽነት ደረጃ መለኪያና ማሳያ ነው፡፡

የኢንፎርሜሽን ነፃነት መብት በመንግሥት ወይም በመንግሥት አካላት እጅ የሚገኝ ኢንፎርሜሽንንና እሱን ማግኘትን በሚገዛው የሕግ ማዕቀፍ ውስጥ ያለውን የኢንፎርሜሽን ነፃነት መብት ብቻ የሚመለከት አይደለም፡፡ በዚህ ውስጥ የሚገኘውም የነፃነቱ ዳር ድንበር እየሰፋና እየተስፋፋ ነው፡፡ ለምሳሌ የአፍሪካ የሰብዓዊና የሕዝቦች መብት ኮሚሽን ያወጣው እ.ኤ.አ. የ2012 ኢንፎርሜሽን የማግኘት ሞዴል ሕግ በግለኛ እጆች የሚገኙ፣ በየትኛውም መብት ለመገልገል ወይም ይህንኑ መብት ለመከላከል የሚረዱ መረጃዎች የማግኘት መብትንም ያካትታል፡፡ አንደኛው የኢንፎርሜሽን ነፃነት መብት ዓይነት ይኼ ነው፡፡

ሁለተኛውና ሰፋ ያለው የኢንፎርሜሽን ነፃነት መብት ከመንግሥት ውጪም ያለውን፣ በሌሎችም እጅ ጭምር የተያዘውን ወይም እነሱ ጋ የሚገኘውን ኢንፎርሜሽን ማግኘት ብቻ ሳይሆን፣ ይህ ኢንፎርሜሽን በነፃ መንሸራሸሩንና እንደ ልብ መናኘቱን የሚመለከተው ነው፡፡

ይህንን ሰፋ ያለውን (በመንግሥት እጅ የሚገኘውን ኢንፎርሜሽን በማግኘት ላይ ብቻ ያልተወሰነውን) የኢንፎርሜሽን ነፃነት መብት በተለይ በመንግሥት ላይ ከተቋቋመ ግዴታ አንፃር በሦስት ፈርጅ ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡

አንደኛው በመንግሥት ላይ የተጣለው የመንግሥት ግዴታ የመከልከል ግዴታው ነው፡፡ ራሱ የማክበር ግዴታው ነው፡፡ ተከልከል፣ ተከልክለሃል መባሉ ነው፡፡ ይህ ግዴታ የሚመነጨው ማንም ሰው ያለመንግሥት ጣልቃ ገብነት ኢንፎርሜሽን የመቀበልና የማስተላለፍ የማሠራጨት ነፃነት ስላለው ነው፡፡ በዚህ ትርጉምና አንድምታ መሠረት መንግሥት አሉታዊ ግዴታ አለው ማለት ነው፡፡ ሳንሱር በማንኛቸውም ስምና መልኩ ክልክል ነው ማለት የዚህ ግዴታ ዋነኛ ማቋቋሚያ ነው፡፡

ሁለተኛው ዘብ የመቆም የመንግሥትን ግዴታ የሚያቋቁመው ነው፡፡ የመንግሥት የማስከበር ግዴታ ነው፡፡ በዚህ መሠረት መንግሥት ሌሎች ግለሰቦችና መንግሥታዊ ያልሆኑ ቡድኖች በሰዎች የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ውስጥ ጣልቃ እንዳይገቡ የማድረግ፣ ሌሎችን የመከልከል የሕግና የሕግ ማስፈጸም ዕርምጃ እንዲወሰድ የሚያስገድድ አዎንታዊ (የአድርግ) ግዴታ አለበት፡፡

ሦስተኛው የመንግሥት ግዴታ ከመንግሥት የግልጽነትና የተጠያቂነት ግዴታ የሚመነጨው፣ በመንግሥት እጅ የተያዘ ኢንፎርሜሽንን የመስጠት ግዴታ የሚያቋቁመው ነው፡፡ ኢንፎርሜሽን የማግኘት መብት ሕግ ፋይዳ እዚህኛው የመንግሥት ግዴታ ውስጥ የሚታቀፍ ነው፡፡

በዚህ መሠረት ለምሳሌ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኘው የኢንፎርሜሽን ነፃነትን የሚመለከተው ሕግ የኢንፎርሜሽን ነፃነት ሕጉ ብቻ አይደለም፡፡ በአዋጅ ቁጥር 590/2000 ውስጥ የተካተተው የመረጃ ነፃነት ሕግ የሚገዛው በመንግሥት እጅ ያለን ኢንፎርሜሽን የማግኘት የነፃነቱን አንድ ገጽታ ብቻ ነው፡፡

የኢንፎርሜሽን ነፃነት በመንግሥት እጅ ያለ ኢንፎርሜሽን ከማግኘት በላይ የሰፋ የኢንፎርሜሽን በነፃ የመንሸራሸርና የመናኘት ጉዳይ የሚመለከት ነው፡፡ በሌሎች ዘርፎችም አውቀንም ሆነ ሳናውቅ የምንወስዳቸው ዕርምጃዎች የኢንፎርሜሽን ነፃነት የአገር ከባቢ አየር ላይ ተፅዕኖ አላቸው፡፡ የኮፒ ራይት ሕጉን ከተወሸቁበት ጥልቅ የዘፈንና የካሴት ጉድጓድ ውስጥ ሆነው ዓለምንና ኢትዮጵያን በጉድጓዱ አፍ ስፋት ልክ ብቻ የሚያዩ ዘፋኞች፣ የሚመኙትና ይሆንላቸው ዘንድ የሚማጠኑት የኮፒ ራይት ሕጉ አፈጻጸም በጣም አደገኛ ነው፡፡ በመንግሥታዊ የመገናኛ ብዙኃን የሞኖፖል ባለመብትነት ምክንያትና በሌሎችም ጭምር የአገሪቷ የድራማና የሲኒማ ኢንዱስትሪ ንጉሠ ነገሥት ሆነው የኖሩት ሰዎች፣ በሳተላይት ቴሌቪዥን ላይ የሚያቀርቡትን አቤቱታ ሰምቶ ኢትዮጵያን እንደገና ‹‹የረሷትን ሰዎች የረሳች›› አገር ማድረግ መሞከር በኢንፎርሜሽን ነፃነታችን ላይ የሚታይ አለማወቅም፣ ጉዳትም ነው፡፡

የኢሚግሬሽንና የቪዛ ሕጋችንና አሠራራችን የጋዜጠኞች እንቅስቃሴ ላይ ተፅዕኖ ካለው፣ የጉምሩክ ሕግና አሠራርም ይህንን ከቁጥር ያላስገባ ከሆነ አገር ስለተሟላ ቀርቶ ስለሚያበረታታ፣ ስለተጀመረ የኢንፎርሜሽን ነፃነት ማውራት አትችልም፡፡

የዛሬ 25 ዓመት ናሚቢያ ዊንድሆክ ላይ በዩኔስኮ አማካይነት የተጠራው የአፍሪካ ጋዜጠኞች ስብሰባ እ.ኤ.አ. ከ1993 ጀምሮ በየዓመቱ ለሚከበረው የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን መነሻና ምክንያት ሆኗል፡፡ ኢትዮጵያም ውስጥ በዓሉን በየዓመቱ ማክበራችን አልቀረም፡፡ በየዓመቱ ያምጣህ እያልን ይህንን ሁሉ ጊዜ በዓሉን እያከበርን ግን የፕሬስ ነፃነቱን ቀን ፀንሶና ወልዶ ለዚህ ክብር ያበቃው የዊንድሆኩ ጉባዔ ያሳለፈው ውሳኔ፣ ዛሬም ኢትዮጵያ ውስጥ የጥበባችን መጀመርያ አልሆነም፡፡ ስለወሬው መስማትም እንጠራጠራለን፡፡

ናሚቢያ ዊንድሆክ ላይ አፍሪካ በገዛ ራሱ የሚያዝ ፕሬስ ወይም ሚዲያ ያስፈልጋታል ተባለ፡፡ በገዛ ራሱ የሚያዝ (ኢንዲፐንደንት) ፕሬስ ማለት ከመንግሥታዊ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖና ቁጥጥር፣ እንዲሁም የፕሬስ ውጤቶችን አትሞ ለማውጣትና ለማሠራጨት አስፈላጊ ከሆኑ ቁሳቁሶችና መሠረተ ልማቶች ቁጥጥርና ተፅዕኖ ነፃ የሆነ የፕሬስ ማለት መሆኑ የታወጀው ከ25 ዓመት በፊት ነው፡፡ ያኔ ተለይተውና ታውቀው የተዘረዘሩት የኢኮኖሚ መሰናክሎችና ከልካይ እንቅፋቶች በወረቀት፣ በሚዲያ ቁሳቁስና መሣሪያ ላይ የተጣሉ የጉምሩክ ቀረጦች፣ ታሪፎች፣ ኮታዎች እንዲሁም በጋዜጣና በመሰል ቁሳቁሶች ላይ የተጣሉ የሽያጭ ታክስ (የቫት) ቀረጦች መሆናቸው ታወቀ፡፡ ጥናቱና ትግሉ እንዲቀጥል ተወሰነ፡፡ የፕሬስ ነፃነት በዓልን የማክበርም ትርጉም ይኼው መሆኑ ተበየነ፡፡ ይህን አገናዝቦ በዘርፍ በዘርፉ ተደራጅቶ ወይም ተቧድኖ የቤቱን ችግር አጥንቶ የሚያቀርብ ጠፍቶ እነሆ 25 ዓመት ሞላ፡፡ ዛሬም ኢትዮጵያ በራሱ የሚያዝ የቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርቶ ጋዜጣ እንኳን የላትም፡፡ ይኼ ጋዜጣ ራሱ ባለስንት ገጽ መሆን እንዳለበት፣ የኮፒዎቹን ብዛት፣ ሌላው ቀርቶ ማተሚያ ቤት የሚገባበትን ቀን የሚወስነው ከጋዜጣው አስተዳደር ውጪ ያለ ሌላ አካል ነው፡፡ ማተሚያ ቤቱ ነው፡፡ ከማተሚያ ቤት የሚወጣበትንም ጊዜ የሚወሰነው ያው የማተሚያ ቤቱ ‹‹የመሣሪያ ጤንነትና ደኅንነት ሁኔታ›› ነው፡፡ የዚህ ሁኔታ ደግሞ በጣም ተለዋዋጭ ነው፡፡ እንዲህ ያለ ተለዋዋጭ ነገር በአገር ምድሩ የለም፡፡ ‹‹አንዴ ሰው አንዴ አፈር›› የሚሉት ነው፡፡ ሰው ሲሉት አፈር፣ አፈር ሲሉት ሰው ይሆናል፡፡

በአገራችን የአሳታሚ ድርጅቶች (የአሳታሚዎች)፣ የኤዲቶርያል ክፍል ሥራና የኅትመቱ ክፍል ሥራ ምናልባትም ብርሃንና ሰላም ጋዜጣ እና ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ከተፋቱ በኋላ አንድ ላይ ሆነው አያውቁም፡፡ የኢትዮጵያ አሳታሚዎች የምርት (Production) ክፍል ሥራቸውን የሚሠሩት፣ ቡኮ ወይም ሊጥ ተሸክሞ መብራት ወዳለበት ቦታ እንደሚንከወከው ቤተሰብ ሌላ ቦታ ነው፡፡ የቤተሰቡ ጉዳይ ጊዜያዊ ችግር የሚባል ነው፡፡ የመብራትና የኃይል መልካም አስተዳደር ችግር እስኪወገድ ድረስ ነው፡፡ የአሳታሚዎች ወይም የፐብሊሽንግ ሀውስስ ነገር ግን ጭራሽ የተለየ ነው፡፡ ሊጡን እስከማዘጋጀት ድረስ ያለው የሥራ ክፍል አንድ ርሱን የቻለ የሥራ ፈቃድ፣ ከዚያ በኋላ ያለው የምጣድ ባለቤት ሆኖ እንጀራውን ጋግሮ የማውጣት የሥራ ክፍል ሌላ ፈቃድ ያስፈልገዋል እንደማለት የተለያየና የተነጣጠለ ነው፡፡ ችግሩ ግን በዚህ ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ ለምን ለአንድ የሥራ ዓይነት ሁለት ፈቃድ አወጣለሁ? የማለት የኩራትና የእምቢተኝነት ጉዳይ አይደለም፡፡ ለዚህ የሚያበቃው ሕግ የዓይን ብርሃንና የእግር መንገድ የማይታወቅ መሆኑ ነው፡፡

ለ17 ዓመታት ለግል የተከለከለው ለመንግሥት ብቻ የተከለለው የጋዜጣና የመጽሔት ሥራ ለግል የተፈቀደው በ1985 ዓ.ም. ነው፡፡ ትልቅ ዕርምጃ ነው፡፡ በተለይም በጻፍክ ብቻ ሳይሆን አነበብክም፣ ተናገርክ ብቻ ሳይሆን ሰማህም እስከ ሞት ድረስ በሚያስቀጣበት አገር አዲስ ምዕራፍ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የደረጃ መለኪያ ግን በጭራሽ ደርግ መሆን የለበትም፡፡

ከ1985 ዓ.ም. ጀምሮ በተጓዝንበት ረዥም የዘጭ እምቦጭ ዘመን ውስጥ ሥርጭቱ ለአንድ የተወካዮች ምክር ቤት የምርጫ ክልል ሕዝብ የሚዳረስ ጋዜጣ ቀርቶ (አንድ መቶ ሺሕ)፣ የጋዜጦች ድምር ባለቤት ለመሆን አልታደልንም፡፡ የሥርጭት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት ራሱ ገና አልገባንም፡፡ የተለየና የሚቃረን ሐሳብን የማቅረብ ነፃነትን የማክበር፣ ጥቅሜ ብሎ ማድመጥን መከራከርንና ቅያሜ ሳይዙ ቂም ሳይቋጥሩ መለያየትን ገና አለመድንም፡፡ ከመኃይም እስከ ምሁር ከተራ ሥራ አጥ እስከ መንግሥት ሹማምንት የሚገለገሉበት ሰፊ ተጠቃሚ ያለው ሚዲያ ዛሬም ሹክሹክታ ነው፡፡ ይህንን ጐዶሏችንን ካላሟላን፣ የበዙ የተባዙ የተዥጉረጐሩ ፕሬሶች ኢትዮጵያን ካላጥለቀለቁ በቀር አፋችንን ሞልተን ስለነፃ ፕሬስ በኢትዮጵያ ማውራት ይቸግረናል፡፡ በዚህ ረገድ ኋላ የቀሩ ውራዎች ብንባል ይገባናል፡፡

ክርስቲያን ኦማንፑር ጋዜጠኛ ነች፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ልዩ አምባሳደርም ነች፡፡ ጋዜጠኛነትንና አምባሳደርነትሽን ምን አገናኘው ተብላ እ.ኤ.አ. በ2016 የፕሬስ ቀን በዓል አጋጣሚ ተጠየቀች፡፡ ‹‹የምን ባህል ነው? የምን ትምህርት ነው? የምን ሳይንስ ነው? ያለ ሁሉም ዓይነት ሙሉና ነፃ የሐሳቦች፣ የዝንባሌዎች ፍጭትና መንጓለል?›› ብላ መለሰች፡፡

እንዲህ ያለ ሐሳብና መረጃ በነፃ የሚንሸራሸርበት፣ የሐሳብና የኢንፎርሜሽን ሸመታው የደራበት ገበያ ሳንመሠርት ስለ ‹‹ተመዘገበ ድል›› ባናወራ ይሻለናል፡፡

  • ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡